(Reporter) ሰበር ዜና:በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩ 23 ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናት የሞት ፍርዱ እንደተነሣላቸው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት አስታወቁ፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት በእስር ላይ የነበሩትና የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩትና ውሳኔ የተነሣላቸው ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው፣ ሻለቃ መላኩ ተፈራ፣ አቶ አብዱልቃድር መሐመድ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ፣ ጄኔራል ለገሠ በላይነህ፣ አቶ ገስግስ ገ/መስቀል፣ መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ፣ መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣ ኮሎኔል ናደው ዘካርያስ፣ ሻምበል በጋሻው አታላይ፣ ሜጄር ጄኔራል ውብሸት ደሴ፣ ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ፣ ኮሎኔል እንዳለ ተሰማ፣ ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ፣ መቶ አለቃ አርጋው ይመር፣ ሻለቃ ደጀኔ ወ/አገኘሁ፣ አቶ እሸቱ ሸንቁጤ፣ ሻምበል ገሠሠ ወ/ኪዳን፣ መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ፣ ወታደር ልሳኑ ሞላ፣ ወታደር አበበ እሸቱ እና ወታደር ዘሪሁን ማሞ ናቸው፡፡
የሃይማኖት መሪዎች የተለያዩ ተጎጂ ቤተሰቦችን አነጋግረው ይሁንታ ካገኙ በኋላ ጥያቄያቸውን ለመንግሥት አቅርበው፣ መንግሥትም ነገሩን በማጤን የሞት ፍርዱ እንዲነሣላቸው መወሰኑን ፕሬዚዳንት ግርማ አስታውቀዋል፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከካቶሊክ፣ ከወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናትና ከኢትዮጵያ እስልምና፣ አራቱም የሃይማኖት መሪዎች በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተነገረው የይቅርታ ውሳኔ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ጥያቄያቸው ለመንግሥትና ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ ይሁንታ ማግኘቱን ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አስታውቀዋል፡፡
የሃይማኖት መሪዎች የሞት ፍርዱ መነሣቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ባደረጉት ንግግር የይቅርታ ጎዶሎ ስለሌለው መንግሥቱ ሙሉ ይቅርታ አድርጎላቸው ከእስር እንደሚለቃቸው ሙሉ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፣ አሁን ለተደረገው ይቅርታ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይቅርታ እንዲደረግላቸው የሃይማኖት መሪዎች ባለፈው ታኅሣሥ ያወጡትን መግለጫ፣ እንዲሁም አንዳንድ የተጎጂ ቤተሰቦች እኛን አላነጋገሩንም ስለማለታቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በወንጀል ሕጉ እንደተጠቀሰው፣ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ሰው ሁለት ሦስተኛውን ከታሰረ በአመክሮ ስለሚለቀቅ፤ የደርግ ባለሥልጣናቱም ከዚያ በላይ ስለታሰሩ ሊለቀቁ ይችላሉ የሚል ግምት አለ፡፡
በታምሩ ጽጌ