ከግሩም ተ/ሃይማኖት
ነገሩ እየተካረረ መግባባት ጠፍቶ ጦርነት በተቀሰቀሰባት የመን 4 ኢትዮጵያዊያን ሰለባ ሆኑ::ሰነዓ ከተማ ውስጥ አሳባ የሚባለው አካባቢ ከሼህ ሳዲቅ ጋር ሲደረግ የነበረው ውጊያ ዛሬ ጋብ ብሎ ቢውልም ክሰነዓ ውጭ ያለው ሁኔታ አልረገብም የሚል አሉ::እነዚህ 4 ኢትዮጵያዊያንም የሞቱት በሰነዓ ከተማ አሳባ በሚባለው አካባቢ በተደረገው ጦርነት ነው::
ያለው ሁኔታ ያሰጋል!!እጅግ አስፈሪነት ያለው ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መፍትሄ ይሰጠን ጥያቄ ይዘው UNHCR በር ላይ ተቀመጡ::ከምንም በላይ ቢሮው ዝምታን ዘላቂ መፍትሄ አድርጎታል::<<..የሞተ የለም ከዚህ ተነሱ..>> በሚል በፖሊስ ለማስነሳት ከማሰብ ያልዘለለ መፍትሄ ሊያቀርብ ያልቻለው UNHCR አማራጭ ሀሳብ ያደረገው የሞቱና የቆሰሉ ሰዎችን ስም እና አድራሻ መጠየቅ ነው::..በስደተኛው ህይወት በማላገጥ ላይ ያለው UNHCR ለሁሉ ነገር መፍትሄ ያደረገው በፖሊስ ከበሩ ላይ ማስነሳት እና ማሳሰር ነው::ከዚህ በፊትም ቢሆን እዛው UNHCR በር ላይ መፍትሄ ካልተሰጠኝ አልነሳም ብለው የተቀመጡት ባልና ሚስቶቸን በፖሊስ አስገድደው ሲያስነሱ ሴቷ በደረሰባት ድብደባ የ5 ወር ጽንስ አስወርዳለች::ከነህክምና ማስረጃው ለህዝብ ማቀረቤ ይታወሳል::..ከስህተታቸው ያልተማሩት ለስደተኛ ቆመናል ከሚል ድርጅት የማይጠበቅ ስራ የሚሰሩት ሰራተኞች ግን ዛሬም በተመሳሳይ ስራ ተሳተፉ::
ይህ መፍትሄ ይሰጠን በስደት ያለንበት ሀገር ሰላም አስተማማኝ አይደለም::አልፎ ተርፎም ጦርነት ተጀምሯል::ህይወታችንን ለማዳን ወጥተን ህይወታችንን ልናጣ ነው ምን ይሻለናል የሚል ጥያቄ የቀረበው ለUNHCR ቢሆንም በዓለም ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጉዳያቸው አድርገው ካልተረባረቡበት ነገ..ነገ..ዘግናኝ እልቂት ..አሳዛኝ ታሪክ ሊከሰት ይችላል::ወገን ሁሉ በየመን ያለ ወገንህን አድን የሚል ጥሪ ኮሚቴዎቹ አስተላልፈዋል::
የሞቱት ሰዎችን ሬሳ አንሳ ተብዬ ተጠይቄያለሁ ያለ ጀማል የተባለ የስደተኛ ተወካይ ሬሳው ኩዌት ሆስፒታል እንዳለ ገልጿል::ይህ የሞቱ የተባለው በአይኑ ያያቸውን ብቻ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል የአይን እማኙ ተናግሯል::