May 16, 2011
37 mins read

ከዓባይ በፊት ሴረኝነታችሁን ገድቡልን

የሰው ልጅ በአንድነት መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የግዝፈቱና የውስብስብነቱ ደረጃ ይለያይ እንጂ አስተዳደርና መንግስት አለ፤ ወደ ፊትም ይኖራል፡፡ ቢያንስ ዛሬ መገመት በምንችለው መጠን የሚከስምበት ወቅትና ሁኔታ አይገኝም፡፡ ስለ አስፈላጊነቱም የተለያዩ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች የተለያዩ አመለካከት አላቸው፡፡ ቶማስ ሆብስ የተባለው የእንግሊዝ የፖለቲካ ሳይንቲስት ‹‹ሰዎች ሁል ጊዜ ስልጣንን ይፈልጋሉ ምክንያቱም ስልጣንን መጨበጥ ለክብርና ለኑሯቸው ዋስትና ይሰጠናል ብለው ስለሚያምኑ፤ በመሆኑም ለስልጣን የማያቋርጥ ትግል መካሄድ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሰው ለሰው ተኩላ ነው፤ በመንግስት ስልጣን አማካኝነት ካልታቀበ እርስ በርስ ይባላል›› ይላል፡፡
‹‹ሰዎች ለህልውናቸው፣ ለኑሮአቸው፣ እንዲሁም ለክብራቸው ዋስትና ያገኙ ዘንድ ለስልጣን መሻኮት ያለ ነው›› የሚለውን ቶማስ ሆብስን አባባል ጃርሜ ቤንታም የተባለው ሌላ የፖለቲካ ሳይንቲስት አይቀበለውም፡፡ ‹‹ማህበረሰባዊ ጥቅም የምንለው የእያንዳንዱ ግለሰብ ጥቅም ድምር ነው፡፡ እናም የመንግስት ዓላማ የእያንዳንዱን ደህንነትና ነፃነት ሳይዘነጋ በተቻለ መጠን የብዙሃኑን ደስታ መፈለግ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንድ ተግባር ለሰዎች ደስታን የሚፈጥር ከሆነ ጥሩ ነው፤ ስቃይንና መከራን የሚያጣ ከሆነ ደግሞ ለስልጣን ዘመን ሳይሆን ለማህበረሰቡ ደህንነትና ጥቅም መቆም አለበት›› ነው የሚለው፡፡
ዓለም ብዙ አይነት መሪዎችን አይታለች፡፡ በአጠቃላይ የሰው ልጅ የታሪክ ሂደት የግለሰብ መሪዎች ወሳኝነት የላቸውም የሚል አመለካከት ቢኖርም በግለሰቦች አመራር ስልጣኔ ሲወድም፤ አገር ሲቆራረስ ታይቷል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ግለሰብ መሪዎች በሚሰጡት አመራር የአገር ስልጣኔ ወደ ፊት ይራመዳል፤ አገርን የበተኑ እንዳለ ሁሉ የአገርን ታሪክና ክብር ያስጠበቁ መሪዎችን ለዚህ መጣጣፍ መነሻ የሆነኝ ጠ/ሚኒስትር መለስ በመጋቢት 22 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ‹‹የውሃ ሀይልና ዘላቂ ልማት 2011›› በሚል ለሁለት ቀናት በቆየው ጉባኤ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ በዚህ ፀሐፊያቸው ተጨንቀው እንዳረቀቁላቸው የሚያስታውቀው የንግግር ፅሑፍ ላይ አንድ የተጠቀሙበት አገላለፅ ለዛሬ ትችቴ መነሻ ሆኖኛል፡፡ በዚህ የንግግር ፅሑፍ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው አገላለፅ እንዲህ የሚል ነው፡፡ ‹‹I am not believer in conspiracy theories but if I were›› ይላል፡፡ ወደ አገርኛው ቋንቋችን ስንለውጠው ‹‹እኔ የሴራ ትንታኔ አማኝ አይደለሁም፡፡ ብሆን ኖሮ ግን…›› ብሎ ‹‹ቢራቢሮ›› ስላሏቸው ግብፅ ፖለቲከኞች ጠ/ሚኒስትሩ ያላቸውን የሴራ ትንታኔ ይዘረዝራሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አባይን አስመልክቶ በስብሰባው ላይ ያነበቡት የዲስኩር ፅሑፍ ላይ የሰፈሩት ሀሳቦች ከዚህ በፊት በጉዳዩ ላይ ከሰነዘሯቸው ብጥስጣሽ አስተያየቶች የጠነከረና ዛሬ ምን ተገኘ? የሚል ጥያቄ የሚያጭር እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡
ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች እንደተናገሩት በዕለቱ ያደረጉት ንግግር ‹‹የህዳሴ ግድብ›› ለተባለው ፕሮጀክት የመጨረሻ መቦሰቻ አድርገው ቆጥረውታል፡፡ ለዚህም በማረጋገጫነት የወሰዱት አሁን ያለውን የአገሪቱን የሀይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ ያሳድጋል ተብሎ የታመነበትን የግድብ ዲዛይን ተሰርቶ የተጠናቀቀው በአጭር ጊዜ ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በወቅቱ በግብፅ ፖለቲካ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
ለግብፅ የውጭና የደህንነት ፖሊሲ አልፋና ኦሜጋ የአባይ ውሃ መሆኑ አከራካሪ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህም ይመስላል ከሰሞኑ የአገሪቱ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የግድብ የመገንባት እቅድ ይፋ ማድረጉ ‹‹ተንኳሽ ድርጊት›› አድርገው በመቁጠራቸው ለጦርነት እንቅስቃሴ ማድረግ በመጀመሪያቸው መረጃዎች እየጠቆሙ ያሉት፡፡ ለዚህ አቋማቸው ማስረገጫ አድርገው እየጠቀሱት ያሉት ውሃን ‹‹በፍትሀዊነት›› ለመጠቀም በሚል የረቀቀውን የትብብርና ማዕቀፍ ስምምነት ላይ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የተሟላ ስምምነትና በአገሮቻቸው ፓርላሜንታዊ ስርዓት ባላለፈበት ሁኔታ ይህን አይነቱን እቅድ በውሃው ላይ እንደሚተገበር ይፋ መደረጉ የሰጠን ፖለቲካዊ መልክ አለ ባዮች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የአገራችን የፖለቲካ ተንታኞች የተቋዋሚ ፓርቲ መሪዎች እቅዱ ለተራ የፖለቲካ ፍጆታና የህዝቡን ወቅታዊ ትኩረት ለማስቀየር ካልሆነ ድጋፋቸውን እንደ ሚሰጡና፤ ለአገር ታስቦ ስለመሆኑ ግን ብርቱ ጥርጣሬ እንዳላቸው በመግለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደነሱ እምነት የኢህአዴግ መንግስት በቅርቡ በኤርትራ መንግስት ላይ የአቋም ለውጥ ማድረጉን በመናገር የህዝቡን ትኩረት ለመሳብ ያደረገው ሙከራ ባለመሳካት ከዛ በተሻለ የህዝቡን ድጋፍና ትኩረት በመሳብ የውይይት አጀንዳ ለማድረግ የወሰነው የአባይን ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ስለመሆኑ የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች አልጠፉም፡፡ በተለይ ከሰሞኑ የወጡ የገዢው ፓርቲ ልሳናትና መግለጫ ላይ በግልፅ እንደ ተቀመጠው ፓርቲው የመጪዎቹን አምስት ዓመታት መቀመጫውን ስልጣኑን ማረጋገጥ ካለበት የአባይ ጉዳይን በመሳሪያነት በመጠቀም መሆን እንዳለበት ያትታሉ፡፡
ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ አንባገነን መሪዎች በስልጣን የመቆያ ስልታቸው ተመሳሳይ መሆኑን እናገኛለን፡፡ ለህዝብና ለአገር የቆሙ በመምሰል፤ ስለ ህዝብ መደስኮር፣ በህዝብ ጥቅም ላይ ማሴር፣ ለስልጣን ጥበቃ ተባባሪ የሚሆኗቸውን አስመሳይ ፓርቲ ግለሰቦችን ጥቅም ማጉረስ፣ ተቀናቃኝን መደቆስና ማዳከም፣ መከፋፈል በቃ ጊዜው ሲያመች በጠላት ፊት እንደ አንበሳ ማግሳት፣ ዕድል ፊቷን ስታዞር እንደ ቀበሮ ውስጥ ለውስጥ መሄድ፡፡
እ.ኤ.አ 68 (1960 ዓመት በፊት) ሮምንና ግዛቷን በንጉሰ ነገስታት ያስተዳድር የነበረው ኔሮ ክላውዲዎስ ቄሳር ይባል ነበር፡፡ ወደ ንጉሳዊ ስልጣኑ የመጣው በ17 ዓመቱ በእናቱ ሴራ ታግዞ ነበር፡፡ እናቱ አግሪ ፒና ባሏን (የኔሮን እንጀራ አባት) በመርዝ አስገድላ ልጇን ለዙፋን አበቃችው፤ የኋላ ኋላ በእርሷም ለአገራቸው ሮማም ላይበጃቸው ይህ ድርጊት ግን ኔሮን ወደ ህዝብ ከማቅረብ ይልቅ አያራቀው መጣ፡፡ ይህን የተገነዘበችው እናቱ ምክር ለመስጠት ብትሞክርም አልተሳካላትም፤ እንዲያውም ወደ ግዞት ላካት፡፡ በመጨረሻም አስገደላት፡፡ ወዳጁን ፒቲያን ለማግባት የቀድሞ ሚስቱን ከሌላ ሰው ጋር ወሲብ ፈፅማለች በሚል ሰበብ ፈታት፣ ቆይቶም አስገደላት፡፡ አይ የሴረኝነት ፖለቲካ፡፡
የሮማን ታሪክ ከ1960 ዓመት በፊት ያህል ጊዜና ቦታን አቆራርጠን በአይነ ህሊና ወደ ሮማ ታሪክ ማማተራችን አለምክንያት አይደለም፡፡ የዛሬው የኢትዮጵያ ቄሳርን በሴራ ትንተና ላይ የተመሰረተውን አመራር ለማስቃኘት ለመሞከር እንጂ፡፡
የሴራ ትንተና/ንድፍ ሀሳብን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋለው ፒተር ጀምስ የተባለው ፈላስፋ ሲሆን የንድፈ ሀሳቡም ዋነኛ አላማ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በተጨባጭ ማረጋገጥ ያልተቻሉ ጉዳዮችን የሴራ ትንታኔ/ንድፈ ሀሳብ አቅራቢው ድብቅ ኢላማውን በውስጡ በማስላት የአድማጩን ትኩረትና ስሜት ለማሳትና ሊሆን የሚችለውን (Hypothetical) እርምጃ በሚፈልገው መልኩ ቃኝቶ የማቅረብ ስልት ነው፡፡ እንደ ንድፈ ሀሳቡ እምነት የሴራ ትንታኔ/ንድፈ ሀሳብ መሰረቱ ፍርሃት፣ ጥርጣሬና ስጋት ናቸው፡፡ አንድ ሰው በሆነ ነገር ሲጠራጠርና ወይም ሲሰጋ ነገሩ በተፈጥሯዊ ኡደቱ እንደ ሚፈፀም ከማመን ይልቅ ትንታኔ አቅራቢው ሊሆን በሚፈልገው ወይም ትንታኔ ባቀረበው መልኩ የማየትና የማቅረብ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የብዙ ጨለምተኛ (Pessimist) ፖለቲከኞች መገለጫ ሲሆን ችግሮችን ወደ ውስጥ ከማየት ውጫዊ በማድረግ (Externalize) ይታወቃሉ፡፡ የዚህም ተግባራቸው ውጤት በሌላ አካል ላይ ፍረጃና ሽብር በመንዛት ማስፈራራት መሆኑን የንድፈ ሀሳቡ አፍላቂዎች ያስረዳሉ፡፡
በእኔ አስተያየት የአሁኑ የአገራችን መሪ ለአገሪቱና ለህዝብ ከሰሩት ይልቅ የተሳሳቱት እንደሚያመዝን በታሪክ አስባለው፡፡ በስልጣን ወንበራቸው እስከ አሁን ለመቆየት ያላደረጉት እንደ ሌለ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በመመሪያ የተቋውሞ እንቅስቃሴ መሪዎችን ፀረ ሰላም፣ ጥገኛ፣ ሽብርተኛ፣ ፀረ-ዴሞክራሲና የመሳሰሉት ፍረጃዎችን በመለጠፍ ለማሰር፣ ለማሰቃየት ብሎም ለመግደል የህግ ገደብ የሚባል ነገር በኢህአዴግ ውስጥ አልነበረም፡፡ ለዚህ ሁሉ እርምጃቸው መደላደል (Ground) የሚፈጥሩበት ደግሞ ግንባሩ የተካነበት ሴራ ትንታኔ ስልት መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
በዚህ ረገድ የመጀመሪያው ታሪካዊው የሴራ ትንተና ለመድረክ የበቃው ኤርትራን ለማስገንጠል ኢህአዴግ የተከተሉት አቅጣጫ ነበር፡፡ ለዚህ እንቅስቃሴ ህጋዊ መሰረት ያደረጉት የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የተባለው በስድስት ቃላት የተገነባ ሀረግ ነው፡፡ ይህም ኤርትራን ከማሳጣቱ በተጨማሪ በአሁኑ ትልቁ ኢትዮጵያ ላይ የመበታተን አደጋ የጋረጠና እኩልነት ዋስትና የማይሰጥ የአስተዳደር ዘይቤ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የሴራ ትንተና ኤርትራ ጎጆ ለማውጣት ከኮሚኒስት ድርሳኖች ተገልብጦ የመጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም መለስ የሚመሩት ህወሓት ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ ለኤርትራው ግንባር ከመስጠቱም በላይ በኢህአዴግ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ ኢትጵያ የኤርትራ ቅኝ ገዥ መሆኗን እስከ ማስፈር ደርሷል፡፡ በዚህ የሴራ ትንተና የልብ ልብ የተሰማቸው የኤርትራ ታጠቃሚዎችም ትግላችን የነፃነት ትግል ነው በማለት፤ ነገሩን ታሪክ መልሰው ከዓላማቸው አንፃር በመከለስ፣ የሁለቱን ህዝቦች ታሪካዊ ትስስርና ኤርትራውያን ላንድነት ያደረጉትን ትግል በመካድ ኢትዮጵያና ኤርትራ በታሪክ ምንም የሚያገናኛቸው ነገር ኖሮ አያውቅም፤ ኤርትራውያን በሙሉ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ ለነፃነት ሲታገሉ ነው የቆዩት የሚል በሴራ ትንታኔ ላይ የተመሰረተ አዲስ ታሪክ በመፍጠር እነሱ ሳያምኑበት ዓለምን ለማሳመን በመሞከር ኢትዮጵያን ያለወደብ ማስቀረታቸው ታሪካዊ ስህተታቸው አንድ ብሎ ጀመረ፡፡
በዚህ ወቅት ሌላው በታሪክ ምፀት የታጀበው ክስተት ‹‹አማራ›› የተባለውን ብሔር ከአሁኑ ስርዓት ለማግለልና ከተቀረው ብሔር ብሔረሰብ ለማጋጨት የተጎነጎነው የሴራ ትንታኔ ነው፡፡ ይህም ‹‹የነፍጠኛው ስርዓት›› ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ በዚህ የሴራ ትንተና መሰረት ነፍጠኝነት በአማራው ብሔር በተለይም በሰሜን ሸዋ የተፈጠረ በተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች የተስፋፋ እንደሆነና አማራው ህዝቡ የተቀረውን በጭሰኝነት ጠፍሮ መሬቱን ቀምቶ የፖለቲካ ስልጣኑን፣ የኢኮኖሚ የበላይነቱንና የሀብቱ ምንጭ አድርጎ የተደላደለ ‹‹ነፍጠኛ›› ሀይል እንደሆነ ያቀርቡታል፡፡ የዚህ የሴራ ትንተና የመጨረሻ ግቡ ‹‹የአማራው ብሔርን›› የመቶ ዓመት የገዥነት ስያሜ በመስጠት አሁን ካለው ስርዓት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የማራቅ ስልት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡
በዚህም የአሁኑ ስርዓት ምሰሶ ናቸው የሚባልላቸው ብሔር ብሔረሰቦች አማራውን ያጋራ ታሪካዊ ጠላታቸው አድርገው እንዲያዩትና በታሪክ አጋጣሚ የነበረውን መስተጋብር እንዲያቋርጡና እንዲበቀሉት በተሰጠ የቤት ስራ በጣም ብዙ የብሔሩ ተወላጆች ለአሳዛኝ ግፍና ስቃይ መዳረጋቸው የቅርብ ጊዜ ሴራ ትንተና ውጤትና ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ ሁሉም የሚያስታውሰው ነው፡፡
በዚህ ስር ኢህአዴግ ኦነግን ከሽግግር መንግስቱ ለማስወጣት የተጠቀመበትን እና የመአህድን መመስረት ተከትሎ እንዴት ኢህድን ወደ ብአዴን እንደተሸጋገረና ሌሎች ታዳጊ ክልሎችን ለመቆጣጠር ‹‹አጋር ፓርቲዎች›› በምን አይነት የሴራ ትንተና ላይ እንደመሰረተ ማካተት ይቻላል፡፡
የአገራችን ሴረኛ ፓርቲ ሌላው ማደናገሪያና የሴራ ትንታኔ የሚያነጣጥረው አርሶ አደሩ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ቆሜለታለሁ የሚለው ምንነቱ ገና ግልፅ ላልሆነው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ በፓርቲ እምነት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መሰረቱ ደግሞ ሰፊው አርሶ አደር ነው፡፡ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቆሜያለው ከሚሉት ኢህአዴግ ባለስልጣናት ውስጥ ብዙዎቹ የነገሩን ምንነት የማይረዳቸውና የማያውቁ በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት ብቻ ሐረጉን ደጋግመው የሚጠሩት ካልሆነ በምንነቱ ላይ ከመለስ በቀር የሚያውቀው እንደሌለ ይነገርለታል፡፡ መለስም የሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲን የሚጠይቁትን ምዕራባዊያን የሚመቱበት በትር ያገኙ እየመሰላቸው የሆነ በአደባባይ የሚሰቀል መፈክር ፈብርኮ ከመስቀል ያለፈ ማብራሪያ ሲሰጡ አይስተዋልም፡፡ የተወሰነ ማብራሪያ ሲሰጡ አይስተዋልም፡፡ የተወሰነ የሰጡት ማብራሪያ ካለ የሚታወቁበትን የሴራ ትንታኔ በመጠቀም ፓርቲያቸው አርሶ አደሩን ለማልማት የቆመና ተቋዋሚዎች ደግሞ ለአርሶ አደሩ ንቀት እንዳላቸው በማቅረብ ወደ መቶ የተጠጋው የፓርቲያቸው የምርጫ ውጤት ከአርሶ አደሩ መሆኑንና ነጋዴው፣ ባለሀብቱ እንዲሁም የከተማ ምሁሩ የፓርቲ የአይዶሎጂ ጠላት አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ የዚህ የሴራ ትንታኔ አላማም የስርዓቱ መሰረት በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚቻለውን አርሶ አደሩ እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ አንፃራዊ የፖለቲካ ንቃት ያለውን የከተማውን ዜጋና በመካከለኛ መደብ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል የሚመጣበትን የስልጣን ተቀናቃኝ ቡድንና የፖለቲካ ማሻሻያ ጥያቄ ወደ ጎን ለማድረግ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተቀራራቢ የሆነው የሴራ ትንታኔ ልማታዊ መንግስት (Developmental state) የተሰኘው ነው፡፡ ይህ ፅንስ ሀሳብ በዓለም ደረጃ የቆየ ቢሆንም በአገራችን በስፋት የተዋወቀው ከታሪካዊው ምርጫ 97 በኋላ ሲሆን፤ ወቅቱም ኢህአዴግ ህዝቡን በሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት ፉካሬ ለማሳመን የሚጥርበት ጊዜ ሲሆን፣ የፍልስፍናውም ይዘት የዜጎች ሆድ በሆነ ነገር ከሞላ የዴሞክራሲ፣ የፍትህና የነፃነት ጉዳይ በምፅአት ጊዜም ቢሆን ይደርሳል የተባለበትና በመለስ የሴራ ትንተና ላይ የተመሰረተው አለማዊ ስብከት ነው፡፡
ወደ ምርጫ 97 ዋዜማ በእዝነ ህሊናችን መለስ ብለን በወቅቱ የህዝብን ቀልብ በሳበውና የቀድሞ ቅንጅትና ኢህአዴግ መካከል የተፈጠረውን ፍጥጫ ስናስታውስ አንድ ነገር እናገኛለን፡፡ በምርጫ ክርክሩ ወቅት፤ እንደ ዛሬ ህዝቡ ከሰማይ አውርዶ ሳይከሰክሳቸው አቶ ልደቱ ከዶ/ር ብርሃኑ ቀጥሎ የመድረክ አንበሳ ነበሩ፤ እናም አቶ ልደቱ በአንደኛው ክርክር ላይ የትግራይ የነፍስ ወከፍ ድጎማ ለሌላው ክልል ከተመደበው ይበልጣል ብለው ከተናገሩ በኋላ በመለስ የሚመራው ኢህአዴግ እንደ እመጫት ነብር ቁጡ በመሆን ቅንጅትን ኢንተርሀሞዌይ ነው ብለው ፈረጁት፡፡ ይህም በመለስ የሴራ ትንታኔ ቅንጅቶች ልክ ኢንተርሃሞዌይ የተባለው ቡድን በ1980ዎቹ ውስጥ በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ያካሄደ የሚሊሺያ ቡድን የዘር እልቂት በትግራይ ተወላጆች ላይ እየደገሰ ነው ሲሉ ወነጀሉት፡፡ በኢንተርሃሞዌይ የሴራ ትንታኔ ሌላ በወቅቱ ኢህአዴግ ቅንጅትን ለመምታት ሴራውን የጠነሰሰበት በዶ/ር ነገደ ጎበዜ መፅሐፍ ላይ ተመስርቶ ኢህአዴግ ያቀረበው የሴራ ትንታኔ ነው፡፡ በእርግጥ የመለስ ቀኝ እጅ አቶ በረከት ነበሩ፤ መፅሐፉን ክርክሩ ወደ ማካሄድበት አዳራሽ ይዘው በመምጣት ቅንጅት የሚመራው በዚህ መፅሐፍ እንደሆነ አሳይተዋል፡፡ ይህም የሴራ ትንተና የቅንጅት ከምርጫው ማግስት የቅንጅት አመራሮች ለዕድሜ ልክ እስራት ለበቁበት ጉዳይ ዋና የፍርድ ቤት ጭብጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የሚገርመው ግን ዶ/ር ነገደ ጎበዜ የህብረት አባል ድርጅት የሆነው የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ ንቅናቄ (መኢሶን) መሪ ስለነበሩ የሚቀርቡት ለቅንጅት ሳይሆን ለህብረቱ መሆኑ ነው፡፡ በጥቅሉ ጠ/ሚኒስት ሩ የሚያራምዱት ሴራ ትንተና፤ አገርንና ህዝብን የሚጎዱ የበርካታ ስህተቶች መሰረት መሆኑን በመገንዘብ በቃላቸው ከፀኑ ጠ/ሚኒስትሩ ከአምስት ዓመት በኋላ ከስልጣን ሲወርዱ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚኖራቸው ቦታ (Legacy) ምን እንደሚሆን ሊያሳስባቸው የሚገባ ይመስለኛል፡፡
እንደዚሁም የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤት ወደ ድንበራችን አንድ ሜትር እንኳን ባልተጠጋበት ሁኔታ ጦርነት ታውጆብናል በሚል በሰው አገር ላይ የተፈፀመው ወረራ በዚሁ የሴራ ትንተና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ላይ በ1993 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ አቶ ስዬና ገብሩን ጨምሮ ወሳኝ ተቀናቃኞቻቸውን ለማስወገድ የቦናፓርቲዝም የሴራ ትንተና መለስ እንደተጠ ቀሙ ይታወሳል፡፡ በኋላ ላይ ግን ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንዳ መለከቱት መለስ ይህን አይነት የቦናፓርቲዝም ትንተና ወደ መድረክ የመጡት የክፍፍሉ መንስኤ የኤርትራ ጉዳይ ሳይሆን የፓርቲው ውስጣዊ መበስበስ እንደሆነ በማሳየት የህዝቡን ትኩረት ለማስቀየስና በኋላ ላይ በሙስና አማካኝተው እነ ስዬን ወደ እስር ቤት ለመወርወር ያለመ ነበር፡፡
በዚህ አይነት የሴራ ትንተና ኢላማ ከነበሩት መካከል ሲቪል ማህበረሰቡና ነፃው ፕሬስ ይገኙበታል፡፡ ነፃ የብዙሃን ማህበራትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና አንኳሶ በማየትና የተቋዋሚ ፓርቲዎች አጋር አድርጎ በማቅረብ እንቅስቃሴያቸውን በህግ ለመገደብ ችሏል፡፡ ይህም የሆነው በምርጫ 97 ወቅት ተቋዋሚን ረድተዋል የሚለው የመለስ የሴራ ትንታኔ ነው፡፡ ይህ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃ ባለመኖሩ ለትንታኔው ሁነኛ ግብአት አድርጎ የተጠቀመበት የሁለት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞች ያውም በግላቸው በወቅቱ በግል ጋዜጦች የሰጧቸው ሙያዊ ቃለ ምልልስን በአመፅ መቀስቀስ ከቅንጅት መሪዎች ጋር አብሮ ማሰሩን ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የሲቪል ማህበሰቡ በተጣለበት የህግና የፋይናንስ ገደብ የተነሳ የሚጠበ ቅበትን ዜጎችን ስለመብቱ የማስተማርና ነፃ ምርጫ የአገሪቱ እንዲካሄድ የማገዝ ኃላፊነቱን ገዢው ፓርቲ በአምሳሉ ለፈጠራ ቸው ‹‹ማህበራት፣ ሊግና ፎረም›› እንዲለቅ ተደርጎ ይገኛል፡፡
ነፃውም ፕሬስ ቢሆን ዘወትር በሚቀመጡበት ህጋዊና አስተዳደራዊ እንዲሁም ሌሎች ገዳብ ስልቶችን በመጠቀም ዘርፉን በማዳከም ሜዳውን በገዢው ሳንባ ለሚተነፍሱት ለማስፋት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህ እርምጃ መነሻ የሆነው የሴራ ትንተናም ነፃው ፕሬስ የመረጃ ነፃነት አዋጁ ስራ ላይ ሊውል ባለመቻሉ የተነሳ ከመንግስት አካላት መረጃ ለማግኘት ያለበትን ችግር ላይ በመንተራስ ፕሬሱን ‹‹ሚዛናዊ›› ባለመሆ ንና የተቋዋሚ ፓርቲ ልሳን አድርጎ በማቅረብ የተለያዩ የህት መት ዋጋን መጨመርና በገበያው እንዲቀጥሉ የማይፈልጋቸው ን ህትመቶች ማስታወቂያ እንዳያገኙ የማድረግ ስልት ነው፡፡
ዋናውና አቻ ያልተገኘለት ጦር የተመዘዘበት ደግሞ ‹‹ሀቀኛ ተቋዋሚ ፓርቲዎች›› ላይ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢህአዴግ የምንጊዜም የብትሩ ኢላማዎች ቢሆኑም በምርጫ 97 ከታየው የተቃዋሚዎች አቅምና ያላቸው የህዝብ ድጋፍ ከታወቀ በኋላ ደግሞ እንዳያንሰራሩ አከርካሪያቸው ከመመታቱም በላይ እንቅስቃሴያቸውን በመከታተል ከዳዴነት አልፈው በሁለት እግራቸው ለመቆም የሚሞክሩት ላይ የተለያዩ አይነት የሴራ ትንታኔዎችን በመቀመር የማያዳግም በትር ማሳረፍ ቋሚ የገዢው ፓርቲ ስትራቴጂ ማድረጉን ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ስትራቴጂ የቅርብ ጊዜ ማሳያ የሆኑት ብቸኛው የፓርላማ አባል የህገ መንግስቱን ማሻሻያ በተመለከተ ላቀረበው ጥያቄ ተቋዋሚዎች ግልፅና ተጨባጭ አደጋ (clean and present danger) እስከሚሆኑ ገዢው ፓርቲ እንደማይጠብቅና በሌላ አነጋገርም ፓርቲዎች እንዳይጠናከሩ፤ ከዛም በፊት በተለያየ ስልት እንደሚያዳክማቸው መለስ በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ የዚህም ስትራቴጂ ማስፈፀሚያው ታክቲክ ‹‹የማምከኛ ስርዓት›› ተብሎ በፓርቲ የደህንነት ሰዎች የሚጠራው ነው፡፡ ይህም ማለት በሀቀኛ ተቃዋሚነታቸው የሚታወቁ ፓርቲዎችን ለመከፋፈል ከተቻለም ለማምከን የሚያስችል ስራ በፓርቲዎቹ ውስጥ እንደሚሰራ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም አልሳካ ብሎ ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ከቻሉ የተለያዩ አስፈሪ ፍርጃዎችን በመለጠፍ ወትሮም ህዝቡ በሚገኝበት የፍርሃት ቀፎን የተነሳ ፓርዎች ባላቸው የአባላትና የፋይናንስ ድርቀት ላይ ተጨማሪ ጫናን በመፍጠር ፓርቲዎቹን ማክሰም ነው፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳ የሚሆነውና የሴራ ትንታኔአቸው የመጨረሻው ደረጃ እንደደረሰ የታየበት ባሳለፍነው ሳምንታት መለስ መድረክን በአጠቃላይ በተለይም አንድነትን በሽብርተኝነትና አመፅን በማነሳሳት መክሰሳቸው ነው፡፡ በወቅቱም መድረክ ታስረውብኛል ብሎ ያቀረባቸው የኦነግ አባላት እንደሆኑና አሁን ካሉት የፓርቲ አመራሮች መካከል የኦነግ አባላት እንደሚገኙበት በሴራ ትንታኔቸው አረጋግጠዋል፡፡ እንደ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ከሆነ ጠ/ሚኒስትሩ መድረክ በተለይ አንድነት ላይ ያተኮረው በአሁኑ ወቅት ብቸኛ የሚያሰጋው ፓርቲ በመሆኑ ነው፡፡ ስጋቱም የሚመነጨው መድረክ የኢህአዴግን የብሔር ፖለቲካ የሚያመክን መድኃኒት ይዞ በመምጣቱና የመድረክ መሪዎች እነ ዶ/ር ነጋሶ፣ ገብሩና ስዬን የመሳሰሉ የቀድሞ የፓርቲው መሪዎች ቁልፍ ቦታ መያዛቸው ስላስበረገገው ነው ይላሉ፣ ልክ ብርቱካን የመጀመሪያዋ የሴት መሪ ሆና ብቅ ስትል የሴቶች ጉዳይ ከኔ በላይ ላሳር ለሚለው ኢህአዴግ ማምከኛ መሆኗ ለዳግም እስራት መብቃቷን በማስታወስ፡፡
በአጠቃላይ በአገራችን ታሪክ አንፃር ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎችን ስናይ በአብዛኛው አገርና ህዝብን የሚወዱ በህዝቡም ዘንድም በጣሙን የሚከበሩ እንደ ህዝብ ከህዝብ ጋርም የሚኖሩ በደስታም ሆነ በሀዘን ወቅት ከሚመሩት ህዝብ ጎን የማይለዩ፤ በጦርነት ጊዜ ግንባር ቀደም አዝማች ሆነው ሠራዊታቸውን በማዋጋት ለድል የሚበቁ፤ በአገር ክህደት ወንጀል እና አፍራሽ ድርጊት ያከናውናሉ ተብለው በፍፁም የማይጠረጠሩ ክቡርና ውድ መሪዎች ነበሩ፡፡ የአሁኑ መሪያችን ግን ከእነዚህ ከተጠቁሰት የጥንታውያን መሪዎች የመልካም ባህሪ ገላጭ ተግባራት ውስጥ ስንቶቹን እውን እንዳደረጉ በትክክል ማወቅ ያስቸግራል፡፡µ

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop