April 29, 2013
21 mins read

ድምፃዊት አስቴር ከበደ – ከ25 ዓመት በኋላም ዝናዋ ናኝቷል

ከዕጸገነት አክሊሉ

በአገሪቱ ሙዚቃ ውስጥ ተወዳጅና ስመጥር ከሆኑት ባለሙያዎች ተርታ ትመደባለች። በሙዚቃው ዓለም ለአጭር ጊዜ ብቅ ብለው አንቱታን ካተረፉና ዘመን ተሻጋሪ ሥራን ካኖሩ ሙዚቀኞች መካከል የምትጠቀስ ናት። ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ነው ወደ ሙዚቃው ዓለም ጎራ ያለችው።በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ ሥራን በመሥራት በትውልዱ ዘንድ አይረሴነትንም አትርፋለች።
ጥበብ ለእርሷ ሁሉም ነገር ቢሆንም የሕይወት አጋጣሚ ሆኖ ሳታስበው ከጥበቡ ዓለም ለ 25 ዓመታት ራሷን አግልላም ቆይታለች። የኋላ ኋላ የሙያው ፍቅር አስገድዶ ወደ መድረክ መልሷታል የዛሬዋን አምዳችንን – ድምፃዊት አስቴር ከበደን።
ድምፃዊት አስቴር ከበደ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም በአባቷ የሥራ ፀባይ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የመዘዋወር አጋጣሚ ነበራት። ጅማ፣ ወልቂጤና ወሊሶ ጥሩ የልጅነት ጊዜያት ማሳለፏን አልዘነጋችውም።
እናትና አባቷ ካፈሯቸው ዘጠኝ ልጆች መካከል አስቴር ሦስተኛዋ ናት። በዚህ በቤተሰብ ውስጥ ይኸ ለወንድ ይህ ደግሞ ለሴት ተብሎ የተከፋፈለ አስተዳደር የለም። ሁሉም እኩል ነው፤ ሁሉም በነፃነት የመማር፣ የሚፈልገውን የማድረግ ዕድሜው ሲደርስም ያዋጣኛል ብሎ በመረጠው የሕይወት ጎዳና የመጓዝ ዕድል ተሰጥቶታል።
አስቴርም ከትምህርቷ ጎን ለጎን የሕይወት ጥሪዋን የምታስተናግድበትን ዕድል የነፈጋት አልነበረም። ለዚህም ነው በትምህርት ቤት በወላጆች ቀን ሙዚቃ የማቅረብ ዕድል ያገኘችውና ለሙዚቃ ሕይወቷም መሰረት የጣለችው።
« በትምህርት ቤታችን በየዓመቱ የሚከበረው የወላጆች ቀን ለእኔ ልዩ ስሜትን የሚፈጥርብኝ ነበር፤ ምክንያቱም ተሰጦዬን ላወጣበት የምችልበት ብቸኛው አጋጣሚ ነው። በዚያን ዕለት በጓደኞቼ ፊት ቆሜ የምዘፍንበት ጊዜ በመሆኑም እጅግ ደስ ይለኛል» ትላለች።
እንዲህ በትምህርት ቤት የተጀመረው የሙዚቃ ፍቅርና ተሰጥዖን የማውጣት ልምድ ደግሞ ከዕድሜ ጋር አብሮ እያደገ መጣ። በውስጧ የተፀነሰው የሙዚቃ ፍቅር እያደገ ሲሄድ ካልወጣሁ እያለ ይተናነቃት ጀመር ። ይህንን ያወቀችው አስቴርም ፍላጎቷን ለመገደብ አልሞከረችም ይልቁንም ፍላጎቴን ያወጣልኛል እንዲሁም ያሰብኩበት ደረጃ ያደርሰኛል ያለችውን መንገድ መፈለግ ጀመረች እንጂ። በወቅቱ ያገኘችው ብቸኛው አማራጯ የእድሜ እኩዮቿ ተሰጥዖአቸውን የሚያወጡበትን የቀበሌ ኪነት ነበር። ጊዜ ሳታጠፋም ወደ ቀበሌ ኪነት ተቀላቀለች። ከዚያም ደረጃዋን እያሻሻለች ወደ ከፍተኛ የኪነት ቡድን ገባች። ይህ አካሄዷ ደግሞ ቶሎ ወደ ቴአትር ቤቶች እንድትቀላቀል የራሱን መንገድ ጠረገላት።
በወቅቱ የነበረው አስተሳሰብ ቤተሰብ ልጆቹን በራሱ መንገድ ቀርጾ ማሳደግን የሚደግፍ ነበር ። ልጆቹ ወደ ጥበቡ ዓለም ለመግባት ሲያስቡ በሰላም ሁኔታዎችን የሚያመቻች ቤተሰብ ቁጥር እጅግ አናሳ ነበር። የአስቴር ከበደ ቤተሰቦች ግን ከዚህ ፍጹም የተለዩ ነበሩ። የልጃቸውን የጥበብ ጥሪ ለማስተናገድ አልተቸገሩም። ጥረቷን በማድነቅም እንድትገፋበት አበረታቷት።
«በቤተሰቤ በኩል ይህንን አትሆኚም። እንድትሆኚ የምንፈልገው ያንን ነው። የሚል ሙግት አልገጠመኝም። ሆኖም ከከፍተኛ ኪነት ወጥቼ ሲኒማ ራስ እንደተቀጠርኩ ብዙም ሳልቆይ ለመድረክ ሥራ ወደ ቀድሞው አሰብ ክፍለ ሀገር እንድሄድ ታዘዝኩ ፤ በዚያን ጊዜ ደግሞ ከቤት ወጥቼ አድሬ አላውቅም ነበር። ምን ብዬ ነው የምነግራቸው የሚለው ፍርሀት በጣም አስቸግሮኝ ነበር። ሆኖም ከቤታችን ውስጥ አንደኛው ወንድሜ በጣም ሙዚቃ ይወዳልና ለእርሱ ስነግረው ‘ ምንም ችግር የለውም ንገሪያቸው ‘ አለኝ። ነገርኳቸው ያንን ያህልም ጫና ሳያሳድሩብኝ ተቀበሉኝ።»
አሰብ የመጀመሪያ ሥራዋን ያቀረበችባት ቦታ ናት። በወቅቱ ከዘፈኑ ባሻገር የብሔር ብሔረሰቦችን ውዝዋዜም ደርባ ትሰራ ነበር። እናም አሰብ በቆየችባቸው ጊዜያት በይበልጥ የሰራችው የብሔር ብሔረሰቦችን ውዝዋዜ እንደነበርም ታስታውሳለች። የመጀመሪያዋ እንደመሆኑም የሕዝቡ አድናቆትና አቀባበል ይበልጥ ወደ ጥበቡ እንድታዘነብል አድርጓታል።
አንድ ሙዚቃ እንጋብዛችሁና ዘገባው ይቀጥላል

ድምፃዊት ሂሩት በቀለ ለእርሷ ሞዴል እንደሆነቻት የምትናገረው አስቴር የራሷን ሥራ ከመሥራቷ በፊትም አዘውትራ ትጫወት የነበረው እንዲሁም ሲኒማ ቤት ለመቀጠር ተፈትና ያለፈችበት ሙዚቃም የሂሩት በቀለ መሆኑን ታስታውሳለች።
ከዛሬ 25 ዓመት በፊት የሠራችው የራሷ የሙዚቃ አልበም ደግሞ ብዙ አድናቂዎችን እንድታፈራ ከማድረጉም ባሻገር ዘመን ተሻጋሪ በመሆን እስከ አሁን ድረስ እየተደመጠ ይገኛል።
«ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑ ጥቂት ሥራዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ሥራዎቹ እጅግ የተለፋባቸው በመሆናቸው እንዲሁም ዜማና ግጥም የሰጡኝም ሰዎች በሙያው በሳል ስለነበሩ ነው»ትላለች ስለ መጀመሪያ ሥራዋ ስትገልጽ።
አስቴር ከበደ ዘመን አይሽሬ ስለሆነው ብቸኛው የሙዚቃ አልበሟ ስትገልጽም የስምንቱን ዘፈኖች ግጥምና ዜማ የሠራው አርቲስት ንዋይ ደበበ እንደሆነ ትናገራለች። «ፍቅር እንዳሰቡት» የሚለውን ዜማ ደግሞ አርቲስት ደበሽ ተመስገን እንዲሁም ሙሉ ገበየሁ እንደሰጧት ታስታውሳለች። እዚያው አልበም ላይ «ለጤና ያድርግልኝ» የሚለውን ዜማ ደግሞ እርሷና ሙሉ ገበየሁ በጋራ ነበር የሠሩት።
ድምፃዊት አስቴር ምንም እንኳን ከእነዚህ ታላላቅ ባለሙያዎች ጋር የመሥራት ዕድል አግኝታ የሙዚቃ አልበሟ እጅግ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ቢሆንም ብዙ ሳትጠቀምበት፥ በአድናቂዎቿም ሳትጠገብ ነበር በትዳር ምክንያት ኑሮዋን ከኢትዮጵያ ውጭ ያደረገችውና ከሙዚቃው ዓለም ራሷን ያገለለችው።
«ሙዚቃዬ እንደወጣ ወዲያው ትዳር መስርቼ ወደ ሳውዲ አረቢያ ነበር የሄድኩት። በእዚያም ከ25 ያላነሱ ዓመታትን ቆይቻለሁ። ወደ አገሬ የመምጣት ዕድሉ ቢኖረኝም ሙዚቃን የመሥራት አጋጣሚ ግን አልተፈጠረልኝም ። ከሙዚቃ ተለይቶ መቆየቱ እጅግ ፈታኝ ቢሆንብኝም ልጆች የማሳደግ ድርብ ኃላፊነት ስለነበረብኝም ወደዚያ አዘምብዬ ለብዙ ዓመታት ከሙዚቃው ራቅሁ» በማለት ነው ለ25 ዓመታት ከሙዚቃ የራቀችበትን ምክንያት የምትገልጸው።
የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ እናት የሆነችው አስቴር «ልጆቼ አድገው እኔም ወደ ምወደው የሙዚቃ ሕይወት ተመልሼ» የሚለውን ምኞቷን ለማሳካት 25 ዓመታትን በትዕግስት ጠብቃለች። አሁን ደግሞ ያ የተመኘችው ቀን ደርሶ ልጆቿ አድገውላታል፤ ወደምትወደው የሙዚቃ ሥራም ተመልሳለች።
ከ25 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ሙዚቃው ሕይወት ተመልሳ ለአድናቂዎቿ ያን ተስረቅራቂ ድምጿን ማስደመጥ ችላለች። ዳግም ወደ ሙዚቃ ስትመለስ እዚያው ሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ከአርቲስት ታምራት ደስታ ጋር ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ያዜመችው። ይህ ጅማሬ ደግሞ አገሯ ገብታ ተጨማሪ የሙዚቃ ሥራዎችን እንድትሠራ አድናቂዎቿንም እንድታዝናና መነሳሳትን እንደፈጠረባት ትናገራለች።
«ሳውዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ከታምራት ደስታ ጋር ሥራዬን ሳቀርብ ከተመልካቹ ጥሩ አቀባበልን አየሁ። ለካ አድናቂዎቼ አልረሱኝም የሚል ስሜትን ፈጠረብኝ። ይህ ደግሞ ቶሎ አገሬ ገብቼ የሙዚቃ ሥራን እንድሠራ አደረገኝ ።»
ከ25 ዓመታት የውጭ አገር ኑሮ በኋላ ጉዞ ወደ አገር ቤት ሆነ። አስቴር አገር ቤት የገባችው እንዲሁ ልጆቿን እያሳደገች ለመኖር ብቻ አልነበረም። ይልቁንም ሙዚቃዋን ሳይጠግቡ በድንገት የተለየቻቸውን አድናቂዎቿን በሙዚቃ ሥራዋ ለማዝናናትም እንጂ። እንደተመኘችውም ዳግም ከሙዚቃ ጋር ተገናኝታ ችሎታዋን ማስመስከር ጀመረች። በየመድረኩ በዚህ ትውልድም ተወዳጅ የሙዚቃ ሰው መሆኗን እያስመሰከረች ትገኛለች።
አስቴር ምንም እንኳን የተዋጣላት ሙዚቀኛ ብትሆንም ከብዙ ዓመታት ቆይታ በኋላ ነውና ወደ ሙያው የተመለሰችው እንግድነት ብጤ ሳይሰማት ይቀራል ብሎ መገመት ያስቸግራል። እርሷ በሙዚቃው ዓለም ነግሳ በነበረበት ወቅት እንዳለው ሳይሆን የሙዚቃ ሥራውም በእጅጉ ተለይቷል። በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎችም ተፈጥረዋልና እንዲያው የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ እንዴት አገኘሽው? ስል ጥያቄዬን ሰነዘርኩ።
« በአሁኑ ወቅት ያለው የሙዚቃ ሁኔታ ጥሩ ነው። የባለሙያዎቹ የፈጠራ ችሎታ፣ የወጣቶቹ ጥረትና ስኬት ያስገርማል፤ የህብረተሰቡ ሙዚቃ አድማጭነት በአጠቃላይ የሚታየው ነገር ለመሥራት ያነሳሳል። በተጨማሪም የሙዚቃ ቀረፃውና ቅንብሩ ከድሮው ሙሉ በሙሉ ተለውጧል ማለት ይቻላል፤ በእኔ በኩል ደግሞ ብዙም ምክር የሚለግሱኝ ሰዎች ባለማግኘቴ ትንሽ ከብዶኝ ነበር» ትላለች ዘመንን እያነጻጸረች።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ካሴት ሲሰራ በሙሉ የሙዚቃ መሣሪያ በመታገዝ ነበር።ዘፋኙ አንዴ ወደ ቀረጻ ከገባ ግጥም ቢሳሳተው እንኳን ለመመለስ ከባድ ነበር። ብዙ ጥንቃቄና ችሎታን የሚጠይቅ ነበር። ሥራው አድካሚ ቢሆንም ዘፈኖቹ በጥራትና በብቃት የተሰሩ በመሆናቸው ተወዳጅነታቸውና ተደማጭነታቸው ያንንኑ ያህል ነበር። አሁን ሥራው እጅግ ቀሏል፤ ብዙ ነገሮች በኮምፒውተር አጋዥነት ይሠራሉ። ሙዚቀኛው በቀረፃ ላይ ስህተት ቢፈጽም ያ ተሰርዞ እንደገና መቀዳት ይችላል፤ የልምምድ ጊዜውም ብዙ ነው። በአጠቃላይ እነዚህ የዘመን ልዩነቶች በመፈጠራቸው የሙዚቃ አሠራሩ ተለውጧል ትላለች።
ተጨማሪ ሙዚቃ ግብዣ….ከዘ-ሐበሻ – ዘገባው ከዘፈኑ በታች ይቀጥላል

አስቴር ሙዚቃ ለመሥራት ስትነሳ ከከበዳት ነገር መካከል በእርሷና ሙዚቃውን ሊሰሩላት በሚስማሙት ወገኖች መካከል የሚደረጉ ውሎች፥ የአከፋፈል ሁኔታና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች የማታውቃቸው መሆናቸው ነው። እርሷ ሥራው ላይ በማተኮሯ ስለምታገኘው ገንዘብ ተገቢውን ትኩረት ሰጥታ አልተከታተለችም። በጥንቃቄ መፈረም ስላለባቸው ጉዳዮች ባለማወቋ እንደተቸገረችም አጫውታኛለች።
ድምፃዊት አስቴር ወደ ሀገሯ ከመጣች ጥቂት ጊዜያት ተቆጥረዋል። ይሁን እንጂ አዳዲስ ሥራዎችን ለአድናቂዎቿ ለማቅረብ አልቻለችምና ምክንያቱ ምን ይሆን? ስል ጥያቄ አቀረብኩላት።
«ከዛሬ 25 ዓመት በፊት የዘፈንኩት ዘፈን አሁንም አዲሱ ትውልድ እየሰማውና በምሽት ክለቦች አካባቢም እየተዝናናባቸው ይገኛል። ይህ ደግሞ ለእኔ በጣም አስደሳች ነው። ስለዚህ እሱ ትንሽ ይሰማ ብዬ እንጂ አርፌ አልተቀመጥኩም። አዲስ ሥራ ለመስራት ከተለያዩ ሰዎች የግጥምና ዜማ ሥራዎችን እያሰባሰብኩ ነው።»
በአሁኑ ወቅት ሙዚቃ ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት ዘርፍ ሆኗል። ቀድሞ በእነርሱ ዘመን ትልቅ ገንዘብ አወጣ የተባለ ካሴት የሚሸጠው ከ2ሺ ብር ባልበለጠ ዋጋ እንደነበር የምትገልጸው አስቴር ፤ አሁን የቀድሞውን ዜማዎቿን በድጋሚ ሰርታ (ሪሚክስ ) በ3 መቶ ሺ ብር መሸጧንም ትናገራለች።
አስቴር ሁለተኛውን የሙዚቃ ሥራዋን ለመሥራት ስታስብ እጅግ ከባድና ፈታኝ የሆነባት ነገር የግጥምና ዜማ ጉዳይ ነው። በአሁኑ ወቅት የሚዘጋጁ ግጥምና ዜማዎች የቶሎ ቶሎ ሥራ መሆናቸውን ታዝባለች። « መምረጥ ካልተቻለ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሁሉም በዘመኑ መልካም ቢሆንም የድሮ የግጥምና ዜማ ሥራዎችን የሚስተካከል ግን አላየሁም። ስለዚህም የተሻለ ሥራ ለመሥራት በጥንቃቄ መምረጥና ደጋግሞ ማሰብም ያስፈልጋል» ባይ ናት።
በርካታ ወጣቶች ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመቀላቀል ይፈልጋሉ። ከዚያም ባሻገር በተለያዩ ሁኔታዎች እንደ ኢትዮጵያን አይዶል፣ባላገሩ አይዶል እንዲሁም ሌሎች መሰል ውድድሮች ላይ በመካፈል ተስጥዖአቸውን ይፈልጋሉ። «ይህ ሁሉ መልካም ነው» የምትለው አስቴር ሆኖም ታዋቂ ለመሆን አልያም ሙዚቀኛ ለመሆን መቻኮል ሳይሆን በትዕግሥት በሰል አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል በማለት ትመክራለች። ዋናው ነገር ግን ውጤታማ ለመሆን በውስጣቸው የሥራውን ስሜት በማሳደግ ሳይታክቱ፣ ሳይሰላቹ መሥራት ነው ባይ ናት። «ዛሬ የሠራሁት ሙዚቃ ወይም ፊልም አድማጭ ተመልካች አላገኘም ብሎ መንገድን መሳት ተገቢ አይደለም። በትዕግሥት ያሰቡበት መድረስ ይቻላል» ስትልም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
የቅጂ መብትን ከማስከበር አንፃር መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ለጥበቡ የሰጡት ትኩረት እጅግ በጣም የሚያስመሰግን በመሆኑ ህብረተሰቡም የእዚህ ትግል ተባባሪ በመሆን ኦርጂናል ሥራዎችን በመግዛት የሚወዳቸውን አርቲስቶች ማበረታታትና መደገፍ እንደሚጠበቅም ትናገራለች።
አስቴር በአጭር ጊዜ ውስጥ እውቅናን ያተረፈች፤ ለ25 ዓመታት ከሙዚቃው ዓለም እርቃ ቆይታ በድጋሚ እውቅናዋንና ዝናዋን ያስመለሰች የሙዚቃ ሰው ናት። መዚቃ ለጥበብነቱ መሠራት አለበት የሚለው አቋም ያላት ሙዚቀኛ ናት። ለምትሠራቸው ሙዚቃዎችም ከፍተኛ ጥንቃቄ በማደረግ እውቅናዋንና ተወዳጅነቷን እንዳስጠበቀች ለመቀጠል እየሠራች ትገኛለች። ለሌሎች ወጣት ድምፃውያን አርአያ መሆን የምትችል መሆኗንም ዘመን ባልሻራቸው በሥራዎቿ አስመስክራለች።

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop