‹‹የተመኘሁትንና የፈለኩትን ነው የሆንኩት›› ድምጻዊ አቤል ሙሉጌታ




በሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣውን አቤል ሙሉጌታ ዘፈኑን ካደመጡት በኋላ ቃለ ምልልሱን ያንብቡት።
ጥያቄ፡- ‹‹ተገርሜ›› አልበም እያስገረመ ነው? እውነት ሐሰት?
አቤል፡- /ሳቅ/ እውነት፡፡ ከማየው ከምሰማው ከሚደርሱኝ አስተያየቶች በመነሳት አድማጩ ላይ ጥሩ ነገር ስላለ አዎ ተገርሜ እያስገረመ ነውና እውነት ነው እላለሁ፡፡
ጥያቄ፡- የሰው አፈጣጠሩ የገረመህ ይመስላል?
አቤል፡- ያው ከፍጥረታት ሁሉ የበላይ በመሆኑ ይህንን፣ በመረዳት ነው የሰራሁት፡፡ አልበሙም ላይ እንደሚለው ከፍጥረት ሁሉ የበላይ የሆነውን ሰው ያለውን የበላይነት በመረዳት የተጻፈ ነው፡፡ ምክንያቱም ውበት ያን ያክል ያማረ ቢሆን የፀሐይ የጨረቃን ውበት ብትረዳ እንኳን ሰው የሌለበት ነገር ባዶ ነው የሚሆነው፡፡ እና ሰው ለሁሉም ነገር ውበት ነውና ከተፈጥሮ ሁሉ የበላይ የመሆኑ ነገር ስለገባኝ ነው ተገርሜን የሰራሁት፡፡
ጥያቄ፡- አልበሙ እያደር እንደሚጣፍጠው ወይን ሆነ ልበል? አሁን አሁን ብዙ ቦታ ይሰማል?
አቤል፡- በጣም /ሳቅ/ አሁን አሁን እየተሰማ ነው፡፡ በጣም ደስ የሚል እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡
ጥያቄ፡- አንተ ተገርሜ አልክ፡፡ እኛ ደግሞ በኮሜ እየጨፈርን ነው፡፡ ስሜትህ ምንድን ነው?
አቤል፡- የሚገርምህ እኔ ለአልበሙ ርዕስ ተገርሜን ልምረጥ እንጂ ኮሜ ቀድሞ እንደሚወደድ በፊትም እገምት ነበር፡፡ የሆነው ነገር ስለደረሰ ብዙም አልተገርምኩም፡፡ ግን ተገርሜ ለስላሳ ዜማ እንደመሆኑ ሰውን ባያስጨፍርም በየቢሮው በየኮምፒውተሩ ተጭኖ ሲሰማ ታያለህ፡፡
ጥያቄ፡- የኮሜን ትርጉም ምንድን ነው?
አቤል፡- /ሳቅ/ ነይ ማለት ነው፤ አንድ ጊዜ ነይ እንደማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ጭብጡ ትንሽ ለየት ያለ ይመስላል፡፡ ቆንጆ አይተን የእኔ በሆነች የሚሉ ግጥሞች የለመደው ጆሯችን በሆነች እህቴን ሲሰማ ደስ ይላል፡፡
አቤል፡- ጥበብ እንደሚታወቀው እውነታን ማሳያ መስታወት ነች፡፡ ታሪኩ ላይ እንዳየነው ከእህቴ ጋር ኑሮ አለያየን፡፡ ለጉዲፈቻ ተሰጠን፡፡ ካደኩ በኋላ እናቴን የምትመስል ሴት አየሁ፡፡ እናቴን የማውቃት በፎቶና በልጅነቴ ባለችኝ ውስን ትዝታ ሊሆን ይችላል፡፡ እና ይህች ልጅ እህቴ እንዳትሆን ብዬ ቀረብኳት፡፡ እውነትም ሆነች፡፡ ይህ ነው ታሪኩ፡፡
ጥያቄ፡- ከተደመጠ በኋላ ታሪኬ ነው ሲል ሀሎ ያለህ አለ?
አቤል፡- የሚገርምህ ሲያለቅሱ ያየሁበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንዴ የእኔ ቢሆንስ ብለህ በቦታው ራስህን የምታስቀምጥበት ሁኔታ አለ፡፡ እና አዝነው ያለቀሱ አጋጥሞኛል፡፡ እስካሁን ግን ታሪኬ ነው ያለኝ የለም፡፡ የእኔም ታሪክ አይደለም /ሳቅ/

ጥያቄ፡- ከዚህ በፊት የምትታወቀው ነይ ማታ ማታ በሚለው ዜማህ ነበር እና ፖስተርህ ላይ ነይ ማታ ማታ አለመጻፍህ አልጎዳህም?
አቤል፡- የጎዳኝ ቢመስልም አልጎዳኝም፡፡ ምክንያቱም ያሰብኩትን አግኝቻለሁ ነው የምለው፡፡ በዘፈኔ እንድታወቅ ስላልፈለኩ ነው፡፡ ነይ ማታ ማታ ብዬ ከጎን ብፅፍ አቤል የሚለውን እሰርዘዋለሁ፡፡ አሁን ግን ባለማድረጌ አቤል ሙሉጌታ የሚለው ስሜ ታውቋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በትላንትናው ስራዬ ተሸሽጌ ሳይሆን ይዤው በመጣሁት ስራ ተፈትኜ አድማጭ ጆሮ በመድረሴ ደስተኛ ነኝ፡፡
ጥያቄ፡- ኮሜን ብቻ ተጋኖ እየተሰማ መሆኑ ሌሎቹን ስራዎችህን አልቀበረብህም?
አቤል፡- ይሄ በእኔ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የተለመደ ነገር ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም አልበምህ በአንዴ አይፈነዳም፡፡ ለምሳሌ ሄለን በርሄ ብትወስድ መጀመሪያ ‹‹ልቤ›› የሚለው ዘፈኗ ብቻ ነበር በስፋት ይደመጥ የነበረው፡፡ ከዛ እያለ እያለ ነው ሙሉ አልበሟ የተሰማው፡፡ እና ቶሎ የሚወደደው ገበያ ይይዛል የምትለው ስራ ነው፡፡ እንዳልኩህ ኮሜ እንደሚወደድ ገምቻለሁ፡፡ መገናኛ ብዘሃንም ያን በስፋት ለቀቁት፡፡ አሁን አሁን ግን ሌሎቹንም እየለቀቁት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ገዳም ስለገባችው እንስት ታወራን?
አቤል፡- ገዳም ገባች አሉ ቁጥር ሁለት ተሰርቷል፡፡ ቁጥር አንዱ ላይ ‹‹ይፍረዱኝ አባት›› ነበር የሚለው፡፡ ቁጥር ሁለት ላይ እኛ የነፍስ አባት ፈርደዋል፡፡ የፈረዱት ግን ቢጫ ልብሷን ለብሳ አይታው ጠይቃው እንድትሄድ ነው እንጂ ከገዳም እንድትወጣ አልፈቀዱም፡፡ ያንን ነው የፈረዱት፡፡
ጥያቄ፡- ክሊፑ ላይ ይቀጥላል ይላል?
አቤል፡- አዎ ይቀጥላል፡፡ በምን መልኩ እንደሚቀጥል አሁን ላይ መግለጽ ቢያስቸግርም ገዳም ገባች አሉ ይቀጥላል፡፡
ጥያቄ፡- ውሸት ላይ እንዴት ነህ?
አቤል፡- /ረዥም ሳቅ/ እኔ እንዲህ አላደርግም የሚል እኮ ሃጢያተኛ ነው፡፡ እና ማንም ሀጢያት አልሰራም ቢል እሱ ውሸታም ነው፡፡
ጥያቄ፡- ስለ ውሸት ማንሳቴ እንዳትዋሸኝ በማሰብ ነው፡፡ አልበምህ ላይ ‹‹አቤል ነዶ ነዶ ሆነ ባዶ›› የሚል ነገር አለ፡፡ በእውነታው ነደህ ነደህ ነው በጥበብም የመነዘርከው?
አቤል፡- ኧረ አልነደድኩም /ረዥም ሳቅ/ አቤል አልነደደም፡፡
ጥያቄ፡- ስለ ፍቅር ምን ትለናለህ?
አቤል፡- ፍቅር ከሁሉም በላይ አንደኛ ነው፡፡ በተለያየ ነገር በተለያየ መልኩ ልትዘፍን ትችላለህ፡፡ እንታረቅ ወይም ታረቁ ብሎ መዝፈንራሱ ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ ፍቅር ታላቅ ነገር ነው፡፡
ጥያቄ፡- አልበምህ የፍቅር ታላቅነትን ታጋሽነትን ይቅር ባይነትን ይሰብካል፡፡ አልተሳሳትኩም?
አቤል፡- ልክ ነህ፡፡ በአሸናፊነት ውስጥ በይቅር ባይነት ውስጥ ፍቅር አለ፡፡ ፍቅር ከሌለ አንድ ሰው ይቅር ማለት አይችልም ማለት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ይዘቱ ይለይ እንጂ ሁሉም ነገር ፍቅር ነው፡፡
ጥያቄ፡- ‹‹አልሰማም›› የሚለው ዘፈንህ ለእዚህ ጥሩ ማሳያ ናት፡፡
አቤል፡- ‹‹አልሰማም›› የሚለው ዘፈን የዘር ልዩነትን ጉዳይ ለማጥበብ የተሰራ ስራ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁንም አንዳንድ ቤተሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዘራቸው ውጪ ልጆቻቸው ትዳር እንዳይመሰርቱ የሚፈልጉ በእርግጥ አሁን አሁን እየቀረ ቢመጣም ይህን ነገር የበለጠ ለማጥበብ በማሰብ የተሰራ ስራ ነው፡፡ ከየትም ይሁን አቤል ከወደደ ወደደ ያገባል፡፡ ተው የሚሉኝን አልሰማም ነው የሚለው፡፡
ጥያቄ፡- ፍቅር መሀል ይቅርታ ምንድን ነው ትላለህ? ‹‹ኧረ ተዉኝ›› የሚለው ስራህ ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል?
አቤል፡- አዎ! ኧረ ተዉኝ የሚለው ስራ ቻይነትን ትዕግስትን የሚያሳይ ነው፡፡ ሰው ወዶ ብቻ አይደለም ሰው የሚያፈቅረው፡፡ ከነስህተቷ ተው አትሆንህም እየተባለ ሊወዳት ይችላል፡፡ ሰዎች ለምን አትተዋትም ሊሉት ይችላሉ፡፡ እሱ ግን ይወዳታል፡፡ ተዎኝ ከነጥፋቷ ልውደዳት በቃ ፍቅሯ ይግደለኝ ስሞት አንደኛውን አርፈዋለሁ የሚል ጭብጥ ነው ያለው፡፡
ጥያቄ፡- ለአይዲያዎችም ትጠበባለህ ልበል?
አቤል፡- በጣም፡፡ ማለት እኔ እንደማምነው ሙዚቃን ሆይ ሆይ በሚል ብቻ መጠቀም ሳይሆን ተሰጥኦው የተሰጠን ሰዎችን እንድናስታርቅ እንድናስተምርበትም ስለሆነ በምንሰራው ሜሎዲ ወይም ዜማ ጥሩ አይዲያ ተጠቅመን ሰዎችን ማስተማር አለብን የሚል እምነት ስላለኝ ነው ለአይዲያ የምጨነቀው፡፡
ጥያቄ፡- የዛሬ ስድስት ዓመት አንድ አልበም ሰማህ አልበሙን ወደድከው፡፡ ከዛም ዘፋኝ መሆን አለብኝ ብለህ ወሰንክ፡፡ ሆንክም፡፡ ስለዚህ ታወጋኝ?
አቤል፡- አዎ፡፡ የተመኘሁትን የፈለኩትን ነው የሆንኩት፡፡ ሰው ያልማል እግዚአብሔር ይፈጽማል፡፡ እንግዲህ ዓለምኩኝ፡፡ በማለሜ ውስጥ ጥረት ተፈጠረ፡፡ በጥረቴ ውስጥ ደግሞ ስኬት መጣ ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- በአጭር ጊዜ ሁለት አልበም ለዛውም የተወደዱ መልቀቅ ለጥበብ መፈጠርህን የሚያሳይ ነው፡፡ የተለየ ሚስጥርስ አለው?
አቤል፡- ምንም የተለየ ምስጢር የለውም፡፡ ጥረት ነው፡፡ ጥረት የሚመጣው ከፍላጎት ነው ብዬሃለሁ፡፡ ፍላጎት ይኑርህ ለማሳካት ትጥራለህ፡፡ ያ ደግሞ ስኬት ጫፍ ላይ ያደርስሃል፡፡ አሁን እንደውም ቀጣይ አልበሜን ለማውጣት ሁለት ዓመት የምቆይም አይመስለኝም /ሳቅ/
ጥያቄ፡- እኔ ጨርሻለሁ ስቱዲዮ ነው ችግሬ የምትል ትመስላለህ?
አቤል፡- እየሰራሁ ነው፡፡ ያው ሙዚቃ ህይወትህ እስከሆነ ድረስ አትቀመጥም፡፡ ሁሌም በስራ ላይ ነህ፡፡ ዝግጁ ሆነህ መጠበቅ አለብህ፡፡
ጥያቄ፡- የሌላ ድምጻዊያን ስራ ሰርተህ ታውቃለህ?
አቤል፡- እንደማንኛውም ሰው ናይት ክለብ ሰርቻለሁ፡፡ የሰዎችን ነው የምትጫወተው፡፡
ጥያቄ፡- አሁን አሁን አሻሽዬ በማለት ቆየት ያሉ ዘፈኖች እየቀረቡልን ነው፡፡ ትስማማበታለህ?
አቤል፡- አሻሽዬው ነው ተብሎ ሳያሻሽሉት ሲቀሩ ነው ጥሩ ያልሆነው፡፡ እንጂ አሻሽለውት ከሆነ ታሪኩን ለልጅ ልጅ አስተላለፉት ማለት ነው፡፡ ደግሞም በህጋዊ መንገድ መሆን አለበት፡፡ አሻሽለው ከሰሩት ችግር የለውም፡፡
ጥያቄ፡- አንዱ ኮሜን ልስራው ቢልህ ትፈቅዳለህ?
አቤል፡- አምስት አስር ዓመት ያልሞላውን ዘፈን መጫወት ጥሩ አይደለም፡፡ ግን ሃያ ሰላሳ ዓመት የሞላቸውን ቢሰሩ እደግፋለሁ፡፡ ግን ኮሜን ልስራ ቢለኝ እንጃ ልፈቅድም ላልፈቅድም እችላለሁ /ሳቅ/፡፡
ጥያቄ፡- እንደ ድሮ ብዙ የሙዚቃ ኮንሰርቶች የሉም፡፡ ድርቀቱ ከምን የመጣ ነው ትላለህ?
አቤል፡- ያው ፍላጎት ነው፡፡ ፍላጎት የሚመጣው ደግሞ ጥሩ ኑሮ ሲኖርህ ሲመችህ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሰው በእዛም በእዚህም ውጥረት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ህይወትን ለማሸነፍ ስለሚሮጥ ኮንሰርት ትዝ አይለውም፡፡
ጥያቄ፡- የአልበም መጥፋትስ?
አቤል፡- የአልበም እንደልብ ያለመውጣትም አለ፡፡ በነገራችን ላይ ኢንዱስትሪው ራሱ ሞቷል፡፡ ካለው ችግር አንጻር አሳታሚዎች የንግድ ዘርፋቸውን እየቀየሩ አሳታሚነትን እየተዉ ነው፡፡ ያሉትም ሙዚቃን መግዛት አይፈልጉም ኮፒ ራይት ያለመከበሩ የፈጠረው ችግር ነው፡፡
ጥያቄ፡- ሁሌም ብትዘፍንለት የማይሰለችህ ነገር?
አቤል፡- ሁሌም የማስበውና እመኘው የነበረ ነገር አለ፡፡ በቅርብ የወጣው የሃይሌ ሩት አልበም ላይ ሰው ከዝንጀሮ አይደለም የመጣው የሚል ስራ አለው፡፡ ያው ተገርሜ ማለት ነው፡፡ እና ስለ ሰው ብዘፍን ብሰራ አይሰለቸኝም፡፡ ሰው ከዝንጀሮ አይደለም የተፈጠረው የሚለው እኔም ውስጥ ነበር፡፡ ሃይሌ ሩትስ ዘፋኞች ሳይ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ጥያቄ፡- በሙዚቃችን ላይ ባይደረግ የምትለው ነገር አለ?
አቤል፡- ከእውነት የሸሹ ወደ ሃጢያት የሚመሩ ነገሮችን ከእኔ ጭምር ባንሰራ ደስ ይለኛል፡፡
ጥያቄ፡- በሌላ ሰው ቢመለስ ቢያምርም በእስካሁን ጉዞዬ በሀገራችን ሙዚቃ ላይ አሻራ አለኝ ትላለህ?
አቤል፡- ያው እነሱም በዛም በሰራህ ቁጥር አሻራ እየጣልክ ነው የመጣኸው፡፡ በተለይ ሌላን የማትመስል ከሆነ አንተ የራስህ ነገር ካለህ ያ ማንነትህ መለያህ ነውና ያ መለያህ ደግሞ አሻራ ያስጥልሃል፡፡ እና አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ጥርጥር የለውም፡፡
ጥያቄ፡- ከአልበም በኋላ ሩጫው ምንድን ነው?
አቤል፡- አልበም ማውጣት ብቻ አይደለም ስራው፡፡ በጣም የሚከብደው አውጥቶ ፕሮሞት አድርጎ ሰው ጆሮ እንዲደርስ ማድረግ ነው ከባዱ ስራ፡፡
ጥያቄ፡- ከህይወት ምን ተማርክ?
አቤል፡- ችግርን ተምሬያለሁ፡፡ ህይወት ውጣ ውረድ ናት፡፡ በውጣ ውረድ ውስጥ ትዕግስት ግድ እንደሆነ ተምሬያለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ስታዝን ምን ታደርጋለህ?
አቤል፡- ሳዝን የሚገርምህ እንባ አውጥቼ ማልቀስ አልችልም፡፡ በጣም ነው የምጎዳው፡፡ ካለቀስኩም ድምፄ አይሰማም፡፡
ጥያቄ፡- ባገኘው የምትለው ሰው አለ?
አቤል፡- በፊት በፊት የምመኛቸው ነበሩ፡፡ አሁን ግን ባገኘኋቸው የምላቸውን አግኝቼያቸዋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ሞት ለአቤል?
አቤል፡- ሞት መልካም ሰርቶ ማለፍና ክፉ ነገር ሰርቶ መሞት ይለያያል፡፡ ከነሀጢያቴ መሞትን አልፈልግም፡፡ ያኔ ሞት ለእኔ ሞት ነው፡፡ መልካም ሰርቼ መሞት ግን ለእኔ ህይወት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ለአንድ ሰው ትንሳኤ ስጥ ብትባል?
አቤል፡- ይሄ ጥያቄ ለሚገባው ይጠየቅልኝ /ሳቅ/ ምክንያቱም ትንሳኤ ከመስጠት የማይችልን ሰው ትንሳኤ ብትሰጥ ማለቱ ራሱ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም /ሳቅ/
ጥያቄ፡- በምድር ላይ ባይኖር የምትለው ነገር?
አቤል፡- ያው ሁላችንም የምንጠላው ረሃብ ባይኖር ደስ ይለኛል፡፡ እንደረሃብ ያለ መጥፎ ነገር የለም፡፡
ጥያቄ፡- ስቱዲዮ እንደከፈትክ ነገርከን፡፡ አውጋን እስኪ?
አቤል፡- ስቱዲዮ ከፍቻለሁ፡፡ ሁለት አይነት ስራ ነው የምንሰራው፡፡ የሙዚቃ ሰራና ፊልምም ውስጥ የመግባት ሀሳቡ አለን፡፡ ፊልምም ሙዚቃንም አጣጥመን በእዚህ ዓመት ወይም በሚቀጥለው ዓመት አንድ ነገር እንሰራለን እላለሁ፡፡
ጥያቄ፡- የድምጻዊያን ችግር ብለህ ነው የከፍትከው ወይስ አዋጪ ነው በሚል?
አቤል፡- ጥበብ ውስጥ እስካለህ ድረስ ከጥበብ መሸሽ ስለማትችል ነው፡፡ ሁለተኛ እኔም ለመጠቀም ሌላውንም ለመጥቀም ነው፡፡ ምክንያቱም እኔም ዜማና ግጥም ስለምሰራ እኔም ዜማና ግጥም ስለምሰራ ጓደኞቼንም ለማሰራት አንተ አንድ እርምጃ ከተራመድክ ጓደኛህም እንዲራመድ ከማሰብ ነው፡፡
ጥያቄ፡- እናጠናቅ?
አቤል፡- የኢትዮጵያ ህዝብን አመሰግናለሁ፡፡ በልልኝ፡፡
ጥያቄ፡- እግዜር ያክብርልኝ፡፡S

ተጨማሪ ያንብቡ:  “በጨርቆስ ዙሪያ የሚነገሩ ቀልዶች እዚያው ጨርቆስ የሚፈጠሩ ናቸው” አርቲስት መኮንን ላዕከ
Share