
ማንነቱ ባልታወቀ ወይም በራሱ በዘሃበሻ የኢዲቶሪያል ቦርድ የመለሰ ዜናዊ አገዛዝ የልማታዊ መንግስት ነበር፣ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ምድር የሚታየው የኢኮኖሚ ቀውስና የድህነት መስፋፋት የአቢይ አህመድ አገዛዝ የኒዎ-ሊበራሊዝምን “የኢኮኖሚ ፖሊሲ” በመከተሉ ነው ተብሎ በተከታታይ ለተጻፈው የተሰጠ መልስ!!
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ነሐሴ 19፣ 2017(Augsut 25, 2025)
መግቢያ
በአቶ መለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው፣ ቀጥሎ ደግሞ በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኛ፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ በአጠቃላይ ሲታይ በእነዚህ በተለያዩ የአገራችን መሪዎች በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውና የሚሆነው “ የኢኮኖሚ ፖሊሲ” ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚባለው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት((IMF) ተጽፎ የመጣው ነው። በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና፣ በአጠቃላይም የዓለም ኮሙኒቲው የሚባለውን ስም የያዘው፣ የየአገሮችን ዕድል ለእሱ በሚስማማ መልክ በሚያከረባብተው ዕምነት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የማክሮ-ኢኮኖሚ መዛባት ስላለባቸው(Macro-economic Imbalances) ንጹህ በንጹህ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ እንዲሸጋገሩ ከተፈለገ የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት መሻሻል አለበት። የመንግስትም ጣልቃ ገብነት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ አልከበት በማለትና በጊዜው በመለሰ ዜናዊ በሚመራው የኢህአዴግ ግፊት በማድረግ የተቋም ማስተካከያ(Structural Adjeustment Programs) የሚባለውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያድረግ አስገደዱት። በዚህ ወደ አንድ ትውልድ የሚጠጋ የአገዛዝ ዘመን በአንድ ወቅት በአቶ በረከት ሰምኦን አገላለፅ „ኢህአዴግ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈና፣ ኢኮኖሚውም በአስተማማኝ መሰረት“ ላይ እንደቆመው አብስረውልን ነበር። እንዳሉት ከሆነና በዚያን ወቅት መንግስታቸውም ሊያሳምነን እንደሞከረው ይህ “በፀና መሰረት ላይ የቆመው ኢኮኖሚ” አገዛዛቸው መንግስት በሚከተለው „ለልማት አትኩሮ በሰጠው የኢኮኖሚ ፖሊሲ“ አማካይነት ነው። በሌላ አነጋገር ይሉን የነበረው፣ የኢህአዴግ አገዛዝ 27 ዐመት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲያደርግ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሌላ ሳይሆን ልማታዊ የመንግስት(Developmental State) ፖሊሲን ዋናው መመሪያው በማድረግ ነበር።
ኢህአዴግ ስልጣን ከጨበጠ ወዲህ በተለይም በመጀመሪዎቹ አስራ አምስት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ በአፍሪካ ውስጥ ተወዳዳሪነት የሌለው የኢኮኖሚ ዕድገት ታይቷል እየተባለ ሲነገረን ከርሟል። እንደ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የመሳሰሉት ይህንን የእነ አቶ መለስን “የኢኮኖሚ ዕድገት” ትክክል ለመሆኑ ያረጋግጣሉ። እዚህ ባለንበት አገርም ስለአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲወራ ፈረንጆች ሊያሳምኑን ይሞክሩት የነበረው፣ አንድ ሰሞን ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች በአማካይ ወደ ስድስት በመቶ የሚጠጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳሳዩና፣ ይህንን ዐይነቱን ዕድገት የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ሊደርሱበት እንደማይችሉና የሚጓጉትም እንደሆነ አብስረውልን ነበር። እንደዚህ ዐይነቱን “የመረቃ ዕድገት” ካስመዘገቡት አገሮች ውስጥ አንዷ በጊዜው በኢህአዴግ አገዛዝ የምትመራው ኢትዮጵያችን እንደነበረች ተነግሮናል። አንድ ሰሞን ደግሞ ዘ ሰን ተብሎ የሚጠራው የእንግሊዝ ጋዜጣ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ስትወዳደር የኢኮኖሚ ዕድገቷ በአስር እጥፍ እንደሚበልጥ አብስሮልናል። እነዚህን የመሳሰሉት አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ መሰረትና ይዘት የሌላቸው ድጋፍና አገላለጾች በአንድ በኩል እንደነ አቶ መለስ ለመሳሰሉት አገዛዝ ቀጥተኛ ድጋፍና የስልጣን ዕውቅና ሲሰጡ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን ያህልም ስለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለሰውልጅ ስልጣኔ ጠለቅ ብሎ ለማየት ለማይችልም ሆነ ለማወቅ ለማይፈልግ ማደናገሩ የማይቀር ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንዳንድ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ወይም ሌላ ከውጭ አገር ከብዙ ዐመታት ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው፣ በተለይም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ትላልቅ ፎቆችና መንገዱን ያጣበቡ ትላልቅና አዳዲስ መኪናዎችን ሲያዩ ሲነገራቸው የከረመው ዕውነት እንደሆነ ለማመን ጥቂት ደቂቃም አይፈጅባቸውም። ውይ አገራችን! እንዴት አድጋለች ማለታቸው አይቀርም።
ወደ ኢህአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ይዘትና ፍልስፍና ስንመጣ እነ አቶ መለስ በጊዜው ተግባራዊ ሲያደርጉት የከረሙት ፖሊሲ ልማታዊ የመንግስት ፖሊስን መሰረት ያደረገ የተሃድሶ የአገር ግንባታ ክንዋኔ እንጂ በኒዎ-ሊበራሊዝም መሰረተ-ሃሳብ ላይ የተመረኮዘ አይደለም እያሉን ነበር። እንዲያውም አልፈው ተርፈው ኒዎ-ሊበራሊዝም ምን እንደሆን ለማያውቀው ህዝባችን በጊዜው ተቃዋሚው ኃይሎች የኒዎ-ሊበራሊዝምን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገሉ ናቸው እያሉ ማደናገር ጀምረው እንደነበርና፣ ዛሬም እንደሚያደርጉ የታወቀ ጉዳይ ነው። ይሁንና ከአንድ ሁለቴ በስተቀር የኒዎ-ሊበራሊዚምን የኢኮኖሚ ፍልስፍና በሚመለከትና፣ የኢህአዴግ አገዛዝም ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ተግባራዊ ሲያደርግ የነበረውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንድ በአንድ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማነፃፀር ሰፊ ትንተናና ትምህርት ከተቃዋሚው ኃይል የተሰጠ ምንም ነገር አልነበረም። ስለሆነም „የሌባ ዐይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ“ እንደሚሉት አነጋገር በጊዜው የአቶ መለስ አገዛዝ ማንም የሚጋፈጠኝ የለም፣ የእኔን ፖሊሲ ትክክለኛነት የሚያረጋግጡልኝ ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖች፣ እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የመሳሰሉት አሉ በማለት በስልጣን ዘመኑ የማያስፈልግ ውዥንብር ይነዛ ነበር። በዚያው ሰሞን ደግሞ “የፌዴራሉ መንግስት” ስለ ድህነት ጉዳይ እንዲጠና በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፣ በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ያለው ድህነት ከመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ዐመታት ጋር ሲወዳደር ከ38.7 በመቶ ወደ 29.6 በመቶ ቀንሷል በማለት መዝናናት ጀምሮ ነበር። ይሁንና በጊዜው ሌሎች ጥናቶች እንደሚያረጋግጡትና የተጨባጩም ሁኔታ ያሳየን የነበረው፣ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሀብታምና በደሀ መሀከል ከፍተኛ የገቢ ልዩነት እንደነበር ነው። በተጨማሪም ከቆሻሻ ቦታ እየለቀመ የሚበላው ከሰማንያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ በአዲስ አበባ ብቻ እንደሚገኝ የታወቀ ጉዳይ ነበር። በጊዜው በዓለም ባንክ የወጣው የሚሌኒዩም 2015 የኢኮኖሚ ግቦች “በአብዛኛው አገሮች ተግባራዊ መሆን” የሚያበስረው ሪፖርት እንደ አቶ መለስ የመሳሰሉትን አገዛዝ ሊያዝናናቸውም ቢችልም በግልጽ የሚታየውን ነገር ማንም ሊክደው አይችልም። በተጨማሪም የእነ ፕሮፌሰር ስቲግሊትዝ ግልጽ ድጋፍና በጊዜው ታትሞ በወጣው መጽሀፋቸው ውስጥ „Good Growth and Governance in Africa„ በሚለው እነ አቶ መለስ ያቀረቡት አስተዋጽዖ “States and Markets: Neoliberal Limitations and the Case for a Developmental State“ በአንድ በኩል ብዙዎቻችንን ሊያሳስትና ሊያዘናጋ ሲችል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከእነ ፕሮፌሰር ስቲግሊትዝ የሚሰጠውን ግልጽ ድጋፍ በይፋ ለመዋጋት ያስቸግር ነበር። የሚያስቸግረው ድጋፋቸውን ፉርሽ ለማድረግ ሳይሆን፣ የኖቭል ዋጋ ተሸላሚ ስለሆኑ የእሳቸውን ለአቶ መለስ የሰጡትን ድጋፍ ውድቅ ለማድረግ ቢቻልም እንኳ በቀላሉ አመኔታ ለማግኘት ሰለማይቻልና “አንተ ደግሞ ማን ሆነህ ነው እኚህን የመሰሉ ታላቅ የኢኮኖሚ ሊቅ የምትጋፈጣቸው” የሚሉ አጉል ዘመቻ ስለሚያካሄዱ ነው። በተለይም በኢኮኖሚ ቲዎሪ የፍልስፍና ትግል ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች እንዳሉ ለማያውቁና፣ ከፍተኛ ትግልም ተካሂዶ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንደተገነባ ለማይገነዘቡት እነ ፕሮፌሰር ስቲግሊትዝ ለአቶ መለስ የሚሰጡት ድጋፍ ሊያሳስታቸው እንደሚችል በቀላሉ መረዳት ይቻል ነበር። እዚህ ላይ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ፕሮፌሰር ስቲግሊትዝ ለእነ አቶ መለስ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ድጋፍ ቢሰጡም በጊዜው አሉ ከሚባሉ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚስቶች አንዱ ሲሆኑ፣ በተለይም በሶሻል ፎረም ላይ እየተገኙ ስለሶስተኛው ዓለም አገሮች ኢኮኖሚ ሁኔታና ስለ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ መዛባት የሚሰጡት ትንተናና ድጋፍ የሚያስመስግናቸው ነው። ይሁንና ግን የሚሰጡት ትንተና የተወሰነ ሎጂክን በመከተል ሲሆን፣ ከእሳቸው አቀራረብ ጋር የማይስማሙም እንዳሉ ግልጽ መሆን አለበት። በተለይም በየአገሮች ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ከውጭው ዓለም ጋር ስላለው መቆላለፍና፣ ይህም በራሱ ለዕድገት እንቅፋት መሆኑን በቲዎሪያቸው ውስጥ ለማጠቃለል አይጥሩም ወይም አይፈልጉም። ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከፖለቲካዊ ሁኔታ አስቸጋሪነትና አመችነት እንዲሁም ከጥገና ለውጥ አስፈላጊነት ጋር ለማያያዝ አይቃጡም። ያም ሆኖ የተወሰነ ሃሳባቸውን ብንጋራምና ለሶስተኛው ዓለም አግሮች የነበራቸውንና ያላቸውን ወገናዊነት ብንቀበልም ለምን ግን ከእንደዚህ ዐይነቱ ግራ ከሚያጋባ አመፀኛ መንግስት ጋር ቆመው ግራ እንደሚያጋቡን በጊዜው ግልጽ አልነበረም።
ወደ ልማታዊ መንግስትና በጊዜው በፀና መሰረት ላይ ስለቆመው ኢኮኖሚያችን ጋ ስንመጣ አቶ መለስም ሆነ አቶ በረከት ሰምዖን ፅንሰ-ሃሳቦችን ከመሰንዘራቸው በስተቀር ፍልስፍናቸው ምን እንደሆነና፣ በፀና መሰረት ላይ የቆመው ኢኮኖሚያቸው ምን ይመስል እንደነበር በጊዜው በግልጽ አላስረዱንም። ስለዚህም ይህንን በሰፊው የመተንተኑና አንባቢውን የማስረዳቱ ጉዳይ እኛ ለተከበረችና፣ በሳይንስና በቴኮኖሎጂ እንዲሁም ባሸበረቁ ከተማዎች ማበብ ስላለባት ኢትዮጵያ ለምንታገለው ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህም እነዚህን ሽንጣቸውን ገትረው ዐይን ያወጣ ውሽት ይነዙ የነበሩትንና አሁንም ያሉትን አፈቀላጤዎቻቸውንና የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ማጋለጥ ያስፈልጋል።
ግልጽ መሆን ያለባቸው ፅንሰ-ሃሳቦች- የልማታዊ
መንግስትና የተሃድሶ ትርጉም!
በመጀመሪያ ደረጃ የልማት ተቃራኒው ጥፋት ነው። ማውደም ማለት ነው። ስነ ስርዓት ያላቸውን ነገሮች ማዘበራረቅ ወይም እንዳልነበሩ ማድረግ ጥፋት ይባላል። ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸውንና ዕውነተኛ ሀብት ለመፍጠር የማያስቸሉና፣ እንዲሁም የመንፈስ ተሃድሶ የማያመጡ የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደጥፋት ይቆጠራል፤ ወይም እንደምናየው ውጤታቸው ጥፋት ነው። ጥፋት በተለያዩ መልኮች ሊገለጽ የሚችልና አብዛኛውን ጊዜም ከአዕምሮ መበላሸት ጋር ሊያያዝ የሚችል አጉል ድርጊት ሲሆን፣ በሌላ ወገንም ከባህል ተሃድሶ ጉድለት ወይንም ጭንቅላትን በጥሩ ዕውቀት ካለመግራት የተነሳ አንዳንድ አመፀኛ ሰዎች በሌላው ላይ ወይም በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንደጥፋት ይቆጠራል። በተጨማሪም ብዙም ሳያወጡ ሳያወርዱ ዛፎችን እንዳለ ማውደም፣ ስለአአካባቢ ሁኔታ በቂ ጥናትና ግንዛቤ ሳይኖር የጥሬ-ሀብት ለማውጣት ሲባል መሬትን መቦደስና መሬት ውስጥ ያለውም ውሃ እንዲመረዝ ማድረግ እንደጥፋት የሚቆጠር ነው። አንድ ግለሰብም ሆነ በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ አርቆ ከማሰብ ጉድለት የተነሳ በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሰው መዘበራረቅ ወይም የአካባቢ መዛባት እንደጥፋት ሊቆጠር ይችላል። ተፈጥሮም ሲያገረሽባት የመሬት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉትን ውርዥብኝ በመላክ አንድን ከተማ ድምጥማቱን ታጠፋለች። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ከ20 ዓመት በፊት በጃፓን የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥና ሱናሚ ተፈጥሮ ሲያገረሽባት የምታደርገው ነገር ነው ልንለው እንችላለን። በሌላ በኩልም “ጤናማ ጥፋት” ይኖራል። ይህም ማለት ለምሳሌ አንድ ህዝብ ከተዝረከረከ ኑሮ ስነ ስርዓት ያለው ኑሮ ለመመስረት ሲፈልግ ከተማዎችን ይቆረቁራል። በዚህን ጊዜ የግዴታ ደንን በመመንጠር እንደ ማሰብ ኃይሉ ውበት ያለው ከተማ ወይም በስርዓት ያልታቀደ ከተማ ይሰራል። ይሁንና ግን ዛፎችን በመቁረጥና መሬትን በመቆፈር የተፈጥሮን ህግ ያናጋውን ያህል፣ በተፈጥሮ ውስጥ በሚከሰቱ አደጋዎች እንዳይረበሽና አካባቢውም እንዳይናጋ ከፈለገ ከተማን ለመገንባት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች በሳይንስ የተጠኑ መሆን አለባቸው።
ከዚህ ስንነሳ ዕድገት(Development) በብዙ ቅራኔዎች የተዋጠ ነው ማለት ነው። የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ስላለውና በቁጥርም እየጨመረ ስለሚሄድ የግዴታ አካባቢውን ማልማት አለበት። አካባቢውን ለማልማት ደግሞ በማሰብ ኃይሉ በየጊዜው የተሻሉ የማምረቻ መሳሪያዎች(Instruments of Labour) መፍጠርና መስራት አለበት። በዚህ መሰረት በአንድ በኩል ስራውን ሲያቃልል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ምርታማነትን ይጨምራል። በተጨማሪም በተፈጥሮ ላይ የተወሰነ የመቆጣጠር ኃይልን ያገኛል። ዕድገት(Development) እንደ ሰዎች ወይም አገዛዞች ንቃተ ህሊና የተለያዩ መልኮች የሚኖሩትና አቅጣቻዎችን የሚይዝ ነው። እንደ የምሁራን ዕውቀት አቀሳሰምና የርዕዮተ-ዓለም ዝንባሌ ዕድገት የተለያየ ትርጉም ይሰጠዋል። በአውሮፓ ምድር ውስጥ በመርካንትሊዝም አማካይነት እንደ እንግሊዝ ያሉ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ከገነቡና ካጠናከሩ በኋላ ሌላው አገር የእነሱን ፈለግ እንዳይከተል ሲሉ በመርከንታሊዝም ላይ ዘመቻ በመክፈት የነፃ ንግድን((Free Trade) አርማ ማውለብለና መስበክ ጀመሩ። ስለሆነም ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ጀምሮ ዕድገት የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ የግዴታ በርዕዮተ-ዓለም ሽፋን በመሸፈን የበለጠ አወዛጋቢና ውዥንብር ነዢ የሆነ የመጣ ፅንሰ-ሃሳብ ለመሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በተለይም ካፒታሊዝም የበላይነትን ከተቀዳጀ ከአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን አንስቶ፣ ይበልጥ ደግሞ በሃያኛው ክፍለ-ዘመን ለሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብሎ የወጣው የኢኮኖሚ ዕድገት ትምህርት የዕድገት ፅንሰ-ሃስብ እንዲጣመም በማድረግ የሰው ልጅ እንዲሰቃይና ተፈጥሮም እንዲበዘበዝ አድርጓል፤ እያደረገም ነው።
ይሁንና ግን የዕድገትን መሰረተ-ሃሳብ ወደ ኋላ ተመልሰን በጥሞና ስንመረምረው እንደዛሬው ዐይነት በጥፋት ላይ ያተኮረና የሰውን ልጅ ወደ ባርነት የሚገፈትር፣ ወይም አንዱን የበላይ ሌላውን ደግሞ ተገዢ የሚያደርግ ፅንሰ-ሃሳብ አልነበረም። ዕድገት ሲባል የተስተካከለና የተሟላ ነበር። በተለይም በነሶክራተስ የተደረሰው ፍልስፍና እንደሚያሰተምረን በአጠቃላይ በተፈጥሮ ውስጥ ተፈጥሮን የሚገዛት የኮስሞስ ኃይል(Cosmic Order) አለ። በዚህ ህግ መሰረት ተፈጥሮ ራሷን በማንቀሳቀስና በማደስ፣ እንዲሁም አዳዲስ ዕፅዋቶችንና ኃይሎችን በመፍጠር በዘለዓለማዊ ተንቀሳቃሽኒነት የምትገኝ ነች። ስለዚህም ይላል ላይብኒዝ “እግዚአብሄር ከፕላኔቶች ሁሉ ለሰው ልጅ ተስማሚው የሆነቸውን ሁሉን ነገር የምታሟላውን ፍጥረ-ነገሮች ያየዝች መሬትን ፈጥሮልናል”። በመሆኑም የሰው ልጅ የኮስሞስንና የተፈጥሮን ህግ በመረዳት ለሱ የሚሆነውን የዕድገት ፈለግ መቀየስ አለበት። ሰልሆነም ዕድገት ሲባል በአንድ ቦታ ላይ የሚካሄድ፣ እዚያ ቦታ ብቻ የሚቀርና ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ኑሮ የሚያናጋ አይደለም። ዕድገት ሲባል በይዘቱ ሁለንታዊ ሲሆን ከታች ወደ ላይ ቀሰ በቀስ በሁሉም አቅጣጫ ውበት ባለው መልክ እያደገና እየሰፋ የሚሄድ ነው። በተጨማሪም ዕድገት ሲባል አንድ ወጥ አይደለም። በተፈጥሮ ውስጥ አንድ ዐይነት ዛፍ ወይም አንድ ዐይነት አበባ እንደሌለ ሁሉ፣- ምክንያቱም ተፈጥሮ ሚዛናዊነት የሚኖራት የተለያዩ ነገሮች ተቻችለው ሲኖሩና አንድ ወጥ ነገር ተፈጥሮን ስለሚቀናቀን ነው- በህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥም ዕድገት ሲባል ሁሉንም ነገሮች ያካተተ ነው። ይህም ማለት ፓለቲካዊ ወይም ኢንስቲቱሽናዊ፣ ባህላዊና ህብረተሰብአዊ ወይም ማሀበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ለወጦችን ያካተተ ነው። እነዚህ አንድ ላይ ተጣምረው የሚሂዱ ናቸው። አንደኛው ከሌላው ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም። ልክ አንድ ህጻን ልጅ የተሟላ አሰተሳሰብና ዕድገት እንዲኖረው ከተፈለገ ከተወለደ ጀምሮ ለአቅመ-አዳም እስኪደርስ ድረስ ከፈተኛ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ህብረተሰብአዊ ዕድገትም እንደዚሁ ከተቻ ወደላይ በጥንቃቄና በከፍተኛ ዕውቀትና ዕውቅና የሚካሄድ መሆን አለበት። ዕውነተኛ ዕድገት ከላይ ወደታች የሚጫን አይደለም፤ ወይም የጥቂት ሰዎችን ፈላጎት ለማሟላትና እነሱ በአቀዱት ዕቅድ የሚካሄድ አይደለም። ዕውነተኛ ዕድገት ከፍተኛ ዕውቀት ባላቸው ስዎች ቢነደፍም፣ የመጨረሻ መጨረሻ ግን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ የሚያሳትፍና የዕድገትንም ትርጉም እንዲረዳው የሚያደርግ መመሪያ መሆን አለበት። ለምን እንደሚኖር፣ ምንስ መሰራት እንዳለበትና ወዴትስ ማምራት እንዳለበት እንዲገነዘበው የሚያደርግ መሆን አለበት።
ሰለዚህም ነው ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ በኋላም እስከዛሬይቷ ቱርክ ድረሰ የተስፋፋውን የዕድገት ፈለግ ስንመለከትና፣ በተለይም ከአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተካሄደውን የመጀመሪያውን የሬናሳንስ(Early Renaissans Period) እንቅስቃሴና የከተማ ግንባታ፣ እንዲሁም በእነዳንቴ የተደረሰውን የአምላኮች ኮሜዲስ ስናነብ የምንረዳው ዕውነተኛ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው የሰው ልጅ ከጨለማና ከጥፋት አስተሳሰቡ የተላቀቀና ቀናውን መንገድ የተከተለ እንደሆን ብቻ ነው። ስለዚህም በፕሮፌሰር ኤሪክ ራይነርት ዕምነት ዕውነተኛ ዕድገት የሰውን አዕምሮ በቁጥር ውስጥ የሚያስገባ መሆን አለበት። ምክንያቱም ጥፋትም ሆነ ዕድገት የሚባለው ነገር ባለማሰብም ሆነ በማሰብ ኃይል እየተረዱ ተግባራዊ የሚሆን በመሆኑ የግዴታ በመጀመሪያ ደረጃ የመንፈስ ተሃድሶ ያስፈልጋል ማለት ነው።
ከዚህ ስንነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ በእነ እቶ መለስ ይለፈፍ የነበረው የተሃድሶ ሂደት በጭንቅላቱ የቁመ ነበር ማለት ይቻላል። ተሃድሶ ማለት ሌላ ሳይሆን ሬናሳንስ ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ትክክለኛና ሳይንሳዊ ዕውቀትን መልሶ ማግኘት ማለት ነው። ፅንስ-ሃሳቡም የግዴታ ከግሪክ ፍልስፍናና ሳይንስ እንዲሁም በልዩ ልዩ ነገሮች የሚገለጸው ስልጣኔ፣ ማለትም በድራማ፣ በፖለቲካል ዲስኮርስ፣ በአርክቴክቸር፣ በስክለፕቸርና በተለያዩ ጥንታዊ ስዕሎች … ወዘተ የሚገለጸውን መሰረተ ያደረገ ነው። ዋናው መሰረተ-ሃሳቡና ዐላማውም የሰውን ልጅ ከእግዚአብሄር ጋር በማቀራረብና የመንፈስን የበላይነት እንዲቀዳጅ በማድረግና፣ በተጨማሪም ሙሉ በሙሉ ግለሰብአዊ ነፃነት እንዲቀዳጅ በማድረግ የሚኖርባትን ምድር እንደ ኮስሞስ ስርዓት ውበት እንዲኖራት እንዲያደረግ ነው። ከአስራሶስተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የግሪክ ሊትሬቸር ወደ ላቲን ሲተረጎም ርብርቦሽ የተተደረገበት የግሪኩን ስልጣኔ ዋና ሃሳብ ለመረዳት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነዳንቴ በቀደዱት ፈለግ አንድ ትውልድ በአዲስ አስተሳሰብ በመታናጽ ለስልጣኔ ይነሳል። ራፋኤል፣ ዳቪንቺ፣ ሚካኤል አንጀሎ፣ ፔትራርካና ሌሎችም በሺህ የሚቆጠሩ በአንድ ጊዜ ከሰማይ እግዚአብሄር እንደወረወራቸው ለስልጣኔ ታጥቆ በመነሳት ተዓምር ይሰራሉ። የኢጣሊያንንም ህዝብ ከጨለማ ዘመን በማላቀቅ የስልጣኔውን መስረት ጥለዋል።የኢጣሊያንም ህዝብ ማንነቱን እንዲያገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይህ ዐይነቱ በጣሊያን የተከሰተው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮችም በመተላለፍ ምሁሩን ማዳረስ ጀመረ። ሁሉም በዚህ በተቀደሰ ዕውነተኛ የዕድገት ፈለግ መሳከር ጀመረ። ተፈጥሮን በመቃኘት ውብ ውብ ነገሮችን መስራት ጀመረ። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ተሃድሶ ማለት ሁለንታዊና ከጭንቅላት በመነሳት ወደታቸ በመውረድ ተፈጥሮን በእዲስ መልክ የሚቀርጽ ነው። ተሃድሶ ማለት ተፈጥሮን እንዲያው ተብዝባዥ የሚያደርጋት ወይንም ነፍስ እንደሌላት የሚቆጥር እንቅስቃሴ አይደለም። ተፈጥሮም እንደሰው ልጅና እንሳሳት ውስጣዊ ህይወት ያላትና፣ በውስጣዊ የመንቀሳቅስ ኃይሏም ለህይወታችን የሚሆኑ ነገሮችንም የምትለግሰን ስለሆነ በዕድገት ስም የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በሙሉ የተፈጥሮን ህግ የሚጥሱ መሆን የለባቸውም።
ችግሩ ካፒታሊዝም የበላይነትን ሲቀዳጅ ይህንን የተሃድሶንና የዕድገትን ትርጉም በአፍጢሙ በመድፋት ተፈጥሮንና ስውን ተብዝባዥ ማድረግ ጀመረ። ሁሉም ነገር ለትርፍ የሚሰራና፣ ማንኛውም ነገር ከዋጋና ከጥቅም(Cost-Benefit)አንፃር የሚተመን መሆን ጀመረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዕድገት ሲባል ከተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ግኑኝነት ጋር የተያያዘ ነው። የግዴታ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነትን የተቀዳጀውን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው። የማንኛውም ሰው አስተሳሰብ በዚህ በየጊዜው እየዳበረ ግን ደግሞ የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል እያቀጨጨው ከሚሄድ የተንዛዛ የፍጆታ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂም ዕድገት ከዚህ የካፒታሊዝም ዕድገት ሎጂክ ጋር የተያያዙ እንጂ በምንም ዐይነት የሰውን ልጅ ስራም ሆነ ኑሮ ለማቃላል እየተባሉ የተፈጠሩ አይደሉም። ካፒታሊስቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሚፈልጉት ከፍተኛና ተከታታይ ትርፍ ያመጣልናል ብለው የገመቱ እንደሆን ብቻ ነው። ለምሳሌ ኃይልን በማመንጨት ከሰድሳና ከሰባ ዐመታት በፊት ለማንኛውም ቤተሰብ የሚዳረስ ከፀሀይ የሚፈልቅ ኃይል ዳብሯል። ይህ ግኝት ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የተቀበረ ነበር። በየጊዜው በሚደርሰው የኒውክላር ኃይል አደጋና፣ በተለይም ደግሞ የራዲዮአክቲቭ ቆሻሻዎችን መጣያ ቦታ አስቸጋሪ ስለሆነና ከህዝብም ከፍተኛ ግፊት በመፈጠሩ ካፒታሊስቶች ስትራቴጂያቸውን እንዲቀይሩ ተገደዋል። እንደዚሁም አሁን ለመኪና ቤንዚንና ዲዝልን ከመጠቀም ይልቅ ወደ ኤልክትሮ ባትሪዎች ለመሸጋገር በማምራት ላይ ናቸው። ባጭሩ ከአራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ከገዢዎች አስተሳሰብ ውጭና የእነሱን ጥቅም ከሚያንፀባርቅ የዕድገት ፈለግ ሌላ ዕድገት የለም። በሃምሳኛው ዐመትም ሆነ ዛሬ ስለዕድገት ሲወራ ከካፒታሊዝምና ከግሎባል የካፒታሊዝም እንቅስቃሴ ሎጂክ ጋር የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ወደሶስተኛው ዓለም አገሮች ስንመጣ፣ በተለይም አሜሪካን የበላይነትን ከተቀዳጀ ወዲህ በአንዳንድ የኢምፕሬሲስት አስተሳሰብ ባላቸው በአሜሪካን ምሁሮች ለሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብሎ የተዘጋጀ ዘመናዊነት(Modernization) የሚባል የዕድገት ፈለግ አለ። በዚህ ዙሪያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰፋ ያለ ክርክር ተካሂዷል። ኒዎ-ማርክሲስት በሚባሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፒታሊዝም አማካይነት የተካሄደውን የተዛባ ዕድገትና ያልተስተካከለ የንግድ ግኑኝነት እንቅስቃሴ በመቃውም ሰፋ ያለና አመርቂ ጥናት አካሂደዋል። እንደዚሁም በመልቲ ናሽናል ኩባንያዎች የሚካሄደውን የተቆጠበ በሶስተኛው ዓለም አገሮች ርካሽ የሰውን ጉልብት ለመጠቀምም ሆነ ለመበዝበዝ ሲባል የሚተከሉትን ኢንዱስትሪዎች አስታኮ ሰፋ ያለ ጥናትና ክርክር ተካሂዷል። በሌላ አነጋገር፣ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ፍጹም የበላይነትን የተቀዳጀው ጎሎባል ካፒታሊዝም በየአገሮች ውስጥ እየገባ አላዋቂ መሪዎችንና ምሁራንን ተገን በማድረግ ተግባራዊ ያደረገው መጠነኛ የኢንዱስትሪ ተከላዎች በየአገሮች ውስጥ ከፍተኛ መዛባትንና የሀብት መባከንን አስከትሏል። በሃምሳኛው ክፍለ-ዘመን የምትክ-ኢንዱስትሪ(Import-Substitution-Industrialization) እየተባለ በአፍሪካና በማዕከለኛውና በላቲና አሜሪካ አገሮች የተካሄደው ዕድገት የሚመስል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምን አስፋፍቷል። በዚያው መጠንም በአንድ በኩል የመንግስታትን የመጨቆኛ መሳሪያዎች ሲያጠናክር፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሀብት በጥቂት ስዎች እጅ እንዲከማች በማድረግ ወደ ውስጥ ከፈተኛ የሆነ የዕድገት መዛባት እንዲፈጠር አድርጓል። የከተማዎች ካለዕቅድ መሰራትና፣ ስራ ለመፈለግ ሲል ወደ ከተማዎች በመፈለስ ጥቂት ከተማዎችን ማጣበብ የጀመረውና በአልባሌ ስራዎች የተሰማራው የዚህ ዐይነቱ የተሳሳተ የግሎባል ካፒታሊዝም የዕድገት ሎጂክ እንቅስቃሴ ውጤት ነው። ይህ ዐይነቱ የዕድገት ፈለግ ውጤት አላመጣም ከተባለ ወዲህ በአፍሪካ ምድር ውስጥ መሰረታዊ ፍላጎትን(Basic Needs) ከማሟላት ከሚለው መመሪያ ጀምሮ በአረንጓዴው አብዮት(Green Revolution)ውስጥ በማለፍና እስከመዋቅር ማስተካከያ(Structural Adjustment Programs)ድረስ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የዕድገት ፈለግ እንደየጊዜው ለግሎባል ካፒታሊዝም በሚስማማ መልክ በመቀየስ ምን ማድረግና እንዴትስ መራመድ እንዳለባቸው ተወስኗል። ይህም ማለት እያንዳንዱ የሶስተኛው ዓለም አገር በራሱ ተነሳሽነትና ለራሱ ፍላጎት የሚሆነውን የዕድገት ፈለግ እንዳይቀይስ ከመጀመሪያውኑ በመታገድ መንገዱ ሁሉ እንዲጨልምበት ተደርጓል። በተለይም በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በዘጠናኛው ዓመት የተስፋፋው ግሎባላይዜሽን የሚባለው አዳዲስ ተዋንያንን በመፍጠር “ኢንቬስተሮች” የሚባሉት እንደ አሸን በመፍለቅ የአፍሪካን የጥሬ ሀብት ወደ መቆጣጠር አመርተዋል። ሆቴል ቤቶችና ትላልቅ አፓርትሜንቶችን መስራቱ ከዚህ ዐይነቱ የግሎባል ካፒታሊዝም እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ እንደገና አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም በማስፋፋት ሀብት በከፍተኛ ደረጃ አንዲባክንና ሰፊው ህዝብም በኑሮ ውድነት እንዲሰቃይ የተደረገብትን ሁኔታ እንመለከታለን። አገራችንም የዚህ ዐይነቱ ሰለባና ህዝቧም በከፈተኛ ደረጃ የሚፈናቀሉባት አገርና በአዲሱ የገዢ መደብ ሰውነቷን ገልጣ እንድትሰጥ የተገደደች አገር ሆናለች። የእነ አቶ መለስ ዜናዊ የልማታዊ መንግስት እሴት ይህንን የግሎባል ካፒታሊዝምን ዘረፋ የሚያዘጋጅና ህዝባችንን የሚያፈናቅል የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝም ይህንን ጥልቀት በመስጠት የአገራችን ሀብት እንዲዘረፍና፣ የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋና የዕድገቱም ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲዘበራረቅ ለማድረግ በቅቷል። ይህም ሁኔታ በህዝባችን ላይ ከፍተኛ የህሊና መረበሽን ፈጥሯል። ዘራፊዎችንና ወንበዴዎች እንዲስፋፉ አድርጓል። በዚያው መጠንም ደካማው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቃበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህም መሰረት በአቢይ አህመድና በግብረአበሮች አስተሳሰብ የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት፣ ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ የሚከፍቱ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እዲቋቋሙ ቅድሚያ መስጠት፣ ለሰፊው ህዝብ የሚሆኑ በሚገባ የታቀዱ የመኖሪያ ቤቶች መስራት፣ የታቀዱና የሚያማምሩ ከተማዎችን ማስፋፋትና መገንባት ሳይሆን ትላልቅ ህንጻዎችን መስራት፣ ትላልቅ ሆቴልቤቶችን መገንባት፣ $ 10 ቢሊዮን በመመደብ በአፍሪካ ውስጥ ትልቅና ተወዳዳሪ አይገኝለትም የተባለውን የአውሮፕላን ጣቢያ መስራትና እነዚህን የመሳሰሉትን እንደ ኢኮኖሚ ዕድገት ይመለከቱታል። በዚያው መጠንም ሰፊው ህዝብ ቆሻሻ ቦታ እንዲኖር መደረግ፣ ከቆሻሻ ቦታ ምግብ እየፈለገ እንዲበላ መደረግና አቅጣጫውንም እንዲያጣ ማድረግ እንደ ኖርማል ነገር ይታያል። በዚህ ዐይነት ሁኔታው ውስጥ የተፈጠረው አዲስ የህብረተሰብ ክፍልና ምንምም ሳይሰራ ሀብታም ለመሆን የበቃው ደካማውንና ኮሰስ ብሎ የሚታየውን የህብረተሰብ ክፍል የሚሳደብበትና የሚንቅበት ሁኔታም ተፈጥሯል።፡
የልማታዊ መንግስት ምንነትና ተግባር በታሪክ ውስጥ!
አብዛኛውን ጊዜ ስለልማታዊ መንግስት ወይም ስለ ዴቬሎፕሜንታል መንግስት የሚጽፉ የኢኮኖሚስት ምሁራን የሚሰሩት ትልቅ ስህተት አለ። ይኸውም የመንግስትን በዕድገት ውስጥ ተሳትፎም ሆነ ዋና አቀናጅ መሆን ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ እንዲሁም ከታይዋንና ከአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ አገሮች ጋር ብቻ ስለሚያያዙ ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ ስህተት እንደሆነና የታሪክንም ማህደር ላገላበጠ፣ በፕሮፌሰር ኤሪክ ራይነርት How Rich Countries Got Rich የሚለውንና፣ በፕሮፌሰር ሊያህ ግሪንፊልድ The Spirit of Capitalism የሚለውን መጽሀፍ ላነበበና በኢኮኖሚ ዕድገት ትምህርት ውስጥ ያልተካተቱን ብዙ መጽሀፎችን ላገላበጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በአጠቃላይ ሲታይ የብዙ መቶ ዐመታት ወይም በሺህ ዐመታት የሚቆጠር ታሪክ አንዳለው ወዲያውኑ ሊገነዝብ ይችላል።
ከአምስት ሺህ ዐመታት ወይም ከዚያን ጊዜ በፊት ትላልቅ ፕሮጀክቶች፣ እንደ ቤተመንግስቶች፣ ፒራሚዶች፣ የመስኖ ግንባታዎችና የከተማ ቁርቆራዎች ይካሄዱ የነበረው በዚያን ዘመናት በነበሩ አገዛዞች ነበር። የግብጽ ስልጣኔ በቀሳውስቱና በፋራኦኖች የሚመራና ተግባራዊ የሚሆን ነበር። ካርል ቪትፎገል የሚባለው ታላቅ ምሁር እንደሚያስተምረን በቻይና ትላልቅ ፕሮጀክቶች ይሰሩ የነበረው፣ በአሲያን ዲስፖቶች(Asiatic Despotism)ወይም The Hydrolic Society እያለ በሚጠራው አስተዳደር ነበር። ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ተግባራዊ መሆን የጀመረው የግሪኩ ስልጣኔ ሶሎን በሚባለው ከኦሊጋርኪው መደብ በፈልቀ ታላቅ ፈላስፋና የድራማ ሰውና ታላቅ መሪ ነበር። በዘመነ ሪናሳንስ የተጀመረውንና፣ ከፍተኛ የተሃድሶና የዕድገት ክንውን ስንመለከት የመንግስት ሚና ከፍተኛ ቦታን እንደያዘ እንገነዘባለን። በ1338 ዓ.ም የነበረው ታላቁ የሪናሳንስ ምሁር አምብሮጊዮ ሎሬንዘቲ The Allegory of Good and Bad Government በሚለው ስራው የሚያረጋግጠው በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ የመንግስትን ማዕከላዊ ቦታ በማስመር ነው። ስለዚህም ይላል አምብሮጊዮ፣ “አንድ ጥሩ መንግስት በቆንጆ ከተማዎች ግንባታ፣ በንግድ ዕድገትና እንቅስቃሴ የሚገለጽና፣ እንዲሁም በማኑፋክቱር አብዮት ሲረጋገጥ፣ መጥፎ መንግስት ደግሞ ህብርተሰቡን በማበላሸትና አቅጣጫውን በማዛነፍ ይገለጻል ይላል”። ሰለዚህም ይላሉ ፕሮፌሰር ራይንከርት“ The usfullness of a State in the process arises out of the Renasissance concept of common weal-or the „common good“- a systemic dimension which is lost in the atomistic and static structure of today`s mainstream economics.“ በመቀጠልም በሬንሳንስ ዘመን የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ሰፋ ያለና በዕውቅና እንዲሁም በአይዲያሊዝም ላይ በመመራት የተካሄደ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ፕሮፌሰር አልበርት ሂርሽማን የተባሉትና ብዙ ስለ ዕድገት ኢኮኖሚክስ የጻፉ አሜሪካዊ ምሁር እንደዚህ ዐይነቱ የተቀደሰ የመንግስት ሚና ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀመሮ እየተስፋፋ የመጣው የገበያ ኢኮኖሚ በሚባለው በመተካት ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ እንደመጡ ያመለክታሉ። በእነ አዳም ስሚዝና በኋላ ደግሞ በሄኔሪ ቱሮ የሚመራው ክንፍ የመንግስት ጣልቃ-ገብነትን በመቃወም የመንግስት ሚና እጅግ ዝቅ ማለት እንዳለበት ያስረዳሉ። ይሁንና ግን በተጨባጭ እንደታየው በተለይም ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በምዕራብ አውሮፓ ብሄረ-መንግስታት ሲቋቋሙና ወደህብረተሰብ ግንባታ ሲያመሩ የመንግስት ሚና ከፍተኛ ቦታን እየያዘ እንደመጣ እንገነዘባለን። በታሪክ ውስጥም በግለሰብ አነሳሽነት ብቻ አንድ አገር የተገነባበት ቦታና ማረጋገጫም የለም።
በዘመነ መርከንታሊዝም ከኮልበርትም በፊት የነበሩ ባለስልጣናትና ኮልበርት ራሱ፣ በጊዜው የፈረንሳይ የገንዘብ ምኒስተር የነበረው ይመሩበት የነበረው ፖሊሲ የመንግስትን ሚና ማዕከለኛ ቦታ በመገንዘብ ነበር። ኮልበርት እንደሚለው የገንዘቡን ምንጭ ከያዝኩ ትላልቅ ስራዎችን መስራትና ህብረተሰቡን ማደራጀትን አውቅበታለሁ ይላል። ስለዚህም የፈረንሳዩ የእነኮልበርት የኢኮኖሚ ፖሊሲና በጀርመንና በአውስትሪያ ይካሄድ የነበረው ካሜራሊዝም የሚባለው የህብረተሰብ ግንባታ መመሪያ ዋናም መሰረተ-ሃሳብ አዳዲስ ዕውቀቶችን በማዳበር ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚሆነውን ፈለግ መቅደድ ነበር። ስለዚህም በጊዜው የነበረው ዕምነት በቁጥር የሚለካ አንዳች የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ሳይሆን፣ በተወሰነ አይዲያሊዝም ላይ በመመስረት ዘላቂነት ያለው ዐይነተኛና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ነው። የሰውን ልጅ የተፈጥሮን ጸጋ በማላባስ አልፎ አልፎ ተፈጥሮ የምታደርስበትን አደጋ ለመከላከል የሚያስችለውን መሳሪያዎች በመስራት እሴት ያለው የተረጋጋ ማህበረሰብ ለመገንባት ነው። ፕሮፌሰር ራይከርት እንደገና በተፈጥሮ ሳይንስና በህብረተሰብ ሳይንስ መሀከል ያለውን ልዩነት ሲገልጹ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ስለቁጥር የሚያወራ ሲሆን፣ የህብረተሰብ ሳይንስ ግን ስለሰው ልጅና ስለኑሮው ሁኔታ መሻሻል ነው ይሉናል።“In the activist-idealistic tradition, economics and social sciences require a different kind of understanding from the natural sciences. The social sciences, concerned with ends and values instead of laws, should aim to understand (verstehen). ስለዚህም ይህ ዐይነቱን የሰውን ልጅ ምንነተና የስልጣኔ ፍላጎት ማዕከላዊ ቦታ የሚሰጥ በሃይፖቴሲስ መልክ ደጋግሞ በመጠየቅና መልስ በመፈለግ በሚገኝ ዕውቀት ብቻ ነው ተግባራዊ የሚሆነው። ይህንንም የዕውቀት ምንጭ ፒየርስ የተባለው ፈላስፋና ሳይንቲስት ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመመልከትና በማንበብ ከዚያም በመነሳት አዲስ ቲዎሪ በመፈለግ የሚገኝ ለችግር መፍቻ የሚሆን ፖሊሲ ነው ብሎ ይጠራዋል። ከዚህ በመነሳት ነው ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በፍጹም ሞናርኪዎች አገዛዝና በታላላቅ ፈላሳፋዎች ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና የአገር ግንባታ መካሄድ የጀመረው። ይህ በተግባር ሲተረጎም፣ የፍጹም ሞናርኪዎች ሚና የማኑፋክቱር አብዮት እንዲካሄድ በተለይም ለነቁ ኃይሎች (active forces) አስፈላጊውን የገንዘብ ዕርዳታ መስጠት ነበር። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን (Infant industries) ከውጭ በሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች እንዳይጎዱ የዕገዳ ፓሊሲ ማካሄድ ነበር። ወደ ውስጥ ለሰፊ ገበያ ማነቆ የሆኑ የኬላ ዕገዳዎችን በማንሳት የሀብት እንቅስቃሴ እንዲካሄድ ሁኔታውን ማመቻቸት ነበር። በዚህ ዐይነቱ የጣልቃ ገብነት ፖሊሲ ምቀኝነትና ተንኮል ቦታ አልነበራቸውም። አብዛኛዎቹ የተማሩና በፈላስፋዎች የሚመሩ ስለነበር እንዴት አድርገን የጠነከረ አገርና ህብረተሰብ እንገነባለን ነበር ህልማቸውና ተግባራቸው። በጊዚው እንደ ኢህአዴግና አሁን ደግሞ እንደ አቢይ አህመድ የብልጽግና አገዛዝ የምቀኛ አገዛዞች በሁሉም ነገር ውስጥ ጣልቃ በመግባትና ለማደግ ደፍ ደፍ የሚለውን ጭንቅላት ጭንቅላቱን በመምታት ሀሞቱ እንዲፈስ የሚያደርጉ አለነበሩም። ይህንን ዐይነቱን በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊስ አሜሪካን በእነ እብራሃም ሊንከንና በእነ ሃሚልተን ዘመን፣ ጀርመን ደግሞ በንጉስ ፍሪድሪሽ ሁለተኛውና በኋላ ደግሞ በቢስማርክ አማካይነት ተግባራዊ በማድረግ ለጀርመን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመራ የኢንዱስትሪ አብዮት ያካሄዱበትን ሁለ-ገብ ስትራቴጂ ማየት እንችላለን። በዚህ ዐይነት በዕውቅ ላይ በተመሰረተ በመንግስት የተደገፈ ፖሊሲ ጀርመን ሁለት ትውልድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ እንግሊዝንና ፈረንሳይን ቀድማ መሄድ ችላለች።
ወደ ጃፓን ስንመጣ ደግሞ በሜጂ ዲይናስቲ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከኋላ የመያዝና “catch-up” የመቅደም ስትራቴጂ ነው። ካርል ሞስክ የተባለው የጃፓን ኤክስፐርትና፣ እንዲሁም ደግሞ ፕሮፌሰር ሊያን ግሪንፊልድ ዘ ስፕሪት ኦፍ ካፒታሊዝም በሚለው ግሩም መጽሀፋቸው ውስጥ ስለ ጃፓን የኢኮኖሚ ዕድገት ሲያትቱ መሰረቱ የተጣለው ከ1600-1868 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በቶኩጋዋ ዲይናስቲ ዘመን እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚያን ጊዜ የነበሩ የፊዩዳል ባላባቶች በመሀከላቸው ስምምነት በመፍጠር በገጠር ውስጥ የእርሻ ምርት እንዲያድግና ከተማዎች እንዲያብቡ በማድረግ Prot-Industrial Economy እንዲካሄድና፣ ይህ የጎጆ ኢንዱስትሪና የከተማዎች ግንባታ ለስዎች ተሰባስቦ መኖር አመቺ ሁኔታ ሲፈጥር፣ በኋላ ብቅ ላለው የሜጂ ዲይናስቲ መነሻ እንደሆነለትና በመንግስት የሚደገፍ ሰፋ ያለ አገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ግንባታ ማካሄድ እንደ ጀመረ ያስረዳሉ። የሜጂ ዲይናስቲ ዋና ፍልስፍና ሀብት መፍጠርና አገር መገንባት ሲሆን፣ በሚሊታሪ ደግሞ ጠንክሮ መገኘትና፣ ይህንን ግብ ለመምታት ሰፋ ያለ የኢንፍራስትራክቸር ግንባታ ማካሄድ ነበር። ይህ ሁኔታ ለኢንዱስትሪ አብዮት አመቺ መንገድ ይከፍትለታል። በመቀጠልም ዘመናዊ የሆነ የናቫልና የወታደር ተቋም ይገነባል። በዚህም መሰረት ራሱን በማጠናከር ከምዕራቡ ዓለም የሚመጣበትን ግፊት ለመቋቋም ሁሉን ነገር ያመቻቻል።
ወደ ተጨባጩ የግንባታ ፖሊሲ ስንመጣ ዋና መቀመጫውን ቶኪዮ ያደረገው የሜጂ ዲይናስቲ ሰፊው ህዝብ እንዲማር የግዴታ የመሰረተ ትምህርት እርምጃ ይውሰዳል። በተጨማሪም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመች ልዩ ዐይነት የኢንጂነሪንግ ፋክሊቲ በመክፈት አዲስ ኤሊት እንዲኮተኮት ያደርጋል። የገንዝብ ምኒስተሩ ደግሞ በ1882 ዓ.ም ባንክ ኦፍ ጃፓን የሚባለውን በማቋቋም ለግል ባንኮች መመሰረት መሰረቱን ይጥላል። በዚህ አማካይነት ለኢንዱስትሪ ዕድገትና መስፋፋት ሰፊ የፊናንስ ሲይስተም ይገነባል። በተለያዩ ደሴቶችና ከተማዎች መሀከል ግኑኝነት እንዲፈጠር በእንፋሎት ሃይል የሚነዳ የባቡር ሃዲድ እንዲስፋፋ ሁሉን ነገር ያዘጋጃል። በዚህ መሰረት የጃፓን ህዝብ እንደ አንድ ህዝብ ሆኖ እንዲነሳ መሰረቱን ጣለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት እንዲኖረውና የኢንዱስትሪዎች የማምረት ኃይል ከፍ እንዲል አዳዲስ ቴኮኖሎጂዎችን ከውጭ በማስመጣትና በመኮረጅ የኢንዱስትሪዎች ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። ባጭሩ ለጃፓን ዕድገት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ብቻ ሳይሆን ዋና መሰረቱ፣ ዕውቅናን ያዘለ ስልትን በመከተልና በከፈተኛ ዲሲፕሊን በመመራት ስኬታማ አደረጃጀትን በማዘጋጀት የኢንስቲቱሽኖችና የህዝቡ እንዲሁም የኤሊቱ መመሪያ በማድረግ ነው። ዲሲፕሊን በሌለብት፣ የስራ ባህልና ፍላጎት ባልዳበረበት፣ በዚህ ላይ ደግሞ ብሄራዊ ስሜት ባልታከለበት አገር ውስጥ አንድ አገር ሁለ-ገብ የሆነን የኢኮኖሚና የህብረተሰብን ዕድገት ልትቀዳጅ እንደማትችል ከሆላንድ እሰከጀርመንና እስከ ጃፓ ድረስ ያለው የዕድገት ፈለግ ያረጋግጥልናል። ይህንን መሰረተ-ሃሳብ ፕሮፌሰር ሊያህ ግሬንፊልድ በመጽሃፋቸው ውስጥ ያሰምሩበታል። በሳቸውም ዕምነት በግለሰብኝነት ላይ የተመሰረተ ነፃነትና የብሄራዊ ስሜት (Nationalism) ወይም Individualistic –civic type of nationalism በመኖር ብቻ ነው በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ካፒታሊዝም ሊያድግ የቻለው። ለዚህ ደግሞ የመንግስት ሚና ከፍተኛ ቦታን ሲይዝ፣ አደናቃፊና ምቀኛ ሳይሆን አጋዢና አመቺ ሁኔታዎችን ፈጣሪ መሆን እንዳለበት በግሩም ብዕራቸው በዝርዝር ያስረዱናል።
በዚህ መልክ በጃፓን ብቻ ሳይሆን ካፒታሊዝም ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሶም ቢሆን የመንግስት ሚና በሌላ መልክ ቀጠለ እንጂ ሙሉ በሙሉ ከእንግዲህ ወዲያ ሁሉንም ነገር ለገበያው ኃይሎች ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ የወጣበት ቦታ የለም። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገር ኢኮኖሚዎች በመከስከሱ ከጦርነቱ አገግመው የወጡት እንደፈረንሳይና ጀርመን የመሳሰሉት አገሮች በመንግስት ጣልቃ-ገብነት አማካይነት ከተማዎቻቸውን እንደገና መገንባት፣ ኢንዱስትሪዎቻቸውን መጠጋገንና የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት ለመስጠት ዩኒቨርሲቶቻቸውንና ኮሌጆቻቸውን በአዲስ መልክ በማዋቀር አጠቃላይና ሁለ-ገብ ግንባታቸውን ነው የቀጠሉት። የኒዎ-ሊበራልዚም ርዕዮተ-ዓለም ከመቃብሩ ከወጣ በኋላ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ፣ በተለይም ከ1980ዎቹ ዐመታት ጀምሮ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት እንደሰይጣን ስራ በመወሰድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለንጹህ የገበያ ፖሊሲ በስተቀር መፍትሄ የለም በማለት ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አካዳሚሺያኖች ማሳሳት ጀመረ። ብዙ የዋሆች ወደ ተግባር ሲለወጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የማይችለውን የኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚ ቲዎሪን የሙጥኝ ብለው በመያዝ በቀጥታ ለአገሮቻቸው ውድቀት ሁኔታዎችን አመቻቹ። ሀብት እንዲባክን፣ ሰው እንዲበታተን ወይም አገሩን ጥሎ እንዲወጣና በሰው አገር ተንከራቶ እንዲኖር አደረጉ። ምክንያቱም ቀላል ነው። በአገር ውስጥ ዕድገት ሲኖር፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ተምሮና የስራ ዕድል አግኝቶ ቤተሰብ መስርቶና ልጆች ወልዶ የኑሮን ጸጋ የሚጎናፀፍ ከሆነ ከአገሩ የሚስደድበት ምክንያት የለም። ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኒዎ-ክላሲካል ወይም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የተኮተኮተው ቢሮክራትና የቴክኖክራት ኃይል፣ አገር፣ ህብረተሰብ፣ ብሄራዊ-ነፃነት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ መንፈስን የሚያድስና ጥንካሬ የሚስጥ፣ እንዲሁም እሴትን የሚያጎናጽፍ ባህል መገንባትን እንደመመሪያው አድርጎ ባለመውሰዱ ወይም ደግሞ ባለማወቁ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን አገሮች በአሜሪካ ጉያ ስር ተወሽቀው እንዲታሹ በማድረግ የመጨረሻ መጨረሻ ውድቀት ላይ ጣላቸው። ጃፓንና ደቡብ ኮርያ ዛሬ ደግሞ ቻይና እንደሚያረጋግጡልን ራሱን ለውጭ ኃይል ያላጋለጠ፣ ብሄራዊ አጀንዳን ያስቀደመ፣ እንዲሁም ደግሞ በዲሲፕሊናን በታታሪነት የሚሰራ ኤሊት የመጨረሻ መጨረሻ ተልዕኮው ዕድገትን ማምጣትና ህዝቡ ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ነው። የእነ አቶ መለስና አሁን ደግሞ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ችግርም ይህንን በሰፊው አለማጥናትና ከሰውነት ጋር አለማዋሃድ ነው። ተንኮልንና ምቀኝነትን በማስቀደም ዕድገት የሚባል ነገር ተግባራዊ የሚሆን እየመሰላቸው ወደ መቶ ሰላሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብና በመጭው ትውልድ ላይ ያፌዛሉ፤ የታሪክ ወንጀል ስርተዋል፤ ይሰራሉም። የእነ አቶ መለስ የዴቬሎፕሜንታል የመንግስት ፖሊሲ ብሄራዊ ባህርይ የሌለው፣ አገርና ህብረተሰብ የሚሉትን መሰረተ-ሃሳቦች ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ዘለዓለማዊ ድህነትን የሚያጎናጽፍ አደገኛ ፖሊሲ ነው። አጀንዳቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን የጥቂቶችና ለጥቂቶች ተብሎ የተዘጋጀ ነው። ከዚህ ስንነሳ በእርግጥ እነ አቶ መለስ ይሉን እንደነበረው በመንግስት የሚደገፍ የታቀደና ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፓሊሲ እያካሄዱ ነው ወይ? ከ28 ዐመት የኢህአዴግ አገዛዝ በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየተሳሰረ የመጣና በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠረው በሰራ ጥማት ለሚሰቃየው ህዝባችን የስራ ዕድል እየሰጠው ነው ወይ? ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ዳብሯል ወይ? ኢህአዴግ 27 ዐመት ያህል ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየው የኢኮኖሚ ፖሊሲስ በእርግጥስ ወደ ርስበርሱ የተሳሰረ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያመራ ነበር ወይ? ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ኢህአዴግ 27 ዐመት ያህል ሲመራበት የከረመውን ፖሊስ ጠጋ ብለን እንመርምር።
በእርግጥስ የኢህአዴግ አገዛዝ ልማታዊ መንግስት ነበር ወይ?
ኢህአዴግ ስልጣን ከጨበጠ ከሁለት ዐመት በኋላ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በመስማማት ድርጅቱ ያቀረበለትን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አንድ በአንድ ተግባራዊ አድርጓል። የፖሊሲውን ምንነትና በተግባር ላይ ሲመነዘር ምን ዐይነት ውጤት እንደሚያመጣና እንዳመጣ ከዚህ ቀደም ባወጣኋቸው ጽሁፎቼ ላይ በሰፊው አብራርቼአለሁ። ጽሁፎቹን እንደገና ማገላበጡ የኢህአዴግ አገዛዝ የልማት መንግስት መሆኑና አለመሆኑን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ
ያም ሆነ ይህ እ.አ በ1993 ዓ.ም ተግባራዊ የሆነው የተቋም ፖሊሲ (Structural Adjustment Programs) ቲዎሪያዊ መሰረቱ ኒዎ-ሊበራሊዝም ነው። ይህም ማለት ቲዎሪው በይዘት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ክስተታዊ ነው ማለት ነው። በሌላ አነጋገር, በቲዎሪው መሰረት የአንድን አገር ወይም ህብረተሰብ ኢኮኖሚም ሆነ አጠቀላይ ህብረተሰብአዊ ችግር የሚረዳው ወደ ውስጥ በመግባትና በሰፊውና በጥልቀት በማጥናት ችግሩን በማውቅ ሳይሆን የተወሰኑ የማክሮ ኢኮኖሚ መሳሪያዎችን በመውሰድና ከዚህ በመነሳት ችግሩ እንደሚፈታ ለማሳመን በመሞከር ነው። ሀለተኛ፣ የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴል የአንድን ህብረተሰብ ችግር ከኢኮኖሚ አንፃር ብቻ ነው የሚመለከተው። ከመጀመሪያውኑ ፖለቲካዊ፣ ኢንስቱቲሽናዊ፣ ማሀበራዊና ባህላዊ ነገሮችን በማጣመር የችግሩን ጥልቀት ለመረዳት ጥረት አያደርግም። ለምሳሌ የካፒታሊስትን ስርዓት የዕድገት ታሪክ ስንመረመር ከባህል አብዮት በፊት ከመጀመሪያውኑ በተወሰኑ መሳሪያዎች ብቻ የነበሩባቸውን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት አልቃጡም። በሶስተኛ ደረጃ፣ ከዚህ በፊት ደጋግሜ ለማብራራት እንደሞከርኩት የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴሉ አጠቃላይ የሆነ ህብረተሰብአዊ ሀብትን ለመገንባት የሚያስችል አይደለም። ሞዴሉ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የሀብት ሽግሽግ በማድረግ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህ መልክ ፈጣሪና ኢንቬስት ለማድረግ የሚችል አዲስ ኃይል ብቅ አንዳይልና እንዳያድግ ያደርጋል። በአራተኛ ደረጃ፣ በማኑፋክቹር ላይ ከተመሰረተ የምርት እንቅስቃሴ ይልቅ ንግድና የተቀረው የአገልግሎት መስክ እንዲስፋፋ ያደርጋል። በተለይም ከአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገትና ፍላጎት እንዲሁም የሀብት አቅርቦት ጋር ሊሄዱ የማይችሉ ትላልቅ ሆቴል ቤቶች በመስራት ውሃንና ኃይልን እንዲሁም ምግብን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጋራ የሚያደርግ ነው። በዚህ መልክ ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲኖር ማገዙ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ህዝብ አትኩሮ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲሆን ያስገድዳል። በአምስተኛ ደረጃ፣ ሰፋ ያለ የስራ ክፍፍል እንዳይዳብር ዕንቅፋት ይሆናል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አገዛዙ በሚከተለው የተቀናቃኝ ፖሊሲ በግል ሀብታቸው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ቀስ ቀስ እያለ ያጠፋቸዋል። ምክንያቱም በኢኮኖሚ እያደገና እየዳበረ የሚመጣ ኃይልም ለፖለቲካ አገዛዝ አያመችም በማለት አይ በሙስና ውስጥ እንዲዘፍቅ ያደርገዋል፣ ካሊያም ደግሞ ሀበቱን በመንጠቅ ያዳክመዋል። ስለሆነም እንዲዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ሞዴል ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች በሙሉ ሰፊ ውንብድና መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን የመንግስት መኪናዎች የበለጠ ጨቋኝ እየሆኑ በመምጣት ህዝቦች አፎይ ብለው እንዳይኖሩ ተደንግጎባቸውል። ተፈጥሮአዊ መብታቸው በመነጠቅ በፍርሃት ዓለም ተውጠው እንዲኖሩ የተገደዱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች በየአገሩ እንዳሉ የታወቀ ነው። በስድስተኛ ደረጃ፣ ለአንድ አገር ዕድገት አስፈላጊው የሆነው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምርምርና ምጥቀት እንዳይኖር ከመጀመሪያውኑ ያግዳል። ሳይንስና ቴኮኖሎጂ ካልዳበሩ ደግሞ የተለያዩ የምርት ማምረቻ መሳሪያዎችንና፣ እንዲሁም ለአንድ ህብረተሰብ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችንንም ሆነ ከአደጋ ሊከላከሉ የሚችሉትን መሳሪያዎች ሊያመርት አይችልም ማለት ነው። በአንጻሩ ግን ዕውነተኛ በመንግስት የተደገፈ የልማት ፖሊሲ ያካሄዱ አገሮች በሙሉ ቅድሚያ የሰጡትና አሁንም የሚሰጡት በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ኢኮኖሚ መገንባትን ነው። ዋና ዓላማቸውም ሰፋ ያለና የጠለቀ ሀብት በመፍጠር ጠንካራ አገር መመስረት ነው። ለዚህም ነው ዛሬ ራሳቸውን መቻልና መከበር የበቁት።
ከዚህ ስንነሳ ኢህአዴግ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ያካሂድ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንም መልኩ ሰፋ ያለ ሀብት የሚፈጥር አልነበረም። የቢራ ፋብሪካ ማስፋፋት፣ በሰሊጥ ተከላ ላይ በማትኮር ጥሬ ሀብቱ አገር ውስጥ እስከመጨረሻ ድረስ እንዳይመረት አድርጓል። በዚህም መልክ መሰረታዊ የሆነን የኢኮኖሚ ህግን ጥሷል፤ እየጣሰም ነው። አንድ አገር የጥሬ ሀብቷን እንዳለ ከነነፍሱ ወደ ውጭ የምትልክ ከሆነ በኢኮኖሚ ልታድግ አትችልም። በአስራ አምስተኛውና በአስራስድሰተኛው ክፍለ-ዘመን ይህንን የተገነዘቡት እንግሊዝና ፈረንሳይ በጊዜው የነበረባቸውን የኢኮኖሚ ድክመት ለመቅረፍ የወሰዱት እርምጃ የግዴታ የጥሬ-ሀብት ወደ ውጭ እንዳይላክ በማድረግ ነበር። በአስራአራተኛውና በአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጣሊያን በኢኮኖሚ የበለጸገች ስለነበረች እንደ እንግሊዝ የመሳሰሉትን የጥሬ-ሀብት አምራች አድርጋ ነበር። በጊዜው ስልጣን ላይ የነበረው በሄነሪ ሰባተኛው የሚመራው አገዛዝ ይህንን በመረዳት ወደ ማኑፋክቹር አብዮት በመሸጋገር የበግ ፈርና ሌሎች የጥሬ-ሀብቶች ወደ ውጭ እንዳይወጡ ነው ያገደው። እንደዚሁም ፈረንሳይ በእነ ኮልበርት ዘመን ከእንግሊዝ የሚመጣባትን የኢኮኖሚ ጭነትና መዛባት ለመቋቋም የቻለችውና ወደ ኢንዱስትሪ አብዮት ለመሸጋገር የበቃችው የጥሬ-ሀብቷን በመቆጣጠርና እዚያው አገር ውስጥ ደረጃ በደረጃ እንዲመረት በማድረግ ነው። ከዚህ ስንነሳ የኢህአዴግ ፖሊሲ አንድ በአንድ የዴቬሎፕሜንታል ስቴትን የኢኮኖሚ ፖሊሲን የሚጻረርና አገራችንን ለረዥም ዐመታት ደካማና ደሀ እንዲሁም በውጭ ኃይሎች ተጠቂ የሚያደርጋት ነበር። ይህንን ዐይነቱን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው የአቢይ አህመድ አገዛዝ የተረከበውና የሚያካሂደውም። ይህም ማለት በሁለቱም መሀከል በይዘት ምንም ዐይነት ልዩነት የለም። ሁለቱም አገዛዞች ብሄራዊ ባህርይ የላቸውም። ስልጣን ላይ የተቀመጡት የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ነው።
ሰለሆነም በመለሰ ዜናዊ የሚመራው በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ህዝባችንን ከመሬት እያፈናቀለ ኢንቬስተሮች ለሚባሉ የሚሰጠው ሰፋፊ የጋሻ መሬት በመሰረቱ የዴቬሎፕሜንታል ስቴትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚቃወም ነው። 1ኛ) እንደዚህ ዐይነቱ የመሬት ማፈናቀል እርምጃ የተወሳሰበና እርስ በርሱ የተያያዘ በቤተሰብ ላይም ሆነ በአነሰተኛና በማዕከለኛ ገበሬዎች የሚታረስ የእርሻ ክንውን እንዳይካሄድ ያግዳል። 2ኛ) ለኢንቬስተሮች የተሰጠው የእርሻ መሬት ለአገር ውስጥ ፈብሪካዎች የጥሬ-ሀብት እንዳያመርት ታግዷል። 3ኛ) አንድ ወጥ የሆነ የአመራረት ስልትና በተወሰኑ ምርቶች ላይ ያተኮረ የእርሻ ክንዋኔ እንዲካሄድ ይገፋፋል። ይህ ደግሞ የተፈጥሮን ህግ የሚጻረርና የአካባቢን መዛባትን የሚያስከትል ነው። ከዚህም ባሻገር በላቦራቶሪው ውስጥ የተዳቀሉ ዘሮች ከመሬት ውስጥ ውሃን የመምጠጥ ኃይላቸው ከፍ ያለ ስለሆነ ከረዥም ጊዜ አንጻር ድርቀትን ያስከትላሉ። 4ኛ) በገጠር ውስጥ የስራ- ክፍፍል እንዳይዳብር ከማገዱም ባሻገር ገበሬው ኮሙኒቲ እንዳይመሰረት ያደርገዋል። ይህም ማለት በገጠር ውስጥ በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለጽ የባህል እንቅስቃሴ እንዳይኖር ያግዳል። በጊዜው የስኳር ምርት ለማስፋፋት ይካሄድ የነበረው እርምጃና ወደ ሰድስት የሚጠጉ የስኳር ፋብሪካዎች ተከላ ዕቅድ የአገራችንን ኢኮኖሚ እንዲዛባ ያደርገዋል። ልክ እንደ ብራዚል ገበሬውን ወደ ተራ ባርነት እንዲቀየር የሚያደርግ ነው። ይህም ማለት ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ የዴቬሎፕሜንታል ስቴትን መሰረተ-ሃሳብ ይፃረራል። በተጨማሪም የአበባን ተከላ ማስፋፋትና ቡናን የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ዋና ዕምብርት ማድረግና ሌሎች አጠቃላይ የሀብት ፈጠራን የማያመጡ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎች በመሰረቱ ከዴቬሎፕሜንታል ስቴት ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም። ታቃራኒው ናቸው ማለት ነው።
ወደ ከተማዎች ስንመጣ፣ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለልማት እየተባለ የሚካሄደው የመሬት ንጥቂያና ተፈናቃዮች ራሳቸውን እንዲገድሉ ወይም በየሜዳው ወድቀው እንዲቀሩ ማድረግ ከዴቪሎፕሜንታል ስቴት ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ዕውነተኛ በመንግስት የሚደገፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የህዝብን መብት የሚረግጥና ከቦታቸው የሚያፈናቅል አይደለም፤ መሆንም የለበትም። አካባቢው መልማት ካለበት ደግሞ የግዴታ ለብዙ ዐመታት በቦታው የሚኖር ሰው ሌላ አማራጭ ማግኘት አለበት፤ ወይም ደግሞ የቀድሞው ቦታ ሊመለሰ የሚችልበት ሁኔታ ከመጀመሪያውኑ መታቀድና መዘጋጀት አለበት። የኢህአዴግ ፖሊሲ ግን በተለይም ደሀውንና ድጋፍ የሌለውን የህበረተሰብ ክፍል የሚመታና ሶሻል ዳርዊኒዝምን የሚያስፋፋ ነበር። በተለይም በሪል ስቴት ስራ የተሰማሩ ከዓለም አቀፍ የፊናንስ ካፒታል ጋር የተቆላለፉ ኃይሎች የሚሰሩት የታሪክ ወንጀል በቀላል ቋንቋ የሚገለጽ አልነበረም። እነ አቢይ አህመድም ይህንን ነው በመረከብ ጥልቀትና ፍጥነት ለመስጠት የቻሉት። ቀድሞ ትግሪዎች በአቢይ የአገዛዝ ዘመን ደግሞ ኦሮሞዎች ነን የሚሉ ከዚህም ከዚያም በመምጣትና በመሰባሰብ፣ እንዲሁም ከውጭ የገንዘብ አበዳሪ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር የሀብት ቁጥጥር ለማድረግ ችለዋል። ህዝባችን በአገሩ ውስጥ ሁለተኛ ዜጋ እየሆነ እንዲታይ ተደርጓል። በኮሞዲቲ ገበያም ያለው ሁኔታ ከዚህ የሚያንስ አይደለም። የተሰተካከለና ሚዛናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚቀናቀን ኃይል በመፍጠር አገራችንን ዘለዓለሟን የጥሬ-ሀብት አምራች ሆና እንድትቀር የሚያደርግ ነው። በዚህም ምክንያት ቡና አምራቹ ገበሬ ህዝባችን ኑሮው በምንም ዐይነት ሊሻሻል አልቻለም። ከጎጆ ቤቱ አልተላቀቀም። ልጆቹን ለማስተማር አንዳይችል ተደርጓል። በሚያገኘው በዓለም ገበያ ላይ በሚወሰን ዋጋ የምርቱን ሂደትና ኑሮውን ለማሻሻል የቻለ አይደለም። በአንፃሩ ግን የኮሞዲቲ ገበያውን የሚቆጣጠሩት ግለሰቦችና የመንግስት ባለስልጣናት ልዩ ዐይነት ኑሮ በመኖር ለዋጋ መናርና ለሀብት ነጠቃ ምክንያት ሆነዋል ማለት ይቻላል።
ከዚህ ስንነሳና በተለይም እየጨመረ የመጣውን ድህነትና የቆሻሻ መኖሪያዎችን አካባቢ ስንመለከትና በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የኑሮ ውድነት ስንመረምር የኢህአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አባዛኛውን ህዝብ የባሰውኑ ወደ ድህነት የገፈተረና ወደፊትም እንደገፈተረ እንመለከታለን። የአቢይ አህመድ አገዛዝም ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር በመመሰጣጠርና በመታዘዝ በተከታታይ በሚያድረገው የገንዘብ የቅነሳ ፖሊሲና፣ የገንዘብን መተመን በአቅራቢና በጠያቂ ማድረጉ የኑሮን ውድነት አባብሶታል። ዝቅተኝ አገቢ ባለው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲሆን ፈርዶበታል። የመግዛት ኃይሉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ተደርጓል። ይህ በውስጥና በውጭ ኃይሎች በተቀነባበረና በረቀቀ መልክ የሚካሄደው ኢኮኖሚያዊ መዛባትና፣ እንዲሁም የሀብት ቁጥጥርና ዘረፋ ልዩ ዐይነት የህብረተሰብ ግኑኝነት እየፈጠረ ነው ማለት ይቻላል። እንደዚህ ዐይነቱን በዓለም እቀፍ ፊናንስ ካፒታል የሚደገፈውን የኢኮኖሚ ፖሊሲና የሀብት ዘረፋ ዘመናዊ ፊዩዳሊዝም ተብሎ ሊጠራ ይቻላል። በዘመናዊነትና በዕድገት ስም ገበሬውን ወደ ቀን ሰራተኛነትና ወደ ጥገኝነት የሚለውጠው ነው። ከዚህ ስንነሳ ምን መደረግ አለበት ወደሚለው እናምራ።
ምን መደረግ አለበት!
የኢህአዴግ አገዛዝ በጊዜው ከመሻሻልና ራሱን ከማረም ይልቅ በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ እየባሰበት የመጣ አገዛዝ ነበር። በአፍሪካ ውስጥም ተወዳዳሪነት የሌለው ጨቋኝ አገዛዝ ብቻ ሳይሆን አገራችንን በሁሉም አቅጣጫ እንድትዳከምና በዘለዓለማዊ ውዝግብ ውስጥ ወድቃ ህዝቧ ነፃነትን እንዳይቀዳጅ የሚያደርግ አስቸጋሪ አገዛዝ ሆኖ ብቅ ብሎ ነበር። አቢይ አህመድም ከእነ መለሰ ዜናዊ የቀሰመውን ተንኮል ጥልቀት በመስጠት የአገራችንን ውድቀት ለማፋጠን ችሏል። የህዝባችንን ኑሮ ለማመሰቃቀል ችሏል። ራሱ አገዛዙ በህዝባችን ላይ ሽብርተኝነትን እያካሄደ እያለ ለነፃነትና ለመብት የሚታገሉ ኃይሎችን በሽበርተኝነት የሚወነጅል አገዛዝ ነበር። የአንድ አገር ህልውና ስልጣን ላይ ባለው የገዢ መደብ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በጠቅላላው ህዝብም የመንፈስ ጥንካሬና በስነስርዓት መኖር ነው። ለዚህ ደግሞ ኢኮኖሚ ቁልፍ ቦታን የሚይዝና፣ የአንድ አገር ውድቀትና ጥንካሬ በኢኮኖሚ ሁኔታ የሚወሰን ነው። አንድ አገዛዝ ሆን ብሎ አንድን አገር የሚያዳክም ከሆነ፣ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር ሀብቷ እንዲዘረፍ የሚያደርግ ከሆነ፣ ባጭሩ ህልውናዋን የሚያዳክም ከሆነ በህዝብ ዘንድ ምንም ዐይነት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። የአንድ አገዛዝ ዕውቅናና ተቀባይነት ሊወሰን የሚችለው በሚሰራው ጥሩም ሆነ መጥፎ ተግባር ነው። እንዲያው በህገ-መንግስት ብቻ እያታለለ ሊኖር ምንም መብት የለውም ማለት ነው።
ከዚህ ስንነሳ የአንድ አገር ዕድገትና ህልውና ሊወሰን የሚችለው ባለው የፖለቲካና የመንግስታዊ አወቃቀር ሁኔታ ነው። ይህም ማለት አንድ አገዛዝ ራሱንና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ለማደለብ ሲል የመንግስቱን መኪና የባሰ ጨቋኝ የሚያደርግ ከሆነና ከውጭ ኃይሎች ጋር በብዙ ድሮች የተሳሰረ ከሆነ ለአገር ህልውናና ለጠቅላላው ህብረተሰብ ተስማምቶ መኖር አደገኛ ነው። አንድ ህዝብ እየተዘረፈ፣ እየተጨቆነ፣ የኑሮው ሁኔታ እየተበላሸበትና አቅጣጫውም የሚጠፋው ከሆነ ይህ እንደተፈጥሮ ህግ መታየት የለበትም። የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየውም እንደዚህ ዐይነት ነገር እንዴት ሊመጣ ቻለ? ብሎ በመጠየቅ ራሱንና አካባቢውን ለመለወጥ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። ሁኔታውን ለመለወጥም ሆነ ለማሻሻል የማይችል ምሁርም ሆነ ህዝብ በታሪክ ውስጥ እየተጠቃ የሚኖርና በመጭውም ትውልድ ተጠያቂ የሚያደርገው ነው። ስለዚህ ለአንድ አገር ዕድገት ቁልፉ የመንግስቱ አወቃቀር ሁኔታና የሚያካሄደው የፖለቲካ ዐይነት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። በታሪክም እንደተረጋገጠው የፖለቲካ ሁኔታ ሲሻሻልና ህዝቡም ነጻነትን ሲቀዳጅ ነው ሃሳብ ሊመጣለትና ህብረተሰቡንም ሆነ ኢኮኖሚውን ሊያሳድግ የሚችለው። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ህዝብ የበለጠ ነጻ እየሆነ በመጣ ቁጥርና ከላዩ ላይ ያለው ጭነት ሲቃለልለት የመፍጠር ኃይሉም ይዳብራል፤ ህብረተሰብአዊ ሀብት ይፈጥራል። ስለዚህም የፖለቲካ ጥያቄና የመንግስቱ መኪና ጉዳይ ቁልፍ ቦታን ይይዛሉ ማለት ነው። ህዝባዊ ባህርይ እንዲይዙና ታሪካዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በአዲስ መልክ መደራጀት አለባቸው። ህዝብን ከማስፈራራት ይልቅ የህዝብ ወዳጅና አለኝታ መሆን አለባቸው። ህብረተሰብአዊ ፍቅርን የሚለግሱና አገራችን ተከብራ እንትኖር የሚያድርጉ ሆነው መደራጀት አለባቸው። የሰላዮች መጨፈሪያ መሆን የለባቸውም። ባጭር ቋንቋ የኢህአዴግ፣ አሁን ደግም የአቢይ አህመድ የብልጽግን አገዛዝ ታሪካዊ ተልዕኮአቸው ጥፋት በመሆኑና ሊታረምም የማይችል ስለሆነ ከኮመን ሴንስ አንፃርም ሆነ ከተፈጥሮ ህግ ሁኔታ ስልጣን ላይ መቆየት ያለባቸው አይደሉም። ወደፊትም እንደዚህ ዐይነቱ አገር አጥፊ ኃይል የፖለቲካ ህይውት አይኖረውም፤ሊኖረውም አይገባም። የዛሬው የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአገራችን ምድር የመጨረሻውን የጨለማ አገዛዝ የፈጠር ስለሆነ መወገድ አለበት። እንደዚህ ዐይነት ሰይጣናዊ አገዛዝ ሲወገድና የታሪክ ቆሻሻ መጠያ ቦታ ሲጣል ብቻ ነው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈት የሚቻለው። ዕውነተኛ ነፃነትንም መቀዳጀት የሚቻለው። አንድ አገርና ህዝብ የማንም ወርጋጦችና የአላዋቂዎች መጨፈሪያ መሆን የለባትም። ወደ ተለያዩ የሃይማኖት መስቢኪያ መድረክነትም መለወጥ የለባትም። የእያንዳዱ ግለሰብ መለኪያነትም ፈጠራ፣ ምርታማነት፣ ታማኝነት፣ ሰውን አካባሪነትና አገርን ማፍቀር መሆን አለባቸው። እያንዳንዱ ግለሰብ እነደሰው ልጅ የሚከበርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። መንግስትና የመንግስት አካላትም ወይም አገዛዙ የህዝብ አገልጋዮች እንጂ ልዩ ፍጡሮች እንዳልሆኑ መታወቅ አለበት። በአጠቃላይ ሲታይ የመንግስቱ መኪና በምንም ዐይነት ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት መለወጥ የለበትም። የመንግስትም መኪና በተለያዩ መሳሪያዎች የሚደልብበትና ህዝብም የሚፈራበት ሁኔታ መቅረት አለበት።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው ካለኢንስቲቱሽናል ሪፎርም ምንም ነገር መስራት አይቻልም። የተቀላጠፈና ሰውን የሚያከብር አሰራር ካለ ለፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ያመቻል። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡትና፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም በሰዎች የሚካሄድና በጊዜና በአካባቢ የሚወሰን እንደመሆኑ መጠን የኢንስቲቱሽን ለውጥና፣ ኢንስቲቱሽኖች በልዩ ልዩ የስራ መስክ መዳበር ያለባችው እንደሆኑ የበለጸጉ አገሮች ታሪክ ያስተምረናል። ከዚህ ጋር ተያይዘው በመንግስት የሚደገፉ የምርምርና የጥናት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አፍላቂ ኢንስቲቱሽኖች መቋቋም አለባቸው። ይህ ሁኔታ የግዴታ ያለውን የትምህርት ተቋም በአዲስ መልክ ማደራጀት እንዳለብን ይጠቁመናል። በእሃዴግ የአገዛዝ ዘመን ካለበቂ ጥናት፣ የሰውና የማቴሪያል ኃይል፣ እንዲሁም ካለበቂ ላቦራቶሪና ቤተ-መጻህፍት የተቋቋሙት ኮሌጆች ወይም ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ዕደ-ጥበብ ማሰልጠኛነት መቀየር አለባቸው። ከዚህም ስንነሳ ስፊና አጠቃላይ የሆኑ የዕደ-ጥበብ ሙያ መስኮችንና የኢንጂነሪንግ ኮሌጆችን ማስፋፋቱና ማዳበሩ ለዕድገት አመቺ ነው። የጊዜውም ጥያቄ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መገንባት ነው። ከዚህ ውጭ ከውጭ የሚመጣን ውድድር መቋቋም አይቻልም። እንዲያውም ለዕድገት ዋናው ቁልፉ የጥሬ-ሀብት ተትረፍርፎ መገኘት ሳይሆን የዕውነተኛ ዕውቀት ባለቤት መሆነ ነው። በየአገሩ እንድምናየው የጥሬ-ሀብት አገር አምራቾች በዕድገታቸው የተዛነፉና በሙስና ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ነው ያላቸው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ግን የተፈጥሮ ህግ አይደለም። ከባህል ተሃድሶ አለመኖር ጋርና ከህብረተሰበአዊ ኃላፊነት አለመሰማት ጋር የተያያዘ የአገዛዝ ስልት ሲሆን፣ በተጨማሪም የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመከተል ጋር የሚያያዝ ነው።
ለአንድ አገር ዕድገት መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን ወሳኙ፣ በአገር ውስጥ ከብዙ ክርክር በኋላ የሚዳብር የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲም መኖር ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። አንድ አገዛዝም በእርግጥም ለአገሩ ዕድገት የሚቆረቆርና በታታሪነት ሊሰራ የሚችለው በጥሩ ቲዎሪና ፖሊሲ የሚመራ ሲሆን ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በየጊዜው መመርመር አለበት። ስለዚህም አንድ አገዛዝ የሚመራበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአገሩን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን አለበት። ለውጭ ኃይሎች መፈናፈኛ የማይሰጥ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ከደሙ ጋር ያዋሃደ ኢትዮጵያዊ ኃይል ያስፈልጋል። ይህ ኃይል ዕውቀት ያለው፣ በአዋቂዎች የተከበበና ምክር የሚሰማ መሆን አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ለአንድ አላማ በአንድነት መነሳት አለባቸው። በሳይንስ የማይረጋገጥን ርዕዮተ-ዓለም ሽፋን የሚያደርግና ከአገር ጥቅም ይልቅ ለራሱና ለውጭ ኃይሎች ጥቅም የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት ለዕድገትና ለህብረተሰብአዊ መተሳሰር እንቅፋት እንደሚሆን ከመጀመሪያውኑ መታወቅ አለበት። ስለሆነም ለአገር እታገላለሁ ብሎ የሚነሳ ማንኛውም ኃይል ከውጭ ኃይሎች ጋር በጥቅም የተሳሰረ መሆን የለበትም። በሌላ አነጋገር፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከውጭ ኃይሎች ጋር የውስጥ ለውስጥ ግኑኝነት የፈጠረና በእነሱም አማካይነት ስልጣን ላይ እወጣለሁ የሚል የመጨረሻ መጨረሻ ተልዕኮው ጥፋት ይሆናል። ከብዙ የአፍሪካ አገሮች ታሪክ የምንማረው በተለይም አሜሪካንን ተገን አድረገው ስልጣን ላይ የወጡ ኃይሎች ህዝቦቻቸውን ወደ ዕውነተኛው ነፃነት ሊያመሩት አልቻሉም። ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚሄዱ የአሰራር ዘዴዎች ወይም ባህሎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ስነ-ምግባርና ሞራል፣ ዲሲፕሊንና የጠበቀ አደረጃጀት፣ ግን ደግሞ በየጊዜው የሚሻሻል፣ ታታሪነትና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት፣ ጥበብን የሚያስቀድም የአሰራር ስልት ለአገር ዕድገት በጣም ያመቻሉ። ይህም ማለት ለፖለቲካ ስልጣን ወይም ኃላፊነት እታገላለሁ የሚል የግዴታ በራሱ ላይ የባህል ለውጥ ለማካሄድ የሚዘጋጅና ሂስንም የሚቀበል መሆን አለበት። ተነካሁ ብሎ የሚያኮርፍ ለኃላፊነት ብቃት የለውም።
ወደ ሀብት ጥያቄ ስንመጣ የኢህአዴግ አገዛዝም ሆነ በአሁኑ ወቅት የአቢይ አህመድ አገዛዝ አዲስ የሀብት ግኑኝነትና ክፍፍል ሁኔታ ፈጥረዋል። የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ሰፊውን ህዝብ ከመሬቱና ከንብረቱ አፈናቅለውታል፤ እየተፈናቀለም ነው። ይህም ማለት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ሀብት በሙሉ ከተመረመር በኋላ በመንግስት ቁጥጥር ስር በመዋል ወደ ህዝብ የሚመለስበት ሁኔታ መዘጋጀት አለበት። ከዚህም በላይ በተለይም ለውጭ ኢንቬስተሮች እየተባለ የተሰጠው የእርሻ መሬት ካለምንም ካሳ ተወርሶ ለአራሹ ህዝብ መመለሰ አለበት። ለህዝብ መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ባለስልጣናትና የውጭ ኢንቬስተሮች በአካባቢው ላይ ላደረሱት ጉዳትና የህዝብ መፈናቀል ተጠያቂ ሲሆኑ፣ በተለይም ኢንቬስተሮች ካሳ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። እዚህ ላይ በአንዳንድ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የሚናፈሰው እንደዚህ ዐይነቱ እርምጃ የዓለም አቀፍ ህግና ስምምነትን ይጥሳል የሚለው ትጥቅ አስፈቺ አነጋገር ቦታ የለውም። አገርህን አንተ በፈለግኸው መልክ አትገንባ የሚል ህግ የለም። በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ ሀብት ሆነ መሬትም ጭምር በዚያ አገር የሚኖር ህዝብ ሀብት ነው። እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እንደዚህ ካደረጋችሁ ብድር አንሰጣችሁም የሚለው ዛቻ ቦታ የለውም። ማንኛውም ከውጭ የሚመጣ ግፊትና ጫና በእኛ የተባበረ ኃይልና ዕምነት ብቻ ነው ሊፈርስ የሚችለው። በመሆኑም የእርሻ መሬት በግለሰብም ሆነ በማህበር በመደራጀት ለሚያርስ ሁሉ በይዞታ ይሰጠዋል። ገበሬው መሬቱን በስነስርዓት የማልማት መብትና ግዴታ ሲኖረው፣ የመሸጥ ወይም የመለወጥ መብት አይኖረውም። ከወላጅ ወደ ልጅ የሚተላልፍ ይሆናል ማለት ነው። የከተማ ቦታዎች ደግሞ ህብረተሰቡ እንዲኖርበት ሆነው ጥበባዊ በሆነ መልክ የሚዘጋጅበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሰፊውን ህዝብ ወደቆሻሽ መኖሪያ ቦታ የሚገፈትር አጉል ፖሊሲ ይቆማል። ሪል ስቴትስ የሚባሉ የአገርን ዕድገትና የሰፊውን ህዝብ መብት ያላከተቱና ለተወሰነው የህበረተስብ ክፍል ተብለው የሚሰሩ የህንፃ አሰራሮች እንዲቆሙ ይደረጋሉ። የሪል ስቴቶች መስፋፋት ልዩ ዐይነት ሰግሪጌሽንን የሚያመጣ ስለሆነ መቆም አለበት። ስለሆነም የከተማን ቦታ ሰፊው ህዝብ በግለሰብም ሆነ በማህበር በመደራጀት ከአራት ፎቅ በላይ ከፍ የማይል ቤት እንዲስራ ማንኛውም ድጋፍ ከመንግስት እንዲሰጠው ይደረጋል። ለዚህ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ያለው፣ የተለያየ የዲንጋይ ዐይነት፣ ለጡብ የሚሆን አፈርና ሌሎች ማቴሪያሎች ለቤት ስራ የሚያመቹ ናቸው። በአውሮፓ ውስጥ የቤት አሰራርን ታሪክ ላጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስ ነው ከተማዎችንና አዳራሾችን እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶችን መገንባት የተቻለው። ፍላጎትና ዲሲፕሊን ካለ የማይሰራ ነገር የለም ማለት ነው። ለከተማዎች ግንባታ የሚሆን አርኪቴክተሮችን፣ የህንፃ ስራ አዋቂዎችን፣ የከተማ ዕቅድ አውጪዎችን፣ ሶስዮሎጂስቶችንና ፈላስፋዎችን ያቀፈ ልዩ ኢንስቲቱት እንዲቋቋም ይደረጋል። ከውጭ ከጣሊያን፣ ከፖላንድ፣ ከፖርቱጋልና እነዚህን ከመሳሰሉት አገሮች አዋቂዎችና አናጢዎች በማምጣት ብዙ ትምህርትና ልምድ መቅሰም ይቻላል።
አንድን ከተማም ሆነ አገር ለመገንባት የገንዘብ ጉዳይ ወሳኝ ነው። ስለሆነም በሶስት አቅጣጫ የሚሰራ የባንክ አደረጃጀት መቋቋም አለበት። በየክፍለ ሀገሩ ርካሽ ብድር የሚስጡ የመንግስት ባንኮች መቋቋም አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ ለዕድገት የሚሆንና በግለሰቦች እጅ ያለን ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ልዩ የዕድገትና የመልሶ መገንባት ባንክ ይቋቋማል። ከዚህም በላይ በሳንቲም የሚቆጠር ልዩ ዐይነት ፈንድ ሬይዚንግ ሲይስተም ይፈጠራል። በዚህ መልክ የሚገኘው ገንዘብ ለየክፍለ ሀገሮች እንደፍላጎታቸውና ዕድገታቸው የመገንቢያ ዕርዳታ ይሰጣቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ በግለሰብ ደረጃ የሚንቀሳቀስ የባንክ ኢንስቲቱት ይመሰረታል። የግለሰብ ባንኮች ጥብቅ የሆነ የአሰራር ህግን እንዲከተሉ መመሪያ ይወጣል። በሶስተኛ ደረጃ፣ በማህበር የተደራጀና የሚተዳደር ባንክ ይቋቋማል። የእነዚህ ሁሉ የገንዘብ ምንጭ የማዕከላዊ ባንክ ሲሆን፣ በተለይም የብደርን አሰጣጥ የሚቆጣጠር ልዩ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ይቋቋማል። በዚህ መልክ በባንክ አማካይነት ሊንቀሳቀስ የሚችል ሀብት በመፍጠር ለማኑፋክቱር ተከላና የግዴታ ለጠቅላላው የአገር ግንባታ እንዲውል ይደረጋል። በብድር የሚሰጠው ገንዘብ ወለዱ ዝቀተኛ በመሆን ከብዙ ዐመታት በኋላ የሚከፈል ይሆናል። የውጭ ገንዘብን በሚመለከት የግዴታ የውጭ ምንዛሪ በመግንስት ቁጥጥር ስር ይውላል፤ ወይንም እንደ አስፋላጊነቱ ማዕከላዊ ባንኩ ለማሽንና ለዕድገት የሚያገለግሉ ኢንዱስትሪዎችንና የጥሬ ሀብቶችን ለማስመጣት ለአስመጪዎች ያከፋፍላል። ግለሰቦች የውጭ ገንዘብ ወደ ውጭ እንዳያወጡ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ማንኛውም የጥቁር ገበያና የአየር ባየር ንግድ እንዲሁም ደላላነት በህግ ይከለከላሉ። ከዚህ በተረፈ ለሞራል ብልሹ የሚሆኑ የመጠጥ ዐይነቶችና፣ ቅጥ ያጣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የማይጓዝ የፍጆታ ዕቃ እንዳይገባ ይታገዳል፤ ወይም በመቶ ፐርሰንት ይቀረጣል። በተጨማሪም በአገር ቤት ውስጥ የሚመረቱ ተመሳሳይ ምርቶች ከውጭ በገፍ እንዳይገቡ ገደብ ይደረግባቸዋል፣ ወይም ከፍተኛ ቀረጥ ይጫንባቸዋል። ከዚህ በተረፈ ከውጭ የሚመጡ ሰከንድ ሃንድ ዕቃዎች በጥብቅ የሚከለከሉና እንደ መኪና የመሳሰሉት ደግሞ የተወሰነ ስታንደርድን ያሟሉ መሆን አለባቸው። የአገሪቱን የትራንስፖርቴሽን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ቦታዎች ባሉበት ቦታ በአየር ላይ የሚንቀሳቅስ ቀላል ባቡር ማስገባት፣ በዚህ ዕውቀት ካለቸው እንደ ስዊዘርላንዲና አውስትሪያ ጋር ልዩ ስምምነት ማድረግ። በረባዳ ቦታዎች ደግሞ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ ስትሪት ካር እንዲስፋፋ ማድረግ። በዚህ መልክ የመኪናን መግባት በመቀነስ በከተማዎች ያለውንም የትራፊክ አደጋና የመንገድ ጥቦት መቋቋም ይቻላል።
የአንድ አገር ኢኮኖሚ ፖሊሲው የመጀመሪያው ዓለማ የአገርን ሀብትና የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ ድህነትን ማሰወገድ ነው። በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኒዎ-ሊበራሊዝም ሳይሆን በዕውቅ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ ነው። ጀርመን ሁለት ሶስተኛው የሚሆነው ኢኮኖሚዋና ንብረቷ በጦርነቱ ምክንያት ከወደመና ከፈራረሰ በኋላ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ ዐመት ባለው ጊዜ ውስጥ መልሳ የገነባቸው በተዓምር ሳይሆን በመደራጀት፣ በዲሲፕሊንና በፍላጎት በመመራት ነው። እነዚህን መመሪያዎች ያላደረገ በፍጹም ጤናማና ጠንካራ አገር ሊገነባ አይችልም ማለት ነው።
ይህ ማለት ምን ማለት ነው። የኢትዮጵያን ዕድገትና ስልጣኔ ከአቢይ አህመድ አገዛዝ ባሻገር ማየት አለብን ማለት ነው። በምርጫ ተወዳድሬ ስልጣን ይዤ አገር እገነባለሁ ማለት ለአገዛዙ በጭቆናህ ግፋበት እንደማለት ይቆጠራል። የኢትዮጵያ ህዝብና አገር ወዳዱ ኃይል በዛሬው አገዛዝና በህገ-መንግስቱ መቃብር ላይ አዲስ ህገ-መንግስት በመፍጠር ወደ አገር ግንባታ የሚሸጋገርበት መሆን አለበት። ስለሆነም ከምንጊዜውም በላይ ከውዥንብር በመላቀቅና ህዝብን ከማደናበር ታግዶ ወደ ተባበረና ለዕድገት ወደሚያመች ስራ መሰማራቱ የአቢይን አገዛዝ ዕድሜ ያሳጥረዋል። የኢትየጵያ ህዝብ የሚሻውና የቀን ተሌት ህልሙ ከእንደዚህ ወደ ወሮበላነት የሚጠጋ አገዛዝ መላቀቅ ብቻ ነው።
ይህንን ካልኩኝ በኋላ ሰሞኑን በተከታታይበዘሃበሻ የሚባለው ድረ-ገጽ ላይ በመለሰ ዜናዊ ይመራ የነበረው የኢህአዴግ አገዛዝ ልማታዊ መንግስት ነበር እየተባለ የሚጻፈው የውሸትና አደናባር ጽህፍ መቆም አለበት። የመለሰ ዜናዊና የአቢይ አህመድ አገዛዞች በቅርጽ ቢለያዩ ሁለቱ አገር አውዳሚዎች ናቸው። ሁለቱ አገዛዞች በአገራችን ምድር ሙስናንና ብልግናን በከፍተኛ ደረጃ ያስፋፉ ናቸው። ሁለቱም አገዛዞች የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና የሌሎች የብሄራዊ ነፃነታችን ጠላቶች የሆኑ ተጠሪዎች ናቸው። ባጭሩ ሁለቱም አገዛዞች አጥፊዎችና አገርን አውዳሚዎችና ተንኮለኞች ናቸው። ስለሆነም የመለሰ ዜናው አገዛዝ ልማታዊ ነብር እየተባለ የሚጻፈው ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መቅረት አለበት
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
ማሳሰቢያ: በተለይም ስለኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን አወዛጋቢ ጉዳይ ለመረዳት ከዚህ በታች
የተዘረዘሩትን መጻህፍት ማየቱ ይጠቅማል።
Angresano, James, The Political Economy of Gunnar Myrdal, UK, 1997
Blaug, Mark(ed), Thorsten Veblen: Pioneers in Economics, London, 1991
Greenfeld, Liah, The Sprit of Capitalsim, England: London, 2001
Kate Raworth; Doughunt Economics: Seven Ways to Think Like a 21st Century Economist,
London, 2017
Landes, David, The Wealth and Poverty of Nations, New York, 1999
Landes, David, The Unbound Prometheus: Technological Change and
Industrial Development in Western Europe from 1750 to
the present, New York, 2008
Reinert, Erik, How Rich Coutries Got Rich and Why Poor Countries Stay Poor,
London, 2007
Reinerr, Erik, The Role of the State in Economic Growth, Journal of Economic
Studies, 26.2/5, 1999, pp. 268-326
Steve Keen; Debunking Economics: The Naked Emperor Dethroned? UK, 2011
https://zehabesha.com/neoliberal-economic-policies-are-failing-ethiopia/