
የወለጋ ሰው የሆኑትን ነጌሌ ቦረና ኑሯቸውን መስርተው የቦረናው ልጅ የሆነውን መምህርታዬ ቦጋለን አፍርተውልናል:: መምህር ታዬ አዲስ ኮምፓስ ላይ ዛሬ ባደረገው ቃለ ምልልስ በመንግስት አዋጅ የጅምላ የኃይማኖት ለውጥ ቦረና ውስጥ ተደርጎና አዳራሹ ሞልቶ ሰዎች ዛፍ ስር ሁሉ ይጠመቁ እንደነበር ተነግሮኛል ሲል ይደመጦል::
መምህር ታዬ ቦጋለ እንደ ታሪክ መምህርነቱ ሊያውቀው ሲገባ ያላወቀው ወይም ጠይቆና መርምሮ ሊረዳው የሚገባው ነገር ቢኖር ቦረና ውስጥ የተደረገው [የሱን ቃል ለመዋስ ከተፈቀደልኝ]mass religious conversation (ወይም የጅምላ የኃይማኖት ለውጥ የተካሄደው የዋቆ ጉቱን ጭፍጨፋና የከብቶች ዘረፋን ተከትሎ ሰብዓዊ እርዳታ እናድርስ ብለው በሄዱ በኖርዌይ ሚሽን መካነ እየሱሶች እንጂ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኃዶ ወይም/እና በኢትዮጵያ መንግስት አዋጅ እንዳልነበረ ነው::
የኖርዌዮቹ ሚሽኖች ጨፍጨፋ የደረሰባቸው የቅብር ዘመዶቼ ገና ከደረሰባቸው shock ሳይወጡና ሙታናቸውን ሳይቀብሩ ቅድመ አያቶቼን አያቶቼና እና አባቴን በአንድ ለሊት አዲስ ጥምቀት..አዲስ ስምና አዲስ ኃይማኖት ከብስኩትና ከንፁህ የመጠጥ ውኃ ጋር ሰጥተዋቸው አድረዋል::
ኮርማ ይሰኝ የነበረው ወንድ አያቴን ያዕቆብ ብለውት ነው እንግዲህ እስከዛሬ ጎዳና ያዕቆብ እየተባልኩ የምጠራው እንጂ ከዋቆ ጉቱ ቱሩፋትና ከሚሽን mass religious conversation በፊት ያዕቆብ የሚባል ስም በቤተሰብ ታሪኬ ውስጥ አልነበረም::
ታዲያ የቦረናው ወንድሜና መምህሩ ታዬ ቦጋለ ይህንን የዋቆ ጉቱ ጭፍጨፋ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅማ አዋቂ ፈና ወደ ፕሮቴስታንት የቀየሩት የኖርዌይ ሚሽኖችን ድርጊት በንጉሱ አዋጅ እንደተደረገና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኃዶ እንደተፈፀ አድርጎ ማቅረብ ስለምን ፈለገ?
እርግጥ ነው ምናልባት የዋቆ ጉቱን ጭፍጨፋ ሲሰሙ አገር ወዳድና ድንበር ጠባቂ የሆነውን አርበኛ ማኀበረሰብ የደረሰበትን ጭፍጨፋናበአካል እዛ ድረስ ሄጄ ሀዘኔን ልግለፅ እርዳታም ላድርስ ብለው ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ቦረና ድረስ ሄደው ከእጃቸው አዋቂዎች ሶስት ሶስት ብር…ህፃናት ደግሞ አንድ አንድ ብር ተቀብለዋል::
አባቴም አያቶቼም ከንጉሱ እጅ ስለተቀበሉ ገንዘብ ሲተርኩልኝ ኖረዋል::
የሚሽኖችንም የኃይማኖት ልወጣ ርብርብ ተመልክተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኃዶ ቤተ ክርስቲያን ለሚጠመቅ አዋቂ ስድስት ሜትር አቡጀዱ ለህፃን ሶስት ሜትር አቡጀዱ እንሰጣለን ሲሉ ቦረና ሲዳማዎች(ቦረና ከሱ ቋንቋ ውጭ የሚናገረውን ሁሉ ሲዳማ ብሎ ነው የሚጠራው) አብደዋል ውኃ ለሚረጭላቸው የአመት ልብስ የሚሆን አቢጀዲ ይሰጣሉ ብሎ ልጅ የሌላቸው ልጅ እየተቀባበሉ ሶስት አራቴ ሲጠመቁ ውለውና አጥማቂዎቹን ግራ ሲያጋቡ ውለዋል::
ይህንን ከሆነ መምህር ታዬ ቦጋለ በመንግስት አዋጅ ያለው ምናልባት ቢያብራራው መልካምም ጠቃሚም ነው::
ቦረና ነባር ኃይማኖቱን ትቶ ወደ ክርስትና የመጣው በዋቆ ጉቱ ጭፍጨፋ የዋቆ ጉቱ ተፈናቃዮቹን ባስጠለለው ሚሽን እንጂ በንጉስ አዋጅ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኃዶ እንዳልነበረ መምህር ታዬ ቦጋለ ጠፍቶት ከሆነ የዋቆ ጉቱ ተፈናቃዮች ሰለባዎችና የታሪኩ ባለቤቶች የሆኑ (የጃዋር የመጀመሪያ ሚስቱ እናት ጨምሮ) አባት አያቶቻችን በህይወት አሉና እነሱ መጠየቅ ታሪክ ከማንሻፈፍ ይታደጋል::
በስህተት የተደረገ ወይም የተነገረ ከሆነ ማለት ነው::
ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ታሪክ እጅ መንሻ ወይም የጦር መሳሪያ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል ለብሄርተኞቹ እጅ መንሻ ወይም ዘውዳዊ ስርዓቱን ኦርቶዶክስ ተዋኃዶ ማጥቂያ ከሆነ ግን ጥናትም እርምትም አይኖረውምና በመንገድህ ቀጥል የወንዜ ልጅ
Godana Yacob