ክፍል አንድ
ኤፍሬም ማዴቦ(emadebo@gmail.com)
የምርጫ ሥርዓት ሰፋ የለና አንዳንዴም ውስብስብ የሆነ የዲሞክራሲ ተቋም ነው፣ ይህ ጽሁፍ በተደጋጋሚ ስለምርጫ ሥርዓት እንድጽፍ ለጠየቁኝ በተለይ ጀማሪ ለሆኑ አንባቢያን ታስቦ የተዘጋጀ ነው፣ ጽሁፉ በተከታታይ የሚቀርቡ አራት ክፍሎች አሉት። የምርጫ ሥርዓትን በጥልቀት ለማወቅ ከዚህ ጽሁፍ በተጨማሪ የተለያዩ መጽሃፍትን ማንበብ አስፈላጊ ነው፣ የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
Choosing Electoral Systems: Proportional, Majoritarian and Mixed Systems. Electoral Systems – A Comparative Introduction: New York: Palgrave Macmillan Electoral Systems and Democracy: Baltimore: The John Hopkins University Press. Electoral Systems Design – The New International IDEA Hand Book
የምርጫ ሥርዓት ልብራል ዲሞክራሲንም ሆነ ሶሻል ዲሞክራሲን በሚከተሉ አገሮች ዉስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት የዲሞክራሲ ተቋም ነው። የምርጫ ሥርዓት የተረጋጋ የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዲፈጠር የማድረግ ባህሪይ እንዳለው ሁሉ፣ ማህበረሰብን ቀውስ ዉስጥ ይዞ የመግባት ባህሪይም አለው። አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል በዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ዉስጥ የማሳተፍ ባህሪይ አላቸው፣ አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች ደሞ የማህበረሰብን ውክልና በትክክል ማንጸባረቅም አይችሉም። ኢትዮጵያ ዉስጥ በ27ቱ የህወሓት/ኢሀአዴግ ዘመንም ሆነ ባለፉት 6 አመታት ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ትኩረት ካልተሰጣቸው የዲሞክራሲ ምሶሶዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የምርጫ ሥርዓት ነው። በተለይ የምርጫ ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው? ስንት አይነት የምርጫ ሥርዓቶች አሉ፣በተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች መካከል ያለው ልዩነትና ተመሳሳይነት ምንድነው? ዋና ዋናዎቹ የምርጫ ሥርዓት ስራዎች ምንድናቸው? ከተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች ዉስጥ ለአገራችን ይበጃል ብለን የምንመርጠውን የምርጫ ሥርዓት የምንመርጠው በምን መመዘኛ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት አልተደረገባቸውም። በዚህ የተነሳ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ ልህቁን ጨምሮ አብዛኛው ማህበረሰብ የ”ምርጫ ሥርዓት” ስለሚባለው ቁልፍ የዲሞክራሲ ተቋም ያለው ግንዛቤት አነስተኛ ነው። በምርጫ 2013ቱ ዘመቻ ግዜ ከተገነዝብኳቸው ብዙ ነገሮች ውስጥ አንዱ፣ የምርጫ ሥርዓትና የምርጫ ህግ ተመሳሳይ ጽንሰሃሳቦች ናቸው ብለው የሚያምኑ የፓርቲ መሪዎችና ምሁራን መኖራቸውን ነው፣በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ በግልጽ እንደምንመለከተው በምርጫ ሥርዓትና በምርጫ ህግ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ።
ባለፉት ሠላሳ አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ልህቃኑ፣ምሁሩ፣ተማሪውና ሰራተኛው በተከታታይ ካስተጋቧቸው ህዝባዊ መፈክሮች ዉስጥ አንዱና ዋነኛው “ከአሁን በኋላ በህዝብ ላልተመረጠ መንግሥት አንገዛም” የሚል እጅግ በጣም ግዙፍና ትርጉም አዘል መፈክር ነው። “በህዝብ ላልተመረጠ መንግሥት” የሚለው ሐረግ ህዝብ የመንግሥት ሥልጣን ትክክለኛ ምንጭና ባለቤት እንደሆነና፣የህዝባዊ ሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጠው ደግሞ በምርጫ እንደሆነ ያመለክታል። ምርጫ እንዲኖር ደግሞ የምርጫ ሥርዓት ያስፈልጋል።
ባለፉት ሰባት አመታት ገዢው ፓርቲ ብልፅግናን ጨምሮ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን በስራ ላይ ያለው አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት እንዲቀየር በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፣ወደኋላ ዞር ብለን ስንመለከት የምርጫ ሥርዓታችን ይቀየር የሚለው ጥያቄ ከጠሚ አቢይ አህመድ በፊትም የነበረ ጥያቄ ነው። ለመሆኑ አሁን በስራ ላይ ያለው አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ለምንድነው ወይም ምን ስላላደረገ ነው ይቀየር የምንለው? ይህንን የምርጫ ሥርዓት የሚተካው የምርጫ ሥርዓትስ ምን እንዲያደርግልን ነው የምንፈልገው?
የምርጫ ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው?
በውክልና ዲሞክራሲ ውስጥ ህዝብ ተወካዮቹን የሚመርጥበት፣ የመረጣቸውን ተወካዮቹን ተጠያቂ ማድረግ የሚችለውና ውክልናቸውን ካልወደደው ደግሞ ማስወገድ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብቻ ነው። የምርጫ ሥርዓት ከአንድ ማህበረሰብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር እንዲዛመድ ተደርጎ ከተቀረጸ የተለያዩ ማህበረሰቦችን ማቀራረብ፣ ግጭቶችን ማለዘብና ሌሎችንም ለዲሞክራሲ መለምለም አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የያዘ ሁለገብ የዲሞክራሲ ተቋም ነው።
ዲሞክራሲ ከአገሮች ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንዲዛመድና እንዲመሳሰል ከሚያደርጉት ተቋሞች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የምርጫ ሥርዓት ነው። ከምርጫ ሥርዓት ውጭ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን የሚያፋጥኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፣ የዳበረ የፖለቲካ ባህል መኖር፣ ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ የሚያደርግ የማህበረሰብ ክፍል (Civic Sociey) መኖር፣ ውጤታማና ቀልጣፋ የመንግሥት መዋቅር መኖር፣ ጠንካራ ኢኮኖሚና ሰፊ መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል መኖር ለዲሞክራሲ አስተማማኝነትና ዘላቂነት ዋስትናዎች ናቸው። ሆኖም አነዚህ የዲሞክራሲ ዋስትናዎች የረጂም ግዜ የህብረተሰብ መስተጋብር ውጤቶች ናቸው እንጂ ሞዴል ገንብተን ዲዛይን የምናደርጋቸው ኩነቶች አይደሉም። የምርጫ ሥርዓትን ግን ግባችንን እስካወቅን ድረስ ወደ ግባችን እንዲያደርሰን አድርገን ዲዛይን ማድረግ እንችላለን።
በአንድ አገር ዉስጥ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ፣በአካባቢ አስተዳደር ደረጃ ወይም በከተማ ደረጃ ሊካሄድ ይችላል። የምርጫ ሥርዓት ማለት እነዚህ በተለያየ እርከን የሚደረጉ ምርጫዎች ከተካሄዱ በኋላ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በምርጫ የሚያዙ የኃላፊነት ቦታዎች እንዴት ምርጫውን ላሸነፉ ፓርቲዎችና የግለሰብ ተወዳዳሪዎች አንደሚደለደሉ የሚቀምር ዘዴ ነው። በሌላ አነጋገር የምርጫ ሥርዓት ማለት ህዝብ በምርጫ የሰጠውን ድምፅ ወደ ፓርላማ መቀመጫነት የሚመነዝር ሥርዓት ነው። ይህ ዋነኛው የምርጫ ሥርዓት ስራ ነው፣ሆኖም የምርጫ ሥርዓት ይህንን ዋነኛውን ሥራ ሲሰራ አብሮ የሚሠራቸው ሌሎች ብዙ ሥራዎች አሉ።
በአገር አቀፍ፣ በከልል፣ ወይም በከተማ ደረጃ በሚካሄዱ ምርጫዎች ላይ ተገኝቶ ድምፅ የሚሰጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዜጋ አለ፣ሆኖም ግን እያንዳንዱ ድምፅ ሰጪ ላሰኘው ተወዳዳሪ ድምፁን የሚሰጠው የራሱ በሆነ የግል ምክንያት ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በሚሰጠው ድምፅ ዉስጥ የሚመሳሰሉና የሚለያዩ ግለሰባዊ ፍላጎቶች አሉ፣ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች የሚሰጡት ድምፅ ለተመሳሳይ ዕጩ ተወዳዳሪ ይሆናል፣ ፍላጎታቸው ሲለያይ ደግሞ ድምፅ የሚሰጡትም ለተለያዩ ተወዳዳሪዎች ይሆናል። በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እነዚህን በግለሰቦች ደረጃ የሚሰጡ የተለያዩ ድምጾችን አሰባስበው የትኛው ፓርቲ ምን ያህል የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት አለበት የሚለውን ዐቢይ ጥያቄ በተለያየ መልኩ የሚመልሱ የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች አሉ።
ዛሬ በዓለም ውስጥ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሥራ ላይ የዋሉ ብዙና የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች አሉ። እያንዳንዱ የምርጫ ሥርዓት የራሱ የሆኑ ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሉት። የአንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች ግብ ጠንካራ የሆነ የአንድ ፓርቲ መንግሥት እንዲመሠረት ማድረግ ሲሆን ሌሎች የምርጫ ሥርዓቶች ደግሞ በተቻለ መጠን አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት መመሥረት የሚችልበትን መንገድ ይገድባሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን የሚደረግበት መንገድ በአገሩ ውስጥ በሚገኙ የፖለቲካ ተዋንያን ባህሪይ ላይ እና በፓርቲ ሲስተም አደረጃጀት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል። አንድ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ በማህበረሰቡ ውስጥ ካለው የመንግሥት ቅርፅ (ፓርላማ፣ ፕሬዚደንታዊ ወይም ድብልቅ) እና የመንግሥት አወቃቀር (ፌዴራል፣ አሃዳዊ) ጋር አብሮ እንዲሄድና እንዲሁም የማህበረሰቡን ባህል፣ የፖለቲካ ታሪክና ማህበራዊ አደረጃጀት ከግምት ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ ዲዛይን ከተደረገ የሚከተሉት ጥቅሞች ይኖሩታል-
- በሥልጣንላይየሚገኘው ፓርቲና መንግሥት የተሳለጠ አሠራር እንዲኖራቸው ያደርጋል፣
- መንግሥታዊመረጋጋትንይፈጥራል፣ በተለይ አንድ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑን በተረጋጋ ሁኔታ ለመጨረስ ዕድል ያገኛል
- የህዝብተወካዮችውክልና ጠንካራ ህጋዊነትና ቅቡልነት ይኖረዋል
- የፖለቲካሥርዓቱግጭቶችንና አለመግባባቶችን የማብረድ ችሎታ ይኖረዋል
- ህዝብ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ላይ ያለውተዓማኒነት እያደገይሄዳል
- ህዝብበዲሞክራሲያዊሥርዓቱ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ይጨምራል
እነዚህ ስድስት ነጥቦች ዲሞክራሲን በአዲስ መልክ በሚጀምሩ አገሮች ውስጥ ለዲሞክራሲ መስፋፋትና ዘላቂነት ዋስትናዎች ናቸው። የአንድን አገር የፖለቲካ ታሪክ፣ ባህል፣ የብሔር ብሔረሰቦች ጥንቅርና የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ዲዛይን የተደረገ የምርጫ ሥርዓት ለዲሞክራሲ ዘላቂነት ዋስትና እንደሆነ ሁሉ ለይድረስ ይድረስ ዲዛይን የተደረገ የምርጫ ሥርዓት ደግሞ በፖለቲካ ተዋንያን መካከል መራራቅን፣ አለመግባባትንና ልዩነቶችን በማጦዝ የዲሞክራሲ ነቀርሳ ሊሆን ይችላል።
ህዝብ መሪዎቹን በምርጫ እየመረጠ በሚሾምባቸው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ውስጥ ሁሉ የፖለቲካ ሥርዓቱ ለህዝብ የሚሰጠውን የውክልና አድማስ ስፋትና ጥልቀት የሚወሰነው ሥርዓቱ ምርጫ ለማካሄድ በሚጠቀምበት የምርጫ ሥርዓት ነው። ከዚህ ቀጥሎ የተቀመጡት ሁለት ሠንጠረዦች የአብላጫ ድምፅና ተመጣጣኝ ውክልና ] የምርጫ ሥርዓቶች መራጩ ህዝብ የሰጠውን ድምፅ ወደ ፓርላማ መቀመጫ በመለወጡ ረገድ ምን ያህል እንደሚለያዩ ያሳያል።
ሠንጠረዥ አንድ – አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት
ተወዳዳሪ ፓርቲ |
ፓርቲው ያገኘው ድምጽ |
መቶኛ |
ውጤት |
እናት ፓርቲ |
2510 |
25.1% |
|
ህብር ኢትዮጵያ |
2513 |
25.13% |
አሸናፊ |
ባልደራስ |
2505 |
25.05% |
|
ነፃነትና እኩልነት |
2472 |
24.72% |
|
ጠቅላላ ድምፅ |
10,000 |
100% |
|
የምርጫ ወረዳ መጠን (District Magnitude)= 1
ተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓት (ፓርቲ-ዝርዝር/Party List)
ተወዳዳሪ ፓርቲ |
መጀመሪያ ዙር ድምፅ
ቆጠራ |
ኮታ |
ፓርቲው በመጀመሪያ
ዙር ያገኘው መቀመጫ |
ከጠቅላላ ድምፅ ላይ -ኮታ ሲቀነስ ቀሪ |
ፓርላማ መቀመጫ |
ጠቅላላ ፓርላማ መቀመጫ |
እናት ፓርቲ |
1438 |
714 |
1
|
724 |
1 |
2 |
ህብር ኢትዮጵያ |
1276 |
714 |
1 |
562 |
|
1 |
ባልደራስ |
780 |
714 |
1 |
66 |
|
|
ነፃነትና እኩልነት |
566 |
–
|
|
566 |
1 |
1 |
ኢዜማ |
500 |
– |
|
500 |
|
|
ኢህአፓ |
440 |
– |
|
440 |
|
|
ጠቅላላ ድምፅ = 5000፣
የምርጫ ወረዳው መጠን (District Magnitude) = 5 ኢምፔሪያሊ ኮታ = (ጠቅላላ ድምፅ)/ (ጠቅላላ መቀመጫ + 2) = 5000/(5+ 2)= 714
የምርጫ ወረዳ መጠን ማለት = ከአንድ የምርጫ ወረዳ ለፓርላማ የሚመረጠው ሰው ብዛት በመጀመሪያው ሠንጠረዥ ላይ የተካሄደው ምርጫ በአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ነው፣በምርጫው የተሳተፉት አራቱ ፓርቲዎች ያገኙት ድምፅ ብዛት ተቀራራቢ ነው። ለምሳሌ እናት፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ባልደራስና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲዎች በምርጫ ያገኙት ድምፅ በቅደም ተከተል 2510፣ 2513፣2505 እና 2472 ነው። ሆኖም ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ የቅርብ ተወዳዳሪውን እናት ፓርቲን በሦስት ድምፅ ብቻ ስለበለጠ ወይም ከጠቅላላው ድምፅ 25.13% በማግኘት በምርጫው አሸናፊ ሊሆን ችሏል። በምርጫ ወረዳው ከተሰጠው ጠቅላላ ድምፅ 74.87% የሚሆነውን ድምፅ ያገኙት እናት፣ባልደራስና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ አላገኙም፣ወይም በምርጫ ወረዳው ዉስጥ 74.*% የሚሆነው ድምፅ ባክኗል። አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትና ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ የሚለያዩት እዚህ ላይ ነው።
በሁለተኛው ሠንጠረዥ ላይ የተካሄደው ምርጫ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ነው፣በዚህ የምርጫ ሥርዓት ህግ መሰረት አንድ ፓርቲ በመጀመሪያው ዙር የፓርላማ መቀመጫ ለማኘት በምርጫ ያገኘው ድምፅ ከኮታው መብለጥ አለበት፣ለምሳሌ፣ አምስት ተወካዮች በሚመረጡበት የምርጫ ወረዳ ስድስት ፓርቲዎች ቢወዳደሩና ሁሉም ፓርቲዎች በምርጫ ያገኙት ድምፅ ለምርጫው ከተቀመረው ኮታ በላይ ከሆነ፣ከህዝብ ካገኙት ድምፅ ላይ ኮታው ይቀነስና ከፍተኛ ቀሪ ያላቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት ፓርቲዎች እያንዳዳቸው አንዳንድ የፖርላማ መቀመጫ ያገኛሉ፣ይህ የማይሆን ከሆነና፣ሦስት ፓርቲዎች ብቻ በመጀመሪያው ዙር ቆጠራ ከኮታው በላይ ድምፅ ካገኙ እያንዳንዳቸው አንዳንድ የፓርላማ መቀመጫ ያገኙና ስድስቱም ፓርቲዎች በምርጫ ካገኙት ድምፅ ላይ ኮታው ይቀነስና ቀሪያቸው ከፍተኛ የሆነው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ፓርቲዎች አንዳንድ የፓርላማ መቀመጫ ያሸንፋሉ።
ለምሳሌ፣ በሁለተኛው ሠንጠረዥ ላይ እንደሚታየው እናት ፓርቲ በመጀመሪያው ዙር ሁለት የፓርላማ መቀመጫ አግኝቷል፣ምክንያቱም አንደኛ- እናት ፓርቲ በመጀመሪያው ዙር ቆጠራ በምርጫ ያገኘው ድምፅም(1438) ቀሪውም(724) ከኮታው በላይ ነው፣ ህብር ኢትዮጵያና ባልደራስ ፓርቲዎችም በመጀመሪያው ዙር ቆጠራ በምርጫ ያገኙት ድምፅ ከኮታው በላይ ስለሆነ አንዳንድ የፓርላማ መቀመጫ አግኝተዋል። ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የፖርላማ መቀመጫ ማግኘት የቻለው ከእናትና ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲዎች ቀጥሎ ከፍተኛ ቀሪ (566) ስላለው ነው (የበለጠ ለመረዳት ሁለተኛውን ሠንጠረዥ ሁለትን ይመልከቱ)።
በሁለተኛው ሠንጠረዥ ላይ ስድስት ፓርቲዎች በምርጫው ተሳትፈው አራት ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ አግኝተዋል። በመጀመሪያው ሠንጠረዥ ላይ 2010 ድምፅ አግኝቶ የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፍ ያልቻለው እናት ፓርቲ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በተካሄደው ምርጫ 1438 ድምፅ አግኝቶ ሁለት የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፍ ችሏል።
ሠንጠረዥ አንድና ሁለት ላይ የተካሄዱት ምርጫዎች በአንድ የምርጫ ወረዳ ውስጥ እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ምርጫዎች አይደሉም። ምርጫው በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄድ ቢሆንም ሁለቱ የምርጫ ሥርዓቶች የሚያስገኙት ውጤት በመጀመሪያውና በሁለተኛው ሠንጠረዥ ላይ ከተመለከትነው ውጤት የቁጥር እንጂ የዓይነት ልዩነት አይኖረውም (Quantitative,not qualitative)። ለምሳሌ፣ ምርጫው በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ቢካሄድና የምርጫ ሥርዓቱ አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ቢሆን፣ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ከአራቱ ፓርቲዎች ማለትም እናት፣ ከባልደራስ፣ከህብር ኢትዮጵያና ከነፃነትና እኩልነት ፓርቲዎች አንዱ የፓርላማ መቀመጫ ያሸንፋል። አብላጫ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ መንግሥት የሚመሰርተው አብዛኛውን የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፈ ፓርቲ ስለሆነ፣ ከሦስቱ ፓርቲዎች የበለጠ የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፈው ፓርቲ መንግሥት ይመሰርታል።ይህ ማለት ደሞ ሠንጠረዥ አንድ ላይ የሚታየው የምርጫ ውጤት በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደ ምርጫ ውጤት ቢሆን ኖሮ መንግሥት የሚመሰርተው ፓርቲ ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ ይሆን ነበር ማለት ነው። ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ግን በአንድ የምርጫ ወረዳ ዉስጥ የፓርላማ መቀመጫ የሚያሸንፉ ፓርቲዎች ቁጥር ከሁለት በላይ ሊሆን ስለሚችልና ብዙ ጊዜ አንድ ፓርቲ ከግማሽ በላይ የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፍ ስለማይችል አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት መመሥረት አይችልም። ለምሳሌ፣ ሠንጠረዥ ሁለት ላይ የተካሄደው ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ ቢሆን ኖሮ እናት ፓርቲ ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር የጥምር መንግሥት ለመመሥረት ይገደድ ነበር።
የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን መመዘኛዎች
አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንጀምር ከምንወስናቸው ትልልቅ ውሳኔዎች አንዱ፣ “ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ያስፈልጋል”’ የሚለውን ጥያቄ አግባብ ባለው መልኩ መመለስ ነው። በምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሂደት ውስጥ ደረጃ በደረጃ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከረጂም ግዜ የእርስ በርስ ግጭትና አለመረጋጋት ተላቅቀው ዲሞክራሲን እንደ አዲስ በሚገነቡ አገሮች ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ መወሰን ያለባቸው እጅግ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ የሆኑ ተቋማዊ ውሳኔዎች ናቸው። በታሪክ ወደኋላ ሄደን አገሮች ዲሞክራሲያቸውን ሲገነቡ የምርጫ ሥርዓታቸውን እንዴት እንደመረጡ ስናይ፣ የምርጫ ሥርዓት በብዙ አገሮች ውስጥ የሊህቃኑ ስምምነት ወይም ታስቦበት የተሰራ የጥናትና ምርምር ውጤት ሳይሆን በአጋጣሚ የመጣ የብዙ ኩነቶች ውጤት ነው። አንዳንድ አገሮች ውስጥ የቅኝ ገዥዎች ቅርስ ነው፣ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ደግሞ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ጎረቤት አገሮች የተቀዳ ነው። የምርጫ ሥርዓት ከየትም ይምጣ ከየት፣በአገሮች የወደፊት የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት የዲሞክራሲ ተቋም ነው። የምርጫ ሥርዓት በአንድ አገር ውስጥ በሚገኙ የፖለቲካ ተዋንያን ባህሪይ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያደርግ ተቋም ስለሆነ አንዴ በስራ ላይ ከዋለና የፖለቲካ ተዋንያኑ ከለመዱት በኋላ ለመቀየር አስቸጋሪ የሆነ ተቋም ነው። ስለዚህ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ከመደረጉ በፊት የሚከተሉት የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን መመዘኛዎች በሚገባ መፈተሽና መታየት አለባቸው።
የምርጫ ሥርዓት ዲዛይህ ሂደት ሲጀመር የዲዛይን መመዘኛዎችን ዝርዝር፣ የምርጫ ሥርዓት በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲያደርግልን የምንፈልጋቸው ነገሮች ዝርዝርና፣ ባጠቃላይ እንዲኖረን የምንፈልገው የህግ አውጪ አካልና የህግ አስፈጻሚው አካል ምን መምሰል እንዳለባቸው የሚያመለከት ዝርዝር በግልጽ ተለይቶ መቀመጥ አለበት።የምርጫ ሥርዓት ብዙና የተለያዩ መመዘኛዎች አሉት። አንዳንዶቹ መመዘኛዎች እርስ በርስ የሚጻረሩ አንዳንዶቹ ደግሞ የሚደጋገፉ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የምንቀርጸው የምርጫ ሥርዓት እንዲያደርጋቸው የምንፈልጋቸው ነገሮችም አንዳንዴ እርስ በርሳቸው ሊፃረሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ አዲስ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ ሁለት ዋና ዋና ግቦች ካሉንና፣ አንደኛው ግባችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የግል ተወዳዳሪዎች ተመርጠው ምክር ቤት እንዲገቡ ከሆነና ሁለተኛው ግብ ደግሞ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ከሆነ፥ እነዚህን ሁለት ግቦች አንድ ላይ ይዞልን የሚመጣ የምርጫ ሥርዓት የለም፣ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ግባችንን እና የምርጫ ሥርዓት መመዘኛዎችን ጎን ለጎን በቅደም ተከተል ማስቀመጥና ማነጻጸር አለብን።የምርጫ ሥርዓትን ዲዛይን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ መመዘኛዎች እንደየአገሩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ሊለያዩ ይችላሉ። ሆኖም ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርቡ ዘጠኝ የምርጫ ሥርዓት ቀረፃ መመዘኛዎች በየትኛውም አገር ውስጥ የምርጫ ሥርዓት ቀረፃ ሲደረግ እንደ መመዘኛ ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው።
- ውክልና
ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሚካሄድበት በየትኛውም አገር ውስጥ የምርጫ ሥርዓት ተቀዳሚ ሥራ ህዝብ በምርጫ የሰጠውን ድምፅ ወደ ፓርላማ መቀመጫነት መቀየር ነው፣ ወይም አንድ ህዝብ በምርጫ የሰጠው ድምፅ ቁጥሩን/ብዛቱን በሚመጥን መልክ የፓርላማ ውክልና እንዲኖረው ማድረግ ነው። አንድ ህዝብ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሄዶ ለሚፈልገው ዕጩ ተወዳዳሪ ድምፁን ሰጠ ማለት ለዚያ ተወዳዳሪ ‹‹በኔ ቦታ›› ሆነህ እኔን የሚመለከቱኝን ውሳኔዎች ወስንልኝ ብሎ ውክልና ሰጠው ማለት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የምርጫ ሥርዓቶች ሥራ ይህንን ከህዝብ የሚመጣ ውክልና ህጋዊ እንዲሆን ማድረግ ነው። ስለዚህ ውክልና ከምርጫ ሥርዓት ቀረፃ መመዘኛዎች ውስጥ ቁልፍ የሆነ መመዘኛ ነው።
2.የምርጫ ሂደትን ቀላል፣ ተደራሽና አሳታፊ ማድረግ
ምርጫ ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ወይም የተማረና ያልተማረ ሳይል ለሁሉም ዜጎች እኩል የተሰጠ መብት ነው። የአንድ አገር ዜጎች ይህንን መብታቸውን በሚገባ እንዲጠቀሙ የምርጫ ሂደት ሁሉም የህብረተሰብ አባል በቀላሉ የሚረዳውና እንዲሁም ሳይቸገርና ሳይጨነቅ ወድዶና ፈቅዶ የሚሳተፍበት ግልጽ ሂደት መሆን አለበት። የምርጫ ሂደት ቀላልና ያልተወሳሰበ ነው የሚባለው የድምፅ መስጫው ወረቀት ሰዎች በቀላሉ የሚረዱት ሲሆን፣ ድምፅ ሰጪው ህዝብ የድምፅ መስጫ ቦታዎችን ብዙ ርቀት ሳይጓዝ በቀላሉ ማግኘት ሲችልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ድምፁን ሰጥቶ ወደቤቱ መመለስ ሲችል ነው። ምርጫ የሚካሔድበት ወቅትም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፣ ለምሳሌ፣ አንድ ድምፅ ሰጪ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲሄድ ከዝናብ፣ ከበረዶና ከከፍተኛ ሙቀት መጠበቅ አለበት። ዝናብና በረዶ የምርጫ ሂደትን ማስተጓጎል እንደሚችሉ በብዙ አገሮች በተግባር ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ድምፅ ሰጪው የሚመዘገብበት መዝገብ (Electoral Registry) ወቅቱን ጠብቆ የሚታደስ ሲሆንና የድምፅ አሰጣጡ ሂደት ሚስጢራዊነት የተጠበቀ ሲሆን ድምፅ ሰጪው በምርጫውና በምርጫው ሂደት ላይ እምነት ይኖረዋል። ምርጫ መራጩን ህብረተሰብ ሙሉ በሙሉ አሳታፊ ማድረግ እንዲችል ለእያንዳንዱ ድምፅ ሰጪ እንደየፍላጎቱ ትርጉም መስጠት አለበት፣ ወይም የምርጫው ውጤት የድምፅ ሰጪውን ጥቅምና ፍላጎት ማንጸባረቅ አለበት። ለምሳሌ፣ አንድ ድምፅ ሰጪ ድምፁን ሲሰጥ የሱን ድምፅ ያገኘው ዕጩ ተወዳዳሪ ምርጫውን አሸንፎ ፓርላማ ውስጥ ሲገባ በድምፅ ሰጪው ኑሮና በወደፊቱ የአገሩ አቅጣጫ ላይ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብሎ ማመን አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ድምፅ ሰጪው ህብረተሰብ ድምፄ ይባክናል የሚል ስጋት ውስጥ መግባት የለበትም። የምርጫ ሥርዓት ምርጫን አሳታፊ፣ ተቀባይነት ያለውና ተዓማኒ በማድረግ ረገድ የሚጫወተው አዎንታዊ ሚና ለዲሞክራሲ አዲስ በሆኑ አገሮች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ጉዟቸው ዘመናት ባስቆጠሩ አገሮች ውስጥም በግልጽ ይታያል። ለምሳሌ፣ አውስትራሊያ ከ1919 ዓ.ም. እስክ 1946 ዓ.ም. ድረስ የተጠቀመችበት አማራጭ ድምፅ (Alternate Vote) በመባል የሚታወቀው የምርጫ ሥርዓት የፖለቲካ ተዋንያኑ በምርጫ ውጤት ላይ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጡ አድርጓል። የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት ለብዙ ዓመታት የተጠቀመበትን አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን ‹‹ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ” (Single Transferable Vote) በሚባል ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ከለወጠ በኋላ በ1948 ዓ.ም. የተካሄደው የፌዴራል ሴኔት ሁሉንም የፖለቲካ ተዋንያን ፍላጎት ያረካ የምርጫ ውጤት ሊገኝ ችሏል።
- የፖለቲካፓርቲዎችንማበረታታት
የረጅም ጊዜ የዲሞክራሲ ልምድ ያላቸው አገሮች ልምድ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን አንድ ትልቅ ሀቅ አለ፣ እሱም የአንድ አገር ዲሞክራሲ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚሰነዘሩበትን አደጋዎች ሁሉ ተቋቁሞ የፖለቲካ ሥርዓቱን የተረጋጋ ማድረግ የሚችለው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውስጥ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ፣ውጤታማና እነሱ እራሳቸው የተረጋጉ ሲሆኑ ነው። የምርጫ ሥርዓቶች እንደዓይነታቸውና እንደ ጠባያቸው በፓርቲዎች ጥንካሬና ውጤታማነት ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።
አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች ለአንጃ መፈጠርና ለፓርቲዎች መሰነጣጠቅ አመቺ ሁኔታዎችን ስለሚፈጥሩ እንደዚህ ዓይነት የምርጫ ሥርዓቶች ባሉበት አገር ውስጥ የፓርቲዎች ክምችት ይኖራል። ብዙ ፓርቲዎች ባሉበት አገር ደግሞ ከጥቂት ትልልቅ ፓርቲዎች ውጭ የብዙዎቹ ፓርቲዎች ድርጅታዊ ጥንካሬ የላላ ነው። ይህ የሚነግረን የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ በቅርብ መታየት ከሚገባቸው መመዘኛዎች ውስጥ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥንካሬ መሆኑን ነው። አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር አቀፍ በሆኑና አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ማሰባሰብ በሚችሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲመሰረቱ ይገፋፋሉ። ሌሎች የምርጫ ሥርዓቶች ደግሞ ፓርቲዎች በአካባቢያዊ ጉዳዮች ወይም በዘውግና በሀይማኖት ዙሪያ እንዲመሰረቱ ይገፋፋሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ በዘውግ፣ በቋንቋና በሃይማኖት የተከፋፈሉ አገሮች የምርጫ ሥርዓታቸውን ዲዛይን ሲያደርጉ እነዚህን ሁኔታዎችና ሌሎችንም ብዙ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው።የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ የህልውናቸው መሠረት አድረግው የሚቆሙለት ዓላማ አለ። ለአንዳንድ ፓርቲዎች ይህ ዓላማ ዘውግ፣ቋንቋና ሃይማኖት ሊሆን ይችላል፣ ለአንዳንድ ፓርቲዎች ደግሞ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተቱ የፖለቲካ ዕሴቶችና ፖሊሲዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት እንደሚደራጁ ወይም በምን ዙሪያ እንደሚደራጁ የሚመርጡት በዘፈቀደ አይደለም። በዚህ ምርጫ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ የተለያዩ ተቋሞች አሉ። ከእነዚህ ተቋሞች ውስጥ አንዱ የምርጫ ሥርዓት ነው። የምርጫ ሥርዓት በፓርቲዎች ምሥረታ፣ አደረጃጀትና ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
- በህግአውጪውአካል ውስጥ መንግሥትን የሚቃወምም የሚቆጣጠርም አካል እንዲኖር ማድረግ
የአንድ አገር ፖለቲካ ሥርዓት ጥንካሬና ብቃት የሚለካው ሥልጣን ላይ ባለው የህግ አስፈጻሚና የህግ አውጪ አካላት ብቃትና ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ውስጥ ባለው የተቃዋሚ ኃይል ጥንካሬና መንግሥትን የመቆጣጠር ችሎታ ጭምር ነው። ፓርላማ/ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የአናሳው ክፍል ድምፅ መሰማቱን ማረጋገጥ የሚችሉ፣ የህግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የሚመረምሩና የሚጠይቁ፣ የህግ አውጪው አካል የሚያወጣቸውን የህግ ረቂቆች በጥሞና ተመልክተው መተቸት፣ መቃወምና በህግ ረቂቁ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ከመሆናቸው ባሻገር በሚቀጥለው ምርጫ በሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት የተሻሉ አማራጮች መሆናቸውን ማሳየት አለባቸው። የጠንካራ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ከምርጫ ሥርዓቱ ባሻገር የሌሎች የብዙ ተቋሞች ውጤት ነው። ሆኖም አንድ የምርጫ ሥርዓት የጠንካራ ፓርቲዎችን መፈጠር የማያበረታታ ከሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጅምር ከወዲሁ የተበላሸ ይሆንና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ደካማ ያደርገዋል።
- የምርጫሂደትንዘለቄታዊነት ማረጋገጥ
ምርጫ ዝግጅቱ ተጀምሮና ምርጫው ተካሂዶ የምርጫው ውጤት ለህዝብ እስኪገለጽ ድረስ ከፍተኛ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የሰው ኃይል ግብአት የሚያስፈልገው ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው። ይህ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ትናንሽና ደሃ አገሮችን ብቻ ሳይሆን ትላልቅና ኃብታም አገሮችንም ጭንቀት ውስጥ የሚከት አድካሚና ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ሂደት ነው። ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች የምርጫ ሥርዓታቸውን ሲቀረጹ የመራጩን ህዝብ የትምህርት ደረጃ፣ የሰለጠ የሰው ኃይል መኖርንና የገንዘብ አቅማቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው። አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች ለምሳሌ፣ ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ (Single Transferable Vote) የምርጫ ሥርዓት ባለቸው አገሮች ውስጥ የድምፅ መስጫ ካርዱ ብዙ መግለጫ የሚያስፈልገው ከመሆኑም ባሻገር የድምፅ አሰጣጡም ሆነ በተለይ የድምፅ ቆጠራው ሂደት የሠለጠኑ ሰራተኞችን ብቻ ሳይሆን ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችም የሚያስፈልጉት ውስብስብ ሂደት ነው።
አንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ነው የሚባለው በትንሹ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሁሉንም የሚያሳትፍ ምርጫ ወቅቱን እየጠበቀ በተከታታይ ማካሄድ ከቻለ ነው። ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ በተከታታይ እንዲካሄድ አገሮች ለምርጫው ሂደት የሚያስፈልጉ የተለያዩ የሰው፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ግብአቶችን ማሟላት አለባቸው። በበጀት መጓደል ወይም በድምፅ አሰጣጥና በድምፅ ቆጠራው ውስብስብነት የተነሳ ምርጫዎች የሚስተጓጎሉ ወይም የምርጫው ውጤት የሚዛባ ከሆነ የምርጫው ሥርዓት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ የምርጫ ሥርዓት ሲቀረጽ ከፍተኛ ጥንቃቄና የቅርብ ክትትል ከሚያስፈልጋቸው መመዘኛዎች ውስጥ አንዱ የበጀት ጥያቄ፣ድምፅ የሚሰጥበት መንገድና የድምፅ ቆጠራው ሂደት ውስብስብነት ነው።
- ተራማጅኃይሎች/ለዘብተኞች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ማድረግ
ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በብሔር፣ በሃይማኖትና በቋንቋ በተከፋፈሉ አገሮች ውስጥ ከዋና ዋናዎቹ የምርጫ ሥርዓት ግቦች ውስጥ አንዱ የብሔርና የሃይማኖት አክራሪነትን ማለዘብ ወይም ተራማጅ አስተሳሰቦችን ማበረታታት ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በብሔር ፖለቲካ ውስጥ በታቃራኒ ጫፎች ላይ የሚገኙ ተቀናቃኝ ኃይሎች ከፖለቲካ መቆሳሰል ተላቅቀው በምርጫ ወቅት አንዱ ለአንዱ መመረጥ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉበትን የምርጫ ሥርዓት መርጦ መቅረጽ ነው። አንዳንድ የ ምርጫ ሥርዓቶች ከፍጥጫ ይልቅተቀራርቦ መነጋገርን፣ ከጥላቻ ስብከት ይልቅ በአሰባሳቢ የጋራ ሃሳቦች ዙሪያ መወያየትን እና ባጠቃላይ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በውይይት መፍታትን ያበረታታሉ።
- የግለሰብተወካዮችንለመረጣቸው ማህበረሰብ ተጠያቂ ማድረግ
አንድ ድምፅ ሰጪ በምርጫ ወቅት ከብዙ ተወዳዳሪዎች ውስጥ አንዱን መርጦ ድምጹን የሚሰጠው በዕጩ ተወዳዳሪው ላይ ባለው እምነትና ዕጩ ተወዳዳሪው በምርጫ ወቅት አደርጋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ነው። በዚህ መንገድ የተመረጠ ዕጩ ተወዳዳሪ ምርጫውን አሸንፎ ምክር ቤት ከገባ በኋላ ለመራጩ ማህበረሰብ የገባውን ቃል የማይፈጽም ከሆነ፣ ድምፅ ሰጪው ይህንን ተወካይ ቃሉን ባለማክበሩ ተጠያቂ ማድረግ መቻል አለበት። ድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ እንዲወክሉት የመረጣቸውን ተወካዮቹን ተጠያቂ የማድረግ ችሎታው እንደየምርጫ ሥርዓቱ ይለያያል። ተጠያቂነት የዲሞክራሲ አንዱ ምሶሶ ነውና፣ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ በሚገባ መታየት ካሉባቸው መመዘኛዎች ውስጥ አንዱ መሆን አለበት።
8.መንግሥትን ተጠያቂ ማድረግ
ከውክልና ዲሞክራሲ የማዕዘን እራሶች ውስጥ አንዱና ትልቁ የመንግሥት ባለስልጣኖችና የህዝብ ተወካዮች ለመረጣቸው ህዝብ ተጠያቂዎች መሆናቸው ነው። በሚቀጥለው ክፍል በስፋት እንደምንመለከተው አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች ተጠያቂነትን ያሳንሳሉ። ለምሳሌ፣ ዝግ ፓርቲ-ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ማን መወዳደር እንዳለበትና በምርጫ ካርዱ ላይ በሚወጣው የስም ዝርዝር ላይ የየትኛው ተወዳዳሪ ስም መቅደም እንዳለበት የሚወስኑት የፓርቲ መሪዎች ናቸው፣ አንድ ፓርቲ በወረዳ ደረጃ ምርጫውን ሲያሸንፍ የምርጫ ወረዳውን ወክሎ ፓርላማ ውስጥ የሚገባው ሰው ማን መሆኑን የሚወስኑትም የፓርቲው መሪዎች ናችው። እንዲህ ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ለህዝብ ተጠያቂ የሚሆኑት ፓርቲዎች ናቸው እንጂ ፓርቲዎችን ወክሎ ፓርላማ ወይም ምክር ቤት የገባው ግለሰብ አይደለም። ህዝብ በፓርቲና በግለሰብ ደረጃ ተወካዮቹን ተጠያቂ ሲያደርግ ልዩነቱ የሰማይና የምድርን ያክል ነው። ከምርጫ ሥርዓቶች ሁሉ የህዝብ ተወካዮችን ድምፅ ለሰጣቸው ህዝብ ተጠያቂ በማድረግ የመጀመርያውን ደረጃ የያዘው ብዙሃንነት/Plurality በመባል የሚታወቀው የምርጫ ሥርዓት ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ የህዝብ ተመራጮች ለመረጣቸው ህዝብ ቅርብ ናቸው። አንድ የህዝብ ተወካይ ለመረጠው hብረተሰብ ተጠያቂ ነው ሲባል ይህ የህዝብ ተወካይ በምርጫ ወቅት ለህዝብ አደርጋለሁ ብሎ የገባውን ቃል ፈጽሟል ወይም አልፈጸመም ከሚለው ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ለህዝብ አደርጋለሁ ብሎ የገባውን ቃል ያልፈጸመ፣ማድረግ የማይገባውን ነገር ያደረገ ወይም ውክልናውን በሚገባ ያልተወጣ የህዝብ ተወካይ እንደገና የመመረጥ ዕድሉ የጠበበ ነው። በብዙ አገሮች ውስጥ ህዝብ ሃላፊነታቸውን የማይወጡ ተወካዮቹን ጠርቶ መጠየቅ ይችላል፣ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ደግሞ የሥልጣን ዘመናቸው ከማለቁ በፊት ውክልናቸውን ማንሳት ይችላል።
- ዓለምአቀፍየምርጫ ደረጃ ማሟላት
በመሠረቱ ምርጫ የአገሮች ጉዳይ ነው። የሚካሔደውም በአገር ደረጃ ነው።በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ምርጫ የለም። ሆኖም ምርጫ ከሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች ለምሳሌ፣ ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሂደት ስለሆነና ሰብዓዊ መብቶች ደግሞ በይዘታቸው ዓለምአቀፋዊ ስለሆኑ በየአገሩ ውስጥ የሚካሄደው ምርጫ ማሟላት ያለበት ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎች አሉ።
ሁሉም አገሮች ተስማምተው ያፀደቁትና ህጋዊ ተፈፃሚነት ያለው አንድ ወጥ የሆነ ዓለም አቀፍ የምርጫ ህግ ባይኖርም ዛሬ በየትኛውም አገር ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ማሟላት ያለባቸውን መለኪያዎች በተመለከተ ዓለም አቀፍ ስምምነት አለ። ለምሳሌ፣ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ለሁሉም እኩል መሆኑ፣ መምረጥ የሚችለውን ዜጋ ሁሉ የሚያሳትፍና ጊዜውን ጠብቆ የሚካሔድ መሆኑ፣ ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ መኖሩ፣ ተገድዶ ወይም ተማልሎ ድምፅ አለመስጠትና “አንድ ሰው፣አንድ ድምፅ” የሚሉ መርሆዎች ዓለም አቀፍ የምርጫ ደረጃ መለኪያዎች ናቸው። ይህ ማለት ደግሞ አንድ ምርጫ ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት አንዲኖረው ወይም ዓለም አቀፍ የምርጫ ደረጃዎችን አሟልቷል እንዲባል እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን መርኆዎች ማሟላት አለበት ማለት ነው።
በአንድ አገር ውስጥ ምርጫ ለዜጎች ይዞት ከሚመጣው መሠረታዊ መብቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ውክልና ነው። በአገሮች ውስጥ ያለው የውክልና ስፋትና ጥልቀት ደግሞ በአገሮቹ ውስጥ ካለው የምርጫ ሥርዓት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። አገሮች ይህንን ወይም ያንን የምርጫ ሥርዓት መምረጥ አለባችው የሚል ዓለም አቀፍ ህግም ሆነ መመሪያ የለም። ሆኖም በአንድ አገር ውስጥ ምርጫ ሁሉም ዜጎች በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ መወከላቸውን፣ የወንዶችና ሴቶች እኩልነት መረጋገጡን፣ የአናሳ ቡድኖችና የአካል ጉዳተኞች መብት መከበሩን ማረጋገጥ አለበት የሚሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ ዓለም አቀፍ የፖለቲካና ሲቪል መብቶች ስምምነትና ሌሎችም አህጉራዊ ስምምነቶች አሉ።
ከላይ ያየናቸው ዘጠኝ ነጥቦች የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ በከፍተኛ ጥንቃቄ መታየት ያለባቸው መመዘኛዎች ናቸው። በአንድ አገር ውስጥ አንድ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ ይዟቸው መምጣት ያለበትና እንዳይኖሩ መከላከል ያለበት ነገሮች አሉ። የእነዚህ ሁለት ነገሮች ዝርዝር ሙሉ በሙሉ ከታወቀና ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ ሌላው በጥንቃቄ መታየት ያለበት ጉዳይ እነዚህን የምርጫ ሥርዓቱ ይዟቸው መምጣት ያለበትና እንዳይኖሩ መከላከል ያለበትን ነገሮች እንደየጠባያቸው ማስተናገድ የሚችል የምርጫ ሥርዓት ካሉን አማራጮች ዉስጥ መምረጥ ነው። የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ የዲዛይኑን ሂደት የሚያግዙ አያሌ መሣርያዎች አሉ። የምርጫ ወረዳ መጠን (District Magnitude)፣ የምርጫ ወረዳ የሚከለልበት ደንቦችና መመሪያዎች፣ የምርጫ ካርድ ቅርፅና ይዘት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ሚና፣ የኮታ ዓይነትና ድምፅ የሚሰጠው ህዝብ ለምርጫ የሚመዘገብበት መንገድ ዋና ዋናዎቹ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን መሣርያዎች ናቸው። እነዚህ የዲዛይን መሣርያዎች በዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ የተለያየ ስለሆነ አንድ የምርጫ ሥርዓትዲዛይን ሲደረግ እነዚህ መሣርያዎች በቡድንም በነጠላም እየተመረጡ ሥራ ላይ ሲውሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።እነዚህን የዲዛይን መሣርያዎች ስንጠቀም መሣርያዎቹን አስመልክቶ ያለን መረጃ ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑን መረጋገጥ አለበት። ለምሳሌ፣ በአንድ የምርጫ ወረዳ ውስጥ ስላለው የህዝብ ብዛት፣ የህዝብ አሰፋፈርና ብዝኃነት (Population Distribution and Diversity) መረጃ ሳይኖረን የምርጫ ወረዳ መጠን (District Magnitude) ውይይት ውስጥ መግባት አይቻልም። የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን መሣርያዎች ውጤታማነት የሚለካው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውስጥ ባሉት የተለያዩ ተቋሞች ዓይነት፣ ጥራትና ጥንካሬ መጠን ነው። ለምሳሌ፣ የፓርላማ ሥርዓት ባለባቸው አገሮችና ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲ ባለባቸው አገሮች ውስጥ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን መሣርያዎች ውጤታማነት ይለያያል።
አዲስ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን የሚያደርጉ አገሮችም ሆኑ የምርጫ ሥርዓታቸውን መቀየር የሚፈልጉ አገሮች ከላይ የተመለከትናቸውን ዘጠኝ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን መመዘኛዎች በስፋትና በጥልቀት መመልከት አለባቸው። እነዚህ መመዘኛዎች አንዳንዶቹ እርስ በርስ የሚቃረኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሽ የማይገናኙ ስለሆኑ አንድ አገር ውስጥ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ እነዚህን መመዘኛዎች በቅደም ተከተል ማስቀመጥና የምርጫ ሥርዓቱ ዲዛይን ከሚደረግላቸው አገሮች ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማገናዘብ ያስፈልጋል።የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሂደት ከመጀመሩ በፊት የምርጫ ሥርዓቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስወገድ አለበት ተብሎ የሚታመንባቸውን ዋና ዋና ነገሮች ዘርዝሮ በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ጊዜ እየጠበቁ ከሚመጡ ችግሮች ያድነናል። ለምሳሌ፣ በብሔርና በቋንቋ በተከፋፈሉ አገሮች ውስጥ የአናሳ ቡድኖችን ውክልና የሚያሳንሱ እርምጃዎች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ስለዚህ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ብዙ ብሔሮች በሚገኝባቸው አገሮች ውስጥ ዲዛይን የሚደረገው የምርጫ ሥርዓት የእያንዳንዱ ብሔር በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ መወከሉን ማረጋገጥ አለበት። አለዚያ የምርጫ ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ ህጋዊነትና ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ እየገባ የግጭትና ያለመግባባት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በአለማችን ላይ ብዙ ህብረ-ብሔር አገሮች አሉ፣ ሆኖም የሁሉም አገሮች ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድና የዲሞከራሲ ልምድ ይለያያል፣ ይህ የሚያሳየን አገሮች ህብረ-ብሔር ስለሆኑ ብቻ አንድ አይነት የምርጫ ሥርዓት እንደማያስፈልጋቸው ነው። ለምሳሌ፣ ናይጄሪያ ውስጥ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ለተለያዩ ብሔሮች ውክልና ሊሆን ይችላል፣ ጋና ውስጥ ደግሞ ቅድሚያው ጠንካራና የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር ማድረግ ሊሆን ይችላል። እነዚህን ሁለት የተለያዩ ግቦች አጣምሮ የያዘ የምርጫ ሥርዓት ስለሌለ ጋና እና ናይጄሪያ በሁሉም መልኩ ተመሳሳይ የሆነ የምርጫ ሥርዓት ሊኖራቸው አይችልም። እንደዚህ ሲባል ግን ናይጄርያ ጠንካራና የተረጋጋ መንግሥት አያስፈልጋትም ወይም ጋና ውስጥ የብሔረሰቦች ውክልና በቀላሉ መታየት አለበት ማለት አይደለም። የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሂደትን አስቸጋሪና ውስብስብ የሚያደርጉትም እንደዚህ ዓይነት አሻሚ ምርጫዎች ናቸው።
ከላይ የተመለከትናቸው መረጃዎች ሁሉ የሚያሳዩን የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ ብዙ ጊዜ፣ ብቃት ያለው የሰው ኃይልና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ነው። ለመሆኑ ማነው የአንድን አገር የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ማድረግ የሚገባው? አንድ አገር አዲስ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲያደርግም ሆነ በሥራ ላይ ያለውን የምርጫ ሥርዓት መቀየር ሲፈልግ ትልቁን የዲዛይን ሥራ ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው አገር በቀል ጠበብቶች ናቸው። ዓለም አቀፍ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ጠበብቶች የቴክኒክ ዕርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ። ነገር ግን የአንድን አገር የፖለቲካ አውድ፣ የማህበረሰቡን የፖለቲካ ባህልና ማህበራዊ አደረጃጀት ጠንቅቀው የሚያውቁ የአገሩ ሰዎች ስለሆኑ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ የዲዛይኑን ሂደቱን በበላይነት መምራት ያለባቸው የአገር ውስጥ ጠበብቶች መሆን አለባቸው። ክፍል ሁለት ላይ የምርጫ ሥርዓት ግቦችንና የምርጫ ሥርዓት አይነቶችን እንመለከታለን።
ክፍል ሁለት ሐሙስ ሐምሌ 24 ይቀርባል