ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ሐምሌ 22፣ 2017(July 29, 2025)
ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በፈረንጆች አቆጣጠር በ25. 7. 2025 በዘሃበሻ ላይ ባወጣው የእንግሊዘኛ ጽሁፉ፣ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስተር ተብዬው ስንትና ስንት ወንጀል እየሰራ፣ በተለይም በአማራው ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እያካሄደና ተግባራዊ በሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲም ምክንያት የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ አጠቃላይ ድህነት በሰፈነበት ጊዜና ህዝባችንም ሰብአዊ መብቱ በተረገጠበት ወቅት…ወዘተ. ቁጥራቸው ይህ ነው የማይባል ፖለቲከኛ ነን ባዮችና ምሁራን ለአቢይ አህመድ አገዛዝና ለራሱ ለጠ/ሚኒስተሩም ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚሰጡት በመፀፀት አስነብቦናል። ፖለቲካዊ ድጋፋቸው ግን በምን መልክ ይገለጽ እንደሆነና፣ ከምንስ በመነሳት ወይም በምንስ ምክንያት እንደሚደግፉት አልባራራልንም። በሌላ ወገን ደግሞ በአገራችን ምድር አንድን አገዛዝ ወይም የፖለቲካ ድርጅት ነኝ ባይን ወይም የታወቀ ግለሰብን በጭፍን መደገፍ የተለመደ ስለሆነ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ አቋማቸውን ለማወቅ ቸግሮች አጋጥመውት ሊሆን ይችላል። እሱ ብቻ ሳይሆን በእብዛኛዎቻችን ዘንድም ያለ ችግር በመሆኑ የአብዛኛዎችን የፖለቲከኛ ነን ባዮችን አቋም እንደዚህ ነው ብሎ በትክክል ለመናገር ያስቸግራል። ለማንኛውም ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ያስነበበን ነገር ትክክል ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ግን የሚወቅሳቸውን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችንና ምሁራን ነን ባዮችን ምን ዐይነት የፖለቲካ አቋም ወይም ርዕይ እንዳላቸው በግልጽ አልነገረንም። በደፈናው ብቻ ነገሩን በመተንተን ሳይሆን ቁጥራቸው ትንሽ ነው የማይባል ፖለቲከኞችና ምሁራን ነን ባዮች የአቢይ አህመድን ፖለቲካ እንደሚደግፉ በመፀፀት አስነብቦናል።
በአጠቃላይ ሲታይ በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር በሳይንሳዊ፣ በፍልስፍናና በቲዎሪ ላይ የተመሰረተ ጠለቅ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ያልተለመደ ወይም የማይታወቅ በመሆኑ ማንም እየተነሳ ምንም ዐይነት የፍልስፍና መሰረት ሳይኖረው፣ ወይም ደግሞ ይህንን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም ነው የማካሄደው ሳይል በፖለቲካ ዓለም ውስጥ በመግባት ግራ ሲያጋባ ይታያል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ግልጽነት ላለውና ጭግርን ለሚፈታ የትግል ዘዴ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በሌላ አነጋገር ግልጽነት ያለውና በመሰረተ-ሃስባና በርዕይ ላይ የተመሰረተ ትግል ማካሄድ አይቻልም ማለት ነው። ከዚህም በላይ ተጨባጭ ሁኔታዎችን፣ ማለትም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህላዊ ሁኔታዎችንና፣ በግልጽ የሚታዩ እንደከተማ አገነባብ የመሳሰሉትንና፣ አብዛኛው ህዝብ ደግሞ በቆሻሻ ቦታዎች እየኖረ እያየ ይህንን እንደ ኖርማል አድርጎ በመውሰድ የሚያነብበትና የሚተነትንበት ሳይንሳዊና የቲዎሪ መሳሪያ ስለሌው በደፈናው ብቻ እየተነሳ ፖለቲከኛ ወይም ምሁር ነኝ በማለት የሚሆነውን የማይሆነውን ነገር ሲዘላብድ ይታያል። አብዛኛው ህዝብም ነገሮችን የማገናዘብና፣ ለምን በቆሻሻና በድህነት ዓለም ውስጥ እንደሚኖር ራሱን ስለማይጠይቅ ተጋጊጠውና ተኳኩለው በየቴሌቪዥኑ የሚቀርቡትንና የቃለ-መጠይቅ መልስ የሚሰጡትንና የሚናገሩትን ሲሰማ እነዚህን ሰዎች እንደ ዕውነተኛ ፖለቲከኞችና ምሁራን ማየቱ የሚያስገርም አይደለም። ይህ ዐይነቱ ችግር በእኛ አገር ብቻ ያለ ሳይሆን እንደቫይረስ በመስፋፋት ስንትና ስንት የፍልስፍና፣ የኢኮኖሚ፣ የሶስይሎጂ፣ የፖለቲካ ቲዎሪና የተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር በተካሄደበትና በመጽሀፍም ተጽፎ እንደልብ በሚገኝበት የካፒታሊስት አገሮች ውስጥም ሳይቀር ያለ ችግር በመሆኑ ባለፉት አስርና አስራአምስት ዓመታት ፖፑሊስት የሆኑ፣ የፋሺስት ወይም የቀኝ አመለካከት ያላቸው በመደራጀትና በመወዳደር የምርጫ ውድድር በሚኖርበት ጊዜ በብዙ ድምጽ በመመረጥና ፓርሊያሜንት ውስጥ በመግባት ለአገዛዝ የማያመች አስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ይገኛሉ። በተለይም ከሌላ አገር መጥተው በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ለብዙ ዓመታት እየሰሩ የሚኖሩና ቀረጥም የሚከፍሉና ተወልደው ተዋልደው የሚኖሩ በዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ ውዥንብር የተነሳ ግራ ተጋብተው ይገኛሉ። ይህ ጉዳይ በተለይም ትረምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ ከተመረጠ በኋላና አስተዳደሩን በቁጥጥሩ ካስገባ በኋላ አፍጦ አግጦ ያለ ችግር ነው። ሰለሆነም የተገለፀላቸው ምሁራንና ሳይንቲስቶች ግራ በመጋባት የፖለቲካ ግፊቱን ለመቋቋም የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አንዳንድ ከመንግስት የተወሰነ ድጋፍ የሚያገኙ የታወቁ ዩኒቨርሲቲዎችም በጀታቸው እንዲቀነስ፣ ከዚህ ቀደም የተሰጣቸውንንም የተወሰነውን መልሰው ለመንግስት እንዲከፍሉ ማሳሳቢያ ተስትጧቸዋል። በአጠቃላይ ሲታይ ጠለቅ ያለ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ውይይትና ክርክር እንዳይካሄድ እየተደረገ ነው። መጠየቅና መከራከር እንደ ወንጀለኝነት እየተቆጠረ ይገኛል። በአጭሩ ነገሮችን በወዳጅና በጠላት ወይም በጥቁርና በነጭ እየከፋፈሉ ማየት የጊዜው ባህል ሆኗል። ዝም ብሎ እንደከብት መነዳት የዘመኑ ፈሊጥ ሆኗል ማለት ይቻላል።
ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከመምጣቴ በፊት ምሁራዊና ፖለቲካዊ አመለካከት ምን ማለት ነው? እንዴትስ እነዚህ ዐይነት መሳሪያዎች ሊፈልቁ ቻሉ? በሚለው ላይ ትንሽ ማብራሪያ ልስጥ። በአጠቃላይ ሲታይና ወደ ኋላ የጊዜ ጉዞ(Going back in Time) ስናደርግ ዛሬ የሰው ልጅ የሚጠቀምባቸው ነገሮች፣ መጓጓዣዎች፣ የአኗኗር ሁኔታዎች፣ የመገናኛ መስመሮች፣ ኢንተርኔትና ስማርት ፎንና ሌሎችም ነገሮች በሙሉ ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆኑ የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ የፈጠራቸው ነገሮች ናቸው። አብዛኛዎቹ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶች፣ እንዲሁም ፍልስፍናና ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማንበቢያ የቲዎሪ መሳሪያዎች በሙሉ ራሳቸውን ባስጨነቁና፣ የሰው ልጅም ከእንስሳ የተሻለ ስለሆነ በዚህ ዐይነት አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ መኖር የለበትም በማለት ራሳቸውን በሰዉ ጥቂት ተመራማሪዎች አማካይነት ነው። በተለይም ዕድገትንና ሌላ አስተሳሰብን የሚጠሉና በራሳቸው አኗኗር ብቻ የሚደሰቱ አገዛዞች ስለነበሩ እነዚህን ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ መዋጋቱ የዘመኑ የትግል ዘዴ ነበር።
ወደ ፖለቲካ ስንምጣም ፖለቲካና ፖለቲካዊ አመራር፣ እንዲሁም መንግስታዊ አወቃቀር በአንድ ህዝብና አኗኗሩ፣ እንዲሁም የመፍጠር ኃይሉ ላይና የተሻለ ኑሮ የመመስረቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅዖ ስለሚኖራቸው ከሶስት ሺህ ዓመት በፊት ይኖሩ የነበሩ ተመራማሪዎች ይህንን ችግር ለመፍታት ይጨነቁ የነበሩት የጭንቅላትን ጉዳይ፣ ማለትም ጭንቅላት በትክክል የመቀረፁን ወይም ያለመቀረፁን፣ ከልጅነት ጊዜ ጀምሮ የሚሰጡትን የትምህርት ዐይነቶችና አስተዳደግን አስመልክቶ ምርምር በማድረግ ነው። ምክንያቱም ማንኛውም መጥፎም ሆነ ጥሩ ነገር በጭንቅላት አማካይነት ስለሚውጠነጠን ወይም በሚገባ ሰለሚታሰብና ስለማይታሰብ የግዴታ በጭንቅላት ላይ ከፍተኛ ምርምር ማድረግ ነበረባቸው። ፖለቲካ የሚባለውም ነገር በጭንቅላት አማካይነት በዘፈቀደ ወይም ደግሞ በተጠና መልክና በፈላስፋዎች በመደገፍ ወይም ባለመደገፍ ስለሚካሄድ የግዴታ በአንድ ህዝብ በሰላም የመኖር ወይም ያለመኖር፣ ስነ-ስርዓት ያለው ኑሮ ለመመስረት ወይም ያለመመስረት፣ ከተማዎችንና መንደሮችን በዕቅድና ለሰው ልጅ መኖሪያ አድርጎ ጥበባዊ በሆነ መልክ መስራት ወይም አለመስራት፣ ፖለቲካዊ አደረጃጀት መኖርና አለመኖር፣ ንቃተ-ህሊና መዳበርና አለመዳበር… ወዘተ. እነዚህ ነገሮች በሙሉ ከፖለቲካ አወቃቀርና የመንግስትን መኪና ከጨበጡ ሰዎችና ካላቸውም ዕውቀት ጋር፣ ወይም ፍልስፍናዊ አመለካከት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ የሰውን ልጅ ከጥፋቱ አድነው ተብለው እግዚአብሄር ከሰማይ እንደላካቸው በተለይም ከሶስት ሺህ ዓመት ጊዜ ጀምሮ ማሰብና በትክክል መስራት፣ እንዲሁም ለምንድነው ነገሮች በዚህ መልክ የሚታዩት፣ ለምንስ በሌላ መልክ አይታዩም፣ የሰው ልጅ ማለት ምን ማለት ነው? ከየት ነው የመጣው፣ በዚህች ዓለም ላይስ ምንድን ነው የሚሰራው? ወይንስ ተልዕኮው ምንድ ነው? የመጨረሻ መጨረሻስ ወዴት ነው የሚያመራው? በአጠቃላይ ሲታይ የህይወት ትርጉሙ ምንድን ነው? የሚለውን በማንሳት የሰው ልጅ ከእንስሳ የተለየና በማንም ራሱን አሳብጦ በሚገኝ ራሱ የስው ልጅ ፍጡርም በሆነ መነዳት እንደሌለበት ለማመለክት ሞከሩ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ምሁራዊ አስተሳሰብ ሊዳብርና መልክም ሊይዝ የቻለው። ለዚህ ደግሞ መሰረተ-ሃሳቦች ወይም መመሪያዎች በሚገባ ተነድፈውና በእየ ኤፖኩ እየተሻሻሉ፣ በመሀከሉ ደግሞ በአብዛኛው መልክ እየተዘበራረቁና ዕውቀት የሚመስሉ፣ ይሁንና የተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ሁኔታ፣ እንዲሁም የህብረተሰብን ህግና አመሰራረት በሚመለክት ረገድ ጭንቅላትን የሚጨፍኑና አስተሳሰብን የሚያዛንፉ ነገሮች በመፈጠራቸው የተነሳ በ21ኛው ክፍለ-ዘመንም የማቴሪያል ሁኔታዎችም ቢሻሻሉምና ተትረፍርፈውም ቢገኙ፣ በአንድ በኩል በጣም ጥቂት የሆነው ናጥጦ ሲኖርና ጦርነትን ሲያካሂድ፣ ሌላው ደግሞ ተቸግሮና በጭንቅላቱ ላይ የቦንብና የጥይት ናዳ እየወረደበት የተረገመ ፍጡር ይመስል ይኖራል። ስቴፓን ሜስትሮቪክ የሚባለው የሶስዮሎጂ ምሁር የባርቤሪያን መንፈስ ወይም ቴምፕራሜንት(The Barbarian Temperament) በሚለው መጽሀፉ ውስጥ አረመኔያውነትና ስልጣኔ እዚያው በዚያው ይኖራሉ በማለት እንዳስቀመጠው ነገሮች ተዘበራርቀው ይገኛሉ። ይሁንና ግን ይህን ዐይነቱ ሁኔታም ራሱ ፀሀፊው በትክክል እንዳስቀመጠውና ሌሎችም ለምሳሌ ሊዎ ኮፍለር የተባለው የማርክሲስት ምሁር እንዳለው አንድ ቦታ ላይ ምናልባትም በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በጊዜው የመደብ ትግል ቀስ በቀስ እየዳበረ በመጣበት ጊዜ የሰብአዊነት እንቅስቃሴ ደበዛው እንደጠፋና የከበርቴውም መደብ ተልዕኮውን ለማሟላት ባለመቻሉ የኋላ ኋላ ላይ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ላይ በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ፋሺዝም የሚባለው እንቅስቃሴ በመፈጠርና በመዳበር፣ እንዲሁም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን በማፍራትና ጭንቅላታቸውን በመሸፈን አንደኛው የሰው ልጅ ሌላ ዘር ነው ብሎ በገመተውና እንደጠላቱ በፈረጀው ላይ በመነሳት በመጀመሪያ ስድስት ሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዲዎችን እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልክ ሲገድል፣ ህፃናት ደግሞ ቆዳቸው ከሰውነታቸው እየተገፈፈ በመውጣት ህይወታቸው እንዲያጣ ተደርጓል። ይህ ዐይነቱ አረመኔያዊ ድርጊትም የኋላ ኋላ ላይ ወደ 50 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ህይወት ማለፍና ለታሪክ ውድመት ምክንያት ሊሆን ችሏል። የሚያስገርመው ነገር በዚያው ዘመን የሴሚቲክ ወይም የአይሁዲ ዘር ጥላቻ ያለባቸው የታወቁ ምሁራን ወይም ፈላስፋዎች ሳይቀሩ የሂትለርን ድርጊት አወድሰዋል፤ ደጋፊዎቹም ነበሩ።
ለማንኛውም ቀደም ብሎ በግሪክ ምድር የተፀነሰው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ወደ ዘጠኝ መቶ ዓመታት ያህል ከተዳፈነ በኋላ፣ በአስራ አምስተኛው፣ በአስራስድስተኛው፣ በአስራሰባተኛውና በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን እንደገና በመቀጣጠልና ሌላ አቅጣጫን በመያዝና በመስፋፋትም፣ “ጊዜው ዝም ብሎ በጭፍን መገዛት ወም መነዳት አይደለም፣ ጊዜው የብርሃንና የምርምር፣ እንዲሁም ጥያቄ በመጠየቅ የመፍጠር ጊዜ ነው “ በማለት በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከፍተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሊዳብር ቻለ። ከዚህን ጊዜ በኋላም በአስራአምስተኛው፣ በአስራስድስተኛው፣ በአስራሰባተኛውና በአስራስምንተኛው ክፍል-ዘመን በሚገባ ያልዳበሩ እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉና፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ እንደሶስዮሎጂ የመሳሰሉትም በመፈጠራቸውና በመዳበራቸው ልዩ ዐይነት የዕውቀት አቅጣጫ ተቀየሰ። በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመነ ጀምሮ ደግሞ ካፒታሊዝም እንደ ስልተ-ምርት እየዳበረ ሲመጣና ቀደም ብሎም በተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት ምክንያት የተነሳ ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ አወቃቀርም በመፈጠሩ የተነሳ እንደማርክሲዝም የመሳሰሉ ሳይንሳዊ ቲዎሪዎች ከጊዜው ሁኔታ በመነሳት ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማንበቢያ ዘዴ ለመሆን ቻሉ። በኢንዱስትሪ አብዮት የተነሳና በካፒታሊዝም መዳበር ምክንያት በተለይም በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ የስራና የአኗኗር ሁኔታው ሊሻሻል ባለመቻሉ፣ እንዲሁም ደግሞ ካፒታሊስት የሚባለው መደብ ትርፍን ከማትረፍና ከማካበት በሰተቀር ለሰራተኛው መደብና ስለአስራሩ ሁኔታ የማያስብ ስለነበረና፣ ጨቋኝም ስለነበር ይህንን ሁኔታ የተመለከቱ ምሁራን ጠለቅ ብለው በመመራመር የራሳቸውን ቲዎሪ ማፍለቅ ጀመሩ። ይህ የሚያመለክተን ወይም የሚያረጋግጠው ምንድነው? በአውሮፓ ምድር ውስጥ በጭፍን መነዳት፣ ወይም አንድን አምባገነናዊ አገዛዝ ዝም ብሎ የመቀበል፣ ወይም የማምልከ፣ በምድር ላይ የሚታዩትንም አስቀያሚ ነገሮች እንደተፈጥሮአዊ አድርጎ መቀበል እንደማያስፈልግና ሁኔታዎችንም መለወጥ እንደሚቻል ነው የሚያረጋግጠው። በተለያዩ ኤፖኮች በገዢ መደቦችና አጫፋሪዎቻቸው የሚፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ፣ ፍትሃዊነት ማጣት፣ ጦርነትን መቀስቀስና ምክንያቱን መረዳት ጥያቄ የሚያነሱ የተገለፀላቸው ጥቂት ምሁራን ብቻ ናቸው። ከዚህም በመነሳት አንድን ህዝብና አገርን ካልተገለፀላቸው ሰዎችና በጭፍን ከሚጓዙ ይሁንና ግን የፖለቲካውን ሁኔታ ከሚያዘበራርቁ ማላቀቅና ህጋዊና ፍትሃዊነት ያለው ስርዓት መገንባት ዋናው ተግባር ነበር።
ይህ ጉዳይ ግን በአገራችን ምድር የተለመደ አይደለም። በተለይም የፊዩዳሉ ስርዓት በሰፈነበትም ጊዜ ሆነ በኋላ ላይ አብዮት ተካሂዷል በሚባለበት ዘመን ከግብግብ በስተቀር ከሳይንስ አንፃር ሁኔታዎችን በማንበብና የቲዎሪ መመሪያ በማዳበር በየጊዜው የሚታየውን የፖለቲካ አወቃቀር፣ ፖለቲካ የሚባል ነገር ካለ፣ ተግባራዊ የሚሆነውንና፣ የመንግስትን አወቃቀርና ጭቆናዊ በሆነ መልክ መዘጋጀቱንና፣ የመንግስትን መኪና የጨበጡ ሰዎች የሰለጠኑ ወይም ያልሰለጠኑ፣ ምሁራዊ ግንዛቤ ይኑራቸው ወይም አይኑራቸው፣ ከዚያም በመነሳት ተግባራዊ የሚያደርጓቸውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎችን አስመልክቶ ምርምርና ጥናት፣ እንዲሁም ትንተና ስለማይሰጥ ስልጣን ላይ የተቀመጡትንና አገርን በዘፈቀደ የሚመሩትን በሳይንሱ የሚጋፈጥ ኃይል በፍጹም ብቅ ማለት አልቻለም። በዩኒቨርሲቲም ደረጃ ክሪቲካል ቲዎሪ ስለማይሰጥና ራሳቸው አስተማሪዎች ወይም ፕሮፌሰሮችም ክሪቲካል በሆነ መልክ እንዲያስቡና ጥያቄም እንዲያነሱ ሆነው ባለመሰልጠናቸውና፣ ከውጭ ተጽፈው የሚመጡ በአብዛኛው አንድ ዐይነት አመለካከትን የሚያንፀባርቁና ወይም ፍጹማዊ እንደሆኑ የሚታዩ ትምህርቶችን በማስተማር አብዛኛው ተማሪ ትምህርቱን ጨርሶ በሚወጣበት ጊዜ ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማንበብና የራሱን ግምግማ በመሰጠት የአስተሳሰብ አድማሱን ሊያሰፋ በፍጹም አይችልም። በተለይም ይህ ዐይነት አንድ ወጥና ፍጹማዊ አስተሳሰብ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ላይ የሚንፀበራቅ ነው። በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና የኢኮኖሚ ፖለቲካ በየኤፖኩ ከሁኔታው ጋርና በኃይል አሰላለፍ ለውጥ ምክንያት የተነሳ በየጊዜው በአዲስ መልክ ተዘጋጅተው ተግባራዊ እንደሆኑ ስለማይታወቅ አብዛኛው ተማሪ በነፃ ገበያና ንግድ ላይ ብቻ በማተኮር፣ በተለይም ህብረተሰብና የሰው ልጅ ምን እንደሆኑ እንዳይማር በመደረጉ የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ትምህርት ብቻ ተምሮ በመውጣት የውጭ ኃይሎችን ትዕዛዝ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ ህዝባችንና አገራችን ከፍተኛ ውድቀትን እንዲከናነቡ ለማድረግ በቅቷል። በኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ ፈጣሪና የስራ-መስክ ከፋች የሆነ የኢንዱስትሪ ባለቤትና የቴክኖሎጂ ሰው ከመፍጠር ይልቅ ዘራፊና የአገርን ባህል አውዳሚ፣ እንዲሁም የአካባቢ ውድመትን የሚያስከትል የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር በማድረግ በዚያውም መጠን ፋሺሽታዊ አገዛዝ እንዲፈረጥም ለማድረግ ተበቅቷል። ይህንን ሁኔታ በመገንዘብ የየራሱን ግምገማ የሚሰጥ የተገለፀለትና ለሰው ልጅ ተቆርቋሪ የሆነ ምሁራዊ ኃይል ሊፈጠር ባለመቻሉ፣ ካለም ዝም ብሎ የሚመለከት በመሆኑ ሰፊው ህዝባችን ግራ ተጋብቶ ይኖራል። ባጭሩ የተገለፀለት ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር ውስጥ አንድ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ወይም አንድ ግለሰብ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ላይ በማላገጥና በመዝረፍና ሀብትን በማዘረፍ የታሪክን ሄደት ያበላሻል። አንድ አገርና ህብረተሰብ ታሪክና ስልጣኔ የሚሰራባቸው ከመሆን ይልቅ የብልግና ኢንዱስትሪ የሚስፋፋባቸው ይሆናሉ። ባለፉት 35 ዓመታት ይህ ሁኔታ ነው የሚታየው።
በተለይም ህወሃት የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመት ስልጣን ሲጨብጥና ሃያ ሰባት ዓመታት ያህል ስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ እየተመከረ ኢ-ሳይንሳዊ ፖለቲካ ሲያካሄድና አገርን ሲያወድም ዝምብሎ ከመነዳት በስተቀር ይህንን ሁኔታ የሚተነትንና ለህዝባችን የሚያስተምር ኃይል ሊፈጠር ባለመቻሉ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን አማራጭ እንደሌለው አድርጎ መቀበል ተግባራዊ ማድረግ የተለመደ ነገር ሆኗል። በአብዮቱ ዘመን በተፈጠረውም እጅግ አሳሳችና አደገኛ ሁኔታ የተነሳና፣ በአንዳንድ ጥራዝ ነጠቅ አብዮተኛ ነን በሚሉ ጠለቅ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብር የከተማ ውስጥ የሽብር ትግል ስለጀመሩና ተራማጅ የሚባለውንም እያነጣጠሩ መግደል እንደ ፈሊጥ አድርገው በመውሰዳቸው ብዙ አስተዋፅዖ ለማበርከት ይችሉ የነበሩ ምሁራን እንዲገደሉ ተደረጉ። እነዚህ አብዮተኛ ነን ይሉ የነበሩ ምሁራንና በመንግስት መኪና ውስጥ የተሰገሰጉ ህብረተሰብአዊ ዕድገትንና የሰፊውን ህዝብ ኑሮ መሻሻል የሚጠሉ ቢሮክራቶችና ቴክኖክራቶች በአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት የሚደገፉና የሚመከሩ ስለነበሩ ግራ ናቸው የተባሉ ኃይሎችን እያነጣጠሩ መግደል የተለመደ ነገር ነበር። በደቡብ አሜሪካ ውስጥ በጅምላና ነገሩ ሳይገባቸው በእነፒኖቼትና በአርጀንቲና ጄኔራሎች ይደረግ የነበረው ጭፍን ጭፍጨፋ በአብዮቱ ዘመን በአገራችንም ምድር እንዲፈጠር ለመደረግ በቃ። የአገራችንን ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ራሱ አብዮተኛ ነኝ የሚለውና ለውጥም ፈላጊ ነኝ ይል የነበረው እዚያው በዚያው ገዳይና ሁኔታዎችን ማዘበራረቁ ነው። ባጭሩ በተፈጠረው የተደነባበረ ሁኔታ የሚያስብና የሚመራመር ምሁራዊ ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ደግሞ ስልጣን ላይ ለተቀመጠውና ለውጭ ኃይሎች አመቺ ስለሚሆን ኢ-ሳይንሳዊና ኢ.-ህዝባዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ በአገርና በሰፊው ህዝብ ላይ የኢኮኖሚ ጦርነት እንዲካሄድ ለማድረግ በቅቷል።
ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ምርር በማለት ወዳነሳው ሁኔታና ወዳስነበበንም ጽሁፍ ጋ ስንመጣ እነዚህ የአቢይን አገዛዝ ይደግፋሉ የሚባሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ነን ባዮች ለምን አገዛዙን እንደሚደግፉ የራሳቸውን ትንተና በመስጠት አላስነበቡንም። በመሰረቱ አንድ ፖለቲከኛ ወይም ምሁር ነኝ ባይ አንድን አገዛዝ ሲደግፍ ለምን እንደሚደግፍ ማስረዳት ወይም አቋሙን ግልጽ ማድረግ አለበት። እዚህ አውሮፓ ውስጥ አንድ የተለመደ ነገር አለ። ቀኝ ነን ብለው የሚንቀሳቀሱ ምሁራን ነን ባዮችና ፖለቲከኞች አሉ። እነዚህ ቀኝ ነን የሚሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ህብረተሰብን በሚመለከት የራሳቸው ቲዎሪ ሲኖራቸው፤ በተለይም ዘር-ተኮር ፖለቲካን ያካሂዳሉ። ይህም ነገር በሁሉም መስክ እንዲስተጋባ ይፈልጋሉ። ይሁንና በታሪክ እንደተረጋገጠው እነዚህ ኃይሎች በአንድ አገር ውስጥ ውዝግብ እንዲፈጠር የሚሰሩ ናቸው። አንድ ህብረተሰብም ቆሞ የሚቀር እንደሆነ አድርገው ስለሚያምኑ በሂደት ውስጥ ከሌላ አገሮች ከመጡ ሰዎች ጋር በመጋባት መቀያየጥ እንደሚፈጠርና የባህልም ለውጥ እንደሚኖር ሊረዱ በፍጹም አይችሉም። ጥሩ ነገር ቢሆንምና የሚኖሩበትም ቢሆን ጭንቅላታቸው በጥላቻ መንፈስ የተመረዘ ሰለሆነ ራቅ ብለው ማሰብ አይችሉም። ወደ አገራችን ስንመጣ የአቢይ አህመድን አገዛዝ ይደግፋሉ የሚባሉት ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ምሁራንና ፖለቲከኛ እያለ የሚጠራቸው፣ ዘመናዊ ትምህርት የሚባለውንም ቢቀስሙ በመሰረቱ ምሁራዊ ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም። ጥያቄዎችን እስካላነሱ፣ እስካልተመራመሩና አማራጭ መፍትሄም እስካላቀረቡ ወይም በትንተና መልክ እስካላስነበቡን ድረስ ዲግሪ ስለጨበጡና አልፈው አልፈው በዩቱብ ቻናል ላይ የሚሆን የማይሆን ነገር ስለተናገሩ ብቻ እነዚህን ሰዎች እንደ ፖለቲከኛና ምሁራን አድርጎ መቁጠር ስህተት ነው። አንድን አገዛዝ ብቻ በጭፍን መደገፍ አንድን ሰው ፖለቲከኛ ወይም ምሁር ነው ሊያስብለው የሚቻልበት ምንም ምክንያት የለም።
ይህ ጉዳይ አልፎ አልፎ በአንዳንዶቻችንም ላይ የሚታይ ነው። በአማርኛም ሆነ በእንግሊዘኛ ጽሁፎችን በድረ-ገጾች ላይ ለማስነበብ ብንችልም በምን ፍልስፍናና ሳይንሳዊ መሰረተ-ሃሳብ ላይ ተመርኩዘን እንደምንጽፍ ግልጽ አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ለምሳሌ የአቢይ አህመድን አገዛዝ በሚመለከት በሁላችንም ዘንድ መደናበር ይታያል። ለምድን ነው እንደዚህ የሚያደርገው? ከማለት በስተቀር አቢይ አህመድና አገዛዙ በዓለም አቀፍ የፋሺሽታዊ የአገዛዝ ሰንሰለት ውስጥ የተካተተና የእነሱንም ትዕዛዝ በመቀበል ግልፅና ግልፅ ያልሆነ ጦርነት የሚያካሄድ ለመሆኑ በፍጹም አይታወቅም። በአጠቃላይ ሲታይ አቢይ አህመድና አገዛዙ ትዕዛዝን በመቀበል ተግባራዊ ከማድረግ በሰተቀር የራሱ የሆነ ምሁራዊ መሰረት የለውም። በአካባቢው ያሉትም ትዕዛዝን ከመቀበል በሰተቀር በራሳቸው ህሊና በመገዛት ትክክል አይደለም፣ በዚህ መልክ አገራችንና ህዝባችንን ለማስተዳደር እንችልም የሚሉ አይደሉም። የፖለቲካ አማካሪ ሆነው የሚሰሩትን እንደ ፕሮፌሰር አልማርያም የመሳሰሉትን ሁኔታና የዶክትሬት ዲግሪ ማዕረግ ያላቸውና ውጭ አገር እየኖሩና እየተመላለሱ የአቢይን አገዛዝ የሚደግፉትን ስንመለከት እነዚህ ሁሉ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናና ሳይንሳዊ ዕውቀት የሌላቸው ናቸው። አንድ ሰው ውጭ አገር በሰላም የተደላደለ ኑሮ እየኖረና አገር ቤት ሄዶ ተመልሶ ሲመጣ አቢይ አህመድ የሚሰራው ትክክል ነው ብሎ የሚቀበል ወይም የሚያምን ሰው የማሰብ ኃይል የለውም ማለት ነው። ህዝብ በዋጋ ግሽበት እየተሰቃየና እየተዘረፈ እየሰማና እየተመለከተ ይህ ነገር እንደማይደረግ አድርጎ ዝም የሚል ሰው ይህ ዐይነቱ ሰው መንፈሰ-አልባ ነው ማለት ይቻላል። የፕሮፌሰርነትና የዶክትሬትነት ማዕረግ ከማንጠልጠል በስተቀር የአገራችንና የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ሊያስነብብ የሚችል ሳይንሳዊ ዕወቀትና ግንዛቤ የሌለው በመሆኑ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችን እንደምሁራን መመልከት በፍጹም አይቻልም። ይሁንና ግን ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያንን የማወናበድ ኃይላቸው ከፍ ያለ ነው። አብዛኛው ወጣት ኢትዮጵያዊም ሆነ ራሱ የአቢይን አገዛዝ እጠላዋለሁ ወይም እቃወማለሁ የሚለው ሰነፎች ስለሆኑ ጥያቄ የማንሳትና የመራመር፣ እንዲሁም ደግሞ የራሳቸውን ግምገማ የመስጠት ልምድ የላቸውም።
ግልጽ ለማድረግ በሳይንስ ዓለም ውስጥ ሶስት ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማንበቢያ ዘዴዎች አሉ። 1ኛው፣ የክርቲካል ራሺናል ዘዴ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ነገሮችን በጥልቀት በመመርመርና ቲዎሪ በማዳበር የችግሩን ምንጭ በመረዳት ፍቱን መፍትሄ መስጫ ዘዴ ነው። ይህ ዐይነቱ ዘዴ ከጭንቅላት የሚወጣ ሲሆን፣ እነ ፕሌቶንና ተከታዮቻቸው፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ እነ ላይብኒዝና ካንት እንመመመሪያ በማድረግ ፍልስፍናንና የተፈጥሮ ሳይንስን በማዳብር የሰው ልጅ ከነበረበት አስቀያሚና ጨቋኝ ሁኔታ እንዲላቀቅ በማድረግ የዕውቀትን መንገድ የከፈቱ ናቸው። ታላላቅ ሳይንቲስቶች በሙሉ ይህንን መሰረት በማድረግ ነው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝት የፈጠሩትና እኛም ተጠቃሚ እንድንሆን ለማድረግ የበቁት። ሁለተኛውና ዛሬ በዓለም አቀፈ ድረጃ የተስፋፋው ኢምፔሪካል ወይም ኢምፔሪዝም በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በዳታ ላይ ያተኮረና የቲዎሪ አስፈላጊነትን አትኩሮ የማይሰጥ ወይም የተወሳሰበ ቲዎሪና በጥልቀት መመራመር አያስፈልግም ብሎ የሚያምን ነው። በተለይም እነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ የዓለም ኮሙኒቲው የሚመራበት በጣም አደገኛና አሳሳች የሆነ መሳሪያ ነው። በተለይም እንደኛ ባለ ኋላ-ቀር በሆነ አገር ውስጥ ስርዓት ያለውና ሁለ-ገብ የሆነ ለውጥ መምጣት የለበትም የሚል ነው። አንድ ነገር ብቻ ያውም ክስተታዊው ነገር ከተሻሻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብሎ የሚያምን ነው። ሁለ-ገብና ጥልቀት ያለውንና ጭንቅላትን ክፍት ለማድረግ የሚችለውን ሳይንሳዊ ዕውቀት እንዳይተገበር የሚታገልና በአሳሳች ምክር የሶስተኛው ዓለም ፖለቲከኞችንና ቴክኖክራቶችን የሚያሳስት ነው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት አማራጭ ቲዎሪን የማይቀበልና፣ በተለይም የቢሮክራቶችና የቴክኖክራቶች መመሪያ መሳሪያ በመሆን ሁለ-ገብ ዕውቀትና የሰፊው ህዝብ ኑሮ እንዳይሻሻል የሚያደርግ ሳይንሳዊ ዕውቀት እንዳይስፋፋ መሰናክል የሚፈጥር ነው። ይህንንም የኢምፔሪካል መሳሪያ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ጠቅላላው አገዛዝ የሚመሩበትና የዓለምን ህዝብ እንደፈለጋቸው የሚበውዙበትና የሚያሽከረክሩበት ነው። ይህ ዐይነቱ መመሪያ በይዘት ሲታይ ፋሽሺታዊ ነው። ፋሺሽታዊ የሚያሰኘው በክሪቲካል ቲዎሪ የማያምንና፣ ሁኔታዎችን በጥቁርና በነጭ በመሳል፣ ወይም በወዳጅና በጠላት በመፈረጅ ውስብስብ ሁኔታዎችን እንዳንገነዘብ የሚያደርግ ነው። ወደ ሶስተኛው ጋ ስንመጣ የማርክሲስት ክሪቲካል ቲዎሪ ሲሆን፣ መሰረት የሚያደርገውም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግኑኘቶችን በመመርመር የራሱን ትንተና የመስጫ ዘዴ ነው። በተለይም የመደብ አሰላለፍን በመመርኮዝ የምርት ኃይሎች በማንኛው የህብረተሰብ ኃይል ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ በመመርመር፣ የግዴታ መሰረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት ብሎ የሚያምን ነው። ስለሆነም ከመጀመሪያው የክሪቲካልና የራሽናል ቲዎሪ ጋር በመዳበል ሰብአዊ የሆነ የህብረተሰብ ስርዓት ሊፈጠር የሚችልበትን ሁኔታ የሚያግዝ ወይም እንደመመሪያ የሚያገለግል ዘዴ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በፕላቶናዊዉ መንገድና በማርክሲስታዊዉ መንግድ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሁለቱም የሚያነሱት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ፍትሃዊነትን ነው። በአጠቃላይ ሲታይ በተለይም ባለፉት ሰማኒያ ዓመታት ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ እየሆነ በመምጣቱና በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠርንም ህዝብ ህይወት የሚደንግግ በመሆኑና፣ ከአዎንታዊ ተፅዕኖው ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖው ከፍ እያለ በመምጣቱ እንደምንመለከተው በተለይም የሶስተኛው ዓለም ህዝቦች የአኗኗር ሁኔታ በጣም እየተበላሸ በመምጣቱ የተነሳና አምባገነናዊ አገዛዞች የሰፍኑ በመሆናቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህዝቦች በአገራቸው ውስጥ ለመኖር ስለማይችሉ እየተሰደዱ በመሄድ ሌላ አገር ውስጥ እንዲኖሩ የተገደዱበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በሌላ አነጋግር፣ የየአገሮችም ሆነ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ የተወሳሰበ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ፖለቲከኞች ነን የሚሉትና ስልጣንን የጨበጡ በሙሉ ምንም ዐይነት ፍልስፍናና መመሪያ ስሌላቸው አገሮቻቸውን ወደ ሲኦልነት ለውጠዋል ማለት ይቻላል። በዓለም አቀፍ ደረጃም አንድ ዐይነት ወጥ አመለካከትና አገዛዝ የሰፈነ ይመስላል። ከአሜሪካኖችና ግብረ-አበሮቹ ቁጥር ውጭ የሆነ አገዛዝ ያለ አይመስልም።
ወደ አገራችን ተጨባች ሁኔታ ስንመጣ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ዝም ብሎ ልታይ ልታይ ከማለትና እንደ አዋቂ ከመለፍለፉ በሰተቀር ተጨባጭ የሆነ መመሪያ የለውም። ዝም ብሎ ብቻ የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን ምክር እየተቀበለና ግፊትም እየተደረገበት ህዝባችን በሲኦል ዓለም ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ በቅቷል። በአንድ በኩል የእነ ዓለም አቀፍ የገነዝብ ድርጅትን የገንዘብ ቅነሳ ፖሊሲና የገንዘቡ የመግዛት ኃይል በገበያ ህግ ብለው በሚጠሩት እንዲደነገግ እያደረገና ህዝባችንንም ፍዳውን እያሳየ፣ እዚያው በዚያው ደግሞ ኢትዮጵያ የብርኪስ(BRICS) አባል እንድትሆን አድርጓል። ሰውየው ግራ የተጋባ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃም አወናባጅ የሆነ ሰው ነው። በሌላ አነጋገር፣ አገዛዙ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ቡችላ ሆኖ እያለና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲንም ተግባራዊ እያደረገ ለምን የብሪክስ አገሮች አባል ለመሆን እንደፈለገ አይታወቅም። ወደፊት ብሪክስ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ አባላት አገሮች ምን ምን ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለባቸው ስለማናውቅ ለጊዜው ፍርድ ለመስጠት አንችልም። የሚነሳው ጥያቄ ግን አንድ አገር የብሪክስ አባል በመሆኗ ብቻ ነፃና ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መገንባት ትችላለች ወይ? ለህዝቦቿም አስተማማኝ ሁኔታን መፍጠር ይቻላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው መነሳት ያለበት።
ወደ ፕሮፌሰር መሳይ ጥይቄና ወደ አስነበበን ጽሁፍ ጋ ስመጣ ራሱ ፕሮፌሰሩ እንደዚያ ብሎ ከመጻፉና ከማስነበቡም ባሻገር ምሁራንና ፖለቲካ ተብዬዎች ለምንና በምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም በመመራት የአቢይን አገዛዝ እንደሚደግፉ ማብራሪያ መሰጥት ነበረበት። ከዚህም በላይ በጅምላ ብዙ ምሁራንና ፖለቲከኞች ይደግፉታል ከማለት ባሻገር የስም ዝርዝር አውጥቶ ቢያቀርብልን ምናልባት ለጥያቄና ለትግልም ያመቻል። በሌላ ወገን ግን እነዚህ አቢይ አህመድን እንደግፋለን የሚሉ ምሁራንና ፖለቲከኛ ነን ባዮች ማወቅ ያለባቸው ነገር ህዝባችን በኑሮ እንዳይሻሻል፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብና የህግም የበላይነት የሰፈነበትና ለህዝብ አስተማማኝ የሆነና አገር ወዳድ አገዛዝ እንዳይመሰረትና እንዳይፈጠር መንገዱን እንደሚዘጉ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በአገራችን ምድር ሳይንስና ቴክኖሎጂም እንዳያብቡና ሁለ-ገብ የሆነና ህዝባችንን ከድሀነትና ክኋላ-ቀርነት የሚላቅቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳይተገበር በጭፍን እንደሚመሩ ማወቅ አለባቸው። በመሰረቱ እነዚህ ኃይሎች የአሜሪካንን የበላይነት የሚናፍቁና በእሱም ፋሺሽታዊና አገሮችን የመደፍጠጥ የኃይል ፖለቲካ የሚያምኑ ናቸው። ባጭሩ ያልተገለፀላቸውና ኋላ-ቀር ምሁራንና ፖለቲከኞች ናቸው። መልካም ግንዛቤ !!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
ማሳሰቢያ፤ሌሎች ኢትዮጵያንን የምጠይቀው ነገር ለምንና ምን መምሰል እንዳለባት ኢትዮጵያ ነው የምትታገሉት? በደንብ ግልጽ እንዲሆንላችው የሚገባው ነገር ለአንድ ህዝብና አገር ለመታገል ጠለቅ ያለ ዕወቀትና ግልጽነት ያለው አመለካከት ያስፈልጋል። እንደምትመለከቱት በየአገሮችም ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አምባገነናዊ አስተሳስብና በጉልበት ማመን እየተስፋፋ መጥቷል። የሶስተኛው ዓለም አገሮች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው የካፒታሊስት አገሮችም አምባገነን እየሆኑ በመምጣት ላይ ናቸው። በሰላም የሚያምኑ ሳይሆኑ ሁሉንም ነገር በጦርነት ለመፍታት እንችላለን ብለው የሚያምኑ ናቸው። በተለይም እኔ የምለውን የማይቀበል ጠላቴ ነው የሚለውን አስተሳሰብ በማስፋፋት ሌላና አማራጭ አስተሳሰብ ያለውን ሰው እንደ ጠላት የሚመለከቱ ናቸው።
በዚህ አስተሳሰባቸውም የታሪክ መጨረሻ ላይ ደርሰናል ብለው የሚያምኑ ናቸው። ይሁንና ግን በዚህ ዐይነት አስተሳሰባቸው የዲያሌክቲክስን ህግ እየተፃረሩ ናቸው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ለአገሬ እታገላለህ የሚል በሙሉ ተሰባስቦ ማጥናት አለበት። መደጋገፍና መተባበርም አለበት። የአንድ አገር ህዝብ ዕድል በአንድ ድርጅትና በአንድ ወጥ አስተሳሰብም ሊለወጥና ሊሻሻልም እንደማይችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። ሰለሆነም ከጭፍን አስተሳሰብ ለመላቀቅ የግዴታ በቲዎሪ መታጠቅ ያስፈልጋል። ሳይንሳዊ ከሆነው የዕውቀት መመሪያ ጋር መተዋውቅ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ከጭፍን አስተሳስብ ለመላቀቅ ያቻላል። በዚህ አማካይነትም ዕውነተኛ ግለሰብ አዊ ነፃነትን መጎናፀፍና በራስ መተማመን ይቻላል። በተረፈ እንደዚህ ዐይነት ጽሁፍ በራሱ አይጻፍም። አንድን ጽሁፍ ለመጻፍ ማሰብ፣ ማውጣትና ማወረድ ያስፈልጋል። ስለሆነም የድረ-ገጼ ውስጥ በመግባት አስፈላጊውን ዕርዳታ እንድታደርጉ እጠይቅችኋለሁ።በተደራጀና በመተጋገዝ ብቻ ነው ሳይንሳዊ ጽሁፎችን ማቅረብና ማስነበብ የሚቻለው።