ይነጋል በላቸው
አንድ ወቅት በርቀታዊ መልካም ግንኙነት እንግባባ የነበረ ወዳጄ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ከአንከር ሚዲያው መሣይ መኮንን ጋር ሲነጋገር አሁን አደመጥኩ፡፡ የተሰቀለች ብዕሬን ማውረድና ይህችን ማስታወሻ መጫጫር ያሰኘኝም የነሱ ውይይት ነው፡፡ ኤፎ ባለህበት ሰላምህን ያብዛልህ፤ ለሀገራችንም ያብቃን፡፡ መሣይም አንደኛው የሀገር ባለውለታ ለመሆን ታሪክ አድሎሃልና በርታ፡፡
በመሣይና ኤፍሬም ውይይት ዋናው የተነሣው ነገር ስለብርሃኑ ነጋ የክህደት ጉዞ ነው፡፡ ሁሉ ነገር እያለው ለምን የዚህ አቢይ አህመድ የሚባል ወፈፌ ኩታራ ልጅ አሽከር ሊሆን እንደበቃ ነበር ይነጋገሩበት የነበረው አንኳር ጉዳይ፡፡ እኔም የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛልና በተለይ በሰሞነኛው የፖለቲካ ሙቀት ስማቸው ከሚነሱ ግለሰቦች መካከል ሦስቱን በሚመለከት ጥቂት ነገር ለመተንፈስ ወደድኩ፡፡ ከ120 ሚሊዮን የማይተናነስ ሕዝብ በዝምታው ጸንቶ ለዚህ ዓይነት ተዋራጅ ሕይወት መዳረጉ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ይሄ “ዕዝ ነው” የሚሉት አነጋገር ሀሰት እንዳልሆነ እየተረዳሁ ነው፡፡
ከሦስቱ የመጀመሪያው እነኤፍሬም ያነሱት ብርሃኑ ነጋ የሚባው ጉደኛ ፍጡር ነው፡፡ ስለእርሱ ያወሱት ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ከሀብትም ሀብት፣ ከዝናም ዝና፣ ከትምህርትም ትምህርት … ሁሉም ነገር የተሟላለት ሆኖ ሳለ እንዴት ለአንድ እዚህ ግባ ለማይባል የታናሹ ታናሽና ምናልባትም ልጁ ሊሆን ለሚችል አጭበርባሪ ብላቴና አሽከር ሊሆን ቻለ? የሚለው ጥያቄ ብዙዎቻችንን የሚያስጨንቅ ነው፡፡ በርግጥም በለዬለት የማይምነት ድቅድቅ ጨለማ የተዋጠው ኦሮሙማ ካሉት የሌላ ነገድ አሸርጋጆችና ተላላኪዎች መካከል እንደብርሃኑ ነጋ የተማረ ቀርቶ የግሩ ዕጣቢ የሚሆን የለም፡፡ “Is”ን ከ“was” መለየት ለማይችሉትና በአማራ ጥላቻ ላበዱት ማይማን ኦሮሙማዎች የብርሃኑ ከነሱ ጋር መገኘት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ለርሱ ግን ወደፊትም ወደኋላም ሰባት ዘሩን የሚያስወቅስ መርገምት ነው፡፡ ሳያጡ ማጣት ያሳዝናልና በግሌ ብርሃኑ ያሳዝነኛል፡፡ የንስሃ ጊዜ ቢያገኝ ደግሞ ደስ ባለኝ፡፡ የነገሮች ፍጥነት አሳሳቢ ነውና እንዲመለስ ወዳጆቹ (ይ)ምከሩት፤ የማይቻል ነገር የለምና ይህም ይቻላል፡፡ ቆም ብሎ የማሰብ ጉዳይ ነው፡፡
አዎ፣ ብርሃኑ፣ ኤፍሬም እንደገለጸው የባለብዙ ዕውቀትና ግንዛቤ ባለቤት ነው፡፡ ለርሱ እንኳንስ በአግባቡ የማይሠራበት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትርነት ማዕረግ ይቅርና የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትርነትም ሲያንሰው ነው፡፡ እንኳንስ እርሱ፣ በ1990ዎቹ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ ተሸካሚ የነበረና ከዚያም በፊት ከአራተኛ ወይ ከሰባተኛ ክፍል ትምህርቱ ተቆራርጦ በመሽረፊት አዟሪነትና በተላላኪነት የዕለት ጉርሱን ይሸፍን የነበረ አቢይ አህመድም ጠ/ሚኒስትር ሆኗል፡፡ ስለሆነም ብርሃኑን ለዚህ የውርደት ደረጃ ያበቃው ነገር በጥናትና ምርምር መፈተሸ ይኖርበታል፡፡ አንዳች ውስጣዊ ግፊት ወይም ፍላጎት ባይኖረው ኖሮ ትዳሩንና ልጆቹን ሳይቀር በሰው ሀገር እርግፍ አድርጎ ትቶ (በትኖ ላለማት ነው) ለዚህ በካፈርኩ አይመልስኝ ላይ የተመሠረተ ለሚመስል ቅሌት ባልተዳረገ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የስብዕና ትንሽነት በትምህርት ልኂቅነት አይሸፈንም፡፡
እንደኔ ግን ለዚህ ሰውዬ መዋረድ ዋናውን ድርሻ ይወስዳል ብዬ የምገምተው ለአማራ ያለው የከረረ ጥላቻ ነው፤ እንደአባሪም ሰውዬውን እንደተጠናወተው የማስበው የሥልጣን ፍቅር የገማ ጭቃ ውስጥ ከትቶ እያርመጠመጠው እንደሚገኝ ቢታመንም በሚገባ ያስኬዳል፡፡ በቋሚነት የተሰጠው ቦታ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ዋናው ማዕከል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ እሱና ገነት ዘውዴ በዚያ ቦታ ሊመደቡ የቻሉት ትምህርትን ከኢትዮጵያ እንዲሰደድና በምትኩም ማይምነት እንዲነግሥ በውጤቱም ነባር የዕውቀትና የባህል ዕሤቶች እንዲጠፉ በተሸረበ የውስጥና የውጭ ሤራ ነው – ግልጥ እኮ ነው፡፡ ይህ የዐድዋ ድል የወለደው ዓለም አቀፍ የበቀል ሤራ ቀንዱና ጭራው የት እንዳለ ይታወቃል፡፡ ሀገርን ለማጥፋት ዋናው ቁልፍ ያለው ትውልድን ከዕውቀት ማዕድ ማራቅ ነው – አእምሮውን ማምከን፤ በቴክኖሎጂ አጋንንታዊ ጋጄቶች ሥነ ልቦናውን ማራቆት፣ የሀገራዊና ቤተሰባዊ የእምነትና የሃይማኖት የትስስር ገመዶችን በጣጥሶ ትውልዱን አውላላ ሜዳ ላይ መጣልና በማንነት ኪሣራ እንዲሰቃይ ማድረግ፡፡
ትምህርትን ማጥፋት ትውልድን ማደንቆር ነው፡፡ ጥይት መተኮስ ሳያስፈልግ አንድን ሀገር ማጥፋት የሚቻለው የትምህርትን ጥራትና ይዘት በመለወጥ ነው፡፡ እኛም ጋ እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡ አንድ የ5ኛ ይሁን የ6ኛ ክፍል የማኅበረሰብ ሣይንስ መጽሐፍ ላይ “እስክስታ በብዙ የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች የሚታይ የውዝዋዜ ዓይነት ነው” የሚል ትምህርት ካየሁ በኋላ “ረገዳ” በ“እስክስታ” የመቀየሩ ምሥጢር ገባኝና በአግራሞት ስቄ ዝም አልኩ – ካለዛሬም ለማንም አልተነፈስኩም፡፡ ለማንኛውም የደነቆረ ትውልድ ሀገር ተቀደደች ተበጣጠሰች ጉዳዩ እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ ዋና ዓላማው የሚሆነው የዕለት ጉርሱንና የዓመት ልብሱን በመሸፈን ዙሪያ ማድረግ ስላለበት ነገር ነው፡፡ አእምሮውን የተነጠቀ ትውልድ ደግሞ ለዚህ ዓላማው ሲል ዘረፋንና ስርቆትን ጨምሮ ሰይጣን ራሱ የሚፀየፋቸውን የክፋትና የኃጢኣት ተግባራት ሳይቀር ካላንዳች መሳቀቅ ያደርጋል፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለውም ይሄው ነው፡፡ አሁን ንግዱንና አገልግሎቱን ሁሉ ብታዩ እርስ በርስ መባላት ፋሽን ሆኗል፡፡ የዛሬ አሥርና አሥራ አምስት ዓመት 40 እና 50 ብር ትገዛው የነበረ አንድ ኪሎ ታጥቦ የተቀሸረ ቡና አሁን 1700 ስትባል ሻጩም አያፍርም፤ ገዢውም አያንገራግርም፡፡ ድሃው ቤቱ ተቀምጦ ሞቱን ይጠባበቃል፤ ሌባና ሌባው ይገበያያል፤ ሙሰኛና ዘራፊ ይምነሸነሻል፡፡ ፈረሱላ በርበሬ አምስት ብር እንዳልተገዛ አሁን አንዷ ኪሎ ከ1200 ብር በላይ ስትገባ መንግሥታዊ ገልማጭም ሆነ ቆንጣጭ የለም – ኳስ አበደች ይሉሃል እንደዚህ ነው፡፡ የትምህርት መጥፋት እንግዲህ ሆድን እያሰፋ ጭንቅላትን እንደሚያጠብ ከዚህ በላይ ማስረጃ የለም፡፡ እግዜር ይሁንሽ ኢትዮጵያየ! በነገራችን ላይ ታዲያ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች አካባ የሚታየውን የደመወዝን እርከን በተመለከተ ከብር 2000 አካባቢ ጀምሮ እስከብር 20000 አካባቢ (በአማካይ ማለት ነው) የሚልኮሰኮስ መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ትልቁ ዶፍተር በደሞዝ ቀን ተሠልፎ 9567.87 ብር ይቀበልና /ይዝቅና/ እየሮጠ ሄዶ ለቤት አከራዩ ብር 10000 ይከፍላል፡፡ በምን እንደሚኖር አስላው፡፡ “አስላው” ይል ነበር ዳንኤል ክብረት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ግን አንጎልን ባወጣ መሸጥ ጥሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በሀገራችን አንጎል ከሌለህ እንጂ ካለህ መኖር ይከብድሃል ወይም አትችልም፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ የጎን ገቢ ያላቸው ሰዎች እንደምንም እየኖሩ ነው፡፡ ሌላውን ተወው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ ከትምህርትና እሱን ተከትሎ ከሚመጣ ዕውቀት ጋር የመፋታት ችግር የሚከሰት መሆኑን ልብ ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም የከፋ ነገር አለ፡፡
ሰሞኑን የሆነውን እናስብ ለምሣሌ – ትናንት መሰለኝ፡፡ ኦሮምያ በሚባለው አካባቢ ታጣቂዎች ወደ አንድ ከተማ ይገባሉ፡፡ በዚያም አካባቢ በየቤቱ ያገኙትን ሕጻናትንና አሮጊቶችን በጥይት ይጨርሳሉ፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ አምስት ልጆችን ከእናታቸው ጋር ገድለዋቸዋል፡፡ ወጣ ብሎ የነበረ አባት ሲመለስ ሁሉንም ሞተው ሬሣቸው ተጋድሞ አገኘ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? የምንስ ውጤት ነው? አንድ ሰው የማያውቀውን ሰው ለመግደል እንዴትና ለምንስ ይነሳሳል?
ተመልከቱልኝ፡- አንድ ሰው ከታጠቀ ኃይል ጋር ውጊያ ቢገጥምና ቢገዳደል ያባት ነው፡፡ አንድ ሰው ቀደም ሲል በሆነ ነገር የተጣላውን ወይም የተቀያየመውን ሰው ቢገድል የነበረ ነው – ወንጀል ቢሆንም፡፡ አንድ ሰው የተዘጋ ቤት ከፍቶ በመባግት በሰላም የተቀመጠ ሕጻን ይሁን ሽማግሌ፣ ወንድ ይሁን ሴት የማያውቀውንና ያገኘውን ሁሉ በጅምላ ከገደለ ያ ሰው ከዕብድም በላይ ነው፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ በጥላቻ የተሞሉ እኚህን መሰል ዐውሬዎችን እንደፈጠረና ንጹሓንን እንዲገድሉ ጃዝ ብሎ እንደሚለቅ በየሥፍራው በሚከናወኑ ይህን መሰል ጭካኔዎች መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ እንግዲህ የትምህርት መጥፋት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ የውሸት ዶክትሬቱንና ማስትሬቱን እርሱት፡፡ በነሽመልስና አቢይ ጭንቅላት ውስጥ የታጨቀው የጥላቻ መርዝ ብቻ ነው፡፡ ያም መርዝ አማራንና ኢትዮጵያን ካላጠፋ ዕረፍት የሚባል አይኖረውም፡፡
ከፍ ሲል ለመጠቆም እንደተሞከረው ሥልጣኑን የያዙት ሰዎች ለአማራ ካላቸው በበሬ ወለደ ትርክት ላይ የተመሠረተ ጥላቻ ጎን ለጎን በሥልጣን ሱስና በፍቅረ ንዋይ ደዌ የተለከፉ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ የተበላሸ ስብዕናቸው ሲሉ ደግሞ ከፀሐይ በታች የማይሠሩት ወንጀል የለም፤ የሰላም መስፈን ለነዚህ ሰዎች የህመማቸው መንስኤ ነውና ሰላም ስሟ ሲጠራ ራሱ መላ ሰውነታቸውን ያንዘረዝራቸዋል፡፡ ለዚህም ነው አቢይና ሽመልስ ከጀሌዎቻቸው ጋር ተመሳጥረው የጫካ ሸሌና ማነው ሸኔና የከተማ ሸኔ በሚል በኅቡዕና በግልጽ ገዳይና ጨፍጫፊ ቡድኖችን በማቋቋም በሁለቱም ልምጮቻቸው ሕዝብን እየገረፉ የሚገኙት፡፡ የብርሃኑ ነጋ የዚህ ትራጄዲ ተውኔት አካል ሆኖ መገኘት በውስኪ ለሚጽናና ኅሊናው የቀውስ መንስኤ ሊሆን ቢችልም በአንድ በኩል ግን ለአማራ ጥላቻው እንደስኬት ቢቆጥረው ሰው ነውና ብዙ አንፈርደበትም፡፡ ብሬን እናውቀዋለን! “አማራ ለ3000 ዓመታት ገዝቷልና ከአሁን በኋላ ይበቃዋል” ያለ ጀግና እኮ ነው ፡፡
አንድ ጤናማ ነኝ የሚል ሰው – በመሠረቱ – አቢይ አህመድ ጋ ሊገኝ አይችልም – በምንም መንገድ፡፡ ይህ ሰው፣ ሰው ጠፍቶ እንጂ አማኑኤል ሆስፒታል በከፍተኛ ክትትል ሥር ሊገኝ የሚገባው የዕብዶች ንጉሠ ነገሥት ነው፤ ተራ ዕብድ አይደለም፡፡ ከአንደበቱ አንድም ዕውነት የማይገኝ ሰው፣ የሥልጣን ዘመኑ ሁሉ የጎረቤት ሀገራትንና መሪዎችን ጨምሮ የገዛ ዜጎችን በማጋጨትና በማናጨት፣ በማዋጋት፣ በማጭበርበርና ሕዝብን በመዝረፍ የሚታወቅን ሰው በሚኒስትርነትም ይሁን ከዚያ ባነሰ የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታ ለማገልገል እሱ ጉያ ውስጥ መወተፍ የገንዘብ ፍቅርን ወይም የሥራ ዕድልን ብቻ አያመለክትም፡፡ ለጣዖታዊው ሉሲፈራዊ አምላኩ የሰው ደም በየቀኑ ካልገበረ እንቅልፍ የማይወስደውን ሰው ማገልገል የመጨረሻ ዋጋው ከዚያ ሰው ሊለይ እንደማይችል የነሂትለርንና ሙሶሊኒን መጨረሻ መመርመር ይገባል፡፡ እኔ ለምሣሌ በርሀብ እሞታታለሁ እንጂ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ደሞዝ ተከፋይ ሆኜ በአንድም መዝገብ መገኘትን አልፈልግም፡፡ የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ጠባሳ በኔና በቤተሰቤ እንዲያስቀር አልፈልግም፡፡
ሌላው ሰው ኮሎኔል ደመዘ ቀውዱ ነው፡፡ ሀገራችን መቼስ የዕንቆቅልሽ ሀገር እንደመሆኗ አጻጻፌም ልክ እንደሷው ሊሆን እየዳዳው ነው፡፡ ወንድሞቼ እህል ነፍስን አውሎ ከማሳደሩ አኳያ ጥሩ ቢሆንም እንደኤሣው ከማድረጉ አንጻር ግን መጥፎ ነው፡፡ አቤልንና ቃየልን ያገዳደለው እህል ነው፡፡ የኤሣውን ብኩርና ለታናሽ ወንድሙ ለያዕቆብ ያሸጠው እህል ነው፡፡ ብዙ የዓለማችን ጉዳዮች ግልብጥብጣቸው የሚወጣው በእህልና ከእህል ጋር በተያያዘ ነው፤ ሌላውን ትያትር ተውት፡፡ መሠረቱ ግን እሱ ነው፡፡ ወሲብና ሥልጣንም ትልቅ ተፅዕኖ እንዳላቸው አውቃለሁ፤ ግን ሳይበሉ መዋሰብም ሆነ መንገሥ የለምና ቀዳሚው የመፋጃ ሜዳ የእህል ዐውድማ ነው፡፡
ከደሜ ጋር ይህን ማያያዝ ለምን እንዳስፈለገኝ አላውቅም፡፡ ምናልባት ወልቃይት በአንዳንድ የዘይት እህሎችና በጥጥ ምርት የከበረች ስለሆነች ይሆናል፡፡ ያ ምድራዊ አዱኛም ወዳጅን አስክዶ ከጠላት ጋር ቢያስማማና ቢያፋቅር የእህል ተፈጥሯዊ ወጉ ነውና አዲስ አይደለም፤ ይሁዳ በ30 አላድ ክርስቶስን የሸጠው ለዚህም አይደል? – ሊያውም ሳይበላው ተሰቅሎ ለሚሞት ነገር፡፡ ለማንኛውም የት ይደርሳል የተባለው ኮሎኔል በሰሞነኛ የ9ኛ ዓመት የሐምሌ 5/ 2017 በዓል ላይ የተናገረው ነገር አንድምታው ቀላል አይደለም፡፡ እሱን ተመችቶት ስለኖረ የአማራን ጀኖሳይድ ለመታገል ጫካ የገቡ ሰዎችን – ከነችግራቸውም ቢሆን – ሲቃወም በመስማቴ ገርሞኛል፡፡ አካሄድን መተቸት ያለ ነው፡፡ እሱ ግን ከናካቴው የትግል ምክንያት የላቸውም ብሎት አረፈው፡፡ “ፋኖ የሚታገልበት ምክንያት ስለሌለ ለ‹ፀሐዩ መንግሥት› እጁን በመስጠት በሰላም አርፎ ይቀመጥ” አለ – ደሜ፡፡ የሕጻን አንሻ አምላክ ይፋረድህ እንዳልል እኔ እንደሱ አልጨክንም፡፡ ግን ያሳዝናል፤ የእውነት አምላክ በቶሎ ፍርዱን ይስጠን፡፡ ሀገራችን ወዴት እየሄደች እንደሆነ ግራ ገባኝ፡፡ የሚታመን ሰው ጠፋ፡፡ ትልቅ የሚባልና የምናከብረው አመዛዛኝ ሰው አጣን፡፡ ለሆድ ተገዢው፣ ለመኖር ሳይሆን ለመብላት የሚኖረው በዛና ተቸገርን፡፡ የፋኖ ትግል ተጠልፏል ሲልም ተደምጧል፡፡ እዚህ አካባቢ የየትኛው ፋኖና በየትኛው አካባቢ የሚለው ማብራሪያ ቢያስፈልገውም በጥቅሉ “የፋኖ ትግል ኢምክኒያታዊ ነውና ለአቢይ እጅ ስጡ” ማለት ግን በተለይ ላለፉት ሰባት ዓመታት በአማራ ላይ የደረሰውን ዕልቂትና የሀብት ንብረት ውድመት እንዲሁም ቤት ፈረሳና መፈናቀል “አሜን፤ ይደረግልኝ፤ እንዲያውም ይህም ሲያንሰኝ ነው” ብሎ የመቀበል ያህል ነው፡፡ ዐይን በጥቅም ሲታወር ከዚህም በላይ እንደሚኬድ እነተመስገን ጥሩነህና አገኘሁ ተሻገር ምሥክሮች ናቸው፡፡ ከወለጋ ተደውሎ “በአማራነታችን ምክንያት እያለቅን ነው ድረሱልን” ሲባል “ቻሉት፤ እዚያ ምን ወሰዳችሁ ሲጀመር? ከነሱ ጋር ተስማምታችሁ ኑሩ … ስለእናንተ አያገባንም ….” ያለው ሆድ አደሩ አገኘሁ ተሻገር በፌዴራል መንግሥት ተብዬው የአቢይ ዕቃ’ቃ መጫወቻ አሻንጉሊት ፓርላማ የአማራ ወኪል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እናም አማራው እየተደቆሰ ያለው፣ አማራ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ እየተደረገ ያለው በለየላቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶቹ ብቻ ሣይሆን በገዛ ልጆቹ በአማሮች ጭምር ነው – ለዚህም ዋጋቸውን እንደሚከፈሉ በበኩሌ አሣምሬ አውቃለሁ፤ ያንንም ቀን አምላኬ እንደሚያሳየኝ አምናለሁ፡፡
ይህ የዕልቂት ሂደት የሚቆመውና የሚስተካከለው ግን አማራና አማራዊነት ሲያሸንፍ ብቻ ነው፤ ሊነጋ ሲል የሚታየው ጨለማ ገነገነ እንጂ ያ የነጻነት ቀንም እጅግ ቀርቧል፡፡ የአማራ ጠላቶች አማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ አማራን ከመጨረስ በመለስ የሚቆም አለመሆኑን የምንረዳው አንድን አማራ በመግደል ብቻ ሳይረኩ ሕጻን ሽማግሌ ሳይሉ ሕይወቱን የቀሙትን አማራ ሬሣውን የሚያቃጥሉና በመኪና ወይም በሰው እየጎተቱ ጮቤ በመርገጥ የደስታቸው ምንጭ የሚያደርጉ መሆናቸውን ስንታዘብ ነው – እነሱም ያሳዝኑኛል፤ በጤና እንዲህ አይሆኑምና፡፡ ይህ በየትኛውም ሌላ ሀገር ያልታዬ የጥላቻ ጥግ የሚቆመው ታዲያ ፍቅርንና አብሮነትን የሚያውቅ የማኅበረሰብ አካል አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ነው፡፡ እንዳልኩህ ይህንንም በቅርቡ እናያለን – የሚተርፍ ያየዋል፡፡
ሦስተኛው ሰው ታዬ ቦጋለ አረጋ የተባለው እስስትን የሚያስንቅ ተለዋዋጭ ፍጡር ነው፡፡ ይህ ሰው ሰሞኑን ወደአቢይ ጎራ ተገልብጦ ለአቢይ አህመድ ጽላት ሊያስቀርጽ መሆኑ እየተወራ ነው – ይሳካለት፡፡ ንግግሩን አዳመጥኩት፡፡ አቢይን እንዴት እንደሚያወድሰው ብትሰሙት፣ አቢይ ራሱ ክው ብሎ መደንገጡ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የሚያደርገውን ስለሚያውቅ የታዬ ቦጋለን የመሰለ ማንቆለጳጰስ ለሽርደዳ ወይም ለሌላ ሥውር ፍላጎት እንጂ እውነቱ ሌላ መሆኑን አቢይ መገንዘብ አያቅተውምና፤ ኩሸትን ከእውነት መለየት የሚችሉ የአቢይ አማካሪዎችም ዝም አይሉም፡፡ “ይቺ ጎንበስ ጎንበስ ዕቃ ለማንሳት ነው” ይባላል፡፡ የታይሻ እንዲህ መዝቀጥ ለሆነ ዓላማ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ በታዬ ቦጋለ ዕይታ አቢይ አህመድ የዐዋቂዎች ቁንጮ፣ የብልኆች ብልኅ፣ የፈላስፋዎች አባት፣ የሙያዎች ሁሉ አበጋዝ… እንደሆነ ሲያሞከሻሸው ይደመጣል፡፡
ግን ግን ያቺ በልጅነቴ የማውቃት ኢትዮጵያ ወዴት ተሠወረች? ወይዘሮ ኅሊናን ምን በላት? ወይዘሪት ይሉኝታን ምን ዋጣት? አቶ ሀፍረትስ ለዚህ ዓይነቱ ያገጠጠ መሣቂያ መሣለቂያነት ዳርጎን ወዴት ኮበለለ? አስጨናቂ ዘመን! ሲነጋ የምናፍርበት እጅግ ብዙ ሰቅጣጭና እጅግ ብዙ የተመሰቃቀለ ማኅበራዊ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ እግዚአብሔር ይሁነን፤ አላህ ይድረስልን፤ ዋቃና ጦሳም አይርሱን፡፡ ሌላ ምን ይባላል?