አክሎግ ቢራራ (ዶር)
አንድ የሚያስደንቀኝ ነገር አለ፡፡ ይህች በተከታታይ የአገር ውስጥና የውጭ ሃይሎች በመተባበርም ሆነ በግል ግፍና በደል የሚያደርሱባት አገር እንዴት ልትፈርስ አልቻለችም? የሚለው ነው፡፡ ይህ ተአምር ሆኖ አገኘዋለሁ፤ የቸራትም ፈጣሪ ሊሆን ይችላል የሚግል ግንዛቤ አለኝ፡፡
ልጆቿን ሆነ ብለው በዘውግ፤ በዘር የከፋፈሏት እናማን ናቸው? ለምን? የውጭ ደጋፊዎቻቸውስ ሚና ምን ያህል ነው?
የማስስበው ተጨማሪ አስተያየት ግን፤ በተአምርም ይሁን በሌላ ይህች ታሪክና እውቅና ያላት አገር ልትቀጥል የምትችለው ግን መላው ህዝቧ ተባብሮ በሰላም፤ በፍቅር፤ በፍትህ፟፤ በእኩልነት፤ በመከባበር፤ በመተሳሰብ አብሮ ሲኖርና ኑሮውን ለማሻሻል የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነው፡፡ ድህነት ግጭት የሚፈጥር መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ስልጣን የያዙት ግለሰቦችና ደጋፊዎቻቸው ይህ ለኛ ይጠቅማል የሚል እምነት እንዳላቸው አልጠራጠርም፡፡
ታላቅ አገር ወርሶ ሥግብግብ፤ ትንሺና ለውጭ ሃይሎች ተገዢ፤ አጎብዳጅ መሆን፤ ሃገርን በሙስና የተበከለች ማድረግ ሁላችንንም በተከታታይ በታሪክ እንድሚያስወቅስ ምንም አልጠጠራጠርም፡፡
የኢትዮጵያን ኋላ ቀርነትና ሁሉን መስፈርቶች የሚያካትት ድሃማነት (multidimensional poverty) ወያኔ ሥልጣን ከያዘበት ወቅት ጀምሮ ለማስገንዘብ ከሞከሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነኝ፡፡ እድገትንና ልማትን መለየት ካልቻልን ችግሩ ይቀጥላል፡፡ ልማት አብዛኛውን ህዝብ ይመለከታል፡፡ እድገት በጥቂቶች ለጥቂቶች ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን የገቢና የኑሮ ልዩነት እየሰፋ እንጅ እየጠበበ ሊሄድ አይችልም፡፡ ሰላምና እርጋታ አይቻልም፡፡
አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በድሃማነት፤ በኑሮ ውድነት ተበክሏል፡፡ በክልሎች መካከል ያለው የእድገትና የልማት ልዩነት ሁኔታውን ያባብሰዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ለማን ይበጃል? ባለሥልጣናቱ ለመመስረት የሚመኙት አንድ አገር ነው ወይንስ የተለያዩ አገሮች? እኛስ?
ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት የድርቅ ረሃብ መኖሩን ይክዳሉ፡፡ አንድ ሚሊየን ወገኖቻችንን ለሞት የዳረገው ታላቁ ረሃብ ተብሎ የሚጠራው ከ 1983 እና 1985 ዓመተ ምህረት ከተካሄደበት ወዲህ የድርቅ ረሃብ በአገራችን መከሰቱ ያሳፍራል ብል አልሳሳትም፡፡ ጥያቄው ለምን? የሚለው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከ1 1952 ጀምሮ በተከታታይ በውጭ እርዳታ የምትመካና ጥገኛ አገር መሆኗን በራሱ ያስተቻል፡፡ እርዳታው ምን መዋቅራዊ ለውጥ አስከተለ? የምርት ሃይልን አጎለመሰ? የስራ እድል ለወጣቱ ትውልድ ፈጠረ? ለማንና ለምን ጥቅም ዋለ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በውጭ እርዳታ ላይ የወሰዱት አቋም ራሳችንን እንድንገመግም ያስገድደናል፡፡ በርግጥ ውሳኔው ረሃቡን ያባብሰዋል፡፡ የጥገኝነት መዘዙ ይኼው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ራሷን ከመቻል ውጭ አማራጭ የላትም፡፡ ራሷን ለመቻል ደግሞ ሰላምና እርጋታ፤ ፍትህ፤ እውነተኛ እኩልነት፤ ዲሞክራሳዊ አገዛዝ፤ ተጠያቂነትና ሃላፊነት ያስፈልጋል፡፡
የአሁኑ ረሃብ ልክ እንደ ዱሮው በድርቅ፤ በመጥፎ የመሬት ይዞታና ግብርና ፖሊሲ፤ በየእርስ በእርስ ጦርነት፤ በአየር ጠባይ ለውጥ የተከሰተና የተበከለ ነው፡፡ ልማት ይህንን ሁኔታ ለመቅረፍ ለምን አልቻለም? ብለን የመጠየቅ ግዴታ አለብን፡፡ ህንድ፤ ቻይና፤ ባንግላደሽ ወዘተ የድርቅ ረሃብን ለመፍታት ችለዋል፡፡ እኛ ምን ነክቶን ነው?
ረሃብ ወረርሽኝ ነው፤ ሺብርተኛነት ነው፡፡ አይምርም፡፡ ለወገን ድጋፍ መስጠትም አለብን፤ አንድ ልጅ ማዳን በራሱ የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ የሚረባረቡትን አመሰግናለሁ፡፡
የመሬት ይዞታና የግብርና ፖሊሲው መቀየር አለበት፡፡ የገጠሩን ኢኮኖሚ ዘመናዊ ማድረግ አለብን፡፡
ወደ መሰረታዊው ግምገማየ ስመለስ ለማሳሰብ የምፈልገው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በብዙ ሁኔታዎች የተበከለች አገር ናት ለማለት እንችላለን፡፡
የአንድ ነገድ/ዘውግ፤ ብሄር/ዘር መለየት ፖለቲካ በክሏታል፤ አድክሟታል፤ እያደኸያት ነው፡፡ ረሃብ መጨመሩ ሁኔታውን አባብሶታል፡፡
የዘውግ የበላይነት መርህ መከሰቻዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ በእንግሊዝኛ ያቀረቡትን ስለምጋራው ይባርከዎት እያልኩ ሙሉ በሙሉ እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ፡፡ ትርጉም የራሴ ነው፡፡ ሃላፊነቱ የራሴ ነው፡፡
የዘውግ የበላይነት (ethnic hegemony) እንዲሳካ፤ ተቋማዊውና የተለመደ እንዲሆን ሲፈለግ ታሪክን ሙሉ በሙሉም ማጥፋት ባይቻልም መበረዝ (deconstruct) ያስፈፍልጋል፡፡ ተቋማትን፤ ምስሎችን፤ ባህሎችን፤ እምነትን፤ ቋንቋን ወዘተ ልክ እንደ ሌሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ባሁኑ ወቅት አዲስ አገር፤ አዲስ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት እየተደረገ ነው፡፡ በማን ስም?
ይህ ሂደት ጣልያን ካደረገው የተለየ አይደለም፡፡ የጣልያን የበላይነት፤ የጣልያን ባህል፤ የጣልያን ቋንቋ፤ የጣልያን የበላይነት እና አዛዢነት ወዘተ፡፡
ፕሮፌሰር ህይሌ እንደሚሉት ታሪኩን የረሳ ይረሳል፡፡ “ታሪክ ያለፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የማንነት፣ የፍትህ እና የሀገር ክብር የሚወዛገቡበት የጦርነት አውድማ ነው። ታሪካዊ ትረካውን የሚቆጣጠሩት ሰዎች እራሳቸውን የሚያዩበት፣ ማህበረሰቦች ፍትህን የሚሹበት እና ሀገራት በዓለም መድረክ ላይ ክብራቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው።” ታሪኩን (መነሻውን) የሚክድ ህዝብ መድረሻውን አያውቅም፡፡ በቀላሉ ለውጭ ህይሎች ታማኛና ተገዢ (pawn) ይሆናል፡፡
“ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ ሥልጣኔዎች አንዷ ነች፣ ሆኖም የቅኝ ግዛት ትረካዎች ይህንን እውነታ ለማጥፋት ለረጅም ጊዜ ሲጥሩ ቆይተዋል። የአድዋ ድል (1896) የአውሮፓን ቅኝ ግዛት በተሳካ ሁኔታ የተቋቋመች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን አረጋግጧል። ሆኖም ፋሽስት ኢጣሊያ ያንን ታሪክ በሽብር እና በፕሮፓጋንዳ ለመፃፍ ሞከረ። እንደ አዲስ አበባ ጭፍጨፋ ያሉ ክስተቶች መጥፋታቸው ኢትዮጵያውያ ን ወጣቶችን ታሪካዊ ማንነታቸውን በማሳጣት ለውጭ ተጽእኖ እንዲጋለጡ አድርጓል።”
የፕሮፌሰር ሃይሊ ትንተና ያስታወሰኝ፤ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ተገኝተው “የአድዋ መንፈስ” በሚል ርእስ ያቀረቡትን የባርባዶስ ጠቅላይ ሚንስትር ሚያ አሞር ሞትሊን ታሪካዊ ንግግር ነው፡፡ የነገድ/ዘውግ/የዘር ልዩነት እንዴት አምካኝ እንደሆነም በድፍረት ለመሪዎች አቅረበዋል፡፡ ሰሚ ካለ ማለት ነው፡፡
ጠባብ ብሄርተኛነት፤ ዘረኛነት እልቂት እንደሚያስከትል ደጋግመን አይተናል፡፡ በራሳችን አገር በሰሜኑ ጦርነት ብቻ አንድ ሚሊየን ወገኖቻችን ሞተዋል፤ በብዙ መቶ ሺህ የሚገመት ወታደር አልፏል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ሌላ አምካኝና ጨካኝነት ያአለው ጦርነት በአማራው ላይ እየተካሄደበት ነው፡፡ ይህ እንዴት ብሎ ነው ናዚስቶችና ፋሽስቶች ካደረጉት የሚለየው?
ተጠያቂነትና ፍትህ ከሌለ ሁኔታው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ለእልቂቱ ማን ተጠያቂ ሆነ? “የናዚ ባለስልጣናትን ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ከሚያደርጉት የኑረምበርግ የፍርድ ሂደት በተለየ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በጭካኔ ስለያዘች ፍትሃዊ ፍርድ ገጥሟት አያውቅም። ቶከን ካሳ ሲከፍል፣ ግራዚያኒን ጨምሮ የጣሊያን የጦር ወንጀለኞች ከመኮነን ይልቅ በጣሊያን ተከብረዋል። የምዕራባውያን ሀገራት እና ቫቲካን የኢትዮጵያን ስቃይ ችላ ብለዋል ምክንያቱም የቅኝ ግዛት ግፍ እውቅና መስጠቱ ዓለም አቀፋዊ የበላይነታቸውን ይፈታተነዋል።” ይህ አባባል ትክክል ነው፡፡
ምእራባዊያን አንድ ሰሞን የሰሜኑን ጦርነት አውግዘው፤ በጦር ወንጀል፤ በእልቂት፤ በሴቶች መደፈር የሚጠረጠሩ ሁሉ ለፍርድ ይቅረቡ ካሉ በኋላ ጉዳዩ ተረሳ፡፡ ለምን? ዕኛስ ምን ክትትል አድረኛል? እኔ በሃያላን ላይ እምነት የለኝም፡ እንዲያውም ሁኔታውን ያባባሱት እነሱ ናቸው ለማለት እችላለሁ፡፡
የሌለ ትርክት እየፈጠሩ ያለፈውን ማጥፋት (propagate false narratives and deconstruct Ethiopia) ታስቦበበት በስልት የሚሰራ የአንድ ብሄር የበላይነት ዘዴ ነው፡፡
“ታሪክ ሲረሳ ሀገራዊ አንድነት ይዳከማል፣ የውጭ ሃይሎች መለያየትን ይበዘብዛሉ። ዛሬ የኢትዮጵያ መንግስት የታሪክ ቅርሶችን ችላ ማለቱና ማፈራረሱ፣ የቦታዎች ስያሜ መቀየር እና የታሪክ ምሁርነትን ማፈኑ የጣሊያንን ቅኝ ገዥነት ኢትዮጵያዊ ማንነትን የማጥፋት ስትራቴጂን ያሳያል። በአንድ በኩል ኢትዮጵያውያንን ስልታዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል፤ በሌላ በኩል የጋራ ትውስታን እና ሀገራዊ አንድነትን ስኪታማ ለማድረግ መሞከር ፈጽሞ የማይቻል ያደርገዋል።”
እያወደሙና አያመከኑ ማልማት፤ እጨፈጨፉ አገርን አንድ ማድረግ አይቻልም ማለት ነው፡፡ አገርን እናድን ለሚሉት ወገኖቸ እባካችሁ አገርን ለማዳን በአማራው ህዝብ ላይ የሚካሄደው እልቂት ይቁም በሚል ተረባረቡ እላለሁ፡፡ አምካኙንን አካል አውግዙ፡፡
“ያለፈውን የረሳ ህዝብ የወደፊት ህይወቱን ያጣል። ኢትዮጵያ እየተጠቃች ያለችው በጦርነትና አለመረጋጋት ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ ንቃተ ህሊናዋ በመደምሰስ ነው። ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን ካላስመለሱ፣ ሙሶሎኒ እንዳሰበው በውጭ ኃይሎች በተጣሉ ድንበሮች ላይ እየተፋለሙ የተበታተኑ የጎሳ መከታ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የላቸውም።”
ለዚህ ዋናውና መሰረታዊው ምክንያት የውጭ መንግሥታት ጣልቃ ገብነት አይደለም፡፡ የውስጡ የዘውግ የበላይነት ፖለቲካና አዲስ ታሪክ ፈጠራ ጉዞ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ የሚመክሩን ለራሳችን ስንል ላለፈው ታሪካችንም አምባሳደር እንሁን ነው፡፡ ይህ የአማራ ህዝብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ጉዳይ ነው፡፡ ታሪካችን የጋራ እንጅ የአንድ ዘውግ አይደለም፡፡ የአንድ ዘውግ የበላይነት ጉዞ ይህንን ህብረብሄራዊ አንድነት በክሎታል፡፡
የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት በጦርነት ሊፈታ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ከራሷ የእርስ በእርስ ጦርነት አምካኝነት እና ከጎረቤቷ ከሱዳን አገር አፍራሽ ጦርነት ልትማር ይገባታል፡፡
በ April 2023, የጀመረው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ለብዙ መቶ ሽህዎች ህይወት መቅሰፍት ሆኗል፡፡ በብዙ ሚሊየን የሚገመት የሱዳን ህዝብ ተፈናቅሏል፡፡ ጦርነቱ ለጎረቤት አገሮች ማለትም ለኢትዮጵያ፣ ለቻድ፤ ለደቡብ ሱዳን፤ ለኤርትራ ስጋት ከፈጠረ ቆይቷል፡፡ የካርቱም ከተማ ወድማለች፤ ዳርፉር የደም ውቅያኖስ ሆናለች፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን የውጭ መንግሥታትና ሃይሎች ወገንተኛ በመሆን ሎጅስቲክስ እየሰጡ ሁኔታውን አባብሰውታል፡፡ ለምሳሌ ልክ ኢትዮጵያ ላይ እንደምታደርገው የተባበሩት ኤምሬትስ፤ በተጨማሪ ቱርኮች፤ ሩሲያኖች፤ አሜሪካኖች፤ ግብዖች፤ ሳውዲዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ወገን ለይተው ይደግፋሉ፡፡
ይህ ሁኔታ ክቀጠለ ሱዳን የመከፋፈል እድሏ ከፍተኛ ነው፡፡
ለማጠቃለል፤
በኢትዮጵያ ሆነ በሱዳን የሚያዋጣው የፖለቲካ መፍትሄ እንጅ ጦርነት አይደለም፡፡ ጦርነት አምካኝ መሆኑን በትደጋጋሚ ትንተናዎቸ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡
በመጨረሻ ለወጣቱ ትውልድ የምመክረው እባካችሁ፤ ማንበብና መማር አይሰልቻችሁ፡፡ እውቀት ሃይል ነው፡፡ እንደ ሱስ ሶሻል ሜድያ ብቻ መከታተሉ በቂ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ እንዳሉት “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በ1937 የሆነውን ማወቅ እና መጪው ትውልድ ስለ አዲስ አበባ እልቂት እንዲያውቅ ማድረግ አለበት።”
የምጨምረው ከዚህ ተምረን አሁን የሚካሄደው እልቂት እንዲቆም ለመላው የዓለም ህዝብ ሳንሰለች እናሳስብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት ከዜጎች ክብር፤ ህልውናና መብት ጋር አብሮ መሄድ አለበት፡፡ ህዝብ እየጨፈጨፉ አገርን ለመታደግ አይቻልም፡፡ ፍትህ ከሌለ አገርን ማዳን አይቻልም፡፡
“ የጎሳ መከፋፈልን እምቢ እንበል፤ ታሪካዊ መጥፋትን እንቃዎም፤ የሀገር ሀውልቶች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ቅርሶች እንዲጠበቁ እንረባረብ” ካሉት ከፕሮእፌሰር ሃይሌ ምክረ ሃሳብ የምጨምረው፤ ከዘውጋዊ መለያ ማንነት ይልቅ አብሮ፤ ተፋቅሮና ተከባብሮ መኖርን እናስተጋባ፤ ጦርነትና እልቂት እንዲቆሙ ድርሻችን እንወጣ ነው፡፡
ለጊዜው ቢሆን አገዛዙ ይስማናል የሚል እምነትን ወደ ጎን እንተወው፡፡
ክብር ይስጥልኝ ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ፡፡
February 21, 2025