July 23, 2024
37 mins read

ሞግራው  

Bullበላይነህ አባተ ([email protected])

አቶ ጫኔ ማረሻን ተእርፍ፣ እርፍንም ተሞፈር፣ ሞፈርንም ተምራን፣ ምራንንም ተቀንበር፣ ቀንበርንም ተማነቂያ አስማምቶ ኩሊና ዳመናን ይጠምድና ከቆቅ ውሀ ማርያም በስተሰሜን እንደ ሰማይ ከተዘርጋው የበርባር ሜዳ እያፉጫጨ ሲያርስ ይውላል፡፡ ኩሊና ዳመና ማረሻው ከለስላሳ ምድር ሲገባ ተስማምተው ይራመዳሉ፡፡ ከጠጣር ምድር ሲቸከል ግን መራመዱን ይተውና እንደ ኢትዮጵያ ታጋዮች እርስ በርስ በመጋፋት አቅማቸውን ያባክናሉ፡፡ አቅማቸውን አባክነው መራመድ ሲሳናቸውም በጠማጁ ጅራፍ ይጠበጠባሉ፡፡

ኩሊና ደመና ቆቻ ሲጠመዱ ወይፈኑ ሞግራው ግን ሲግጥና እንቅልፉን ሲለጥጥ ይውላል፡፡ ሞግራው ከኋላው እንደ ጦሮ ሾሎ ከፊቱ ግን እንደ ራስ ደጀን ተራራ ገኖ ሲጎማለል ግዳይ የጣለ አንበሳ ይመስላል፡፡ ይህ አንበሳዊ ሞገሱና ኢትዮጵያዊ ትእቢቱ እንደ ጉልላት ከተቦጀረው ሻኛውና እንደ አድባር ከተገተረው ቀንዱ ተዳብሎ ግርማን አከናንቦታል፡፡ ይህ  የተከናነበው ግርማም ካቶ ጫኔ በረት ተርፎ በድፍን ቆቅ ውሀ ይፈሳል፡፡

ሞግራው እንደ ጀግና ሌላውን እማይነካ፤ ከነኩት ግን እንደ አራስ ነበር የሚቆጣ የከብትን መብትና ግዴታ የተረዳ ቆፍጣና ወይፈን ነው፡፡ በዚህ ቆፍጣና ባህሪውም እንኳን ከቀንድ ከብቶች ክብርን ከማያውቁት አህዮችም ከበሬታን አግኝቷል፡፡ ሞግራው ባዕድ ከብት ሲመጣ ጥርሱን አነቃንቆ ወደመጣበት ይመልሳል፡፡ በዚህ አይደፈሬነቱ እንኳን በሰፈሩ በድፍን ቆቅ ውሀም ታውቋል፡፡ ያካባቢው ሰዎች እንደ አንዳርጌ ካሳ እሚያስፈራ ሽፍታን በስሙ መጥራት ፈርተው የምድር-ለምድሩ ብለው እንደሚጠሩት ከብቶችም የሞግራውን ስም መጥራት ፈርተው የመስክ- ለመስኩ ብለው ይጠሩታል፡፡

ኩሊና ደመና በቆቻ እርሻ አቅማቸው መነመነ፡፡ ይህን የአቅም መመንመን የተረዳው አቶ ጫኔ ሞግራውን ረዳት ሊያደርገው ወሰነና ሊያሰለጥነው ቀንበር እንደተኛ ከሞግራው ማጅራት ጫነ፡፡ የተጫነበት ቀንበር ሞግራውን እንደ ዛር አስጎራና ከተኛበት አስነሳው፡፡ ሞግራው ቀንበሩን እንደ ሟርት አሽቀንጥሮ ጣለና ደጋግሞ ረገጠው፡፡ ይህንን እብሪት የተመለከተው አቶ ጫኔም በመጫኛ ጠልፎ ሌላ ቀንበር ተሸከም አለው፡፡ ሞግራው ግን አይኑን እንደ ጉርጥ አጉረጠረጠና አቶ ጫኔን አሻፈረኝ አለው፡፡ አቶ ጫኔ በጅራፍ ቢገርፈው፣ በወገልም ቢጠብሰው ማህተመ ጋንዲን፣ ኔልሰን ማንዴላን፣ ማርቲን ሉተር ኪንግን፤ ሳሙኤል አወቀን ሆነና ቁጭ አለ፡፡ እርሱም እንደነዚህ ፍትህ ፍላጊዎች እምቡ… ብሎ ጮኾ “ቀንበር ይውደም!” ሲል አመጠ፡፡ አቶ ጫኔም እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግና እንደ ሳሙኤል አወቀ ገዳዮች ጭራቅ ስላልሆነ የሞግራውን ጽናት አድንቆ ምሀረት አደረገና መግረፉን አቆመ፡፡ ምህረት የተደረገለት ሞግራውም ወደ መስኩ ነጎደ፡፡

ሞግራው ቀንበር ሳይሸከም የእርሻው ወራት አልፎ መኸሩ ደረሰ፡፡ መኸሩ ሲደርስም አቶ ጫኔ ሞግራውን እህል ለመውቃት ሊጠቀምበት ፈለገ፡፡ አቶ ጫኔ ጥር አስራ አራት ቀን ጤፍ ሲወቃ ኩሊና ዳመና አውድማ ውስጥ አንገታቸውን አቅንተው ለመታፈን አፋቸውን ሲሰጡ ሞግራው ግን አሁንም ዓይኖቹን ተዋሻቸው አውጥቶ እንደ ልቅ አንጎለጎለና አሻፈረኝ አለ፡፡ አቶ ጫኔን በንቀት ደፍቶ እያዬ “ቡ…እምቡ…እምቡ…! ቡ…እምቡ…እምቡቡውውው!!!…” ብሎ እንደ ሸላዩ ሞላ ሰጥአርጌ አቅራርቶ ቀንዱን እንደ በልጅግ ከወድያ ወዲህ እያገላበጠ  ፎክሮ እምቢተኝነቱን ወደ ኃይል አሸጋገረ፡፡ ማፈኛውንም ከአቶ ጫኔ እጅ እንደ ጪላት በምላሱ ነጥቆ አመንዥኮ ቦጫጨቀ፡፡ ግራ የገባው አቶ ጫኔም ሞግራውን ሳያፍን “ዙር!” አለና ጀርባውን በለበቅ ሸነቆጠ፡፡ ሞግራውም ሽንቆጣውን ታግሶ ጤፉን እየጎረሰ መዞሩን ቀጠለ፡፡ ጤፉ ጭድ ሲሆንና ከሚጎረሰው ፍሬ ሲያጣ ካውድማ ወጣና ፈረጠጠ፤ ሊመልሱት ሲከጅሉም እንደ ግራር ቅርንጫፎች በተዘረሩ ቀንዶቹ አስፈራርቶ አመለጠ፡፡

ሞግራው ከሜዳው ሳሩን ከአውድማም ፍሬውን እየዛቀ ማጅራቱ እንደ እባጭ አበጠ፤ ሻኛውም እንደ ጤፍ ክምር ተጎለለ፡፡ አቶ ጫኔም ሞግራውን ሊገራ እንደማይችል አመነ፡፡ በዚህም ምክንያት ለፋሲካ ቅርጫ ሊያቀርበው ወሰነ፡፡ የአቶ ጫኔ ባለቤት ወይዘሮ የሻረግ ግን “ሬሳዬ ሳይወጣ ወይፍኔ አይታረድም!” አለች፡፡ የወይዘሮ የሻረግ ተቃውሞ ያበሳጨው አቶ ጫኔም “በማጀቱ አዝዥ፣ የውጩን ለኔ ተይ!” አለና ሞግራውን ለቅርጫ አቀረበው፡፡ ለቅርጫ ሊታረድ ሲቀርብ ወይዘሮ የሻረግ ከማጀቷ ወጥታ “ሞግራው! እነዚህን ሆዳሞችን አንጰርጵረህ ዘለሰኛ ጣላቸው” ስትል አዘዘችው፡፡ ሞግራውም የሰማት ይመስል “ቡ…ቡ…እምቡ…እምቡኡኡኡ!” ብሎ አቅራርቶ ፎከረና መጥለፊያ መጫኛ ይዘው በመደዳ የቆሙትን ምስጥ እንዳመሸከው አጥር ዘለሰኛ ጣላቸው፡፡ ዘለሰኛ ተወደቁበት ተነስተው ዳግም ሊጠልፉ ሲሞክሩ ከጠላፊዎች አንዱ የሆነውን የቀበሌውን ሊቀመንበር ሞግራው ሰቅስቆ አነሳና እንደ ኳስ ወርውሮ ከግራር ሰቀለው፡፡ ከግራር የተሰቀለውን ሊቀመንበር የተመለከተ አንድ የሰፈሩ ሰው “ሊቀመንበሩ ለፍርድ ወደ እግዚሃር እየቀረበ ነው” ሲል ሌላው በሊቀመንበሩ ምግባር የተንገፈገፈ ተመልካች ቀጠለና  “ተወንበሩ እንጅ ተግራሩ እንዳታወርዱት!” ሲል ተማጠነ፡፡ በዚህ ግርግር ሞግራው ጠላቱን ድባቅ እንደመታው አበበ አረጋይ እየተጎማለለ ከብቶችን ተቀላቀለ፡፡ የሞግራው እምቢተኝነት እንቅልፍ የነሳው አቶ ጫኔ ሞግራውን በበልጅግ ሊገለው ከጀለ፡፡ ነገር ግን ከብትን በጥይት መምታትም ሆነ ሳይባርኩ መብላት ክልክል መሆኑን አስታወሰና በሞግራው ፋንታ አመጽ እማያውቀውን ኩሊን አረደና ለቅርጫ አቀረበ፡፡ ሞግራውንም ለመሸጥ ወሰነ፡፡

በሞግራው ድል ማግስት የእነ ወይዘሮ የሻረግ ጎረቢት ወይዘሮ ሙሉእመቤት “የሻረግ፣ ወርቅ ያንጥፉ፣ ታንች ወዲያ፣ ሥለናት፣ ጦቢያው! “ኑ ቡን ጠጡ…!” ብላ ጎረቢቶቿን ጠራች፡፡ መጀመሪያ ወይዘሮ ታንቺ ወዲያ ነጠላዋን ደርባ መንቀር- መንቀር እያለች፤ ቀጥሎም፣ ወይዘሮ ሥለናት ትፍትፍ መቀነቷን ሸክፋ ሸፈፍ-ሸፈፍ እያለች፤ ከዚያም ወይዘሮ ወርቅ ያንጥፉ ንቅሳቷን እንደ ጀንበር አብርታ ጎርደድ-ጎርደድ እያለች፤ ቀጥሎም ወይዘሮ ጦቢያው ጠልሰሟን ሹዋ! ሹዋ! አድርጋ ዘንከት-ዘንከት እያለች ከመጡ በኋላ ወይዘሮ የሻረግ ሎሚ እሚመስሉ ተረከዞቿን በአልቦ አስጊጣ ያንን እንደ ሐረግ እሚታጠፈ እሚዘረጋ ወገቧን ሳብ- እረገድ ሳብ-እረገድ እያደረገች ተጀንና ገባች፡፡ ሁሉም ወይዛዝርት እንዝርታቸውን እያሾሩ መፍተል ጀመሩ፡፡ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ከኩሊ ቅርጫ ሥጋ ጠብሳ ከአዋዜ ጋር አቀረበች ፡፡ ተኩሊ ስጋ የተዘጋቸውን ጥብስ የተመለከተችው ወይዘሮ የሻረግ በሐዘን ተውጣ “ሲቀልበኝ የኖረውን ኩሊን ልብላ? እርም ይሁንብኝ አልነካውም” አለች፡፡ ወይዘሮ የሻረግ ማዘኗን የተረዳችው ወይዘሮ ሙሉእመቤት “ሳትማከሩ ነው ኩሊ ለቅርጫ የቀረበው?” ስትል ጠየቀች፡፡ “ሳትማከሩ አልሽ? ሚስቱን እሚሰማ እንኳን ተቆቅ ውሀ ተድፍን ጦቢያም አንድ ጥቀሽ!” አለች ወይዘሮ የሻረግ አንዷን ጣቷን ሽቅብ እንደ አንቴና ቀስራ፡፡

ተወይዘሮ የሻረግ የተስማማችው ወይዘሮ ሙሉእመቤት “እሱስ እውነትሽን ነው! የሞግራውን ድምጥ ሲሰሙ ጆሯቸው ይቆማል እንጅ እኛንስ ጀሮ ዳባ ነው እሚሉን!” ብላ ሳትጨርስ ሁሉም ሴቶች ሞግራውን ሲሸሹ ምስጥ እንዳነከተው አጥር ተያይዘው የወደቁት ባሎቻቸውን ባይነ-ህሊናቸው መጡባቸውና “እህህህ… እህህህ…እህ….እህህህ.. እያሉ አንዴ አፋቸውን ሌላ ጊዜ ሆዳቸውን እየያዙ እንስተሚፈነዱ ሳቁ፡፡ እስተምትፈነዳ የሳቀችው ወይዘሮ ወርቅ ያንጥፉ “ሞግራውን ምን ብትቀልቢው ነው እንደ በሰበሰ አጥር በመደዳ ያነጠፋቸው? ብላ ወይዘሮ የሻረግን ጠየቀቻት፡፡ የተጠየቀችው ወይዘሮ የሻረግም “ቀለብ ነው ብለሽ ነው? ቀለብ ቢሆንማ ጫኔም ሞግራው ታረጀ ግራር የሰቀለውን ሊቀመንበር ይቅርና መንግስትንም አንቀጥቅጦ እንደ ባዶ ቁልቢጥ ይገለብጥ ነበር” አለች፡፡ “ሊቀመንበሩማ ሊቀግራር ሆነ እኮ!” አለች ወይዘሮ ሙሉእመቤት፡፡ “እውነትም ሊቀግራር! ተሞግራው ቀንድ ተስፈንጥሮ ተግራሩ ሲወተፍ ንፋስ የወሰደው አሮጌ ባርኔጣ መሰለ” ብላ ወይዘሮ ጦቢያ ሳትጨርስ ሊቀግራሩ ተግራሩ ላይ አገልግሎቱን የጨረሰ የወፍ ጎጆ መስሎ ታያቸውና ” እህህህ… እህ..  እህህህህህ.. ወይኔ ፈነዳሁ! እህህህ… እህ..  እህህህህህ.. ወይኔ ፈነዳሁ!” እያሉ አሁንም ሳቁን አቀለጡት፡፡

“ሞግራው በነካ እጁ ጠሐፊውንም፤ ገንዘብ ያዡንም፤ እኒህን ካድሬ እሚባሉትንም ተሊቀግራሩ ጎን ቢያስቀምጣቸው ጥሩ ነበር አለች” ወይዘሮ የሻረግ ቡናዋን ጨልጣ ፍንጃሉን ከገንዳው እያስቀመጠች፡፡ ብዙም ያልሳቀችው ወይዘሮ ሥለናት “የሰው ጉዳት አያስቅም፤ ጡር ነው” አለች፡፡ በወይዘሮ ሥለናት ሐሳብ ያልተስማማችው ወይዘሮ ጦቢያው “አንቺ ደሞ ልብሽ እንደ ተነደፈ ጥጥ ስስ ነው!  እነ ሊቀግራሩ እኮ የጋኔን ተከታዮች ናቸው፡፡” አለች፡፡ “እነ ሊቀግራሩ የጋኔን ተከታይ ተተባሉ! የጋኔን ተከታዮች የሚሸኑባቸው የእኛ ባሎች ምን ሊባሉ ነዋ!” ስትል ጠየቀች ወይዘሮ ሙሉእመቤት፡፡ “ጡርቂ” ብላ ወይዘሮ የሻረግ ባንድ ቃል ስትመልስ ጡርቂ በነወይዘሮ የሻረግ ባህል የወርደት ቃል ስለሆነ አሁንም ሴቶቹ በሳቅ ፈነዱ፡፡ ወይዘሮ ሥለናት ሳይቀር ፈርፈር ብላ ሳቀች፡፡ “እኛ ጡርቂ ታቅፈን የምናድረውሳ ምን እንባል?፡፡” ስትል ጠየቀች ወይዘሮ ወርቅ ያንጥፉ በበኩሏ፡፡ “ጡርቂ ታቃፊዎች!” ስትል መለሰች ወይዘሮ የሻረግ አሁንም፡፡

ወይዘሮ የሻረግ እንዝርቷን አስቀምጣ “እንደ ሞግራው ቀንበር አይጫንብንም፤ አፋችንም አይታፈንም፣ አንገዛም፣ አንሸጥም እስታላሉ ድረስ ጡርቂቆችን ማቀፍ እናቁም!” ስትል አድማ ጠራች፡፡ “ተባሎቻችን ስለሚያፋታን በዚህ አልስማማም ” አለች ወይዘሮ ታንቺ ወዲያ፡፡ “ድንቄም ባል! ያህያ ባል ተጅብ አያስጥል!  ያንጠለጠለው ሁሉ ባል ነው?” አለች ወይዘሮ ጦቢያ ወይዘሮ የሻረግን በመደገፍ፡፡ “ያንጠለጠሏትን ይዘው መለኮ ፍለጋ ካምቦ ቢሄዱሳ!” ስትል ወይዘሮ ሥለናት ስጋቷን ገለጠች፡፡ “የካምቦ መለኮም ቆፍጣናና ጀግና ይመርጣል! መለኮም ጡርቂ መታቀፍ አይፈልግም” አለች ሁሉም ሴት እንደ ራሷ እሚመስላት ወይዘሮ የሻረግ፡፡ “የካምቦ ወንዶችስ ተኛዎቹም የባሱ ጡርቂዎች ናቸው፡፡ ጀርሲ ቀሚስ ላሰፋ ካምቦ ኸጄ የጥጥ ፍሬ እሚያህል ቦሊስ ወጋግራ እሚያህለውን ፊቱን እንደ ሙሽራ የተቀባባና ጠጉሩን እንደ ሴት የከፈከፈ ጠብደል ሲጠበጥበው አይቼ ቦሊሱን ሳይሆን የተጠበጠበውን መለኮ ጠብደል ጠፍጥፊው-ጠፍጥፊው አሰኘኝ” አለች ወዘሮ ወርቅ ያንጥፉ፡፡ “የካምቦው መለኮ ወንድ መንጦርቀቅ ወደኛም ተዛምቶ ቤታችን በጡርቂቆች ተሞላ እኮ! ጡርቂ መጠፍጠፉን ተቤታችን እንጀምር!” እየተባባሉ ቡናውን አክትመው ተለያዩ፡፡

ወይዘሮ የሻረግ ወደ ቤቷ ተመልሳ ከጎረቢቶቿ ጋር ያወሩትን ስታወጣ ስታወርድ ሞግራው ከዋለበት እንደ ልማዱ ሻኛውን አንዴ ወደ ግራ ሌላ ጊዜ ወደቀኝ እያጎማለለ መጣ፡፡ “ቆፍጣናው ሞግራውዋ” ብላ ገበታ ስታሳየው መጣና የቀረበለትን ውሀ በጨው መጠጣት ጀመረ፡፡ ሞግራው የጨው ውሀውን ሲጠጣ  ወይዘሮ የሻረግ ቦራ ግንባሩን በጣቶቿ እያከከች “በመጫኛ ጠልፈው ሊያርዱህ ሲከጅሉ ያሳዬኸው ጀግንነት እንደ አምስቱ ዘመን የነበላይ ዘለቀና ጫኔ ተረፈ ጀግንነት  በብራና እሚጣፍ ታሪክ ነው፡፡ በተለይ ያንን መዋጮ ታላዋጣችሁ ሽኳር የለም፣ ጉቦ ታልሰጣችሁ ላምባ የለም፣ መቅቡጥ ታልሰጣችሁ አሞሌ ጨው የለም፣ እኔን ታልመረጣችሁ ማዳበሪያ የለም! እሚለውን ጅርብሳም ተሊቀመንበርነት ወደ ሊቀግራርነት መቀየርህ ቅዱስ ሥራ ነበር። ሊቀግራሩ ማዳበሪያ እንድታገኙ ምረጡኝ ሲላቸው ካርዳቸውን አንጠልጥለውና ጅናቸውን እንደ ቡችላ ወትፈው እሚንጦሎጦሉትንም ተግራር ብትሰቅላቸው ሸጋ ነበር!” ብላ ሳትጨርስ “ቡኡ…” አለ ሞግራው ፊቱን ወደ ወይዘሮ የሻረግ አዙሮ፡፡

ሞግራውን ውሀ በጨው ካጠጣች በኋላ ወይዘሮ የሻረግና አቶ ጫኔ ራት በልተው ተኙ፡፡ አቶ ጫኔ  “እህ..እህ.. ብሎ ጎረሮውን ጠራረገና  ሲፈራ ሲቸር ወይዘሮ የሻረግን ሊያቅፍና ሊፈቅድ ቀኝ እጁን ዘረጋ፡፡ ” ወግድ! ንክች ታረገኝና! አትንካኝ! አትንካኝ ብያለሁ! ጡርቂ! ቦቅቧቃ!” አለች በቁጣ፡፡ “እምቢ ታልሽ ሌላ ሚስት ይፈለጋላ !” አለ አቶ ጫኔም ሊያስፈራራ፡፡ “አይጡም፣ ሞጭሞጭላውም ሲያዝዘው እሺ እሚል ቦቅቧቃ እምትፈልግ ታለች ትውሰድህ! እኔ የሻረግ ደመላሽ እንደ ባርያ እሚታዘዝ ወንድ በዘሬም የለ! ድፍን ጉባያና ሸበል ይመስክር ” አለች፡፡

ይህ ወይዘሮ የሻረግና አቶ ጫኔ የተጋጩበት ሌሊት ሲነጋ ወይዘሮ የሻረግን ሳያማክር አቶ ጫኔ ሞግራውን ሊሸጥ መጬ ገበያ ነዳው፡፡ መጬ ገበያ በቁሳቁሶችና ብሉይ ኪዳን ለመብል በፈቀደው ሁሉ ጢም ብሎ ገና ሳይረፍድ አልባ ባልባ ሽቷል፡፡ ባውንዱ፣ ዝሐውና ጥለቱ በምዕራብ ገጥ ተደርድሯል፡፡ ጤፉ፣ ስንዴው፣ ሽምብራው፣ ባቄላው፣ አተሩ፣ ምስሩ፣ አብሹ፣ ጌሾው፣ ቅርንፉዱ፣ ዘቃቅቤው፣ ሎሚው፣ ብርቱካኑ፣ ሙዙ፣ እንኮዩ፣ አገዳው፣ ማሩ፣ ቅቤውና አደሱ ከደቡብ እሰተ ሰሜን ተዘርግቷል፡፡ በጉ፣ ፍየሉ፣ ወይፈኑ፣ ጊደሩ፣ ላሙንና በሬው ደግሞ በምስራቅ ገጥ ተገትሯል፡፡ አቶ ጫኔና ሞግራውም በምስራቁ ገጥ ቆመዋል፡፡

ከሞግራው አይኑ ያረፈ አንድ ገዥ “ባለ ወይፈን” ብሎ ጠይቆ አቶ ጫኔ “ወዲህ ሲል!” ጠጋ አለና “ስንት ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡ አቶ ጫኔ አመፀኛውን ሞግራውን መገላገል ስለሚሻ አነስተኛ ዋጋ ጠየቀ፡፡ በዋጋው ማነስ የደነገጠው ገዥም “ምን ጉድለት ቢኖርበት በዚህ ዋጋ ይሸጠዋል?” ብሎ አሰበና ጉድለቱን ለመፈለግ ሞግራውን አገላብጦ ተመለከተው፡፡ የጨው አንካር እያሳየ ” እንክ..እንክ  እምጱ….እምጱ” እያለ ሞግራውን አባበለው፡፡ ሞግራው ግን  ፀጉሩ፣ ሻኛውና ጅራቱ እንደ አድዋ አርበኛ ጦር ተገተረ፡፡ ገዥው  አሁንም “እንክ … እምጱ …እምጱ..”  እያለ ተጠጋው፡፡ ትእግስቱ የተሟጠጠው ሞግራው ይህንን ገዥ በቀንዱ አንስቶ በሻኛው እሽኮኮ ያዘና ከጡጦ እንዳልወጣ ልጅ ነጠር- ነጠር እያደረገ አጫወተው፡፡ ከዚያም በቀንዶቹ አፈስ አርጎ እንደ ኳስ ወደ ሰማይ አጉኖ አፈር በአካፋ እንደሚዝቅ ግንበኛ ወደ ኋላው አሽቀነጠረው፡፡ “እግዞ መሀርነ ክርስቶስ!” አለ ብዙ ሕዝብ እራሱን እየያዘ፡፡ ሞግራው ያሽቀነጠረው ሰው ሊቀመንበር ሳለ ግፍ የሰራባቸው ያገሩ ሰዎች ደሞ “የእግዚሃር ቁጣ ነው! ለባለስልጣን እየተላላከ በሰራው ግፍ ተፈረደበት! ትውል ትደር እንጅ የእግዚሃር ፍርድ አትቀር” እያሉ ይንሾካሾካሉ። ይህንን ሹክሹክታ የሰማ ያቶ ጫኔ ጎረቢት “ሞግራው ተመላእክት ይነጋገራል ልበል? ግፈኛ ሊቀመንበሮችን እያነሳ ተግራር ይሰቅላል፤ ተመሬትም ያነጥራል! ወይ ታቦተ እስራኤል” አለ፡፡

ሞግራው ላለመሸጥ በወሰደው እርምጃ በከብት ገበያው ግርግር ተፈጠረ፡፡ ወደ ተፈጠረው ግርግር ስንዴ ዘርግታ የተቀመጠችው ወይዘሮ የሻረግ ፊቷን ስታዞር ሞግራውን ተከቦ አየቸው፡፡ “የጭንቅ አማላጅቱ! ሞግራውን  ማን አመጣው!” አለችና ስንዴውን በትና በራ ከበት ገበያ ስትደርስ ሞግራው ያሽቀነጠረው ሊቀመንበር ወንድም ሞግራውን በክላሽንኮቭ ሊገል ሲገለገል አየችው፡፡ አይኗ ተማቶቱ ወጥቶ ከንፈሯ እየተንቀጠቀጠ “እኔን ግደል!” አለችና በሞግራውና በገዳዩ በመካከል ቆመች፡፡ አንዴ መሳሪያውን ወደ ደቀነው የሊቀመንበሩ ወንድም ሌላ ጊዜ ወደ ተመልካቹ ሕዝብ እየዞረች “ቀንበር እምቢ፣ ማነቂያ አሻፈረኝ፣ ሲያፍኑት አካኬ ዘራፍ፣ ሲገርፉት እምቢ! ሲያርዱት እንጃባክ፣ ሲሸጡት እንጃልህ ! የሚል ጀግና ይሸለማል እንጅ አይገደለም፡፡” አለች፡፡ አሁንም አፍጥጦ ወደ እሚያያት ሕዝብ ዞራ “ሞግራው ገብር ሲሉት እሽ፣ መዋጮ ሲሉት እሽ፤ ለሽኳር ጉቦ ሲሉት እሽ፣ ለጨው መቅቡጥ ሲሉት እሽ፣ ለማዳበሪያ ምረጡን ሲሉት እሽ እሚል ጡርቂ አደለም! ሞግራው ጅናውን ወትፎ የሚንጦለጦል ቡችላ አደለም፡፡ ስለዚህ እንኳን ሊገደል አይሸጥም” ስትል “እውነቷን ነው! ትክክል ነው! እያለ አብዛኛው የገባያው ሕዝብ አጨበጨበ፡፡ ይህን የወዘሮ የሻረግን ንግግር የሰማ ተከተማ የመጣ የዶሮ ነጋዴ “ይህቺ ሴትዮ ለሆዱ ሲል ሕዝብ የሚፈጀው ፌደራል ፖሊስ ቢኖር አልቆላት ነበር” አለ፡፡ ወይዘሮ የሻረግ ሕዝቡ የልቡን ስለተናገረችለት አደነቃት፡፡ እንኳን ሕዝቡ ሞግራውን ሊገል የቃጣው የሊቀመንበሩ ወንድም በጀግንነቷ ተደንቆ ከእግሯ ወደቆ ይቅርታ ጠየቃት፡፡

በወይዘሮ የሻረግ ወኔ የተደሰቱ መልከ መልካሟ እማማ ማራኪ “ጎሽ የኔ ልጅ! ጅግና ውለጅ! ብለው መረቁና እንደ መስፍን ወልደማርያም ከዘራቸውን ተመርኩዘው ካጠገቧ ቆሙ፡፡ ወይዘሮ ማራኪ “ወንድ እወዳለሁ!” ሲሉ ወንዱ ሁሉ ወንድነቱን ሊያሳይ ከተከሻው ነፋ፤ ከደረቱ ለጠጥ፤ ከአንገቱም ቀና ማለት ጀመረ፡፡ “እምወደው ግን እንደናንተ ዓይነቱን በቀውጢ ወቅት አንገቱን እንደ ክረምት አይጥ ተጉድጓድ እሚወትፍ እንዳይመስላችሁ!” ሲሉ ደረቱን የነፋው ወንድ ሁሉ እንደሽቦ እየተኮማተረ መሸሽ ጀመረ፡፡ “እምወደው በቀውጢ ወቅት አንገቱን መዞ ደረቱን ነፍቶ አሻፈረኝ! እምቢ! እንጃባክ! የሚል ጀግና ነው! እግዜር እስተቀማኝ ድረስም አሻፈረኝ የሚል ጀግና ሚስት ነበርኩ፡፡ ምነው አሻፈረኝ እሚል ወንድ ጠፋ! የጀግና ማሳውን አገሬን ምን ነካው! ምን አገኘው!” አሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፡፡

እማማ ማራኪ ቀጠሉና “አሻፈረኝ የሚል ስለጠፋ ውርደታችን ዳግ አቷል፡፡ ዩንበርቲ የበጠሰ አንድ አስኳላ “ባለስልጣኑ ድፍን አማራን ባባዶ እግሩ እሚሄድ ክላጫም ብሎ ሰደበ!” አለኝ፡፡ አሁን ማ ይሙት ክርስቶስ በባዶ እግሩ መሄዱን እማያውቅ ታኒካ ራስ እንዴት ስልጣን ይይዛል? እንዴትስ ድፍን አማራን ክላጫም ብሎ ሰድቦ ተስልጣን ይቆያል? ይህንን ስድብ ተሰማሁ ጀምሬ መንፈሴ እንደ ድቡቅ ደፍርሷል” አሉ እንደ ድቡቅ የደፈረሰውን መንፈሳቸውን ሊያሳዩ ጣታቸውን ከራስቅላቸው ተክለው። “ይህን አሳዳጊ የበደለው ለከት የለሽ ባለስልጣን እንኳን ዥልጦ እሚያወርድ ጅግና ጠፍቷል፡፡” አሉ ከዘራቸውን  እንደ አለንጋ እየሰበቁ፡፡ ወይ አገሬ! ያምስቱን ዘመን ፋኖዎች የተኩት የኔ ዘመን ጀግኖች ታሪክ እንኳን ስንክሳር ነው፡፡ እንኳን ዝቅዝቅ ታይተውና ተሰድበው ትምርት ቤት ታልሰራችሁ፣ መንገድ ታልጠረጋችሁ ሽልንግ ታምሳ አንገብርም እያሉ መንግስትን ያንቀጠቀጡ እጅግ ብዙ ነበሩ! የእነ አንጋች አዳሙ፣ የእነ ፍታራሪ ጫኔ! የእነ አንዷለም አዘነ፣ የእነ ቦራ ባዩ! የእነ ደምስ አላምረው፣ የእነ ባምላኩ አባጅዎን፣ የእነ ውባለ ተገኔ፣ የእነ ፍታራሪ ትርፌ፣ የእነ ሰውነት ያዜ፣ የእነ አንዳርጌ ካሳ አጥንት ይመስክር! አሉ፡፡ “እሳት አመድ ይወልዳል! እማይህ ወንድ ሁሉ ሰንቅህ የላላ፤ ሱሪህ የተውለደለደ የማትፋጅ አመድ ነህ” ሲሉ አንድ የእንቁላል ነጋዴ “እማማ ሱሪን ጭን ላይ ታጥቀው እሬባቸውን እያሳዩ መዥገር እንደ ሸበባት ላም አጎንብሰው የሚውለደለዱትን የካምቦ ልጆች ቢያዩ ምን ሊሉ ነው?” አለ፡፡

በእማማ ማራኪ ንግግር ቅቤ የጠጣችው ወይዘሮ የሻረግም እማማ ማራኪን አመስግና የሞግራውን ግንባር እያከከች “አንበሳዬ ዳግም አኮራኻኝ፡፡ ወደፊትም ሊጠምድህ፣ ሊያፍንህ፣ ሊገርፍህ፣ ሊያርድህ፣ ጨው ሊከለክልህ፣ ሊገዛህ፣ ሊያዋርድህ እሚሻውን እንደ እምቧይ እያነሳህ አፍርጠው!” ስትለው “እምቡ… እምቡ..” አለ፡፡ ወይዘሮ የሻረግም የሞግራውን እምቡ እንደ እሽታ ቆጥራ “እመቤቴ ማሪያም እሽ ትበልህ! ቅዱስ ምቺያልም ይከተልህ!” ብላ መረቀችው፡፡

ገበያተኛው የሞግራውን፣ የወይዘሮ የሻረግና የእማማ ማራኪን ጀግንነት እያደነቀ ወደየመጣበት ተመለስ፡፡ ወይዘሮ የሻረግም ስልትሸጥ የወሰደችውን ስንዴዋን ለሞግራው አበላችና ከአቶ ጫኔ ጋር ወደ አገራቸው መጓዝ ጀመሩ፡፡ ትንሽ እንደተጓዙም “ሀረግዋ” አለ አቶ ጫኔ ሰምታው በማታውቀው የቁልምጫ አጠራር፡፡ ሚስትን በቁልምጫ መጥራት በባህሉ ያልተለመደ ስልሆነና ብርቅ ሆኖባት እንዲደግመው ፈልጋ ነጠላዋን ጎርሳ እየሳቀች እንዳልሰማች ሁሉ ዝም አለች፡፡ “ሀረግዋ!” አለ አሁንም ድምጹን ጨመር አድርጎ፡፡ “አቤት” አለች ልቧ ፍርክስክስ ብሎ በለሰለሰ ድምፅ፡፡ “አንችም ሞግራውም አኮራችሁኝ፣ ታንችም ተሞግራውም ተምሬአለሁ፡፡ ታሁን በኋላ እኔም አሻፈረኝ እላለሁ” አለ፡፡ ባቶ ጫኔ የሐሳብ ለውጥ የተደሰተችው ወይዘሮ የሻረግ “እማማ ማራኪ ታኒካ ራስ ያሉትን ያንን ድፍን አማራን የተሳደበውንም አሻፈረኝ ትለዋለህ አደል?” አለች፡፡ “ታኒካ ራሱ ባለስልጣን አውሬ አዬኝ ይበል!” አለ አቶ ጫኔ፡፡ “ግን.. ግን..ግን እንዳትጎዳው! ጅግና በትግስት ትምርት ይሰጣል እንጅ እንደ ጡርቂ አያሰቃይም፡፡ ጨስ ቅሩብ እንዳስተማሩትም ባምሳሉ የሰራውን ሰው ማሰቃየት አይገባም፡፡ ሞግራውን እንኳን አታይም! ታግሶ ታግሶ ሲደፍሩት እንደ እምቧይ ሰማይ አድርሶ ያፈርጣል እንጅ እንደ ላም አሸናፊ በአሰስ በገሰሱ አይተናኮልም፡፡ “ብላ የጀግናን ባህሪ በምሳሌ አስረዳችው፡፡ “ምክርሽን ተቀብያለሁ ሀረግዋ!” አለ አቶ ጫኔ፡፡

በአቶ ጫኔ የባህሪ ለውጥ የረካችው ወይዘሮ የሻረግም እንኳን በቁልምጫ በስሙም የማትጠራውን ባሏን “ጫኑዋ!” ብላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠራችው፡፡ እርሱም ዳግም እንድትጠራው ፈለገና እንዳልሰማ ሁሉ እያፉጫጨ ማዶ ማዶ ማየት ጀመረ፡፡ “ጫኑዋ!” አለችው ድምጿን ከበፊቱ ከፍ አርጋ፡፡ “እመይት!” አለ አቶ ጫኔ፡፡ “ዛሬ ማታ ስንተኛ እንደ በቀደሙ “ወግድ! አትንካኝ! እያዋልኩ አላመናጭቅህም” አለችና በነጠላዋ ፊቷን ሸፍና በሳቅ ተንፈራፈረች፡፡ እርሱም ነጠላውን ከአፍንጫው ጣል አርጎ በሳቅ ፈነዳና እቅፍ አረጋት፡፡ “ተው… ተው… ሰው ጉድ ይላል! መሪጄታ ዲበኩሉ ‘ለሁሉም ግዜ አለው’ ያሉትንም አስታውስ አለችው፡፡ ወይ አንቺ! አንዴ ጀግና! ሌላ ጊዜ ቄስ መልሶ ደሞ መሪጄታ ያረግሻል! ታድዬ!” ብሎ ቀለደና “እሽ ለሁሉም ጊዜ አለው!” ብሎ ወገቧን ለቀቀ አርጎ እንደ ባህሉ እሱ ከፊት እየተጎማለለ እሷም ከኋላ እየተንዥራገደች ሞግራውን እየነዱ ተደጃቸው ደረሱ፡፡ ተደጃቸው እንደደረሱም መጠመድን፣ መታረድን፣ መታፈንን፣ መሸጠንና መገዛትን በእምቢተኝነትና በክንዱ ያንበረከከው ሞግራው “ቡ! እምቡ..! ቡ! እምቡ! ቡ! እምቡ…” ብሎ ፎክሮ  እንደ በላይ ዘለቀ ነፃነቱን ሲያበስር ወይዘሮ የሻረግና አቶ ጫኔ “ትምርትህም መልክትህም ገብቶናል” ብለው  ሞግራውን እጅ ነሱና ተቃቅፈው ወደቤታቸው ገቡ፡፡

 

መጀመርያ ሐምሌ ሁለት ሺ ሰባት ዓ.ም. እንደገና ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ “ይድረስ ለእገሌ” ማለቱ ሰለቸኝና ተውኩት እንጂ ዛሬም መጻፍ የፈለግሁት የአማራን ዕልቂት ለመታደግና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር እየተዋደቁ ላሉት ወገኖቼ ነው – በፋኖም ይሁን በሌላ ስም፡፡ ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የነገድና

ጀልባዋ አትሰምጥም፤ የሚሰምጥ ግን አለ!

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] (https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/) ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

Go toTop