ታሪካችን ወደኋላ ብለን ስናማትር አነ ኢሕአፖ ፣ ኢዲዩ እና ወ.ዘ.ተ. ፖርቲዎች ትግላቸውን እያጧጧፉ ወደ መንበረ እርካቡ እያኮበኮቡ ባሉበት ወቅት እነዚህን ፖርቲዎች ይመሩ የነበሩ መሪዎች ከመጋረጃ ጀርባ ከመንግስት ጋር ወይም ከፖርቲዎቹ ተቀናቃኞቻቸው ጋር ውስጥ ለውስጥ አየተሻጠሩ ፣ እየተሞዳሞዱ እና ከድል በኋላ ስልጣኑን እንቀማለን በሚል የስልጣን ጥሜት በሕዝብ ቅቡልነት ያላቸውን ፖርቲ መሪዎች አስበልተዋል እንዲሁም የመሪዎችም መመታት “ መሪው የተመታ ጦር እንደሚበረግግ በግ ነውና“ ትግላቸው ከግብ ሳይደርስ ፣ ብዙ ታጋዮች መስዋት ሁነው ፣ እርካበ ሥልጣኑ በማይገባው አካል ገብቶ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ያየው እና ያሳለፈው ስቃይ የቅርብ ዓመታት ታሪክ እና በቁጭት የሚታወስ ክስተት ነው።
ለምሳሌ ኢዲዩ ( የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት) የደርግን መንግስት ሲፋለም የነበረ ሲሆን በነ ጄነራል ነጋ ተገኝ ፣ በራስ አዳነ ስዮም ፣ ራስ መንገሻ ስዩም ፣ አጣናው ዋሴ እና ወ.ዘ.ተ. እየተመራ በሕዝብ ቅቡልነት አግኝቶ ደርግን አንቀጥቅጦት ነበር። ነገር ግን ኢዲዮ በአሻጥር ከኢሕአፖ መሪዎች ጋር ፍትጊያ ውስጥ እንዲገባ የቀድሞው ወያኔ ( የአሁኑ ህወሃት) ሰርጎ ገቦች ማለትም እንደ ራስ መንገሻ ስዩም ባሉ አቀባባሪነት ራስ አዳነ ስዩምን በማስመታት እና በመግደል የኢዲዩ ትግል ጫፍ ሳይደርስ እንዲጨናገፍ ሁኗል።
የኢሕአፓ ትግል በአብዛኛው የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረውን የበርሃ ትግሉን ወደኋላ ትቶ በከተማ “የነጭ ሽብር እና የቀይ ሽብር” የእርስ በርስ መገዳደል ሆን ተብሎ እና በሻጥር እንዲያተኩር እነ መኤሶን ፣ ህወሃት እና የደርግም እጅ ታክሎበት የኢሕአፖ የበረሃው የአሲንምባ ትግል እየተጨናገፈ በብሄር ጡዘት በሰከሩት እና አፍቅሮተ ህወሃት በነበራቸው በእነ በረከት ስምኦን ፣ አዲሱ ለገሰ ፣ ተፈራ ዋልዋ እና ወ.ዘ.ተ. እጅ በመግባቱ እና በመውደቁ በሚያሳዝን መልኩ ስፍር ቁጥር የሌለው ወጣት እረግፎ ትግሉ አፋፍ ሳይደርስ ሊኮላሽ ችሏል።
ወገኖቼ አንድ ሊታወቅ የሚገባው በኢሕአፖ ፣ በኢዲዩ እና በሌሎች አደረጃጀት ፖርቲወች ከ1966 ወዲህ በአሻጥር ፣ በደባ እና በእርስ በርስ ሽኩቻ “ የጦስ ደሮ” ሁነው የተሰውት የአማራ ልጆች ፣ ምሁራን እና አመራሮች እንጂ የሌላ ብሔር ተወላጆች እነ በረከት ስምኦን ፣ እነ እራስ መንገሻ ስዩም ፣ እነ አዲሱ ለገሰ እና መሰሎቹ አልነበሩም ይልቅኑ እራሳቸውን “ኢድህን” ምናምን ብለው በመሰየም ከህውሃት ጋር በመለጠፍ የአማራን ህዝብ አገላተዋል ፣ አስጨፍጭፈዋል እና ዐፅመ እርስ ቱን እነ ወልቃይትን ፣ ራያን ፣ መተክልን እና መሰሎችን አሳልፈው ለህውሃት አስረክበው ነበር። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአማራ ምድር የአማራ ነገድ ኖረ እንጂ በቀኝ አዙር ከመገዛት ውጭ ከእራሱ እትብተ ምድር የተወለዱ ወይም የተፈጠሩ መሪዎች ኑረውት ወይም አፍርቶ አያውቅም ።
የአማራ ሕዝብም “ከእትብቴ የወጡ አማራ ልጆቼ የአስተዳድረኝም” ብሎ አያውቅም ። በስመ አማራ የተሰባሰቡ የሌላ ብሔር ቅልቅሎች አፅመ እርስቱ ድረስ ወርደው በላዩ ላይ እየተሾሙ አስተዳደሩት ፣ መሩት ፣ ፍርደ ገምድል ሆኑበት፣ አሰሩት ፣ አንገላቱት ፣ ገደሉት እና ረግጠው አሰቃዩት እንጂ። ይህም የሆነው አንገት ማተቡ ላይ ያንጠለጠለው “የኢትዮጵያዊነት መርህ እና ፍቅር ይበልጥብኛል” ስለሚል እና “ስለሚያጎላድፈው እና ፈሪሃ እግዚአብሔርም” ስላለበት “እሺ ፣ ይሁን” ብሎ ከመገዛት ውጭ ሌላ አማራጭ ስላልነበረው ነበር።
አሁን ግን ኢትዮጵያዊነት “እንደ ወላጅ እና ልጅ” ግንኙነት እንዲሆን አማራውን እያስገደደው መጥቷል “ ዝንጀሮዋ መጀመሪያ መቀመጫየን” እንዳለችው “ልጅ ወላጅ ደህና ሲሆን ነውና” በሰላም ፣ በፍቅር እና በስርዓት ተኮትኩቶ የሚያድገው ፣ አማራውም “ መጀመሪያ እራስ ደህና” ብሎ ፣ “ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር ፅጋ እና ድጋፍ ራሴ የሰራኋት” በመሆኗ “የትም አትሄድብኝም” ብሎ ለራሱ ደህንነት እና የመኖር ዋስትናውን ለማስጠበቅ ተነስቷል ፣ ማንም ከግዲህ በኋላ ምንም ሆነ ምን ከዓላማው የሚነቀንቀው እንደሌለ ሊሰመርበት ይገባል።
ይህን የማይናወጥ አቋሙን እና ውሳኔውን ወደተግባር ለመለወጥ ደግሞ እንደ ትላንትናው በስማ በለው ፣ በምስለኔ ፣ በጭቃ ሹም ፣ በስመ አማራ ተብየዎች እና የእንግዲህ ልጆች እንዲመራ የሚደረገውን አካሄድ “እርሜ ነው” በማለት የአማራ ሕዝብ ወስኖ እና “ሆ” ብሎ ስለተነሳ ፣ ከራሱ አብራክ የወጡ ልጆች እንዲመሩት እና እንዲያስተዳድሩት ፋኖን እርካብ እና ልጓም አድርጎ እየተፋለመ ይገኛል።
እነዚህን መሰረታው መርሆዎች ፣ መስፈርቶች እና ነጥቦች መሰረት አድርጎ የአማራ ፋኖ መሪ የመሆን ወይም የግለሰቦች ወደ ስልጣን እርካቡ የመምጣት ጉዳይ ሳይሆን የሚከተሉት እንኳር ነጥቦች መሰረት እድርጎ ሊከወን ይገባል እንላለን ፣ በአራቱ የአማራ ግዛት አፅመ እርስቶች ማለትም በጎጃም ፣ በሽዋ ፣ በጎንደር እና በወሎ ላይ የማያወላውል አቋም ያለው እና ለነዚህ አካባቢዎች የኢኮኖሚ ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ምህዳሮች መስፋት ፣ ማደግ ፣ ጥንካሬ እና ልዕልና ፀንቶ የሚታገል ፣
. አዲስአበባን ጨምሮ የወልቃይት የራያ እና ነባር የአማራ አፀመ እርስቶችን ወደባለቤቱ የአማራ ሕዝብ ይመለሱ ዘንድ የማያውላዳ አቋም ያለውና ይህን እውን ለማድረግ ፅኑ አቋም ያለው ፣
-የአራቱን አካባቢዎች ማለትም የሽዋ ፣ የወሎ ፣ የጎንደርን እና የጎጃምን ባህል ፣ ወግ ፣ ትብህል እና ቱፊት በውል ፣ በደንብ የሚያውቅ እና የኖሩበት ሊሆኑ የግድ ይላል ፣
– በፋኖ ትግል ምስረታ እና እንቅስቃሴ በፋና ወጊነት ከጅምሩ ጀምሮ ንቁ ተሳታፊ እና ከመስራቾቹ አንድ የሆነ፣
– የአማራ ህዝብ ሆነ የአማራ ፋኖ ታጋዮች ከቀደም ጀምሮ ለአማራ ሕዝብ ነፃነት ፣ ሰብአዊ መብት መጠበቅ በመሪነት የተቀበሉት እና ለዚህ ዓላማ ከጅምሩ እና ከመነሻው ጀምሮ መስዋዕት የከፈለ መሆኑን የሚያቁት እና ያረጋገጡለት ፣
– ለአማራ ሕዝብ ልእልና እና ሰላም ዱር ቤቴ ብሎ የገባና እራሱን አሳልፎ ለመስጠት የማይናወጥ እቋም ያለው ፣
– የአማራ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን የፀና እምነት እና አቋም ያለው ፣
– ከድርድር በፊት የአማራ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን የሚታገል እና በዚህ አቋሙ ሸብረክ የማይል፣
– ከዚህ በፊት በተቋቋሙ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች መሪ ሆኖ ከሆነ እጩ ተመራጩ ባሳየው ለውጥ እና እምርታ አንቱነትን ያተረፈ እና በመሪነቱ ወቅት የመራው ፖርቲ ወይም ድርጅት ዓላማው ግብ እንዲመታ ያደረገ መሆኑ በመስፈርትነት ሊታይ የግድ ይላል ፣
– መቸም የእኛ ሃገር ትግል አንዱ በመሪነት የታጨ ወይም የተሰየመ ከጎኑ ያለውን አጋር መሪ ስልጣኔን ይቀማኛል በሚል ስጋት ፣ መንግስቱ ኃይለማሪያም ኮለኔል አጥናፉ አባተን እና ኮለኔል ተፈሪ ባንቲን ፣ መለስ ዜናዊ ክንፈን እና መሰሎችን ፣ እነ አብይ ኢጅነር ስመኘውን ፣ ጀነራል አሳምነው ፅጌን እንደ በላቸው የዚህ አይነት የተደበቀ ማንነት የሌለው መሆኑ ሊረጋገጥ እና ማነነቱ ከግለ ታሪኩ ጋር ነጥሮ ወጥቶ ሊመረመር የግድ የሚል ይሆናል፣
የመሪነት መስፈርቶች ከትንሽ በጥቂቱ እነዚህ ቢሆንም በአራቱ የአማራ ጠቅላይ ግዛቶች ያሉ መሪዎች ከላይ የተጠቀሰው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ፣ ሻጥር ፣ ደባ እና ከመጋረጃ ጀርባ ከጠላት ጋር እና ከብልፅግና ጋር በጎንዮሽ በውጭ ሃገራት ግፉት በሚደረጉ ሻጥር አዘል የድርድር ክንውን ህሳቤ እና ሽረባዎች ሰለባ እንዳይሆኑ ከወዲሁ እንመክራለን።
ድል ለፋኖ
ከተዘራ አሰጉ ( ከምድረ እንግሊዝ)።