የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጉዳይ – ግርማ ካሳ

449073862 10232214419573936 6621678961808397589 n

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከቀድሞ የሰማያዊ ፕርቲ መሪ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጋር፣ በዋሺንገትን ዲሲ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ከሆኑት፣ ሚስተር ማሲንጋ ጋር ውይይቶች አድርገዋል፡፡ በጋራ የተነሱትም ፎቶ ይፋ ሆኗል፡፡

አቶ ገዱ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩ ናቸው፡፡ የርሳቸው በዚህ መልኩ ወደፊት መምጣት እጅግ በጣም ትልቅ ክስተት ነው፡፡ በግሌ በአዎንታዊነት ነው የምቀብለው፡፡ ለአገዛዙም ትልቅ የዲፕሎማሲ ሽንፈት ነው፡፡

ማሲንጋ ከአቶ ገዱ ጋር በዚህ መልኩ ፎቶ ተነስተውም መልቀቃቸው፣ በራሱ ትልቅ መልእክቶች አሉት፡፡ አንደኛው የብልጽግና መንግስት አገር ማስተዳደር እንዳልቻለና አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ከድምዳሜ መድረሱን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሁሉንም ፋኖዎችን የሚወክል የፖለቲካ መሪ ስለሌለ፣ አቶ ገዱና ምን አልባትም ኢንጂነር ይልቃል፣ በፋኖዎች መካከል እንደ መካከለኛ እንዲያገለግሏቸው ሳያስቡም አልቀረም፡፡

አቶ ገዱ፣ በዚህ መንገድ በይፋ ወደ ትግሉ መምጣታቸው የሚያበረታታ ቢሆንም፣ ለአቶ ገዱ ያለኝ አክብሮት እንደተጠበቀም፣ በርሳቸው ዙሪያ አንድ በትልቁ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ግን አለ፡፡ እኔም ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ፡፡

አቶ ገዱ ለረጅም ጊዜ ብአዴን የነበሩ ሰው ናቸው:: ባልሳሳት አሁንም አስተሳሰባቸው ወያኔና ኦነግ ጠፍጥፈው በሰሩት በአማራ ክልል ማእቀፍ ውስጥ ያሉ ነው የሚመስለኝ:: ይህንን እንዲሁ አይደለም የምለው፡

1ኛ እርስቸው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር የነበሩ ጊዜ ከአማራ ክልል ውጭ ስላለው የአማራም ሆነ አማራ እየተባለ ግፍና ሰቆቃ ስለደረሰበት ማህበረሰብ ይህ ነው የሚባል ያደረጉት ነገር የለም፡፡

2ኛ ባለፍው ጊዜ በአማራ ክልል የተጀመረውን ጦርነት በፓርላማ በይፋ መቃወምቸው በኔም ሆነ በብዙ ህዝብ ዘንድ ትልቅ አድንቆትን ያተረፈላቸው ቢሆንም፣ ያኔ በተናገሩት ንግግር፣ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጥያቄ አቅርበው፣ የሽግግር መንግስቱ ያሉት ግን፣ የፌዴራልን ሳይሆን የአማራ ክልል መንግስት ነበር፡፡ ያ አነጋገራቸው፣ ባህር ዳር የመስተዳደር ለውጥ እስከመጣ ድረስ አራት ኪሎ እነ አብይ አህመድ ይቀጥሉ የሚለውን እንደመቀበል ተድርጎ የሚቆጠር ነው፡፡

እነ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ፣ ብዙ ጊዜ የአማራ ክልል መንግስት መስተዳደሮች ተቀያይረዋል፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተነስተው፣ በተጠባባቂ ር እስ መስተዳድርነት አቶ ላቀ አያሌው፣ አቶ ላቀ አያሌው ተቀይረው፣ ዶር አምባቸው መኮንን፣ የዶር አምባቸው መኮንን ህልፈት ተከትሎ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተነስተው አቶ አገኘው ተሻገር፣ አቶ አገኘው ተሻገር ተነስተው ዶር/ ይልቃል ከፍያለ፣ ዶር ይልቃል ከፍያለ፣ ፋኖ ሲያባርራቸው አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርእስ መስተድደር ሆነዋል፡፡ በስድስት አመት፣ በኦሮሞ ክልል አንዱ ሺመለስ አብዲሳ ተቀምጦ፣ በአማራ ክልል ሰባት ርእስ መስተዳደሮች ተቀያይረዋል፡፡

አሁንም በአማራ ክልል የሽግግር መንግስት ተብሎ ሌላ ስምንተኛ ርእስ መስተዳደር ለመሾም ካልሆነ በቀር፣ የፌዴራል መንግስቱ በኦነጋዊምና ዘረኞች ስር እስካለ ድረስ የህዝቡ ስቃይና መከራ አያቆምም፡፡

ሌላው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከአብይ አህመድ ጋር እንጂ ከጨፍላቂ የኦሮሙማ ፖለቲካ ሓይሎች ጋር ችግር ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ በአስተሳሰቡ ሙሉ ለሙሉ ከአብይ አህመድ በምንም ከማይሻሉ ከነ ለማ መገርሳ ጋር አብረው ስሩ ቢባሉ ፍቃደኛ የሚሆኑ ነው የሚመስለኝ፡፡

ከስድስት አመታት በፊት ለውጥ የተባለው እንዲመጣ የአማራ ወጣት የተጫወተው ሚና የማይናቅ ብቻ ሳይሆን የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ነው፡፡ እነ አቶ ገዱ ህዝብን አሰልፈው፣ ህወሃት ላይ ባይነሱ ኖሮ፣ እነ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን አይመጡም ነበር፡፡ በነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ትከሻ ላይ ነው እነ አብይ አህመድ ስልጣን የጨበጡት፡፡

አዎን እነ አቶ ገዱ እንደ አብዝኞቻችን፣ እነ አብይ አህመድና ለማ መገርሳ፣ “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ፣ መደመር፣ ፍቅር፣ አንድነት .” ሲሉ ተታለው፣ አምነዋቸው፣ ኦህዴዶች አራት ኪሎ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ በዚያ አልወቅሳቸውም፡፡ ብዙዎቻችን ተታለን ነበርና፡፡

ሆኖም እነ አብይ አህመድና እነ ለማ መገርሳ ሲሉት እንደነበረ እንዳልሆነ እነ አቶ ገዱ አስቀድመው ነበር ያወቁት፡፡ ግን ከጅምሩ ቀይ መስመር አስምረው፣ ነገሮችን ማስተካከል ሲችሉ አላስተካከሉም፡፡ ለዚህም ሃላፊነት መውሰድ አለባቸው፡፡ እነርሱ የኦሮሞ ኦነጋዊ ፖለቲከኞችን አምነው፣ ትልቅ ህዝብ ከጀርባቸው እያለ፣ በኦሮሞ ፖለቲከኞች አውትስማርት (outsmart) ሆነው ፣ ህዝቡ ለትልቅ ጥፋት ዳርገውታል፡፡ ለዚህም ይቅርታ የመጠየቅ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡

እስቲ ጥያቄዎችን ላቅርብ፡

አሁንም አቶ ገዱ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን የመለማመጥ፣ የማባባል ዝንባሌ ነው ያላቸው ?

ይህ ኦነግና ህወሃት የሸነሸኑት ኦሮሚያ የሚባለው ዘረኛና የምድር ሲኦል የሆነው ክልል መፍረስ አለበት ብለው ያምናሉ ወይ ?

ነው ወይስ አሁንም በናዝሬት፣ በአሰላ፣ በሸኖ፣ በዱከም፣ በወሊሶ፣ በሞጆ፣ በኪረሙ፣ በአብ ደንጎሮ፣ በፍቼ በመሳሰሉት ቦታዎች የሚኖረው አማራ ኦሮሚያ በሚባለው ለአስተዳደር አመች ባልሆነው ክልል ውስጥ እንዲቀጥል ነው የሚፈልጉት ?

አሁንም የአማራው ማህበረሰብ አቅም ቢስ የሆነ ይመስል፣ ኦህዴዶችን፣ ኦነጎችና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ማስቀየም የለብንም የሚል ደካማና ሽምድምድ አመለካከት ነውን ያላቸው ?

አሁን ያለው ዘረኛና ከፋፋይና ጸረ ኢትዮጵያዊ ስርዓት ስር ነቀል በሆነ መልኩ መቀየር አለበት፡፡ የዘር ክልል መፍረስ አለበት፡፡ አማራው የፈለገው ብቻ ሳይሆን ሁሉም የተስማሙበት፣ ሁሉን አሸናፊ የሚያድርግ ሕግ መንግስትና አወቃቀር መኖር አለበት፡፡ ያለፈውን ኮተት ስርዓት ጥገናዊ ለውጥ አድርጎ፣ አብይ አህመድንና ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ቀይሮ ለመቀጠል መሞከር ፣ የህዝቡን ትግል ማምከን ነው፡፡

ከአክብሮት ጋር ለአቶ ገዱ ፣ አመለካከታቸው ለውጭ አገር ዜጎች፣ ለአሜሪካኖች ለመናገር ከደፈሩ፣ ለህዝብ ወጥተው ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲመልሱ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ብዙ ሊሰሩ፣ ብዙ ሊያበረከቱ የሚችሉ ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ ሆኖም ነገሮችን ማጥራት አለባቸው፡፡ አቋማቸውን መስመሮቻቸውን ማጥራት አለባቸው፡፡ የነ አብይ አህመድ ጉድና ሴራ ማጋለጥ አለባቸው፡፡ መሽሞንሞኑና ከመጋረጃ ጀነርባ መቀመጡን ትተው፣ ከአገዛኡ ጋር ታንጎ ለሚደንሱ ህሊና ቢስ ብአዴኖች፣ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት በይፋ ጥሪ ማቅረብ መጀመር አለባቸው፡፡ በአማራ ክልል ሚሊሺያ፣ የአድማ ብተና ቡድን የሚባሉ፣ እነርሱ አራት ኪሎ እንዳይታዘዙ፣ ፋኖን እንዲቀላቀሉ መልእክት በይፋ ቢያስተላልፉ ብዙዎች ከሞት ሊያድኑ ይችላሉ፡፡

ተስፋ አለኝ፣ አቶ ገዱ ማጥራት ያለባቸው አጥረው፣ አመለካከታቸው ከህዝብ አመለካከት ግር ከሆነ፣ ምን አልባት ከፋኖዎች የፖለቲካ አመራር መካከል አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

1 Comment

 1. አቶ ግርማ፦
  ያለህን ስጋት እጋራለሁ። አቶ ገዱን በስልክ እንጂ በግንባር አላውቃቸውም። በስልክ በክልል ጉዳይ ላይ ላቀረብሁት ጥያቄ ፈጣን መልስ በመስጠታቸው የሕዝብ አጋር ናቸው የሚል ግምት አለኝ። ቢሆንም የጠየቅሀቸው ጥያቄዎች ሁሉ ሊመለሱ ይገባል። አቶ ገዱ ያመጡት አንዱ ትልቅ ቁም ነገር የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ነው።

  ምሥረታው በግልብነት፣ በበቀል ስሜት፣ በጥቅምና በጠባብነት እንዳይመራና የደርግና የኢሕአዴግ ስሕተት እንዳይደገም፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያከብሩ ዜጎች ሁሉ በሀቀኛ ወኪሎቻቸው በኩል እኩል የውይይትና የውሳኔ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማረጋገጥ ብዙ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። አገር ለመገንባትም ሆነ የኢትዮጵያንም ነፃነትና ሉዓላዊነትት ለማስከበርና ለመጠበቅ ሁሉም ባለ አገር እኩል ያገባዋል።

  ደርግ ሲጀምር “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ማለቱን አድንቄ ሳልጨርስ፣ የሀገር ባለውለታዎችን ሰብስቦ አጭዶ፣ ትውልድ የገነቡትን ትልቅ ሽማግሌ ንጉሠ ነገሥት እንደ ወንበዴ አሥሮ፣ በሰላም ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ፌደራል ወይም ኮንስቲቱሽናል ሥርዓት ሊያሻግር ሲችል፣ ዓላማው ሥልጣንና ቂም በቀል መወጣት ስለነበረና አገር ወዳድ ነኝ ማለቱ ለውንብድናው ሽፋን ሆኖ፣ ከእሥር ቤት በየካቲት 1982 ዓ.ም. ወጥተው የሽግግር መንግሥትን ለዲሞክራሲያዊ ፌደራል ሥርዓት እንዲያበቃ አድርገው ገንብተው በ1986 ዓ.ም. ፌደራል ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃን እንዳዋለዱት ትልቁ አፍሪቃዊ መሪ ኔልሰን ማንዴላ አርቆ ማስተዋልና አገርና ሕዝብ መውደድ ስላልፈጠረበት፣ በአምባ ገነን አገዛዝ ሕገ መንግሥትና በመፈክር አገር ሲያተራምስና የድሀ ልጅ በጦርነት ሲማግድ ሰንብቶ፣ ኤርትራንም አስገንጥሎ፣ በፈጠራ በደል በቀልና በሥልጣንና ገንዘብ ፍቅር ለታወረው ሕወሀት አስረክቦን፣ ከፊሉ የደርግ አባል ወደ እሥር ቤት ሲወርድ፣ ከፊሉም ፈረጠጠ። የደንቆሮ አገዛዝ ሥርዓት መጨረሻው ይኸው ነው።

  የሕወሀቱ መሪ መለስ ዘናዊና አጋሩ የኦነጉ ሌንጮ ለታም ከምርኮኞቹ ጋር በፋሽሽት ጣሊያን መርህ መሠረት በ1983 ዓ.ም. አገር ከልለው፣ ኦሮሚያ የሚባል ሰፊ አዲስ ግዛትና ሌላ ታሪካዊ ዳር ድንበሩ የተንሰራፋ ትግራይ መሥርተው፣ በጠቅላላ 9 ክልል ለ9 ምርጥ ጎሣ አካፍለው፣ የቀሩትን 74 ጎድሣዎች ለዘጠኙ ተገዥ አድርገው፣ ዲሞክራሲያዊነትም ሆነ ፌደራልነት ያልነካው ሕገ መንግሥት አርቅቀውና አጽድቀው፣ ራሳቸውን ኢሕአዴግ ብለው ሰይመው፣ 27 ዓመት ካተራመሱን በኋላ፣ የአምባገነን አገዛዘ ሥርዓት የመጨረሻ ዕጣ ፈንታው ውድቀት በመሆኑ፣ አርቆ ለአገር ማሰብ ያልቻለው የመለስ ዜናዊና ሌንጮ ለታው ኢሕአዴግም በ2010 ወደቀና ብልፅግና የኢሕአዴግን የአገዛዝ ሥርዓት ወርሶ ተተካ።

  እንደ ኔልሰን ማንዴላ ለአገርና ለወገን አርቆ ማሰብ ያልፈጠረበትና ሀቀኛ ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማዋለድ አቅመ ቢስ የሆነው የመለስ ዜናዊው ኢሕአዴግ፣ ኢትዮጵያን ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለማብቃቱ፣ ዛሬ መለስ ቆምሁላት ያላት ትግራይና ሌንጮም የታገለላቸው ኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከመሪዎቻቸው አስከፊ ጠባብነት ያተረፉት፣ ሞት፣ እልቂት፣ ረሀብ፣ መፈናቀል፣ ስደትና የሀብት ውድመት ብቻ ነው። የሚያሳዝነው፣ ኢትዮጵያን ተከታትለው በነፍጥ የገዟት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና መለስ ዜናዊ፣ ከሌሎች ውድቀትና ስኬት ባለመማር፣ የኔልሰን ማንዴላና ሲሪል ራማፖዛ እንጥፍጣፊ ችሎታ ያልነበራቸው ድኩማን መሆናቸውን ለዓለም ከማሳየታቸው በላይ፣ የታሪካዊት አገራችንን መልካም ስምና ዝና ማዋረዳቸው ነው። ይህ አሳፋሪ የውድቀት አመራር ታሪክ ወደፊት ሊመጣ በሚችል የሽግግር መንግሥት አመራር እንዳይደገም አገር ወዳዶች ሁሉ ሊያስቡበት ይገባል።

  ከዛሬው የውድቀት አገዛዝ ለመውጣት፣ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ዓይነት በሥልጣን ጥማት፣ በብዝበዛና በበቀል ስሜት ያልታወሩ፣ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው፣ አገርና ሕዝብ ወዳድ ምሁራን የሚመሩት የሽግግር መንግሥት ምሥረታ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ዝግጅት እንዲረዳ የኔልሰን ማንዴላን የሽግግር መንግሥት ሂደት የሚገልጽ መጽሐፍ ርዕስ ከዚህ በታች አስፍሬያለሁ።

  Steven Friedman and Doreen Atkinson, eds. (1994). The Small Miracle: South Africa’s Negotiated Settlement. South African Review 7. Ravan Press, Johannesburg.

  ለሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያበቁን ሲችሉ፣ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም፣ መለስ ዜናዊና ሌንጮ ለታ ከደቡብ አፍሪቃው ኔልሰን ማንዴላ እጅግ ያነሱ መሆናቸውን፣ አርቆ አለማሰብና አገርና ሕዝብም ያለመውደድ ጉድለት እንደተጠናወታቸውና ጠባብ አዕምሮም እንደነበራቸው ዓለም አይቷል። ኢትዮጵያንም በማሳነሳቸው አዋርደውናል። ወደፊት ግን ይህ ውርደት እንዳይደገምና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ሰላም ጠፍተው ጦርነት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ረሀብ፣ ስደትና የሀብት ውድመት እንዳይከሰቱ፣ ሰፊና ለም አገር ከሰፊ የውሀ ሀብት ጋር እያለን አመራር በማጣት ብቻ የስንዴ ተመፅዋች እንዳንሆን ሁሉም ዜጋ ሊያስብበት ይገባል።

  ለማኝነትና የወጣቱ አደገኛ ስደት ከ50 ዓመት ወዲህ ተማርን የምንል ዜጎች ባግባቡ ማሰብና መሥራት፣ ማሠራትም አቅቶን፣ ሳንሠራ የተየሠራውን እየወረስን ለመበልጸግ አቋራጭ ፍለጋ በምሥራቅና በምዕራብ አገራት የግልበጣና መፈክር ምሁር ለመሆን ስንልከሰከስ ሰንብተን ያመጣነው ውርደት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

b249e9a0 3139 11ef b7f5 2d174badf3ee.jpg
Previous Story

‘ሕይወቴ አደጋ ላይ ነው’ የሚሉት የ‘ጦርነት ይቁም’ ሰልፍ አስተባባሪው ፖለቲከኛ ዳንኤል ሺበሺ ተሰደዱ

191490
Next Story

ሱሌማን አብደላን ፍለጋ..

Go toTop