ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

Beklu Emiruአብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም ከመሬት ቁጭ ብድግ እያደረገ የሚቁነጠነጥ ነው፡፡ አድማጭ የተባለው ጥቂቱም የሚያዳምጠው ከተናጋሪው ትምህርት ለመቅሰም ሳይሆን ከተናጋሪው ረጅም ንግግር ስህተት ፈልጎ ለመቃወም ወይም አቃቂር ለማውጣት ነው፡፡ አብዛኛው ሰው በፍርሀት ላብ ተነክሮ አድማጭ መስሎ እሚታየው ባዶ ራስ ቅል የተሸከመ ጭራቅ ካድሬ አዳራሽ ውስጥ ሰብስቦ ሲደነፋበት ብቻ ነው፡፡ እንደ አለመታደል የቅድመ አያቶቻችንን ለእውነት የመቆምን፣ የማዳመጥ ትእግስትና ለመናገር ያለመቸኮልን ችሎታ አሽቀንጥረን ጥለን የዘቀጥንበት መጤ ባህል ይኸንን የሚመስል ነው፡፡

ቅድመ አያቶች ይሉት እንደነበረው ሁሉ ፕሉታርክ* የተባለ ግሪካዊ ፈላስፋ “የማዳመጥ ችሎታ የትክክለኛ ህይወት መሰረት ነው” ይላል፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍም ያዕቆብ 1፡19 ላይ  ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ይሁን” ል ያስተምራል፡፡ እግዚያብሔር ወይም ተፈጥሮም ይኸንን እንድንፈጥም ሁለት መስሚያ ጆሮዎች፣ ሁለት መመልከቻ ዓይኖችና አንድ መናገሪያ ምላስ ሰጥኖናል፡፡ ግብራችን እንደሚገልጠው እኛ ግን ጆሯችንን መጠቀም ባለመቻላችን ወደ ድፍንነት ምላሳችንን ደሞ ከመጠን በላይ ስለተጠቀምን ወደ አምስት እጥፍ መንታነት የተቀየረ ይመስላል፡፡ አይናችንም ፈዞ ዓይኔን ግንባር ያርገው ብለን የምንምል ቀጣፊዎች ሆነናል፡፡ ይህ ኢተፈጥሯዊ የሆነ ባህል እውቀት ለመገብየት የተተከሉልንን ጆሮዎች ደፍኖ፣ ለማስተዋል የተቀመጡልንን ዓይኖች አውሮ ከድንቁርና መቀመቅ ውስጥ እየዶለን ይገኛል፡፡ በዚሁም ተብሶ በሶቅራጥስ አባባል እውቀት አልባ መሆናችንን ስለማናውቅ  የመንፈስ ልእልና ምንዱብ ድሀዎች መሆናችንን ያሳያል፡፡

ሰው እውቀት የሚገበየው አንድም በመስማት ሁለትም በማየት ወይም በማንበብ ነው፡፡ መናገርና መጣፍ የእውቀት ማሰራጫ ወይም ማካፋያ መንገዶች ናቸው፡፡ በደንብ አዳምጦ ወይም በሚገባ አንብቦ እውቀት ያልገበየ ሰው ቢናገር ዝምብሎ “ቂው ጪር እቂው..” ዓይነት የወፍ ጫጫታ ቢጥፍም እንኳን ከዘመን ዘመን የሚሻገር በወቅቱም ተነስቶ የሚጣል የቤት ቆሻሻ ነው፡፡ ሳያውቁ መናገርና ሳያነቡ መጣፍ የማህበረሰባዊ ግንኙነታችን ከማበላሸት አልፎ ለማዳመጥ የፈጠኑ ለመናገር ግን የተቆጠቡ ቅድመ ዓያቶቻንን በአጥንት፣ በደምና በጥበብ የገነቧትን አገር እያሳጣን ነው፡፡

እንደ አካላዊ የማህበረሰብ ግንኙነቶች ሁሉ ለበጎ ነገር መዋል የነበረባቸው እንደ ፌስ ቡክ፣ ትዊተር፣ ዩ ቱብ፣ ቲክ ቶክና ሌሎችም መገናኛ መንግዶች ሳያዳምጡ በሚናገሩ፣ ሳያነቡ በሚጥፉ እውቀት አልባዎች እየተጨናነቁ ነው፡፡ በእውቀት አልባዎች የሚሰራጭ ወሬ የሚያስፋፋው ቅጥፈትን፣ ውሸትን፣ ክህደትንና  የእውቀት ድህነትን ወይም ድንቁርናን ነው፡፡ ድንቁርና ደሞ ሶቅራጥስ ደጋግሞ እንዳለው የአረመኔነት ምንጭ ነው፡፡ የድንቁርና ዋናው ምንጭ ደግሞ በሚገባ አዳምጦ ወይም አንብቦ በመንፈስ ልእልና (ዊዝደም) የዳጎሰ እውቀት አለመገብየት ነው፡፡

እውቀትን እንደ ፒ ኤች ዲ፣ ኤም ዲ፣ ማስተርስ ወይም ሌላ ዓይነት ዲግሪ ጋር የማገናኘት ትልቅ ስህተት ሲሰራ ዘወትር ይታያል ፡፡ በአገራችንም ሆነ በዓለም ላይ በእውቀታቸውና በመንፈስ ልእልናቸው የሚጠቀሱት ብዙዎቹ ሰዎች ዲግሪ የጫኑ አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ ዲግሪ አልጫኑም፤ በመንፈስ ልእልና በተሸፈነው ኣጅግ የዳጎሰ እውቀታቸው ግን በአገራችን የሚስተካከላቸው አልነበረም፤ ዛሬም የለም፡፡ ሊዮ ቶልስቶይ ዲግሪ አልነበረውም በእውቀቱ ግን በሩሲያ ምድር የሚስተካከልው ብዙም አልነበረም፡፡ ሶቅራጥስ እንኳን ዲግሪ ሊኖረው በአግባቡ ትምህርት ቤት ግብቶም የዓመት ወይም የሁለት ዓመት ኮርስ አልጨረሰም፡፡ ፍልስፍና ሲተረክ ግን ሶቅራጥስ ካልተነሳ ትረካው የተሳካ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ዲግሪና ቆብ የእንጀራ መብያ ሰፊ ሳህን እንጅ እውቀት አይሆንም፡፡ እንዲያውም ዲግሪ  ወይም ቆብ ጭኖ ሳያዳምጥ የሚናገር፣ ሳያነብም የሚጥፍ የእውቀት ድሀ የትምህርት ቤት ደጃፍ ሳይረግጥ ከማዳመጥ መናገርን ተሚመርጥ ከንቱ ዜጋም የከፋ ነው፡፡ እነዚህ እውቀት አልባዎች በአረመኔነት ሲሰማሩ ዲግሪ ወይም ቆብ የጫነው በካራ ስለት ዲግሪ ወይም ቆብ የሌለው ጎጋ ደሞ በካራው ደንደስ የሚመሰሉ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብ በአንክሮ መመልከት ያለበት ዲግሪ ወይም ቆብ ጭኖ ሳያውቅ ተሚለፈልፈው፣ ሳያነብም ተሚሞነጫጭረው ምሁር ወይም መነኩሴ ነኝ ባይ አረመኔ ነው፡፡

የመናገር ነፃነት እንደ መተንፈስ ሁሉ የማንኛውም ፍጡር መብት ነው፡፡ ዳሩ ግን ሰው መጮህ ወይም መናገር ያለበት እንደ ወፎች በደመ ነፍስ ተነድቶ ሳይሆን ለማዳመጥ፣ ለማስተዋልና ለማንበብ ተግቶ ዓይምሮን በእውቀትና በጥበብ ማሟሻ አሟሽቶ ነው፡፡ ገና ለገና የመናገር መብት አለኝ በሚል ከንቱ ውዳሴ ከማዳመጥ መናገርን፣ ከማየትና ከማንበብም መጣፍን አስቀድሞ በእውቀት ላይ ያልተገነባ ባዶ አስተያየት የሚወሸክት ወይም ንግግር እንደ ክር የሚተረተርን ጉድ “ቋዋ…ቁ  ቋ ቁ…” እያለ ተሚጮህ ቁራ በምን ልንለየው ነው?

ቅድመ አያቶቻችን ትተውልን ያለፉት ጥበብ፣ ፍልስፍናና ባህል ከመጠምጠም መማር ይቅደም፤ ለማዳመጥና ለማስተዋል ፍጠን፤ ለመናገርና ለመጣፍ አትቸኩል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የአያቶቻችን ፈለግ በመከተል ለመናገር ወይም ለመጣፍ ተመቸኮላችን በፊት ተራውጠን ዓለም ታከማቸችው የእውቀት ዘረፎች ሁሉ በማዳመጥ፣ በማየትና በማንበብ እንደ ንብ ቀስመን የእውቀት ማር ሰርተን በመንፈስ ልእልና ግምጃ እንሸፍን፡፡ ይህ በመንፈስ ልእልና የተሽሞነሞነ የእውቀት ማር ሰፈፍ ሳይኖረን የዲግሪ ቆብ ተለብደን፣ ፒ ኤች ዲ፣ ኤም ዲ፣ ማስተርስ አለኝ እያልን ምሁር መምሰሉ ያሸማቀን፡፡ ከአቡጊዳ እስከ ስንክሳርና መጽሐፍ ትርጓሜ ደርሰን በፍልስፍናዊ ቅኔ እንደ አዋዜ ታሽተን ራስ ቅላችንን በእውቀት የማር ሰፍፍ ሳንሞላ ጥምጣም አውሎ ነፋስ አስመስለን ሊቀ ካህናት፣ ሊቀ ሊቃውንት፣ መጋቢ ሀዲስ፣ መጋቢ ብሉይ፤ መላከ ብርሃን ወዘተርፈ መባሉ እጅግ ያሳፍረን፡፡

ለራሳችን፣ ለማህበረሰባችን፣ ለአገራችን፣ ለስብእናና ለመለኮት ስንል ለማዳመጥ፣ ለማስተዋል፣ ለማንበብና ለመማር እንትጋ፡፡ ከመናገር ማዳመጥን፣ ከመጣፍ ማስተዋልና ማንበብን ከመጠምጠምም መማርን እናስቀድም! እንደ ቁራ ስንጮህ፣ እንደ አሳማ ስንዝቅ፤ እንደ ጅብ ስንዘነችር ብቻ ኖረን ወደ አፈር ላለመመለስ አዳምጠን፣ አስተውለንና አንብበን ያካበትነውን የእውቀት የማር ሰፈፍም በመንፈስ ልእልና ሸፍነን ሰዎች ሆነን ለመኖርና የማይጠፋ ፈለግ ትተን ለማለፍ  እንጣር፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

*Philosophy 101: Plutarch on Listening  https://philosophycourse.info/plutarchsite/plutarch-listening.html

ግንቦት ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.

1 Comment

  1. በላይነህ የጻፍከው በቂ ነበር በአባሪነት ያቀረብከውም ሰነድ ከጳፍከው በተጻራሪ ሌላ ነገር ስለሚያሳስበን።የዘመናዊ ትምህርት ምስክር ወረቀቶች በጣም አሳሳች ሁነዋል ህብረተሰቡም ከሚገባው በላይ ክብር ስለሰጠው ወረቀቱን ወረቀቱን ከተሸከመው በላይ ስለሚያከብረው በወረቁቱና በወረቁቱ ተሸካሚ መሀል ልዩነቱ ጠፍቷል። ባጠቃላይ ዶፍቶሩም ፕሮፌሰሩም ትምህርቱ የተቃኘለት ወረቀቱን በሰጠው አገር እንጅ ለሌላው አገር አይደለም። እንደው እሩቅ ሳትሄድ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ተማርኩ ባሉበት የትምህርት ዘርፍም ሆነ ተራ ግንዛቤ በሚጠይቅ ውይይት ላይ ምን እንደሚናገሩ ምን እንደጻፉ ግንዛቤ ሳይጨብጥ በትዝብት እንሰነባበታለን። እሳቸውም ነገሩ ይከብዳቸዋል መሰል እንዳጓሩ እንደተቆጡ እንደተጨነቁ ከመድረኩ ይሰናበታሉ በእንግሊዝኛ ላስረዳ ካሉ ደግሞ ከዚህ ይክፋል። አረጋዊ በርሄም ሆነ መራራ ጉዲና ከዚህ የተለዩ ኡይደሉም። እንግዲህ እነዚህ ግለሰቦች ለዚህ ድክመታቸው የተቸራቸው ትልቅ ቦታ በርትታችሁ አበላሹ የሚል ነው። አለፍ ሲል ደግሞ ከድንቁ ደያስ ብዙ ዲግሪ የተሰጠው ጠብደል መሀይም ቄሮ መበራከቱንም ክግንዛቤ እናስገባ። ጣጣችንን ሲያበዛው ደግሞ ሰው እንዳያነብ በዩቲዩብ አማካይነት ያልተማሩ ሰዎች እያስማሩን ነው። ቅጣቱ ከላይ ይመስላል

Leave a Reply

Your email address will not be published.

191437
Previous Story

ፋኖ ዘመነ ካሴ ማን ነው

566rggggggff
Next Story

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

Go toTop