የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

June 20, 2024

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው)

 

  1. እንደመንደርደሪያ

ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual Day›› ጉባኤ ነው፡፡

የዚህ ‹‹የአፍሪካ መንፈሳዊ ቀን›› ክብረ-በዓል እሳቤ በ‹‹Universal Peace Federation›› አማካኝነት ተፀንሶ በኋላም በዚሁ ዓለም አቀፍ ድርጅት የአፍሪካ ቅርንጫፍ በኩል- ‹‹የአፍሪካ ሃይማኖቶች ጉባኤ ለሰላምና ለዕድገት/The Interreligious Association for Peace Development Africa›› በሚል ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በተፈራራመው የመግባቢያ ሰነድ/MOU ዕውን የሆነ የአፍሪካውያን ሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤና በዓል ነው፡፡

በዚህም መሠረት ባሳለፍነው ሳምንት ‹የአፍሪካ ሃይማኖቶች ኅብረት ለአፍሪካ ሰላምና ዕድገት› በተባለው ተቋም በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተደረገው ጉባኤ፤ ከመላው አፍሪካ ሀገራት የተጋበዙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የባህል እምነቶች ተወካዮች፣ የመገናኛ ብዙኃን… ወዘተ የተሳተፉበት መድረክ ነበር፡፡

የዚህ ጉባኤ ዋንኛ አጀንዳም የአፍሪካ የትምህርት ሥርዓት ነበር፡፡ ‹‹በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመንፈሳዊ ሕይወት ብቁ የሆኑ አፍሪካዊ/ሰዎችን ማፍራት የሚያስችል ትምህርት/Educating the African Person to be Spiritually Fit in the 21st Century በሚል መሪ ቃል ተካሄደው ጉባኤ ከኢትዮጵያና ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት የመጡ ምሁራን እንደየሃይማኖታቸው አስተምህሮ፤ ሥርዓትና ትውፊት አጭር የሆነ ጥናታዊ ገለጻን አቅርበው ነበር፡፡

ስለ ጉባኤው በጥቂቱ ይህን ካልኩና መረጃ ከሰጠው ዘንድ- ‹ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ በዚህ አፍሪካዊ ጉባኤ ላይ የነበራት ተሳትፎ በዕውኑ የሺሕ ዘመናት ታሪኳንና ክርስቲያናዊ ባህሎቿንና እሤቶቿን በሚመጥን ደረጃ ነበር ወይ?!›

በበርካታ አፍሪካውያን ዘንድ ‹‹የአፍሪካ እናት ቤ/ክ›› ተብላ የምትጠራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዚህ ጉባኤ ላይ፤ ይህን የእናትነት ሚናዋን፤ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ታሪካዊ- አርዓያነቷ ተምሳሌነቷ በዚህ ጉባኤ በሚገባ ለማሳየት ችላለች ወይ?!›› በሚለው ሐሳብ ዙሪያ የግል ትዝብቴንና ታሪክን መነሻ አድርጌ ጥቂት ለውይይት መነሻ የሚሆን ሐሳብ ለማካፈል ወደድኹ፡፡

አስቀድሜ ግን፤ ‹የኢትዮጵያ ቤ/ክ የውጪ/ዓለም አቀፍ ግንኙነትን› በተመለከተ ያሉ ታሪካዊ ዳራዎችን፤ መረጃዎችን በአጭሩ ለመቃኘት ልሞክር፡፡

 

  1. የኢትዮጵያ ቤ/ክን የውጪ ግንኙነት ታሪክን በወፍ በረር፤  

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እምነትን በተመለከተ የግንኙነት መስመሯን ወደ ውጭ መዘርጋት የጀመረችው ቅድመ ክርስትና ከ1000 ዓ.ዓ. ገደማ ጀምሮ ነው፡፡ በቃልም በመጣፍም የቆየን የሀገራችን የሺሕ ዘመናት የሃይማኖት ታሪክ እንደሚነግረን ንግሥተ ሳባ በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን ሲያመልክ የነበረ ሕዝቧን በመወከል ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ከንጉሡ ከሰሎሞን ጋር በመወያየት እግዚአብሔር ለእሱና ለሕዝቡ የገለጠውን ሕገ-ኦሪት ይዛ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡ ሕዝቧንም በዚሁ የኦሪት ሕግና እምነት እንዲመራ አድርጋለች፡፡

ንግሥተ ሳባ የጀመረችው ግንኙነትም በኋላ የመንፈሳዊ ጥበብ ፍለጋ ጉዞዋ ሌላ ውጤት በሆነው ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክና እሱ ባመጣቸው ሌዋውያን ካህናት አማካይነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህ በኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ በኢትዮጵያ/በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የተጀመረው ታሪካዊ ግንኙነት የኢትዮጵያዊ የውጪ/ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ማብሰሪያ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ለአብነትም፤ ከጥቂት ወራት በፊት የውጪ ጉዳይ ሚ/ር መስሪያ ቤት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ቤተ-መዘክር/ሙዚየም ‹‹የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ›› በተመለከተ ባዘጋጀው ሰፊ ዐውደ-ርእይ/ኢግዚቢሽን፤ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገችው ጉዞ የኢትዮጵያ ውጪ ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ ጅማሬና ብስራት እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

ከዚሁ ታሪካዊ ክሥተት ጋር በተያያዘም ከጥቂት ዓመታት በፊትም ኢትዮጵያን የጎበኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚ/ር ቤኒያምን ኔታንያሁ፤ በሀገራችን ፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው ያነሱትን ሐሳብ ልጥቀስ፡፡

‹‹… ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ ከሰለሞን ጋር በተገናኙበት፤ የሁለቱን ሀገራት የሺሕ ዘመናት ታሪካዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ቁርኝት ከተፀነሰባት፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና ትብብር በፍቅር ካጸናበት ከሰላም ከተማ፤ ከኢየሩሳሌም ከዳዊት ከተማ የከበረ ሰላምታን ይዤላችሁ መጥቻለሁ…!!››

ይህ በመካከለኛው ምሥራቅ- በኢትዮጵያና በኢየሩሳሌም መካካል የተጀመረው ግንኙነት በጊዜ ሂደትም የክርስትና ሃይማኖት ወደ ሀገራችን እንዲገባ ምክንያት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬ በጅሮንድ /የገንዘብ ሹም/ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሥርዓተ-አምልኮ ለመፈጸም ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው ጉዞ የክርስትና ሃይማኖት ወደ ሀገራችን እንዲገባ ዋንኛው ምክንያት ነበር፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትና ታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት፤ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምኖ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ ክርስትናን በመያዝ ወደ ሀገራችን የገባው የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬ በጅሮንድ /የገንዘብ ሹም/ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ባኮስ ነው፡፡

ከሦስት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላም በሲሪያውያኑ ወንድማማቾች አማካኝነት በአክሱም ቤተ-መንግሥት የተሰበከው የክርስትና ሃይማኖት- ‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት› የመሆን ዕድልን አገኘ፡፡ ይህ ታሪካዊ/ሃይማኖታዊ ክሥተት ደግሞ በአፍሪካ ክርስትናን ለመቀበል በግንባር ቀደምት ከምትጠቀሰው የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ጋር የኢትዮጵያ ቤ/ክ የእናትነትና የልጅነት መንፈሳዊ ግንኙነት ከመፍጠር በዘለለ ዓባይን ውኃ መሠረት ያደረገ የዓባይ/የውኃ ፖለቲካን/Hydropolitics ካባን እንዲደርብ ትልቅ ምክንያት ሆኗል፡፡

 

  1. የኢትዮጵያቤ/ክ እና የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ግንኙነት

በግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ መካከል ሃይማኖትን መሠረት ያደረገው ግንኙነት ግብጻውያን በሀገራችን ላይ ለሚያራምዱት የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ የማእዘን ድንጋይ መሆኑን የታሪክ ምሁሩ ባሕሩ ዘውዴ (ኢመሬትስ ፕሮፌሰር) ‹‹The Modern History of Ethiopia 1855-1991›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፤

‹‹… በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ እንደ ግብፅ ጉልህ ስፍራ የያዘ ኖሮ አያውቅም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ክርስትና ከተቀበለችበት ከ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ በእስክንድርያው ፓትርያርክ የሚሾም ግብፃዊ መኾኑ ያቺን አገር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መሪ ተዋናይ አድርጓታል፡፡›› ሲሉ የሁለቱን አገራት ጥብቅ የኾነ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ትስስር በኋለኛዋ ዘመኗ ኢትዮጵያ በሃይማኖት ሰበብ የተለየ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንድምታን ይዞ ብቅ እንዳለ ያስምሩበታል፡፡

ሃይማኖት እና የዓባይ ውኃ አሁንም ድረስ በሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የግንኙነት ማዕቀፍ እንደሆነ ዘልቋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ በግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ግብዣ ግብጽን በጎበኙበት ወቅት፤ የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታውድሮስ ለኢትዮጵያውያኑ ልኡካን ባስተላለፉት መልእክታቸው፤

‹‹… ኢትዮጵያ እና ግብጽ እንዲሁም ሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናት  በዓባይ  ወንዝና  በሃይማኖት  አማካኝነት  ጽኑ የ ኾነ  ትስስርና ኅብረትን  ፈጥረዋል፤  በሃይማኖት  በኩል ደግሞ ግብጽ እና ኢትዮጵያ መቼም ሊበጠስ የማይችል የመንፈስ አንድነት መፍጠራቸው– ‘በራስህ  ላይ  እንዲሆን  የማትፈቅደውን  በሌላው  ላይ እንዲሆን አትፈቀድ፤በሚለው  ክርስትያናዊ  አስተምህሮ  መሠረት በዓባይን ውኃ  በተመለከተ፤  ሁለቱ ሕዝቦች  በሰላም፣  በመተሳሰብና  በመፈቃቀድ  መርሕ እንደምንቀጥል እምነቴ የጸና ነው፤›› ነበር ያሉት፡፡

ይህንኑ የሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናትንና ሀገራትን ግንኙነት በተመለከተ፤ ዋልአ ሁሴን የተባለች የግብጽ ፓርላማ ዘጋቢና የአፍሪካ ጉዳዮች ኤክስፐርት/ተንታኝ፤ ‘‘Egypt Uses Church to Bolster Ties with Ethiopia’’ በሚል ርእስ ሰፋ ያለ ዘገባን አስነብባ ነበር፡፡

ዋልአ በዚህ ዘገባዋም፤ ‹‹የግብጽ መንግሥት ኢትዮጵያ ‘‘የግብጻውያን ሕይወት’’ በኾነው በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን ታላቁን የኅዳሴ ግድብ በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አማካኝነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሰላማዊ የሆነ ድርድርና ስምምነት እንዲኖር ማድረግ የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል፤›› ነበር ያስነበበችው፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን በሁለቱ አኀት አብያተ ክርስትያናት መካከል ለሺሕ ዘመናት የዘለቀው ግንኙነት ከፍጥረት ማግሥት ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ ይህ ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ትላለች የአፍሪካ ጉዳዮች ኤክስፐርቷ ዋልአ ሁሴን፤ ‘‘ይህ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ግንኙነት በኋለኛው ዘመን በክርስትና ሃይማኖት ዋልታና ማገርነት ወደ ልዩ መንፈሳዊ አንድነት ማደጉን፤’’ ታብራራለች፡፡

ይህን የታሪክ ሐቅ መሠረት ያደረጉት የአልሃዛር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት የኾኑት ፕሮፌሰር ሼኽ አሕመድ አል ጣይብ በወቅቱ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና ከልዑካናቸው ጋር በነበራቸው ውይይትና ቆይታም፤

‘‘የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ቤ/ክ የዓባይ ውኃን በመተመለከተ- በሃይማኖትና በታሪክ በጥብቅ በተሳሰረው የግብጽ ሕዝብ ላይ የወዳጅነትና የትብብር መንፈስ አቋም እንዳለው ነው የምገነዘበው፤›› ሲሉ ነው ለቅዱስነታቸውና ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ ያላቸውን በጎ ተስፋ የገለጹት፡፡

በተመሳሳይም፤ ይህን የኢትዮጵያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ግንኙነት መሠረት በማድረግ ሙስጠፋ አል ላባድ የተባለ ሊባኖሳዊ ፖለቲከኛና ጸሐፊ/ጋዜጠኛ፤ ‹‹Egypt is Battling Ethiopia over the Nile Water›› በሚል ርዕስ ከዓመታት በፊት አንድ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር፡፡ ይህን የአል ላባድን መጽሐፍ ‹‹አልስ ሳፊር›› የተባለ የሊባኖስ ዕለታዊው የዐረብኛ ጋዜጣ የመጽሐፉን አጭር ዳሰሳ በፊት ገጹ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡

ራኒ ጌሃ የተባለ ጋዜጠኛ የሊባኖሱን ‹‹አልስ ሳፊር›› ጋዜጣ ዳሰሳም፤ ‹‹Egypt and Ethiopia Heading toward a War over Water›› በሚል ርዕስ በእንግሊዘኛ አሳትሞ ወሬውን ለዓለም መገናኛ ብዙኃን አድርሶት ነበር፡፡

ሊባኖሳዊው ጸሐፊ ሙስጠፋ ላባድ በዚህ መጽሐፉ፤ ‹‹ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን የውኃ ድርሻ በተመለከተ ለምታነሳው ጥያቄዎችና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የጀመረችውን ድርድር ፈር ለማስያዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሺሕ ዘመናት እናት በሆነችው በግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በኩል አማራጭ ዕድሎችን ማማተር እንዳለባት ነበር፤›› ሲወተውት የነበረው፡፡

የኢትዮጵያ ቤ/ክ ከግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክን ጋር የነበራትን ለ1600 ዓመታት የዘለቀው ግንኙነት በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ሊነሳ የሚችል በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎችን የያዘ ነው፡፡ ወደእነዚህ ሰፊ ዝርዝር አጀንዳዎች ለመግባት አዳጋች ቢሆንም ነገርግን በአብዛኛው የቤተክርስቲን ምሁራን ዘንድ፤ በሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ግንኙነት የቅኝ ግዛት ባህሪ የነበረውና በሀገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ የጣለ ግንኙነት ነበር በማለት ይከራከራሉ፡፡

ይህን በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ የሚነሳውን በኢትዮጵያና በግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ በኩል ለ1600 ዓመታት የዘለቀውን ግንኙነት፤ የታሪክና የሃይማኖት ትስስር ውል እንደያዝን ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለውን የታላቁን የኅዳሴ ግድብ በተመለከተ ግብፅ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቤ/ክን በኩል የተማሕጽኖ ጥያቄ ስታቀርብ ነበር፡፡

በተለይ ግብጻውያን ለሺሕ ዘመናት የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ኮፕቲክ ከኢትዮጵያ ቤ/ክን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ- የዓባይ ውኃን በተመለከተ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በኩል ጥያቄያቸውን ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ለማቅረብና ግፊት ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ሙከራ አድርገዋል፡፡ የዚህ እሳቤ ዋንኛ መነሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ቤ/ክ እና የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ከነበራቸው ሺህ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት የሚመዘዝ ነው፡፡

ወደኋላ ተጉዘን የታሪክ መዛግብትን ስናገላብጥም የቀደሙ ኢትዮጵያውያን ክርስትያን ነገሥታትና ገዢዎች የዓባይ ውኃን ከግብጽ የሃይማኖት አባቶች ሊቀ ጳጳሳትን ለማስመጣትና በክርስትያን ግብጾች በእምነታቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው ግፍና መከራ እንደ መደራደሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ለአብነትም ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ (ካልዕ) በጻፉት ‘‘የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ’’ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፤

‘‘በዛግዌ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ ለመገደብ በተደረገ እንቅስቃሴ የተደናገጡት የግብጽ ገዢዎች የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ የኾኑትን አቡነ ሚካኤልንና አቡነ ገብርኤልን ብዙ ስጦታ አስይዘው ወደ ኢትዮጵያ ልከው ነበር፡፡’’

በሌላ በኩልም ግብጻውያን ክርስትያኖች ይደርስባቸው የነበረውን ግፍና መከራ በተመለከተ ዜና የደረሳቸው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ለግብጽ ሱልጣን/ገዢ በመልእክተኞቻቸው በኩል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ልከውላቸው ነበር፡፡ ይህን ከስድስት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ወደ ግብጽ ገዢ/ሱልጣን የላኩትን የማስጠንቀቂቀያ ደብዳቤ በተመለከተም፤ ጁሊያን ጂ. ፕላንቴ የተባሉ አውሮፓዊ ምሁር፤ ‘‘The Ethiopian Embassy to Cairo of 1443 A Trier Manuscript of Gandulph’s Report, with an English Translation’’ በሚል ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ባቀረቡት ጥናታዊ ድርሳናቸው እንዲህ ለንባብ አብቅተውት ነበር፡፡

ንጉሥ ዘርዓያዕቆብ በርካታ ገጸ-በረከት ይዘው ለተማጽኖ የመጡትን በግብጹ ሱልጣን መልእክተኞች አማካኝነት የላኩት ደብዳቤም በከፊል የሚከተለውን መልእክት የያዘ ነበር፤

‹‹… ያመጣችሁት ብርና ወርቅ እንዲሁም ሌሎች ስጦታዎቻችሁ ለራሳችሁ ይሁኑ፣ እኔ የክርስቲያን ንጉሥ ነኝ ገዢዎቻችሁ በተደጋጋሚ በግብጻውያን ክርስቲያን ወንድሞቻቻን ላይ ለሚያደርሱት ግፍ በቀልን ላድርግ ብል ዓባይን ውኃ በመገደብ የከፋ ነገር ላደርስባችሁ እችል ነበር፤ ግና ሕዝቤና እኔ በንጹህ ኅሊና የምናመልከው ጌታዬ፣ አምላኬና ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር አምላክ ነውና ያስተማርኝ ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ግራውን ደግሞ አዙርለት ስለሚል ስለአምላኬ ፍቅርና ውለታ ስል ያሰብኩትን ሁሉ ትቼያለሁ፤ መንግሥታችሁ በክርስቲያን ግብጻውያን ወንድሞቻችን ላይ የሚያደረሰውን ግፍ ብቻ እንዲያቆም ንገሩት…፤››

ኢትዮጵዊው ንጉሥ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ለግብፁ ሱልጣን የላኩት ይህ ደብዳቤ በሮም፣ ቫቲካን በብሎቲክ ቤተ-መጻሕፍት በማይክሮ ፊልም ቁጥር/MS. 477 fol. 251r- 252v ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

ይቀጥላል . . .

ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለአፍሪካ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

191372
Previous Story

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

191391
Next Story

ፕሬዝዳንቷ ፋኖን ደገፈች | በአገዛዙ ባልስጣናት ላይ አሜሪካ ማዕቀብ እንድትጥል ሴናተሩ ጠየቁ

Go toTop