አብይ አህመድ የሽግግር ሥርዓት አስፈላጊነትን ወይም አላስፈላጊነትን እንዲወስን ፈፅሞ ሊፈቀድለት አይገባም!!!

Fake CounselJune 9, 2024

ጠገናው ጎሹ

የዚህ አስተያየቴ ዓላማ ግልፅና ግልፅ ስለሆነው እና የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስከፊና አደገኛ የሞራልና የሥነ ልቦና (የሰብዕና)   ቀውስ የተጠናወተው አብይ አህመድ ከስድስት ዓመታት በላይ  ስለፈፀመውና ስላስፈፀመው  ፖለቲካ ወለድ ወንጀል መዘርዘርና መተንተን አይደለም። ለምን? ቢባል እንኳንስ የሰብአዊነትና የዜግነት እሴቶች (መብቶችና ነፃነቶች) ጨርሶ ትርጉም እንዲያጡ የመደረጋቸውን ግዙፍና መሪር እውነት በመስማት ሳይሆን በመኖር (በመከራው ተሞክሮ) የሚያውቀው መከረኛ የአገሬ ህዝብ ለዘመኑ የኢንፍርሜሽን ቴክኖሎጅ ምሥጋና ይግባውና የዓለም ማህበረሰብም በሚገባ ያውቀዋልና ነው።

ይህ ማለት ግን አስከፊ በሆነ ሁኔታ በመከረኛው ህዝብ ላይ ስለ ወረደውና እየወረደ  ስላለው ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ የተፃፈው፣ የተነገረው፣የታየውና  የተሰማው በቂ ወይም ከበቂ በላይ ነው ለማለት አይደለም። በቂ ነው ብንል እንኳ የመከራው ዶፍ እስካልቆመ ድረስ መናገሩና መነጋገሩ ከቶ ሊቆም አይችልም፤ መቆምም የለበትም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ምን ሆነና ምንስ እየሆነ ነው (what happened and what is happening) የሚለውን ምን መደረግ አለበት ( what is to be done) ከሚለው ጥያቄ ጋር እያነፃፀርንና እያቆራኘን ካላስኬድነው እንደ አብይ አህመድ አይነቱን ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ዲስኩር (መነባንብ) እየተከተልን ወደ መሬት በማይወርድ ግልብ ስሜት እየሞቅንና እየቀዘቀዝን የመከራንና የውርደትን ዘመን ማራዘም ነው የሚሆንብን።

ለዚህ ነው የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሞራል፣ የሥነ ልቦና እና የሥነ ምግባር ቀውስ የተጠናወተው መሆኑን እጅግ ግዙፍና መሪር በሆነው የስድስት ዓመት አገዛዙ እጅግ ከበቂ በላይ ያወቅነውንና የምናውቀውን ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ ቢያንስ ግልፅና ቀጥተኛ በሆነ የሃሳብ ይዘትና አቀራረብ በቃህ በማለት በአንፃራዊነት ህልውና፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ እና የጋራ እድገት የሚረጋገጥባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያስችላሉህዝብ አቀፍና ሁለገብ ትግሎችን ሂሳዊ በሆነና የፖለቲካ ጥበብን በተላበሰ ሁኔታ ማገዝና ማበረታታት ለነገ የሚባል መሆን የለበትም።

እንዲህም ሲሆን ነው ኮሚሽን ተብያቸው ገደብ የለሽ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት አካል እንደሆነ ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳቸውን ከነዙብን በኋላ የገድብ የለሽ ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ሥጋት ላይ ይጥላል የሚሉት የሽግግር መንግሥትና የሽግግር ፍትህ ጥያቄ ሲነሳ ያዙንና ልቀቁን የሚሉትን እኩያን ገዥ ቡድኖች ከፈለጉ የሂደቱ ተሳታፊ በመሆን የበደሉትን መከረኛ ህዝብ እንዲከሱ እና ካልፈለጉ ግን ከመከረኛው ህዝብ የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ፍኖተ ተጋድሎ ላይ ዘወር እንዲሉ ቁርጡን በማሳወቅ ወደ ፊት መገስገስ የሚቻለው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የሽግግር መንግሥት ጥያቄን ውድቅ ለማድረግ ከተጠቀመባቸው ምክንያቶች ዋና አድርጎ የጠቀሰው ምርጫን ነው። በትክክለኛው ትርጉሙና ተግባራዊነቱ ምርጫ የምርጫ ካርድ አዘጋጅቶ ሳጥን ውስጥ የመጨመር ጉዳይ ሳይሆን በተገቢው ግንዛቤ ላይ በተመሠረተ እና የነፃነትና በራስ የመተማመን ጉዳይ  በሰፈነበት አውድ (environment) አስፈላጊ የሆነ ህጋዊነትንና ሌሎች የማስፈፀሚያ ደንቦችንና መመሪያዎችን አሟልቶ ራሱን በእጩነት ላቀረበ ፓርቲ ወይም ድርጅት ድምፅን የመስጠት እና ካሸነፈም  ተልእኮውን በሙሉ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት መወጣቱን የመከታተልና የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ይህንን መሠረታዊ የምርጫ ምንነትና እንዴትነት  ሀ) ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ከሚነግረን የአገራችን እጅግ የተበላሸ (ሁሉን ጠቅላይ ከሆነው የገዥ ፓርቲ ሸፍጥና ሴራ) ጋር ለማመሳሰል በፍፁም አይቻለመ ለ) ከሁሉ የከፋውና የጠቅላይ ሚኒስትር ተብየውን “በምርጫ አሸንፌያለሁና ሽግግር አይሠራም” ባይነት ውድቅ (ፉርሽ) የሚያደርገው መሪር ሃቅ ብልፅግና ተብየው የተከበረችበትን እርሷነቷን ለርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት አሳልፋ በመስጠት ባዋረደችው ብርቱካን ሚዴቅሳ መሣሪያነት  ምርጫ ውስጥ እንዲገባ የተፈቀደለት ቢያንስ ለስሙ ህጋዊ ነው የሚያሰኘውን ቅድመ ሁኔታ ሳያሟላ የመሆኑ ጉዳይ ነው።

ፖለቲካ ወለድ የሆነውን የመከራና የውርደት ምክንያትና አስከፊነት ከምር በሆነ አቀራረብና ይዘት የማወቁ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ   እጅግ ፈታኙና ወሳኙ ጥያቄ (ጉዳይ) ግን በመስማት ሳይሆን በመኖር የተረዳነውን የመከራና የውርደት እኛነት እንዴትና መቼ ወደ የደስታና የክብር እኛነት እንለውጠው (What is to be done and when)? የሚለው ነው። ለዘመናት የዘለቀውንና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እጅግ አስከፊ (deeply tragic) በሆነ ሁኔታ የቀጠለውን የእኩያን ገዥዎች ሥርዓት ለዚህ  ፈታኝና ቁልፍ ጥያቄ  ተገቢና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ ታግለንና አስወግደን ለሁሉም ዜጎች የሚበጅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን  እውን ለማድረግ  ባለመቻላችን ምክንያት የአገራዊ ምክክርን ሂደትና ይዘት በእነርሱና በእነርሱ (በእኩያን ገዥ ቡድኖች) ልክ የለሽ ፍላጎትና ጥቅም መሠረት መሆን እንዳለበት ይኸውና ረግጠውና አስረግጠው እየነገሩን (እያስጠነቀቁን) ነው።

ምንም እንኳ ለስድስት ዓመታት የመጣንበትና በእጅጉ የሰለቸ የሴራና የሸፍጥ ዲስኩር አካል በመሆኑ አዲስና አስገራሚ ባይሆንም ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው መከረኛው የአገሬ ህዝብ “የሽግግር …” የሚባል ነገር እንደማይሞከር ያውቅለት ዘንድ የደሰኮረው ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ዲስኩር ከፍተኛ ትኩረትንና ተገቢውን አፀፋዊ ምላሽ የግድ የሚል ነው።

አብይ አህመድ ለሸፍጥ፣ ለሴራ፣ ለብልግና እና በአጠቃላይ ለእኩይ የፖለቲካ አጀንዳው (ዓላማው) ሽፋን ሰጭነት ያገለግሉት ዘንድ በአዋጅ ካቋቋማቸውና በዘመቻ መልክ ካሰማራቸው አካላት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን  (Ethiopian National Dialogue Commission) ተብየው በአዲስ አበባ አደረግሁት ባለው   የምስራች አብሳሪ አውደ ተውኔት  ላይ ተገኝቶ በተለመደው ሴረኛ ፣ ሸፍጠኛ፣ ባለጌና አደገኛ  አንደበቱ (ሰብዕናው)  ብዙ ከዘላበደ በኋላ ኢትዮጵያ  ውስጥ  የሽግግር መንግሥት አይኖርም። በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ብቻ ነው የሚኖረው።  ሃሳቡን የሚያቀርቡት  ተላላኪዎችና ከፋፋዮች ናቸው ”  በማለት  የአሻንጉሊትነት ቅብአተ ሹመት ቀብቶ የሾማቸውን ኮሚሽነሮች ተብየዎችን  ወራዳና አዋራጅ ተልእኮ በማያሻማ ሁኔታ ግልፅና ግልፅ አድርጎታል 

በህወሃት ጠርናፊነት እየተመራ ለዘመናት በዘለቀና እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚያው ሥርዓት ውላጅ በሆነው የኦሮሙማ/የብልፅግና ጠርናፊነት ለመግለፅ በእጅጉ በሚከብድ ሁኔታ እንዲቀጥል በተደረገ ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር ግዙፍና መሪር እውነታ ሥር የሚገኝ  መከረኛ ህዝብ የሽግግር  መንግሥትና የሽግግር ፍትህ ከአገራዊ ምክክር (national dialogue) አጀንዳዎች አንዱ  መሆን እንዳለበት ለሚያቀርበው ጥያቄ  “የተላላኪዎችና የከፋፋዮች ስለሆነ አያስፈልግም” በሚል ከመሳለቅና ከማስጠንቀቅ የበለጠ የአብይ አህመድንና የካምፓኒውን (የጠርናፊውን ቡድን) ፍፁም የሆነ እኩይነት (evil mindedness and evil-guided political behavior ) ማሳያ የለም።

እርግጥ ነው ከአብይ አህመድ አይነቱ ማነኛውንም ዘዴ ተጠቅሞ (by hock or crook) ልክ የሌለው የሥልጣን እና የግል ዝናን ጥማት የማርካት ክፉ ልክፍት ከተለከፈና በዚህም ምክንያት ናላው (አእምሮው) ክፉኛ ከታወከ ፖለቲከኛ የሚጠበቅ ነውና ከቶ ሊያስገርመን አይችልም። በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ከሆነ በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ የተጨማለቀው ምንነቱና ማንነቱ በፍትህ አደባባይ ሊያስጠይቀው እንደሚችል የሚያሳስበውና የሚያቃዠው ጠቅላይ ሚኒስትር የሽግግር መንግሥትና የሽግግር ፍትህ የሚለውን ሃሳብ ባነበበና በሰማ ቁጥር “እንዳትሞክሯት” የሚል የማስጠንቀቂያ ዲስኩር ቢደሰኩር የማይጠበቅ አይደለም።

እጅግ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ባለጌ፣ ጨካኝና ትውልድ ገዳይ የሆነውን የገዥ ቡድኖች ሥርዓት ረጅምና መሪር ተሞክሯችን ተጠቅመን ቢቻል አደብ ለማስገዛት ካልሆነ ግን ያለንበትን ዘመን በሚመጥን የጋራ ትግል (ጥረት) ገንቢና ዘላቂ ፍኖተ ለውጥን ፈልገን ለማግኘትና  ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ  እስካልተዋጣልን ድረስ ልክ የሌለውና አደገኛ የሥልጣንና የግል ዝና ልክፍተኛ (excessive self-aggrandizing   or  narcissist personality) ልክፍተኛ የሆነው የአብይ አህመድ አይነት ፖለቲከኛ ሰለባዎች ሆነን እንቀጥላለን።

ከዚህ አስከፊና አስፈሪ የፖለቲካ እኛነት ሌላው መውጫ መንገድ  ፈጣሪውንና አሳዳጊውን ህወትን በስልት (ግልብ በሆነ የስሜት ፈረስ በሚጋልብ የህዝብ ድጋፍ)  የበላይነቱን ተረኝነት ተቆጣጥሮ ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት አዙሪቱን እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ያስኬደውንና እያስኬደ ያለውን  የኦሮሙማ/የብልፅግና የፖለቲካ ተውኔት እንደ እውነተኛ ለውጥ በመቁጠር አለን የሚሉትን የትምህርት ደረጃ፣ የሥራ (የሙያ) ልምድ እና የእድሜ ተሞክሮ ጨርሶ በማይመጥን  ሁኔታ  የሴረኛ፣ የሸፍጠኛ፣ የባለጌና የጫካኝ ገዥ ቡድን ተጋላቢ ፈረሶች (የሰው ሥጋ ለባሽ አሻንጉሊቶች) በመሆን  የመልካም ትውልድ ተምሳሌቶች ሆነው የመገኘትን ወርቃማ እድል ያበላሹትን የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተብየዎችን ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለቢጤዎቻቸውና በአጠቃላይ ለትውልድ ገንቢ የሆነን አስተማሪነት በተላበሰ ሂሳዊ አስተያየት ልክ እንዳልሆኑ የመንገሩ አስፈላጊነት ነው።

በእውነት ስለ እውነት መነጋገር ካለብን እንኳንስ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ እና የሙያና የእድሜ ተሞክሮ ካለው ወገን የዘመን ጠገቡንና በተለይም ከስድስት ዓመታት ወዲህ ፈፅሞ ለመግለፅ በሚከብድ ሁኔታ አስከፊ እየሆነ የመጣውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ አስከፊ ውጤት ከርቀት ወይም ከዳር ቆሞ ሳይሆን በመኖር የሚያውቅ እና ሚዛናዊና ቅን ህሊና ያለው ፊደል ያልቆጠረ ወገንም አሳምሮ የሚያውቀውንና በእጅጉ የሚፀየፈውን ሥርዓት የኮሚሽነርነት ቅብአተ ሹመት ተቀብሎ ራስን በትውልድ ማፈሪያነት ላይ ማግኘት ከሰው ልጅ አስቸጋሪ ባህሪ አንፃር የሚገርም ባይሆንም በእጅጉ ያሳዝናል።

መከረኛው የአገሬ ህዝብ በታሪክ ያጋጠሙት የውጭ ወራሪዎች ከፈፀሙበት ግፍ ጋር ሲነፃፀር ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ አስከፊ የሆነ ፖለቲካ ወለድ ግፍ የፈፀሙበትና እየፈፀሙበት ያሉት የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሥርዓት ሰላማዊ በሆነ የመሸጋገሪያ መንግሥት አማካኝነት ወደ አስተማማኝና  ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ይቻል ዘንድ ያቀረበውን ጥያቄ “የከፋፋዮችና የተላላኪዎች” በሚል ከሚሳለቅና “ካላረፋችሁ እናንተን አያርገኝ” የሚል  የግብዝነትና የትዕቢት መርዙን የሚረጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ በአሻንጉሊትነት ካቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ተብየ አገር ከፖለቲካ ወለድ መከራ ይፈወሳል ብሎ ማመንና የተውኔቱ አጃቢ መሆን ራስን የመከራና የውርደት አዙሪት ሰለባ አድርጎ ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆን ነው።

አዎ! ዘመን ጠገብ በሆነው ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት አዘቅትና አዙሪት ሰብረን መውጣት አቅቶን ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ  ለማመን ቀርቶ ለማሰብ በሚከብድ  ሁኔታ ውስጥ ራሳችንን ያገኘነው የጋራ የፖለቲካ ግንዛቤን በተላበሰ፣ በቀቢፀ ተስፋ ሳይሆን ግልፅ በሆነና  ወደ ድርጊት በሚተረጎም ራዕይ፣ ክስተቶች ጋር በሚለዋወጥ ሳይሆን ፅዕኑ በሆነ መርህ፣  በሰበብ አስባቡ በሚልፈሰፈስ ሳይሆን በማይናወጥ የዓላማና የግብ መሠረት ላይ በቆመ ትግል (ተጋድሎ) እውን ለማድረግ ባለመቻላችን መሆኑን ተረድተን በገንቢ ፀፀትና ከምር በሆነ ለውጥ ፈላጊነት  ዛሬውኑ በቃ! ካላልን ኢትዮጵያ የአብይ አህመድና የፖለቲካ ቁማር ካምፓኒው (ገዥ ቡድን) መጫወቻ ሆና ትቀጥላለች ወይም እንዳልነበረች ትሆናለች።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

191027
Previous Story

የፋኖ እርምጃ :- ከትጥቅ ትግል እስከ ሀሳብ ትግል | የመከለከያው ካንፕ በፋኖ ተሰበረ | ፋኖን ማሸነፍ አቅቶናል “ጄነራሎቹ” 60,000 ፋኖ በኤርትራ በርሃ | | ህዝቡ ግልብጥ ብሎ ወደ አደባባይ ወጣ! ቀጥታ ስርጭት ከአላማጣ ከተማ!

4
Next Story

አብይ አህመድ አሊ ሰይጣናዊ ፔንጤ! እግዛብሔር ነፍህን አይማረው!!!! | ከሞት በብዙ ታምራት ተርፊያለሁ | የ4ኪሎው ንጉሥ ፍፃሜው ደርሷል

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |
Go toTop