በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
- እንደ መንደርደሪያ
ዓለምን ክፉኛ ባመሰቃቀለውና ሚሊዮኖች በገፍ ባለቁበት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አውሮፓውያኑ የተገበሩት አንድ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ነበር፡፡ ይህ የተኩስ አቁም ‹‹the Christmas Truce/የልደት በዓል ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም›› በመባል ይታወቃል፡፡ መነሻውም አውሮፓውያን በታላቅ መንፈሳዊና ባህላዊ ድምቀት በሚያከብሩት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት/በገና በዓል ሲሆን፤ በዚህ ሰላም በታወጀበት የደስታ/የሐሤት ቀን- ‹‹መዋጋት፣ ጦርነትና ደም መፋሰስ የሚገባ አይደለም፤›› በሚል ተግባራዊ ያደረጉት እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡
እንዲሁም እንደ ክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮም፤ ‹‹Christmas is the Holiday of Forgiveness and Gifts/የልደት/የገና በዓል የዕርቅ/ይቅርታ እና የስጦታ በዓል ነው!›› በሚል በልደት በዓል ዋዜማና የበዓሉ እለት- በጦርነቱ ወቅት በሁለት ጎራ ተከፍለው ሲፋለሙ የነበሩ አውሮፓውያን ወታደሮች ጊዜያዊ የሆነ ተኩስ አቁም በማድረግና ስጦታ በመለዋወጥ የገና በዓልን ያለ መሳሪያ የተኩስ ልውውጥ ያሳለፉበት ክሥተት ነው- ‹‹the Christmas Truce/የልደት በዓል ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም›› ስምምነት፡፡
ይህን በጎ የሆነ ታሪካዊ ክሥተት ይዘን እኛስ እንዴት ነው ቢያንስ በዚህ ፍቅር፣ ሰላምና ዕርቅ በሚሰበክበትና በሚታሰብበት የዐቢይ ጾም እና የረመዷን የጾም ወራት- ‹የጾም ወራት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም/the Fasting Truce› እንዲደረግ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች አዋጅ ቢያስነግሩ ምን አለበት፤ መንግሥትም ከእልክና በመሳሪያ ኃይል ችግሩን እፈታለኹ ከሚለው ግትርነት ወጥቶ የሃይማኖት አባቶችን በቅንነት መንፈስ ቢተባበር፡፡
ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከሁለት ዓመት በፊት የኮረና ወርረሽኝ ወቅት በሃይማኖት ተቋማትና በመንግሥት ትብብር በሁሉም ቤተ-እምነቶች ጸሎት/ምሕላ ታውጆ ነበር፡፡ የኮረና ወረርሽኝን በተመለከተ በወቅቱ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፤ ኮረና ሕይወታቸውን የነጠቀን ወገኖቻችን ቁጥር አሥር ሺሕ እንኳን አይሞላም፤ እንደ ሀገር ያደረሰብን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሰብአዊ ቀውስም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን የሀገራችን ክፍል (በትግራይ፣ በአማራና በአፋር) ካደርግነው ጦርነትና አሁንም በአማራና በኦሮሚያ የሀገራችን ክልሎች ካለው ጦርነት ጋር ሲነጻጸርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ባሳለፍነው የሁለቱ ዓመት ጦርነት ያደረሰብንን ምስቅልቅል በጥቂቱ ለማስታወስ እንሞክር እስቲ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ባደርግነው የእርስ በርስ ጦርነት በታሪካችን ከውጪ ወራሪ ኃይሎችም ሆነ እርስ በርሳችን ባደርግናቸው ጦርነቶች ከደረሰው እልቂት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት… ወዘተ አንጻር አቻና ተወዳዳሪ ያለው አይደለም፡፡
ከሃይማኖት አባት እስከ ሀገር ሽማግሌ፣ ከአፈ-ነቢብ እስከ ምሁራን፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በሆንበት በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት የደረሰው እልቂት (የቁጥሩ ነገር አከራካሪ ቢሆንም በዚህ ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝብ ለሞት መዳረጉ ይነገራል)፤ መፈናቀል፣ የመሠረተ ልማት ውድመት… በአጠቃላይ ሰብአዊና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊውና ፖለቲካዊ ቀውሱ ከምንገምተው በላይ ነው፡፡
የጦርነት ጐዳና ብዙ ስብራት አምጥቶብናል፡፡ የትግራዩ ጦርነቱ ይቍም እንጂ፣ ትቶት ያለፈው ጦስ ቀላል አይደለም፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቈጠሩትን ሕይወት አሳጥቷል፤ በርካቶችን የአካል ጉዳተኝነት ዳርጓል፡፡ ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ዜጐችን አፈናቅሏል፤ ከእጥፍ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለከፍተኛ ምግብ እጥረት አጋልጧል፡፡ ልጆችን ያለወላጅ፣ ወላጆችን ያለ ልጅ አስቀርቷል፤ ሚስቶችን መበለት አድርጓል፤ ሕፃናትን ሳይቀር ማግዷል፡፡ ኢትዮጵያ- እናቶችና አረጋውያን ልባቸው ክፉኛ የተሰበረባት ምድር ሆናለች፡፡
በዚህ ጦርነት ውስጥ፣ ልጆቻችን፣ እኅቶቻችንና እናቶቻችን ዘግናኝ በሆነ መልኩ ተደፍረዋል። የአካል ጉዳታቸውና የሥነ-ልቡና ስብራታቸው ከቃል በላይ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራችን ስም ጠልሽቷል፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሣ ጥላቻ ተዘራቷል፡፡ የምዕራቡ ዓለምም ፊቱን አዙሮብን ከርሟል፡፡ በርካታ የጤና፣ የትምህርትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፈርሰዋል። አኮኖሚያችንን አድቅቋል፣ ዕዳችንንና ኑሯችንን አክብዷል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሁሉ ረገድ አክስሮናል፤ አጠቃላይ በሀገሪቱ በጦርነቱ የደረሰው ውድመት 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ወይም 28 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር እንደሆነና ለመልሶ ግንባታ ብቻ ከ 20 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ በተለያዩ ጊዜያት ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ሊፈታ ከሚችል ግጭት ውስጥ የተወለደ የወንድማማቾች ጦርነት እንደመሆኑ መጠን፣ በታሪካችን ትልቅ ጥቍር ጠባሳ ትቶ አልፏል፤ ገናም እያለፈ ያለ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የጦርነት ውድመትና ቀውስ መማር ያቃተን እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ከጦርነት አዙሪት ለመውጣት አልተቻለንም፡፡
ከዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ቀውስ መውጣት እንዲቻለን የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ ተግባራዊ የሆነ ርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ለኮረና ወረርሽኝ አገር አቀፍ ጸሎትን/ምሕላን ያወጀው የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ፤ ዛሬስ ቤተ-እምነቶች አስተባብሮ ምነዋ ሚሊዮኖችን ለሳጣንና አሁንም በየቀኑ ዜጎቻችንን እንደ ቅጠል እያረገፈ ላለው የእርስ በርስ ጦርነት- አገር አቀፍ ጸሎት/ምሕላ እንዲታወጅና በዚህ የጾም ወራትም ‹‹የተኩስ አቁም›› እንዲተገበር መልእክት ለማስተላላፍ ስለምን ደከመ?!
በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች ዘንድ የሚገኙ ምእመናን በጾምና በጸሎት የፈጣሪን ፊትና ምሕረት በሚሹበት በዚህ ቅዱስ የጾም ወራት- በሁሉም ወገን ያሉ ተፋላሚዎች ጠመንጃቸውን ዘቅዝቀውና የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፤
በነጋ ጠባ በጦርነት እሳት እየተለበለቡ ያሉ ዜጎቻችን ጥቂት እረፍት እንዲያገኙ፤ በግፍ እየታረዱና በጠራራ ጸሐይ እየታገቱ ያሉ ወገኖቻችንም የሚታደጋቸው ያገኙ ዘንድ፤
የእናቶችና የሕፃናቱ ዋይታና ሰቆቃ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን ያባራ ዘንድ፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባኤ ሁለቱ ታላላቅ ቤተ-እምነቶች በጾምና በጸሎት ተጠምደው በሚገኙበት በዚህ ቅዱስ የጾም ወራት ‹የጾም ወራት የተኩስ አቁም ዐዋጅ› በሃይማኖት አባቶች/መሪዎች አማካኝነት ቢታወጅ የሚል ለውይይት መጫሪያ የሚሆን ሐሳብ ለማንሳት ወደድኹ፡፡
- ዕርቀ-ሰላምን ማውረድ ስለምን ተሳነን…?!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ምእመናን ዘንድ ዘንድ የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም/ዐቢይ ጾም የምንጾምበት እንዲሁም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድም የታላቁ የረመዷን ጾም የሚከናወንበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ እናም በተለይ በእነዚህ ጊዜያት አብልጠን በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ወደ ፈጣሪ መቅረብ እንዳለብን፤ ለፍቅርና ለበጎ ሥራ እንድንተጋና ሰላምን ዕርቅን እንድናወርድ የየሃይማኖቱ መምህራን ለምእመናኖቻቸው አብዝተው ያስተምራሉ፤ ይመክራሉም፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍትም፤ ‹‹ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ መባህን በመሠዊያው ላይ ከማቅረብህ በፊት ከወንድምህ ጋር አስቀድመህ ታረቅ፤ ይቅር እንድትባሉ ይቅር በሉ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፤ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፡፡ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ ዕርቀ-ሰላምን የሚሰብኩ (የሚያስታርቁ) ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና…፤›› በሚሉ የምክርና የተግሣጽ ኃይለ-ቃላት ልባችንን ለሰላምና ለዕርቅ፤ ለፍቅርና ለበጎ ሥራ የተከፈተ/የቀና እንዲሆን አብዝተው ያስተምሩናል፡፡
ግና ይህ አስተምህሮ ከቃል ባለፈ በልባችን ውስጥ ፍሬ እንዳላፈራ አሁን የተዘፈቅንበት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
‹‹አብዛኛው ሕዝባችን ሃይማኖተኛ ነው፤›› በሚበልባት ሀገራችን ኢትዮጵያ- ሰላምና ዕርቅ እንደ ሰማይ የራቀን፣ እርስ በርሳችን የምንጣላና የምንጠላላ፤ የምንዋጋና የምንበቃቀል፤ የምንከፋፈልና የምንከፋፋ… ሕዝብ ከሆንን ዓመታትን እያስቆጠርን ነው፡፡ በርግጥ ብዙዎች የሚቀኑበት በርካታ አኩሪ ታሪኮች ያለን ታላቅ አገር የመሆናችንን ያህል በተቃራኒው ደግሞ እንደ ሕዝብ የእርስ በርስ ጥላቻችን፣ ቂምና በቀልን አስወግድን ዕርቀ-ሰላምን በማውረድ ረገድ አሁንም ድረስ በትልቅ ፈተና ውስጥ ያለን ሕዝብ ነን ብል ከእውነታው የራቅኹ አይመስለኝም፡፡
ለአብነት ያህልም፤ ሚሊዮኖችን የገበርንበት የእርስ በርስ ዕልቂት ገና ደሙ በቅጡ ሳይደርቅ፣ የእናቶቻን እንባ ሳይታበስ፤ የሕፃናቱ ሰቆቃና ዋይታ አባሽ/የሚያብሰው ሳያገኝ… ለሌላ እልቂት፣ ለሌላ ጦርነት ጦራችንን ሰብቀን፤ ሰይፋችንን ስለንና ጋሻችንን ወልውለን፤
እረ ጥራኝ ጫካው፤
እረ ጥራኝ ዱሩ፤
ለአንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ፡፡ በሚል ዜማ ወደ ሌላ ጦርነት፤ ወደ ሌላ እልቂት ተሸጋግረናል፡፡
በርግጥም ጦርነትን ባህል ያደረግን፣ የእርስ በርስ ውጊያን የገና ጨዋታን ያህል የቀለለብን ሕዝብ ኾነናል፡፡ አንድ ኬንያዊ ወዳጄ፤‹‹… እናንተ ኢትዮጵያውያን ችግራችሁን ለመፍታት ቁጭ ብላችሁ ከመነጋገር ይልቅ አስቀድማችሁ የጦርነት አማራጭን ካስተናገዳችሁና ብዙ ነገር ከከሰራችሁ በኋላ ነው በስንት ተማጽኖ ለንግግር/ለድርድር የምትቀመጡት…›› በማለት ልቡ ያዘነበትን ትዝብቱን አካፍሎኛል፡፡
ዛሬም ቁጭ ብሎ ከመነጋገር፣ ከመደራደር ይልቅ በጥላቻ ላይ ሌላ ጥላቻን፣ በበቀል ላይ ሌላ በቀልን፣ በቂም ላይ ሌላ ቂምን እየደረብን የሞትን፤ የእልቂት መንገዱን ተያይዘነዋል… እናም ዛሬም የኢትዮጵያችን የደም ምድር/አኬልዳማ እንደሆነች ዘልቃለች፡፡
የሚያሳዝነው ወደፈጣሪያችን አብዝተን የምንቀርብበት፣ ለዕርቀ-ሰላም የምንትጋበት በምንልበት በዚህ ቅዱስ የጾም ወራት እንኳን የሰላም ምክንያት ሆነን የወገኖቻችን እልቂት ልንገታ፣ የእናቶችንና የሕፃናትን ዋይታ ልናስቆም፣ ሰላምን ልናወርድ አልተቻለንም፡፡
የሃይማኖት አባቶቻችንም ከመግለጫ ጋጋታ በስተቀር እንደ ጥንቱ ባህልና ትውፊት ታቦት ተሸክመው፣ መስቀል ይዘው መንግሥትን ለመገሠጽ፣ ዐውደ-ግንባር ድረስ ወርደውም ዕርቀ-ሰላምን ለማውረድ፤ ጎራ ለይተው የሚፋለሙ የአንድ እናት ምድር የማኅፀን አብራኮችን ‹አንተም ተው አንተም ተው› ብለው ለመዳኘት አልተቻላቸውም… እንደውም አንዳንዶች በአደባባይ ወጥተው ጦርነትን የሚያውጁ፣ ‹‹እንዴት አንድ ገዳይ፣ እንዴት አንድ ወንድ ይጠፋል?!›› የሚሉ የጦርነት ሰባኪ የሃይማኖት አባቶችን ታዝበናቸዋል፡፡
- እንደ መውጫ
እ.ኤ.አ. በ2015 በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሰላምን ለማስፈንና ግጭቶችን ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች እና መንፈሳዊ መሪዎችን ሚና በተመለከተ ከኢጋድ አባላተ-አገራት የተውጣጡ የሃይማኖት መንፈሳዊ አባቶች እና መሪዎች ‹‹IGAD Countries Religions Leaders Consultation on the Welfare of the Region›› በሚል መሪ ቃል የተሳተፉበት አንድ ስብሰባ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ለሦስት ቀናት ተካሂዶ ነበር፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የደቡብ እና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፤ ‹‹Peace and the Human Race›› በሚል ርእስ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው የሚከተለውን ሐሳብ አንስተው ነበር፤
‘‘ሃይማኖትና ሃይማኖተኝነት ጎልቶ በሚታይበት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አብዛኛው ሕዝቧ አማኝ በሆነባት ሀገር የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ግጭቶች በሚከሠቱበት ወቅት ግጭቶቹ አስከፊ ወደሆነ ደም መፋሰስና ጦርነት እንዳያመሩ በሰላምና በዕርቅ እንዲቋጩ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው፤’’ ያስረዳሉ፡፡
ታሪካዊ አብነቶችን ለመጥቀስም ያህልም፤ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና፣ በተለይም ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለማችን የሚገኙትን ሦስቱን ታላላቅ ሃይማቶችን- ጁዳይዝምን፣ ክርስትናን እና እስልምናን በሰላም ተቀብላ ያስተናገደች፣ የዘር/የብሔር/የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት … ወዘተ ልዩነት ሳያግዳት፣ ከፍ ባለ ሰብአዊነትና ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ ‹ሰላምና ፍትሕ› በጽናት የቆመች ሀገር መሆኗን ለዓለም ያሳየች ናት፡፡
ስለሆነም፤ እነዚህን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ መልካም እሤቶቻችንን ከፍ በማድረግ- እኛ የሃይማኖት መንፈሳዊ አባቶችና መሪዎች፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እና በአጠቃላይም በአፍሪካና በመላው ዓለም- ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩና የሰላም፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ምልክት/Symbol እንድትሆን በማድረግ ረገድ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት የነበራቸውና አሁንም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ስለሆነም የሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎች ቢያንስ በዚሁ የጾም ወራት እንኳን የመድፍና የመትረየስ ላንቃዎች ዝም ይሉ ዘንድ፣ በግፍ እየታረዱና እየተጨፈጨፉ ያሉ ወገኖቻችንን እንባና ደም ይቆም ዘንድ፣ የእናቶችና የሕፃናቱ ሰቆቃና ዋይታ ይገታ ዘንድ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን በተፋላሚዎች መካከል የተኩስ አቁም ይደረግ ዘንድ የሰላም እንደራሴ፣ አስታራቂ ሆነው ሊቆሙ ይገባል፡፡
በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች ዘንድ የሚገኙ ምእመናን በጾምና በጸሎት የፈጣሪን ፊትና ምሕረት በሚሹበት በዚህ ቅዱስ የጾም ወራት- በሁሉም ወገን ያሉ ተፋላሚዎች ጠመንጃቸውን ዘቅዝቀውና የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፤
በነጋ ጠባ በጦርነት እሳት እየተለበለቡ ያሉ ዜጎቻችን ጥቂት እረፍት እንዲያገኙ፤ በግፍ እየታረዱና በጠራራ ጸሐይ እየታገቱ ያሉ ወገኖቻችንም የሚታደጋቸው ያገኙ ዘንድ፤
እንዲሁም የእናቶችና የሕፃናቱ ዋይታና ሰቆቃ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን ያባራ ዘንድ፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባኤ ሁለቱ ታላላቅ ቤተ-እምነቶች በጾምና በጸሎት ተጠምደው በሚገኙበት በዚህ ቅዱስ የጾም ወራት ‹የጾም ወራት የተኩስ አቁም ዐዋጅ› በሃይማኖት አባቶች/መሪዎች አማካኝነት ቢታወጅ…፡፡
ቢያንስ በዚህ ፍቅር፣ ሰላምና ዕርቅ በሚሰበክበትና በሚታሰብበት የዐቢይ ጾም እና የረመዷን የጾም ወራት- ‹የጾም ወራት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም/the Fasting Truce› እንዲደረግና የድርድርና የዕርቅ መንገድ እንዲመቻች የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች አዋጅ ቢያስነግሩ ምን አለበት፤ መንግሥትም ከእልክና በመሳሪያ ኃይል ችግሩን እፈታለኹ ከሚለው ግትርነት ወጥቶ የሃይማኖት አባቶችን በቅንነት መንፈስ ቢተባበር መልካም ነው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!!