የዘመን ጠገቡ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ክፉ አዙሪት መሰበሪያው እንዴትና መቼ ይሆን?

March 25, 2024

ጠገናው ጎሹ

ይህ ጥያቄ እጅግ ግዙፍ፣ ፈታኝና ዘመን ጠገብ እንጅ አዲስ እንዳልሆነና ሊሆንም እንደማይችል በሚገባ እገነዘባለሁ ። ለዘመን ጠገቡ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማመን ቀርቶ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ የቀጠለውን የባለጌ፣ የሴረኛ፣ የሸፍጠኛ፣ የፈሪና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች የፖለቲካ ሥርዓት አስወግደን ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓተ ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ ያልተሳካልን ይህንኑ ቁልፍ (ወሳኝ) ጥያቄ በአግባቡና ወደ ውጤት ሊተረጎም በሚችል ሁኔታ ለመመለስ ባለመቻላችን ነውና አሁንም ከመሪሩ ውድቀታችን ተምረን ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እስካልቻልን ድረስ ጥያቄው ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል። የሚሻለው ብቻ ሳይሆን ብቸኛውና ትክክለኛው ፍኖተ መፍትሄም ይህንኑ ከምር ተረድቶ ጥያቂውን በአግባቡ መመለስ ነው።

ቀድምት በሆኑ የፖለቲካ ሥርዓቶች የተፈፀሙት አስቀያሚ ስህተቶች በዘመኑ ከነበረው የህሊናዊ ንቃትና ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሊታዩና ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገባ የመሆኑ እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ጎሳን/ዘርን ፣ ጥላችን፣ መለያየትንና መገዳደልን ህገ መንግሥታዊ ያደረገውን የሩብ ምዕተ ዓመት ህወሃት/ኢህአዴግ) መራሽ ሥርዓተ ፖለቲካ እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚሁ ሥርዓት ውላጆች በሆኑ የኦሮሙማ/የኦነግ/ ፖለቲከኞች የበላይነት እየተካሄደ ያለውን ሰቆቃዊ አገዛዝ ከምር ከመፀየፍ፣  ከመታገልና ለዜጎች ሁሉ የሚመች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ከማድረግ ይልቅ ከመከራና ከውርደት ጋር እየተለማመድን ቀጥለናል።

ይህ ደግሞ በተራው ዘመን ጠገብና በእጅጉ አስከፊ የሆነን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚያስችል አዳዲስ አስተሳሰብና አሠራር ከመሞከር ይልቅ ለዘመናት የመጣንበትንና የወደቅንበትን አስተሳሰብና አካሄድ እየደጋገመን አዲስ ወይም የተለየ ውጤት የምንጠብቅ ጉዶች (ደካሞች) አድርጎናል።

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳው ዒላማ ያደረጋቸውን የየሃይማኖት ተቋማት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማእረግ አባላትን ሰብስቦ የተወነውን እጅግ የወረደና አዋራጅ ተውኔተ ሴራ ከምር ያስተዋለ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው መከራንና ውርደትን ከመለማመዳችን የተነሳ አገርን ምድረ ሲኦል ያደረጉትንና እያደረጉ ያሉትን እኩያን ገዥ ቡድኖች በእግዚአብሔር ስም እያወደስን በራሱ በፈጣሪ ላይ የምንሳለቅ ጉዶች የመሆናችንን መሪር እውነት የሚስተው አይመስለኝም።

“ተሞክሮ ያልሠራን ተመሳሳይ ነገር እየደጋገሙ የተለየ ውጤት መጠበቅ ቂልነት/ጤናማ ያልሆነ ባህሪ/ የአእምሮ ሸውራራነት/እብድት ነው (insanity is doing the same thing over and over again and expecting different results.)” ይህ አባባል የሳይንቲስት አልበርት ኤንስተይን እንደሆነ የሚነገርለት ቢሆንም ትክክለኛው ባለቤት በትክክል ማን እንደሆነ እስካሁን በተሟላ ሁኔታ ስምምነት ላይ የተደረሰ አይመስለኝም።

ባለቤትነቱ የሳይንቲስቱም ይሁን የሌላ ሰው ትልቁ ጉዳይ አባባሉ ለየትኛውም አይነት የሰው ልጅ የህይወት ዘርፍ እውነትነት ያለው ፣ትኩረት የሚሻ እና በሰፊው የሚጠቀስ ከመሆኑ ላይ ነውና በዚሁ መሠረታዊ ግንዛቤ ወደ ተነሳሁበት የእኛው ጉዳይ ልለፍ።

አንድ ነገር (አስተሳሰብና አካሄድ) የሚያሳየውን የአወንታዊ ለውጥ ውጤት አበረታችነት በመገምገም ለተወሰነ ጊዜ መታገሥና አስፈላጊ ከሆነም በድጋሚ መሞከር ትክክል ነው። ለዘመናት የተሞከረንና ለመቁጠር እጅግ በሚያስቸግር ሁኔታ ደጋግሞ የወደቀን (ያልሠራን) አስተሳሰብና አካሄድ የሙጥኝ ማለት ግን እንኳንስ ልዩ የማሰቢያ አእምሮ እና ብቁ አካል ለተቸረው ሰብአዊ ፍጡር ለደመነ ፍስ እንስሳትም አይሆንም። እንስሳት አደጋ ባጋጠማቸው ቦታና አካባቢ ወይ አይሄዱም ቢሄዱም ደመ ነፍስነታቸው በፈቀደላቸው መጠን ተጠንቅቀው ነው። ይህንን ተገንዝበን ነፃነትና ፍትህ እንደሚፈልግ ሰብአዊ ፍጡርና እንደ ማህበረሰብ (እንደ ህዝብ) መሆን የሚገባንን ባለመሆናችንና ማድረግ ያለብንን ባለማድረጋችን ነው እንደ አብይ አህመድ አይነት ህሊና ቢስ ፣ባለጌና ጨካኝ ገዥዎቻችን ለመግለፅ በሚያስቸግር ደረጃ የመከራና የውርደት ማራገፊያቸው ያደረጉንና እያደረጉን የቀጠሉት።

አዎ! ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን የአገራችንን ዘመን ጠገብ ፣ ሁለንተናዊ ፣ ተደጋጋሚና አስከፊ ቀውስ (ውድቀት) ከምር ልብ ካልነው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ በእጅጉ ያሳፍራል፤ ያስደነግጣልም። ለነገሩ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ከመከራውና ከውርደቱ ጋር ስላለማመዱን ማፈርና መደንገጡም ከጊዜያዊ ግልብ ስሜት የማያልፍ እየሆነብን ከተቸገርን ዘመናትን አስቆጠርን። ከዚህ የከፋ የምንነትና የማንነት ቂልነት/ውርደት/ስንኩልነት (insanity) ይኖር ይሆን?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያውራምባው ታይምስ ድረ ገጽ ባለቤት ዳዊት ከበደ ወይስ ቀለለ?

ለርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ይውል ዘንድ በአብይ አህመድና በካምፓኒው (በአገዛዙ) በታሰበበትና በተዘጋጀ መድረክ አዲስ አበባን ጨምሮ በለየለት ደጋፊነታቸው የታወቁትን፣ የእውቀት ማነስ ያለባቸውንና የምን ቸገረኝነት ባህሪ ማንነት ሰለባዎች የሆኑትን ግለሰቦች ከየክልሉ በካድሬዎቹ አማካኝነት እያስመለመለ (እያስመረጠ) በመሰብሰብ ሊፈላሰፍባቸው፣ ሊሳለቅባቸው፣ ከፋፍሎ በማላተም የሴራውና የሸፍጡ ሰለባዎች ሊያደርጋቸው፣ ወዘተ ሲሞክር እና በከፊልም ቢሆንም ሲያስጨበጭባቸው መታዘብ ሚዛናዊና ክፉ ነገርን የሚፀየፍ ህሊና ላለው ሰው በእጅጉ ያማል።

ብዙውን ጊዜ በሌሎች ወይም በራሳችን ወይም በሁለቱም ምክንያት ከወደቅንበት አለመነሳት ብቻ ሳይሆን ይበልጥ አስከፊ የሆነን የውድቀት አባዜ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፍን የቀጠልነው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ራሳችንን ለምንና እንዴት? ብለን ከምርና ከቁጭት በመጠየቅ ተገቢና ዘላቂ መፍትሄ አምጦ ከመውለድ ይልቅ በክስተቶች የትኩሳት ፈረስ ስንጋልብ የእነ አብይ አይነት ሴረኛ፣ ሸፍጠኛ፣ ባለጌና ጨካኝ ገዥዎች ወጠመድ ሰለባዎች ስለምንሆን ነው።

ይህ ደግሞ የምንመራው እርኩስነትን/እኩይነት በሚፀየፍ የመንፈስ ቅዱስ ሃይል ነው የሚሉትን የየሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ሊቃውንትና ባለ ሌላ ማዕረግ አባላትንም ሰለባዎቹ ሲያደርጋቸው  የፈተናችን ክብደት ይበልጥ አስከፊ ያደርገዋል። የሰሞኑ የቤተ መንግሥቱና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች መድረከ ተውኔት አዲስ ወይም የሚገርም ባይሆንም የደረስንበትን የውርደትና የአዋራጅነት ደረጃ በግልፅና በቀጥታ አሳይቶናል (ነግሮናል) ።

 እጅግ ከባዱ ጥያቄ ይህ መሪር እውነታ ትምህርት ሆኖን ለእልህ አስጨራሽ ትግልና ለእውነተኛ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እውን መሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳለን ወይንስ ገና ከዚህ የከፋና የከረፋ ውርደትና አዋራጅነት እንጠብቃለን? የሚለው ነው።

ገና መንበረ ሥልጣኑ ላይ እንደ ተሰየመ የሃይማኖት ተቋማትን በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እንዴት አድርጎ የርካሽና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታው አካል ሊያደርጋቸው እንደሚችል አስቦና አቅዶ በአስታራቂነት ስም በመቅረብ፣ “ብረትን እንደ ጋለ ምታ” ነውና በራሱ የጉዞ አውሮፕላን አሳፍሮ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ፣ ወደ አገር ቤት ከተመለሱም በኋላ “የዘመናችን ሙሴ ነህ”  የሚል ውዳሴ አብይ አህመድ እንዲቀኙለት አድርጎቸዋል። ከአምስት ዓመታት በላይ በሆነው የመከራና የውርደት አገዛዙ ደግሞ  በቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮችና ተከታዮች ፣ እና በአጠቃላይ በሌሎች ንፁሃን ዜጎች ላይ  የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ እዚህ ግባ የሚባል ተገቢ እርምጃ ያልወሰዱ መሆናቸውን በሚገባ አውቋቸዋል።

ለዚህም ነው በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ያመፁትን የዘር ልክፍተኛ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆፖሳት ተብየወች በእርሱ ርካሽ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አማካኝነት ቀኖናን ሽረው ሲሾሙለት ጨርሶ የናቃቸውና በእንወያይ ስም ጽ/ቤቱ ድረስ እየጠራ የሚሳለቅባቸው። ከሰሞኑ ደግሞ  ያሾማቸውን ካድሬዎች  ልብሰ ተክህኖና ልብሰ ጵጵስና አልብሶ እና መስቀል አስጨብጦ የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳው ተዋንያን በማድረግ የዚህ ትውልድ ማንነት፣ ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት በእጅጉ ፈትኖታልና ፈተናውን መወጣት የዚህ ትውልድ የቤት ሥራና ሃላፊነት ነው የሚሆነው።

ለማሳያነት ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን እንደሚከተለው ልጥቀሳቸው፦

·         ከስድስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በየሰዓቱና በየቀኑ አገር ምድረ ሲኦል ስትሆን እንኳንስ ለማስቆም “ለሆነውና እየሆነ ላለው አሳዛኝ ሁኔታ ሁሉ ሀዘኔን እየገለፅሁ ፤ይህ ይቆም ዘንድም እንደ የአገር መሪ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ለማለት የገደደው ሴረኛና ጨካኝ ሰው በሃይማኖት መሪነት ስም ጠርቶ ላናገራቸው ወገኖች “በዚህ በፆም ወቅት እስኪ ኑ እና እንነጋገር ያላቸው የመጀመሪያው መሪ” እንደሆነና እድለኞች እንደሆኑ ያምኑ ዘንድ ይሳለቅባቸዋል።ባይገርምም ህሊናን በእጅጉ ያቆስላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተስፋችን በእግዜር ነው! (በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት በዓለማችን ለተፈጠረው ታላቅ ቀውስ ማስታወሻ)

 

·         ሌላው ሁሉ ቢቀር ስለ ጣልቃ ገብነቱ የቤተ ክህነት አልባሳት ለብሰው የጎሳ/የዘር ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ካድሬነታቸውን በግልፅና በቀጥታ ካስመሰከሩ የሲኖዶሱ አባላት ተብየዎች የተሻለ ማስረጃ  የሚገኝ ይመስል “በሃይማኖታዊ ተልእኳችሁና ሥራችሁ ፈፅሞ ጣልቃ ገብቸ የማላውቅ ድንቅ መሪ ነኝና ልታደንቁኝ ይገባል” በሚል አይነት እጅግ አስቀያሚ የግብዝነት ሰብእና አፋቸውን ሊያዘጋቸው ሲሞክር፤ ካድሬዎቹ ወደ ፈጣሪነት የሚጠጋ አድናቆት እንዲያስተጋቡለት ያለ ንግግር ሲግባባቸው ፣ ሃይማኖትን እንጀራ መብያ ያደረጉ አብዛኛዎቹ ተሰብሳቢዎችን  ደግሞ በጭብጨባና አንገት መነቅነቅ ድንቅ መሪነቱን እንዲያረጋግጡለት ሲያማልላቸውመታዘብ ትእግሥትን በከፍተኛ ደረጃ ይፈታተናል።

 

·         ለስድስት ጊዜ ያህል ወደ ፓትርያርኩ የሄበደት ምክንያት እኩይ ዓላማውንና እቅዱን ከቻሉ እንዲደግፉለት ፣ ካልሆነ ግን ቢያንስ አርፈው እዲቀመጡ ለማስድረግ መሆኑን ለመረዳት የሚያስቸግር ይመስል “ብቸኝነት ይሰማቸው ይሆናል በሚል ስድስት ጊዜ ወደ ቢሮቸው ሄጃለሁ” በሚል መጀመሪያም ለርካሽ የፖለቲካ ተውኔት የተዘጋጀውን መድረክ ይበልጥ አርክሶታል።

 

·         የፖለቲካ ወላጆቹን፣ አሳዳጊዎችንና አሰልጣኞችን (የህወሃት ኤሊቶችን) የበላይነት በተሃድሶ ለውጥ ስም ከቤተ መንግሥት መንበረ ሥልጣን አስወግዶ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ስሪቱን ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ብልግና፣ ሴራ፣ ሸፍጥ እና የጭካኔ ሰይፍ ያስኬደበትንና እያስኬደ ያለበትን ግዙፍና መሪር ሃቅ የተትረፈረፈ ነፃነትን ከማስተዳደር (ማኔጅ ከማድረግ) ከባድነት ጋር በማያያዝ ከደሙ ንፁህ እንደሆነ ሲነግራቸው (ደንቆሮዎች እንደሆኑ ሲሳለቅባቸው) ፀጥና ረጭ ብለው የሚያዳምጡ አዳራሽ ሙሉ የሃይማኖት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማእረግ አባላትን እየመረረንም ቢሆን እንድንታዘብ አድርጎናል።

 

·         የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን ህንፃን በነፃና በእርሱ ችሮት የመለሰላት ይመስል ህንፃ መለስንላችሁ፤ እኛ እኮ አድልኦ አናውቅም ፤ የትኛው መንግሥት ነው …? ” ሲል ተሳልቆባቸዋል።

 

·         “የሰጠናችሁን ቦታዎች አቆሽሻችኋልና ቆሻሻን መፀየፍ አለባችሁ” ሲል አስተማሪ ተማሪዎችን ሊመክርበት (ሊተችበትና ሊያርምበት) ከሚገባው በታች በወረደ  አቀራረብ ሲወርፋቸው ( ሲያጎሳቁላቸው) ማየትና መስማት በእጅጉ ያሸማቅቃል። የታዘበው የቦታ አያያዝ ችግር ቢኖር እንኳ ሲሆን ለቤተ/ክህነቱ ጽ/ቤት ካልሆነም እንደ ማሳሰቢያ ሥነ ሥርዓት ባለው ሁኔታ መግለፅ ሲቻል በመሪዎች በኩል ቤተ ክርስቲያኗንና ተከታዮቿን ዝቅ ያደረገ መስሎት የለመደበትን የሸፍጠኝነትና የብልግና አንደበቱን ሲከፍት መታዝብ እውነተኛውንና ትክክለኛውን የኢትዮጵያዊ ጨዋነት ከልብ ለሚያውቅ የአገሬ ሰው በእጅጉ ይረብሻል።

 

·         ስድስተኛ ዓመቱን ሊደፍን ቀናት ብቻ በቀሩት የመከራና የውርደት አገዛዙ ምክንያት ለንፁሃን ዜጎቿ ምድረ ሲኦል ስለ አደረጋት አገር በችግሩ ልክ ደፍረው ባይናገሩም አሳምረው የሚያውቁትን ተሰብሳቢዎች  “ጥቃቅን ክስተቶችን እየተከተላችሁ ትልቅ ችግር እንዳለ ማጋነኑ ይቅርባችሁ፤ አይጠቅማችሁም/አይጠቅመንም” በሚል በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በመከረኛው ህዝብ ላይ ሲሳለቅ መታዘብ ትእግሥትን በእጅጉ ይፈታተናል።

 

·         አገርና ህዝብ ከሚገኙበት ለመግለፅ የሚያስቸግር ሁለንተናዊ ውድቀት (ቀውስ) አንፃር እጅግ ግዙፍ፣ አንገብጋቢና ጥልቅ የሃሳብ ልውውጥና ፍጭት ሊነሱበት ይገባ የነበረውን መድረክ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ 326 መግለጫዎች አወጣችሁብኝ በሚል በለመደው የብልግና (ያልተገራ) እና አደገኛ በሆነ አንደበቱ ሲዘላብድ መታዘብ የሚነግረን መሪር እውነት ይህ ትውልድ በትእግሥትና በሌለ ሰላም ስም ከመከራና ከውርደት ጋር እየተለማመደ ከመኖር (መኖር ከተባለ)  ክፉ አባዜ ለመላቀቅ የተሳነው መሆኑን ነው።

 

·         የሃይማኖት መሪዎችን እየጠሩ የማስጠንቀቂያ ሥልጠና በመስጠትና ከካድሬዎች በተሻለ አቀራረብና ይዘት እንዲያስተላልፉ (እንዲያስጠነቅቁ) በማድረግ እና በየሰፈሩ የሽብር ፕሮፓጋንዳ በማካሄድ ተከበሩ የተባሉትን የመስቀልና የጥምቀት በዓላት “በተትረፈረፈ ሰላምና ፍስሃ ያስከብርኩላችሁ ድንቅ መሪ እኔ ነኝ” የሚል አይነት የግብዝነት ዲስኩር ሲደሰኩርባቸው መታዘብ ለኦርቶዶክስ ብቻ ሳይሆን ጤናማና ሚዛናዊ ህሊና ላለው ለየትኛውም ሃይማኖት አማኝ የአገሬ ሰው ምነው ይህን ያህል ቁልቁል መውረዳችን? ያሰኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እያደባ በመስፋፋት ላይ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል (Creeping Genocide) - በዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ

 

·         የአገር መከላከያና የፅታ ሃይሎች ተብየዎች በቤተ ክርስቲያንና በተከታዮቿ ላይ  ለዓመታት የመከራና የጥፋት ዶፍ ሲያወርዱ እንደ ህግና ሥርዓት አስፈፃሚ የመንግሥት አካል መሪነቱ ምን እንዳደረገና ምን እያደረገ እንደሆነ ሲጠየቅ ጠያቂው ሊቀ ጳጳስ በማሳያነት የጠቀሷቸው አካባቢዎች ሃገረ ስብከት ሃላፊ በመሆናቸው ብቻ “ገዳዮችና ተገዳዮች ለእርስዎ ነው የሚቀርቡዎት” የማለቱን ልክ የሌለው የብልግና እና  የትዕቢት ድፍረት ከምር ለታዘበ ባለ ጤናማ ህሊና ሰው የሚሰማውን መሪር ስሜት ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም።

 

·         “ከአገር ቤት አልፎ በአረብ አገር ቦታ እንዲሰጣችሁ አድርጌያለሁና በቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ ላይ ስለደረሰው መከራና ጥፋት አትጠይቁኝ” አይነት ምላሽ ሲሰጥ ህሊናው የማያስጨንቀው ሰው መሪ ከሆነባት አገር የተሻለ ነገንና ከነገ ወዲያን መጠበቅ ራስን ከማታለል አያልፍም።

 

·         የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማዕረግ አባላትን ሰብስቦ ሥልጣነ መንበሩን ለመንጠቅ ወደ ላይ የሚንጠራሩትን (መሰላሉን የሚረግጡትን) ነቅተው ይከላከሉለት ዘንድ በእንስሳት ምሳሌነት ሲነግራቸው በአድናቆት ፈዘው ሲያደምጡት ከምር ለታዘበ ባለ ሚዛናዊ ህሊና ሰው ምነው ምኑ ነካን የሚል ከባድ ቁጭት ሳይፈጥርበት የሚቀር አይመስለኘም።

 

·         ከእስልምና ሃይማኖት መሪዎችና ባለ ሌላ ማዕረግ አባላት ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ የተቸረው ውደሳና ምርቃት ደግሞ ምነው እነዚህ ናቸው እንዴ “እስላም ማለት ሰላም ማለት ነው” የሚለውን ድንቅ ትርጎሜ የሚሰብኩን? የሚል ፈታኝ ጥያቄ ያስነሳል። ስድስት ዓመታት ሊሞላው ቀናት ብቻ በቀሩት የአገዛዝ እድሜው በንፁሃን ዜጎች ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የመከራና የውርደት ዶፍ ያወረደውንና እያወረደ ያለውን የአገር መሪ ተብየ ያለምንም ይሉኝታ የእግዚአብሔርን (የአላህን) ስም  እየጠሩ የአድናቆት፣ የምሥጋና እና የምርቃት ቃላትን የማዥጎድጎዱ አሳዛኝ እውነታ (tragic reality) የሚነግረን ውድቀታችን የአንድና የሁለት የሃይማኖት ተቋማት ሳይሆን የሁሉም መሆኑን ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም።

እኩያን የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ፈጣሪዎችና ቁማርተኞች ደግሞ ይህንን ዘመን ጠገብ የሆነ የአስከፊ ውድቀት ልማዳችንን አሳምረው ስለሚያውቁ አሳምረው ተጫውተውብናል፤ አሁንም ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ይጫወቱብናል ።

መቸም የአገራችን የሃይማኖት ተቋማት በንፁሃን መከራና ደም ለሚነግዱ ነጋዴዎች ሰለባነት ራሳቸውን አሳልፈው በሰጡና እየሰጡ በቀጠሉ “መሪዎቻቸው” ምክንያት ምን ያህል አሳፋሪ  ሁኔታ ላይ እንደ ወደቁ ስድስት ዓመታት እየሆነው ካለው የአብይ አህመድና አገዛዝ ግዙፍና መሪር ሃቅ  በላይ የተሻለ ማስረጃ አይገኝም።

የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ሊቃውንትና ሰባኪዎች ይህንን ግዙፍና መሪር እውነታ ከትናንት ዛሬ ከምር ተረድተውና እጥፍ ድርብ የሆነውን (የመንፈሳዊና የመልካም ዜግነት) ሃላፊነትና ተግባር ተወጥተው እኩያን ገዥ ቡድኖች ምድረ ሲኦል ያደረጓትን አገር ለመታደግ መስዋዕትነት መክፈል ቢሳናቸው እንኳ ፖለቲካ ወለድ የሆነውን መከራና ውርደት በሚመጥን አቋምና ቁመና ለመገዳደር ይሞክሩ ይሆናል ብሎ የጠበቀው ወገኔ ቁጥር ቀላል የነበረ አይመስለኝም።

ከሰሞኑ ያየነውና የታዘብነው ግን የዚህን ተቃራኒ ነው። ይህ ደግሞ የሚነግረን (የሚያሳየን) ዘመን ጠገብና አስከፊ ከሆነው አጠቃላይ ማለትም ከፖለቲካዊ፣ከኢኮኖሚያዊ፣ ከማህበራዊ፣ ከሞራላዊ፣ ከሥነ ልቦናዊ፣ ከሥነ ምግባራዊና ከመንፈሳዊ የቀውስ (የውድቀት) አዙሪት ሰብረን ለመውጣት የሚጠብቀን ፈተና በእጅጉ ከባድ መሆኑን ነው።

 

ታዲያ ከዚህ ክፉ አዙሪት ለመውጣት አማኝነታችን፣ ፆማችን ፣ ፀሎታችን፣ እግዚኦታችን ወይም ሞህላችን ፣ ስብከታችን፣ ስግደታችን፣ ነቢይነታችን፣ የሃይማኖት አባትነታችን (መሪነታችን)፣ ወዘተ ወደ ተግባር ሊተረጎም የሚችል እና በነፃነት ጥረንና ግረን እንኖር ዘንድ ፈጣሪ በአምሳሉ እንደፈጠረን ሰብአዊ ፍጡርነታችን የሚስማማንን ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ከምር ማረጋገጥ ይኖርብናል።

 

 

 

4 Comments

  1. ችግሩ ማንን እንመን ነው። የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል እንዲሉ እልፎች ለህዝብ ልዕልና ብለው የተሰውለት የሃበሻው የዲሞክራሲ መንገድ አንዴ በመለዪ ለባሽ ሌላ ጊዜ በብሄር ሰካራሞች እየተበረዘና እየተደለዘ ዛሬ ላለንበት የኦሮሞ ፓለቲካ ደርሰናል። በየጊዜው የመጣውን መንግስት ማወደስ የሃበሻ ፈሊጥ ነው። ነጠላና ጋቢውን ከመንገድ ላይ አንጥፎ እንዳለመነ ንጉሱን ወታደራዊ ሃይሉ አምዘግዝጎ ሲጥላቸው ወረተኛው ሃበሻ ሌባ ሌባ እያለ ነበር የሰደባቸው። የመንግስቱን እጅ ለመጨበጥ በመስቀል አደባባይ ሰውን የተረማመድት እነዚያ ወጣቶች ዞረው ተመልሰው በዚህና በዚያ ጎዳና ተሰልፈው ሃገር ካስፈረሱትና ወገንን ካስጨረሱት ሃይሎች መሃል አንድ ጎን ናቸው። በኢትዮጵያ ፓለቲካ ቀልቀሎና ስልቻ፤ ጆኒያና አቆማዳ ስማቸው ይለያይ እንጂ አገልግሎታቸው አንድ እንደሆነ ሁሉ ፓለቲካውም ስም እየቀየረ በየዘመናቱ ብቅ ይበል እንጂ ለህዝባችንና ለምድሪቱ አንድም ትሩፋት አላስገኙም። የስም ለውጥ የይዘትን ለውጥ አያስገኝምና!
    ሃይማኖት የሰው መጨቆያ፤ የባለ ጊዜ መጠቀሚያ እንደሆነ ምንም የሚያከራክር ነገር አይደለም። ለሰማይ ቤት አድረናል የሚሉ ናቸው ትላንትም ዛሬም ትራምፕን ከሰማይ እንደወረደ አስመስለው ያላሰለሰ ድጋፍ የሚያድርጉለት። ግለሰቡ ግን ጥቁር ጠል፤ ገብረ ቢስና በጭራሽ የሚናገረውና የሚኖረው ኑሮ የማይገናኝ ነው። አሁን ይመርጡታል። አተራምሶና ሃገሪቱን መሳቂያ አድርጎ ያከትምለታል። የሃበሻ መሪዎችም የእምነት ሰዎችን ለራሳቸው መሳሪያ እንዳደረጓቸው ከወያኔ የበለጠ ማሳያ የለም። ግን ጳጳሱና ጠ/ሚ መለስ በቀናት ልዪነት ነው ይህችን ዓለም የተሰናበቱት። ሰው ጅል ነው እኖራለሁ እንጂ እሞታለሁን አያስብም። ሁሌ በለው፤ ሁሌ ጥለፈው፤ ሁሌ ማታለልና አፈናና ግድያ ነው።
    አሁን ባለው የሃበሻ ፓለቲካ ያልሰከረ የለም። ሁሉም ለዘሩ ያለቃቅሳል። ሰው መሆን ግን ተረስቷል። የሃበሻ ክፋት ወንዝ ተሻጋሪ ነው። የማይለቅ ክፉ በሽታ። የትግራይ አክቲቪስቶች እውቋ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊን ሥራዋን እንድትለቅ ያደረጉት እነዚህ እኛን ካልመሰልሽ የሚሉ የዘር ሾተላዪች ናቸው። ሰው በራሱ አስቦ በራሱ ለመኖር የማይቻልበት ዓለም ውስጥ እንገኛለን። ውሸቱ እውነት፤ እውነቱ ውሸት የሆነበት ዝንቅ ዓለም! ለእነዚህ የዘር ቱልቱላዎች Political Tribes: Group Instinct and the Fate of Nations – Amy Chua እንዲያነቡ እጋብዛቸዋለሁ። ለነገሩ በራሱ የፈጠራ ታሪክና በጅምላ ፓለቲካ የተለጠጠ ጭንቅላት የሌላን ሃስብ መቀበል ይችል ይሆን? አላውቅም! በቅርቡ ከእስር የተፈታው ኮ/ሌ ቢንያም ተወልደ እንዲህ ሲል አደመጥኩት፤ እኔን እንድታሰር ከፍተኛ ድርሻ የነበረው አሁን የሃገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የሆነው ዶ/ር አብርሃም በላይ ነው ይልና በመቀጠልም ዶ/ር አብይ ኢንሳ ውስጥ ተላላኪ ነው የነበረው ይለናል። ዛሬም ብቀላና ስድብን ዛሬም ድንፋታን አይተውም። እድሜ ለአብይ መንግስት ከገባበት ጉድጓድ አውጥቶ ወደ አሜሪካ ያሻገረው የወያኔ የነፍስ አባት አቶ ስብሃት ነጋ አሜሪካ ላይ ሆኖ ዛሬም ፓለቲካው ውስጥ ሲዘባርቅ መስማት ያማል። ግን ለዚህ አይደል ከዘመናት በፊት ” ሃገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የተባለው። ደም አፍሳሽና ሴረኞች እየተፈቱ ንጽሃንን ወደ ዘብጥያ ማውረድ ሃበሻው የተካነበት ጉዳይ ነው።
    በመደምደሚያው የዚህ የፓለቲካ የመገዳደልና የመጠላለፍ አዙሪት የሚለቅን አስተሳሰባችን ሲቀየር ብቻ ነው። እውቋ ኢትዮጵያዊት ፕ/ር ሃረገወይን አሰፋ እንዳሉት ” በሰው ደረጃ ነው ማሰብ ያለብን” ሌላው ሁሉ የእንዘጥ እንዘጥ ፓለቲካ አሻሮና አድሮ ጠፊ ነው። ሰው መርጦ አይወለድም። የዘርና የቋንቋው መሸራከት እስካልቆመ ድረስ በሰውኛ ማሰብ በጭራሽ አይቻልም። ኦነግ አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ ህዝቤ አለቀብኝ ይላል። ሌሎች ሲሞቱና ሲፈናቀሉ ግን ጭራሽ ድምጽን አያሰማም። የሙት ፓለቲካ! ሃገር እያፈረሱና እያስፈረሱ ለህዝብ ነው የሚባል የገበጣ ጫዋታ። ዛሬም ትላንትም የጠበንጃ አምላኪዎች ጋጋታ … ትርፍ የለሽ መጠፋፋት። ማብቂያ ይኖረዋል? አላውቅም። እኔን ሁሌ የሚያበግነኝ ነገር በስልት የሚዘረገፈውን ገፈታ ወሬ ሁሉ እውነት እንደሆነ አርገው የሚሰለቅጡና እንቅልፍ ለራሳቸው አጥተው ሌላውን እንቅልፍ የሚነሱ ቱልቱላዎች ናቸው። በዚህም በዚያም ከሚረጨው ወሬ 10% እንኳን እውነትነት የለውም። ሞተ ያሉት ሲኖር፤ ጠፋ ያሉት ሲገኝ፤ ተረታ ያሉት ሲረታ፤ የድብልቅ ወሬ ፍሬፈርሲኪ! Trust Me, I’m Lying: Confessions of a Media Manipulator ተመልከቱ። በእኛ ላይ ነው የሚጫወቱት። መንቃት፤ እንደ ሰውኛ ማሰብ ለራስም ለሃገርም ለወገንም ይጠቅማል። የዘር ፓለቲካ እያለ ኢትዮጵያ ከችግር አትወጣም።

  2. ወንድም ተስፋ፦
    የዚህ የፓለቲካ የመገዳደልና የመጠላለፍ አዙሪት የሚለቅን አስተሳሰባችን ሲቀየር ብቻ ነው። ” ብለህ የተቸገርህ መሆኑን ገልጸሀል። የፖለቲካ ችግራችን የሚወገደው ፖለቲከኞችን መቆጣጠር ስንችል ብቻ ነው። የማንቆጣጠረው ፖለቲከኛ ሲሻው በጎሣ፣ ሲሻው በመንደር፣ ሲሻው በሃይማኖት፣ ሲሻው በቂም በቀል ማተራመስ ይችላል። ማገጃ ስላላበጀንለት፣ ማን ያግደዋል። በአሜሪካና በአውሮጳ ፖለቲከኞች ማገጃ አላቸው። ለምሣሌ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊዝ ትራስና ቦሪስ ጆንሰን ከሥልጣን በተከታታይ የተባረሩት በጠመንጃ አልነበረም። በአሜሪካ ፕሬዚደንት ሪቻርድ ኒክሰን ከሥልጣን የወረዱት በተኩስ አልነበረም። በሕገ መንግሥታቸው ቀይ መስመር ያለፈ መሪ ከሥልጣን እንደሚባረር ተደንግጓል። በኢትዮጵያ “ቀይ መስመር” የሚባል ነገር የለም። በአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲ የሕግ ዶክቶሬት ባለው አስተማሪ በተዘጋጀው ሕገ መንግሥታችን መሪ አይተችም፣ አይከሰስም፣ አይወቀስም፣ ለፍርድ አይቀርብም፣ ከሥልጣንም አይወርድም። የደርግም ሆነ የዛሬው ሕገ መንግሥት ከአራዊት የጡንቻ አስተደዳደር የተለየ አይደለም። አራዊት ልዩነታቸውን የሚያስከብሩት በጡንቻ ነው። ካለፈው ተምረን የወደፊት አስተዳደር ማሻሻል የሚባል አልፈጠረብንም። እንደ አገር፣ ከፈረጆች የምናንሰው በዚህ ነው።

    ደርግ ለፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የሚመቸውን ሕገ መንግሥት አረቀቀና ከሕዝብ ተነጥሎ ሲንገታገት ቆይቶ ተባረረ፣ መለስና ሌንጮም እንደ መንግሥቱ ኃይለማርያም ለረግጦ አገዛዝ የሚመቻቸውን ሕገ መንግሥት አርቅቀው አጸደቁና ሲያተራምሱን ይኸው 30 ዓመት አለፈ። ውጤቱ ዘላለም ማልቀስና ማስለቀስ ነው። ለዚህም ነው ፈረንጆችም የሚንቁን። ካለፈው መማርና ማሰብ እንደማይችለው እንስሳ ይቆጥሩናል። እንደዚያ ቢያስቡም አይፈረድባቸውም።

    መፍትሔው ያልተገራ ፈረስ እንደማይበጅ ሁሉ፣ በሕግ የማይገራ መሪም ዘላለም ሲያምሰን፣ ሲያዋጋን፣ ሲያሳድደንና ሲገድለን ይኖራል። መከላከያን፣ ፖሊስንና ደህንነትን ያለገደብ የሚያዝዝ መሪ፣ ለዜጋ መብት አክብሮት አይኖረውም። ይህ ዓይነት መሪ ዘውድ ባይጭንም ንጉሥ ነው። ታዲያ መፍትሔው የዚህን ንጉሥ ሥልጣን ወደ ባለቤቱ ወደ ሕዝቡ መመለስ ነው። በዚህ አምድ ላይ እንደሚታየው፣ ማልቀሱ፣ መተራረቡ፣ መሰዳደቡ፣ የውድቀት ታሪክ መተረኩም አያዋጣም። ተሰባሰቡና፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚበጅ የፓርቲ አመሠራረት፣ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት፣ ዲሞክራሲያዊ የምርጫ ሥር ዓት፣ ዲሞክራሲያዊ የመንግሥት አደረጃጀት፣ ወዘተ… እንዴት ሊሆኑ እንደሚገባ ረቂቅ ሰነድ አዘጋጁና ለውይይት አቅርቡ። ያለው ሕገ መንግሥት ምን እንደሚጎድለውም አስቀድመን እንወያይበት። አሜሪካና አውሮጳ ብዙ የተለያየና በያገሩ እርስ በእርስ የሚናከስ ዘር ይዘውም እንደ እኛ አይጋደሉም። ለምን አይጋደሉም ? ማልቀሱ ይብቃና በቁም ነገር ላይ እንወያይ ! የብዙ ምሁር አገር የመገንባት አቅም በከንቱ ለቅሶ እየባከነ ነው ! እንማማር፣ እንደግ !

  3. ማንም ማንንም ፓለቲከኛ መቆጣጠር አይችልም። ይህ በህልም ዓለም የመኖር አባዜ ነው ሰውን እያገዳደለ ያለው? አሁን በምድሪቱ ላይ በየቀኑ የሚፈጸመውን በደልና ክፋት ያመጣው ፓለቲካና ፓለቲከኞችን እንቆጣጠራለን አርፎ ተርፎም የራሱን ባህሪ የማይቆጣጠር የወታደር መንጋ ሳንጃ ባፈሙዝ በማለት ተፈጥሮን እቆጣጠራለሁ ብሎ ካፋከረ በህዋላ የተከሰተ ገመና ነው። እውቁ ጸሃፊ አቤ ጉበኛ ” ፓለቲካና ፓለቲከኞች” በተሰኘው ድራማ ነክ መጽሃፉ ላይ እንዲህ ይለናል። ” ውሃን ማን ያናግረዋል ቢሉ ድንጋይ” እንዲሉ እንዲሁ አንድ የሌላውን ሃሳብ ሳይረዳ እድሜ ልክ እየተራረድ መኖር ጀግንነት አይደለም። ወያኔ ድጋሜ ውጊያ በአማራ ህዝብ ላይ ከፍቷል። ኦሮሞው ነጻ አወጣሃለሁ የሚለውን ህዝብ በመጨረስና በማስጨረስ ላይ ይገኛል። አማራው በፋኖ ፍትጊያ እንደ ገና ዳቦ በሁለት እሳት መካከል ሆኖ በመቀቀል ላይ ይገኛል። ነጻነቱ የቱ ላይ ነው? ያኔም ረሃብ፤ ዛሬም ለቅሶ፤ ሞትና እልቂት ያልተለየው ህዝባችን እፎይ የሚለው መቼ ነው?
    የእኔ እና አንተ ይህ ይሻላል ያ አይበጅም እያሉ መሟገቱ ቡዙም ፋይዳ የለውም። ሰው አውሬ ሆኗል፡፤ ሰው በቁሙ እንደ ሰንጋ በሬ የሚበለትበት ምድር ላይ ፍትህ ርትዕ ይኖራል ብሎ ማላዘን ራስን ማሞኘት ነው። አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ታጣቂ ሃይሎች ህዝብን የሚያስጨንቁበት፤ ሴቶች ያለምንም ርህራሄ የሚደፈሩት፤ የትምህርት ተቋሞች የሚጋዪበት፤ የህክምና መስጫ ጣቢያዎች የተዘረፉበት፤ አርሰው የሚያበሉ ገበሬዎች በጅምላ የሚገደሉበትና የሚታገቱበት ምድር ናት። ሰው ድረሱልኝ ተጠቃሁ ሲል ብሄርህ ከየት ነው፤ ቋንቋህ ምንድነው ተብሎ የሚጠየቅበት ሃገር አድርገዋታል። ስብዕና ተሟጧል። እኔ አንተ የምታልማት ኢትዮጵያ አትታየኝም። እሳት በልቷት ጭስ የሚጨስባት እንጂ። በብልጽግና ስም ድህነትን ያሰፈነው የጠ/ሚ አብይ መንግስት ብዙም አይቆይም። ግን የብልጽግናው መንግስት መፈንገልም ሆነ በፈቃድ ከስልጣን መውረድ በአፓርታይድ ክልል ለተዋቀረችው ኢትዮጵያ ለውጥ አያመጣም። ይህ ጊዜ የሚነገረን ይሆናል። ሰው ደም ተቃብቷል፤ በዘርና በጉሳ ተሸንሽኗል፡ በፈጠራ ታሪክ ጭንቅላቱ ተሞልቷል። የኢትዮጵያ ሁኔታ ለእኔ ” ኦሮማይ” ነው። አንተ የምታምነውን እመን፤ እኔን ግን ለቀቅ አርገኝ!

  4. እንደ ስምህ ቁም እንጂ፣ ባጭሩ አትረታ ! የኢትዮጵያን ያለፉት 600 ዓመታት ታሪክ ብታስታውስ እንኳ፣ አገራችን በተደጋጋሚ ወድቃ ተነስታለች ። ዛሬም ከብዙ ጠባቦችና ራስ ወዳዶች ጋር ብዙ ጀግና ልጆችም አሏት ! ሲጨንቅህማ ለቀቅ የለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share