በላይነህ አባተ ([email protected])
የዚህ ዓመት አዳዲስና ወረተኛ የአድዋ በዓል አክባሪ ገጸ ባህሪያት የአድዋ በዓል እንዳይከበር ወይም ሥለ አደዋ እንዳይዘፈን ዘመቻ ከማድረግ ወደ “አድዋ በዓል የእኛ ነው!” ከመቅፅበት መሸጋገር በዶቃ ከሚጣሉ የአንድ ዓመት ልጆች ባህሪ ያነሰ ነው፡፡ እነዚህ አዳዲስ ገጸ-ባህሪያት “የአድዋ ድል ድላችሁ ነውና አብረን እናክብረው” ሲባሉ ” እምቢየው የጨቋኙ አማራ በዓል!” እያሉ ዛሬ እስከ ነጋች ድረስ “ጨቋኙ አማራን” ሲያቀነቅኑ ኖሩ፡፡ እነዚህ አቀንቃኞች ዛሬ በጫጉላ ጊዜአቸው ግን ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ይኸንን ለአስርተ- ዓመታት እንዳይከበር ሲታግሉት የነበረን ብሔራዊ በዓል እንደ ባንክ ዘርፈው ለመውሰድ ሲሽቀዳደሙ ማየት የሚገርም ነው፡፡ ይኸ ሲለምኑት እምቢ ያለ ሲለምን ይገኛል ዓይነት በራስ ያለመተማመን ቅብጥብጥ ባህሪ “እምቢኝ አረፋውን!” ያለችውን ከንቱ ሙሽራ የሚያስታውስ ነው፡፡
ድሮ ድሮ ገና “አማራ ጨቋኙ! መዘፈን ከመጀመሩ በፊት ሁለት ከተለያዬ አገር ያሉ ቤተሰቦች ልጅህን ለልጄ ተባባሉ፡፡ በባህሉ፣ በደንቡና ሥርዓቱ መሰረት መጀመርያ እንደ አንቱ የተባሉ ሶስት ሽማግሌዎች ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ተላኩ፡፡ የተላኩት ሽማግሌዎችም ከተነጠፈላቸው ሻሽ የመሰለ አጎዛ ከውጪ ተቀምጠው ልጅቱን የምትታጭለትን ጎበዝ የአጥንት ጥራት፣ ቁምነገረኛነትና ጀግንነት አስረድተው እሽም እምቢም ሳይባሉ ሌላ ቀነ ቀጠሮ ይዘው ተመለሱ፡፡ በሁለተኛው ቀጠሮ ሲመለሱ ወደ ቤት እንዲገቡ ተጋበዙ፡፡ ወደ ቤት እንዲገቡ መደረጉ የእሽታ ዳር ዳር መሆኑ ነበር፡፡ ሽማግሌዎቹ የቤቱን ጣራ፣ ግድግዳና መከታ እንደዚሁም የቤት እመቤቲቱን እጥፍ ዘርጋ የሚል ወገብ፣ ኮራ ያለ ዳሌና አበጥ ያለ መቀመጫ በዓይናቸው ፎቶ እያነሱ ትንሽ እንደቆዩ እንዲበሉ “እጃችሁን ታጠቡ!” ሲባሉ “እሺ ታልተባልን ምንም አንቀምስም!” አሉና ተተቀመጡበት ተነሱ፡፡ የልጅቷ ወላጆች፣ አክስትና አጎቶችም በመደዳ ተደርድረው “እሽ!” ብለው ሽማግሌዎችን እንዲቀመጡ አደረጉ፡፡ እሽታን ያገኙት ሽማግሌዎችም ተነስተው ከመደቡ የተደረደሩትን ሁሉ ጉልበት ስመው የታጨችዋን ልጃገረድ በቃል-ኪዳን ተረከቡ፡፡ ከዚያም “የባለሙያ ልጅ ናት!” እንዲባል እናቲቱ ለባላቸው እንኳ ሰርተውት የማያውቁትን የሚጥም ምግብ፣ ጠላና ጠጅ አቅርበው ሽማግሎችን አስደስተው ወደ አገራቸው መለሱ፡፡
ሽማግሌዎች እሽታን አግኝተው በተመለሱ በስድስት ወር ውስጥ ድል ባለ ድግስ ልጆቹ ተጋቡና ተጨጎሉ፡፡ ሙሽሪቱ መቀነቷን እስከምትፈታ ተመደብ ጉብ ብላ ፀሐይ ሳይነካት እየዋለች፣ ሙሽራውም እንደዚሁ ጠንካራ ሥራ ሳይሰጠው እንደ አራስ ምርጥ ምርጡን እየበሉ ለሁለት ወራት ያህል ተሞላቀቁ፡፡ በ“ኩርኩም፣ ፏደሬ፣ ገበጣና የመሳሰሉት የጫጉላ ጨዋታዎች ተዝናኑ፡፡ የሙሽራው ሚዜዎችና ፍቅራቸውን ለመግለጽ የፈለጉ ወዳጆችና ዘመድ አዝማዶች ዶሯቸውን እያረዱ፣ እንጎቻ እያነጎቱና ፍትፍታቸውን እየፈተፈቱ የሙሽራውንና የሙሽሪትን ህይወት ገነት አስመሰሉ፡፡ ሙሽራዋ በዚህ የጫጉላ ዘመኗ ሁሉም ሰው የእርሷ አገልጋይ ፣ በዓለም ያለ ነገር ሁሉ ለእርሷ፣ ዓለም እራሷ ለእርሷ ምስላ ታየቻት፡፡
ዳሩ ግን የጫጉላ ዘመኑ ዘላለማዊ ስላሆነ በሁለት ወር አለቀና ሙሽሮቹ ጎጆ ወደ መውጣት ተሸጋገሩ፡፡ የሙሽራው እናት ለስድስት ወር የሚያገለግል ድልህ፣ ጨው፣ ቅባኑግ፣ ቅቤ፣ ቅርንፉድ፣ ዘቃቅቤ፣ ዝንጅብል፣ ዱቄት፣ ሽሮ፣ ቋንጣና የመሳሰሉትን አዘጋጅተው፣ የሙሽራው አባትም ጥማድ በሬ፣ መሬትና የበሬ ዕቃ አዘጋጅተው መርቀው ጎጆ አወጧቸው፡፡ ሁሉ ነገር ተሟልቶ ቢሰጣቸውም ለሙሽሮች ይህ ሽግግር አንቀጥ ሆነባቸው፡፡ በተለይ አስተዳደግ ለበደላትና በራሷ እምነት ለሌላት ሙሺሪት የጎጆ ነገር ወህኒ ቤት መስሎ ታያት፡፡ ተመደብ ተኮፍሳ ኩል በሚኩሉ፣ ጣት የሚያስቆረጥም ምግብ በሚያዘጋጁ፣ “አፈር ስሆን” እያሉ በሚያጎርሱ ወይዛዝርት እየታጀበችና እየተንቀባረረች መዋሏ እንደታሪክ ወደ ኋላ ቀረና ምግብም ሆነ የወር ጨው (አስቤዛ) ማዘጋጀቱ ከከንዷ አረፈ፡፡ ሙሽራውም በእናትና በአባት ሐሳብ እየተንደላቀቁ መኖር አከተመና ያችን ሁለቱን ሸፍና የያዘችውን ጎጆ የማስተዳደር ቀንበር በጫንቃው ላይ ወደቀ፡፡ ያችን ጣራ ተከልለው፣ በራቸውን ገርብበው፣ በአንድ ሞሰብ በልተው፣ በአንድ ቅል ጠጥተው የሚኖሩ ሰዎች ሁለቱ ብቻ ሆኑና ቁጭ አሉ፡፡ በጫጉላ ዘመን የተዋወቁት ገላ-ለገላና ወዝ-ለወዝ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ብቻቸውን ሲኖሩ ግን አመል-ለአመል፣ ባህሪ- ለባህሪ መተዋወቅ መጣ፡፡ በተለይ የሥነ ልቡና ዝግጅት ያልተደረገበት የጎጆ ጣጣ እንኳን ተደብቆ የኖረን አዲስ አመልንም ያስወጣል፡፡ በመሆኑም እየዋሉ እያደሩ በሄዱ ቁጥር እነዚህ የትዳር ጓደኞች የተደበቁና አዳዲስ አመሎች ማውጣት ጀመሩ፡፡ ሶስት ጉልቻ ለማቆም የጀመሩበት ወራት በጨመረ ቁጥር ሙሽራይቱ የምታሳየው እንግዳ አመል እጅግ እየበረታና እጅ እግር የሌለው እየሆነ መጣ፡፡ ለምሳሌ እንተኛ ሲል እንቀመጥ፣ እንውጣ ሲል እንግባ፣ ቁጭ እንበል ሲል እንቁም፤ ብርሃን ሲል ጨለማ፤ ጥቁር ሲል ደግሞ ነጭ ትላለች፡፡ ወደ ሰሜን ሲያመለክት ወደ ደቡብ ትጠቁማለች፡፡ ደግ ነሽ ሲላት ክፉ ነኝ፣ ሰነፍ ነሽ ሲላት ጎበዝ ነኝ ትልና ድርቅ ትላለች፡፡ እንብላ ሲል እንጹም፤ እንዝፈን ሲል እናልቅስ ትልና ልቅሶዋን ትለቀዋለች፡፡ ሌላው ቀርቶ ቆንጆ ነሽ እያለ ሊያንቆለጳጵሳት ሲሞክርም በምሬት “እምቢዬው አስቀያሚ ነኝ” ትልና እውነት አስቀያሚ ለመምስል ከንፈሯን አዛንፋና አጨማዳ አሽሙረኛ መስላ ቁጭ ትላለች፡፡
የኑሮ ጎዳና እንኳን በተቃራኒ አቅጣጫ እየተራመዱበት እጅ ለእጅ ተያይዞ እየተጓዙበትም ቀጥ ያለ መስመር አይዝም፡፡ ይህም በመሆኑ የእነዚህ በተለያዬ አቅጣጫ መራመድ የጀመሩት ባልና ሚስት ኑሮ አንድ ስንዝርም ወደፊት ሊራመድ አልቻለም፡፡ ለጎጆ መውጫ የተሰጧቸው ሶስቱ ጉልቾች ተጋደሙ፡፡ እንኳን ቤቱ ምድጃውም እንደ ሬሳ ቤት ቀዘቀዘ፡፡ በዚህ የተጨነቀው ባል “በበሬው መልስ!” በሚል ብሂል ጎጆውን ከመፍረስ ለማዳን የመግባቢያ ቋንቋውን ቀይሮ በተቃራኒ የመናገር ስልት ፈጠረ፡፡ መሄድ ከፈለገ እንተኛ፣ መብላት ከፈለገ እንጹም፣ መቆም ከፈለገ እንቀመጥ፣ ምስራቅን ለማሳየት ከፈለገ ወደ ምእራብ እያመለከተ፣ ቆንጆነቷን ለመግለጽም አስቀያሚ የሚለውን ቃል እየተቀመ ኑሮን ትንሽ ወደ ፊት ፈቀቅ ለማድረግ ትልቅ ጥረት አደረገ፡፡ ዳሩ ግን አንድ በሬ ጠምዶ ማን አርሶ ያውቃል? አንድ ጉልቻ ጥዶስ ማን አብስሎ ያውቃል? በአንድ እንጨት ብቻስ ማን ጣራ ሰቅሎ ያውቃል?
በዚህ የኑሮ ኩርንችት ውስጥ ሳሉ የፍስለታ ግድፍት ደረሰ፡፡ እንደሚታወቀው የሚስት ወላጆች የፍስለታ ግድፍት እንቁጣጣሽ፣ መስቀል፣ ገናና ፋሲካ በመሳሰሉት የባእል ቀኖች ልጆቻቸውን ከነባሎቻቸው ደግሰው ይጠራሉ፡፡ በዚህ ደንብ መሰረትም እነዚህ አዲስ ጎጆ ወጪዎች የፍልሰታን ግድፍት ከሚስቲቱ ወላጆች ጋር አብረው ሊያሳልፉ መዘጋጀት ጀመሩ፡፡ አዲሱ አምቻ አማቶቹን በቅርበት የሚያየው ለመጀመርያ ጊዜ ስለነበር “የክት ልብስ” የሚላትን ዳርዳሯ በቀለማም ክር የተዋበችን ሙታንታውን በቀበቶ ጠስቆ፤ በዚያ ላይ ቦግ ቦግ ያለ ኪስ ያለውን ኮቱን ደርግሞ፤ ከኮቱ በላይ በእንዶድ እብድ እስቲል የታጠበውን ጋቢውን አጣፍቶ፤ ግራና ቀኝ የወረደውን የጋቢውን ክፍል ሰብስቦ በትክሻዎቹ ላይ ጉብ አደረገ፡፡ ጉብ ባለው የግራ ትከሳው የአባቱን አጪር ምኒሽር አነገተ፡፡ በቅኝ እጁ ደሞ በቅባት የወዛ ዱላውን ጨበጠ፡፡ ለባብሶ ሲጨርስም ወደ ደጅ ወጣ አለነና ጥላውን አይቶ ሸበላ ጎበዝ መኖኑን አረጋገጠ፡፡ ሚስቲቱ እንደዚሁ ወላጆቿን ለማየት ጓጉታ ጠጉሯን በሚዶ ነቃቅሳና አደስ በጎረሰ ቅቤ አውዝታ፤ ራሷን ዙሪያውን በባውንድ አስራ፤ በጥልፍ ያማረውን ቀሚሷን በተለያዩ ቀለማት በተሽቆጠቆጠ መቅነት ሸክፋ፤ ተቀሚሷ ላይም መቀነት መፍታቷን የሚናገረውን ነጠላዋን ጣል አደረገች፡፡ እንደ መርገፍ የረገፉትን የአይኗን ሽፋፍቶች ኩል አልሳና ፊቷን በአምባሬ ጪቃ አውዝታ የዛገችዋን ክብ መስታዎትዋን ከሙዳይዋ አውጥታ፤ ፈገግ-ቆጣ፣ አይኖቿን ክፍት-ክድን፣ አንገቷን መለስ-ቀለስ እያደረገች እንደ እመይቴ ውድነሽ በጣሙ ክብ ፊቷን ደጋግማ አይታ “ይቺ ናት አስናቀች አለሙ” አለች፡፡ መቀባባቱንና መኳኳሉን ስትጨርስም መቃ አንገቷን በትከሳዎቿ አሻግራ መጀመሪያ ወደ ቀኝ ተዚያም ወድ ግራ በመዞር የተጀነኑ ዳሌዎቿን ቃኘችና ጥላዋን በቀኝ እጇ ዘርግታ በልጃገረድ ፍጥነት ሳይሆን አሁን በተማረቸው የወይዘሮዎች አካሄድ እርምጃዋን እንደ ጣቃ እየሰፈረች ሳብ-ረገድ ሳብ-ረገድ እያለች በአልቦ በተዋቡ እግሮቿ ከባሏ ኋላ ጉዞዋን ቀጠለች።
ፍስለታ የሚውልበት ነሐሴ አባይ፣ አዋሽ፣ ባሮ፣ ገናሌ፤ ዋቢ ሸበሌ፣ መረብና ተከዜ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ወንዞችና ጅረቶች አፍር ጎርሰውና ጎልበተው በጀብደኝነት እየተጥመለመሉ የሚፈሱባቸው ወሮች መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ከሚስቲቱ ዘመዶች አገር የሚደረሰው በክረምት እንደ ዝሆን የሚግበሰበስና እንደ አንበሳ የሚያገሳ ወንዝን ተሻግሮ ነበር፡፡ ባልና ሚስት ተደግሶ የሚጠብቃቸውን ድግስ እያሰቡና ልክ አጠገባቸውን እንዳለ ሁሉ በአፍንጫቸው እያሸተቱና በምላሳቸው እያጣጣሙ እንደዚሁም ሲደርሱ በቀኝ የሚጣለውን ላታማ ሙክት በናላቸው እያወጡ-እያወረዱ ሲጓዙ ይህ ድልድይ-አልባ ወንዝ ከመጠን በላይ ጢም ብሎ እያጓራ ሜዳውን ሳይቀር አልብሶት አገኙት፡፡ ወንዙ ሞልቶ ቢፈስም አቶ ባል ኢትዮጵያን እንዳዋረደው አሳነባሪው ሄኖክ ሳይሆን ስንቱን ከማእበል ያዳነ፤ “ተዋኙ አይቀር እንደ ሰፈፈ በላይ!” የሚባል ቆፍጣና ዋናተኛ ነበር፡፡ እንዲያውም የሰፈሩ ልጃገረዶች የዚህን ዋናተኛ ሥምና ጉብዝና በዘፈን እያነሱ ፍቅራቸውን ስለሚገልጹ ይህቺ የግልንቢጥ ሚስቱ ትቀና ነበር፡፡
ይህ በወንዝ አሻጋሪነቱ አገር ያወቀው ቆፍጣና ባል ባለቤቱን “ተሸክሜ ላሻግርሽ” ሲላት የቤቱ ዓመልም ገበያ ወጣና “አሻፈረኝ ራሴ እሻገራለሁ!” አለች፡፡ አቶ ባልም “ራስሽ መሻገር ከፈለግሽም በመልካው ተሻገሪ!” አለና መልካውን ጠቆማት፡፡ ወይዘሮ ሚስት ግን “አሻፈረኝ በድንብልዙ እሻገራለሁ!” አለችና የቀሚሷን ግራና ቀኝ ጫፍ ወደ ላይ ስባ በመመቀነቷ አስገብታ አዙሮ በመድፋት በሚታወቀው ድንብልዝ እግሮቿን ከተተች፡፡ ትንሽ እንደተራመደች እንደፈረስ የሚጋልብ ማእበል ያን ሲቆነጃጅ ያረፈደውን ገላ አጠበና የቆመችዋን ወይዘሮ በሆዷ አስተኛት፡፡ አቶ ባል ሚስቱን ለማዳን በቅልጥፍና ዘሎ ገብቶ “እጄን ያዥኝ! እጄን ያዥኝ!!” እያለ ሲጮህ እርሷ ግን “እምቢኝ ውሃውን ነው! እምቢኝ ውሃውን ነው!” እያለች የማይጨበጥ ውሀ ለመጨበት ሞከረች፡፡ “እኔን መያዝ ካልፈለግሽ ጀጀባውን ያዥው! ጀጀባውን ያዥው” እያለ ሲጮህ እርሷ አሁንም “እምቢኝ አረፋውን ነው! እምቢኝ አረ..ፋውን ነው!!” እምቢኝ አረ..ፋ..ው…ን!!! እያለች የማይጨበጥ አረፋ ለመጨበጥ እየሞከረች ከወንዙ ጋር ሄዳ አረፈች፤ አቶ ባልም አረፈ፡፡
በአማራና “በጨቋኙ አማራ!” አቀንቃኞች መካከል ለግማሽ ክፍለ-ዘመን የተኪያሄደው የገመድ ጉተታ የእምቢኝ አረፋውን ጉተታ ነው፡፡ አማራ በሽማግሌ ምልጃና በጋብቻ፤ በመሳምም በመጎሸምም ኢትዮጵያ የምትባል ጎጆ ለመስራት ዓለም ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ትልቅ መሰዋእትነት ከፈለ፡፡ ድንበሯና ክብሯ እንዲጠበቅም ከፍተኛውን መስዋእትነት ሲከፍል ኖረ፡፡ ከፍተኛ መስዋእትነት ለመክፈሉ ልዩ ጥቅም ሳይጠይቅና “በባዶ እግሩ እሚሄድ!” እየተባለ “የኢትዮጵያን አንድነት እንጠብቅ!” ሲል የአማራ ጨቋኝ አቀንቃኞች “አሻፈረኝ ይህ የነፍጠኛና የትምክህተኛ ሐሳብ ነው!” አሉና በብሔር ብሔረሰቦች ለቦጫጨቅ ተማምለው ለሃምሳ ዓመታት ይህችን በቅድመ አያቶቻችን አጥንትና ደም የተገነባች ውብ አገር ብልት በማውጣት እንዳልሰለጠነ የቄራ አዲስ ቅጥር ሰራተኛ ሲዘነችሯትና ሲቦጫጭቋት ኖሩ፡፡
በቋንቋ ቢላዋ ቦጫጭቀው ቡጪቅጫቂውንም እሴት አልባ ለማድረግ ፊደል ተበደሩ፡፡ ይኸንን ያዩ ነፍጠኞችና ትምክተኞች “የሰው ወርቅ አያደምቅ የኢትዮጵያን ፊደል ተጠቀሙ!’ ሲሏቸው “እምቢኝ የአውሮጳውያንን ነው! እምቢኝ የላቲንን ነው!” እያሉ ደጋግመው ጮኹ፡፡ እንደ ፊደላችን ሁሉ ትልቅ እሴት የሆነውን “የአድዋ ድል አለም አቀፋዊ ድል ነውና አብረን እናክብረው ሲሏቸውም ” እምቢኝ! የአድዋ ድል የነፍጠኛች ድል ነው! ብለው ይኸንን የነፍጠኞችን ድል ማንም እንዳያከበርና ሥለነፍጠኞችም ማንም እንዳይዘፍን ለማድረግ በዘፈኑት ዘፋኞችም የኢኮኖሚ ማእቀብና አድማ ጠሩ፡፡
ይኸንን የአማራ ጨቋኝ አቀንቃኞች አልጋ ሲሉሽ መደብ፤ መደብ ሲሉሽ ወለል ባህሪ የተገነዘቡ ነፍጠኞችና ትምክህተኞች ኢትዮጵያ የምትባለውን ጎጇቸውን ከመፍረስ ለማዳንና የራሳቸውን ዘርም ከመጥፋት ለማዳን እንደ አስናቀች አለሙ ባለቤት አቶ ሰፈፈ በላይ መላ መምታትና በተቃራኒው ማሰብ ጀመሩ፡፡ በተቃራኒው ማሰብ የጀመሩት ነፍጠኞችና ትምክህተኞችም “እኛም እንደ እናንተ በብሔራችን ተደራጅተን ራሳችን እንከላከላለን” ሲሉ የአማራ ጨቋኝ አቀንቃኞች ህሊናቸውን እንደ ለገሰ ዜናዊ ሙሽልቅ አድርገው ፋቁና “እናንተ ዘረኞች፣ በዘር መደራጀታችሁን አቁሙ!” እያሉ የእምዬን ወደ አብዬ ዓይነት ጩኸት ሌት ተቀን አቀለጡ፡፡ ነፍጠኞቹና ትምክህተኞቹ በተጨማሪም “ለማጋራት ብለን እንጅ የአድዋ ድልም የእኛ ስለሆነ እኛው እናከብረዋለን!” ብለው ለብቻቸው በምድርም በኢንተርኔትም ማክበር ሲጀምሩ የአማራ ጨቋኙ አቀንቃኞች አሁንም “እምቢየው! የአደዋ ድልም የእኛ ነው!” ብለው ዓለም ጉድ እስቲል ጮኹ፡፡ “ባይሆን እጃችንን ያዙና አብረን ለመጀመርያ ጊዜ ተስፋፊ ቅኝ ገዥ ያንበረከኩትን አርበኞች እንዘክራቸው” ተብለው ሲለመኑ “እምቢኝ አረፋውን!” እያሉ ከጎርፉ ጋር መንጎድ ቀጠሉ፡፡
የእምቢኝ አረፋውን ባህሪ እስከ መቃብር ስለሚከተል የአማራ ጨቋኙ አቀንቃኞች በዚህ ዘመን የባሰውን በዝቅተኝነት መቀመቅ ውስጥ ዘቅጠው የአድዋን ድል ማክበርን ወንጀል አድርገውት አረፉ፡፡ የእምቢኝ አረፋውን ባህሪ ጀጀባውን ሲባሉ አረፋውን፣ ነፃነትም ሲባሉ ባርነትን አስመርጦ በጎርፍ አስጠርጎ የሚወስድ እርኩስ ባህሪ ነው፡፡ ከራስ ባህልና ሃይማኖት የሌላውን፣ ከራስ ፊደልና የግዜ ቀመር የቅኝ ገዥን፣ ከነፃነትም ባርነት፣ ከጀጀባም አረፋውን የመረጠ መጨረሻው የማያምር ነው፡፡
ተጻፈ የካቲት ሃያ ሶስት ቀን ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.