ዶ/ር በቀለ ገሠሠ
ከታላቁ አድዋ ድል ብዙ መማር ይኖርብናል
1ኛ/ የአመራር ብቃት፣
ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ ‘
ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ።
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።
የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው።
በነዚህ ታላላቅ አርበኞች አመራርና መስዋዕትነት ነበር ያንን እጅግ በጣም አኩሪ ድል የተጎናጸፍነው።
2ኛ/ የሃቅ አምላካችን ድጋፍ
ኢትዮጵያ ታበጽሕ ኢዴዊሃ ሃበ እግዚአብሔር ፣
ክቡር ሞቱ ለጻድቅ ቅድመ እግዚአብሔር ።
3ኛ/ የህብረት ኃይል
ፋኖ አርበኞቻችን በህብረት ተንቀሳቅሰው፣ በባዶ እግራቸው ከሺ ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ተዋግተው ነበር ታላቅ ድል ያጎናጸፉን። ዛሬ ግን ባንድ ላይ ቆመን መዘከር እንኳን እያቃተን ነው።
4ኛ/ የጣሊያ/አውሮፓ ሸፍጦች፣
የቤርሊን ኮንፌረንስ በመባል የሚታወቅ ስብስብ አደረጉ። ጥቁር ትል ነው፣ ቅንቡርስ ነው፣ ነፍስ ያለው ሰው አይደለም ብለው ተስማምተው አፍሪቃን ሊቀራመቱ ወሰኑ። ኢጣሊያ የውጫሌን ስምምነት አጭበርብራ በቅኝ ልትገዛን መጣች፣ አቸንፈን በውርደት ሰደድናት። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ክብር ከማስመዝገቡም በላይ ፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎና ድል ተምሣሊት ሆነ፡፡
40 ዓመታት ጠብቃ እንደገና በማይጨው መጣችብን። ምንም እንኳን ጀግኖች አባቶቻችንና አያቶቻችን ለአምስት ዓመታት በዘመናዊ መሣሪያና መርዝ ጪስ ቢጠቁም በመጨረሻ አቸንፈው ነፃነታችንን አስጠበቁልን።
5ኛ/ ከነዚህ የነፃነት ድሎች ምን እንማራለን?
ህብረት ኃይል መሆኑን፣
ዛሬ በአማራውና ኦርቶዶክስ ተከታዮች ላይ የተቃጣው ጥቃት ቶሎ መቆም እንዳለበት፣ ፋኖ የተነሳሳው አትግደሉኝ፣ አታፈናቅሉኝ፣ በማለት ራሱንም ቤተሰቡን ለመከላከል እንጂ የማንንም ነገድ ወይ ሀይማኖት ለመጋፋት አለመሆኑን።
ስለዚህ ህብረት አጠንክረን ሰላም አውርደን ወደ እድገት ጎዳና ብንራመድ ይበጀናል።
ህብረት ከሌለን እንደገና ከውጪም ረዥም ቂም በያዙብንና የተፈጥሮ ሀብታችንን ሊቆጣጠሩ በሚመኙት ኃይሎች በቀላሉ ልንጠቃ እንደምንችል መገንዘብ ይኖርብናል።
እግዚአብሔር ቅን ልቦና ሰጥቶን ይታረቀን።