ጠ/ሚ አብይ ውስጥ ያፈጠጠው አምላክ

ጠ/ሚሩ ምን አይነት መሪ ናቸው ብለን እራሳችንን ብንጠይቅ መልሱን ለማግኘት ነፍስያችንን ማዳመጥ አያስፈልገንም፣ ምክነያቱም ግራ የሚያጋቡ መሪ አይደሉምና፡፡ ጠ/ሚሩ ወደ ስልጣን ለመምጣት አቅደውና ብዙ ለፍተው ነው አዚያ የደረሱት፡፡ ይህን ደግሞ በጻፉት እርካብና መንበር መጽሐፋቸውና እናቴ ከሰባት አመቴ ጀምሮ ነግራኛለች በሚሉት ነገራቸው ደጋግመው የገለጹት ነገር ነው፡፡

ጠ/ሚሩ ወድ ስልጣን በመጡበት ግዜ በሃይማኖት ረገድ ሊጫወቱ የፈለጉትን ሚና ገጽታ ግንባታ ያከናወኑት እራሳቸውን የኦርቶዶክስ፣ ሞስሊሙና ፕሮቴሰታንት እምነቶች የበላይ ጠባቂ (Patron) በማድረግ ነው፡፡

በስልጣን ማኮብኮቢያው ግዜያቸው አሜሪካ መጥተው በወያኔ ግዜ ከተለያዩ የኦርቶዶክስ ሲኖዶሶች በውጭ የነበረውን እሳቸው በተሳፈሩበት አውሮፐላን ጭነው ወደ ሃገር ቤት በማስገባት አስታረቁ ተባለ፡፡ በዚያው በአሜሪካ ቆይታቸው አሜሪካን ከሚኖሩ ሞስሊሞች ጋር ባደረጉት ስብሰባ የሱፊያ ሞስሊም ታላላቅ ሰዎችን ሰይድና (ጌታዬ) እከሌ ብለው እየጠሩ ከሞስሊሞች ጋር ህብረት እንዳላቸው ገለጹ፡፡ አዲስ አበባ ተመልሰው ሄደው ተለያይተው የነበሩ ፐሮቴስታነቶችን የህብረት ማእቀፍ ሰሩላቸው፡፡ ፕሮቴሰታንቶቹ በግልጽ የበላይ ጠባቂነታቸውን ስልጣን በመስጠት አረጋገጡላቸው፡፡

ከዚያማ ምኑ ቅጡ አሻጋሪው ሙሴ ተባሉ፡፡ በሞስሊሞቹም ዘንድ የሚፈልጉትን የመሃዲነት ስልጣን በያገኙትም በትልልቅ ሞስሊም ሸኮች አስቀድሞ የተነገረላቸው ንጉስ መሆናቸው በሰፊው ተተረከ፡፡

ከዚያም ጠ/ሚሩ ስልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ መስቀል አደባባይ ተብሎ የሚጠራውን ምንም እንኳ ይዞታነቱ የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ቢሆንም ለኦርቶዶክሱ፣ ሞስሊሙና ፕሮቴስታንቱ ሻሞ በማለት ሃይማኖት የግል ነው ሃገር የጋራ ነው ብሎ በዜግነት መስፈርት በሃገር ዙሪያ ሲሰባሰብ የነበረውን ህዝብ መልሰው በሃማኖታዊ ጎራ እንዲለያይ ለማድረግ እርመጃቸውን አንድ ብለው ጀመሩ፡፡

የሐይማኖቱን ነግር አሁን ላይ ሆነን ስንመለከተው በአውሮፕላን ከአሜሪካ ጭነው ያሰገቧቸውን ጳጳሳት መልሰው ከቦሌ አየር ማረፊያ እያባረሯቸው ይገኛል፡፡ ሲኖዶሱ ሶስት ቦታ  ተፈንክቶ ሌላ የሰላማና የጴጥሮስ መንበር የሚል ተፈጥሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ነዳለች፣ ምእመኖቿ ተገድለዋል፣ ተሰደዋል፡፡ እነ ሃጂ ሙፍቲ ከመጅሊሱ ተወግደዋል፣ ሞስሊሙ እርስ በእርሱ ተናጭቷል፡፡ የፕሮቴስታንቱ ነገርማ አይነገርም፣ እንደው ጉድ ብቻ ነው የሚያስብለው፡፡ የራሳቸው መፈራረስና መለያት ሳያንስ አልፈው ተርፈው ኦረቶዶክስ እንደምተበታተን ነብያቶች ነን ባዮቻቸው በአደባባይ ሲፎክሩ ይሰማል፡፡

ይህ ሁሉ ሰብሰቦ መበተን በአጋጣሚ የሆነ ወይም ነገሮች በራሳቸው ሂደት የፈጠሩት ምስቅልቅልዮሽ አይደለም፡፡ ሁን ተብሎ ታቅዶ፣ ለአመታት ተንሰላስሎ የሆነ ቡድን ቅደመ ተከተል አስቀምጦ፣ ከዚህ በኋላ ይህ ይደረጋል በሚል መርሀግብር ወጥቶለት የሚፈጸም ስራ ነው፡፡

ጠ/ሚሩ አስታራቂ ሆኖ በሐይማኖቶች ውስጥ ጥልቅ ሲሉ የነበረው፣ የየቤተ እምነቱን አመኔታ ለማግኘት ነበር፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያን አፍርሰን እንሰራታለን የሚለው ቡድን ያገኘውን አመኔታ ለሚፈልገው አላማ ተጠቅሞበታል፡፡ ያ ደግሞ ሰሜናዊውን ስልጣኔ ድራሽ አባቱን አጥፍቶና ደቡቡን ከፋፍሎ ህዝቦችን መሰልቀጥ ነው፡፡ፐሮጀክቱ እንዲሁ ዝም ብሎ የሚቆም አይደለም፡፡ አማራን፣ትግሬንና ኤርትራን እኒህን የስልጣን ተቀናቃኞች ከነታሪካቸው ሳይደመስስ እረፍት የለውም፡፡

ከመጀመሪያው ጀምሮ በሃይማኖቶችና ሰሜናዊ ህዝቦች ላይ የሚደረገውን ነገር ላስተዋለ ሰው የብልጽግና ኦሮሙማ “በአደናግረህ ወይም አሳምነህ” ግዛ የሚለው መርሁ ከዘ አርት ኦፍ ዲሲፕሽን(The Art of Deception) የተቀዳ ነው፡፡ በእስስታዊ አካሄዱ ከነባሪ ሁኔታዎች ጋር ተመሳስሎ ይቀርባል፣ሰዎች በሚያምኑበት ይምላል(ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፣ ጸልዩልኝ…)፣አንፀባራቂ ቃላትን ይጠቀማል( ብልጽግና፣ የፓርክ ስራው…) አውነታው ግን ሃገሪቱ አሁን ያለችበት ጦርነት፣ረሃብ፣መፈናቀል፣ የዜጎች ግድያና አፈና ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጀግናው እሸቴ ሞገስና ልጁ ይታገሱ እሸቴ በክብር ተሸኙ!

ጠ/ሚሩ በጻፉት እርካብና መንበር መጽሐፋቸው ላይ የሚነበበው ጠላትን እንደበሬ ሳር አሳይቶ ገደል መከተት ፍልስፍናቸውም ከዚሁ ዘ አርት ኦፍ ዲሲፕሽን የተቀዳ ዲኮይንግ(decoying) ፍልስፍና ነው፡፡ ጸሐፊ፣ ፈላሰፋና የጦርነት ንድፍ ተንታኝ ጀነራል ቻይናዊው ሱን ዙ(544 ዓ.ዓ. – 496 ዓ.ዓ.) የጦርነት ኪነ-ስልት(The Art of War) በሚለው መጽሐፉ ሰለ ዲሲፕሺን ብዙ ብሏል፡፡ በጦርነት መኃል ጠላትን እንዴት የተሳሳተ ግምት አሲዘህ እንደምታሸንፈው ያትታል፡፡ በአጠቃላይ ጦርነትን ለማሸነፍ እንዴት መምራት እንዳለብህ የሚናገር መጽሐፍ ነው፡፡

ጠ/ሚ አብይ አንድ ግዜ የብልጽግና ደጋፊ ወጣቶችን ሰብስበው በቆይታቸው ውጤታማ ስራ መስራተቸውን ነግረው እኔ ብሞት አይቆጨኝም ምክነያቱም ገነት ነው የምገባው ብለው  ነበር፡፡ ይህን አባበለቸውን በግልቡ ያየ ሰው እምነታቸውን ብቻ የገለጹ ሊመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ ለተሰብሳቢዎቹ አንደምታው እናንተም እኔ የማወርድላችሁን መመሪያ በማሰከበር ሂደት ላይ መስዋትነት ብተከፍሉ ገነት ትገባለችሁ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሲቪል ወጣቶችን ለእርሳቸው ሙጅሃዲን ጦረኛ ለማድረግ የተጠቀሙበት መንገድ ነው፡፡ እኔ ብነካ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያልቃሉ ብለውንስ አልነበር? ምናልባትም የሪፓብሊካን ጦሩ ኢንዶክተሪኔሽኑን ብንመረምር አብይን መጠበቅ እግዜርን እንደ መጠበቅ ነው የሚል ለሆሳስ ትምህር አይታጣበትም፡፡

የዋቅ ጉራቻ ጥቁር እጆች ከቫይኪንግ ዘውድ ጋር በፒኮክ ምስል ውስጥ ተመሳጥረው የተሳሉበትን የብልጽግና አርማን እንተወውና፣የኦርቶዶክስ ባእላት በመጡ ቁጥር ጠ/ሚሩ እራሳቸውን በክርስቶስ ትርክት ውስጥ እያዩ የሚያሰተላልፉትን መልእክትም እንለፈውና፣ ጠ/ሚ አብይ ውስጥ ያፈጠጠውን አምላክ የሚገልጹ ጥቂት አብነቶች እናንሳ፡፡

አንድ ግዜ ጠ/ሚሩ፣ ክርስቶስ ከሐዋሪያቶች ጋር በታንኴ ሲሄድ መአበል ወጀብ ተነሳና ታንኴይቷ ልትሰምጥ ስትል ተኝቶ የነበረውን ክርሰቶስን ጌታ ሆይ አረ ልንሰምጥ ነው ብለው ሐዋሪያት ቀሰቀሱት…አሉን፡፡ ጠ/ሚሩ ለዚህ ታሪክ አጃቢ አድርገው ያቀረቡት የሳቸው ታሪክ ደግሞ ሃገሪቷ ላይ ግድያ፣መፈናቀልና ጦርነት በሆነበት ሰዓት አንተ የት ሄድክ ተሉኛላቸሁ? አዛው ታንኴው ውስጥ ከእናንተ ጋር ነኝ የለሁት ነው የሚለው፡፡

የዚህ ትርክት ንፃሬው ግራ የሚገባ ነው፡፡ ተኝቻለሁና ቀስቅሱኝ ነው? ወይንስ ከእንቅልፌ ስነቃ ጠላቴ ወዮለት ነው? ውስጣቸው ያደፈጠው መንፈስ ግን  በመዝሙራት ላይ የተገለጸውን አምላክ ያሰታውሳል፡፡ “እግዚአብሔር ከእንቅልፉ እነደሚነቃ ተነሳ፣ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያል ሰው፣ ጠላቶቹን በኋላቸው መታ፣ የዘላለምን  ኀሳር ሰጣቸው፡፡” መዝ 77፣ 65-66

እሳቸው ይህን ከተናገሩ በኃላ ፣መቼም ነቅተው እንጂ ተኝተው አልተናገሩትምና፣  ኢትዮጵያ ውስጥ ወጀቡ ቆሞ፣ ፀጥ ረጭ ያለ ነገር አለ ወይ ብለን ብንጠይቅ መልሱ፣ ምንም ነው፡፡ ጦርነቱ፣መፈናቅሉ፣ ግድያውና አፈናው እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ በክርስቶስ ስም የሚመጣ ግን የሰላም አለቃ መሆን የማይችለው ማን ነው ብለን ከጠየቅን፣ መልሱ አንድ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ያም ሃሳዊ መሲህ ነው፡፡

አሁን በቅርብ ግዜ ሰው ሲሞት ገነት ለመግባት የሚፈልገው፣ ገነት የተዋበች ያትክልት ስፍራ በመሆኗ ነው ካሉን በኋላ፣ እንዴት እኔ በኢትዮጵያ ላይ እየሰራሁ ያለውትን ገነት ይቃወሙታል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ለመቶ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ አስር ፓርክና ሪሶርት ስርቶ እንዲህ መንፏለል ይገርማል፡፡ የሀገሪቱ ህዝብ ኩረማኑን ያህል እቦተው ላይ ብንወስደው ጠጠር መጣያ አጥቶ የሚመለሰው ህዝብ እኮ የትየለሌ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፊታችን እሁድ ሜይ 11 የሚኒሶታውን መድሃኔዓለም ቤ/ክ የወደፊት እጣ ይወስኑ

ለምሳሌ የአንድ ክልል የቆዳ ስፋት ወስደን አዚህ ግባ የማትባለውን የአንድ ወይንም ሁለት ፓረከና ሪሶርት ስፋተ ብናወዳድር ወይም ሬሾ ብናወጣ የቆዳ ስፋት ንፃሬው ዜሮ ነጥብ ዜሮ ዜሮ ዜሮ አያለ ነው የሚቀጥለው፡፡ በአራዳ ቋንቋ የጠቅላዩ ነገር አይነፋም፡፡ ነገሩ ግን የ አርት ኦፍ ዲስፕሺኑ አካል ነው፡፡

ይህ ይቅርና በገነት ያለው እኮ፣ ስላም ነው፣ ፍቅር ነው፣ አንድነት ነው፡፡ ታዲያ እርሰዎና ሰራዊትዎ ቤተክርስቲያን እየከፋፈላችሁ፣ ሃገሪቱን በውጭም በውስጥም የጦርነት አዙሪት ውስጥ ከታቸሁ ሰለ የትኛው ገነት ነው የምታወሩት? እንግዲህ ሃሳዊ መሲሁ ለተከታዮቹ ቃል ሰለሚገባላቸው ሃሳዊ ገነት ካልሆነ በቀር?

አበው  ሲተርቱ “በልብ የሞላው በአፍ ተርፎ ይፈሳል” ይላሉ፡፡ የስነልቦና ባለሞያዎች ደግሞ “ግብር ከቃላት የበለጠ ይናገራል ይላሉ” (Action talks louder than words)፡፡ ጠ/ሚ አብይ ባለፈው ሁለት ወንድና አራት ሴቶች ሚኒስትሮቻቸውን ሰብስበው ተነበርከኩ አሏቸው፡፡ ከዚያም ተቃቀፉ አሏቸው…ወቼ ጉድ!

በአንጎላ ገዢ የነበረች የ17ኛው ክ/ዘ የደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ንግስት ንዚንጋ ፖረቱጋሎቹ ጋር ለድርድረ በቀረበችበት ግዜ ፖረቱጋሎቹ ወንበር ላይ ተቀምጠው ለእሷ ወንበር ሳያቀርቡላት ወደ ድርደሩ አዳራሸ ጋበዟት፡፡ ነገሩ የገባት ንዚንጋ ከአገላጋዮቿ አንዱን ጠርታ በእጁና በእግሩ እንዲነበረከክ ነግራው አንደ ወንበር ተቀምጣበት ድርድሩን ቀጠለች፡፡ ይህቺ ናት የአፍሪካ ሴት ኩራት!

ምነው የንግስት ሳባ፣ የንግስት ፉራ፣ የንግስት ጣይቱ…ልጆች ሰባተኛው ንጉስ አሽካኖቸው ከሆነ ጠገ ብሎ በጆሮቸው ሹክ የሚላቸው ጠፋ? ነገሩን ተዉት ስርአተ አምልኮ (ritual) ነው፡፡ እዚያ ጋር የቆመ ጣኦት አለ፡፡ ሲያሻው ከአንድ ስልጣን ወደ ሌላ የሚያዘዋውር፤ ሲያሸው የሚሰብር፣ ሲያሻው የሚጠግን…ተከታዬቹን እንደ ቤ/ክ ስርአት ተቃቀፉ ተሳሳሙ የሚል…ሰውየው ውስጣቸው ስርአተ-አምልኮታዊነት (Ritualistic) መሆነቸው ተገልጦ የታየበት ክስተት ነበር፡፡ ግብር ከቃላት በላይ ይናገራል መለት ይህ ነው፡፡

አንድ የፓርላማ ተወካይ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ ከአንድ መቶ ሃምሳ ሺህ በላይ ሰው ይወክላል፡፡ ጠ/ሚሩም ሲናገሩ ኢትዮጵን ወክላችሁ ተንበርከኩ ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ እሳቸው እግር ስር ምን ልታደርግ ትፈንደድ? መጽሐፍ እንደሚነግረን ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ብቻ ነው የምታነሳው፡፡ አልበዛም እንዴ ነገሩ? አደረከው እንጂ!

እንግዲህ ሰውዬው አምላክ-አምላክ መጫወት(Playing God) ያምራቸዋል፡፡ አፄ ኃይለስላሴ ጃማይካ ሲሄዱ ዝናብ ዘነበና…ራስ ተፈሪያን የሚባሉ ጥቁሮ ህዝቦች አምላክ ናቸው ብለው አወጁ፡፡ ነጉሱ ግን አሜሪካ ላይ በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ “እኛ ሰው ነን አምላክ አይደለንም”ብለዋል፡፡ ጃማይካኖችንም ለማስተማር የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ጃማይካ ላይ ተክለዋል፡፡ ንጉሱ ሻሸመኔ ላይ ራስ ተፈሪያኖችን አላሰፈሩም፡፡ የመጀመሪያዎቹ አስራ ሁለት ሰፋሪዎች ውስጥ የኒዎርክ ተወላጅ ሞስሊም ጥቁርና የባፕቲስት ቄስ ነበሩበት፡፡ ይህ በእጅ ያለ መረጃ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሀቢባ መሐመድን ጨምሮ የ32ቱ ሰዎች ክስ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን ጠበቆቹ ጠየቁ

ይህን ሁሉ ያልኩት ሰሞኑን በዳንኤል ክብረት አርተኦት የቀረበ የአማራ ክልል ቄስ ነኝ ባይ ጠ/ሚ አብይን ሰማያዊ የሚያደርግ መወድስ አቅርቦ ነበር፡፡ ታዲያ እሳቸው ምን ገዷቸው…፡፡ ሚኒሰትሯ ጠይባ ሃሰንን የምስራቅ አፍሪካ መሲህ ብላቸው ነበር፣ ቄሱ ደገመው እንጂ ሌላ ምን አደረገ?

እሳቸውስ ቢሆኑ የአፍሪካ መሪዎችን ሰብስበው በሄድኩበት ዝናብ ተከትሎኝ ይዘነባል ብለው ኃይለስላሴ-ኃይለስላሴን ሊጫወቱ ሞክረው አልነበረም? መሲህነትን መጠማት ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ የአባይን ግድብ ግን ሞላሁት ያሉት በሳይንስ አርቴፊሻል ዝናብ አዝንቤ ነው ያሉን፣ ምነው በግድቡ ላይ አልተንጎራደዱበት? በቃ በሄዱበት ዝናብ ይከተላቸው አይደል፡፡ እንደው የኦሮሞ ሁሉ መነሻ የሆነውን ሁሌ የድርቅ ሰለባ የሚሆነውን ቦረናን ረሱትሳ?

ስለ ሁሉ ነገር  አዋቂ ሆነው (The know all) በየሙያው ጥልቅ በማለት አራሳቸውን ይገልጣሉ፡፡ እኔ አንድ ነገር (The one and only) ብሆን መቶ ሺዎች ያልቃሉ በማለት በርሃብና ጦርነት የሚገዙትን ህዝብ ያስፈራራሉ፡፡

እነዚ ሁሉ ደግሞ የመሲሁ ምስቅልቅልዮሽ( Messianic Complex) በሽታ ተጠቂዎች ላይ የሚታዩ  ምልክቶች ናቸው፡፡ ተከተሉኝ ከድል ማማ ላይ አውጥቼ እሰቅላቸዋለሁ(Follow me I will take you ቶ the height  of victory) ይላሉ፡፡ የዚህ በሽታ ተጠቂዎች በጉዟቸው ላይ ስለ የሚረግፈው ህዝብ ትንሽም አይቆረቁራቸውም፡፡ መሆን ያለበትና ግድ ነው ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ ከፈለክም ቀረብ ብለህ ካወረሀቸው “ያለ ደም መስዋትነት ስርየት(ድል) የለም” ይሉሃል፡፡ በቃ እነሱ የእግዜሩ በምድር ላይ ተወከልቱ ናቸው፡፡

ትንሽ ግዜ ሰጥተህ ስታያቸው ደግሞ አመባገነኖችን አውግዘው ስልጣን ላይ እንዳልወጡ፣ እነሱ ደግሞ የለየላቸው አምባገነን ሆነው ያርፉታል፡፡ የስልጣናቸው መጨረሻ ሲቃረብ ትእቢተኞች ይሆናሉ፡፡ እነሱ እነደሚሉት አምላክ ቀኝ እጁን አውሷቸው ከኢምንትነት ተነስተው አድራጊ ፈጣሪ እንዳልሆኑ ሁሉ፣ ለሚቀወማቸው ሁሉ ማንም በኃይል አይተካከለኝምና የትም አትደርሱም ይላሉ፡፡

ደጋግመው ለራሰቸው ፍላጎት ፍጆታነት አጣመው የሚጠቅሱት መጽሐፍ ቅዱስ ግን በማይሻረው መለኮታዊ ቃሉ እንዲህ ይላቸዋል፡፡

“ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም፡፡ ፈረስም ከነቱ ነው፣ አያድንም በኃይሉም ብዛት አይመለጥም፡፡” መዝ 32፣ 16 -17

በሃሳዊ መሲህ መንፈስ ለሚመሩ ሁሉ የእነሱ መጨረሻ የሆነውን የአባታቸውን(የዲያብሎስ) ውድቀት መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይተረክላቸዋል፤

“በበደልህ ብዛት በንግድህም ኃጢያት መቅደስህን አረከስህ፣ ሰለዚህም እሳትን ከውስጥህ አውጥቼለሁ እርሷም በልተሃለች፣ በሚያዩህ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ፡፡” ሕዝ 28፣18

ይህ ነው እንግዲህ ጠ/ሚ አብይ ውስጥ አፍጥጦ የሚያየን፣ በእሳቸው ውስጥም እራሱን ሲገልጽ የምንመለከተው አምላክ(god)፡፡

 

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ

——————————–

Phጨ
@kyisfa
·አሰዳቢ፣ ምን አሸማቀቀህ በማታውቀው ቋንቋ?? ሰው ብትሆን አቀላጥፈህ የምትፈልገውን ለመናገር የሚያስችልህ ወርቅ የሆነ አማርኛ የሚባል ቋንቋ ነበረህ። do, does, dጭ እያልክ አትዋረድም ነበር።

 

1 Comment

 1. አንኳኩ እከፍታለሁ ስትለን ሰምተናል
  ግን ሲመሽ ማንኳኳት ትንሽ ይከብደናል
  ቢቻልህስ አምላክ ኖላዊው እረኛ
  የእረፍት ውሃ በጥባጭ እንዳንሆንህ እኛ
  ቁልፉን ከውጭ ጥለህ ሳትሳቀቅ ተኛ
  ከሃብተማሪያም መንግስቴ (ፌስቡክ)
  በቅርቡ ከአንድ የሰማይ አዳሪ ሰው ጋር ስንጫወት ስማ አለኝ – እህ አልኩ ጫወታውን ለመስማት እየጓጓሁ። ፈጣሪ ሰውን በአምሳሉ ፈጠረው በማለት አራባና ቆቦ ረግጦ የሰውን እኩልነት ሊያስረዳኝ ሞከረ። እኔም ወረፋዬን ጠብቄ የእርሱ አምሳል የተኞቹ ናቸው። ዓረቡ፤ የነጩ ዓለም፤ የእስያ ተወላጆች ወይስ እሳት እንደበላው የዛፍ ግንድ የከሰለው፤ አጭሩ፤ ረጅሙ ለመሆኑ የቱን ነው የሚመስለው ስለው አማትቦ በግዕዝ የማይታየውን መንፍሰ ተራግሞ መልስ ሳይሰጠኝ ቀጠሮ አለኝ ብሎኝ ፍትልክ አለ። እንዲህ ነው መልስ ሲጠፋ መውጫ ቀዳዳን መፈለግ። ሃይማኖትን ሁለት ወገኖች ይፈልጉታል። የመጀመሪያው ጭቋኝና ሃይማኖትን ለራሳቸው የስልጣን ባራኪና የክፋት መሸፈኛ የሚያደርጉ፤ ሌሎች ደግሞ ለሰማይ ቤት ብለው የሚከተሉ ናቸው።
  ኢትዮጵያን ዳግመኛ ለመውረር ከጣሊያን የተነሳው ጦር በካቶሊኩ ጳጳስ ተባርኮ ነው መንገድን ያቀናው። በሃበሻው ህዝብ ላይ የመርዝ ጭስ በመጠቀም ሰውና እንስሳን ያወደመው የዚህ የጦር ስብስብ ነው። ዛሬ ላይ ቆመን ተመጻዳቂና ስመ መናኝ የሃይማኖት ሰዎችን ለታዘበ ደግሞ የእልፎች ደም ሲፈስና መከራ ወራጅ ውሃ ሲሆን እንዳላዬ አይቶው ለራሳቸው የሚኖሩ ከሃገራችን ቃልቻ የማይለዪ ጉዶችን እንደሆኑ ልብ ያለው ይታዘባል። ዛሬ በዚህም በዚያም የእምነት ሰዎች ናቸው የሚባሉት የሚፈጽሙትና በደልና ደባ ለተመለከተ ክራራይሶ ያሰኛል። በመናጆ እምነት አብረው እየተመሙ ምኑም ምንም ሳይገባቸው በሃዘን ለተመቱና የመከራ ዶፍ ለወረደባቸው ድምጽ ከመሆን ይልቅ በብሄሩ ሰክሮ በቋንቋው ተለክፎ ሃተፍ ተፍ ሲሉ ማየቱ ምድራዊ ድርጊታቸውን እንጂ ለሰማይ ማደራቸውን አያሳይም።፡ የአማርኛ ቋንቋ እንደ ልብ የሚወላከፉበት ላደላቸው ደግሞ የሚወላድበት ሆኖ ሳለ ቋንቋን እንደ ጠላት ቆጥሮ በፊደሎች ላይ ጥይት የሚተኩሶ የሰው እንስሶች የሚራወጡባት ይህች የሃበሻ ምድር አፍራሽን አፍራሽ እየተካው ይኸው እስከ ዛሬ በእየየ ውስጥ ትገኛለች።
  ጠ/ሚሩን የቀለድበት ሁለት ሃይሎች ናቸው። በአሜሪካ መሪነት ነጩ አለምና የኦሮሞ ፓለቲከኞች ሲሆኑ ሶስተኛ ግን የራሱ የወረት የፓለቲካ ፍቅርና ያዝ ለቀቅ ፓለቲካዊ ተግባር ነው። ወያኔ የራሱን ወታደር በዘርና በቋንቋ ክፍሎ በተኙበት መብረቃዊ ጥቃት ከፈጸመ በህዋላ ተራፊው ሰራዊት መቀሌን እንደተቆጣጠረ በስመ ዲሞክራሲ ገዳይ ሃይሎችን በቃሬዛ ተሸክሞ ካወጣ በህዋላ ምድሪቱ ትርምስ ላይ ነች። ያኔ ወያኔን ሥፍራ አስይዞ ቢሆን ኑሮ በወያኔ እየተደገፉና እየተመሩ በብሄር ስም ዛሬ ላይ የሚፋለሙት ጉልበት አያገኙም ነበር። ዳግመኛና ሶስተኛ ወረራ የፈጸመው ወያኔ በጦር ሜዳው ውሎ ሲሸነፍ አሜሪካኖች የሰላም ስምምነት በማለት የኢትዮጵያ ወታደር ወደ ትግራይ እንዳይገባ እስከ ማስፈራራት ድረስ የደረሱት ተላላኪዎቻቸውን ለማትረፍ ነበር። የደ/አፍሪቃው ውል ውል ሆነ ከተባለ በህዋላ ደግሞ አሜሪካኖች አሁንም የአማራ ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እንዲያደርግ ትዕዛዝ የሰጡት እነርሱ ናቸው። ልዪ ሃይል ይፍረስ መባሉም የአሜሪካ ሴራ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ትጥቅ ፈቶ የማያውቀውን ገበሬና የሃገር ዘብ ፋኖን ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል ሰበብ የተነሳው ውጊያ እንሆ እያተራመሰን ይገኛል። ይህን ሁሉ በግልጽና በድብቅ ከማስፈራራት ጋር ለጠ/ሚሩ ትዕዛዝ የሚሰጡት አሜሪካኖች ሰው የማይታመንባቸው የማጨበጡ ጉሞች ናቸው። ዪክሬን በእነርሱ ግፊት ዛሬ ላለችበት የሞትና የሽረት ፍልሚያ እንዳልገባች ሁሉ አሁን ደግሞ ትጥቅ አንሰጥም በማለት እያዳከሟት ይገኛሉ። አሜሪካን ያመነ ውሃ የዘገነ።
  ጠ/ሚሩ ላይ ያፈጠጠ አምላክ የለም። የተቆጣ እንጂ። የቃላት ጫወታ ካልሆነ በስተቀር የብልጽግናው (የድህነት) መንግስት ትሻልን ትቼ ትብስን እንድንል አድርጎናል። አንድ ነጋዴ እንዳለው ነው። ያው ወያኔ ሰርቆም ቢሆን ያበላሃል። እነዚህ ከራሳቸው ውጭ ሌላ ሰው አያቀምሱም። በቋንቋና በብሄሩ የተሳከረ ህዝብ ለሰላም ጀሮም አይንም የለውም። ከአውራ ጣት አመልካት እጣት ይበልጣል ከሚሉ የፓለቲካ ሰካራሞች ምንም ብልሃት አይገኝም። የአሁኑ የሱማሊያው ድንፋታ፤ የኤርትራው መሪ የካይሮ ምልልስ፤ የየመን ተፋላሚዎች ሚሳኤል ማውዘግዘግና የንግድና ወታደራዊ መርከቦችን ማጥቃት፤ የሱማሊያው መሪ ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ስብሰባ መጥቶ ያስነሳው አቧራ ሁሉ ቅጽፈታዊ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተሸረበ የፓለቲካ ሴራ ነው። ጠ/ሚሩ ልብ ካለውና በእውነትም ኢትዮጵያን የሚወድ ከሆነ እንበለ ፍርድ ያሰራቸውን ሁሉ በነጻ መልቀቅ አለበት፤ ህገ መንግስቱ መበወዙና የብሄር ፓለቲካውን ህዝባችን አክ እንትፍ እንዲለው የጠራ የፓለቲካ ሥራ ሊሰራ ይገባዋል። ካልሆነ ያው ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ፈካሪና አፋካሪዎች ሰካራም የረገጠው ጣሳ ከመሆን የሚያድነው ምድራዊ ሃይል የለም። ባጭሩ በወንጌል ስም ወንጀል የሚሰሩ፤ በቁራን ስም ቅጥፈትን የሚፈጽሙ ሁሉ ሃይማኖታቸው የማታለያ ካባ እንጂ እውነትነት የለውም። ዋሽ ቢሉኝ እዋሻለሁ ንፋስ በወጥመድ እይዛለሁ አይነት የፓለቲካ ጫወታ ለሃገራችንም ሆነ ለአፍሪቃ ቀንድ ጠንቅ ነው። በጊዜ ይታሰብበት።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share