February 18, 2024
13 mins read

የካቲት ሄደ የካቲት መጣ – አንዱ ዓለም ተፈራ

ሐሙስ የካቲት ፯ ቀን ፳ ፻ ፲ ፮ ዓ. ም. (2/15/2024)

በመካከሉ ሐምሳ የካቲቶች አለፉ! ይሄም የካቲት ሊያልፍ ነው!

ዛሬ፤ ሃምሳ ዓመታት ወደ ኋላ ዞሬ የነበርኩበትን ስቃኝ፤ የተመኘሁትና የተከተለው ምን ያህል የተራራቀ መሆኑን ስነዘብ፤ ወይ ጉድ! እላለሁ። በሕልሜም ቢሆን አገራችን እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ትማቅቃለች የሚል ግምት አልነበረኝም። ያን ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ለምን ከሠለጠኑት አገራት ወደ ኋላ ቀረች! የሚል የአገር ወዳድ ስሜት ሁሉን ነገር መመልከቻ መነፅሬ ነበር። በተማሪነቴ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪ ጓደኞቼ ጋር አብሬ ወዲያ ወዲህ ስል፣ በመምህርነቴ በሸዋ ክፍለ አገር በመናገሻ አውራጃ፣ አቃቂ መለስተኛ ትምህርት ቤት መምህራንን ወክዬ ስድስት ኪሎ ከነበረው የመምህራን ማኅበር ጽሕፈት ቤታችን ስመላለስ፣ በሕቡዕ በሚንቀሳቀሰው የጥናት ቡድናችን ስሯሯጥ፤ ኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ቀድዳ ወደ ሥልጣኔ ስትጓዝ ብቻ ነበር የሚታየኝ። ያን ጊዜ ተማሪዎችና ለውጥ ፈላጊው ወገን  ጥያቄዎቻችን ምን ነበሩ? ምኞታችን ምን ነበር? ከዚያ እስካሁን እኒህ ጥያቄዎቻችን እና ምኞታችን ምን አጋጠማቸው? ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ ትኩረት።

ዛሬ ዐማራነት ወንጀል ሆኖ፤ ዐማራዎች በያሉበት እየታደኑ የሚገደሉበት እውነታ ወቅቱን ገዝቷል። ዛሬ አገሪቱ በትውልድ ዞግ አጥሮች ተከፋፍላ፤ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ፣ በቅናትና በጠላትነት የሚመለከትበት ሀቅ በአገሪቱ ሰፍኗል። ዛሬ ጉራጌው በኦሮሞ ገዥዎች እንቅልፍ አጥቶ፤ ነገ ምን እንደሚከተል ሳያውቀው ውሎ የሚያድርበት እውነታ ጠርንቆ ይዞታል። ዛሬ አብይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከዶክተሮች የበለጠ ሕክምና አዋቂ፣ ከሃይማኖት መሪዎች በላይ የሃይማኖት ሊቅ፣ ከኢኮኖሚስቶች ሁሉ በላይ ስለ አገሪቱ የምጣኔ ሀብት ሁኔታ አስሊ፣ ከነጋዴዎች በላይ ነጋዴ፤ ከለማኞች በላይ ለማኝ፤ አልፎ ተርፎም ከፈጣሪ በላይ ፈጣሪ አድርጎ ራሱን ሰይሟል! ወይ ጉድ! ጉድም እኮ  ልክ አለው!!!

መቼም በሺ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስት ዓመተ ምህረት ተቀምጦ፤ በሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓመተ ምህረት የሚሆነውን በርግጠኝነት የሚያናግር፤ ምንም ዓይነት ተዓምር አልነበረም። ዛሬም በሁለት ሺ ስድሳ ስድስት ምን እንደሚሆን የሚነግረን ተዓምር የለም። በተማሪነቴ እንደ ተማሪዎች፣ በመምህርነቴ እንደ መምህር፣ በለውጥ ፈላጊነቴ ደግሞ እንደ ታጋይ የጣርኩት፤ ለዚህ አልነበረም። በመካከል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊና አብይ አሕመድ ገቡና፤ በግላቸው አገሪቱን አንቀሳቃሽ ሆነው፤ የኋሊት ነዷት። ላለንበት ሀቅ ተጠያቂዎቹ እኒህ ናቸው። በአገር መውደድና በወገን ፍቅር የተንገበገብን ተማሪዎች፤ በዚያ ጊዜ ሊኖረን የሚችለውን ዕድል ሁሉ ትተን፤ ለወገን ስንል ሕይወታችን ሠጥተናል። የሰው ልጅ መብት ይከበር ዘንድ፣ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በተግባር ይውል ዘንድ፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል የነበረው የፆታ እኩልነት ይከበር ዘንድ፣ የድሃ ልጅ ትምህርት ያገኝ ዘንድ፣ ከከታማ ውጪ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕክምና ያገኝ ዘንድ፣ መሬት ለሚያርሰው ይሆን ዘንድ፣ አድልዖና ሙስና ይጠፉ ዘንድ፣ ባደባባይ ሰልፍ ወጥተን፣ በፖሊስ ተሳደድን! በተለይ ከክፍለ አገራት የመጣን ተማሪዎች የምንበላው ሳይኖረን ከግቢ ተባረን መግቢያ እንድናጣ ተደርገን! መሪዎቻችን ታሰረው! ያን ሁሉ ስንከፍል፤ በተዓምር ያገራችን “የውጪ ጠላቶች መሳሪያ” ተባልን። በሃያና የሃያዎቹ መጀመሪያ የነበርን ተማሪዎች፤ የአገር ድህነትን ለመቋቋም፣ የአገራችን ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ፣ የተራበውን ለመታደግ፤ የራሳችንን የወደፊት ዕድል ዘጋን። የዕለት ምግባችንን ለወሎ ረሃብተኞች እንዲሠጥ አደረግን። አዲስ አበባን ከቁሻሻዋ ለማላቀቅ ሶስት ቀናት ዘመትን። ያ ነው አሁንም አእምሮዬ ውስጥ ያለው። በርግጥ ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥት ጢሰኛ ነው! ዛሬም ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተገፎ ነው ያለው። ዛሬማ ብሶ ታሪኩና ማንነቱ ተሰርዞ፤ እንደ መንጋ፤ ትግሬ ነህ – ትግሬ በሙሉ እንደ አንድ ትግሬ ብቻ ስለሚስብ፤ አንተም እንደ ትግሬ አስብ፣ ኦሮሞ ነህ –  ኦሮሞ በሙሉ እንደ አንድ ኦሮሞ ብቻ ስለሚስብ፤ አንተም እንደ ኦሮሞ ብቻ አስብ፣ ዐማራ ነህ –  ዐማራ በሙሉ እንደ አንድ ዐማራ ብቻ ስለሚስብ፤ አንተም እንደ ዐማራ ብቻ አስብ፣ እንደ ሶማሊ፣ እንደ ከምባታ፣ እንደ ሃድያ፣ እንደ አፋር፣ እንደ ጋምቤላ፣ እንደ ጉራጌ፣ እንደ አደሬ፣ እንደ አዲስ አበቤ፣ አስብ ተባለ። ለመሆኑ አንዱ ዐማራ አገሩንና የአገሩን ፖለቲካ በሚመለከት፤ ከአንዱ አፋር ምን የተለዬ አሳብ አለው? ሁለት የተለያዩ ኦሮሞ ግለሰቦች፤ ከአንድ ጉራጌ የበለጠ የሚያተሳስራቸው የፖለቲካ አመለካከት አለ? አኙዋኩንስ? በአጥር የተከለሉ፣ የተለያዬ ቋንቋና መንግሥታዊ ስርዓት ያላቸው አድርጎ መግዛቱ ማንን ለመጥቀም ነው?

ይሄ በትውልድ ማንነት ላይ በተመሠረተ የፖለቲካ አገሪቱን የመግዛት አካሄድ፤ ልዩነትን ምርኩዝ አድርጎ ሥልጣን ለመያዝና ለመግዛት የተደረገ ስሌት ነው። ለሰላሳ ዓመታት ባገራችን ነግሦ ስለቆዬ፤ ዘለዓለማዊና ምን ጊዜም ያለ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል። ነገር ግን አገር አፍራሽ ብቻ ሳይሆንል ሕዝብ አጨራራሽ ነው። ይሄም ያልፋል! ከሃምሳ ዓመታት በኋላ፤ ያኔም እንዲሁ አገራችን ከነበረችበት የበለጠ ዘቅጣ እንድትገኝ አልፈልግም። በሥልጣን ላይ ያለ ትክክለኛ ያልሆነ መሪ፤ የሚያስበው ራሱን ዘለዓለማዊ መሪ አድርጎ ማኖር ብቻ ነው። መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፤ እሱ ዘለዓለማዊ መሪ ሆኖ እንዲኖር ነበር ሌት ተቀን የሚያውጠነጥነው። መለስ ዜናዊም! ብቻ መልስስ እስከ ዕለተ ሞቱ ነግሧል! ይሄኛው ደግሞ በጥንቁልና የመጣሁ ነኝ! እያለን ነው። በራሱ የማይተማመን መሪ፤ ከሱ በፊት የነበረውንም ሆነ ከሱ በኋላ የሚከተለውን ይጠላል። ሁሉ ነገር በሱ ተጀምሮ በሱ የሚያልቅ አድርጎ ትርክት ይፈጥራል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በሥልጣን ላይ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ አገኘች አለን! የነበረውን ጨርሶ መካድና አልነበረም ማለት፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርን ፈጣሪ ያደርጋልና! ስላሁኑማ ከኔ የበለጠ አንባቢ ስለሚያውቁ፤ ምን እላለሁ!

ዛሬም መሬት ለአራሹ አልተሠጠም። ዛሬም ሹም ማለት አድራጊ ፈጣሪ ማለት ነው። ዛሬማ፤ እዚህ አትሄድም! በዚህ አታልፍም! እየተባለ ሕዝቡ ባለበት ታጉሯል። ዛሬ መሪው አውቅልሃለሁ! አንቺ ዝም በይ! አንተ ዝም በል! ሆኗል አገዛዙ። በትውልድ ማንነትህና በብልፅግና ብቻ ነው መደራጀት ያለብህ! አለዚያ ትታሰራለህ< ትገረፋለህ፣ ሀብትህ ይነጠቃል፣ ጻደዳለህ፣ ትገደላለህ! ተብሏል ሕዝቡ። የፈረደበት ዐማራ፤ ዐማራነቱ ወንጀል ሆኖ፤ በየተገኘበት እየታደነ ነው። ለምን? ብሎ ለሚጠይቀኝ፤ ከጠንቋይ ቤት ስላላደግሁ፤ አላወቅም! ነው መልሴ። እናቴም ስታሳድገኝ፤ ተማር እንጂ ጠንቋይ ይሆናለህ አላለችኝም።

በኢትዮጵያ የተከሰተ ለውጥ ቢኖር፤ ትልልቅ ሕንጻዎች በየቦታው ተገትረዋል፣ ጥቂት ከገዢዎቹ ጋር የተገናኙ ቢሊየነሮች ብቅ ብለዋል፣ የአንድ ወገን መሆን የሚጠቅምበት፣ የሌላ ወገን መሆን የሚጎዳበት እውነታ ነግሧል። ተጠቂው ዐማራ፤ አሁንስ በቃኝ ብሎ ተነስቷል! የራሴን የነገ ዕጣ ራሴ እወስናለሁ ብሎ አምጿል። ሕዝብ ምን ጊዜም አቸናፊ ነውና፤ ዐማራ ያቸንፋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ነቅቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ መከፋፈሉ ለገዢዎች አመቺ ከመሆን በስተቀር፤ ለሕዝቡ እንደማይጠቅም ስለተረዳ፤ ፋኖን የኔ ብሏል። ፋኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ አውጪ ሠራዊት ነው። አብሮ የመሰለፊያ ሰዓቱ አሁን ነው። ከአካባቢ ጥበቃ ተነስቶ፤ ወደ ሻለቃ፣ ብርጌድና አሁን ወደ ዕዝ የተመነደገው የፋኖ አገር አዳኝ ጦር፤ በየትኛውም ቦታ በር እያንኳኳ ነው። ለምን ዘገዬ እንጂ፤ ለምን ቸኮለ የሚል ማንም የለም። ፋኖ፤ እየመጣ ነው! መብትህን ለማስከበርና ባገርህ ለመኖር የፈለግህ ሁሉ ካሁኑ ተባበር! ይህ ትግል የሁላችንም ነው። ሌላ ዓምሳ ዓመታት መኖር ባልችልም፤ ይህ ሁኔታ ሀቅ ሆን  ያኔ ብቅ እንዲል አልፈልግም።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
Go toTop