December 18, 2023
21 mins read

“የልክልኩን ነገረው/ነገረችው” ፖለቲካ -ጠገናው ጎሹ

sahlewerk
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

እንደ መርህና እንደ አጠቃላይ እውነት (as a matter of principle and general truth) በህዝብ ወይም በአገር ላይ ሁለንተዊ የሆነ የመከራና  የውርደት ዶፍ  እያወረደ የቀጠለውን የባለጌና ሴረኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓትን አስወግዶ እውነተኛ በሆነ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት ለመተካት የሚደረግን የጋራ ጥረት በእውን ሊያግዙ የሚችሉ አጋጣሚዎችንና ግብአቶችን ከየትኛውም አቅጣጫና ግለሰብ ወይም ቡድን ቢመጡ  እሰየው ብሎ  የመቀበል አስፈላጊነትና ጠቀሜታ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ግንዛቤ  ሀሁ ስለ መሆኑ ብዙ የሚያከራክረን አይመስለኝም።

ፈታኝ ጥያቄ የሚገጥመን ይህንን አጠቃላይ መርህና እውነታ ዘመን ጠገብ ከሆነው የገዛ ራሳችን ግዙፍና መሪር ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አንፃር ለመረዳት  እና እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄ አምጠን ለመውለድ  ከምናደርገው እልህ አስጨራሽ የጋራ ተጋድሎ  አንፃር ለማየትና ለመገምገም ስንሞክር ነው።   በሌላ  አገላለፅ  አጠቃላይ መርህንና እውነትን ፅዕኑ ወደ ሆነ የተግባር ውሎ እና አሸናፊ ወደ ሆነ ምንነትና እንዴትነት ካልተረጎምነው አሳሳችና አስቀያሚ ከሆነው “የልክልኩን ነገረው/ችው” የፖለቲካ ወግ አልፈን ለመራመድ ይቸግረናልና ቆም እያለን ራሳችንን መጠየቅ ግድ ይለናል የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ።

ስንሰማቸው የቆየናቸው ቢሆንም ከሰሞኑ ግን በጣም ጎልተው እየሰማናቸው ካሉት የልክ ልካቸውን ነገሯቸው” ፖለቲካ ወጎች መካከል   1) የፕሬዝደንቷ  (ሳህለወርቅ ዘ ውዴዲስኩር  እና  2)  የተረኛ ፣ የባለጌና የጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ስብስብ የሆነው ገዥ  ቡድን  (የብልፅግናማእከላዊ  ኮሜቲ  አባል፣  የኦሮሚያ  ግዛት ምክር ቤት አባል እና  ለእኩይ ፖለቲካ ሽፋን  ሰጭነት የተመሠረተውና   የሰላምን ፅንሰ  ሃሳብንና  እሴትነትን  ዘቅዝቀን  ወይም  ገልብጠን  እንድናነብ ያስገደደን “የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር”  ደኢታ የነበረውና ወደ  እስር ቤት   (ማጎሪያ ቤት) የተወረወረው የታየ ደንደአ ጉዳይ ዋናዎቹ ናቸው።

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ከመርህና ከአጠቃላይ እውነታ አንፃር ምንም እንኳ እነዚህና ሌሎችም መሰል ሰዎች ስለ ራሳቸው መንግሥት ተብየ ዛሬ እንደ አዲስ የሚነግሩንገና    ከዛሬ  አምስት  ዓመታት ጀምሮ በአገር (በህዝብ) ላይ ስለ ወረደውና በመውረድም ላይ ስለሚገኘው  ለመግለፅ የሚያስቸግር የመከራና የውርደት ዶፍ ቢሆንም ከዚህ እነርሱም ራሳቸው  እንደ የሥልጣናቸው ደረጃና  ተግባር ተሳታፊ ሆነው  ዓመታትን ካስቆጠሩበት እጅግ አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ለመላቀቅ እስከጠቀመ ድረስ “እንኳን ወደ ጤናማ ህሊናችሁ ተመለሳችሁ”  ብሎ መቀበል የማይቻል መሆን የለበትም።

ትክክል የማይሆነው እንዲህ አይነቱን የበጎ ነገር አዝማሚያ (ክስተት) ለምን? እንዴት? ከመቸ እስከመቸ? ይህን ለማለት ምን ያህል የመከራ ዶፍ መውረድ ነበረበት?  ከየት  ወደ የት?  እነማን ለእነማንከነማን  ጋርና በምን አይነት የጋራ ስልትምን ያህል ራሳችን ወቅሰናል? ምን  ያህል ተፀፅተናል? ምን ያህል ከገዛ ህሊናችን  ጋር ይቅርታ ተባብለናል?  አብረን ስናቦካውና ስናሰራጨው የነበረው የፖለቲካ መርዝ  ማርከሻ የሆነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ ምን ያህል ዝግጁዎች ነን?  ከተቀረቀርንበት  እጅግ አደገኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ አሽከርነትና አሽቃባጭነት ሰብሮ ለመውጣት ምን ያህል ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ነን?  እጅግ ወራዳና አዋራጅ (ከሰብአዊነት በታች ከሚያወርድ)  የአድርባይነት ደዌ  ፈፅሞ ለመላቀቅ ባንችል  እንኳ በአንፃራዊነት ለመቆጣጠር ምን ያህል ህሊናችን ፈትሸናል?  በገዳይና አስገዳይ ሥርዓት አባልነት ወይም ተሳታፊነት የደም ገንዘብ በደመወዝና በጥቅማጥቅም ስም እየቀረጠፉ ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ ነገሮች በህዝባዊ አልገዛም ባይነት በእጅጉ እየተወጠሩ የመጡ ሲመስለን የተበላሽተናልና የእየተበላሸን ነው አቤቱታና ምሬት ማሰማት ብቻውን ወደ የት እና የትስ ነው የሚያደርሰን? ወዘተ የሚሉ ፈታኝና ወሳኝ ጥያቄዎችን ደፍቀን እጅግ ግልብ በሆነ “የልክልካቸውን ነገራቸው/ነገረቻችው” የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ለመንቦጫረቅ ስንሞክር ነው።

ለዘመናት ከመጣንበት ደጋግሞ የመውደቅ አባዜ ሰብረን ለመውጣት ካልቻልንባቸው ምክንያቶች አንዱ ትልቁንና ውስብስቡን አገራዊ ፈተና ከየራሳችን ውስጣዊ ስሜትና ፍላጎት   (ulterior motive) ግፊት ወይም በተቃራኒው አንፃራዊ ከሆነ እውነተኛ ፀፀትና ይቅርታ ፈላጊነት (real sense of interest in a real sense of regret and apology) መሆኑን ወይም አለመሆኑን ሂሳዊ በሆነ አስተሳሰብ ተረድተን ተገንቢውንና ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ያለመቻላችን የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነታችን ነው። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ በአንፃራዊነት የረጅም ጊዜው ይቅርና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ከእኛ አልፎ ዓለም ከንፈሩን እስኪመጥብንና መሳቂያም እስከሚያደርገን ድረስ በገዛ አገራችንና በገዛ ራሳችን ላይ እየወረደ የቀጠለው የመከራና የውርደት ዶፍም ትምህርት አልሆነን የማለቱ መሪር እውነታ ነው።

የፖለቲካ ሰብዕና ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ የሆነ የሰብዕና ቀውስ የተጠናወተው አብይ አህመድን ጨምሮ ብዙ የገዥው ቡድን አባላት፣ በተቀዋሚነት ስም የሚነግዱ ፖለቲከኞች እና አስከፊ በሆነ መልኩ ደግሞ ሃይማኖትን ከእኩይ ፖለቲካ ጋር የሚቀላቅሉ  የሃይማኖት መሪዎች የደሰኮሩልን ድንቅ ዲስኩሮችም መሪር ትምህርት ሆነውን እጅግ ግልብና አሳሳች የልክልኩን ነገረው/ችው ፖለቲካ አስተሳሰብና ጨዋታ ፈፅሞ ለመውጣት ባንችልም እንኳ  ቢያንስ በቅጡ ለማድረግ ያለመቻላችን አስቀያሚ ውድቀት ነው። በአንፃራዊነት እስካሁን ከሰማናቸው የልክልካቸውን ነገራቸው/ነገረቻቸው ፖለቲካ ግልፅና ቀጥተኛ  የመሆኑ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ከሰሞኑ እያነጋገረን ያለው የሁለቱ ሰዎች ሁኔታም የዚሁ ችግር ውጤት ነው። ለዚህ ነው ለምንና እንዴት በሚል ሂሳዊ አስተያየት (critical way of thinking) ያልተቃኘና ያልተፈተሸ የፖለቲካ አስተሳሰብ ደጋግመን የመውደቃችን ምክንያት ነውና ከምር እንውሰደው ማለት ተገቢ (ትክክል) የሚሆነው።

በቁጥር እጅግ ጥቂቶች ቢሆኑም ስለ ሁለቱ የገዥው ቡድን ባለሥልጣናት በአንፃራዊነትም ቢሆን ሂሳዊ (critical) የሆነ አስተያየታቸውን የሰነዘሩና የሚሰነዝሩ አልነበሩም ወይም የሉም ማለት እንዳልሆነ ግን ግልፅ ይሁንልኝ።

የፕረዝደንቷ “የልክልካቸውን ነገረቻቸው” ዲስኩር እንደ ዜና (እንደ ወሬ) ከመነገር አልፎ ልክ እንደ ትልቅ የፖለቲካ ክስተት ከምር ለውይይትና ለትንታኔ የሚበቃ (የሚቀርብ) ፈፅሞ አልነበረም፤ አይደለምም። የፕረዝደንቷ እጅግ ሥር የሰደደ (በሙያና በሥራ ህይወት ሂደት ውስጥ ያደገና የጎለበተ) የፖለቲካ አድርባይነት (chronic political opportunism) ባህሪ ወይም ሰብእና አሁን ለምትገኝበት እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ ዳርጓታል።

ለይምሰል ወይም ለመምሰል ካልሆነ በስተቀር ቀጣሪዎቿን/ደመወዝ ከፋዮቿን ከምር በሆነ ሃይለ ቃል (critical words) ተቸች በሚል “ታሪካዊት ፕረዝደንት” የሚል አይነት የፖለቲካ ወግ የማራገባችን ጉዳይ የሚነግረን አሁንም እጅግ ግልብና አሳሳች በሆነ የፖለቲካ አባዜ ውስጥ የመሆናችን መሪር እውነት ነው።ይህ ደግሞ ለምንፈልገው እውነተኛ የሥርዓት ለውጥ ትግል አሳሳችና አዘናጊ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነት ነውና ተገቢውን ትኩረት ይጠይቃል።

አድርባይነት (opportunism) የክስተቶችን አካሄድና ትኩሳት እየተከታተሉ ለራስ ፍላጎትና ጥቅም የማዋል ስልት (ዘዴ) ነው። የምሬት ዲስኩሯ ምክንያት ብልፅግና በህዝብ የለውጥ ፈላጊነት ማእበል (ተጋድሎ) የመናወጡ ጉዳይ ጨርሶ ወደ መፍረስ የሚያመራ መስሎ ሲሰማት “ብዬ ነበር (ተናግሬ ነበር)” በሚል ርካሽ የህዝብ ድጋፍ ወይም ተወዳጅነት ለማትረፍ እንጅ በአሻንጉሊትነት የምታገለግለው ሥርዓት ራሱን ለውጦ የዴሞክራሲና የአንድነት ሃይል (ወኪል) ይሆናል ከሚል እምነት ፈፅሞ አይደለም።  የአስከፊ አድርባይነት ልክፍተኝነት ባይሆንማ ኑሮ በገዛ መንደራቸውና አገራቸው እንኳንስ ወልደው፣ አሳድገው ፣ ፊደል አስቆጥረው እና ለወግ ማእረግ አድርሰው ጧሪና ቀባሪ ትውልድ ለማፍራት ራሳቸውም የግፍ አሟሟትና የቁም ሰቆቃ ሰለባ ለሆኑት እናቶችና እህቶች ሲባል ብቻ የይስሙላ ሥልጣን በቃኝ ብሎ ቀሪውን ህይወት በንስሃና በፀሎት መኖር እጅግ ተፈላጊ ውሳኔ በሆነ ነበር።

ለዚህ ነው “የልክልካቸውን ነገረቻቸው” የፖለቲካ ወግ በሂሳዊና ሚዛናዊ እይታ ያልተቃኘና ያልታሸ በመሆኑ ከአድሮ ቃሪያነት አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ሰብረን ለመውጣት ገና ብዙ ይቀረናልና ቆም እያልን ራሳችንን መፈተሽ አለብን ብሎ መከራከር ትክክል የሚሆነው።

የታየ ደንደአ የፖለቲካ ምህዋር በጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ የተጠረነፈ መሆኑን ለመረዳትና ለማስረዳት ብዙ መደከም ያለብን አይመስለኝም። በህወሃት ዘመን ሲታሰርና ሲፈታ የነበረበት ጉዳይም ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን በመታገሉ ምክንያት ሳይሆን በኦሮሞ ህዝብ ነፃነትና መብት ስም የሥልጣን ምህዋሩን በመቆጣጠር እና ቢቻል እንደ ህወሃት ኢትዮጵያን በመጠርነፍ የሁሉም አይነት ፍላጎትንና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ፣ ካልሆነም ግን ነፃ አገረ ኦሮሚያን መመሥረት በሚለው የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም  አቀንቃኝነት ምክንያት መሆኑን ለማስተባበል የሚችል አሳማኝ ማስተባበያ የሚኖር አይመስለኝም።

እያልኩ ያለሁት እውነትን እውነት እና ሃሰትን ሃሰት እንበል እንጅ ከወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ እውነታ (political reality) አንፃር ታየ ለምን ኦነጋዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጅ ወይም አቀንቃኝ ሆነ አይደለም። የታየን በገዛ ጓዶቹ ከሥልጣን መባረርና ወደ እስር ቤት መወርወር አስመልክቶ የሚሰጡ አስተያየቶችን ለመቃኝት ሞክሪያለሁ ፦ ሀ) ከሽመልስ የማምታትና የማሳመን (confuse and convince) የፖለቲካ ስልት ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል ለ) በውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሐ) የታየ የፖለቲካ ሰብእና ግልፅና ፊት ለፊት በመሆኑ ምክንያት ጠምደውት ሊሆን ይችላል የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።

ታየ በአጠቃላይ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ እና በተለይም የኦሮሙማ የፖለቲካ አመለካከትንና ተልእኮን መሸከምና ማስፈፀም ስለከበደው (ስላልፈለገ) የሚል ግን አልሰማሁም ። ለመስማትም አልጠበቅሁም። የጎሳና በቋንቋ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ማእበል በሚያላጋው (በሚያናውጠው) ሥርዓት ውስጥ የነበረውና ያለው የእርስ በርስ ትርምስ  የሚያስከትለውን እንደ ታየ ደንደአ አይነት ክስተት በእርግጠኝነት ወይም ወደ እርግጠኝነት የሚጠጋውን እውነታ (ምክንያት) ለማወቅ ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጅ የታየ ጉዳይ የራሱ የፖለቲካ ሰብእና እና የውስጣዊው የሥልጣንና የጥቅም ሽኩቻ ግጭት ውጤት መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ የሚያመራምር አይመስለኝም። ይህ አይነቱ ግጭት ደግሞ ታየን ይበልጥ እልህ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በስሜት የሚነዳ የፖለቲካ ጀብደኝነት  (victim of emotion-driven political adventure) ሰለባ አድርጎታል።

የታየ የቀጥተኝነት ወይም የግንባር ሰውነት የፖለቲካ ባህሪ በሰከነ፣ ስልታዊ በሆነ ፣ በዲሲፕሊን በታረቀ፣ መነሻውንና መዳረሻውን ባወቀ፣ ራስን ለጥቃት ሰለባነት አሳልፎ በማይሰጥ አኳኋን፣ ከጎሳው አልፎ ለሁሉም  በሚገደው የፖለቲካ እይታ ፣ እና በአጠቃላይ  ዴሞክራሲያዊት የጋራ አገርን እውን ማድረግን ዓላማውና ግቡ ባደረገ የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን ለመረዳት ከባድ አይመስለኝም።

በአጠቃላይ ምንም እንኳ የታየና የቤተሰቡ እንግልት እንደ ሰው የሚያሳዝን ቢሆንም የውስጡን የሥልጣን ሽኩቻ በአላስፈላጊ (ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ሁኔታዎች) ግምት ውስጥ ባላስገባ የፖለቲካ ጀብድ (unnecessary political adventure) ለመግጠም የሄደበት መንገድ የፖለቲካ ብስለትና ጥበብ ሳይሆን የፖለቲካ ቂልነትና ግብዝነት ከመሆን አያልፍም።

ከዚህ ሁሉ የምንማረው መሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው መሪር እውነታ ጋር የማይገናኝ “የልክልኩን/የልክልኳን ነገራት/ነገረችው” ፖለቲካ በራሱ ፈፅሞ የትም እንደማያደርሰን ተገንዝበን ሂሳዊ አስተያየትን  ልምድ ማድረግ እንዳለብን ነው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop