ከአልማዝ አሸናፊ
ዋዮሚንግ: አሜሪካ
ጦርነትን በመሳሪያ ብዛት : በወታደር ቁጥር የበላይነት : ወይም በዛቻና በፉከራ ድምፅ ከፍታ ማሸነፍ እንደማይቻል የዓለም ታሪክ ያስተምረናል:: ሕዝብን የማያቅፍ መንግስትም ሆነ የፖለቲካ ንቅናቄ መጨረሻው ለሌላው በቆፈረበት ቀብር ጉድጏድ ራሱ ይቀበርበታል:: አብይ አህመድ ይህንን ፍፁም ሊረዳ ባለመቻሉ ከአቀፈውና ለስልጣን ካበቃው ሕዝብ ጋር ግብ ግብ ውስጥ ሲገባ መጨረሻው ከደርግና ከወያኔ ውድቀት የባሰ ውድቀት እንደሚሆን አለመገንዘቡ በእርግጥ ይህ ሰው በ”ሆይሆይታ” በቀላሉ የሚሰክር ቂል ነው ወይ ያሰኛል::
እንዴት በፍጥነት ከብርሃን ወደ ጨለማ : ከኢትዮጲያ አንድነት ወደ ኦሮሞ ጎሳ ተቆርቋሪነት (ኧረ ለመሆኑ የትኛው የኢትዮጵያ ጎሳ ነው ከኦሮሞ ጎሳ የተሻለ የሚኖረውና ነው ኦሮሞ ተበደለ እየተባለ ከበሮ የሚመታው? ሰርተው ለፍተው ከመብላት ይልቅ ሕዝብን ከሕዝብ እያጋጩ ኑሮአቸውን የሚመሩ እነጀዋር መሐመድና መሰል አእምሮ ድኩማኖች የሚያራምዱት ውሸት ተሰምቶ አይደለም?) : ከአገራዊነት ወደ ብሔራዊነት : ከሰላም ጥብቅና ወደ ጦርነት ጫሪነት : ልዩነትን በውይይት ከመፍታት አቋም ይልቅ “እኛ የማይበገር ጦር ኃይል ያለን ጉልበተኞች ነንና አርፋችሁ ተቀመጡ” ባይ ጉረኛ መሪ እንደተሸጋገረ ይገርማል::
“በሃሳብ ብልጫ ዓላማን የማሳካት አውድ በተፈጠረበት በመገዳደል የፖለቲካን ዓላማ ማሳካት አይቻልም::” ~ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ:: እውነት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከ2018 እስከ 2022 ዓመተ ምህረት መጀመሪያ ድረስ : በእገር ቤትም ሆነ በውጭ ባሉት አገርን : አንድነትን : አብሮነትንና የሕዝባችንን ሕብረትን በሚወዱና በሚመኙት ኢትዮጵያውያን ያገኘውንና የተሰጠውን መወደድና መፈቀር ሳስብ : የኢትዮጵያን ማንነት አጎድፎ : ኢትዮጵያዊነትን አርክሶ : ጎሣነትና የዘር ጠባብነት እንዲነግስ በማድረግ ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት መከፋፈል እንዲከሰት ያደረገውንና አሰብን አሳልፎ በመስጠት ኢትዮጵያን የባህር መውጫ ያሳጣት ወያኔ ክርስትና አባት የሆነውን ስብሃት ነጋንና ዘመዶቹን በድንገት ከእስር ሲፈታ : ምን ያህል ለዚያ ላከበረው ለወደደውና ላፈቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቀት እንዳሳየ መገመት አያቅትም:: አንድ መታወቅ ያለበት ነገር : የአፊሪቃ አገራት መሪዎች ምን ያህል ቢማሩ ቢሰለጥኑ : ሥልጣን ወዳድ አረመኔዎች ከመሆን አይመለሱም:: ተደጋግሞ ያየነውና የምናየው ሃቅ ነው:: ለሥልጣን የስጋ ዘመዶቻችውን : የቅርብ ጏደኞቻቸውን : ለለውጥ አብረው የታገሉ የትግል አጋሮቻቸውን : ከመግደል ከማስገደል ከማሰር ከማሳሰርና ከማግለል ወደሗላ የማይሉ ሰብዓዊነት የተሳናቸው ሰው መሰል አውሬዎች መሆናቸውን በተለያዩ የአፍሪቃ አገራት መሪዎች ተመስክሯል:: አብይ አህመድም በኢትዮጵያ ይህንን ባህርይ ከዕለት ወደ ዕለት እያስመሰከረ ነው:: መንግስቱ ኃይለማሪያም : አጥናፉ አባተንና መልካም አመለካከት ያላቸውን ግብረአበሮቹን እንደበላ : መለስ ዜናዊና ስግብግቡ ወያኔ በስብሃት ነጋ በረከት : የትግሉ አጋሮቹንና ባልደረቦቹን እንደገደላቸውና እንዳገለላቸው : አብይ አህመድም : ለማ መገርሳንና ሌሎቹን ከየክልሎቹ የወጡትን የለውጡ ቁልፍ ሰዎች ነፍሳቸውን ባያጠፋም : አስተዳደርህ አገር የሚያፈርስና የአገሪቱን ሕዝቦች የሚያገዳድል ነው ቢሉት : ለሆዳቸው በተገዙት ስብዕናና ስብዓአዊነት በተሳናቸው የደህንነት ሃይል አባላት የማያስራቸውና የማያንገላታቸው ለመሆኑ ምንም አስተማማኝ አይኖርም:: ወያኔን ከስልጣን ያባረረው ለውጥ እንዲመጣ የረዱት የአብይ አህመድ ጏዶች ዛሬ አንገታቸውን ደፍተው ድምፃቸውን ባለማሰማታቸው እስር ቤት ያለመግባትና : በጥይት ተመተው ከመሞት ሊተርፉ ችለዋል::
ስብሃት ነጋና ዘመዶቹን ከተደበቁበት ገደል ዋሻ አውጥቷቸው እስር ቤት ሲከት : እነደብረፅዮንና እነጌታቸው ረዳን ማግኘት ሳይችል ቀረ:: ለምን? ቢባል : ስብሃት ነጋ እነዚህ ሁለቱ እንዲሞቱ ስላልፈለገ ይሆናል:: ግን እነአቦዬ ፀሐይንና እነሥዩም መስፍንን እነሴክቱሬ ጌታቸውን : እነዳንኤል አሰፋን እነዘራይንና አበበ አስግዶምን አብይ ገደለ:: እነዚህን ሲገድል ከወያኔ ተንኮል ጀርባ ሆኖ ኢትዮጵያን ለአርባ ዓመታት ሲያተራምስ የነበረውን ስብሃት ነጋን ተጠቅሞ ሳይሆን አይቀርም:: ልክ ስብሃትንና አብረውት ከጉድጏድ ወደጉድጏድ እንደአይጥ እየተዘዋወሩ የነበሩትን መከላከያ ሲይዝ : ስብሃት ነጋ የራሱንና የቅርብ ዘመዶቹን ሕይወትና ነፃነት ለማዳን : በቦንብ የተገደሉ የወያኔ መሪዎች የነበሩበትን ድብቅ ዋሻ ወይም ዋሻዎች አሳልፎ ሳይሰጥ አልቀረም:: አብይ አህመድ ስብሃት ነጋን ሲፈታ : “እኔና ቤተሰቦቼ እስር ቤት እንዳንገላታና ከአገር እንዳንወጣ የማትከለክለን ከሆነ ሌሎች የወያኔ መሪዎች የተደበቁበትን እነግርሃለሁ በሚል ስምምነት ሳይሆን አይቀርም::
አብይ አህመድ ወያኔን ለማጥፋት የፈለገበት ዋና ምክንያት ስልጣኑን የሚቀናቀን እጅግ ጠንካራ ድርጅት ስለሆነ እንጂ : ለኢትዮጲያና ለኢትዮጵያውያን አንድነትና ክብር እንዳልሆነ አሁን እየተረዳን ነው:: ለዚህም ማስረጃ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ F… U : ምን ታመጣላችሁ የሚል ከባድ ንቀት በማሳየትና በውጭ ተበታትኖ ያለውን : እሱን ያከበረውን : ያደነቀውን : የወደደውን ኑና ገናንና ጥምቀትን በአገራችሁ አሳልፉ ብሎ ሲጋብዝ በአክብሮት ጥሪውን ተቀብሎ የገባውን ደጋፊ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን አገር ቤት ገብቶ ባለበት ወቅት ጃንወሪ 7, 2022 ቀን : ስግብግብ አረመኔውን ስብሃት ነጋን ያለፍርድ በነፃ መፍታቱ ነው:: ይህ የሕዝብ ንቀት የአምባገንነነት መገለጫ መሆኑን ጃንወሪ 7, 2022 ከ40 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የአገር ህልውና ሲያጠፋና ሕዝብን ያፋጀ ባንዳና ወንጀለኛ ስብሃት ነጋን አብይ አህመድ በነፃ ሲለቅ ግልፅ አድርጎታል:: ከጃንወሪ 7, 2022 ጀምሮ አብይ አህመድ ከድጡ ወደ ማጡ በመግባቱ ራሱ በስልጣን ላይ የመቆየት ሁኔታው ስለሚያጠራጥረው BY ANY MEANS NECESSARY በሚል መንፈስ ተወጥሮ “በሃሳብ ብልጫ ዓላማን የማሳካት አውድ በተፈጠረበት በመገዳደል የፖለቲካን ዓላማ ማሳካት አይቻልም::” ብሎ የተናገረውን በመርሳት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ተቃዋሚዎቹን በማሰር : በመደብደብና በመግደል የኢትዮጲያን ሕዝብ እያስቆጣና ወደ አላስፈላጊ እልቂት እየገፋፋ ነው:: የአገርን መከላከያ የሕዝብ መግደያ የግል ሰራዊት በማድረግ መከላከያውንም ከሕዝብ በመለያየት የስልጣኑ ማስጠበቂያ በማድረግ ላይ ይገኛል:: የሚያሳዝነው ከኤታማጆሩ ጀምሮ እስከ አነስተኛው መኮንን ይህንን የአብይ አህመድን የስልጣን ጥማትና ሰባተኛው ንጉሥ የመሆን ሕልሙን እንዴት እነዚህ “ተምረዋል” ተብለው የሚታሰቡ የአገርና የሕዝብ አደራ የተጣለባቸው የጦር ሹማምንቶች ሊገነዘቡት አልቻሉም? የእነሱ ቤተሰቦች ከሞላላቸው : ልጆቻቸው ውጭ ተልከው ከተማሩ : ደሃው ሰፊ ሕዝብ በእርሃብ አለንጋ ቢገረፍ : በኑሮው ውድነት ሕዝቡ ቢያለቅስ ምን ደንታ ይሰጣቸዋል? አብይ የተንደላቀቀ ኑሮ ካመቻቸላቸው ሕዝብን በቦንብ መግደል እንጂ ለሕዝብ ምን አስጨነቃቸው? ኢትዮጵያ የሕዝብ መከላከያ ከነበራት ቆይቷል:: ኢሐደግ ከመጣ ጀምሮ ያለው መከላከያ የአገር ሳይሆን ስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ስልጣን አስጠባቂ እንጂ : እኔ የሕዝብ ነኝ ሕዝቤን አልወጋም ብሎ ለሕዝብ የቆመ እንዳልሆነ ታዝበናል::
ላለፉት ሁለት አመታት የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኞች : ጋዜጠኞች : ነጋዴዎች : ምሁራን ላይ የደረሰውን ግድያ እስር ድብደባና መንገላታት እንዳለ ጠብቀን: በቅርቡ በአብይ መንግስት በሕዝብ ላይ የሚደረገውን ግፍ ቆንጠብ ብናደርግ : በአማራ ክልል የሚካሄደው ጦርነት የአግባብ ጦርነት ስላልሆነ ይቁም ለማለት ሰላማዊ ሰልፍ የጠሩትን የኢሕአፓ ፖለቲካ ፓርቲ አመራርን ማሰር : በመንግስትና በኦዴድ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ባለስልጣንና አባል ሆኖ አገርና ሕዝብ የሚጎዳውን የመንግስት አሰራር በማየት እውነት እውነቱን በየጊዜው ሲያጋልጥ የነበረውን ታዬ ደንዳን በውሸት በመወንጀል ማሰር : “በሃሳብ ብልጫ ዓላማን የማሳካት እውድ በተፈጠረበት በመገዳደል የፖለቲካን ዓላማ ማሳካት አይቻልም::” ብሎ አብይ አህመድ ራሱ የተናገረውን ውድቅ ያደርጋል:: አብይ አህመድ : ቃላት መደርደር እንጂ : ቃሉን የማይጠብቅ : ሃይማኖተኛ ይምሰል እንጂ : ፈረሃ እግዚአብሔር የሌለው : ስለሰብዓዊነት ያውራ እንጂ ስብዕና የጎደለው መሆኑን ከዕለት ወደ ዕለት እያስመሰከረ መሆኑን : የሚሰማችሁ ሰዎች ካላችሁ ንገሩልኝ::
ያለአማራና: ያለአፋር ልዩ ኃይሎች የትግራይን ጦርነት መወጣት ያልቻለ መሪ : ለአገሩ ሕልውና በማለት የአማራና የአፋር ሕዝብ : የዚህን አስመሳይ መሪ ጥሪ በመስማት ከጎኑ ቆሞ : ወያኔን ድምጥማጡን አጥፍቶ አገር ያዳነውን ሕዝብ ጦርነት ሲገጥመው : ይህ መሪ የማሰብ ችሎታው የተወዛገበና እንደ አረመኔ የአፊሪቃ መሪዎች ለአገርና ለሕዝብ ማሰብና መጨነቅ ሳይሆን : በሕልሙ (እናቴ ሰባተኛው? የኢትዮጵያ ንጉሥ ትሆናለህ ብላ አልማልኛለች) እንዳሰበው : መሪ (ንጉሥ) መሆን የሚመኝ እንደሆነ እያስገነዘበን ነው:: መሪ እንዲሆንማ በአውሮፓውያን አቆጣጠር ኤፕሪል 2018 ለማ መገርሳ የኦሮሞ ክልል ፕሬዝዳንትነቱን አሳልፎ ለአቢይ አህመድ በመስጠትና የአማራ ክልልና የተቀሩት ክልሎች በመተባበር የድምፅ ብልጫ ሰጥተውት : ወያኔ ካቀረባቸው እጩዎች እሱ እንዲመረጥ ያደረጉት:: ሲመርጡት ዛሬ የያዘውን አገር አፍራሺነት ያራምዳል : ሕዝብን ያስርባል : ያገዳድላልና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ : የኢትዮጵያን መከላከያ በመጠቀም ጦርነት ያውጃል የሚል እሳቤ ወይም ቅዠት ውስጥ ሆነው አይደለም:: የአገሪቱን ኢኮኖሚ የደላላ ኢኮኖሚ በማድረግ ከጤፍ እከቤት ሽያጭና ኪራይ ኗሪዎቹ መኖር የማይችሉባት አገር እያደረጋት ይገኛል:: ኢትዮጵያ ሰርቶ አደሩ ሰፊው ሕዝብ በሰራው መጠን በቀን ሶስቴ ስጋ ባይበላም እንጀራ በሹሮ በልቶ የሚኖርባት አገር መሆን ፋንታ የደላላዎችና የባለሥልጣናት ኪስ ማዳበሪያና ማሰለጫ አገር መሆኗን አብይ አህመድ አያውቅም ማለት ይከብዳል:: ግን ይህንን በአመራሩ ዘመን በአገሪቱና በሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል አብይ አህመድ አያውቅም ሳይሆን : ፍላጎቱ ለሕዝብና ለአገር ሰላም : መሻሻልና ደህንነት ሳይሆን ስልጣን ላይ እንዴት እንደሚቆይ ነው:: በ2018 ሲመረጥ በነበረው መልካም አነጋገርና እንደበት ለስላሳነቱ ሃቀኛ የሆነ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የሚቆረቆር : ኢትዮጵያ ከምትከፋፈልና ከምትፈርስ : ለኢትዮጲያ ማንነትና አንድነት ቆሞ : ከጠባብ ጎሰኞችና ዘረኞች ጋር የማይደራደር : የአቡነ ጴጥሮስን ወኔ የተጎናፀፈ የኢትዮጵያ መሪ ይሆናል ተብሎ ታስቦ ነበር::
አብይ አህመድን በዜና ከሰማሁበትና ከዋዮሚንግ እስከ ሚኔሶታ ዩኤስኤ ድረስ ነድቼ ሄጄ ካደምጥኩበት እስከ ጃንዋሪ 7, 2022 ድረስ : ለኢትዮጲያ የተላከ መሲህ በሚል ግምት ውስጥ ያስቀመጥኩት ሰው ነበር:: ከዚያም በሗላ የወያኔን ቀንደኛ ተንኮለኛ ስብሃት ነጋና ርዝራዚዮዎቹን ሲፈታ ደስ ባይለኝም : ይቅር ለእግዚአብሔር በማለት ከጦርነት ኢትዮጵያ ወጥታ ለዘመናት ያጣችውን ሰላም ሊያመጣ ይችላል በሚል ግምት ድጋፌን ቀጥዬ ነበር:: ግን አብይ እህመድ ከመንግስቱ ኃይለማርያምና ከወያኔ የባሰ ተንኮለኛና የስልጣን ጥማት አዙሮት የጣለው መሆኑን የተገነዘብኩት : ጎረቤት አገር የሆነችው ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት የመንጠቅ ፍላጎት በሚታይበትና : ወያኔ አማራንና አፋርን በመተናኮል ኢትዮጵያን የማድከምና የማከፋፈል ስሜት ባልተረጋጋበት ወቅት: የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል መሳሪያ አስረክባችሁ ወደምትፈልጉበት ስራ መስኮች ግቡ ማለቱና በተመሳሳይ ወቅት ግን በኦሮሚያ እየመለመለ የኦሮሞ ክልልን ልዩ ኃይል ሲያጠናክር : አብይ አህመድ ለአገር ህልውናና ለሕዝብ አንድነት ደንታ ያልሰጠው በጠባብ ጎሰኝነትና ዘረኝነት የተጨማለቀ መሆኑን ባለፉት ሁለት ዓመታት በግልፅ እያሳየን ይገኛል:: እንደኢትዮጵያ መሪ በዓለም የፖለቲካ መድረክ መታየትን እንጂ የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት የሚያስጨንቀው እንዳልሆነ ልታዘብ ችያለሁ:: ጠንካራ አገርና አንድ ያልሆነ ሕዝብ በሌለበት ጠንካራ መሪ ሊፈጠር እይቻልም:: ለዚህም ነው ያለጠንካራ ኢትዮጵያና : ያለሕዝቦቿ አንድነት: አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠንካራ መሪ ሆኖ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ቆሞ መታየት እንደማይችል ማወቅ ያለበት:: ሊቢያ : ሱማሌ : ሱዳን በአፍሪካ : አፍጋኒስታን በሩቅ ምስራቅ : ሊባኖስ : ሶርያ : ኢራቅና ከኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ተሻግረን ባለው የመን በመካከለኛው ምስራቅ : የሚታየውን የአገር መጥፋት የሚያስተውል መሪ : ለአገሬና ለሕዝቤ የምመኘው ይህን የመሰለ የሕዝብን እልቂትና የአገርን ሕልውና ማውደም ነው ወይ ብሎ መጠየቅ በስብዕና የታነፀ መሪ ችሎታ መሆኑን ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል::
አንድ ሃቅና የማይዛባ እውነት : መሪዎች ይመጣሉ : ይመራሉ : ይለቃሉ ወይም ይባረራሉ : ይኖራሉ ወይም ይሰደዳሉ : ቡመጨረሻም ይሞታሉ:: ግን ምን ዓይነት ሞት ይሞታሉ ለሚለው ጥያቄ መሪዎች ራሳቸው ለመመለስ ማሰብ ይኖርባቸዋል:: ብልህ መሪ ከእኔ በፊት መጥተው የመሩና የሄዱ መሪዎች አወዳደቃቸው እንዴት ነበር ብሎ የሚጠይቅ ነው:: የሚያሳዝነው በእኔ ዕድሜ ኢትዮጵያን የመሩት መሪዎች ተከብረውና ተወደው የተሸኙ አለመሆናችው ታሪክ መዝግቦ አስቀምጧል:: አብይ አህመድ የያዘውን የግብዝነትና ማንአክሎኝ ፉከራውን ትቶ : የወደደኝንና ያከበረኝን ሕዝቤን አስከፊቻለሁ:: አቅፎ የደገፈኝን ሕዝብ ለችግር አጋልጫለሁና ተሳስቻለሁ በማለት ታርሞ በ2018 ወዳሳየው ቀልቡ ካልተመለሰ : ካለፉት መሪዎች በባሰ ሁኔታ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያዘገጠ ክፉና አረመኔ የኢትዮጵያ መሪ በመባል የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚመዘግበው ማወቅ ይኖርበታል:: ስለዚህ በዓለም መድረክ የሚታወቀው የኢትዮጵያ መሪ እንጂ የኦሮሞ ጎሳ አባ ገዳ እንዳልሆነ በመገንዘብ : የኢትዮጵያ ታሪክ (ሕዝቦቿ ዛሬ በአካልና በአእምሮ ላሉበት ስቃይና መከራም ሆነ ለኢትዮጵያ ታሪክ ደንታ ካልሰጠው) ዘርማንዘርህን አርክሶ ከሚያስቀምጥህ : ኦሮሞነትን ለስልጣን ብለህ ከማራመድ ይልቅ : ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት በመቆም ለራስህና ለሚቀጥሉት የኢትዮጵያ ትውልዶችህ መኩራሪያ ሁንላቸው ብላችሁ ንገሩልኝ::
ጎሰኝነት የብቸኝነት ነፍጠኞች ማህበረሰብ ነው። እራስን እንደ ጎሳ አባል ብቻ ማየት ወይም መለየት ሰባዊነትን ያሳጣል:: ስንወለድ ሰው ተወለደ እንጂ ኦሮሞ አማራ ትግሬ ተወለደ : ስንሞትም ሰው ሞተ እንጂ አንድ ትግሬ አንድ አማራ አንድ ኦሮሞ ሞተ አይባልም:: ታዲያስ ስንኖር እንዴት እንደሰው መኖር ትተን እንደጎሳ አባል እንኖራለን? እንዴት ያገር መሪ ሰውነትን እሳንሶ ጎሳን ያስቀድማል? እኔ ሰው ሳልሆን ኦሮሞ ነኝ እንዴት ይላል? የመሪ አቋም ለአገር ልማትና ውድመት ትልቅ ሚና እንዳለው አብይ አህመድ አያውቅም ማለት አይቻልም? መሪ በወገናዊነት አንድ የሕዝብን ክፍል ብቻ የበላይ ለማድረግ ሲሞክር ስፊውን የአገር ሕዝብ በማስቀየም የአገሪቱን ሰላም የሕዝብን አንድነት ያናጋል:: በሰላም ለመኖር እንደ አንድ ህዝብ የአንድ ሀገር ዜጋ ለጋራ ዓላማ መስራትና መቆም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የማንነታችን መገለጫና ኩራታችን ስለሆነ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውነት ቁም ብላችሁ ለአቢይ አህመድ ንገሩልኝ:: አለበለዚያ አንዱ ደልቶት ሌላው እየተሰቃየ የሚኖርበትን አገር መምራት አይቻልም:: መጨረሻው መተላለቅ ይሆናል::
ሰላም ለኢትዮጲያ : አንድነት ለኢትዮጵያውያን ይሁን::