ይድረስ በባህር ማዶ የቤተ ክርስቲያንና የገዳም ፕሮጀክት ዘመቻ ለተጠመዳችሁ ወገኖች!

November 17, 2023

T.G

ደጋግሜ እንደምለው ጊዜንና ሁኔታን ያገናዘበ እስከሆነ ድረስ እንኳንስ ቤተ እምነት የተለያየ አገግልግሎት የሚሰጡ ሌሎች ተቋሞችም ቢሠሩና ቢስፋፉ ቅሬታ የሚኖረው ባለጤናማ አእምሮ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

 የአገራችን ህዝብ ለማመን ቀርቶ ለማሰብም በሚከብድ መከራና ሰቆቃ ውስጥ ሆኖ የባእዳንን ነፍስ አድን ምፅዋእት እየተማፀነ ባለበት በዚህ ወቅት ፉክክር በሚመስል አኳኋን በየባህር ማዶ ቤተ ክርስቲያን ወይም ገዳም ለማሠራት በሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ ማሳዘን ብቻ ሳይሆን ህሊናን ይፈታተናል።

በእውነት ምኑ ነካን? ምነው አእምሯችን የትኛው ከየትኛው መቅድም እንዳለበት ማመዛዘን አቃተው? እውን በዚህ አይነት እኛነት የሚሠራን ቤተ እምነት ወይም ገዳም (ያውም ባህር ማዶ) ባርኮ የሚቀበልና ማደሪያው የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ ይኖራል እንዴ? ወዘተ የሚሉ እጅግ ፈታኝ ጥያቂዎችን ያስነሳል።

ክርስቶስ ቃልን ከተግባር ጋር በማዋሃድ ጨካኝ ገዥዎችን እየገሰፀ እና በራሱም ደካማነት ሲሰቃይ የነበረውን ሰብአዊ ፍጡር እያፅናና እና እያስተማረ አሳየን እንጅ በሌለ አቅማችሁ ህንፃ ካልገነባችሁልኝና ካላስዋባችሁልኝ መንግሥተ ሰማያትን አትወርሷትም በሚል ዘመቻ ወርቃማ ጊዜውንና አስተምህሮቱን አላባከነም።  

እናንተ የዘመናችን የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ግን በጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥዎች ምክንያት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መጠንና አይነት መከራና ሰቆቃ እየተገረፉ ከሚገኙ አያሌ ሚሊዮን ንፁሃን በተለይም ህፃናት፣ ወላጆች፣ አቅመ ዳካሞች  ወዘተ ጉሮሮ ላይ እየነጠቃችሁ ወይም እየተሻማችሁ የእግዚአብሔርን ቤት እናሠራለን የሚል ዘመቻ ላይ ከተጠመዳችሁ ሰነበታችሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "በህግ አዋቂ ፣ በመብት አስጠባቂ " ሹም መብት ሲጣስ እንዴት ያማል ?

ከቶ ጊዜ የማይሰጥ  ትኩረትና ርብርብ የሚጠይቀውን  የወገን ጩኸትና ጥሪ እንደሌለ ቆጥሮ ወይም ችላ ብሎ ወይም  በሌላ የዘመቻው አቀንቃኞች በሚያውቁት ምክንያት (ulterior motive)  የሚሠራን ቤት ክርስቲያን ማደሪያው የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ እንደሌለና እንደማይኖር ለመረዳትና ለመናገር ነብይና የሃይማኖት ሊቅ መሆንን አይጠይቅም። የሚጠይቀው የሚዛናዊና የቅን ህሊና ባለቤትነት ሆኖ መገኘትን ብቻ ነው!

ከሁሉም የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው አገረ እግዚአብሔር የምንላት አገር ምድረ ሲኦል ለሆነችባቸው በአየሌ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን አማኝ ወገኖች በቅድሚያ ቅድሚያ ርብርብ እንድረስላቸው፤ አገር መኖሪያ እንጅ የመቃብር እና የቁም ሙት መናኸሪያ ሆናለችና ከዚህ ሰብሮ ለመውጣት  የፈጣሪን ድጋፍ እየተማፀን የምንችለውን አስተዋፅኦ ሁሉ እናድርግ  የባህር ማዶውን የቤተ እምነት ግንባታ ዘመቻ ለጊዜው እናቆየው የሚል የሃይማኖት አባት ወይም መሪ ለማግኘት አለመታደላችን ነው።

 ባለጌና ጨካኝ ገዥዎች አደንቁረው የሚገዙት አልበቃው ያለ ይመስል የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች ነን የሚሉትም  ቃልን ከተግባር ጋር በሚያዋህድ አርአያነት ሃላፊነታቸውንና ተልእኳቸውን ለመወጣት ተስኗቸው  በፈጣሪ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ሲያደነቁሩት መታዘብ የእውነተኛ አማኝ ህሊናን በእጅጉ ይፈታተናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሎሎ ቢንከባልል ያው አሎሎ ፣የሚደፈጠጠው ግን ሳሩ! - አገሬ አዲስ

አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን በጥቅም ወይም በፍርሃት ወይም በአድርባይነት ከባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ጋር እየተሻሹ   ሃይማኖቱን ተረት ተረት እያስመሰሉት ነውና ከምር መናገርና መነጋገር ግድ ይለናል።  የመናገሪያውና የመነጋገሪያው ወቅትና ሁኔታ ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። አዎአግባብነት ያለው እስከሆነ ድረስ አካፋንን አካፋ ለማለት  ( to call it as it is ) መሽኮርመሙ ይብቃንእውነተኛው አምላክ የሚወደውም ይህንኑ እንጅ የሰበብ ድሪቶ እየደረቱና ዙሪያውን እየዞሩ መስሎና አስመስሎ መኖር አይደለም!

የመከረኛውን ወገን የደም ጎርፍን፣የደም እንባን፣ የርሃብና የጥማት ሰደድን፣ የርዛት ብርታትን፣ የጤና መቃወስን፣ የሥነ ልቦና ስብራትን፣ የሞራል ድቀትን፣ እና በአጠቃላይ ከሰብአዊ ፍጡራን በታች የሚያደርግ ተመፅዋዕኝነትን፣ ወዘተ ችላ ብሎ ወይም  ወደ ኋላ ወይም ወደ ጎን ገፍቶ የሚሠራ ቤተ ክርስቲያን ወይም ገዳም በወርቅ ቢሠራም እውነተኛው አምላክ ይፀየፈዋል እንጅ ፈፅሞ አይቀበለውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላማዊ ሠልፍን እንደ ትግል ስልት - በ ሰለሞን ጎሹ

 

3 Comments

  1. ምንም እንኳን የፀሃፊውን ሙሉ ስም ባላውቅም ቲጂ የሚለውን መጠሪያቸውን ተቀብዬ ላቀረቡት እውነትን ፈልቅቆ ዬሚያሳይና ደፋር ትንታኔያቸው ለማመስገን እወዳለሁ::
    እንዳቀረቡት ፈጣሪ በትንጣለለ ሳሎንና ባማረ ህንፃ ውስጥ ብቻ እገኛለሁ አላለም::ክርስቶስም በቤተልሄም ግንብ ሳሎን ውስጥ አልተወለደም አላስተማረም::በሁሉም ቦታ ተገኝቶ ከተገፉት ጋር ቆሞ ግፍና ሃጥያትን ሲቃወም ለፍትህና ለሰው ልጆች ክብር ሲታገል የኖረ በሰው አምሳል የተፈጠረ መሲህ ነበር::ይህንን ተልእኮ እንከተላለን የሚሉ አስመሳይ የዘመናችን የዬእምነቱ መሪዎች ግን በዘመናዊ ቪላ ውስጥ የሚኖሩ በውድ መኪና የሚንቀሳቀሱ በደመወዝ የሚተዳደሩ የመንግስት ቅጥረኞች ሆነዋል::የፈረደበት አማኝም ሳይጠይቅና ሳይመረምር በውግዘት ፍርሃት እዬራደ ማምለኩን ቀጥሎበታል:: የሚሰጠው አስራት ለደካሞች መርጃ ሳይሆን ለነዚሁ የሃይማኖት መሪ ነን ባዮች የመዝናኛና መወደሻ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ሆኗ:: በአገርቤት ዕድሜ ጠገብ ገዳማት በእርጅናና በስርአቱ የጥፋት ሃይሎች ሲወድሙ በዝምታ እያዬ በውጭ አገር የቤተክርስቲያን ግንባታ ውድድር ላይ ተጠምዷል::እርግጥ ነው አማኝ ባለበት ሁሉ የእምነት ቦታ መኖር የሚገባ ቢሆንም በሚታዬው መልኩ ቅጥ ያጣና የተንዛዛ የውድድር መስክ መሆኑ ተገቢ አይደለም::የሃይማኖት አባቶችም የሚራኮቱት በውጭ አገር ለሚገነባው ገዳም የመሪነት ቦታ ለመያዝ ሆኗል ምክንያቱም የሃብት ምንጭ የምቾት ኑሮ የሚገኝበት ስለሆነ ነው ::በአገርቤ ደሃው አማኝ የሚፈልገውን አገልግሎት አያገኝ ክርስትና ለመነሳትም ሆነ ሲሞት ለመፈታት የግድ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ ሆኗል::ይህ በእንዲህ እያለ የሚዘገንነው ደግሞ እብሪተኞች ስልጣን ላይ ወጥተው የሚፈፅሙትን ግፍና በደል ከመቃወም ይልቅ ህዝብ ድምፁን አጥፍቶ ሰግዶ እንዲኖር በማደንዘዝ ተግባር ላይ መጠመዳቸው ነው::የሰው ልጅ በእምነቱና በሚናገረው ቋንቋ ተፈርጆ ሲጨፈጨፍ ሲፈናቀል ከፈፃሚው ስርአት ጋር በመተሻሸት ሃይማኖታዊም ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ግዴታቸውን ዘንግተዋል:: የህዝብን ህይወት ከመታደግ ይልቅ የግል ክብራቸውንና ጥቅማቸውን አስቀድመዋል::የየእምነቱ መርሆ ስለሰው ልጆች ፍቅር ሰላምና አንድነት ከፈጣሪያቸውም ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚያበስር ሆኖ ሳለ የሃይማኖት መሪዎች ግን በጎሳ ገመድ ተተብትበው ጎሰኛ ስርአትን በማጀብ ህዝቡን ለእልቂት አገርን ለመፍረስ አሳልፈው ሰጥተውታል::ከዚህ የበለጠ ፀረ ፈጣሪነት ከዬት ይመጣል? ለውጥ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ በእምነቱና በባህሉም ዘርፍ ጭምር ላይ መካሄድ አለበት ::ስርነቀል ለውጡ ማለትም ያ ነው::እምነት በህንፃ ጋጋታ ሊሸፈን አይገባውም::ህዝብ ከእርሃብና ከበሽታ እንዲሁም ከድህነት ሲላቀቅ የሚያካሂዳቸው የግንባታ ስራዎች በአሁኑ ሁኔታ ህዝብ በርሃብና በሽታ እንዲሁም በጎሳ ማንነቱ በሚጨፈጨፍበትና የአገር ህልውና ባልተረጋገጠበት የተገነቡት በሚፈራርሱበት ዘመን ሊከናወኑ አይገባቸውም ቅደም ተከተል ያገናዘበ ግንባታ ሊሆን ይገባል::ሃይማኖታዊ ሰብአዊና ብሄራዊ :አደራቸውን ያልተወጡ የእምነት አባቶችን የሚጠይቅና የሚገስፅ ምእመና ከሌለ ችግሩና ውድቀቱ የከፋ ይሆናል::የስርአት አገልጋይና ምርኮኛ የሆነ አማኝ የክርስቶስን አስተምሮ የካደ ነው::ክርስቶስ ለሁሉም የሰው ልጆች የመጣ እንጂ የጎሰኝነትን አስተምሮ የሰበከ አይደለም::ጎሰኝነት ለስልጣንና ለሃብት መራኮት የሰይጣን ተግባር ነው::መወገዝ አለበት::

  2. አገሬ አዲስ ጸሃፊው ደጋግሞ እንደገለጸልን ተቃውሞውና የነገሩ ማጠንጠኛ ኮሜዲያን እሸቱ ፈንድ ሬይዝ አድርጎ በውጭ ሃገር ስላስገነባው ገዳም መስለኝ ፡፡ አንድ ግለሰብ ኢኒሼቲቩን ወስዶ እንዲህ ያለ ታላቅ ሃውልት በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ማድረጉ ምስጋና እንጅ ወቀሳ የሚገባው አይመስለኝም፡፡ አገሬ አዲስ እንደገለጽከው የሃይማኖት አባቶች ላይ በእርግጥም ጥያቄ አለ ዋናው ጳጳስ አቡነ ማትያስ አማራው ሲበለት፤ሲቀሰት፤ሲገደል ዝም ብለው በውስጥ መስመርና በገሃድ ለአሜሪካን ኤምባሲም ኡኡ ይሉ የነበረው የትግራይ ነብሰ ገዳዮች የትግራይ አራጆች ተነኩብን ብለው ነበር፡፡ ደቀ መዝሙሩ እንደ መምህሩ እንደሚባለው ተከታዮቻቸውም የሃይማኖት ልልነት ይታይባቸዋል፡፡” ጁዋር መሃመድን የማትቀበል ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ብዬ አልጠራም” ያለውን ቀሲስ(አቶ) በላይን ትልቅ ወምበር ሰጥታ ቤትክርስቲያኑን ከውስጥ ታስንጣለች እነ ሳርዮስና ተከታዮቹን ሳልረሳ ማለት ነው፡፡ በተረፈ ክርስቶስ የበጎች ግርግም ነው የተወለደው እነዚህም አባቶች ያንን ተከትለው ደበሎ ለብሰው ይኑሩ የምትለውም ትንሽ ተለጠጠ ባይሆን ለክፉ ነገር ምሳሌ አይሁኑን ከስጋዊው አለም ለነብሳቸው ያድሉ ብንል መልካም ነው፡፡እንደው እዚህ ላይ አንድ ነገር ባክልበት፡፡ ሉዊስ ፋራቃን ወደ ሳውዲ አረቢያ ተጋብዞ ምግብ ያቀርቡለታል ምግቡ ቀርቦ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ሹካ/ማንኪያ/ቢላዋ የለም እግዜር ያሳይህ አሜሪካዊ ነው፡፡ ቢበዘበት ቢጠይቃቸው “ወንድም ፋራቃን በእጅህ ብላ በረከት ታገኛለህ ነብዩም በእጁ ነው ሲበላ የኖረው” የሚል መልስ ይሰጡታል፡፡ መቼም ፋራቃን መልስ የሚቸግረው ሰው አይደለም ፈጠን ብሎ ታዲያ አንተ ለምን በ7 ሲሪየስ ማርቸዲስ ትሄዳለህ እንደ ነብዩ ለምን በግመል አልሄድክም በረከት እንድታገኝ ብሎ ይመልስለታል፡፡ ታዲያ የአባቶቹንም ጉዳይ አትታከሙ ጫካ ዳገት ቁልቁለቱን በእግራችሁ ሂዱ ማለት ባይቻልም ልክ አብጁለት ለተከታያችሁ ምሳሌ ሁኑ ስትመለኩሱ ሙታችኋልና ግዴታችሁ ተወጡ ማለት በቂ ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም የችግር ናፋቂዎች ሳንሆን የመፍትሄ አፍላቂዎች እንሁን፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ በክፉ ገዥዎቻ ላይ ወድቃለች ጸሎት ማድረግ መስከን ለፍትህ ድምጽ ማሰማት መልካም ይመስለኛል፡፡ በየጥጉ ቁጭ ብሎ እስከዛሬ ለትግሉ አንድ ሳር ያላዋጣ ሁሉ አትርሱኝ አይነት ጽሁፍም መልካም አይደለም ሰላም ሁኑ አንተም ጸሃፊውም፡፡

  3. በውጭ አገር ገዳም ለማሰራት ዝና እና ስም ለማስምዝገብ የሚሮጡ መንኮሳት ዶንኪ በሚባል ይቱብ ገንዘ ኢሰበስቡ እየታየ ነው። በመሆኑም ገደም ከመገንባቱ በፊት አንድ ቤተ ክርስቲያን በገዳምነት የሚሰየመው ወይም ገዳም የሚሆነ እንዴት ነው የሚልው ጥያቄ መልስ ማግኘ ያለበት ይመስለኛል። ስለሆነም በበኩሌ እንደምራዳው በአንድ ቤተክርስቲያን የተለያዩ ታምራት የታየበት እና የተከሰተበት፤ የበቁ አባቶች ወይም ባህታውያን እና ባህታዊት ለየብቻ የሚኖሩበት እና የሚጸልዩበት ደብር መሆኑ ሲረጋገጥቤተ ክርስቲያኑ ወይም ደብሩ በገዳምነት ይሰየማል።እንዲህም ስለገዳም አመሰራረት በሊቃውንቱ ዘንድ አያሌ የካበተ ትንታኔ እና ትምህርት በተለያዩ መጻህፍቶች በሰፊው ይገኛሉ። ገዳም የሚመሰረተው ከዚህ አኳያ ከሆነ ዛሬ በውጭ አገር ገዳም እንገባ በማለት በዶንኪ ዩትብ የሚለፈፈው የአህያ ፋንድያ እና የፍየል ኮረኮር ከሚለቀምበት ቦታ መሆኑ ነው። ሌላ የምሰጋበት ቢኖር መሬት ለመሬት በቧንቧ ውሃ በመሰብ ከአንድ አመት በኋላ ታምር ተከሰተ ወይ ታየ በገዳሙ ጸበል ፈለቀ በማለት የዋሁን ህዝብ የማተለሉ ሥራ እንዳይቀል ነው።ስልሆነም ከላይ T.G. ወይም ጠገና ጎሹ በመደጋገም የሚያስገነዝበው ትክክል እንጄ የሚያስወቅስ አይደለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share