በትምህርት ዕድገትና የማስፋፋት ሽፋን ላይ የግል ትምህርት ቤቶች ያላቸው ሚና ከምንም በላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ባልተናነሰ ምናልባትም በበለጠ የግል ትምህርት ቤቶች እጅግ ብዙ ሽህ ተማሪዎችን በየዓመቱ መጀመሪያ እየተቀበሉ ከሙኣለ ሕጻናት ጀምሮ ያስተምራሉ፡፡ ይህን አገልግሎታቸውንም መንግሥትም ሆነ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ አሳምረው ያውቃሉ፡፡
ይሁንና ሰሞኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች፣ የወላጅ ኮሚቴዎችና የትምህርት ቤት አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት አንድ አስደንጋጭ መመርያ መውጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የግል ትምህርት ቤቶች እስከመዘጋት ሊያደርስ የሚችል ተግዳሮት ሊገጥማቸው እንደሚችል በስብሰባው የተካፈሉና ስማቸው እንዲነገር ያልፈለጉ የግል ትምህርት ቤት ተወካይ ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፡ ቀደም ሲል ክፍያን በሚመለከት የነበረው አሠራር ወላጆችና የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች በመመካከር ስምምነት በሚደርሱበትናየትምህርት ቢሮ ተወካዮች በሚገኙበት በሚደረግ የጋራ ግንዛቤ የመቶኛ ሥሌት በያመቱ ይጨመር ነበር፡፡ አሁን ግን ባልተለመደ ሁኔታ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በተገኙበትና ከከተማው መስተዳድር አዲስ የወጣ ሕግ ነው በሚል ለቀጣዩ ዓመት ወላጆችና ትምህርት ቤቶች ከተስማሙት ውጪ ከ45% በላይ መጨመር እንደማይቻል ውሳኔ ከመተላለፉ ተጨማሪ ማንኛውም የግል ትምህርት ቤት ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ጭማሪ ማድረግ እንደማይፈቀድላቸው ታዟል፡፡
ስብሰባውን የተካፈሉት የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶችና ተወካዮች ይህን አዲስ አሠራር በአግራሞት ካዳመጡ በኋላ ሲጀመር የወላጆችና የትምህርት ቤቶች ስምምነት በቂ ሆኖ ሳለ በዚህ ተራ የግል ጉዳይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አላስፈላጊ መሆኑን ገልጸው የተደነገገው ጭማሬ ከወቅቱ ገበያ ጋር ፈጽሞ የማይሄድና ለሦስት ዓመታት እንዳይጨመር መታገዱም ፍትኃዊ እንዳልሆነ ለማስረዳት ቢሞክሩም የመስተዳድሩ የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በከፍተኛ የዕብሪትና ንቀት መንፈስ ተወጥረው ጉዳዩ ለውጥ እንደማይኖረው አሣውቀዋል፡፡ ይህ አዲስ የተባለ አሠራር ገቢራዊ ከሆነ ብዙ ትምህርት ቤቶች ሊዘጉ እንደሚችሉ በስብሰባው ተንጸባርቋል፡፡ የኑሮ ውድነቱ በየቀኑ ሊባል በሚችል ደረጃ እየናረ ባለበትና የቤት ኪራይና የሥራ ማስኬጃ ወጪው (የሠራተኛ ደሞዝ፣ የመማር ማስተማሩን ክንውን የሚያቀላጥፉ ቁሳ ቁሶችን መግዣ፣ ወዘተ.) በየጊዜው እየጨመረ በሚሄድበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ፍጹም የማንአለብኝነት ሥራ መሆኑን ተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል፡፡ ይሄ ዓይነቱ አካሄድ በተዛዋዋሪ “ትምህርት ቤቶቻችሁን ዝጉና ተማሪዎችን በትኑ” እንደማለት መሆኑንም ተሰብሳቢዎቹ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
በተለይም የመምህራንና ሠራተኞች ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ከኑሮ ውድነቱ በተገናዘበ መልኩ በየዓመቱ የሚሻሻልና የሚያድግ መሆኑ እየታወቀ በየጊዜው የሚከሰተውም የዕቃዎች ዋጋ የዋጋ ንረትም ይህንን መቋቋም እንደማይችል እየታወቀ ትምህርት ቤቶችን በፍርደ ገምድልነት የግል ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት የሚስገድደው ውሳኔ ተግባራዊ ሲሆን ከፍተኛ መናጋት የሚፈጥር፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን መልካም ግንኙነት የሚሸረሽርና ቅራኔን በመፍጠር መንግሥትንና ሕዝብን ለማራራቅ ከመፈለግ የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር የነበረው አሠራር ቢቀጥል ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ እንደሌለ በስብሰባው የተገኙና በአዲሱ አሠራር ክፉኛ የተበሳጩ የግል ትምህርት ቤቶች ባለቤቶችና የትምህርት አመራሮች ገልጸዋል፡፡