በአገራችን ምድር ለተፈጠረውና ለሚፈጠረው ችግርና ወንጀል ዋናው ምክንያት ህገ-መንግስቱ ነው ወይ? የህገ-መንግስቱ መለወጥ የህብረተሰባችንን መጠነ-ሰፊ ችግር 

ሊፈታው ይችላል ወይ?  ለዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ የተሰጠ መልስ!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                        ግንቦት 29 2023

ዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ እየደጋገመ የሚያነሳውና የሚጽፈው ነገር አለ። ይኸውም የህገ-መንግስቱ መለወጥ አስፈላጊና፣ ያሉንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የስነ-ልቦና፣ የባህልና የኢኮሎጂ ቀውሶችን በሙሉ እንደሚፈታ አድርጎ ነው። በዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ ዕምነት ዛሬ አገራችን ላለችበት ቀውስ ዋናውም መነሻና ምንጭ ህገ-መንግስቱ ነው። ይህንንም ሃሳብ ልዑል አስፋው-ወሰን አስራተም ይጋሩታል። በእነዚህ ሰዎችም ዕምነት ህገ-መንግስቱ´ ከተሻሻለ ችግሮቹ መፈታታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎችም ባህርይ አውቶማቲካሊ ሊለወጥ ይችላል።  ይህ ግምት ግን የእነሶክራተስንም ሆነ በኋላ ላይ የተነሱትን የእነ-ላይብኒዝን፣ ካንትንና የሄገልን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ የሚፃረር ነው። በህብረተሰብ ታሪክ ግንባታ ውስጥ ያልተረጋገጠ ነው። እነሶክራተስና ፕሌቶ፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ እነ ዴካም ሆነ የጀርመን አይዲያሊስቶች እንደሚያስተምሩን የሰው ልጅ ችግር ሁሉ የማሰብ ችግር ወይንም ትክክለኛ ዕውቀት አለመኖር ነው ይሉናል። በሌላ አነጋገር፣ በተሳሳተ ዕውቀት ጭንቅላቱ የተቀረጸ ሰው ነገሮችን ሁሉ በጭንቅላታቸው እያቆመ ነው የሚመለከተውና፣ ከዚያ በመነሳት የራሱን ግምት ሊሰጥ የሚችለው። ስለሆነም ከጥንቱ ግሪክ ጀምሮ እስከ ማዕከለኛው አውሮፓ ክፍለ-ዘመን ድረስ የነበሩት በአገዛዞች የተቀሰቀሱት፣ ሃይማኖትንና ጎሳን አሳበው የተደረጉት ጦርነቶች በሙሉ ከአገዛዞች አርቆ አስተሳሰብ ጉድለት ነው ይሉናል። ለዚህ ነው እነ ሶክራተስና ፕሌቶ ዲያሌክቲካዊ የጥያቄ ዘዴዎችን በመፍጠር የሰው ልጅ ራሱን እንዲጠይቅ በማድረግ መልስ እንዲፈልግ መንገዱን ለማሳየት የሞከሩት። ከዚህ በመነሳትና ፍልስፍናን መሰረት በማድረግ ነው ዕውቀት የተባለው፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ማቴማቲክስ፣ በተለይም እንደ ጄኦሜትሪ የመሳሰሉት በሙሉ በሰው የማሰብ  ኃይል ሊፈጠሩ የቻሉት። በጥንታዊ ግሪክ ዘመን፣ እነ ሶክራተስና ፕሌቶ በህይወት በነበሩበት ዘመን ይታገሉ የነበረው የህገ-መንግስት ለውጥ ይደረግ ብለው በመቀስቀስ ሳይሆን፣ ጠቅላላው ዕውቀት የሚባለውና የገዢ መደቦች ይመሩበት የነበረው የተሳሳተ ዕውቀት፣ በመሰረቱ በስግብግብነትና ስልጣን ላይ( Power and Gred) ለመውጣት የተመሰረተው በአዲስ መልክ መጻፍና ጭንቅላቱ በሶፊስታዊ አስተሳሰብ ያልተመረዘ አዲስ ትውልድ መፈጠር አለበት በማለት ነው ያስተምሩት የነበረው። በሌላ አነጋገር፣ ህገ-መንግስት እንኳ ቢለወጥ ህገ-መንግስቱን ያጸደቁትና ህገ-መንግስትን ተገን አድርገው ስልጣንን በመያዝ ስንትና ስንት ወንጀሎች የፈጸሙት ህገ-መንግስት ስለተለወጠ እነዚህ ሰዎች እንደ አዲስ ሰዎች ሆነው ይፈጠራሉ ሊፈተሩ አይችሉም። ማንም ሰው እንደሚያውቀው ጭንቅላታችን እንደ ሶፍትዌር ነው።  ጭንቅላት በአንድ አስተሳሰብ ከተቀረጸና የሰው ልጅ ዕድሜም የተወሰነ ዕድሜን ካሳለፈ በኋላ ቀድሞውኑ በተቀረጸበት አስተሳስቡ ነው የሚገፋበት። ይህንን አስተሳሰብ እነ ፍሮይድ ይጋሩታል። ስለሆነም በሳይንስ፣ በማቲማቲክስና በፍልስፍና ምሁሩ በላይብኒዝ ዕምነት መሰረት የህግ መለወጥ በመሰረቱ የሰዎችን ባህርይና ድርጊታቸውን በፍጹም ሊቀይረው አይችልም። በሌላ ወገን የምንጠቀምባቸውን ሶፍትዌሮች በየጊዜው ማሻሻል ይቻላል፤ ይሻሻሉም። የሚያስቸግረው ግን የሰውን ልጅ ጭንቅላት መቀየር ወይም ማሻሻል ነው፤ በቀላሉ አፕዴት ሊደረግ የሚችል አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አድርባይነት ! የሞራል ዝቅጠት : የለውጥ መርገም ! /(ኢዜማ?) - ከቴዎድሮስ ሐይሌ

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአገራችን ምደር ያለው ትልቁ ችግርና የችግሮቹ ምንጮች አብዛኛዎቹ ምሁራን ጭንቅላታቸው ኢምፔሪሲዝም በመባል የሰውን ጭንቅላት በሚበታትንና በሚበርዝ ዕውቀት መሰል የተቀረጸ በመሆኑ ነው። በዚህ ዐይነቱ ቁንጽል አስተሳሰብ መንፈሱ የተቀረጸ ግለሰብ የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን ግንባታ አስቸጋሪነት በፍጹም ሊረዳ አይችልም። በታሪክ ውስጥ የተሰሩ መልካም ነገሮችን ሁሉ በመካድ አንድን አገር በጨቋኞችና በተጨቋኞች መሀከል ብቻ የሚገለጽና፣ መፍትሄውም ጨቋኝ የሚባለው መደብ ወይም ብሄረሰብ እንዳለ ሲወገድ ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ ነው። መንፈሳቸው በተሳሳተ ትረካ የተቀረጸ ሰዎች ከማንኛውም ዕውቀት ከሚባላው፣ ከፍልስፍና፣ ከተፈጥሮ ሳይንስና ከሶስይሎጂ፣ ህብረተሰብአዊ ትችትን ካዘሉ ሊትረተሮች የራቁ ስለሆነ አንድ ጊዜ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ያንኑ የተሳሳተ ትረካቸውን በማውራት ስልጣንን ላለማጣት የማይሰሩት ወንጀል የለም።

የግሪኩንም ሆነ በኋላ ላይ የተነሳውን በካፒታሊዝም ላይ የተመሰረተውን የምዕራቡን ዓለም የህብረተሰብ ታሪክ በደንብ የተከታተለ ሰው የሚረዳው ነገሮች በሙሉ ልክ ዶ/ር ኪዳነ አለማየሁ በቀላሉ እንዳስቀመጠው የሚታዩ አይደሉም። ስንትና ስንት ነገሮች ከተፈጠሩም በኋላ ነው በተለይም የአውሮፓ ማህበረሰብ በጦርነት ዓለም ውስጥ እንዲዘፍቅ የተገደደው። ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እንደ አጋጣሚ በመሆን የአውሮፓ ማህበረሰብ ሶሶት ጭንቅላትን የሚያድሱ ሂደቶችን በማለፍ ነው ዛሬ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የበቃው። እነዚህም ሪናሳንስ፣ ሪፎርሜሽና ኢንላይተንሜንት በመባል የሚታወቁ ናቸው። እነጆን ሎኮ የህግን-የበላይነት ከጻፉና ካስተማሩም በኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሰላሳኛው ዓመት ጦርነት፣ ሌሎች አነስተኛ ጦርነቶች፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ተካሂደዋል። የታወቀው የጀርመን ፈላስፋና የድራማ ሰው ፍሪድሪሽ ሺለር እንደሚያስተምረን፣ የዲሞክራሲን ጽንሰ-ሃሳብ ከአሪስቶተለስ ጀምሮ ሰምንተናል። ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላም ባርቤሪያን ሆነን ቀርተናል ይላል። በሁለት ሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥም የሰው ልጅ ከተማዎችን ገንብቷል፤ የዕደ-ጥበብ ስራን አዳብሯል፣ ከንግድ ጋርም ተዋውቋል፤ ይህንና ግን ከአረመኔያዊ ባህርዩ በፍጹም አልተላቀቀም ይለናል። በእሱም ዕምነት የዚህ ሁሉ ችግር ዋናውም ምክንያት ልብና መንፈስ ስላልተገኛኑና፣ መንፈስም በጥሩ ዕውቀት ስላልተቀረጸ ነው ይላል።  ይህ ሁሉ የተፈጠረው እነ ጋሊሌዮ፣ እነ ዴካ፣ ኒውተንና ሌሎች ሳይንቲስቶች ተፈጥሮንና ኮስሞስን ተመራምረው ለሰው ልጅ የሚሆን ሳይንሳዊ ግኝቶችን ካፈለቁ በኋላ ነው። የኋላ ኋላ ላይ የአውሮፓ የገዢ መደቦች ህዝቦቻቸውን በጦርነት ካደቀቁ በኋላ ያላቸው አማራጭ የህግ-የበላይነትን በየአገሮቻቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ እኛ የሰለጠን ነን በማለት ሌሎች አገሮችን የቅኝ ግዛታቸው በማድረግ ህብረተሰብአዊ ሂደታቸውን ለማጨናገፍ ችለዋል። እስካሁንም ድረስ በውክልና ጦርነት ርስ-በርስ ያፋጁናል። የበላይነታቸውን ተገን በማድረግ በዕዳ በመተብተብ ከፍተኛ ቀውስ እንድንገባ አድርገውናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች - ይህ ነው አቋማችን!

የዶ/ር ኪዳነ አለማየሁንና የሌሎችንም የህገ-መንግስት መለወጥ ቅስቀሳ የምንቀበል ከሆነ ኃይላችንን በሙሉ በዚህ ላይ ብቻ እንድናውል እንገደዳለን። በነገራችን ላይ ህገ-መንግስቱ ላይ ሰውን ግደል፣ አገር በታትን፣ ሀብት ዝረፍ፣ የማይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል አንዱን አበልጽግ፣ ሰፊውን ህዝብ ደግሞ ደሃ አድርገው የሚል አንቀጽ የለም፤  የአገርንም ሀብት ለውጭ ከበርቴዎች… ወዘተ ሽጥ የሚል አንቀጽ በፍጹም የለበትም። 70% በመቶ የሚሆነው ህገ-መንግስት ጉድለት የለበትም። አንቀጽ 39 የሚለው ነው የሰውን ትኩረት የሳበው። ይህ አንቀጽ ቢነሳ እንኳ ጭንቅላታቸው በተሳሳተ ትረካ የተገነባና ስንትና ስንት ወንጀሎች የሰሩ ሰዎች ስልጣን ላይ እስካሉ፣ ወይም የስልጣን ተካፋይ እስከሆኑ ድረስ የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች ይፈታሉ´ ማለት አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ በሚገባ የተዘጋጀና የተገለጸለት ኃይል እንደሌለ ይገባኛል። ይሁንና ግን እነ አቢይና ሺመልስ አብዲሳ፣ እንዲሁም ወያኔዎች ከውጭ ኃይል ጋር በማበርና ዕርዳታ በማግኘት የሚያደርሱት መጠነ-ሰፊ ጥቃትና ወንጀል የግዴታ መገታትና መንፈሳቸው ያልተበረዙ ሰዎች ስልጣንን መያዝ አለባቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገራችን ምድር እስካሁን ድረስ የሚሰጡ የትምህርት ዐይነቶች የቱን ያህል ለጥፋት እንደዳረጉን በማጥናት ለአዲሱ ትውልድ የሚስማማና ጭንቅላትን ብሩህ የሚያደርግ ትምህርት ማውጣት ያስፈልጋል። በዚያው ሂደት ውስጥ ህገ-መንግስቱንም ማሻሻልና፣ ህገ-መንግስቱን ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የሚያደርጉ የሰለጠኑ ሰዎች ማፍራት ያስፈልጋል። በአዲስ መልክም የሚጻፈው ህገ-መንግስት ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ ወንጀል የሰሩ ሰዎችን በምንም ዐይነት ከተጠያቂነት ሊያድናቸው አይችልም። አዲስ በሚጻፈውና በሚጸድቀው ህገ-መንግስትና ሌሎች ባሉ ህጎች አማካይነት በህዝባችንና በአገራችን ላይ ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው።  ባጭሩ የአገራችን ችግር ህገ-መንግስትን በመለወጥ የሚፈታ ሳይሆን፣ የጭንቅላት ችግር ነው። ሎጂክንና ዲያሌክቲክን ለመረዳት የማይችል፣ ለማዳመጥና ለመግባባት የማይፈልግ፣ ቶለራንስ የሚባልን ነገር የማያውቅ የህብረተስብ ኃይል እስካለ ድረስ ህገ-መንግስት ተለወጠ አልተለወጠ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ሰለሆነም በዚህ ዐይነቱ ፋይዳ-ቢስ ነገር ላይ ጊዜያችንን ባናባክን በጣም ጥሩ ነው። መልካም ግንዛቤ!!

 

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

 

 

4 Comments

  1. ዶር ፍቃዱ ባነሱት እርእስ ላይ ልጨምር የምወደው ህገ መንግስት ለአንድ አገርና ህዝብ ጉዞ የሚቀየስበትና ዜጋ ሁሉ በእኩልነት የኔ ነው ብሎ የሚቀብለው መመሪያ ወይም መተዳደሪያ ደንብ ነው::ህገመንግትን በህዝብ በችሎታቸው የተመረጡ ባለሙያዎችና ተወካዮች አርቅቀው የሚያቀርቡትና በህዝቡ ተሳትፎ ታርሞ ሁሉም አምኖበት በመቀበል በስራ ላይ የሚውል ሲሆን ቅቡልነት ይኖረዋል::እርግጥ ነው ህገመንግስት ከጊዜ ጋር እያደገና እዬሰፋ ያልነበሩ አንቀፆችን እያካተተ ይሄዳል::በሌላም ጎኑ ከጊዜው ጋር የማይሄዱና መቀዬርና ከነጭራሹ መፋቅ ያለባቸው እንቀፆች ይኖራሉ::ህገ መንግስት የህዝቡ መብት እንዲከበር ብቻም ሳይሆን ህዝቡም ለህጉ እንዲገዛ የውዴታ ግዴታ አለበት::ህዝብ በአገሩ ጉዳይ ላይ የመወሰን በሰላም የመኖር መብቱ በማንም እንዳይደፈር የሚከላከልለት የጋራ ንብረቱ ከሆነ ስልጣን በወጣ ቡድን
    ወይም በአገዛዙ ወይም ስልጣን ላይ ባሉ ቡድኖች ፍላጎትና ባለቤትነት የሚያገለግል አይሆንም::በስልጣን ላይ ባለ ቡድን በፈለገው መልክ ከረቀቀና ስራ ላይ ከዋለ ያ አስገዳጅ ትእዛዝ ከመሆን የዘለለ ትርጉም አይኖረውም::
    ህገመንግስት አልፎ አልፎ የአንድን ስርአት ምንነት በግልፅ አያሳይም እንደውም የመሸፈኛ ጭንብል ይሆናል::በወረቀት ላይ ብዙ ውብና ማራኪ አንቀፆች ቢኖሩ እነዚያን በተግባር ለማዋል ካልተቻለ ህገመንግስት መኖሩ ይጎዳል እንጂ አይጥቅምም ::
    ወደ አገራችን ስንመለስ ስርዓቱ የቆመበት ዋና መሰረቱ በጎሳ ህሳቤ ላይ በመሆኑ ህጉንም ያረቀቀው በዚያው ህሳቤ ነው::አንቀፅ ቢጨመር ቢቀነስ ለውጥ አይኖርም::ከስር መሰረቱ ህዝብ በተሳተፈበትና ተቀብሎ ባፀደቀው ከጎሰኝነት የፀዳ ህዝባዊና አገራዊ ክብርን በሚያስከብር ህግ መቀዬር አለበት::
    አንቀፅ 39ን ቦጭቆ በማውጣት የህዝቡንና የአገር ደህንነትና ሰላም ይረጋገጣል ማለት አይደለም::ከአንቀፅ 39 የከፉ አንቀፆችንና ንኡስ አንቀፆችን የተሸከመ የጥፋት ሰነድ ነው::ለመልካም ህገ መንግስት የህብረተሰቡ አስተሳሰብና አመለካከት ወሳኝነው::ህዝቡ ግንዛቤ ከሌለው ለፋሽሽቶችና ለጎሰኞች ለወራሪዎችና ለዘራፊዎች የተጋለጠ ይሆናል::በማር የተለወሰ መርዝ ሲቀርብለት ሳይጠራጠር ወስዶ እራሱንና አገሩን ለአደጋ ያጋልጣል::ጠላት ቁጥጥሩን የሚያጠብቀው ምን ጊዜም የህዝቡን ስሜትና ፍላጎት እየተጠቀመ ነው::የጎሰኞቹም ስርአት እንዲሁ ተቃውሞ ሲበረታበት በትንሽ ሽርፍራፊ ለውጥ ስርዓቱን ዘለአለማዊ ለማድረግ ይሞክራል::
    በተጨማሪ አብይ ይውረድ ሲባል ይሰማል ::ችግሩ የአንድ ግለሰብ ሳይሆን መዋቅራዊና ስርዓታዊ በመሆኑ በግለሰቡ መነሳት ብቻ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም::እሱ ወርዶ ሌላው ጎሰኛ ቢተካ ለውጥ አይመጣም ቢመጣ የጅራፍ ለውጥ ነው::የሚያስፈልገው ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ነው::ቅቡልነት ያለው አገር ወዳድና ህዝብ አክባሪ ልዑላዊነትን የሚያስከብር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲሰፍን እውነትም ለውጥ መጣ ያሰኛል::

  2. የአብይ አህመድ ጨካኝ ዘረኛ ነፍሰገዳዪች የሚሰሩትን ወንጀክ ግድያ ማፈናቀል የምታቀርቡ ሁሉ በምስል በእንግሊዝኛ በማቀረብ ለመላው አለም የሰው መብት አስከባሪና የብልጽግናውን ገፈኛ መንግስት መጽዋቾች በማሳወቅ መጨፍጨፊያው ይቆም ዘንድ ለማስተላለፍ ተባበሩ:: ሁሉም በትዊት በኢንስትግራም በፌስ ቡል በዩቱብ በቲክቶክ ያሰራጭ ለሚጨፈጨፍ ወገናችን ቢያንስ ድምጽ እንሁን!

  3. ህገመንግስቱ ከብዙ ችግራችን አንድ እንጂ በራሱ ችግር አይደለም። ላስረዳ። ወያኔ በአዲስ አበባ ሻቢያ በአስመራ አለቃ ከሆኑ ወዲህ የዘርና የቋንቋ የክልል ጉዳይ ንረው ሊታረሙ ወደማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል። በተለይም እነዚህ ሁለት አጥፊ ሃይሎች ለህዝባቸው የጋቱት የተረት ተረት ፓለቲካ አማራ የችግርህ ሁሉ ምንጭ ነው በተቻለ ሁሉ መጥፋት አለበት በማለት ነው። ይህን የክፋት ኮሮጆ ተቀብሎ አሁን በወረፋው በዚህ ህዝብ ላይ ግፍን የሚፈጽመው የአብይ መንግስት የክፋቱን ልክ ጣራ ላይ አውጥቶታል። ሶስት ጊዜ ወረራ ፈጽሞ አለቅጥ የተደቆሰውን ወያኔ አሁን ነፍስ ዘርቶ እንደገና እንዲያገግም የሚሰራው የብልጽግናው መንግስት የሚይዘውን የሚጨብጠውን ያጣ በደንበር ገተር የሚጓዝ ከቀን ቀን ነገሮች እየከረሩና እየጨለሙ የሄድበት ድርጅት ነው። የኦሮሞ ባለጊዜ ፓለቲከኞች በሰው እንባ ልክ እንደ ወያኔ የሚስቁ፤ በወያኔ የመከራ አሰራር ልክ የሚራመድ ባጭሩ ከወያኔ ቢከፉ እንጂ የሚሻሉበት አንድም መንገድ የለም። አውቃለሁ ቃላቸው ማር ነው። ለነገሩ ኢትዮጵያ ሱሴ ናት ተብለን አልነበር እንዴ? ያ ቀርቶ አሁን ሌላ ዘፈን መጥቶ። የአፍሪቃውያን ችግር ይበልጡ እኛው ራሳችን የምናዘንበው የመከራ ዶፍ ነው። የእህል ክምር አቃጥሎ ተራብኩ የሚሉ ጉዶች ባሉበት ሃገር ላይ ህገመንግስት ተቀየረ አልተቀየረ የሚያከብረው ሰው አይኖርም። መቀየር ያለበት የሰው አስተሳሰብና እይታ ከድንጋይ ዘመን እሳቤ መውጣቱ ነው። መርጦ አልቃሽ፤ መርጦ ገዳይ፤ መርጦ አፈናቃይና ገራፊ ባለበት የዘረኞች ፓለቲካ ውስጥ የሰዎች እይታ አህጉራዊ አልፎ ተርፎም ዓለም አቀፋዊ ካልሆነ በስተቀር የሃገሮች ህግና ደንብ መለወጥ ወይም መሻሻል ብቻውን ለህዝባችን ፋይዳ አያመጣም።
    አሁን አንዴ ቻይና አንዴ ሩሲያ የሚመላለሱት የኤርትራው መሪ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ተጋፍጠው የሚያተርፉት ከምሲን ነገር አይኖርም። ግን በዚህም በዚያም አሳበው ልክ ለዘመናት እንዳደርጉት ሁሉ እርስ በእርሳችን እንድንላተም ዛሬም ነጩ ዓለም እንደማይተኛ ሊገባን ይገባል። አሜሪካ በኤርትራ ላይ ያላት ጥላቻና ጫና መሰረቱ የሚጋልቡት መሪ አለማግኘታቸው ነው። ሩሲያን ቻይናም የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ እንጂ በምንም ሂሳብ ለኤርትራ ያኔም አላሰቡም አሁንም አያስቡም። ምዕራባዊያን መንግስታትን ለማሽመድመድ ስልታቸው እልፍ ነው። ባጭሩ ከየዓለማቱ ወደ ሃበሻ ምድር (ኢትዮጵያ/ኤርትራ) የሚላከውን ገንዘብ ቢያግድ ወገኖች ይራባሉ መንግስታትም ይጎዳሉ። ስለዚህ የኤርትራው መሪ በቻይና የተደረገላቸው አቀባበልና የሩሲያው ቆይታቸውም ምሥራቅ አፍሪቃን ከረሃብና ከቸንፈር የሚያድን ነገር ሳይሆን ቻይናና ሩሲያ ወደ ምጽዋና አሰብ ወደብ ብቅ በማለት እኛን እዪን ለማለት የተለሙት የፓለቲካ እቅድ ነው። ታዲያ ይህን ከኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሻሻል ጋር ምን ያገናኘዋል ለምትሉ መልሱ ይህ ነው። የወያኔ መሪ ዶ/ር ደብረጽዪን በቶሎ ምርጫ ይሁን እያለ ሲደነፋ በቅርቡ በመቀሌና በሌሎችም አካባቢዎች በተደረገ ስብሰባ ላይ አቶ ጌታቸው ሲናገር ወራሪ ሃይላት ኤርትራና አማራ ከትግራይ መሬት እንዲወጡ እናረጋለን፤ ሲል አልፎ አልፎም ቢሆን በዚህም በዚያም ከሞት ተርፈው የሚደሰኩሩት የወያኔ ካድሬዎችም ዳግም ጦርነትን በሚፈልግ አይነት መንገድ በገነፈ ስሜት ሲናገሩ ማየትና መስማት የፍርድን መዛባት ያለቅጥ ያሳያል። እነዚህ ሰዎች እልፍ የትግራይን ልጅ አስጨርሰውና ሌሎችን ጨርሰው ዛሬ ላይ ቆመው ጄ/ምግበ፤ ጄ/ጻድቃን ወዘተ እያሉ መደስኮር ምንኛ ህይወትን መራራ ያደርጋል። ለዚህ ነው የኤርትራው መሪም እስከ አፍንጫው ይታጠቃል ወያኔም በዚህም በዚያም አሜሪካኖች ያስታጥኩታል ውጊያው ቀጣይ እንጂ የሚቆም አይደለም። ለምሳሌ ወያኔ አስረከበ የተባለውን ቀላልና ከባድ መሳሪያ ለተመለከተ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የተሰሩ ወያኔ ስልጣን ላይ እያለ ከማህል ሃገር ተጓጉዘው በየስፍራው ተቀብረው የነበሩ፤ ጭራሽ መስራት የማይችሉ ውዳቂ ልቅምቃሚዎችን እንደሆነ ወታደራዊ የመሳሪያ እውቀት ያለው በቀላሉ ሊረዳው ይችላል። አንድ የታዛቢ ቡድን አባል በግል እንዳለው “የተረከብናቸው መሳሪያዎች ሁሉ የተበላሹ፤ ያረጅና በሶስቱም ግጭቶች ያልተጠቀሙባቸው ናቸው” ብሏል። የአፍሪቃ ህብረት ተወካይ ” ከ 80-90%” መሳሪያ ተረክበናል የሚለውም ያለምንም የሂሳብ ስሌት ወያኔ እንዲህ በል ያለውን ተከትሎ ብቻ ነው። ይህና ሌላውም የዘርና የቋንቋ እንዲሁም የክልል ፓለቲካ ሸፍጥ መገዳደላችን መልክና ዓመሉን እየቀየረ እንዲቀጥል ያደርገዋል።
    ሌላው የተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ድርጅቶች ህብረትና ዘላቂነት አለመኖር የሚያሳየን የሰውን የመጠራጠርና ያለመተማመን የቀረበ መስሎ የተራራቀ አመለካከት ነው። ግንቦት 7፤ ኢዜማ፤ ሌሎችም በምድሪቱ በክልል፤ በዘር፤ በቋንቋና በክልል የተዋቀሩ ሁሉ ዘላቂነት ሳይኖራቸው አንዴ ሲከፋፈሉ፤ ሌላ ጊዜ ስም ሲቀይሩና ሲወነጃጀሉ ማየት የፓለቲካውን ግሽበትና ቁርጠኝነት ማጣት አጉልቶ ያሳያል። ይህ ደግሞ ሁሌም እርስ በእርስ ሊያፋጅን ለሚሹ የውጭ ሃይላት መንገድን ይከፍታል። ድሮም ያየነው ይህኑ ነው። አሁንም የምንመለከተው ያለፈውን የያዘው ጥለፈው የፓለቲካ ስልት ነው።
    በማጠቃላያው ወያኔ ልክ እንደ ታሊባን እንደገና ያንሰራራል፤ ያው የማያባራ መከራውን በትግራይ ህዝብና በአጎራባች ወገኖች ላይ ያዘንባል። አልፎ ተርፎም ኤርትራና ኢትዮጵያ የሚፋለሙበት አጀንዳ ይሰጣቸዋል ባይ ነኝ። በእርግጥ የኤርትራው መሪ አሁን ባላቸው እይታና አቋም በምንም አይነት መንገድ ቢሆን ከኢትዪጵያ ጋር መዋጋትን አይመኙም። የሚያስገድዳቸው ጉዳይ ግን ሊፈጠር ይችላል። የሃበሻዋ ምድር ሰው ሆን ተብሎ በመንግስት ተገሎ በስሙ መንገድ የሚሰየምበት፤ ት/ቤት የሚቆምበት፤ ሃውልት የሚገነባበት የውስልትና ፓለቲካ ያለ ቅጥ የሰፈነባት ምድር ነበረች አሁንም ናት። ባለጊዜዎቹ የኦሮሞ ፓለቲከኞችና ታጣቂዎች ጭካኔም በጊዜው የሚገታ ያሰረው፤ የገረፈው፤ የገደለው፤ ያሳደደው በወረፋው እንደ እድሉ የሚሰፈርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የደም አፍሳሾችና የግፈኞች እድሜ የረዘመ ቢመስልም አጭር ነው። ታሪክ የሚያሳየን ይህኑ እውነታ ነው። ስለሆነም በሃበሻዋ ምድር ኡኡ ተባለ፤ ተጸለዬ፤ ተመከረ ተዘከረ የሚለወጥ ነገር አይኖርም። ዛሬ በኦርቶዶክስ ቤ/ክ እንዲሁም በመስጊዶች ላይ የሚደረገው ግፍና መከራ በፓለቲካ ሂሳብ የተሰራ የግፈኞች ድላ እንጂ በድንገት የተፈጠረ ድርጊት አይደለም። ለዚህ ነው የህገ መንግስቱ መሻሻል ብቻውን ሃገርን ሃገር ሊያረጋት አይችልም የምለው። የሰው እይትና አመለካከት ከጎጡ ተሻግሮ ሰውን በሰውነቱ ሲቀበል ያኔ ብቻ ነገሮች ሊሰክኑ ይችላሉ። አሁን በምናየው ግርግርና አስረሽ ምቺው የብሄር ፓለቲካ ምንም አይነት ነገር ቢለወጥ ህዝባችን ከረሃብና ከግፈኞች ድላ ሊያድነው አይችልም። በቃኝ!

  4. ይድረስ ለተከበርከው ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

    የጻፍከው መጣጥፍ ግልጽና ኢላማውን የመታ ነው::
    እኔም በግሌ ማምንበት ነው:: በአሰቃቂ ድህነትና ባርነት ግዞት እና ጥልቅ ማይምነት በነገሠበት ምድር ውስጥ ሕገ መንግሥት ቀየርክ አልቀየርክ ምንድን ነው ትርጉሙ? በአሪዎስና በዳቢሎስ ደንቆሮና አረመኔ ደደቦች ሚተዳደር ሕዝብ ምን መንግሥት አለውና ነው ስለ ሕገ መንግሥት ሚታሰበው? መጀመሪያ ሌጂትሜት፣ተጠያቂነት፣ርዕይ ያለው መንግሥት ሲኖር ነው በሕግና በሕገ መንግሥት ምትጠይቀው? እራሱ ሕግና ሕገ መንግሥት የሆነን የበሰበሰና የከረፋ ስርአት በምን ሕግስ ነው ምዳኘው? ኪዳኔም በጽሑፍ ያስቀመጠውን አይቻለው አስፋ ወሰንም በቃለ መጠይ የሰጠውን አድምጫለው፣ የኛ የከፋና የመረረ ኑሮና ሕይወት በትክክል አልገባቸውም:: ወንድሜ ሲኦል ውስጥ እኮ ነው ያለነው፣እንዴትስ ብሎ ማስረዳት ይቻላል:: የአምላኮች ጨዋታ የሚለውን የዳንቴ አሊጌሪን በጽሑፍ ብዙ ጌዜ ጠቅሰህ ጽፈሀል እሱስ ምንድን ነው ያለን ሲኦል በር ላይ እንዲህ ብሎ ተለጥፏል “All those who entering hear abandon your hope” ወደዚህ የምትገቡ በሙሉ ተስፋችሁን እርሱት ነው ትርጉሙም “በኢኮኖሚም ሆነ በፓለቲካ ተስፋ የማይሰጥ ሕይወት እንደ ሲኦል ይቆጠራል ነው” ታዲያ እነዚህ ሰዎች ይሄ እንዴት ነው ማይገባቸው? ሲኦል ውስጥ ነው ያለነው ስንል ምሬት ሳይሆን በምክንያትና በተግባር ነው:: አንዱ ዩኤን ሲሰራ ነጮቹ አምሮውን የበረዙት የጃጀ ሽማግሌ ነው፣ሌላኛው በድሎት ያደገና አዲስ አበባ ጀርመን እስኩል የተማረ ውጣ ውረድ ያላየ ሕይወት አልጋ ባልጋ ሆኖሎት ያደገ ነው፣ይልቁን አያቱ በማጨው ጦርነት የጎንደርን ጦር የመሩ በሐበሻ ጀብዱ ቼካዊው ፓርል ሳክ የጠቀሳቸው ጀግና ናቸው:: ይቅርታ አርግልኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታ በትክክል የገባው ሰው እያጣው ነው:: እናቱ የወለደችው አንድ እስክንድር ነጋ ብቻ ነው:: እጅግ በጣም ምናሳዝን ነን ትልቅ ሕብነን ታሪክ አለን ስንል ያስቀኛል:: ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ በሕዝብና የመንግሥት አስተዳደር መጽሐፋቸው እንዲህ ይሉናል “ካልተደራጀና ስርአት ከሌለው ብዙ ሕዝብ፣የተደራጀና ስርአት ያለው ጥቂት ሕዝብ ታሪክ ይሰራል”፣ የስካንድኒቪያ፣ሲንጋፓር እና የኮርያ ሕዝቦች ምሳሌዎች ናቸው:: ቻይኖችም በአገር ወዳድና ቆራጥ መሪዎቻቸው በዓለም ራሳቸውን አስከብረዋል:: ለደነቆረ፣ለደኸየ፣ሲኦል ውስጥ ላለ ሕዝብ መቅደም ያለበት የቱ ነው? ሁሌ እልሀለው ካንተ ውጭ ፍሬ ነገር ያለው ሚጽፍ የለም ቢጽፍ ስሜቱን ወይም አሉባልታ ነው፣ታዲያ የዚህ ተልካሻ ወራዳ ኢሐሳብ ነው ሕዝብን ነፃ ሚያውጣው? እስከ ሕይወይ መስዋትነት ቆራጥነት፣ጥልቅ ዕውቀትና ግንዛቤ፣የተግባር ሰው መሆን ያስፈልጋል ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ፣ከዛ ውጭ ያለው ጉንጭ አልፋና ዊንዶው ድሬሲንግ ነው:: እነዚህ ያሄስካቸው ሰዎችና መሰሎቻቸው፣የገባንበት ቅርቃርና የተቀበርንበት ጥልቅ የመቃብር ጉድጓድ፣ገሀነባዊ የእለት ከለት ሕይወታችን በትክክል አልገባቸውም:: ለደዚህ አይነቶቹ በደንብ ጊዜ ወስደህ በጥናት ላይ የተመሰረተ አስተማሪ ጦማር ብታቀርብልን ተመራጭ ነው::

    ከማክበር ጋር
    ያሬድ መኩሪያ
    አ.አ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share