ይህንን አስደንጋጭ መርዶ ለማመን ሰዓታት ፈጅቶብኛል። ዳዊት ፍሬው ወደ ጣሊያን ለመጓዝ ዝግጅት ላይ እያለ፣ ለጣሊያን ኤምባሲ የድጋፍ ደብዳቤ እንድጽፍለት ሊጠይቀኝ ያለሁበት ድረስ መጣ። በጣም ግሩም በኾነ የተነቃቃ ስሜት ጣሊያን የሚኖሩትን የኮንሠርት መድረኮች ዘረዘረልኝ። ጣሊያን ሀገር ነዋሪ የኾኑ የኢትዮጵያ ‘ኮምዩኒቲ’ አባላት በምን ዓይነት ጉጉት እየጠበቁት እንደኾነም ነገረኝ።
የዳዊትን ጨዋታ ዐዋቂነት የምታውቁት የምትመሰክሩት ነው። ሙዚቃዊ ቀልዶቹን እያከታተለ ነግሮኝ በጣም አሳቀኝ። ደብዳቤውን ጽፌ ሠጠሁት። ከዚያ በኋላ የደወለልኝ ለጉዞው አንድ ቀን ሲቀረው ነበር። ሞቅ ባለ ስሜት እና በመድረክ ጉጉት ስሜት ተሰናበተኝ።
ከዚያች ዕለት በኋላ እጠብቅ የነበረው፣ የመድረክ ቪዲዮዎቹን ነበር። ከቶውንም ያላሰብኩትን የዛሬውን የድንገተኛ ኅልፈቱን ዜና ሰማሁ።
***
ዳዊት ፍሬው ኃይሉ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርቱ ‘ሜጀር’ ያደረጋትን ክላሪኔትን የምር የሙጥኝ ያለ ድንቅ ሙዚቀኛ ነበር። አልቶ ሳክስፎን እና ክራር የሚጫወት ቢኾንም፣ ለክላሪኔት የነበረው ፍቅር፣ ከጋሽ ወዳጄነህ ፍልፍሉ(ነፈስ ኄር) እና ከጋሽ መርዓዊ ሥጦት ጋር የሚያመሣሰለው ነበር።
በሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው፣ የታላላቅ ኮምፖዘሮችን የክላርኔት standard concerto’ዎች’ ተጫውቷል። መምህሩ ፈለቀ ኃይሉ የሚያደንቀው እና የሚያበረታታው ተማሪው ነበር።
ከተማሪ ቤት እንደወጣ፣ኢትዮጵያብሔራዊ ቴአትር ቢግ ባንድ ውስጥ በክላሪኔት እና አልቶ ሳክስ ተጫዋችነት ለተወሰኑ ዓመታት አገልግሏል። በቴአትር ቤት ቆይታው፣ በግሉ፥ የመጀመሪያውን “ኢንስትሩሜንታል” አልበም፣ በፈለቀ ኃይሉ አቀናባሪነት ለማሳተም ችሏል።
ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ፣ በግሩም መዝሙር ከተቋቋመው የ”ዐዲስ አኩዊስቲክስ” ባንድ ጋር አልበም እና በበርካታ ሀገራት ኮንሰርት የማቅረብ ዕድል አገኘ። በኢትዮጵያዊ ቅላፄ በተዋበው የክላሪኔት አጨዋወቱ የተደነቁ ጋዜጠኞች “The Guardian” እና “Independent” ጋዜጦች ሰፊ የአድናቆት ዘገባ ጽፈውለታል።
ከ2004 እስከ 2014 ዓ.ም. በተከታታይ ሦስት የመሣሪያ ቅንብር ሥራዎችን በአልበም አሳትሟል። 2006 ዓ.ም. ላይ፣ በታላቁ ሙዚቀኛ እና መምህር በተቋቋመው “Retrieve Ethio Big Band” ላይ በአልቶ ሳክስፎን ተጫዋችነት የተደነቁ ታላላቅ መድረኮች ላይ ተጫውቷል።
ኮቪድ 19 በተከሰተበት ወቅት፣ ወጣቱ ሙዚቀኛ ኢዩኤል መንግሥቱ በልዩ ኹኔታ ባቀናበረው “ቅኔ ነው ሀገር” በተሰኘው የኦርኬስትራ እና ኳየር ቅንብር የሙዚቃ ሥራ ላይ በክላሪኔት ተጫዋችነት ተሳትፏል።
ዳዊት ከዓለም ታላላቅ ክላርኔቲስቶች ጋር በመድረክ የመጫወት ዕድልም ነበረው። ለአብነት ያህል፥ በአሊያን ኢትዮ ፍራኔሲስ የሙዚቃ ፌስቲቫል መድረክ ላይ፣ ከ”Ether Orchestra” አባላት ጋር ተጫውቷል።(የኔ ሐሳብ የተሰኘችው የግርማ ነጋሽን ሙዚቃ የመድረክ ሥራ ያስታውሷል)፣ በዓለም እጅግ ገናና ስም ካላቸው ክላርኔቲስቶች አንዱ ከኾነው ከፓኩዊቶ ዴሪቬራ ጋር በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መድረክ ላይ፣ “አምባሰልን” ተጫውቷል።
ክላሪኔትን ኢትዮጵያዊ ዐንደበት ከሠጧት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን መካከል፣ የዘመናችን ዕንቁ ሙዚቀኛ ኾኖ በመድረክም በአልበምም የታየው ዳዊት ፍሬው ኃይሉ፣ ብዙ ሊሠራ ባቀደበት፣ ብዙ ውጥኖቹንም ባደራጀበት በዚህ ወቅት፣ በ44 ዓመት ዕድሜው ይህችን ዓለም በሞት መለየቱ ከልብ ያሳዝነኛል። ልብ የሚሰብር ኀዘን ነው የተሰማኝ።
ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ ለሙያ አጋር ጓደኞቹ እና የአድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ። ነፍስ ኄር
DireTube