የብልፅግና መሪዎች “ከአልጋ ሲሉት ከአመድ” አባዜ!!

መቸም ለሃገሬ ሰው የዚህን ጥቅስ ትርጉም መዘርዘር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው። ነገር ግን ክብር ፣ ሞገስ ለሰጠህ ፣ ደጀን ለሆነህ እና ውለታ ለዋለልህ ሕዝብ ሆነ ግለሰብ ምላሽህ አግባብ ያለው ካልሆነ “ከአልጋ ሲሉት ከአመድ” ማለት እንድፍርጥርጥህ ሁንና የእጅህን ታገኘዋለህ” እንደማለት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነ የአማራ ሕዝብ ብልፅግናን “መብታችን አስከብረህ ምራን ፣ ሰላም አውርደህ የሃገር አንድነት አስከብርልን” አሉት እንጂ አልጋውንና የሥልጣን ወንበሩን እንጠቅህ ፣ እንውሰድብህ አላሉትም።

በተለይ የአማራ ሕዝብ ለሶስት ሺህ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን አሳምሮ፣እንገቷን ቀና አድርጎ የመራ ፣ የሕዝብን ሰላምና ደንበር አስከብሮ ያኖረ ማህረሰብ በመሆኑ “የሥልጣን ጥመኞች ሆይ ፣ ዙፋኑ ከአማራችሁ እስኪ እንያችሁ” በምፀት እያሸበሸበ ወንበሩንና መንበረ ሥልጣኑን “እካችሁ” ካላቸው  ሰነባብቷል።

ሃገር እንመራለን ብለው በተከበረው የአያቶቻችንና የአባቶቻችን ቤተመንግስት  ሳይገባቸውና እማይመጥኑ መሆናቸው እየታወቀ መንበሩ ላይ ቁብ ብለው እያመሱን ያሉት “ህወሃቶች እና የኦሮሞ ብልፅግና” ተብየዎች “ከበሮ በሰው ሲያዮት ያምር ሲይዙት ግን ያደናግር” እንዲሉ ግራ ገብቷቸዋል ፣ ተጭበርብሮባቸዋል ፣ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን አሳጥቷቸዋል።

በኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዓመታት የስረወ መንግስታት ታሪክ ነገስታትና መሪዎች   ሥልጣናቸውን ለማዝለቅና ላለማስነጠቅ ጦር ሰብቀው ነገሥታት ከነገሥታት ጋር ይፋለሙ እንደሆን እንጂ የሚመሩትን ሰፊ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጦር አውጀው ፣ በጀት ፣ በመድፍ ፣ በመርዝ  ጭስ ፣ በድሮን እና በአጥፊ ከባድ መሳሪያ ወግተውት ፣ አድምተውት ፣ አፈናቅለውት ወ.ዘ.ተ. አያውቁም ።

ግራ የገባው ብልፅግና ተብየው የወላይታን ፣ የጉራጌን ፣ የትግራይን ወ.ዘ.ተ. ሕዝቦችን ከወጋ ፣ከአደማ እና ካፈናቀለ በኋላ ሰሞኑን ደግሞ “ማነህ ባለተራ” ብሎ የኢትዮጵያ ካስማ እና ማገር የሆነውን ታላቁን የአማራ ሕዝብ ጦር ሰብቆ ያለ የሌለ አጥፊ መሳሪያዎቹን ታጥቆ እየወጋው ይገኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መስከረም ሁለት – ኢትዮጵያ ትቅደም! - ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

በዐፄ ኃይለስላሴና በደርግ ሥረዎ መንግስታት አስተዳደር ወቅት በስርዓቶቹ ቅር በመሰኘትና በመከፋት እነ ኢሕአፖ ፣ ኢዲዮ፣ ወያኔ ፣ ሻቢያ ፣ ኦነግ ፣ አሻፈረኝ ያሉ አማፅያን እና መሰል በፓርቲና በብሔር የተደራጁ ቡድኖች ቢኖሩም ለሃገር አንድነትና ክብር ሲባል ጦርነቶችና መቆራቆሶች ቢኖሩም እንደአሁኑ የብልፅግና መንግስት በአጥፊ መሳሪያዎች አልተደበደቡም ፣ አልተቀጠቀጡም ፣ ይልቅኑ አስተማሪ የሆነ ተመጣጣኝ ሕጋዊ የእርምት እርምጃ ይወሰድባቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ።

ሰሞኑን ደግሞ ጠቅላያችን “ምን ብለው አባሱት” እንደሚባለው  በብሄራቸው የሚቀርባቸውን ወራሪ ኃይል በአማራ አካባቢ  አሰማርተው ለመጨፍጨፍ ቢዳዱም “የአማራን ጀግና ኃያል መራር ክንዱ ሲቀምሱ ‘አትሞክሩን አትችሉንም ፣ እንደ ኢሕአፖ ዘመን ‘ቀይ ሽብር እንጀምራለን ፣ ኢትዮጵያን አትችሏትም’” ወ.ዘ.ተ. እያሉ በለመዱት የስላቅ ቋንቋቸው መናዘዝ ፣ መደስኮርና መጎረር ጀምረዋል።

“ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች” እንዲሉ ለአማራ ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ መቆርቆርና ዘብ መቆም ለመስበክና ለማስተማር መሞከራቸው ትርፉ መላላጥና መሳት ነው እንላቸዋለን።

የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ እንደተነሳ ኃይል አርጎ መቁጠሩና መዘላበዱ አጃይብ የሚያሰኝ ትርኪምርኪ ወሬ ነው እንላለን።

ጠቅላያችን ወደ አማራ ክልል የተላከው ትርክምርኪና አበል ተከፋይ ወራሪ ሰራዊታቸው ድባቅ ሲመታ “የደርግ ዘመንን የቀይ ሽብር አፀያፊ ኩነት እንደግመዋለን ብለው  ልበ ሙሉውን የአማራ ሕዝብ ሊያስፈራሩ ሞክረዋል ነገር ግን ይህ ንግግራቸው ፋይዳ ቢስ መሆኑን ሊረድት ይገባል እያልን ጎንደር ላይም ይህን አረመኔ ድርጊታቸውን በይፋ በጠራራ ፀሐይ ወንድሞቻችንን  ትኩስ በማስመታትና በመግደል በይፋ ጀምረውታል።

ጠቅላዩ ከዕድሚያቸው አንፃር በዚያ የቀይ ሽብር ዘመን ወይ እየዳሁ ነበር ወይም አልተወለዱም ለማለት ስለሚያስደፍር “የቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር” ክዋኔ በደርግና በኢሕአፖ ተቀናቃኝ ፖርቲዎች መካከል የተደረገ የፖለቲካ አታካራና ቁርቁስ በመሆኑ ያቀረቡት መከራከሪያዊ አመክንዮ በጭራሽ ውሃ የማይቋጥር ሲሆን የንግግራቸው ውስጠ ወይራ ሚስጥሩ ግን የአማራን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ያላቸውን ህሳቤ የሚያመለክት ዳርዳርታ እንደሆነ እንረዳለን። እንደ ሃገር መሪ ግን ይህ  ድፍረት የተሞላበት ዛቻ የሚያስተዛዝብ ነው እንላለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ልማት ያለ ነፃነትና ፍትሕ ፋይዳ የለውም

ሌላው የሚገርመው መሪዎቻችን ከቀደም የኢትዮጵያ መሪዎች መማር አለመቻላቸው ነው። በአንድ ወቅት ኮለኔል መንግስቱ ከወንበራቸው መንሸራተት ሲጀምሩ “ ይህ ወርቅ ቢያነጥፉለት ፋድያ የሚል ሕዝብ” ብለው ተሳለቁ ፣ አቶ መለስ ዜናዊ “ ከዚህ ባንዴራ ጀርባ ምን ተደረገ የሚለውን እንጂ ከጨርቁ  ችግር የለብንም” አሉ ፣ ነገር ግን ከዚህ ንግግራቸው በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምላሽ ምን እንደነበር ማንኛችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው።

ጠቅላያችን የአፍ ውለምታ ይሁን በፍርሃት ደንብረው “ አትሞክሩት አትችሉንም” የሚል ንቀት የተሞላበትና የመታበይ ንግግር ጀባ ብለውናል። የሚገርመው በቡድን ተቧድኖ እንደሚናረት የሰፈር ጎረምሳ የሚመሩት ሕዝብ ማን ሆነ ማን እንዲህ ብሎ አፍ አውጥቶ ለጦርነትና ለግጭት መጋበዝ “ለአቅመ ሃገር መሪነት” አለመድረስን ያሳያል።

ሃገርና ሕዝብን “ ጠብ ያለሽ በዳቦ” እንዲሉ የታጠኩትን ድሮን ፣ የጦር ጀት ፣ ከባድ አጥፊ መሳሪያና የአንድ ጎጥ ጦር ሰራዊትን ይዞና ተማምኖ ሰፊውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በመናቅ እንዲህ ያለ ግብዝነት የተሞላበት ንግግር ማድረግ “ ከድጡ ወደማጡ” እንደሚያገባ የሚታወቅ እና እየሆነም ያለ ክስተት ነው።

ቱሪናፋውን እና ጉረራውን ወደ ጎን እንበለውና እንደሚታወቀው ህውሃት ጦሩን ይዞ ጎንደር ላይ “ጀግናውን ኮለኔል ደመቀን” ሊያፍን ወደ  መኖሪያቸው ድረስ በንቀት ተጉዞ ሐምሌ 5 ፣ 2008 ቡድን እንክትክቱ ከመውጣቱ ባሻገር ለውድቀቱ ሰበብ እንደሆነ ልብ ይሏል እንላለን።

የአሁኑን አያድርገውና ጠቅላዩ ላይ የተወረወረን ቦንብ “ከአንተ በፊት እኔን” ብሎ ጨብጦ የተሰዋለትን ህዝብ ፣ ሙሴያችን ፣ የሳላም ቀንዲል ፣ የኢትዮጵያ ካስማ እና ጠበቃ ብሎ ያቆለጳጰሰን ፣ ከሕውሃት መፈንቅለ ብልፅግና የታደገን ወ.ዘ.ተ. የኢትዮጵያ ሕዝብና በይበልጥ ሙሉ የማይናዎጥ ድጋፉን ችሮ የተሰዋላቸውን የአማራ ሕዝብ ፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖን እንደ ጠላት ቆጥሮ ማሳደድ ፣ መግደልና ድምጥማጡን ለማጥፋት መሞከር እኛ አማሮች የብልፅግና መሪዎችን እንደዛች እዳልታደለች እንስሳ “ብልፅግና ሆይ ከአልጋ ሲሉህ ከአመድ” ነህ እንለዋለን። ታሪክ ደግሞ እራሱ ደግሞ እነ ብልፅግና ሆይ የውርደት ማቅ እዳትከናነቡ እናሳስባችዋለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  [ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን] በማሸነፌ ተደስቻለሁ፣ በማሸነፌ አልተደሰትኩም !!

 

ተዘራ አሰጉ

ከምድረ እንግሊዝ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share