የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በፌዴራል መንግስት እና ራሱን የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) እያለ በሚጠራው ቡድን መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም የተደረገውን ድርድር እና በኋላም የተደረሰውን የሰላም ሥምምነት አስመልክቶ በየጊዜው በአንክሮ እየተከታተለ አቋሙን ይፋ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ፓርቲያችን አብን በፌዴራል መንግስት እና በሽብር ቡድኑ መካከል የተደረገውን ሥምምነት አስመልክቶ የልዩነት ሃሳብ የሚያራምድባቸው የተለዩ ጉዳዮች ቢኖሩትም ፣ ሥምምነቱ በተደረገበት አግባብ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና በተለይም በግጭቱ ቀጥተኛ ተጠቂ ሆነው ለቆዩት የትግራይ ፣ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ትልቅ እፎይታ እንደሚሰጥ በማመን ከእነጉድለቱም ቢሆን ለሥምምነቱ ተግባራዊነት ሙሉ ድጋፉን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ይሁንና ዘላቂ ሰላም ያመጣል ተብሎ የተፈረመው የፕሪቶሪያው ሥምምነት አንኳር ጉዳዮች ካለመተግበራቸውም በላይ የጦርነት ቀጠና ሆነው የቆዩትን አካባቢዎች ለ4ኛ ዙር የጦርነት አደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እየተከሰቱ መሆኑን ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እየታዘበ ይገኛል፡፡ በፕሪቶሪያው ሥምምነት አንቀጽ 6(F) መሰረት ትሕነግ በሰላሳ ቀናት ውስጥ የቀላል መሳሪያ ትጥቅ ጨመሮ ጠቅላላ ትጥቅ እንዲፈታ እና በሥምምነቱ አንቀጽ 3(5) መሰረት ደግሞ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ገብቶ ጸጥታ የማስከበሩን ሥራ በተሟላ ሁኔታ እንደሚረከብ ሥምምነት የተደረሰ ቢሆንም ፣ ቡድኑም ትጥቅ ሳይፈታ የሀገር መከላከያ ሠራዊትም ወደ ትግራይ ገብቶ ጸጥታ የማስከበር ሥራውን ሳይረከብ ቡድኑ የገንዘብ እና የማቴሪያል ድጋፍ ሲደረግለት የቆየ ሲሆን ፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ከጠቅላለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ብዛት ያላቸው የምክር ቤት አባላት ባልተገኙበት እና ከተገኙትም ውስጥ ከ60 በላይ ተወካዮች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ባሉበት ሁኔታ ቡድኑ ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲፋቅ ተደርጓል፡፡
በአጀንዳው ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ በተጠራው ስብሰባ ላይ ብዛት ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አለመገኝታቸው እና ከተገኙትም ውስጥም ከ60 በላይ የሆኑት አባላት የውሳኔ ሃሳቡን በመቃወም እና ድምጸ ተዐቅቦ በማድረግ ድጋፋቸውን መንፈጋቸው የሚያሳየው የሚበዙት የምክር ቤቱ አባላት የቡድኑን ከሽብርተኝት መዝገብ መፋቅ የማይደግፉ መሆኑን ሲሆን ፣ ውሳኔው ሕጋዊ ነው ቢባል እንኳ ቅቡል (Legitimate) እንዳይሆን የሚያደርገው ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባት ባልተደረሰበት ፣ የሚበዙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የውሳኔው አካል ባልሆኑበት ፣ የሽብር ቡድኑ ትጥቅ ባልፈታበት እና ይልቁንም ቡድኑ የፕቶሪያውን የሰላም የሥምምነት አንቀጽ 7(1)(D) በመጣስ በተለያዩ አካባቢዎች አዲስ የታጣቂዎች ምልመላ ፣ ስልጠና እና የጦርነት ዝግጅት እያደረገ ባለበት ሁኔታ ቡድኑን ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዝ ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ሲሆን ተገማች በሆነ ጊዜ ውስጥ ለሌላ ዙር ግጭት እና ጦርነት የሚያጋልጥ በመሆኑ ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ውሳኔውን ይቃወማል፡፡ በመሰል አግባብነት በሌላቸው ውሳኔዎች በሕዝባችንና ሀገራችን ላይ ለሚደርሰው በደል ሁሉ የፌዴራሉ መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድም አብን በአንክሮ ያስገነዝባል::
ከፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት ባፈነገጠ ሁኔታ እና የሀገራችን ኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እና ሰላም አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ መንግስት እያሳለፋቸው ያሉ ተከታታይ ውሳኔዎችን ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጽኑ ያወግዛል፡፡ በዚህም በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በጥምር ጦሩ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኝው ድል በመንግስት ውሳኔ እና ትዕዛዝ እየተቀለበሰ እና በሶስት ዙር ጦርነት ከፍተኛ ዋጋ የከፈለው ሕዝባችን ለሌላ ዙር እልቂት እና ውድመት ተጋላጭ እንዲሆን እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ጥምር ጦር የሀገራችን ኢትዮጵያን ኅልውና ለማረጋገጥ የከፈለውን የሕይወት እና የአካል መስዋዕትነት ከፍ ባለ አድናቆት የሚመለከተው እና ሁልጊዜም የሚዘክረው መሆኑን እየገለጸ ፣ በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኝውን ድል አስጠብቆ ለመቀጠል የበኩሉን ኃላፊነት የሚወጣ መሆኑን ያስታውቃል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ
መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም