ኮሚዩኒኬሽን ወይስ ፎልሲፊኬሽን? – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

እንደሀገራችን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ሰሞነኛ መግለጫ ከሆነ 127ኛው የአድዋ ድል በአል ባለፈው የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በወጉ ተከብሮ በሠላም ተጠናቋል፡፡

ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት በጊዜው አይኑን በጨው አጥቦ ለህዝብ በለቀቀው መግለጫ መሰረት አዲስ አበባ ውስጥ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አደባባይ አካባቢ የዚህኑ በአል አከባበር ሆነ ብለው ለማወክ የተነሳሱ አንዳንድ ጸረ-ሠላም ወገኖች በአቅራቢያው ወደሚገኘውና ሀይማኖታዊ የአምልኮና የምስጋና ስነ-ስርአት ወደሚፈጸምበት የገነተ-ጽጌ አራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን ቅጥር ግቢ ዘልቀውና ከምእመናን ጋር ተቀላቅለው ወደውስጥ በመግባት የፈጠሩትን አመጽና ግርግር ለመቆጣጠር የጸጥታ ሀይሎች በወሰዱት ሕግ የማስከበር እርምጃ ጥቂት ምእመናን ከመጎዳታቸው በስተቀር ያጋጠመ ችግር አልነበረም፣ የለምም፡፡፡

እውነቱ ግን እርሱ አልነበረም፡፡ በዘመናዊው አለም በአደባባይ ይቅርና በህቡእ ተፈጽሞ ሊደበቅ የሚችል አንዳች ነገር ሊኖር ከቶ አይችልም፡፡

ተፈጠረ በተባለው በዚያ ሁከት በስፍራው የደረሱ የጸጥታ አስከባሪዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ሀይል ሲጠቀሙ ታይተዋል፡፡ በፈረስ ጀርባ ላይ የተቀመጠን የበአሉ ታዳሚ ጭካኔ በተመላበት የአፈሙዝ ምት ደብድበው በሚዘገንን ሁኔታ መሬት ላይ ሲጥሉና ሲያንፈራፍሩት ተስተውለዋል፡፡ በዚህ ሳይወሰኑ የቤተ-ክርስትያኗን ልእልና ያለአግባብ በመዳፈርና ቅጥር ግቢዋን ጥሰው በመግባት መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጡ በነበሩ ካህናትና አምልኮ ይፈጽሙ በነበሩ ምእመናን ላይ አስለቃሽ የጭስ ቦንብ ተኩሰው የንጹሃንን ህይወት ከመቅጠፍና በብዙኃኑ ላይ አካላዊና ስነ-ልቡናዊ ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ ይካሄድ የነበረው አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡፡

በርግጥ የቅጥፈት ፖለቲካ እንደብልጠት በሚቆጠርባት አለማችን አያሌ መንግሥታት ዜጎቻቸውን በአደባባይ መዋሸታቸው ያን ያህል እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ግን ውሸትን በዚህ ደረጃ ይፋዊና ተቋማዊ ማድረግ የጤና ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዝክረ ዶክተር ተስፋዬ ደበሳይ

አንድዬ በቸርነቱ ይቅር ይበለን ከማለት በስተቀር ሌላ ምን ሊባል እንደሚችል እኔ በበኩሌ ግራ መጋባትን እንደፈጠረብኝ ለመደበቅ አልፈልግም፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share