ምሁር ሆይ ምሁር ሁን!

ተጅብ አፍ አህያ  ተቀበሮ ሽል ውስጥ የሚመኝ በግን፣
ተእባብ እንቁላልም ሲጠብቅ የሚውል የእርግብ ጫጩቶችን
ጅላንፎና ሆዳም ደማገጎ ምሁር ገደለ አገሪቱን፡፡

እንደ ዘፍጥረቱ በእባብ ተመስሎ በእግሩም እየሄደ፣
ምላሱን አትብቶ መርዝ በማር ለውሶ የመለኮትን ቃል እየተናገረ፣
የመጣን ሳጥናኤል እንደ ሄዋን አዳም አምኖ ያዳመጠ፣
የዲግሪ ኮፍያ ታናቱ የጫነ ቆብ ያንጠለጠለ መስቀል የጨበጠ፣
ዛሬ ዓይኑ ሲገለጥ ራሱን ነግንጎ እግዚኦ ዋይ ዋይ አለ፡፡

የሰባኪ ሚዛን ሥራው ነው ተብለው ስንቴ ቢመከሩ፣
በስብከት ሽውታ እንደ ገብስ ገለባ ቀለው የበነኑ፤
ምሁራን ተብለው በምን መዝገበ ቃል ለታሪክ ይቅረቡ?

አያት ቅደመ አያቶች በእምነት በህሊና የደነደኑቱ፣
በዓይን ቀዳዳ ገብተው የፈረንጅን አንጎል አይምሮን ሲያነቡ፣
አቻ የሌላቸው እግዜር የቀባቸው ረቂቅ ጠቢባን ብልሆች ነበሩ፡፡

የልጅ ልጆቻቸው ዶክተር ፕሮፌሰር ተስማቸው መግቢያ የሚቸክሉቱ፣
መውጫው በር ላይም ምሁራን ለመባል ፒ ኤች ዲግሪ የሚደርቱቱ፣
እንደ ተማረ ሰው በሎጅክ አያምኑ ወይ በእምነት አይጠኑ፣
በጭራቅ ሰባኪ እየተደለሉ የባህር ላይ ኩበት ሆኑና ቁጭ አሉ።

ዲግሪን ሆድ ለመሙላት ተጠቅሞ እሚያልፍ ሰው፣
ለመጫን እንክርዳድ ተሚቅም አጋሰስ በምን ነው እሚለየው?

ክብርና ማእረጉን መብትና አገሩን ሸጦ እሚኖር ምሁር፣
ቅርቀብ ተሚጫነው የሰፈር አህያ በምንድን ይለያል?

ፊደልን የቆጠርክ ዩንቨርስቲ የሄድክ ዲግሪህን የኮፈስክ፣
ለማለፍ ተሆነ እንደ አሳማ ዝቀህ ደልቶህ ተንደላቀህ፣
ክብርህ ማእረግህን አገርህ መብትህን እንደ ኩስ ወርውረህ፣
ያቺ ቀን ስትመጣ ይህቺ ዓለም ስትከዳህ ነፍስህ ስትለይህ፣
አርጅቶ እንደ ሞተ የከርከሮ አስከሬን ይቆጠር ሬሳህ፡፡

ሰውነት ባህሪ ገላህን ያለበሰህ መንፈስ ልእልና አንጎልህን የሞላህ፣
ክብር ማእረግህን መብትህና አገርህን  ለሆድ ያልቸበቸብህ፣
የመለኮትን ቃል እየተናገረ ሰይጣን በስብከቱ አማሎ እማይነዳህ፣
ዋሾና ቀጣፊ እርካብ ኮርቻ አርጎ ወጥቶ እማይጋልብህ፣
ምሁር ሆይ ምሁር ሁን እባክህ! እባክህ! በአምላክ በፈጠረህ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዜጎች ሲታረዱ ዘንችረው ያድራሉ! - በላይነህ አባተ

 

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share