አንድ ቀን ነው፤ ዶሮ፣ ፍየል፣ በሬና ሰው በአንድ ቤት ውስጥ አብረው ነበሩ። ከዛ እባብ ቀስ እያለ ወደ ቤቱ ሲገባ መጀመርያ ዶሮዋ ነበር ያየችው “እኔ ምን አገባኝ ጣራ ላይ ስለወጣሁ አይደርሰኝም” በማለት እባብ እየመጣ እንደሆነ ሳትነግራቸው ዝም አለች። እባቡ እየተቃረበ መጣ።
በመቀጠል ፍየሏ ነበር ያየችው ። “መቼም ቤትን የምያኽል ትልቅ በሬ እያለ እኔን ይበላኛል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው ። ስለዚህ ምን አገባኝ መምጣቱን ይሁን መግባቱን የሚያስጨንቀኝ” ብላ ዝምታን መረጠች ።
አሁንም እባቡ እየቀረበ መጣ መጨረሻ ላይ ትልቁ በሬ እባቡን መግባቱ ተመለከተ ። እሱም እባብ ቤቱን እንደገባ ከማሳወቅ ይልቅ በጉልበቱ የሚተማመን ስለነበረ “ቢገባስ ምን አገባኝ ፤ እኔን ምን እንዳይጎድለኝ ፤ ቢነድፍ ሰውዬው እንጂ እኔን ዞር ብሎ አያየኝም ትልቅ መሆኔ እያየ አይደፍረኝም” ብሎ እንደሌሎቹ ሳያሳውቃቸው ቀረ ።
በሚያሳዝን ሁኔታ ግን እባቡ ያሁሉ ክፍተት ስላገኘ ተኝቶ ዓለሙን በእንቅልፍ ልቡ ሲዋኛት ለነበረ ሰውዬው እግሩን ነደፈው ።
በሁኔታው በጣም የተደናገጠ፤ሰውየው ከእንቅልፉ በሰከንዶች ተነስቶ”ኡ ኡ ኡ…” በማለት ጩኸት ማሰማት ጀመረ ። እንዳለ ጎረቤቶቹ ምን አገኘው በማለት ግልብጥ ብለው መጡ ። ታላቆች ተጠርተው እባብ እንደነደፈው ሲነግራቸው ፤ ሰውዬው እንዴት መፈወስ እንዳለባቸው መመካከር ጀመሩ ።
ከዛ አንድ ታላቅ አባት ተነስተው ዶሮዋ በተነደፈው እግሩ እንዲያስቀምጧትና መርዙን በአፏ ስባ እንድታወጣው መከሩ። ትልቁ አባት ያሉትን ሰምተው ነገሩን ሞኮሩት፤ ሰውዬው ግን ተጨማሪ መድኃኒት ሳያስፈልገው አልቀረም ጨርሶ አልዳነም። ዶሮዋም መርዙን ስለሳበችው ሞተች እንጂ “ምን አገባኝ” ማለቱ አልጠቀማትም።
ቀጥሎውም የፍየል መረቅ እባብን የተነደፈ ሰው ከጠጣው ፍቱን መድኃኒት መሆኑ ከመኸል በመነሳት አንድ አባት ተናገሩ ። ድጋሜም እንሞክረው በማለት ፍየሏ ታረደችና በመረቅ መልኩ ለታመመ ሰውዬ አቀረቡለት ። ፍየሏም “ምን አገባኝ” ማለቱ ለራሷ ጥሩ አልገጠማትም።
ታማሚው ባሉት መሠረት መረቁ አንድ ሳያስቀር ጠጣው
“ማን አባቱ ቀና ብሎ ያየኛል”እያለ ሲፎክር የነበረ ታላቁ በሬም ከሞት ልያመልጥ አልቻለም ። ቀኑ መሮጡን አላቆመምና ሟቹ 80(ሰማንያ) ቀኑ ደረሰ። ለተዝካሩ ይሆን ዘንድ እንደባህላችን መሠረት እህልና ውኋ ማጥፋት የግድ ነበረና በሬ መታረድ ስለነበረበት ታላቁ በሬ “ምን አገባኝ ማለት”ቄራ ሳያገባው አልቀረምና ነው።
ለማለት የፈለግሁት ሁላችን ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን ተግባብተን “አንዱ ሲጎዳ ስናይ” ጉዳቱ የሁላችን መሆኑ እናስብ። ዛሬ አንዱን ሲጨንቀው ሲቸገር አይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን ችላ ብለን ካለፍነው ፤ ጊዜው ጠብቆ ችግሩ ወደ’ኛም እንደሚመጣ አንዳንረሳ። እንተጋገዝ እንተዛዘን እንተባበር እንመካከር ልዪነታችን ውበታችን ነው።