እንበል ?! – ሲና ዘሙሴ


ዝሆኖች ሲጣሉ
የሚጓዳው ሣር ነው …
ይኼ ሣር የሚሉት
የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ?
እንበል …
ህዝብ ሣር ነው ?
ገዢዎችም ዝሆን …
አሳር የሚያሳዩት
በማብዛት ሥቃዩን ።

የሰው ሣርነቱ
እውነት አይደለ እንዴ
ዝሆኖች ሲጣሉ
አልተጎዳም እንዴ ?
አለተሰዋም እንዴ ?
አልተሰቃየም እንዴ ?
…………………… ?
ያ ሁሉ ተረስቶ
ዝሆኖች ሲታረቁ
ተባለ ፣ ተባለ
ኑ ሣሮች ሆይ ሣቁ ።
ዝሆኖች ሲጣሉ
የሚጓዳው ሣር ነው
ይኼ ሣር የሚሉት
የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ?
እንበል …
ሣር ህዝብ ከሆነ
ካልታየ እንደሰው
የትኛው ሣር ይሆን
” በዕረቁ ” የሚሥቀው ?
በዕርቁ የሚደሰተው ?
ልጁን ፣ አባቱን ፣ እናቱን …
ዘመድ አዝማዱን …
በዝሆኖቹ እርግጫ
በዝሆኖች ኩንቢ
ያጣው ዜጋ ነው ወይ ?
ታዞ _ የሚስቀው ?
……………….
በግድ እንዲስቅ
ህዝብ ከታዘዘ
በራሱ ሚዲያ
ከተነዘነዘ …
እላለሁ
ይሄ ብልፅግና
ከደረግም
ከኢህአዴግም
የባሰ ጨካኝ ነው ።
በሰው ቁሥል
ሥለት ሰዶ
አመመህ እንዴ
ብሎ ጠያቂ ነው ?
ትላንትና ደርጉ
በቀይ ሽብሩ
በነፃ እርምጃ
የጥይት አረሩ
በሟች በመባከኑ …
ክፈሉኝ እንዳለው
የጥይቴን ዋጋ
” የዩቶጵያው ብልፅግና ”
የኢትዮጵያን ህዝብ
በግድ ሣቅ ይለዋል ።
ህዝብ ፍትህ አጥቶ
በሐዘን ተውጦ
ሆዱን እያከከ
ባድማ ተቀምጦ
እንዴት ሣቅ ይባላል ?
የጦረነቱ ቋስቋሾች
እነሱ ይሳቁ …
እነሱ ያስካኩ
ሞቱን መከራውን
ለፅድቅ ነበር እያሉ
አለዩልንታ እየሰበኩ ።
እነሱ ይሳቁ
ዝሆኖች ስለሆኑ
ያሥለቅሳሉ እንጂ
ቀንበር እየጫኑ ።
እነሱ ይሳቁ …
በወከበው ተተግነው
የሁለቱንም ንብረት
ያለከልካይ አግዘው
የሚ-ን-ደ-ላ-ቀ-ቁ ።
እነሱ ይሳቁ …
በሀብትና በክብረት
እጅጉን የላቁ ።
ይበሉም …
እንግዲህ ምን ትሆኑ
ዝሆኖች ታረቁ
ያለሃጢያታቸው
ሣሮች ግን አለቁ …
ደቀቁ …
ዝሆኖች ሲጣሉ
የሚጓዳው ሣር ነው
ይኼ ሣር የሚሉት
የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ?
እንበላ …
አያሳዝንም ወይ ?
የሰው ልጅ ሣር ሲሆን
በእግዜር አገር
ሰብዓዊነት አክትሞ
በመቃብሩ ላይ
ግብዝ ሲጨፍር ። …
ሲላላስ ” ቀይ አንዱ ” …
አብይ ዜና ሲሆን
ሠላም ለዓለም ሲል
ጌታ ደብረፅዮን
ለገሰ በመዶሻ
አፍ ሲያዘጋ ህዝብን !
እያየ የብረት ሽመሉ …
ሲፈጀው አማራን ።
ህዝብ በዝምታ
በአያሌው ማለቁ ።
” የሺ ጥላ የተባለው
በቅጥፈት መድረቁ …”
በጣም አሥገርሟን
አልን …..
” እንግዲህ ትደንስ
ቁንጫ በአገሬ
እባብም ተነቀሶ
ይዘንጥ _ በሰፈሬ ።
ይሁና …
ጊዜ ያመጣውን
ጊዜ እስኪመልሰው
ጊዜ የሰጠው ቅል
ድንጋዩን ይግመሰው ።
በሠፈረው ቁና
ኋላ እስኪሰፈር
ጅብ ቁርበት ለብሶ
እቤት ገብቶ ይደር ።
ግና ጥያቄ አለን
እኛው ለራሳችን
አያስገርምም ወይ
አያሥደንቅም ወይ
ይኼ መክሸፋችን ? “

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጭቃው - አሁንገና ዓለማየሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share