January 15, 2023
47 mins read

የኦህዴድን አፓርታይድ አገዛዝ በሰላማዊ ትግል በፍጥነት እናስወግድ!!! -አስፋው ረጋሳ

 

Abiy a killerየአገራችን ህዝብ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የኮምዩኒስት ሥርዓት ውላጅ በሆነው የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ከዚያም ቀጥሎ ባለፉት አምስት ዓመታት የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊው ርእዮት በወንጌላዊ ብልጽግና (prosperity gospel) ተጀብኖ ሲናጥና ሲቀጠቀጥ መቆየቱ ይታወቃል። በተለይም ለብዙ ሺህ ዘመናት በአንድነት የኖረውን ህዝባችንን ከፋፍሎ ለመግዛት በኢህአዴግ የተመሠረተው የአፓርተይድ ዘረኛ ሥርዓት በህዝባችን መካክል መለያየትና መቃቃርን ከመፍጠር አልፎ ህዝቡ በጠላትነት እንዲተያይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይወያይበትና ይሁንታውን ሳይሰጥበት በላዩ ላይ በተጫነው ህገ መንግስት አማካኝነት የተዋቀረው የክልል አወቃቀር ህዝባችን በማንነቱ እንዲጨፈጨፍና በገዛ አገሩ እጅግ ለከፋና ለማያባራ መከራ፤ ስቃይና ስደት መዳረጉ ይታወቃል።

የህዝባችን መከራ ባለፉት አምስት ዓመታት የመንግስትን ሥልጣን የተቆጣጠረው ኦነጋዊው ኦህዴድ ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን አስተባባሪነትና አቀናጅነት በከፋ ሁኔታ ቀጥሎ ህዝባችን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሻሸመኔ፣ በቡራዪ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በጌዴኦ፣ በአርሲ፣ በወላይታ፤ በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በአጣዬ፣ ወዘተ በማንነቱ በሺዎች እንዲጨፈጨፍ፣ እንዲታረድ፣ ከነህይወቱ በእሳት እንዲቃጠልና በገዛ አገሩ በሚሊዮኖች እንዲፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ይህንንም ለማስፈጸም ኦህዴድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እስካሁን ድረስ ግልጽ ባላደረገውና ሊያደርገውም በማይፈልገው ከ”ኦሮሞ ነጻነት ግንባር” ጋር ባደረገው ምስጢራዊ ስምምነት መሠረት የግንባሩ ወታደሮች ከነታጠቁት መሣሪያ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ካደረገ በኋላ ይህንኑ አረመኔያዊ ቡድን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን በማስታጠቅና የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ ቡድኑ በወገኖቻችን ላይ በተለይም የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች የሆኑ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮችና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች (አማራ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ወዘተርፈ) በተለይም “የኦሮሚያ ክልል” ተብሎ በተዋቀረው የአገራችን የኢትዮጵያ መሬት “መጤ” የሚል ስም በመስጠት በመቶና በሺዎች የሚቆጠሩትን ህጻናትን፣ ሴቶችን፣ አረጋውያንን ሳይቀር በዘግናኝ ሁኔታ በየጊዜው እንዲጨፈጭፍ፤ እንዲያሳዳድ፣ ንብረቶቻቸውን እንዲዘርፍና መንደሮቻቸውን እንዲያወድም በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጸሀይ የሞቀው፣ ዓለም ያወቀው እውነታ ነው።

የመንግስትን ሥልጣን የተቆጣጠረው ኦነጋዊው ኦህዴድ ይህን ሁሉ የዘር ማጽዳት (ethnic cleansing) እና የዘር ማጥፋት (genocide) በህዝባችን ላይ እንዲፈጸም ሁኔታዎችን ያመቻቸበት ዋና ዓላማ ኦሮሚያ የተሰኘ የቅዠት ሪፐብሊክ ለመመስረት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ጠባብና ዘረኛ ቡድን በተጠቀሰው የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ዘመቻ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሳተፍ መሆኑን ለማረጋገጥ ሩቅ መሄድ አያሻም፤ ለአብነት ያህል፦

1ኛ/ የቀድሞ የኦነግ መሪና በኋላም የኦህዴድ የደህንነት ባለስልጣን የነበሩት ጄኔራል ከማል ገልቹ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በሰጡት የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ይህንኑ በወገኖቻችን ላይ ጭፍጨፋ የሚፈጽመው የኦነግ ሠራዊት በኦህዴድ የጦር መሣሪያና የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንደሚደረግለት አረጋግጠዋል፤

2ኛ/ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን በሴራ የተቀነባበረ ግድያን ተከትሎ በሻሸመኔ ከተማ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆችና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች በውድቅት ሌሊት ሲጨፈጨፉና ንብረታቸው ሲወድም የከተማው ከንቲባ ሁኔታውን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ለሆነው ለሺመልስ አብዲሳ ስልክ ደውለው ሲነግሩት እርሱም ህዝባችንን አስፈላጊውን የጸጥታ ሃይል ልኮ ከመታደግ ይልቅ “አርፈህ ቤትህ ገብተህ ተኛ” እንዳላቸው በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል፤

3ኛ/ እራሱን የ”ኦሮሚያ ነጻ አውጪ ጦር” ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን የሰሜን አሜሪካ ቃል አቀባይ የሆነ ግለሰብ በቅርቡ በወለጋ በአማራ ወገኖቻችን ላይ ከሚደረገው ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ቃለ ምልልስ ባደረገበት ወቅት የኦሮሚያ ነጻ አውጪ ጦር ከኦሮሚያ ልዩ ሃይል ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጧል፤

4ኛ/ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይም ከኦሮሚያ ክልል ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው፤ ንብረቶቻቸው የተዘረፉባቸውና የወደሙባቸው ከሚኖሩባቸው ቀዬዎች ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ለዓመታት የታጎሩት ወገኖቻችን በተለያዩ የዜና ማሠራጫዎች በለቅሶና በሰቆቃ ድምጻቸውን ባሰሙበት ወቅት የዘር ማጥፋት ወንጀሎቹን የሚፈጽሙባቸው “ሸኔ” በመባል የሚታወቀው የኦነግ ሠራዊትና የኦሮሚያ ልዩ ሃይል አባላት ጭምር እንደሆኑ አረጋግጠዋል፤

5ኛ/ የኦነጋዊው ኦህዴድ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፤ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ሽመልስ አብዲሳና በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግንባር ቀደምትነት ፈጣሪዎቻቸውና ጌቶቻቸው በሕዝባችን ላይ በጫኑት ህገ መንግስት ሳይቀር የፌዴራል መንግስቱ ርዕሰ ክተማ ሆና ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር የተዋቀረችውን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካና የአለም የዲፕሎማቲክ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባችን ለሚመኙት የቅዠት ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ለማድረግ ባላቸው ዓላማ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት” የሚል ዘመቻ በካድሬዎቻቸውና በአንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ነን ባዮች ጭምር ከፍተው የተለያዩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከመሆናቸውም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን የመኖሪያ ቤቶቻቸውን በማፈራረስ (bulldozing) እና በማፈናቀል እንዲሁም ይህንኑ ፋሽስታዊና አፓርታይዳዊ እርምጃ በሰላማዊ ሠልፍ የተቃወሙ ወገኖቻችንን በመደብደብ፤ በማሰርና በመግደል ላይ ይገኛሉ፤ በተጨማሪም ከጥቂት ቀናት በፊት በተካሄደው የኦህዴድ ስብሰባ ላይ ሽመልስ አብዲሳ በአዲስ አበባ ከተማና በዙርያው የሚኖሩና ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎቻችንን ጠራርገው ማስወጣት እንዳለባቸው መግለጹ ተዘግቧል፤

6ኛ/ ከዚህ በላይ በስም የተጠቀሱት የኦነጋዊው ኦህዴድ አመራሮች በአዲስ አበባ በሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከተማዋን ለመጠቅለልና የቅዠት ሪፐብሊካቸው ኦሮሚያ ዋና ከተማ ለማድረግ ባላቸው እቅድ መሠረት በኢትዮጵያችን ብቻ ሳይሆን በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ጭምር የየአገሮቻቸው ሰንደቅ ዓላማ መሠረት የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫና፣ ቀይ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ወርዶ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀልና “ኦሮሚያ የመቶ ዓመት እድፍሽ ታጠበልሽ” የሚል ዘረኛና በህዝባችን መካከል የበለጠ መከፋፈልና ጥላቻን የሚያባብስና ባሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሥፍራዎች በመፈጸም ላይ የሚገኘው የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል በከተማዋ ጭምር እንዲፈጸም የሚጋብዝ መዝሙር እንዲዘመር በማስገደዳቸው ይህንን የተቃወሙ ህጻናት፣ ወጣቶችንና፣ መምህራንን በመደብደብ፤ በማሠር፤ በማሰቃየትና በመግደል ላይ ይገኛሉ።

yelencho let lig abiy ahmedበሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከህወአት ጋር በተደረገው ጦርነት የውጪ ታዛቢዎች በዘገቡት መሠረት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎቻችን ካለቁ፣ በመቶ ሺዎች ከቆሰሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶቻችንና እህቶቻችን ከተደፈሩና በሚሊዮኖች ከተፈናቀሉ፤ እንዲሁም በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት የሀገር ሃብትና ንብረት ከወደመ በኋላ ኢትዮጵያን አፍርሰው የየግል የቅዠት ሪፐብሊካቸውን ለመመስረት የተማማሉት የኦነጋዊው ኦህዴድና የህወአት መሪዎች በህዝባችን ላይ ለደረሰው እልቂትና በደል እንዲሁም በሀገር ሀብት ላይ ለደረሰው ውድመት ምንም ዓይነት ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታና ጦርነቱ በስፋት በተካሄደባቸውና ከፍተኛ እልቂት፣ የጦር ወንጀልና፣ የንብረት ውድመት የደረሰባቸው የአማራና የአፋር ወገኖቻችን ባልተወከሉበት “የሰላም ስምምነት” የደረሱበትንና ምናልባትም ወደ ሌላ የጦርነት አዙሪት ሊወስዱን የሚችሉትን ውሳኔዎች ለመተግበር ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች በሕዝባችን ላይ የደረሰው እጅግ ከፍተኛ እልቂትና ጉዳት እንዲሁም የአገር ሀብት ውድመት አንዳች ደንታ ሳይሰጣቸው በ”ፍቅር እንደገና” የጫጉላ ሽርሽር መንግስታዊ ስልጣንን ለመቀራመት ሽር ጉድ በማለት ላይ መሆናቸውን ልብ ይሏል። ባንጻሩም ኦነጋዊው ኦህዴድ በጦርነቱ ወቅት ህወአት አይሏል፣ ለሥልጣኔ ያሰጋኛል ብሎ በገመተ ጊዜ አማራ ወገኖቻችን ማናቸውንም መሣርያ ይዘው መንግስትን ደግፈው በጦርነቱ እንዲሳተፉ የተማጽኖ ጥሪ ባቀረበ ጊዜ በልዩ ልዩ ሙያ ላይ የተሰማሩ ዜጎችና ቀደም ሲል አገዛዙ በግፍ ከውትድርና ያባረራቸው የጦር ጄኔራሎችና ሌሎች መኮንኖች ሳይቀር ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በጦርነቱ ከተሳተፉና ከፍተኛ መስዋእትነት ከከፈሉ በኋላ የሀይል ሚዛኑ ወደኔ አድልቷል ባለ ጊዜ ደግሞ ጄኔራሎቹንና መኮንኖቹን ከሥራ በማባራርና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፋኖ አባላትን በማሳደድ፣ በማሠርና፣ በመግደል እጅግ አሳፋሪ ክህደት መፈጸሙና በመፈጸም ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በተጨማሪም አገራችን በአሁኑ ወቅት በገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ምክንያትና ኦነጋዊው ኦህዴድ በሚከተለው ዘረኛና የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ሕዝባችን እጅግ ቅጥ ባጣ የኑሮ ውድነት በመጠበስ ላይ ይገኛል። አገራችን እፍኝ የማይሞሉ የመንግስት ሥልጣንን የተቆጣጠሩ ባለጊዜዎች የሀገርና የህዝብ ሀብት በመዝረፍ በተለያዩ መንገዶች ወደ ውጪ አገር የሚያሸሹባት፣ የመሬት ወረራ የሚፈጽሙባት፣ የዚሁ ወንጀል ተባባሪዎቻቸው ባጭር ጊዜ ሚሊዬነርና ባለፎቆች የሚሆኑባት፤ እነዚሁ ጥቂቶች እጅግ የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩባትና በአረብ፣ በእስያና፣ በምዕራብ አገሮች የሚንሸራሸሩባት፤ ባንጻሩ ግን ሠፊው ሕዝባችን የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ለልጆቹና ለቤተሰቡ የእለት ጉርስ ሊያቀርብ ያልቻለባትና፣ በቤት ኪራይ፤ በትራንስፖርትና ልዩ ልዩ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት ምክንያት የሚሰቃይባት፤ በመንግስት መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በተረኞች የሚንገላታባት፣ ትምህርታቸውን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያጠናቀቁ ወጣቶች በችሎታቸውና የሥራ ብቃታቸው (merit) ሳይሆን በማንነታቸው ምክንያት የሥራ እድል የሚነፈጉባት አገር ሆናለች።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ የአገር ግንባታ ታሪኳ ታላቅና ዓይነተኛ ሚና ያላቸው የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎችም እንዲሁ የአገዛዙ ሰለባ መሆናቸው ይታወቃል። ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ “ግልጽ ጦርነት” ታውጆባት እጅግ በርካታ ቤተክርስቲያኖች እንዲወድሙና ካህናቶቿ እንዲገደሉ፣ ለብዙ ዘመናት በቤተ ክርስቲያኗ ሕጋዊ ይዞታ ሥር በነበሩና የመስቀልና የጥምቀት በዓል የሚከበርባቸውን ቦታዎች ፍጹም ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በመውረስ፣ የሃይማኖት ግጭት መነሻ እንዲሆኑ በማድረግና በታቦተ ሕግ ፊት ጥይት በመተኮስ ምዕመናንን በመግደል፣ በቤተ ክርስቲያኗ እምነትና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ጭምር ጣልቃ በመግባት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ በተሰጣቸው ሃይማኖታዊ ካድሬዎች ዘለፋ፣ ስድብና የማዋረድ ተግባር ሲፈጸምባት መቆየቱ ይታወቃል።

በሌላ በኩል ኦነጋዊው ኦህዴድ የፍትህ ሥርዓቱን ፈጽሞ ማላገጫ ያደረገው ሲሆን ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸውና መንግስትን በመተቻተቸው ብቻ በዘፈቀደ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በየጎዳናው ማንነታቸው በማይታወቅ ግለሰቦች የሚታፈኑበትና ዓይናቸው ተሸብቦ ታርጋ በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ተወስደው ምስጢራዊ በሆኑ እስር ቤቶች የሚሰቃዩበት፣ የሚንገላቱበት፣ ምናልባትም የሚገደሉበት፣ የፖለቲካ እስረኞች በፍርድ ቤት ከሕግ ውጪ የሚንገላቱበት፣ ያላግባብ ንግድ እስኪመስል ድረስ ከፍተኛ የዋስትና ገንዘብ የሚጠየቁበት፣ ፍርድ ቤት በነጻ ያሰናበታቸውን እስረኞች ፖሊስ ከሕግ በላይ ሆኖ የማይለቅበት ወይንም ከእስር ቤት ቢለቀቁ እንኳን ሌሎች ባለጊዜ የጸጥታ አካላት በእስር ቤት ደጃፍ በመጠበቅ እንደገና ወደ እስር ቤት ወይም ወዳልታወቀ ሥፍራ የሚወስዱበት (revolving door jailing)፣ እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ጠበቆቻቸው ጋር የማይገናኙበት፣ ዓቃቤ ሕግ እጅግ አሳፋሪ በሆነ ድራማ የሀሰት ምስክሮችን የሚያቀርብበት፣ ጠቅላይ ሚነስትሩ ከሕግ በላይ ሆኖ በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ የህወሃት ባለስልጣኖችን ሽማግሌዎች ናቸው በሚል ሰበብ ከእስር የሚለቅበት (ለምሳሌ ስብሃት ነጋና መሰሎቹ) ባንጻሩ ግን ሌሎች አረጋውያንን በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ወደ እስር በተደጋጋሚ የሚወረውርበት (ለምሳሌ አቶ ታዴዎስ ታንቱ)፣ ፍርድ ቤቶች ነጻነታቸው የተገፈፈበትና የተረገጠበት (trampled judicial independence) መሆኑ ይታወቃል።

ኦነጋዊው ኦህዴድ ባለፉት አምስት ዓመታት ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ከፈጸማቸው እጅግ አስከፊና ፋሽስታዊ በደሎች በተጨማሪ የመናገር፣ የመጻፍና፣ ሃሳብን በሰላማዊ መንገዶች የመግለጽ መብቶችን ሲረግጥ የቆየ ሲሆን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተደረገው አገራዊ ምርጫ ከሕዝብ ጋር ተገናኝተው ፕሮግራማቸውንና ፖሊሲያቸውን እንዳያስተዋውቁ ከፍተኛ እንቅፋት፣ ወከባና እንግልት ከመፈጸሙ ባሻገር የኢትዮጵያን ሕዝብ በመሪዎቹ አማካኝነት ክዶ ለአገዛዙ በአሽከርነት ያደረውን ኢዜማ አባላት ሳይቀር በማሠርና በመግደል፣ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በሰልፍ ለመግለጽ የወጡ ዜጎችን ስናይፐር ጠመንጃ በታጠቁ ወታደሮች በጥይት ተኩሶ በመግደል (ለምሳሌ ፋሽስታዊ ቡድኑ ሥልጣን በያዘ ባጭር ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ አምስት ወጣቶች መገደላቸው ይታወሳል)፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰልፈኞችንና ሌሎች ተቃዋሚዎችን በጦላይ፣ በቃሊቲ፣ በዝዋይ፣ ብር ሸለቆና በሌሎች እስር ቤቶች በማጎርና እስረኞቹም ሲፈቱ “አይደገምም” የሚል ከናቴራ በማልበስና በማዋረድ ከደረሰባቸው የአካል ጉዳት በተጨማሪ የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረግ፣ ከጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ ወደ አዲስ አበባ በመንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ አማራ ወገኖቻችን አባቶቻቸውና አያቶቻቸው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ወደመሠረቷትና ወደገነቧት ዋና ከተማቸው እጅግ አሳፋሪና ፍጹም በታሪካችን ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ (unprecedented) እንዳይገቡ በመከልከል፣ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተ መንግስት ከኢትዮጵያችን ታሪክና ከትውልድ አእምሮ እንዲፋቅ እንዲሁም በመጪዎቹ ትውልዶች ጭምር እንዳይታወቅ ለማድረግ በታቀደ ኢትዮጵያን እጅግ አድርጎ በሚጠላው ኦነጋዊው ኦህዴድ አመራር በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሠሪ ሴራና በለመደው የአጭበርባሪነት (smart Alec) ሥራው “የአንድነት ፓርክ” የሚል ስያሜ እንዲሰጠው በማድረግና የአገራችን ብሔራዊ ምልክት ሆኖ ለብዙ ዘመናት የቆየውን አንበሳ በፒኮክ ወፍ በመተካት እንዲሁም በአዲስ አበባ፣ በሐረርና በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ብሔራዊ ቅርሶቻችንን በማፍረስ (desecration)፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማው ጋር በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች የፓርላማውን አባላት እጅግ ከፍተኛ ንቀት በተመላበት ድምጸትና ሁኔታ በዕብሪትና በማን አለብኝነት የሚያዋርድበትና የሚዘልፍበት፣ እንዲሁም ከአረብ፣ ከቱርክና ሌሎችም በታሪክ ለኢትዮጵያችን ቀና አመለካከት ካልነበራቸውና ከሌላቸው መንግስታት ጋር የሚያደርጋቸው ስምምነቶች ለሕዝብ በይፋ የማይገለጹበት መሆኑ ይታወቃል።

ከዚህ በላይ ለአብነት ያህል ለማሳየት እንደተሞከረው አገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና፣ ማህበራዊ የቀውስ ማዕበል ስትናወጥ የቆየች ከመሆኑም በላይ፣ የመንግስት ሥልጣንን በተቆጣጠረው ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን እኩይ የኦሮሚያን የቅዠት ሪፐብሊክ የመመሥረት ዓላማ ምክንያት ህልውናዋ እጅግ አሳሳቢ የሆነ አደጋ (existential threat) ላይ ወድቋል።

ይህ ሁሉ በሆነበትና አሁን በምንገኝበት እጅግ አሳሳቢ ወቅት “ምን መደረግ አለበት?” የሚለው ጥያቄ በሕዝባችን ላይ በየጊዜው የሚደርሰው ጭፍጨፋ፣ መከራ፣ ስቃይና ሰቆቃ እንዲሁም እያንዣበበ ያለው የከፋ አደጋ እጅግ አድርጎ ያሳስበኛል፤ እንዲሁም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፣ መጻኢ ዕድሏም ዕንቅልፍ ይነሳኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ሊጠይቀው የሚገባ ጥያቄ ነው። በመሠረቱ የዚህ ጥያቂ መልስ በሕዝባችን እጅ ይገኛል፤ ምክንያቱም ሕዝብ የአገሩ ባለቤት ነውና!!!

ከሰሜን ኢትዮጵያ ጫፍ አንስቶ እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ ጫፍ አንስቶ እስከ ምዕራብ የሚኖረው ሕዝባችን በአገሪቱ በነጻነት፣ በእኩልነትና፣ በፍትህ የመኖር፣ ዜግነታዊና ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮ በማናቸውም የአገሪቱ ከፍሎች የመኖር፣ የመሥራት፣ ቤተሰብ የመመሥረት፣ ልጆች የማሳደግ፣ ሀብት የማፍራት፣ ወዘተርፈ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ሕዝባችን ይህን በየትኛውም አገር የሚኖር ማንኛውም የሰው ልጅ በዜግነቱ ሊያገኝ የሚገባውን መብት ባሁኑ ወቅት ያገራችንን የመንግስት ሥልጣን የተቆጣጠረው ጠባብ ጎሰኛ ኦነጋዊ ኦህዴድ አገዛዝ ሥር ሊጎናጸፍ የማይችል ከመሆኑም በላይ ይልቁንም ይህ ቡድን አገራችንን ለማፈራረስ ገፍቶ ከገደል ጫፍ እንዳደረሳት መገንዘብ ይቻላል። ሕዝባችን ይህን በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስና የሚጨበጥ (palpable) አደጋ ለመቀልበስ በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች (ፖለቲካዊ፣ ሙያዊ፣ ሲቪክ፣ አካባቢያዊ (grassroot organization) ወዘተርፈ በመሳተፍ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፋፋመውን ሠላማዊ ትግል አጠናክሮ በመቀጠል ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል።

በዚህ ረገድ ባለፉት አምስት ዓመታት በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ሲደርስ የቆየውን እጅግ አስከፊ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎችና የተለያዩ በደሎች በአደባባይ በጀግንነት ሲቃወሙ የቆዩትና ትዳራቸውንና ሕጻናት ልጆቻቸውን እንዲሁም ተጠዋሪ ወላጆቻቸውን ትተው በየጊዜው እየታፈኑ የዘረኛው ቡድን መሪዎችና ቧለሟሎቻቸው ብቻ በሚያውቁቸው ሕገ ወጥ የምስጢር (dungeons) እና በሌሎችም በሚታወቁ እስር ቤቶች በተደጋጋሚ ሲወረወሩና ሲደበደቡ የቆዩ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ጠበቆች፣ እና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፣ እንዲሁም ሌሎች በአገር ውስጥና በውጪ አገር የሚኖሩ አንዳች ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ለሕዝባችንና ለአገራችን ያላቸውን ታማኝነት በዕውነት መሠረት ላይ አጽንተው በመታገል ላይ ያሉ ሐቀኛ ጋዜጠኞች፣ አዕምሮአቸው የታወረ ጠባብ ብሄርተኞች ኢትዮጵያችንን ለማፈራረስ ለአሥርት ዓመታት የረጩትንና እየረጩ ያሉትን የጎሳ ፖለቲካ መርዝ ለማርከስ በግጥሞቻቸው፣ በዘፈኖቻቸው፣ በጽሑፎቻቸው፣ በድራማና ቲያትሮቻቸው ኢትዮጵያችንን በግልና በቡድን (choir) በየጊዜው የሚዘክሩ ታዳጊ ወጣቶችና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች (ለምሳሌ “ኢትዮጵያ የኛ እናት” የተሰኘው ዝማሬ)፣ አቢይ አህመድና ሽመልስ አብዲሳ በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ያደረሱትንና የሚያደርሱትን ፋሽስታዊ በደል በመቃወም በድፍረት በአደባባይ ያወገዙትንና አቢይ አሕመድ ሥልጣን እንዲለቅ ጭምር በግልጽ ደብዳቤ የጠየቁት ለዕውነትና ለፍትሕ የቆሙትን የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎች፣ ለሌሎች የተከበራለቸው መብት ለኔም ሊከበርልኝ ይገባል በማለት ተምሳሌታዊ የሆነ የሰላማዊ ትግል ያደረገው የጉራጌ ሕዝባችን (ምንም እንኳን የአገራችን የፌዴራል አወቃቀር መሆን ያለበት ወያኔ ሕዝባችንን ከፋፍሎ ለመግዛትና አገራችንን ለማፍረስ አልሞ በአገራችን ላይ በጫነው ሕገ መንግስት አማካኝነት በቋንቋ ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች እንደሚደረገው በጂኦግራፊያው አቀማመጥ፣ የአስተዳደር አመቺነት፣ ወዘተርፈ መሠረት መሆን ያለበትና ይህም ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ዘረኛው የኦነጋዊ ኦህዴድ አገዛዝ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ትግል ተገርስሶ ሕዝባችን መክሮና ዘክሮ በሚያጸድቀው አዲስ ሕገ መንግስት ሲተገበር መሆኑን ያስተውሏል)፣ በኑሮ ውድነት ምክንያት ለመኖር መቸገራቸውን በማመልከት የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከዚህም ባሻገር በቅርቡ የኦነጋዊው ኦህዴድ ካድሬዎች ምሁራኑን በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊና ወንጌላዊ ብልጽግና ርዕዮተ ዓለም በድፍረት ሊያጠምቋቸው (አየርላንዳዊው ጸሐፊ ጆርጅ በርናንድ ሾው “ድፍረት ከድንቁርና ይመነጫል” እንዳለው) በሰበሰቧቸው ጊዜ ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው፣ በአዲስ አበባ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጎሰኛው ቡድን በላያቸው ላይ ሊጭንባቸው የሞከረውን ዘረኛ መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ እምቢኝ በማለት መምህራኖቻቸውና ወላጆቻቸው ጭምር በተሳተፉበት ያደረጉት ተጋድሎና “እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም” ዝማሬ፣ በቅርቡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ከንቲባዋና መሰል የኦነጋዊው ኦህዴድ አመራሮች ከሕግና ሥርዓት ውጪ በዕብሪትና በማን አለብኝነት አዲስ አበባን በሚመለከት የሚወስዷቸው ርምጃዎችን በአደባባይ መቃወምና ምክር ቤቱን ለቀው ሊወጡ እንደሚችሉ መጠቆማቸው፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና በባህር ዳር ከተማ በተደረጉ የ”ብልጽግና” ፓርቲና የፓርላማ አባላት በተገኙባቸው ዝግ ስብሰባዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምሪት የተሰጣቸውንና አገራችንን ወደ ከፍተኛ አዘቅት እና የከፋ የርስ በርስ ጦርነት በመግፋት ላይ የሚገኙትን በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙትና በመፈጸም ላይ የሚገኙትን የፓርቲውን ከፍተኛ አመራር አባላት በልበ ሙሉነት ወንጀሎቻቸውን ያጋለጡትና የመንግስትን ሥልጣን ቁንጮ የተቆናጠጡትን ፋሽስቶች ሥልጣን እንዲለቁ የጠየቁትን የፓርቲ አባላት ወደ ፊት ታሪክ እንደሚዘክራቸው ዕሙን ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስና የምንፈልገውን ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት፣ ብሎም ነጻነት፣ ዕኩልነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ለመመስረት ሲካሄድ የቆየው ሰላማዊ ትግል ባንጻራዊነት በአጭር ጊዜና በአነስተኛ መስዋዕትነት ውጤታማ እንዲሆን መላው ህብረተሰባችን በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ እንዲሁም በሌሎች የሕብረተሰብ አደረጃጀቶች (grassroot organizations) መሳተፍና መታገል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ህብረተሰባችን አገራችን የገጠማትን የህልውና አደጋ በቅጡ ተገንዝቦ በአፋጣኝ (with a sense of urgency) ካልተነሳ የገዥዎቻችን አካሄድ ወደ ሰፊና እጅግ የከፋ የርስ በርስ ጦርነት ሊያስገባን የሚችልና አገራችንንም ሊያፈራርስ የሚችል በመሆኑ ነው። እንዲያውም በዚህ ጸሐፊ እምነት አገራችን ባሁኑ ወቅት የምናየውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና፣ የማህበራዊ ምስቅልቅሎቸና የህልውና አደጋ ላይ የደረሰችበት ዋነኛ ምክንያት ህዝባችን በአገራችን ፖለቲካ “የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፤ ልጨቆን፣ ልናቅ፣ ልዋረድ አይገባኝም፣ ሰብዓዊና የዜግነት መብቴ ሊከበር ይገባል፤ የአገሬ ባለቤትና የመንግስት ሥልጣን ምንጭ እኔው ነኝ” በሚል ተገቢና ፍጹም ትክክለኛ ስሜት ያለው ተሳትፎ አናሳነት (limited) በመሆኑና የፖለቲካ መድረኩና የመንግስት አስተዳደሩ በተሳሳተ ትርክትና ጥላቻ አዕምሮአቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ በተሞላ (indoctrinated)፣ ዕውቀት በሌላቸው፤ ብሔራዊ ስሜትና የአገር ፍቅር፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ርህራሄ ፈጽሞ በሌላቸው ዕኩዮች እጅ ላይ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በመውደቋ ነው። የግሪኩ ፈላስፋ ፕሌቶ እንዳለው “ሰዎች በፖለቲካ ውስጥ ባለመሳተፋቸው የሚደርስባቸው አንዱ ቅጣት ከእነርሱ ባነሱ ሌሎች ሰዎች መገዛት ነው።”

አገራችን በአካዳሚ ትምህርት፣ በሥራ ልምድ፣ እንዲሁም በሕይወት ተመክሮ ከፍተኛ የዳበረ ዕውቀት ያላቸው፣ አስፍተውና አርቀው የሚያስቡ፣ የሀገር ፍቅር፣ ብሔራዊ ስሜትና ራዕይ ያላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች የተሠማሩ ዜጎች (የዩኒቨርሲቲና የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና አባላት፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች፣ ነጋዴዎች፣ ገበሬዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ወታደሮች፣ መሐንዲሶች፣ ስፖርተኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በግል ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ ኩባንያዎች፣ ፋብሪካዎችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች፣ በምድርና የአየር የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ የተሠማሩ ሠራተኞች፣ ወዘተርፈ) ያሏት አገር ናት፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ዜጎቿ በአገሪቱ ፖለቲካ በተገቢው መጠንና ደረጃ ባለመሳተፋቸው (“ፖለቲካና ኮሬንቲ በሩቁ” በሚል የተሳሳተ እሳቤ) የፖለቲካውን መድረክ ክፍተት (vacuum) ጎሰኞችና ፋሽስቶች በመሙላታቸው አሁን የምንገኝበት አገራዊ የህልውና አደጋ ላይ ወድቀናል። ይህ እጅግ የተሳሳተ አስተሳሰብ መቀየር ይኖርበታል፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገሮች የሚኖረው ሕዝባችን በተለይም አገራችን አሁን ባለችበት የህልውና አደጋ ምክንያት በፖለቲካ መሳተፍ የምርጫ (choice) ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ (necessity) መሆኑን ተገንዝቦ ዛሬ ነገ ሳይል በመረጣቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ ወይም ሌሎች ሕዝባዊ አደረጃጀቶች በመሳተፍ ኢትዮጵያችንን የማዳን፣ እንዲሁም ይህን ዘረኛ ሥርዓት ከሥሩ ነቅሎ ገርስሶ ለመጣልና ነጻነት፣ ዕኩልነት፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል መቀላቀል ይኖርበታል። እያንዳንዱ ዜጋ ለሰላማዊ ትግሉ በልዩ ልዩ መንገድ የሚያበርክተውን አስተዋጽኦ አሳንሶ ሳያይ (ምክንያቱም “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ነውና) የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል።

ሰላማዊ የትግል ዘዴ (የሥራ ማቆም አድማ፣ የመቀመጥ አድማ፣ የሻማ ማብራት፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ማህበረሰብን የማንቃትና የማስተማር ሥራ፣ ልዩ ልዪ ማዕቀቦችን ማድረግ፣ በሥነጽሑፍ፣ ግጥምና፣ ዘፈን ተቃውሞን ማሰማት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ የውጭ አገር መንግስታት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ዘንድ ድምጽን የማሰማት፣ ወዘተርፈ) ለነጻነት፣ ፍትሕና፣ እኩልነት እንዲሁም የመንግስት ለውጥ ለማምጣት ትግል ባደረጉ በብዙ አገሮች ውጤታማነቱ የተረጋገጠ እንደመሆኑ (ለምሳሌ ሕንድን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ለማውጣት በሞሐንዳስ ማህተማ ጋንዲ የተመራው የነጻነት ትግልና በአሜሪካ በዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መሪነት የተደረገው የሲቪል መብቶችን የማስከበር ትግል) ይህን ከአመጽ ትግል እጅግ በላቀ ሁኔታ የተሻለ ውጤታማ እንደሆነ በፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የተመሰከረለትን የትግል ስልት በአገር ውስጥና በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ከዚህ በላይ በተጠቀሱት አደረጃጀቶች አማካኝነት ሰላማዊ ትግሉን በማስፋትና በማጠናከር እንዲሁም የአገር ውስጥና የውጭ አገር ትግላችንን በተገቢው ሁኔታ በማቀናጀት በአገራችን ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመቀልበስና የጠባቡና ዘረኛውን ኦነጋዊ ኦህዴድ አገዛዝ ገርስሰን ለመጣል የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት እንነሳ።

በድንቁርናቸው፣ ጠባብነታቸው፣ ጎሰኝነታቸው፣ ዕብሪታቸው፣ ማን አለብኝነታቸው፣ ውሸታምነታቸው፣ ሌብነታቸው፣ ከሃዲነታቸው፣ ኢሰብአዊነታቸው ተወዳዳሪ ከሌላቸው እንጭጮች እጅ ላይ የወደቀችውን ውዲቷን ኢትዮጵያችንን ፈጥነን በመነሳት መልሰን እንረከብ (“Let’s Take Back Our Country”)!!!

ሃያሉና የፍትሕ አምላክ እግዚአብሔር ሕዝባችንና አገራችንን ኢትዮጵያን ይታደግልን!!! በሕዝቧ ላይ ይህን ሁሉ እጅግ አስከፊ መከራ፣ ሰቆቃና፣ እንግልት የሚፈጽሙትንና የሚያስፈጽሙትን ይበቀልልን!!! አሜን!!!

አስፋው ረጋሳ
ጥር 2015 ዓም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop