January 15, 2023
10 mins read

መርገመ ቴድሮስ – መስፍን አረጋ

king of King tewedros

እንደ ፋሲካ በግ፣ ሙክትና ሰንጋ
ቅርጫ ተቃርጠውሽ፣ የመሳፍንት መንጋ
መኳንንት ባላባት ሴታውል አንበልጋ(1) ፣
እየቦጠቦጡ በቆላ በደጋ
ሲግጡሽ አይቸ በጠባ በነጋ፣
እንዳተሞችብኝ፣ እንዳትሄጅ ባልጋ
ስለባባሁልሽ፣ ሆዴ ስለሰጋ፣
ፈልቅቄ በማውጣት ከነሱ መንጋጋ
ልታደግ ወስኘ የቀረሽን ሥጋ፣
በዚህ ውሳኔየ ቆርጨ እንድተጋ
ሚስት ገረድ ሁና ሳትለይ ከኔጋ
እንድታበራታኝ፣ እንድታረጋጋ፣
አምላክ የሰጠኝን ትልቂቱን ፀጋ፣
ይዤ ተዋበችን የኔይቱን ለግላጋ
በርሐ ገባሁን ፈንኘ(2) ልዋጋ፡፡

በመሳፍንት ዶማ፣ ዐንካሴ፣ ደንጎራ(3)
የፈራረሰውን የአንድነት ጎራ፣
ዳግመኛ ልክበው ስነሳ ከቋራ፣
እንቅፋቴ ሁሉ ጠፍቶ እስከሚጠራ
እባብና ዘንዶ፣ ጊንጥና ዳሞትራ(4)
ይነድፈኛል ብየ ቅንጣትም ሳልፈራ፣
ገብርየና ገልሞን አስከትየ ጭፍራ
ጠቅልን ኮልኩየ በርሬ እንዳሞራ
ፈጠኘ ደርሸ ከቀጠሮው ስፍራ፣
ጦርነት ገጥሜ በለበን ውጅግራ(5)
እያርበደበድኩኝ የጎጠኛን አውራ
ድል እመታሁኝ በተራ፣ በተራ
እያስተነፈስኩኝ የያንዳንዱን ጉራ፣
እንጨት ሳይቆረጥ ቤት እንዳይሠራ(6)
ሳልወድ በግዴ አንጀቴ እየራራ
ማጥፋት ነበረብኝ ያን ሁሉ ደንቀራ፡፡

ይሄን በማድረጌ ጸንተሽ እንድትኖሪ
ለወዳጅ ለጠላት እንድትጠነክሪ፣
ኢትዮጵያ ተብለሽ በስም ስትጠሪ
ክፉ እሚያስብሽን እንድታሸብሪ፣
ሲገባሽ በክብር ስሜን ልትጠሪ
አንችን እንዳስከበርኩ እኔን ልታከብሪ፣
በተቃራኒው ግን በሱ ተጻራሪ
ሁነሽ ምሳጋናቢስ ውልታ እማትቆጥሪ፣
አሳድመሽበኝ ባንዳና መሠሪ
እናቴን ጨምረሽ ስላልሽኝ ብራሪ
ቅማንት(7) ፣ ምናምንቴ፣ ኮሶ ሻጭ ቸርቻሪ
ቀማኛ፣ ወንበዴ፣ ሽፍታ፣ አሸባሪ
ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ጽንፈኛ አክራሪ፣
ከልቤ አዝኘብሽ፣ ገጥሜ ባዝማሪ
ረግሜሻለሁ ይይልሽ ፈጣሪ፡፡

ያደረ ለሆዱ፣ ለነጭ ፍርፋሪ
ከሃዲ፣ ጡት ነካሽ፣ ከጠላት መካሪ
እንግዴ ልጅ፣ ጭንጋፍ፣ ድባኖ(8) ፣ እራሪ፣
ክብረቢስ፣ ልክስክስ፣ ርካሽ፣ ቅራሪ፣
አተላ፣ አንቡላ፣ ፋንድያ፣ እዳሪ፣
አታላይ ቀጣፊ፣ ዋሾ አጭበርባሪ
የስልጣን ጥመኛ ሸፍጠኛ መሰሪ
ከዘርሽ አይጥፋ ይሁንብሽ መሪ፡፡

በንደዚህ ዓይነቱ ጸያፍ አስነዋሪ
ግምትምት ብለሽ፣ በራስሽ ስታፊሪ
አንገትሽን ደፍተሸ፣ ስታቀሪቅሪ፣
በጎጥ ተከፋፍለሽ ስትነቋቆሪ
በሰይፍ በገዠራ ስትመታተሪ
የልጆችሽን ደም ስታንዠረዥሪ፣
ሬሳ እየገፋሽ በመንገድ ቆፋሪ
ከውሻ አሳንሰሽ ጅምላ ስትቀብሪ፣
ያኔ ተጸጽተሸ እያልሽ ኡኡ እሪ
ውለታየን ቆጥረሽ እንድትዘረዝሪ፡፡

በቁም ተማርኬ በነጭ ፊታውራሪ
ለተተኪው ትውልድ ዋና አስተዳዳሪ
አልሆንም በማለት ፍራት አስተማሪ፣
ጀርባየን ሳላሳይ ለንግሊዝ ወራሪ
እንደጠበኩ ክብሬን አንጡራየን(9) ቀሪ፣
ፎክሬ አቅራርቸ በሰንጎ ደርዳሪ
ጎርሸ ጥይቴን፣ የሽጉጤን አብሪ
ያረፍኩበትን ቀን እንደታጠኩ ሱሪ
ሁልጊዜ በያመት እንድትዘክሪ፡፡

እፍረት ባይኖርሽም፣ ይሉኝታም ባታቂ
እስኪ መልሽልኝ፣ ባጭር ተጠየቂ?
በጥቁር መዲና ባዲስ አበባ ላይ
በተሰየመልኝ ኢምንት አደባባይ
የሚያልፈው ጎዳና ተንጣሎ የሚታይ፣
ጥቁርን በሚንቀው በዘረኛው እኩይ
እንዴት ይሰየማል በንግሊዙ ጠቅላይ?

መርገመ ቴድሮስን አልበላውም ዳዋ(10)
ጦቢያን ሊያራቁታት ሊያደርጋት አሸዋ፣
አባቱ ጠጥቶ በሰላቶ ጽዋ
ዜናዊ አበቀለ መለስን ባድዋ፣
ቅጠሉ መረራ መርዘኛ ግራዋ
በግንዱ ጠምጥሞ ሐረገ ዋልዋ
አድጎ ተንሰራፍተ የደረሰ ሺዋ(11) ፡፡

ቀጠለና ደግሞ ፈዋሽ መስሎ ቀርቦ
ዐብይ ተተካ የመለስ ተስቦ፡፡
መደመር እያለ ቃሉን ብቻ ክቦ
በጎጥ የሚቀንስ በክልል ቀንብቦ
እኛን የሚያከሳ ኬኛን አደልቦ፡፡

ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ
አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ
ደባ እየፈጸመ የሚሰብክ ደቦ(12)፡፡

እንዴት ቢረግማት ነው ቴውድሮስ አምርሮ
ጦቢያ ያበቀለች ጭራቅ በአጋሮ?
ምንስ ቢከፋ ነው የቴወድሮስ መርገም
ጦቢያን የሚገዛት ኦነጋዊ እርጉም?

 

የቃላት መፍቻ

  • አንበልጋ፡ ፈሪ፣ ሥራ ፈት፣ ሴታውል፡፡
  • ፈነነ፡ ወዶ ዘመተ፡፡  ፋኖማለት ደግሞ ወዶ ዘማች ማለት ነው፡፡
  • ዐንካሴ፡ በቀጭን በትር ጫፍ ባንድ በኩል የተዋደደ ሹል ብረት፣ ያንካሴ የወላሴ እንዲሉ፡፡   ደንጎራማለት ደግሞ ከጫፉ ማረሻ የመሰለ መቆፈርያ የተዋደደበት አጣና ማለት ነው፡፡
  • ዳሞትራ (black widow)፡ የሚናደፍ መርዛማ፣ ባለጠጉር ክሰልማ ሸረሪት፡፡
  • ለበን፡ ዘጠኝ ጎራሽ ነፍጥ፣ ጠመንጃ፡፡  አጭር ለበን፣ ረዥም ለበን እንዲሉ፡፡  ውጅግራወይም ውዥግራ (fushigi) ደግሞ ሌላ ዓይነት ነፍጥ ነው፡፡
  • አብናቶቻችን(ማለትም አባቶቻችን እና እናቶቻችን፣ forebears) እንደሚሉት፣ እንጨት ሳይቆረጥ ቤት አይሠራም፡፡  ስለዚህም ሀገር የሚባል የፈራረሰ የጋራ ቤት ሲሠራ፣ አያሌ እንጨት እየተቆረጠና እየተፈለጠ፣ እየተጠረበና እየተላገ መስዋት ይሆን ዘንድ የግድ ነው፡፡  ቤቱ የበለጠ የፈራረሰ ከሆነ ደግሞ፣ መስዋእትነቱም በዚያው ልክ የከፋ ይሆናል፡፡  ስለዚህም፣ ይህ መስዋዕትነት ሌላ ምንም ሳይሆን የግድ መሠራት ያለበት የጋራ ቤት ሲሠራ የሚያስከትለው አይቀሬ መዘዝ (inevitable consequence) ወይም ተጓዳኝ ጉዳት (collateral damage) ነው ማለት ነው፡፡
  • ቅማንት፡ በበጌምድር አውራጃ በከርከርና በጭልጋ የሚገኝ ነገድ፡፡  አንድ የዚህ ነገድ ዐባል የሆነ ሰው ዐደን ዐድኖ ሲመለስ፣  ሌለው ሰው ያገኘውና መኑ አንተ (አንተ ማነህ) ብሎ ሲጠይቀው ከመ አንተ (እንደ አንተ) ብሎ ስለመለሰለት፣ ከዘመን ብዛት ከመ አንተ የሚለው ወደ ቅማንትተለወጠ ይላሉ ታላቁ ሊቅ አለቃ ደስታ ተክለወልድ (ዐዲስ ያማረኛ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 1075)፡፡
  • ድባኖ፡ አጭር፣ የደበነ፣ ዝንብ አከል፡፡
  • አንጡራ(ኦሮምኛ)፡ ሰው ለፍቶ፣ ደክሞ፣ ጥሮ፣ ግሮ ያገኘው ሐብት፣ንብረት፡፡
  • ዳዋ፡ ጥሻ፣ ሣር፣ ቅጠላ ቅጠል፣ ክረምት አፈራሽ፡፡  መናኝ ዳዋ ለብሶ፣ ጤዛ ልሶ፣ ዲንጋ ተንተርሶ ይኖራልእንዲሁም ዐይጥ በበላ ዳዋ ተመታ አንዲሉ፡፡
  • ሺዋ(ሺሕ፣ ሺኋ)፡ የሴት ስም፡፡  የግሼ ባላባት ያገባት የቤታማራ (ወሎ) ባላባት ሴት ልጅ፡፡  ብዙ ልጆች ስለወለደች፣ አባቷ ልጀ ሺኋ (ሺ የሆንሽው ልጀ) አላት፡፡  በዚህ ምክኒያት የልጆቿ አገር ሺዋ ተባለ፡፡  አለቃ ደሰታ ተክለወልድ፣ ዐዲስ ያማረኛ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 1217፡፡
  • ደቦ፡ ብዙ ሰው ተሰባስቦ በሕብረት የሚሠራው ሥራ፡፡  ሌላኛው ስሙ ጅጊ ነው፡፡

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop