December 10, 2022
18 mins read

አደገኛ የበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮዎችን የማይፀየፍ ትውልድ

December 10, 2022
ጠገናው ጎሹ

ዳንኤል ክብረት ማህበር ከተሰኘ ማህበራዊ ሚዲያ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ በጥሞና ተከታተልኩት ።
lemdቃለ ምልልሱን በጥሞና የተከታተልኩት እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት የቆጠረውን ፊደል  ፣ ያነበበውንና የሚያነበውን ንባብ እና የቃረመውንና የሚቃርመውን ተረትና ምሳሌ ጥሩ አድርጎ ባሰለጠነው አንደበቱ እያዥጎደጎደ ሲፈልግ ትናንት የተናገረውን ዛሬ ከሚለው ጋር በቀጥታ እያላተመ  እመኑኝ ሲል ፈፅሞ ምንም የማይመስለው፣ እና ለምንና እንዴት ተብሎ ሲጠየቅ ደግሞ “አይ እናንተ ስላልገባችሁ ነው እንጅ ማለት የፈለግሁት እኮ …”  በሚል በህዝብ መሠረታዊ ግንዛቤ (እውቀት) ላይ ሊሳለቅ ሲሞክር ጨርሶ ህሊናውን የማይኮሰኩሰው ግለሰብ የተለየ በጎ የፖለቲካ፣ የሞራልና የመንፈስ ሰብዕና ተላብሶ ይመጣል የሚል እምነት ስለነበረኝ አይደለም።

ይህ ማለት ግን እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት የአስመሳይነትና የአድርባይነት ልክፍተኞችን እንደ ልማደኛ እየቆጠሩ ማለፍ ያስፈልጋል ማለት አይደለም። የእንዲህ አይነት ግለሰቦችን  አስተሳሰብና አካሄድ በጥሞና እየተከታተሉ ቢቻል ከተዘፈቁበት ክፉ የቤተ  መንግሥት ፖለቲካ አባዜ ራሳቸውን እንዲታደጉ፣ ካልሆነ ግን ጊዜና ሁኔታ አምጦ በሚወልደው ህዝባዊ እምቢተኝነት ተገደው ገለል እንደሚደረጉ በግልፅና በቀጥታ መንገር  የግድ ነውና።

አዎ! በሰአብዊ ፍጡርነት ካባ/ለምድ ተጀቡነው (ተሸፍነው) የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገ እጣ ፈንታውን የመከራና የውርደት እያደረጉበት ያሉትን እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ተኩላዎች ከምር ለመፀየፍና በቃችሁ ለማለት የተሳነው ትውልድ የዴሞክራሲና የዴሞክራሲያዊት አገር ናፋቂ የመሆኑ እንቆቅልሽ በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ በመሆኑ በእጅጉ ሊያሳስበንና ተገቢውን ሁሉ ለማድረግ ከምር ሊያነሳሳን ይገባል።

ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ የምንገኝበት ሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የጎሳ ጥንት ስሌት ፖለቲካ  ቁማርተኞች (ነጋዴዎች) ሥርዓት ማብቃትና በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት ካለበት እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ህሊናቸውንና አንደበታቸውን ለእኩይ ተግባር አሳልፈው የሸጡና የሚሸጡ ወገኖች በግልፅና በቀጥታ በቃችሁ መባል ይኖርባቸዋል።

እንደ ገና ልድገመውና ቃለ ምልልሱን የተከታተልኩት ከእንደ ዳንኤል ክብረት አይነት መስሎና አስመስሎ በመኖር እኩይ ሰብእና ከተካነ “ሙዓዘ ጠበባት”  በጎ ነገር ይገኛል በሚል ተስፋና እምነት በፍፁም አይደለም።  ይህንን ለመረዳት ዳንኤል ክብረት የሸፍጠኛ፣ የሴረኛና የጨካኝ ተረኞችን የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ከተቀላቀለበት ጀምሮ የሆነውንና ያደረገውን ከምር ልብ ማለት ብቻ በቂ ነው።

አዎ! የዳንኤል ክብረት እጅግ አሳሳችና አደገኛ ፖለቲካዊ ፣ ሞራልዊና መንፈሳዊ ሰብእና ትዕሥትን የሚፈታተን ቢሆነም በጥሞና ለተከታተለ ሰው ገና ለቃለ ምልልስ ሊቀርብ ነው ወይም የአደባባይና የአዳራሽ ውስጥ ዲስኩር ሊደሰኩር ነው ሲባል ምን  ሊል  እንደሚችልና  እንዴት  ሊለው  እንደሚችል  ለመገመት  ብቻ ሳይሆን  ለማወቅም  አያስቸግርም   አዎ! አገረ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከኖረችበት የመከራና የውርደት አዙሪት እና  ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኛ ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን ከገባችበት እጅግ ለማመን የሚያስቸግር ምድረ ሲኦልነት መውጣትና ዴሞክራሲያዊት አገር ማድረግ ካለብን እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት እጅግ ወራዳና አዋራጅ ወገኖችን አስተሳሰብና አካሄድ በተመለከተ አካፋን አካፋ በሚል ደረጃ  መነጋገር ይኖርብናል ።

እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ወገኖች ፍርፋሪ የሚወረውሩላቸውን እኩያን የቤተ መንግሥት ጌቶቻቻውን ያስደስትልናል ብለው ካመኑ ሃሰቱን እውነት፣ ኩነኔውን ፅድቅ፣ የግፍ ግድያን የግጭት ጉዳይ፣ ኢፍታዊነትን ፍትሃዊነት፣ የሰብእና ታናሽነትን ታላቅ ሰብእና፣ ኢሞራላዊነትን ሞራላዊነት፣ ጦርነትን ሰላም፣ ርሃብን ጥጋብ፣ ቁልቁል መውረድን ከፍታ፣ ውድቀትን ትንሳኤ ፣ ሲኦልን ገነት፣ ውድመትን የልማት ትሩፋት ፣ እስርና እንግልትን ህግ ማስከበር ፣ የታሪክ አተላነትን የታሪክ አርበኝነት ፣ ገዳይነትንና አስገዳይነትን የአገር ባለውለታነት ፣  ወዘተ አድርገው በማቅረብ “እውነት እውነት እንላችኋለን እመኑን” ሲሉን ጨርሶ ህሊናቸውን አይኮሰኩሳቸውም ።

ይህ እጅግ አስከፊ ምንነታቸውና ማንነታቸው በእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ወገኖች የተጋለጠባቸው መስሎ ሲታያቸውና የሚጣልላቸው የአድርባይነት ፍርፋሪ አደጋ ላይ የሚወድቅ ሆኖ ሲሰማቸው ደግሞ  የአገር ተደፈረች እሪታቸውንና ውግዘታቸውን ያለ ምንም ሃፍረት የሚያዥጎደጉዱ እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት እጅግ አደገኛ ግለሰቦች ከሚተራመሱበት የፖለቲካ አውድ እንኳንስ እውነተኛውን አምላክ “ለዘብተኛውን ሰይጣንም” ፈልጎ ማገኘት ፈፅሞ አይቻልም።

“ዲያቆን እና ሙዓዘ ጥበባት” የተሰኙ የማዕረግ ቅፅሎቹን የገደፍካቸው (የተውካቸው) በስህተት ነው ወይስ  ? ብለው የሚጠይቁ ወገኖች እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ጥያቄውም ተገቢ ነው።

ለዚህ የሚኖረኝ መልስ የመርሳት ጉዳይ ሳይሆን እንደዚህ አይነት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የሆኑ ትርጉሞችና እሴቶች ያላቸውን የሙያና የእውቀት ባለቤትነት ማዕረግ መጠሪያዎችን እንደ ዳንኤል ክብረት ለመሰሉ እጅግ በተበላሸና አደገኛ በሆነ የፖለቲካና የሞራል ሰብእና ለተለከፉ ወገኖች መጠቀም ቅዱስና ርኩስ ነገሮችን የመቀላቀል ያሀል መስሎ ስለሚሰማኝ ልጠቀምባቸው አልፈለግሁም የሚል ነው። ይህንን አባባሌን በየዋህነትም ሆነ በማወቅ የዳንኤል ክብረትና የመሰሎቹ የማስመሰልና የአድርባይነት ሰለባዎች የሆኑ ወገኖችን ስሜት በማይጎረብጥ አገላለፅ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነበር። ይህ ግን ለምድሩም ሆነ ከሞት በኋላ ተስፋ ለሚደረገው ህይወት ፈፅሞ አይጠቅምምና አላደረግሁትም።

አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ጥልቅና የተቀደሰ ትርጉም የተሸከሙ የማዕረግና የሙያ መጠሪያ ፅንሰ ሃሳቦችን (ቃላትን) እናት ምድርን ለንፁሃን ልጀቿ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምድረ ገሃነም/ሲኦል ላደረገና በመድረግ ላይ ለሚገኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት ታማኛ አማካሪ (አገልጋይ) ለሆኑ እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ወገኖች መጠቀም የራስን (የሰብአዊ ፍጡርነትን) መሠረታዊ  ማንነትና ምንነት ብቻ ሳይሆን  አምላክን ራሱን በአስከፊ ወንጀል የተዘፈቁ ፖለቲከኞች ተባባሪ ማድረግ ነው የሚሆነው።

“ዳንኤልና መሰሎቹ በሠሩት ራሳቸው ይጠየቃሉ እንጅ ትውልድ ምን አደረገና ነው…? ” የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችልም እገምታለሁ። ለዚህ ያለኝ መልስ በሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ  መከረኛውን ህዝብ የመከራና የውርደት ናዳ ያወረዱበትንና እያወረዱበት የቀጠሉትን እኩያን ገዥ ቡድኖችን እና እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት እጅግ ሃሰተኛ፣ ነውረኛ፣ ህሊና ቢስ፣ እና ጨካኝ አድርባይ አሽከሮቻቸውን ፈፅሞ ለመፀየፍ እና የነቃ፣ የተደራጀና የተቀናጀ ትግል ለማካሄድ የተሳነው ትውልድ ሃላፊነቱን አልተወጣምና ራሱን መመርመር ይኖርበታል የሚል ነው።

አዎ! እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት የተቀደሰውን ሃይማኖታዊ እምነት ከለየለት የሸፍጠኞች፣ የሴረኞችና የጨካኞች የፖለቲካ ሥርዓት አማካሪነታቸው ጋር እያቀላቀሉ ህዝብን ፍፃሜ ያጣ የመከራና የውርደት መናኸሪያ (ሰለባ) እንዲሆን ሲያስደርጉ  በቃችሁ ለማለት የተሳነው ትውልድ የትኛውን ዴሞክራሲና የትኛዋን ዴሞክራሲያዊት አገር እንደሚናፍቅ ለመረዳት የሚቻል አይመስለኝም።

ምንም እንኳ ዳንኤል ክብረት በቃለ ምልልሱ ለተነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ የሄደባቸው መንገዶች ሁሉ የራሱን ግዙፍና ግልፅ የፖለቲካና የሞራል ሰብእና ውድቀት ከመግለፅ ያለፈ ፋይዳ ባይኖራቸውም አንድ ጉዳይ ግን ባይገርመኝም በእጅጉ አሳዝኖኛል። ያሳዘነኝ ዳንኤል ክብረት ስለ ተናገረው ሳይሆን ዘመን ጠገቡና ማቆሚያ ያጣው የዚህ ትውልድ ውድቀት እንቆቅልሽ መቸና እንዴት ነው የሚፈታው? የሚለው ጥያቄ እንኳንስ አመርቄ የሆነ በቅጡ ስሜት የሚሰጥ መልስ ሳያገኝ የመቀጠሉ ግዙፍና መሪር እውነት ነው።

ዳንኤል ክብረት “እውነትን የማውቀው በማውራት ወይም በመናገር ሳይሆን በመኖር (ሆኖና አድርጎ በመገኘት ነው)” በሚል በመከረኛው ህዝብ መሠረታዊ ግንዛቤ (እውቀት) ላይ እጅግ ርካሽና ጨካኝ ስላቅ ሲሳለቅ “ለነውረኝነትህና ለንቀትህ ገደብ ይኑረው!” ለማለት ፖለቲካዊና ሞራላዊ ልእልና የሚሳነው ትውልድ እጣ ፈንታው የሸፍጠኞች፣ የሴረኞችና የግፈኞች ፖለቲካ ሥርዓት እና የግብረ በላዎቹ ሰለባ ሆኖ ቢቀጥል ያሳዝን እንደሆነ ፈፅሞ አይገርምም!

ውድ አገር ወዳድ ወገኖች ሆይ! ይህንን የዳንኤል ክብረትን “የእውነተኝነት ሰብእና” ዲስኩር በሚሊዮኖች የግፍ አሟሟት፣ በብዙ ሚሊዮኖች የቁም ሰቆቃ እና በአጠቃላይ በመከረኛው ህዝብ ሁለንተናዊ ጉስቁልና ላይ ለተሳለቀውና በመሳለቅ ላይ ለሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ  የቅርብና ታማኝ አማካሪ ከሆነው ዳንኤል ክብረት ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር ከምር ተመልከቱት!!!

እንደ አገር መሪነቱና የንፁሃንን መከራና ሰቆቃ ቢያንስ በሰብዊነት ስሜት እንደሚረዳ ሰው “በሆነው ሁሉ እያዘንኩ ይህ አስከፊ ውድቀት ይቆም ዘንድ ሃላላፊነቴን  ለመወጣት ጥረት እንደማድርግ አረጋግጣለሁ” ለማለት የፖለቲካና የሞራል አቅም ፈፅሞ የሌለውን አብይ አህመድን የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ በእንባ ጎርፍ እንደሚታጠብ ሲነግረን ከንፈራችን እየመጠጥን እንድናምነው የከጀለን እኮ ሌላ ዳንኤል ክብረት ሳይሆን ዛሬም የመፀፀትና የመታረም ሰብእና ፈፅሞ የሌለው ዳንኤል ክብረት ነው።

የራሱን እጣ ፈንታ በነፃነት ለመወሰንና ለመኖር የሚያስችለውን  የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ትግሉን እየቀለበሱ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ  (ከመቃብር ሙትነት ባልተሻለ ) ሁኔታ የመከራና የውርደት ናዳ የሚያወርዱበትን ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችንና እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ግብረበላዎቻቸውን ከምር ለመፀየፍና በቃችሁ ለማለት በአስፈሪ ሁኔታ ወኔው የከዳው ትውልድ መቼና እንዴት ከተለከፈበት የምንነትና የማንነት ቀውስ ሰብሮ ሊወጣ እንደሚችል እንኳን ለማመን ተስፋ ለማድረግም  በእጅጉ ይከብዳል  ።

ይህ ትውልድ ከዚህ ክፉ አዙሪት ሰብሮ መውጣት ካለበት  በአንድ እጃቸው  መጽሐፍ ቅዱስ እና በሌላው እጃቸው   ደግሞ በንፁሃን ደም የጨቀየ የፖለቲካ ሰነድ  ተሸክመው  የመዳን ቀን አሁን ነውና  ንስሃ እየገባችሁ ተደመሩ የሚሉንን ዳንኤል ክብረቶችን  በቀጥታና በግልፅ በቃችሁ ማለት የግድ ነው!

እናም ልብ ያለው ልብ ይበልና አደገኛ የበግ ለምድ ለባሾችን በቃችሁ ይበል!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop