December 11, 2022
10 mins read

በአዲስ አበባ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ

abn

ላለፉት ሶስት አስርተ አመታት በሃገራችን ሰፍኖ የኖረውን የአፓርታይድ አገዛዝ ለውጦ ዲሞክራሲያዊ ሥርአትን በማስፈን እኩልነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እንደሀገር በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለ እና በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ የታለፈ ቢሆንም ፣ ሁኔታወች ዛሬም ከድጡ ወደ ማጡ እየሆኑ ፣ ፈተናዎቻችን እየበረቱ እና አዳዲስ ችግሮች እየተፈጠሩ በአሁኑ ወቅት በሀገራዊ ኅልውና እና ሃገራዊ አንድነታችን ላይ አደጋ የጋረጡ ፈተናዎች ለማያባራ ቀውስ ዳርገውን እንደ ሃገር እየታመስን እንገኛለን፡፡

ይህን በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለ ምስቅልቅል የማስቆም ኃላፊነት ያለበት መንግስታ በአሸባሪና አፍራሽ ሀይሎች ላይ ጨርሶ የበላይነት መያዝ ባለመቻሉ፣ ህግና ስርአት እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈን ቁርጠኛ ባለመሆኑና ፍላጎትም የሌለው በመሆኑ፣ እኩልነትና ፍትህን ለማስፈን ዳተኛ በመሆኑና ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ፤ እንዲሁም ውስጠ መዋቅሩ የአፍራሽ ሀይሎች መደበቂያ ዋሻ በመሆኑና እኒሁ መንግስታዊ ሽፋን የተላበሱ አፍራሽ ሀይሎች የችግሮቻችን መነሻና አባባሽ በመሆናቸው ችግሮች እየተወሳሰቡ እንዲሄዱ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅት በፌዴራል መንግስት መዋቅር ውስጥ በመሸጉ እኒሁ አፍራሽ አካላት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልል የመንግስት መዋቅርን የሚዘውሩ አካላት መካከል የተናበበ ቅንጅት ምክንያት እየተባባሱ ካሉ ቀውሶች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መዝሙር እና ባንዲራን በኃይል ለመጫን እየተሄደ ያለው የማንአለብኝነት አፍራሽ ዘመቻ ቀዳሚው ነው፡፡

የነዚህ መንግስታዊ ሀይሎች ቅንጅት በአዲስአበባ ከተማ እየፈፀመ ያለው ነውር ባንዲራ በጉልበት መስቀልና የባርነት መዝሙር በግዴታ ለማዘመር መሞከር ብቻ ሳይሆን ጨቅላ ህፃናትን “ኦሮሞ የሆኑ” እና “ኦሮሞ ያልሆኑ” የሚል የከፋፋይ አገዛዝ ደንብ ጭምር እያስፈጸመ ይገኛል። የኦሮሚያ ክልል ባንዲራን በጉልበት ሰቅሎ የባርነት መዝሙር ህፃናቱን ለማዘመር የኦሮሚያ ክልል አድማ ብተና ፖሊስ ሃይል ለመጠቀም መሞከሩ ህገ ወጥና ኢሞራላዊ ድርጊት ከመሆኑም ባሻገር ለቅኝ አገዛዝ ምኞቱ ሲል የመዲናዋን የነገ ተስፋዎች በ segregation policy እያመከነ ያለበት ሁኔት በፍጹም የሚወገዝ ነው።

ይህ ከህግም ሆነ ከፖለቲካ መርሆች አንጻር ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እየተከናወነ ያለው መንግስት በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ሰብአዊ ቀውሶች እና በሽበርተኛ ድርጅቶች እየተፈጸሙ ያሉ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ለማስቆም ቁርጠኝነት ባጣበት ወቅት በመሆኑ ሀገሪቱ ከዳርም ከመሃልም በተለኮሰ ግጭት ወደማያባራ ሁሉን-አቀፍ ቀውስ እንድትቀጥል እያደረጋት መሆኑ ያሳስበናል፡፡ ፖለቲካዊ ቀውሱ እና ምስቅልቅሉ ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲወርድ እና የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የሰላም አየር እንዲደፈርስ እያደረገ መሆኑም እጅጉን ያሳስበናል።

ይህ ተግባር የከተማዋን ነዋሪ ለአካል እና ለመንፈስ ያለመረጋጋት መዳረጉን፤ የመማር ማስተማር ሂደቶች መስተጓጎልን፤ በመምህራን እና ተማሪዎች ላይ ጥቃት፣ እስር እና እንግልት ማስከተሉን፤ በከተማዋ ውስጥ ያሉ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ተቋማትን በስጋት ውስጥ እንዲወድቁ ማድረጉን፤ እና የህዝባችንን ማህበራዊ ትስስር የሚያላሉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መፍጠሩን አብን ይገነዘባል፡፡

በመሆኑም:-

1:- የኦሮሚያ ክልል መገለጫ የሆኑትን መዝሙር እና አርማን የአዲስ አበባ ከተማ ህጻናት ተማሪዎች በግድ እንዲዘምሩ እና እንዲያውለበልቡ በማድረግ የመላው ሀገሪቱ መዲና እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካዊ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችን ከተማ የግጭትና የብጥብጥ ማዕከል እንድትሆን የሚደረገውን ጸብ አጫሪ አካሄድ አብን ያወግዛል፣ በአስቸኳይ እንዲቆምም ይጠይቃል::

2:- የችግሩ ጠንሳሽ እና አስፈጻሚው የኦሮሚያ ክልልን ህገወጥ እና ኢ-ፍትሐዊ የፖለቲካ ፍላጎት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ላይ በግዴታ በመጫን የከተማዋን ሰላም እየረበሹ እና የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነቱን እያሻከሩ የሚገኙት ዋነኛ ተዋናዮች በፌዴራል መንግስት የተለያዩ እርከኖች መሽገው የሚገኙ፣ ህዝብ ታግሎ የጣለውን የትላንቱን የጭቆና አገዛዝ መልሶ እንዲመጣ በተለያየ አካሄድ ሀገርና ህዝብን የማተራመስ አጀንዳን ባነገቡ አካላት እና መሠል በኦሮምያ ክልል አስተዳደር ውስጥ በገሀድ የሚታይ ሸኔአዊ መዋቅር በቅንጅት የሚፈጽሙት ሆኖ ሳለ ችግሩን በሌሎች አካላት ላይ ለማላከክ መሞከር ተቀባይነት የሌለው እና ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት የማያስችል መሆኑን አብን ያምናል፡፡

3:- በተያያዘም በአድርግ አታድርግ ውዝግቦች የተነሳ በተፈጠሩ ግጭቶች ለእስር የተዳረጉ አካላትን በአፋጣኝ በመፍታት መንግስት ሰላም የማውረድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አብን ይጠይቃል፡፡

4:- የአዲስ አበባ ከተማን የአፍሪካ እና የመላው አለም የዲፕሎሚሲ ማዕከልነትን የሚጻረር በብሄር ፖለቲካ ቅኝት የሚዘወር የአንድ ክልል አስተሳሰብ በኃይል ለመጫን የሚደረገው ጥረት እንዲቆም እና በመዲናችን የሚገኙ የዓለም አቀፋ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት ከደህንነት ስጋት ነጻ እንዲሆኑ እና የሀገሪቱ ገጽታ እንዳይጠለሽ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አብን ይጠይቃል፡፡

5:- በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግስት እና በአዲስ አበባ ቻርተር ድንጋጌዎች በአዲስ አበባ ላይ የአንድን ክልል አርማ እና መዝሙር በግድ መጫንን የማይፈቅድ በመሆኑ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለችግሩ የማስተካከያ እርምጃ እዲወሰድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አብን ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አዲስ አበባ ከተማን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ እየተውተረተሩ ያሉት አካላት ምኞት በአጭር ይቀጭ ዘንድ ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀጥል እና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነቱን እንዲያጠናክር ለመላው የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪውን ያስተላልፋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ

ታህሳስ 01/2015 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop