ከፕሪቶርያው ስምምነት የምንማረው – ባይሳ ዋቅ-ወያ

መግቢያ፣

ባላፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶርያ፤ በፌዴራል መንግሥቱና በሕወሃት መካከል የተፈጸመውን ስምምነት አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች ተሠንዝረዋል። ስምምነቱን የደገፉም የተቃወሙም ነበሩ። በየራሳቸው ምክንያት። ሁለት ዓመት የፈጀው ጦርነት እጅግ አውዳሚ ቢሆንም፤ ተደራዳሪዎቹ ስምምነቱ ላይ ለመድረስ የፈጀባቸው ጊዜ በጣም አጭር ነበር። አሁን ድርድሩ በሰላም ተጠናቅቆ ተደራዳሪዎቹም ወደየቤታቸው ተመልሰው የስምምነቱን ይዘት በተግባር ለማዋል በተቻላቸው መጠን ደጋፊዎቻውን እያደፋፈሩ ተቃዋሚዎቻቸውን ደግሞ ለማሳመን ትልቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። ሰላም ጦርነትን ማሸነፉን በአደባባይ መቃወም የማያዋጣ መሆኑን የተረዳው ተቃዋሚም በየቀኑ እየለዘበ መጥቷል።

ማንኛውም ማኅበረ ሰባዊ ክስተት የራሱ የሆነ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ጠባሳ በማሕበረሰቡ ላይ ጥሎ ያልፋል። ስለዚህም የሰው ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ካለፈው ስሕተቱ እየተማረና እያስተካከለ ለሚቀጥለው ድርጊቱ እንደሚመች አድርጎ ማሕበረ ሰባዊ ዕድገትን ያጎለብታል። ካለፈው ስሕተት ተምሮ ያ ስሕተት እንዳይደገም የመትጋት ዕድል ለሁሉም ማኅበረ ሰብ እኩል የተሠጠ ጸጋ ቢሆንም፤ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ማኅበረ ሰባቸውን ከአደጋ የታደጉ መሪዎች ግን ብዙ አይደሉም። በተለይም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ።

በበኩሌ፣ ይህን የፕሪቶሪያ ስምምነት እጅግ በጣም አስተማሪ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ከውጭ ሲታይ እንደ ማንኛውም ያለፉት ጦርነቶቻችን በኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ የበላይነት ምክንያት ሕወሃት ተገድዶ እጅ የሰጠበት መድረክ ይመስላል። ግን አይደለም። ምክንያቶቹን ለጊዜው ወደ ጎን ትተን በውጤቱ ላይ ብቻ ብናተኩር፣ ይህ ስምምነት በጣም ብዙ ብዙ ታሪካችንን የቀየሩ ውጤቶችን አስመዝግቦ አልፏል። እንደ ታለመለት በተግባር ይተርጎም አይተርጎም ራሱን የቻለ ሌላ ጥያቄ ነው። የድርድሩ ሂደትና የተደረሰበት ስምምነት ግን እጅግ በጣም ታሪካዊና በደንብ ተጠንቶ ለትውልድ መተላለፍ ያለበት ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ነው።

 

ከስምምነቱ የተማርነው፣

በታሪካችን ውስጥ በተለይም የፊውዳል ሥርዓቱ ለዘመናት በተንሠራፋበት የሰሜኑ ያገራችን ክፍል፣ መሳፍንቶች ሲጣሉ፣ የግድ አንደኛው ወገን አሸንፎ መውጣት አለበት። ማሸነፍ ማለት ደግሞ “አሸንፌሃለሁና መሸነፍህን ብቻ አምነህ ተቀብለህ ከኔ ጋር በሰላም ትኖራለህ” ማለት ሳይሆን፣ መጀመርያውኑ ከኔ ጋር ለመጣላት ማሰብህ በራሱ ወንጀል ስለሆነና ከተሸነፍክም በኋላ ዳግመኛ ላትወጋኝ ማስተማመኛ ስለሌለኝ፣ ቢያንስ ቢያንስ ቀኝ እጅህን እቆርጣለሁ፣ አለበለዚያ ደግሞ ከነነፍስህ ወደ ገደል እውረውርሃለሁ ወዘተ ማለት ነበር። “ከተሸናፊ ጠላት” ጋር አብሮ በአንድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ በእኩልነት መኖር አይታሰብም ነበረ። አሸናፊ ተሸናፊውን፣ ማሸማቀቅ፣ ማዋረድ አለበት። የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ይህን የአሸናፊን ፋሺስታዊ ድርጊት ማኅበረሰቡ እንደ ጀብድ ቆጥሮለት፣ አዝማሪውና እረኛው በዘፈናቸው፣ ቄሱና ደብተራውም በምሳሌና በቅኔ ሲያሞግሱት ይስተዋላል።  አብዛኞቹ የዘመኑ ተከታታይ ነገሥታትም ሆኑ ሰፊው ሕዝብም ከድል በኋላ የሚገኘውን ዝና ለጋር አገራዊ ክብር እንደማዋልና፣ እርስ በርስ መሸማቀቁና መዋረዱ ትክክል አይደለም፣ ካለፈው እንማርና ለወደፊቱ፣ ቢቻል አለመግባባቶቻችንን በሰላም ለመፍታት፣ ካልሆነም ደግሞ ተሸናፊን ላለማዋረድ እንስማማ ብሎ የማኅበረ ሰቡን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ለመቀየር አይሞክሩም ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "በሕግ አምላክ" እልዎታለሁ፤ «የሕግ ቀለም»አስፈፃሚዎችንም ዛሬም ይፈነቃቅሉልን - ዐቢይ ኢትዮጵያዊ

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህን ኋላ ቀር የፊውዳል ማኅበረ ሰብ ባሕል ይቀይራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት በተለይም ውጭ አገር ድረስ ሄዶ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰመው ወጣቱ ትውልድ፣ የተማረበትን አገር የአለመግባባቶችን መፍቻ ዘዴ አዋጪነት ባሕል ተገንዝቦ ወደ አገሩ ሲመለስ በተግባር ይተረጉምና ማኅበረ ሰቡን ከኋላ ቀር አስተሳሰቡ ወደ ፊት ያራምዳል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ራሱ ተመልሶ እዚያው ፊውዳላዊ ባሕል ውስጥ ሲዘፈቅ ይስተዋል ነበር። (የመኢሶንና የኢሓአፓን ታሪክ ልብ ይሏል)። ደርግ ባልወለደ አንጀቱ የትውልዱን እፍታ ወጣትና ምሑሩን፣ ከኔ የተለየ አስተሳሰብ አስተናግዳችኋል ብሎ በግራና በቀኝ ሲፈጅ፣ ከዚህ ድርጊቱ አንዳች ትምህርት ያልቀሰመው ኢሕአዴግም ተመሳሳይ የጭካኔ መዓት ከሱ የተለየ አስተሳሰብ በሚያስተናግዱት ላይ አወረደባቸው። ከወያኔ በኋላም የመጡት ተመሳሳይ መንግሥታትም ጠላት ተብሎ ከተፈረጀው ጋር ሰላማዊ የግጭቶችን መፍቻ ዘዴ ሲጠቀሙ አልተስተዋሉም። እስከ ታሪካዊው የኅዳር 2022 ዓ/ም የፕሪቶሪያው ስምምነት ድረስ።

የፕሪቶሪያው ስምምነት በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከዓድዋ ድል እኩል ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ አኩሪ ታሪክ ነው። የዓድዋው ድል በውጪ ወራሪ ኃይል፣ በተለይም በዘመናዊ መሣርያና ባደጉ አገራት ዕርዳታ አገራችንን በወረረው ጣሊያን ላይ ድል የተቀዳጀንበት የጀግንነት ታሪካችን ሲሆን፣ የፕሪቶርያው ስምምነት ደግሞ ለዘላለም ጠፍሮ ከያዘን “አለመግባባትን በጉልበት ብቻ የመፍታት” ኋላ ቀር ባሕል ለመላቀቅ ዳዴ የጀመርንበት ቀን ነው። የፊውዳል ባሕሉ አባዜ አልለቅ ብሎ የሚያስቸግራቸው አንዳንድ ጽንፈኞች ጎትተው ወደኋላ ካልመለሱን በስተቀር፣ ይህንን የፕሪቶሪያ ስምምነት እንደ መነሻ አድርገን፣ በአፈጻጸሙም ሂደት ከምናገኘው ልምድ ደግሞ እየተማርን  ቀስ በቀስ “አለመግባባትን፣ ተነጋግሮ በሰላም መፍታት” ወደሚለው የተስፋ ምድር እንደርሳለን ባይ ነኝ።

 

ለመሆኑ ከዚህ የፕሪቶሪያ ስምምነት ምንድነው የተማርነው?

ሀ) ከላይ ባጭሩ እንዳልኩት፣ ቅንነትና ፍላጎቱ ካለ ማንኛውንም የርስ በርስ ግጭት ወይም አውዳሚ ጦርነት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ ተኩስን በዘላቂነት አቁሞ ወደ ሰላም ግንባታው መግባት መቻሉን አስመስክረናል። ምንም እንኳ በውጭ ወረራ ጊዜ እሸናፊው ወገን ተሸናፊውን በእኩልነት ሳይሆን አስገድዶ የጦርነቱን መጨረሻ የሚያረጋግጥ ስምምነት ውል ማስፈረም የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ቢችልም፣ የርስ በርስ ግጭቶች ወይም ጦርነቶች ግን የፈለገ መልክ ይኑራቸው፣ የፈለገውን ያሕል አውዳሚ ይሁኑ መጨረሻቸው ስምምነት መሆኑን ተረድተናል። በየርስ በርስ ጦርነት ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ የለምና!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጭራቅ ሽማግሎች-አዞ ሲውጥ ያለቅሳል፣ ዕባብ ሲነክስ ይለሰልሳል፣ በግ ያራጁን ቢላ ይልሳል

 

) በዚች ምድር ላይ፣ የሰው ልጅ ነፍስ ከማንምና ከምንም በላይ ክቡር መሆኑንና በምንም ምክንያት መጥፋት እንደሌለበት አምነው ተቀብለው “አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር ድረስ” ወይም “ለኔ ማኅበረ ሰብ መሸነፍ ማለት ሞት ነው” የሚሉትን ጄኖሳይዳዊ አባባሎችን አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ “ሁለታችንም ተሸንፈናልና ካሁን በኋላ አለመግባባታችንን በሰላማዊ መንገድ ማለትም፣ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መንገድ እንፍታ” ብለው መስማማታቸው ሌላው ወሳኝ የማዕዘን ድንጋይ ነበር፣

 

ሐ) ሌላው ከዚህ ስምምነትና በስምምነቱ ሂደት የተማርነው ነገር ቢኖር፣ በዘመናዊ የመንግሥታት ግንኙነት (International relations) ውስጥ የዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ ጣልቃ ገብነት ወደድንም ጠላንም አይቀሬ መሆኑን ነው። እንደ ለመድነው፣ “ለቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከክን” “በአንነካም ባይነታችን ዓለም ያወቀን” ወዘተ እያልን በአራቱም ማዕዘናት ሰልፍ ወጥተን “የምዕራቡን ዓለም ብናርበደብድም”፣ መጨረሻ ላይ የአንድ እዚህ ግባ የማይባል በዝቅተኛ ደረጃ ከሚገኝ የአሜሪካ መንግሥት ዲፕሎማት “ትዕዛዝ” ልናመልጥ አልቻልንም። በርግጥም የአሜሪካንን መንግሥት “ምክር” ባንሰማ ኖሮ ሊደረግብን የታቀደው ማዕቀብ እጅግ በጣም ሊያዳክመን ይችል ነበር። አስቡት እስቲ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ወዳጆችዋን ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካና ኤዥያ አገራት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንኳን በአገራቸው ማረፍ ይቅርና በግዛታቸው አየር ላይ እንዳይበር ጫና ስታሳድርባቸው! በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሉት ይሆንብን ነበር!

 

መ) ማንኛውም መንግሥታዊ ውሳኔ ምናልባት አብዛኛውን እንጂ መላውን የአገሪቷን ዜጋ ሊያስደስት አይችልም። የፕሪቶርያውም ስምምነት ከዚህ አላመለጠም። አብዛኛው ሕዝብ ሆ ብሎ በደስታ ሲቀበለው፣ የተወሰኑ ጽንፈኞችና እነሱ በቀደዱለት ቦይ ዝም ብሎ በየዋህነት የሚፈሰው ሰፈው ሕዝብ ስምምነቱን ከልቡ አለተቀበለውም። በተለይ የጦርነቱን ገፈት በምንም መልኩ ያልቀመሱት የዲያስፖራ ዜጎቻችን ከዚያ ከሞቀ ቤታቸው፣ “ወያኔ ላይ ወሳኝ ወታደራዊ ድል ተጎናጽፈን ከምድረ ገጽ ካላጠፋነው በስተቀር አገሪቷ ዘላቂ ሰላም አይኖራትም” እያሉ በየሚዲያው ተቋማት የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ይስተዋላሉ። ሌሎች ደግሞ “እጅግ በጣም ተራቅቀው” የስምምነቱን በጎ ጎን ሳይሆን፣ በያንዳንዱ አንቀጽ መካከል ጎደሎውን ፈልገው፣ “እንዲህ የተባለው እኮ ከኋላው ይህንን ለማለት ነው” እያሉ፣ ነገ ከትግራይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በሰላም አንድ ላይ መኖራችን ተረስቶ፣ የለመድነውን የጥርጣሬ፣ ያለመተማመን፣ ቂም የመያዝ፣ ባሕላችንን ይዘው በአደባባይ ወጥተው ሲጮሁ ይታያሉ። የሃሳብ ነጻነት ነውና ይበሉ ብሎ ከማለፍ በስተቀር ሌላ ምን ሊባል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለጎንደር ሕዝብ

 

መደምደሚያ

ስምምነቱ፣ እስከነ ጥቃቂን ጉድለቶቹ በተግባር የመተርጎሙን ሂደት ተጀምሯል። ከልምድ እንደ ታየው፣ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከሚደረገው ሙከራ ይልቅ፣ ስምምነቱን ሥራ ላይ የማዋሉ እንቅስቅሴ እጅግ በጣም አድካሚ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት፣ የጦርነቱን መጀመርያና መጨረሻ የሚወስኑት በጦርነቱ ውስጥ በቀጥታ የማይካፈሉና የውድመቱን ገፈት የማይቀምሱ ግለሰቦች (መሪዎች) ስለሆኑ፣ ለነሱ ከጦርነቱ ወላፈን ራቅ ብለው ሰላም በሰፈነበት አካባቢ በቅንጡ ሆቴሎችና ባማሩ መሰብሰቢያ አዳራሾች ውስጥ ሆነው መደራደሩና መፈራረሙ ይቀላቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ፣ በእነዚሁ መሪዎች ትዕዛዝና ውትወታ፣ ለሆነ “ቅዱስ ዓላማ” ወደ ጦርነቱ የገባው ወጣት ትውልድ፣ ጦርነቱን በአሸናፊነት ጨርሶ “ጠላቱን” ካላንበረከከ ምቾት አይሰማውም። ስለዚህ ታጣቂዎቹ በስምምነቱ መሠረት በቀላሉ ተጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ይመለሳል ብሎ መገመት አይቻልም። (በዚሁ ጉዳይ ላይ አንድ ራሱን የቻለ አጭር ጽሁፍ ይዤ ከሰሞኑ ብቅ ልል ዕቅድ ስላለኝ ላሁኑ ይህንኑ ካልኩ ይበቃል)።

እንግዲህ ትልቁ የቤት ሥራና ኃላፊነት ያለው በኛ፣ የስምምነቱ አወንታዊ ጎን ይበልጥ ይመዝናል ብለን በተቀበልነው ላይ ነው። ይህም ማለት፣ የስምምነቱን ቃልና መንፈስ እንደ ታለመለት ሁለቱ ወገኖች ጠብመንጃቸውን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ እንዳያነሱና በአገሪቷ ከዳር እስከ ዳር ሰላም እንዲነግሥ በያለንበት ሆነን የተቻለንን እናድርግ ነው። እስቲ ሁላችንም በየሙያችን እንሰለፍ። ሁላችንም የፖሊቲካ ተንታኝ አንሁን። ፖሊቲካን ለፖሊቲከኞች እንተውና በተማርነውና ልቀን በተገኘንበት መስክ ብቻ ተሰልፈን፣ ፖሊቲከኞች በሙያቸው ሊጠቀሙበት የሚችሉትን “ጥሬ ሸቀጥ” አምርተን እንስጣቸው። ይህም ማለት በቀላሉ፣ ሓኪሙ ስለ ኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሁኔታ፣ መሃንዲሱ ስለ መንገዶቻችንና ድልድዮቻችን ችግር፣ የታሪክ ምሑሩ ስለ ጋራ ታሪካችን ችግር፣ የሕግ ባለሙያው በአገሪቷ ውስጥ የሕግ የበላይነት ያለመከበር ምክንያት፣ ኤኮኖሚስቱ ስለ ኤኮኖሚ ችግራችን ላይ ያተኮሩ ሳይንሳዊ ጥናቶችን አምርተን፣ ፖሊቲከኞች እንዲጠቀሙበት እናመቻችላቸው። በአጭሩ፣ ሁላችንም በየሙያችን ብንሰለፍ ማን ምን ሠራ ብለን ለመጠየቅና ለማስጠየቅም ያመቻልና። በቸር ይግጠመን።

******

 

ኖቬምበር 15 ቀን 2022 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com

3 Comments

  1. በይሳ ነባሩ አለም የተገለጠልህ አልመሰለኝም የፖለቲካ ማስተሮችህ በቀደዱልህ ቦይ የምትፈስ መሰለኝ የአቶ ጌታቸው ረዳን የቢቢሲ ቃለ ምልልስ ተመልከተው አልሰማም ካልክና ከአቶ ጌታቸው አውድ ባልተያያዘ መልኩ የምታደነቁረን ከሆነ ጽሁፍህን እዚህ ባትለጥፈው ጥሩ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share