አሜሪካኖችን ከህውሃት ጋር ያወዳጃቸውን ሚስጥር ካላወቅን ጦርነቱ አይቆምም በሚል በአቶ አብዱራህማን አህመድ ለአንድ አፍታ ወግ በሚባለው የዩቱቭ ቻናል የሰጡትን ሀተታ አስመልክቶ የቀረበ የግል ግምግማ!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ህዳር 15፣ 2022

ከአስራአምስት ቀናት በፊት አቶ አብዱራህማን አህመድ የህውሃትን አነሳስና አስተዳደግ፣ እንዲሁም መንፈሱ ጦርነትን በማካሄድና በመዝረፍ መታነፁን አስመልክቶ፣ ቀዳማዊ ወያኔና የአሁኑን ወያኔ አመጸኛ ባህርይ ተመሳሳይነት በሚገባ ለማስረዳት ሞክረዋል። ህወሃት በመጀመሪያ ደረጃ ለትግራይ ብሄረሰብ ሳይሆን ለራሱ ጥቅምና የበላይነትን ለመጎናጸፍ ሲል ያራባቸው የተሳሳቱ ትረካዎች በተወሰነው የትግራይ ብሄረሰብ ክፍል ጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ እንድልዩ ፍጡር እንዲያመልከው ለማድረግ የበቃና በምንም ዐይነት በድርድር የማያምን መሆኑን በሚገባ ተንትነዋል። ድርድር ሲባልም በሁለት ድርጅቶች፣ በተለይም ደግሞ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ባላቸውና ህብረተሰብአዊ ችግሮችን በፖለቲካ ውይይትና ደርድር ለመፍታት ይቻላል ብለው በሚያምኑና በመንግስት መሀከል የሚደረግ ድርድር ሲሆን፣ በመቀበልና በመስጠት የሚዘጋ ነው። ከዚህ ባሻገር ለውይይትም ሆነ ለድርድር ዝግጁ ለመሆን የግዴታ ሰፋና ጠለቅ ያለ ምሁራዊ መሰረትና ብስለት አስፈላጊ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የተለያዩ ድርጅቶችም ሆነ መንግስት  የሚያምኑባቸው የየራሳቸው ርዕዮተ-ዓለም ሊኖራቸው ይገባል። ይህንን መሰረት በማድረግ ነው ወደ ድርድር ሊቀርቡ የሚችሉትም። ይሁንና ግን ርዕዮተ-ዓለሜ ይህ ነው፣ ከዚህ ፍቅቅ ልል አልችልም የሚባል ከሆነ ደግሞ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ፖለቲካዊ ሳይሆን ቀኖናዊ አስተሳሰብ ይሆናል። ለማንኛውም ከዚህ ዐይነቱ ግንዛቤ ስንነሳ የህወሃትም(ወያኔ) ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ እወክለዋለሁ የሚለው የአቢይ አህመድ አገዛዝ ምን ዐይነት የፖለቲካ ፍልስፍናና ርዕዮተ-ዓለም እንዳላቸው ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ስለሆነም ምንም ዐይነት የፍልስፍናና የርዕዮተ-ዓለም መመሪያ የሌለው እንደ ህወሃት የመሰለው ቅርጽ የሌለው ድርጅት ስለፖለቲካ ያለው ግንዛቤ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። ህወሃት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሌለውና መንፈሱ በፖለቲካ ቲዎሪ ያልታነፀ በመሆኑም በአጉል ትዕቢት በመወጠር በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ህብረተሰብአዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚፈልገው በመሳሪያ ወይም በጦር ትግል ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብም በእሱ ብቻ ሳይሆን በሚከተሉትም አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች መንፈስ ውስጥ ዘልቆ የገባ ነገር ስለሆነ እነዚህን ሰዎች በፖለቲካ ትንተናና በሎጂክ ማሳመን በፍጹም አይቻልም። አርቆ ማሰብ የሚለውን በጣም አስፈላጊ ጽንሰ-ሃስብ አያውቁም። ስለሆነም የሞራል ብቃት የሌለውና የተወሰነ ስነ-ምግባርን መመሪያ አድርጎ ያልታገለና የማይታገል ድርጅት ስለሆነ ለሰፊው የትግራይ ብሄረሰብ በተጨባጭ ነገሮች የሚመነዘር መፍትሄ ለማቅረብ አልቻለም፤ የኑሮ ሁኔታውን እንዲያሻሽልና ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረው አላደረገውም።  ወያኔ አላስፈላጊና እልክ አስጨራሽ ጦርነት ለ17 ዐመታት ያህል ካካሄደና ቁጥራቸው በቅጡ የማይታወቁ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ከሁለቱም ወገኖች ካስጨረሰና ስልጣንም ላይ ከወጣ በኋላ ከዚህ ዐይነቱ አስቸጋሪና በቀላሉ ለማስረዳት ከማይቻል አደገኛና አገር አፍራሽ ባህርይው በፍጹም የተላቀቀ ኃይል እንዳይደለ ከትንተናቸው መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ይሉናል፣ ስልጣንን ከተቆናጠጠ በኋላ የራሱን የበላይነት በሚገባ ለማደላደል ሲል ኢኮኖሚውን መቆጣጠርና መዝረፍ፣ እንዲሁም የተወሰነውን የትግራይን ክልል መገንባትና የጦር ኃይሉንም ማጠንከር ነበረበት።

የአቢይ አህመድ አገዛዝም ፖለቲካ የህብረተሰብን ችግር መፍቺያ ሳይንሳዊ መሳሪያ አድርጎ የሚቆጥር ሳይሆን  መሸወጂያና ተንኮል መስሪያ መሳሪያ አድርጎ የሚገምት በመሆኑ ወያኔን ከመሰለው የወንበዴና ፋሺሽታዊ ድርጅት ጋር ለድርድር መቅረቡ የሚያስገርም አይደለም። ስለሆነም ነው በተለይም በአለፉት ሶስት ዓመታት ተኩል ጀምሮ የወያኔን አመራርና ካድሬዎችን የሚከታተል ሳይሆን ሌሎች የኢትዮጵያዊነትን አርማ አንግበው ለፍትህና ለዕኩልነት የሚታገሉትንና ሀቁን አፍረጥርጠው የሚጽፉትንና የሚናገሩትን  የሚያሳድደው። ይህም ማለት አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ ስልጣን ከያዙ አንድ ዓመት ባልሞላቸው ጊዜ ውስጥ ነው ወደ ሰይጣንነት የተለወጡትና ህዝባችንን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የከተቱት። ገንዘብና ሌሎች የጥሬ-ሀብቶችን ወደ ውጭ የሚያሸሹት የወያኔ ካድሬዎች  ለጥቂት ጊዜያት ከታሰሩ በኋላ እንዲፈቱ በማድረግና ወደ ውጭ እንዲወጡ አመቺ ሁኔታን በመፍጠር ዛሬ አሜሪካን አገር የቤንዚን ማደያና ትላልቅ ሱቆችን በመግዛት ተንደላቀቅው የሚኖሩ ናቸው። አቢይ አህመድ  ከኢትዮጵያ ህዝብ ይልቅ አገር አፍራሽና ዘራፊ፣ እንዲሁም በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደሉትንና ያሰቃዩትነ ነው የሚያፈቅረው ማለት ይቻላል። ይህም የሚያረጋግጠው የአቢይ አህመድ አገዛዝ ለፍትሃዊነት ያልቆመና የኢትዮጵያን ህዝብ እንደማይወክል ነው። እዚህ ላይ ወያኔን አስመልክቶ በጣም ጥሩ ትንተና የሰጡት አቶ አብዱራህማን አህመድ አቢይና አገዛዙ የሚሰሩትን ከፍተኛ ወንጀልና የፖለቲካ ስህተት ፍርጥርጥ አድርገው ለመናገር አልፈለጉም። ነገሩ ይገባኛል፣ ምናልባት የአገዛዙን ማንነትና የሚሰራውን ወንጀል በግልጽ ቢናገሩ ኖሮ ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊሆን ይችላል።

ለማንኛውም ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ስትራቴጂያዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በቁጥጥሩ ስር አውሎ ከዘረፈ በኋላና ሰፊውን ህዝባችንንም ወደድህነት ዓለም እንዲገፈተር ካደረገ በኋላ በዚህ ዐይነቱ የዘረፋና አገርን የመከፋፈል አካሄዱ ሊገፋበት በፍጹም አልቻለም። በደረሰበት ጫናና ለሰፊው ህዝብም የሚሰጠው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መፍትሄና መልሶች ስላልነበሩት ሳይወድ በግድ ስልጣኑን ለአቢይና ለግብረአበሮቹ ለመልቀቅ ተገዷል። ህወሃት ይህንን ስምምነት በማክበርና እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ ከጥቂት ወራት በኋላ በማኩረፍ እንዳለ ትግራይ በመሄድ ልክ ራሱን እንደ አንድ መንግስት በመቁጠርና እንደገናም ወደስልጣን ሊመለስ የሚችልበትን ዘዴ በማሰላሰል፣ ከብዙ ዝግጅት በኋላ ትግሬ ውስጥ በሰፈረው የሰሜኑ ዕዝ በመባል በሚታወቀው ወገኑ በሆነው ወታደር ላይ በተኙበት ጦርነት በመክፈት በአንድ ምሽት ብቻ ከስምንቶ መቶ በላይ የሚቆጠሩ ወታደሮች ህይወታቸው እንዲሰዋ ለማድረግ የበቃ ድርጅት መሆኑን በሚገባ ለማብራራት ሞክረዋል። በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ ተገዶ በከፈተው ጦርነት ሶስት ሳምንታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የህውሃት የጦር ኃይል በከፍተኛ ደረጃ እንዲዳከም ለማድረግ በቅቷል፤ ብዙ ግብዝ አመራሮችም ተገድለዋል። ይሁንና ከአንዴም ሁለቴም ሆን ተብሎ በተሰራው ወንጅል ህወሃት እንደገና እንዲያንሰራራ አመቺ ሁኔታን በመፍጠር  በተለይም በቆቦ አካባቢ ዘልቆ በመግባት በወሎ ህዝብ ላይ ለጭንቅላት የሚዘገንን ጭፍጨፋ አካሂዷል። ከተማዎችንና መንደሮችን አውድሟል። ትምህርትቤቶችን በማፈራረስና የልምምድ መሳሪያዎችን በማውደም፣ ሌሎችን ደግሞ ዘርፎ ወደ ትግራይ አጓጉዟል። ከዚህም በላይ ባልቴቶችና ህፃናትን በመድፈር ህይወታቸው እንዲበላሽ ያደረገ አረመኔያዊ ድርጅት ነው። ህወሃት ከጥፋት በስተቀር ቀና ተልዕኮ የሌለው ድርጅት መሆኑን  ነው ያረጋገጠው።  በተባበሩት መንግስታት ደንብ መሰረት በህግ የተከለክሉ እጅግ አደገኛ መሳሪያዎችን በመጠቀም አብዛኛዎቹ ህይወታቸው እንዲቀጠፍ በማድረግ፣ ሌሎች ደግሞ ሰውነታቸው ውስጥ ዘልቆ ከገባው ምስማር ጋር እየተሰቃዩ እንዲኖሩ ለማድረግ የበቃ ፋሺሽታዊ ቡድን ነው። አቶ አብዱራህማን አህመድ ህወሃት የፈጸመውን ግፍ  በሚገባ ለማብራራት ሞክረዋል።

በአቶ አብዱራህማንም ዕምነት ይህ ዐይነቱ አመጸኛና እርኩስ ድርጅት አንዳለ እስክልወደመ ድረስ የትግራይ ብሄረሰብም ሆነ፣ በተለይም የአፋርና የወሎ ህዝብ እፎይ ብለው በሰላም ሊኖሩ እንደማይችሉ ነው የተናገሩት፡፟፡ ስለሆነም ከእንደዚህ ዐይነቱ ድርጅት ጋር በድርድር አማካይነት ወደአንዳች ሰላምንና መረጋጋትን ወደሚያመጣ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደማይቻል ያላቸውን ጽኑ ዕምነት ለመግለጽ ሞክረዋል። በእሳቸውም ትንተናና ዕምነት ስምምነት ለመድረስ ያለው ዕድል ከሁለት በመቶ እንደማይበልጥ ነው። ይህም ማለት ድርድሩ ፋይዳ የሌለውና ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበት በመሆኑ ከድርድር በኋላ ይደረስበታል የሚባለው ስምምነት ዋጋ ቢስ እንደሚሆን ነው የሚነግሩን። ስለሆነም ሰፊው ህዝባችንና የተቀረውም የትግራይ ብሄረሰብ በዚህ ዐይነቱ ስምምነት ሰላምንና ብልጽግናን ለማግኘት በፍጹም አይችሉም ማለት ነው።  በሌላው ወገን ደግሞ በአቢይ አህመድ የሚመራው ጦር እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ በተከፈተበት ጦርነት እስከ ትግራይ ድረስ ዘልቆ በመግባት ብዙ ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ከተቆጣጠረና መቀሌንም ከከበበ በኋላ እዚያው እንዳሉ ከማንኮታኮት ይልቅ ልክ አቅም እንዳላቸውና ፖለቲካዊ ኃይልም እንደሆኑ ለምን ከህወሃት ጋር የእርቅ ድርድር ለማድረግ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳመራ ግልጽ ተደርጎ አልተብራራም። ይሁንና ግን የአቢይ አህመድ አገዛዝ ለምን ለድርድርና ለእርቅ ዝግጁ እንደሆነና፣ ከእንደዚህ ዐይነቱ የወንበዴ ድርጅት ጋር ለመደራደር አንዳንድ ባለስልጣናትን እንደላከና ከድርድሩም ምን ዐይነት ውጤት ማግኘት እንደሚችል በቅጡ የተረዳ አይመስልም።  በተለይም ደግሞ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ከዚህ ዐይነቱ የወንበዴና ፋሺሽታዊ ቡድን ጋር ተቀምጦ ለመደራደር ልዑካንን መላኩና መደራደሩም ለወያኔ ፖለቲካዊ ዕውቅና የሰጠው ብቻ ሳይሆን፣ ስልጣን ላይ  ከመውጣቱም በፊትም ሆነ ስልጣን ላይ ከወጣና ስልጣንን ለቆ ከሄደ በኋላ የፈጸመው ግፍ ሁሉ ትክክል እንደሆነና በዓለምአቀፍ መድረክ ላይ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሎታል። የፖለቲካ ኃይልና ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ያለው በማስመሰል በማይገባው ቦታ እንዲቀመጥ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል።  ይሁንና በዚህ ዐይነት አካሄዱ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮች የኢትዮጵያን ህዝብ እንዳለ የሚንቁና፣ ለታሪካችንና ለባህላችን ደንታ የሌላቸው ግብረ-ገብና ስነ-ምግባር የሌላቸው መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅተዋል።

ወያኔ ለአንድም ለመጨረሻም ጊዜ ካከተመለት በኋላ የቀረውን ኃይል እንዳለ መደምሰስና ደብዛውም እንዲጠፋ ለማድረግ ሲቻል የአቢይ አህመድ ለምን ከወያኔ ጋር ለመደራደር ዝግጁ እንደሆን ሚስጥሩን ማወቁ ይህን ያህልም ከባድ አይሆንም። በእኔ ዕምነትም ሆነ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚነግሩን ከሆነ የአቢይ አህመድ ለድርድር ዝግጁ መሆን በተለይም ትግራይ ክልል ውስጥ ዘልቆ በመግባት ህይወቱን የሚሰዋው የተጣመረ ኢትዮጵያዊ ኃይል ሌሎች ጥያቄዎችን ሊያነሳብኝ ይችላል፣ የስልጣን ዘመኔንም ያሳጥርብኛል ብሎ በመገመት ወያኔን በተዘዋዋሪ ስልጣን ላይ ሊመጣ የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት የተጓዘበት አደገኛ መንገድና የጮሌ ፖለቲካ መሆኑን ያምኑበታል። ከዚህ ዘልቆም በመሄድ  ህወሃት ህገ-መንግስቱን እስከተቀበለ ድረስ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ተቀባይነት እንዲኖረው ያስፈልጋል በማለት የሰነዘረው አባባል የሚያረጋግጠው የአቢይን አዕምሮ-ቢስነት ነው። ይህ ሰውዬ ለራሱ ብቻ ከማሰብና ራሱን ከማዳን በስተቀር ፖለቲካዊ በሆነ መንገድና ስትራቴጂካሊ ለማሰብ የማይችል በመሆኑ በፖለቲካ መድረክ ላይ መሰለፍና ስልጣንም ላይ መቆየት የሌለበት ሰው ነው። ከእሱ ጋርም የተሰለፉትና የሚያጅቡትም እንደነ ዲያቆን ዳንዓል ክብረት፣ የሰላም ሚኒስተሩ ታዬ ደንደአና ሌሎችም “የፖለቲካ ተፅዕኖ” ለማሳደር ይችላሉ የሚባሉት አድርባዮች በሙሉ ደቡብ አፍሪካ ላይ የተደረገውን “ድርድር” እንደሰላም አምጭና ጥሩ አጋጣሚ መፍትሄ በማየት የኢትዮጵያን ህዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሳይሆን አቢይን ስልጣን ላይ ለማቆየትና በአድርባይነታቸውም ጥቅማጥቅሞችን እያገኙ ዕድሜያቸውን ለማራዘም ሲሉ ህዝብን ለማሳሳት የሚናገሩት ሳይንሰ-አልባ የሆነ አነጋገር አቢይ ብቻ ሳይሆን እነዚህም ሰዎችም ጤናማ ጭንቅላት ይኖራቸው እንደሆን ለማመን በጣም ያስቸግራል። ሌሎችም በድርድሩ ውስጥ የተሳተፉትና በአገዛዝ ውስጥ የተካለሉት እነ ደመቀ መኮንና ሌሎችም ባለስልጣን ነን ባዮች ከተጠያቂነት የሚያልፉ አይደሉም። የወያኔን ግፍ ካለምንም በመቁጠርና በአቢይ አህመድ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፖለቲካዊ አካሄድ በመመራት ራሳቸው በነፃ ማሰብ እንደማይችሉ ለማረጋገጥ በቅተዋል። ማንኛውም ሚኒስተር የአገዛዙ አንድ አካልና አስፈጻሚም እንደመሆኑ መጠን የህዝብ ተወካዮች ነን ከሚሉት ጋር በመተባበርና በመመካከር የአቢይ አህመድን አደገኛና አገር በታኝ ፖለቲካ ማስቆም በቻሉ ነበር። ይህን ከማድረግ ይልቅ በአንድ ሰው በመመራት ለጥቅም ያደሩና ምንም ዐይነት የፖለቲካ መመሪያና ዕምነት የሌላቸውና ህሊና-ቢሶች መሆናቸው አረጋግጠዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው እነዚህ ሰዎች የቱን ያህል የፓለቲካ ንቃተ-ህሊናቸው ዝቅተኛ እንደሆነና በምንም ዐይነት የፖለቲካ ሰዎች አለመሆናቸውን ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦሮምያ ቤተ ክህነት፡- ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ - ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ወያኔ ወንበዴ፣ ዘራፊና ገዳይ፣ እንዲሁም የአገርን ብሄራዊ-ነፃነት ሻጭና አዋራጅ መሆኑ የተረጋገጠ ከሆነና  የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን ነኝ ብሎ ከሚያምን ጋር ለድርድር አብሮ መቀመጥ ከተቻለና ሌሎችም ሀብታቸውን ይዘው አሜሪካ እንዲሸሹ አመቺ ሁኔታዎች የሚፈጠርላቸው ከሆነ፣ ለምንስ ትናንሽ ወንጀል ከፈጸመው፣ ወይም በከፍተኛ ወንጀል በመከሰስ ወደ እስርቤት ከተወረወረውና፣ እንዲሁም ደግሞ መንግስት የሚሰራውን ህገ-መንግስትን የሚጥስ ወንጀል በሚገባ እየተነተኑ የሚያቀርቡትንና እስር ቤት ውስጥ የታጎሩትን እየፈቱ ከእነሱ ጋር የእርቅ ድርድር አይደረግም? እንደዕውነቱ ከሆነ በጋዜጠኝነት ሙያቸው የሞራል ግዴታ ሆኖባቸው አስፈላጊውን ትንተና የሚሰጡትን ትተን፣ ሌሎች በትናንሽም ሆነ በከፍተኛ ወንጀል ተጠርጥረውም ሆነ ተረጋግጦባቸው እስርቤት ውስጥ እንዲታጎሩ ከተደረጉት ጋር የወያኔና የግብረአበሮቹ ወንጀል ሲወዳደር ልዩነቱ የሰማይና የምድርን ያህል የሚርቅ ነው። የወያኔና የካድሬዎቹ ወንጀል በብዙ ሚሊዮን እጥፍ የሚበልጥ ነው። ወያኔ ከፈጸማቸው ለጭንቅላት ከሚዘገንኑ ነገሮችና አገርን በታቀደ መንገድ ለማፈራረስ የተጓዘበትን ሂደት ስንመለከት ታዲያ በምን ተዓምር ነው በአሰቃቂ ድርጊቱ፣ በአገር አፍራሽነቱ፣ በብሄራዊ ነፃነት አስደፋሪነቱ በዘራፊነቱና የአገራችንን ባህል በአውዳሚነት የሚታወቀው ለወያኔና ለግብረ-አበሮቹ ይህን ያህል ክብርና እንክብካቤ የሚሰጣቸው? ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ወያኔ ስልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ  በኋላና ስልጣንን ሳይወድ በግዱ ለቆ መቀሌ መሽጎ በተከታታይ እንደገና ጦርነት ካወጀ በኋላ ይህንን እርኩስ ተግባሩን የሚያካሂደው የአሜሪካና የግብረ-አበሮቹ ተላላኪ መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው። በተለይም ወያኔ ስልጣን ላይ ወጥቶ ተግባራዊ ያደረጋቸው የከፋፍለህ ግዛ “ፖለቲካና” የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ የአሜሪካንና የእንግሊዝ ፕሮጀክቶች ናቸው። አቢይና ግብረ-አበሮቹ የፖለቲካ ንቃተ-ሂሊና ያለቸው ሰዎች ቢሆኑና የብሄረተኝነት ስሜት ያላቸው ቢሆን ኖር ይህንን ሁኔታ ማጤን በቻሉና ሌላ ዐይነት ህዝብን የሚሰበስብና ኃይል የሚሰጠው ፖለቲካ ማካሄድ በቻሉ ነበር።

ያም ተባለ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ ድርድርና ስምምነት እንደገና ለሌላ በቀላሉ ማለቂያ ወደማይገኝለት ጦርነት እንደሚከተን የማይታበል ሀቅ ነው። የአቢይ አህመድና የግብረ-አበሮቹም ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ህዝብ በማዳከምና ሀሞቱ እንዲፈስ በማድረግ ስልጣናቸውን ማራዘም ብቻ ነው። የእነሱ የበላይነት ዘላቂነት እንዲኖረውና የአገራችንም የጥሬ-ሀብቶች በዓለም-አቀፍ ኩባንያዎች እንዲበዘበዙ ለማድረግ እስከመጨረሻው ድረስ ህዝብን በማወናበድና አቅሙ እንዲዳከም በማድረግ ይገፉበታል። በተለይም በጥሬ-ሀብት ክምችትና በለምለምነቱ የሚታወቀው የወልቃይት ፀገዴ ጉዳይ “በህገ-መንግስቱ መሰረት” መፈታት አለበት የሚለው አነጋገር ይህንን አካባቢ ለወያኔ በመስጠት በተለይም አካባቢን አውዳሚና ጥሬ-ሀብትን ዘራፊ የሆኑት የአሜሪካን ኩባንያዎች መጥተው እንዲሰፍሩ በማድረግ ህልውናችንን እንዲፈታተኑና የተሟላና ተከታታይነት ያለው ዕድገት እንዳይኖር ለማድረግ ነው። የአሜሪካኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የሆነው ብሊንከን ለአቢይ እየደወለ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው የአሜሪካን የስለላ ድርጅትና እነብሊንከን ወልቃይት ፀገዴ መሬት ውስጥ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ማዕድኖች መኖራቸውን በማወቃቸው ነው። ለማንኛውም የወያኔና የአቢይ አህመድን አገዛዝ የፖለቲካ ዘይቤ ስንመረምር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ሁለቱም ጎሳን በጎሳ፣ ሃይማኖትን በሃይማኖት በማጣላትና የከፋፍለህ ግዛው “ፖለቲካ” በማካሄድና ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመስራትና ከእነሱም ትዕዛዝን እየተቀበሉ ተግባራዊ በማድረግ ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳያገኝ ሌት ተቀን የሚሰሩ የነጭ ኦሊጋርኪው መደብ አሽከሮች ናቸው ማለት ይቻላል። ከአንድም ሁለቴም የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ወረራ እየመከተች እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ነፃነቷን ያስከበረች አገርና የራሱ የሆነ ልዩ ዐይነት ባህልና የምግብ አሰራር ልምድ ያለው ህዝብ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መዳከምና ብትንትናቸው መውጣት አለባቸው።  ወያኔ በ27 ዐመት አገዛዙ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ ይህንን አገርን የማውደም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን ተልዕኮ ነው የሚያሟሉት። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም፣ ቤልጂክና ፈረንሳይ፣ እንዲሁም እንግሊዝ በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የሚፈጽሙትን አሻጥር፣ የውክልና ጦርነትና የአገዛዞች ግልበጣ አስመልክቶ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች በአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ላይ ስማቸውን በመጥራት ሲተነትኑና ሲያውግዙ፣ እነህወሃትና አቢይ አህመድ የአሜሪካንና የተቀረው ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች አሽከር በመሆን በህዝባችንና በባህላችን ላይ ጦረነት ከፍተው አገራችንን እያተረማመሱ ነው። 27 ዓመት ያህል የትግራይ ኤሊት የበላይነት፣ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ኤሊት የበላይነት በመስፈን  በጠቅላላው ህዝባችን ላይ ጦርነት በማወጅ ህዝባችንን እርስ በርሱ እያባሉት ይገኛሉ።

ወደ ሁለተኛው ክፍልና በደንብ ወዳልተብራራው ጉዳይ፣ በወያኔና በአሜሪካን መሀከል ስላለው “ፍቅር” ጋ እንምጣ። ይህንንም ሚስጥር ማወቁ ከባድ አይመስለኝም። ከላይ ለማብራራት እንደሞከርኩትና አብዛኛዎቻችንም እንደምናውቀው ወያኔ ፋሺሽታዊና ዘራፊ ቡድን ነው። በሁለት ድርጅቶች ወይም ቡድኖች መሀከል “ፍቅር” ወይም ወዳጅነት የሚኖረው የሁለቱም አመለካከትና ዕምነት ተመሳሳይነት ካለው ብቻ ነው። አንድ ሳይንቲስት ወይም በጣም ጥሩ የፍልስፍና አመለካከት ያለውና በፍትሃዊነትና በሰብአዊነት የሚያምን ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከገዳይና ከዘራፊ ሰው ወይም ቡድን ጋር በፍጹም አይወዳጅም። “ጓደኛህን ንገረኝና የአንተን ማንነት እነግርሃለሁ” የሚባል የእናቶቻችንና የአባቶቻችን አባባል አለ። በወጣነት ዘመናችን እናቶቻችንም ሆነ አባቶቻችን የሚመክሩን ባህርዩ ከተበላሸ ጎረምሳ ጋር በፍጹም እንዳትሄድ እያሉን ነው፡፡ ስለሆነም አሜሪካ ወያኔን አቅፎ ደግፎ እሽሩሩ የሚለው በመሀከላቸው ፍቅር ስላለ ወይም ስለሚወደው ሳይሆን ወያኔ በጣም ጥሩ የሆነ አገርንና ባህል አፍራሽ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖትና ብሄረሰብን ከብሄረሰብ እያጋጨ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚፈልግ የደንቆር ድርጅትና በጣም ጥሩ አሽከር መሆኑን በመገንዘቡ ብቻ ነው። አሜሪካ የበላይነትን ይዞ ከወጣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ፍትሃዊነትንና ዲሞክራሲን ከሚፈልጉና፣ ወደ ውስጥ ደግሞ የተስተካከለ ዕድገትን በማምጣት ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመመስረት የሚፈልጉትን ኃይሎች የደገፈና የሚያግዝ ሳይሆን፣ እስከዛሬ ድረስም ፀረ-ዲሞክራሲና ፋሺሽታዊ ኃይሎችን ነው የሚያግዘውና ወደ ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያደርገው። ይህንን ባህርዩን ለመረዳት ደግሞ የአሜሪካንን የካፒታሊዝምን ዕድገትንና ወደ ኢምፔሪያሊዝምነት መለወጥ ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል።

የአሜሪካን ካፒታሊዝምም ሆነ የተቀረው የምዕራብ አውሮፓው የካፒታሊስት ስርዓት ያደገው  የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚነግረን ወደ ውስጥ በስምምነትና በውድድር አማካይነት ሳይሆን፣ ገበሬውን ከቀየው በማፈናቀልና ወደ ወዝአደርነት በመለወጥና በከፍተኛ ደረጃ በመበዝበዝ ነው። ከተማዎችንና መንገዶችን መስራት የተቻለው የሰውን ኃይል በማንቀሳቀስና በመብዝበዝ ብቻ ነው። የኢንዱስትሪ አብዮት ከእንግሊዝ አልፎ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮችን ሲያዳርስ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች በከፍተኛ ደረጃ እየተበዘበዙ ነው ለካፒታሊዝም ዕድገትና የሀብት ክምችት(Capital Accumulation) አመቺ ሁኔታን የፈጠሩለት። በካፒታሊዝም አፍላ ወቅትና ከዚያም በኋላ የኢንዱስትሪ አብዮት ከተደረገ በኋላ የወዛደሩ አኗኗር በጣም አሰቃቂና ለበሽታም የተጋለጠ እንደሆነ ብዙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። አብዛኛውም ህዝብ በአንድ ክፍል ውስጥ እየተጨናነቀ እንደሚኖርና ይህን ዕድል ያላገኘው ደግሞ በየሜዳው ላይ የሚተኛና የሚኖር ነበር።

የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊዝም አፀናነስና አስተዳደግ ትተን በአሜሪካኑ ካፒታሊዝም ላይ ብቻ ስናተኩር የአሜሪካ ካፒታሊዝም በነጭ ወራሪዎችና ዘራፊዎች የተመሰረተና ወደ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ነጮች ከአውሮፓ፣ በተለይም ከእንግሊዝና ከአየርላንድ ሲሄዱና ሲሰፍሩ ወደ አስራሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ እንዲያኖችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል። ሌሎች ጎሳዎችንም እንዳለ ደብዛቸው እንዲጠፉ አድርገዋል። እዚያ ኗሪ የሆኑት ነጮችና የኋላ ኋላ ከእንግሊዝ ቅኝ-ግዛት የተላቀቁት ለካፒታሊዝም የሀብት ክምችት መሰረት የሆናቸው በባሪያ ንግድ ላይ በመሰማራትና፣ ከአፍሪካ የሄደውን ጥቁር ህዝብ በጥጥና በሸንኮራአገዳ ተከላ ላይ በማሰማራት ነው። ጥቁሮችም ከውሻ በታች የሚታዩና በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ክትትል የሚደረግባቸውና፣ አብዛኛዎቹም በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገደሉ ነበሩ። በጠቅላላው የአሜሪካንን ካፒታሊዝምም ሆነ የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊዝም ዕድገት በምንመለከትበት ጊዜ የባርያ ንግድ፣ የቅኝ-ግዛት፣ ዛሬ ደግሞ የእጅ አዙር ቅኝ-ግዛት ለዕድገታቸውና ዓለም-አቀፋዊ ባህርይ እንዲወስዱ አስችሏቸዋል። የኋላ ኋላ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተለይም ደግሞ ፊዚክስ የመሳሰሉትና የማሺን ኢንዱስትሪ ሲዳብሩ ካፒታሊዝም በመጠኑም ቢሆን ከጥንታዊ የሀብት መበዝበዢያና ማከማቺያ ዘዴ(Primitive Capitalist Accumulation) በመላቀቅ በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት የማምረት ኃይሉ ሊዳብር ቻለ። ባንኮችና ቀስ በቀስም ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ፣ በሁለቱ መሀከል የተፈጠረው መተሳሰር ለካፒታሊዝም ዕድገት ዕምርታን ሊሰጠው ቻለ። ስለሆነም ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድ ልዩ ልዩ የብዝበዛ ዘዴዎችን በመፍጠርና ሀብት ወደ ካፒታሊስት አገሮች እንዲሸጋገር በማድረግ በዚያው መጠንም የሶስተኛው ዓለም  ተብለው የሚጠሩ አገሮች ወደ ተራ ተበዝባዥነት በመቀየር በቴክኖሎጂና በሳይንስ የማደግ ዕድል ተነፈጋቸው። ከእነዚህ የብዝብዛ መሳሪያዎች ውስጥ በርካሽ አበል ሰራተኛውን እንዲያመርት ማድረግና ትርፍን ወደ ካፒታሊስት አገሮች ማሸሽ፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮችን የጥሬ-ሀብት አምራች አገሮች ብቻ አድርጎ ማስቀረት፣ ያልተስተካከለ የንግድ ልውውጥ በማካሄድ የንግድ ሚዛኑ እንዲዛባ ማድረግ፣ በዕዳ መተብተብና ሳይንሳዊ ይዘት የሌለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማድረግ የተስተካከለና ሚዛናዊ የሆነ ዕድገት እንዳይፈጠር በማድረግ ወደ ውስጥ ዝብርቅርቅ ሁኔታዎች በመፍጠር ሀብት በስርዓት ምርታማ ወደ ሆኑ ነገሮች ላይ እንዳይሰማራ ማድረግ…ወዘተ.፣ እነዚህ ሁሉ አንድን አገር ማቆርቆዣ መሳሪያዎች ናቸው። በዚህ መልክ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተዘረጋው የተዘበራረቀ ኢኮኖሚ ፈጣሪ የሆነ የከበርቴ ኃይል እንዳይፈልቅ አገደ። የእነዚህ አገሮች የኢኮኖሚ መሰረት የማሽን ኢንዱስትሪ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሆናቸው ቀርቶ የጥሬ-ሀብት ማምረት፣ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎች ላይ በመሰማራት ለሰፊው ህዝብ በቂ የስራ መስኮች ለመክፈት ያልቻሉበት ሁኔታ ለመፈጠር ቻለ።  አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በተደጋጋሚ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ኢ-ሳይንሳዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለሰፊው ህዝብ በቂ የስራ ዕድል መክፈት ባለመቻላቸውና፣ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት የማይችሉ በመሆናቸው የስራ ዕድል ለማግኘት ያልቻለው ታዳጊ ወጣትና ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ወደ አልባሌ ስራዎች ላይ በመሰማራት ህይወታቸው እንዲበላሽ ተደረገ። በዚህ መልክ የተዋቀረው ደካማ የኢኮኖሚ መሰረት አዳዲስና የነቁ ኃይሎች ብቅ እንዳይሉ አገደ። አገዛዞችን ሊጋፈጥ የሚችልና አማራጭ ፖሊሲ ሊያቀርብ የሚችል ኃይል ብቅ እንዳይል አደረገ። በሌላ ወገን ደግሞ የተዘበራረቀውና በጣም ደካማ የሆነው የኢኮኖሚ መሰረት በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ፋሺሽታዊ መሰልና አምባገነን አገዛዞች ተጠናክረው እንዲወጡ አመቺ ሁኔታን ፈጠረላቸው። ወደ ውስጥ የተዘረጋው ጭቆናዊ አገዛዝ ከወጭው ኃይል ጋር በመመሳጠርና የአፍሪካን ሀብት በመበዝበዝ ሰፊው ህዝብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነፃነትን እንዳይጎናፀፍ አደረገው። በዚህም አማካይነት የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ ራሳቸውን ያልቻሉ  ዘራፊ መንግስታት(Predatory States) ሊመሰረቱ ቻሉ።  በራሳቸው የፖለቲካ ስሌትና ፍልስፍና የማይንቀሳቀሱ የሶስተኛው ዓለም አገር አገዛዞች ደግሞ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ በማሰብ አገሮቻቸውን ወደ ተራ ተበዝባዥነትና በካፒታሊስት አገሮች የሚመረቱ ምርቶች ማራገፊያ ለመሆን በቁ። ይህ የሚያረጋግጠው ካፒታሊዝም ነፃ በሆነና ሌሎች አገሮችን ሳይበዘብዝ እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንዳልቻለ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የካፒታሊዝም ዕድገትና የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም የአፍሪካ ኋላ-ቀርነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብአዴን ‹‹ሰለሞናዊ›› ስርወ መንግስት!? - (ሊያነቡት የሚገባ የአደባባይ ምስጢር)

ይህ ዐይነቱ´ን የብዝበዛ ስርዓት ለማጠናከርና ድህነትን በሶስተኛው ዓለም አገሮች ለማስፋፋት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ችሏል። አሜሪካ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ ብቸኛው ኃያል መንግስት በመሆን በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ዘልቆ ለመግባት የሚያስችል ዕድል አግኝቷል ማለት ይቻላል። በሚሊታሪና በኢኮኖሚ ጠንክሮ የወጣው ኃያል አገዛዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖለቲካዊ ተፅዕኖም ማሳደር ቻለ። በዚያው መጠንም ከእሱ ተፅዕኖ ውጭ የሆኑና የራሳቸውን ዕድገት ለመከተል የሚፈልጉ አገሮችን ኮሙኒስቶች ናችሁ በማለት ጦርነት ሊከፍትባቸው ቻለ። ማንኛውም አገር ካለ አሜሪካና ከተቀረው የካፒታሊስት አገር ፈቃድ ውጭ የራሱ የሆነ አማራጭ የኢኮኖሚ የዕድገት ፈለግ መከተል አይችልም ማለት ነው። በመጀመሪያው ወቅት በ1950ዎች መጀመሪያ ላይ በኮሪያ ላይ በተደረገው ጦርነት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ኮሪያኖች በአሜሪካን አውሮፕላን በመደብደብ ህይወታቸው እንዲያጣ ተድርጓል። ኮሪያም ለሁለት ለመከፈል የቻለችው በቀጥታ በአሜሪካን ጣልቃ ገብነት ነው። እስከዛሬም ድረስ ያለው ፍጥጫ አሜሪካን በሁለቱ ኮሪያኖች መሀከል መቀራረብ እንደሌለበት አጥብቆ ስለሚሰራና እንደ አንድ አገር ሆነው እንዳይገነቡ በማሰቡ ብቻ ነው። እንዲሁም በቬትናም ላይ የተካሄደው ጦርነትና ለስብል የሚሆኑ ቦታዎች መርዝ እንዲረጭባቸው የተደረገው ከአሜሪካን ልቅ ያጣ ባህለ-ቢስና አረመኒያዊ አካሄድ ነው።

ቀደም ብሎም ሆነ ከዚያ በኋላ በአሜሪካን የስለላ ድርጅት አቀነባባሪነት  በአያሌ አገሮች ውስጥ ብዙ የመንግስት ግልበጣዎች ተካሂደዋል። በመጀመሪያ ደረጃ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢራን ውስጥ በተካሄደው ምርጫ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው ሞሳዴክ የሚባለው መሪ ልዩ ዐይነት የዕድገት ፈለግን ለመከተል በመፈለጉ እንዲገለበጥና በሻህ እንዲተካ ለመደረግ በቅቷል። በፓትሪስ ሉቡምባ፣ በኩዋሜ ኑክሩማና በሚልቴን ኦቦቴ ላይ የተካሄዱት የመንግስት ግልበጣዎች በሙሉ የአሜሪካን እጅ አለበት። በ1973 ዓ.ም የቺሌው ፕሬዚደንት ሳልቫዶር አሌንዴ ራሳቸውን እንዲገድሉ የተገደዱት በሲአይኤ በተቀነባበረ ሴራ እነ ፒኖቼት ከሚገድሉኝ ይልቅ ራሴን ባጠፋ ይሻላል ብለው በማሰባቸው ነው። በአርጀንቲናና በተቀሩት የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገሮች ከ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ብቅ ያሉት የወታደር አምባገነን አገዛዞች በሙሉ ፓናማ ውስጥ በሲአይኤና በተቀሩት የፔንታጎን ጄኔራሎች የሰለጠኑ ናቸው። እነዚህ አገዛዞች ኮሙኒዝምን እንዋጋላን በማለት በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ምሁራንና የሰራተኛውንም መሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል። ለከበርቴው ዲሞክራሲ ይታገሉ የነበሩት በሙሉ እንደኮሙኒስቶች እየተቆጠሩ እንዳለ ተገድለዋል። የተቀሩት ደግሞ ወደ ምዕራብ አውሮፓ እንዲሰደዱ ተገደዋል። በቅርቡ ጊዚያት ደግሞ በኢራክ፣ በሊቢያ ውስጥ የተደረጉት አገርን የማከረባበትና የማፈራረስ አካሄዶች በሙሉ የሚያረጋግጡት እነዚህ አገሮች የራሳቸውን መንገድ ተከትለው ለመሄድ በመፈለጋቸው በመሆኑ ነው፤ የታሪክና የባህላቸውም ሁኔታ ከዚህ ውጭ ለማሰብ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ይሁንና ሁለቱም አገዛዞች ከሞላ ጎደል ህዝባቸውን በስነ-ስርዓት ያስተዳድሩ ነበር። ወደ አፍጋኒስታን ስንመጣ ደግም በ1950ዎች፣ 60ዎቹና እስከሰባኛው ዓመተ-ምህረት መጀመሪያ ድረስ አፍጋኒስታን ዘመናዊ የሆነችና የእስላም እንቅስቃሴም የሚታይባት አገር አልነበረችም። ሶሻሊስታዊ አገዛዝ ከተመሰረተ በኋላ የሶቭየት ህብረት ተፅዕኖ በአፍጋኒስታን ውስጥ እያየለ ሲመጣ በካርተር የሚመራው የአሜሪካ አገዛዝ ለታሊባኖች 500 000 000 $ በመመደብ በመሳሪያና በሃሳብ በመደገፍ ጦርነት እንዲያካሂዱ አመቺ ሁኔታን ፈጠረላቸው። ቀሰ በቀስም አክራሪ የእስላም እንቅስቃሴ እያየለ መጣ። ከዚያ በኋላ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በአሜሪካን ላይ የተፈጸመውን የሽበርተኝነት ድርጊት ሰበብ በማድረግ ሸበርተኝነትን ለመዋጋት በሚል በአፍጋኒስታን ህዝብ ላይ ጦርነት ያውጃል። ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ አፍጋኒስቶችም እንደተገደሉ ሲታወቅ፣ ታሊባኖች እንደገና ተመልሰው በመምጣት ስልጣንን ለመያዝ በቅተዋል። በባይደን የሚመራው የአሜሪካን አገዛዝ ብዙ ቢሊዮን የሚያወጣ ዘመናዊ የጦር መሳሪያና እስከነ ሄሊኮፕተር ጭምር ለታሊባኖች ጥሎላቸው እንደሄደ ይታወቃል። ለ20 ዓመታት ያህል አሜሪካንና ግብረ-አበሮቹ አፍጋኒስታን ውስጥ ያካሄዱት ጦርነት የአፍጋኒስታንን ህዝብ ከእስላም አክራሪዎች አገዛዝ በፍጹም ነፃ አላወጣውም፤ ዲሞክራሲንና የነፃ ገበያንም አላጎናጸፈውም። በአንፃሩ አክራሪ እስላሞችና ድህነት የአፍጋኒስታን ህዝብ መለያዎች ለመሆን በቅተዋል። የአሜሪካና የተቀረው የካፒታሊስት ዓለም በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ጣልቃ ሲገባና የመንግስት ለውጥ(Regime Change) መደረግ አለብት ሲል በመሰረቱ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስረዓትን ለመመስረትና፣ ለተስተካከለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል ሳይሆን  የየራሳቸውን ተቀጥያ አገዛዝ ስልጣን ላይ በማውጣት የጥሬ-ሀብትን ለመዝረፍ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲንና የነፃ ገበያን ዕድገት ስንመረምር  ከላይ ወደ ታች የሚጣሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያድጉ ሳይሆኑ ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ የሚያድጉ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የመንግስት መዋቅር የጥገና ለውጥ፣ የተቋም ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለተሟላ ህብረተሰብ ግንባታ የሚያገለግሉ ከቴክኖሎጂና ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር የሚያያዙ ኮሌጆችና የሙያ ማስለጠኛ ተቋማት እንደቅድመ-ሁኔታ ቀስ በቀስና በዕውቅ መስፋፋት አለባቸው። በተወሰነ ቴክኖክራሲያዊ መሳሪያዎች አማካይነት ነፃ የገበያ ኢኮኖሚን በፍጹም ተግባራዊ ለማድረግ አይቻልም። የአውሮፓን የካፒታሊዝምን ዕድገት ስንመረምር እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ  ላይ ለመድረስ አራትመቶ ዓመታት ያህል ፈጅቶበታል። ዛሬ የሚታየው ዕድገትና ሁላችንም ተጣቃሚ ለመሆን የበቃነው ቴክኖሎጂዎች በሙሉ የብዙ ሚሊዮን ህዝብ ደም ፈሶበታል። ከመቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ሰራተኞች፣ ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች የተንደላቀቀ ኑሮ ሳይኖሩ የፈጠሯቸው ቴክኖሎጂዎች በሙሉ ከዚያ በኋላ ለተፈጠረው ትውልድ መጠቀሚያ ለመህን በቅተዋል።  ይሁንና በሳይንስና በቴክኖሎጂ መበልጸግ የአሜሪካንና የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት ኤሊት ሰብአዊና ርህሩህ አላደረገውም። በአንፃሩ በተጎናፀፈው ሳይንስና ቴክኖሎጂ አማካይነት ውስብስብ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን በመስራት የዓለምን ህዝብ የሚያስፈራራና ዕረፍት የማይሰጥ ለመሆን በቅቷል፤ ጭንቅላቱ የሰለጠነና አርቆ አሳቢ ከመሆን ይልቅ በጣም አረመኔ ሆኗል ማለት ይቻላል።  The Barbarian Temperament የሚለውን በMestroviċ የተጻፈውን በጣም ግሩም የሶስይሎጂ መጽሀፍ አንቡ።

አሜሪካና ግብረ.አበሮቹ የተለያዩ ሰበቦችን እየፈጠሩ በማንአለኝበት በየአገሩ እየገቡ የሚያካሂዷቸው ጦርነቶችና የአገዛዞች መወገድ፣ ከኢራቅ ጀምሮ እስከሶሪያና ሊቢያ፣ እንዲሁም አፍጋኒስታን ድረስ ለብዙ መቶ ሺህ ህዝቦች መሞት ምክንያት ለመሆን በቅቷል። ከጦርነት ለማምለጥ የቻለው አንዳንዱ በመንገድ ላይ ሲጓዝ በበሽታም ሆነ በምግብ እጦት ሲሞት፣ የተቀረው ደግሞ እንደምንም ብሎ የሚፈልጋቸው ቦታዎች ለመድረስ የቻለ አለ። ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ ጦረነት ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ አገሮች እየፈለሰ ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚመጣው የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። አሜሪካና የተቀረው የካፒታሊስት ዓለም ብዙም ሳያስብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያካሂደው ጦርነት በህዝብ ፍልሰት የተነሳ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የዲሞግራፊና የጎሳ ወይም የዘር ለውጦች ይታያሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ከነጩና እዚያው ተውልዶ ካደገው ህዝብ ቁጥር ይበልጥ ከውጭ እየተፈናቀለ የሚመጣው የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ በመምጣት ላይ ይገኛል። በዚያው መጠንም ይህንን ህዝብ ለማስተናገድ የሚወጣው ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ፣ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጣውን ስደተኛ ከህዝቡ ጋር ለማዋሃድ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል። አንዳንዶችም ካልቸራል ሾክ እየደረሰባቸው ወደ አልባሌ ቦታ በመውደቅ ለእስር የሚዳረጉ አሉ። ራሳቸውንም የሚስቱ ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣት ላይ ነው። ከውጭ የሚመጣው የህዝብ ቁጥር  በኗሪው ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ባለመቻሉ ለቀኝ አክራሪዎችም ደግሞ አመቺ ሁኔታን እየፈጠራለቸው ነው። ከተለያዩ አገሮች የሚመጣውን ሰውን በሚጠላው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙና በፓርሊያሜንት ውስጥም በቂ መቀመጫ ለማግኘት የቻሉበት ሁኔታ ይታያል። ከውጭ የሚመጣው ህዝብ በተለይም  ከሰለሳና አርባ ዓመታት በላይ ሰርቶ ለማረፍ በሚፈልገው ሽማግሌ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጫና እየሆነበት ነው። ከአዲሱና በፍጥነት ከሚለዋወጠው ሁኔታ ጋር ራሱን ለመለማመድ ባለመቻሉ በመንገድ ላይ ሲሄዱ እንኳ  እየተሸማቀቀ ነው ማለት ይቻላል።

ባጭሩ ከ1945 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረውን የኃይል አሰላለፍ በምንመለከትበት ጊዜ አሜሪካንም ሆነ የተቀሩት የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ምንም ጊዜ ቢሆን ዲምክራሲንና ዕድገትን ከሚፈልጉ አገሮችና ኃይሎች ጋር የቆሙበት ጊዜ የለም። በተለይም ግሎባላይዜሽን የሚባለው ፈሊጥ ዓለምን በፍጥነት ካዳረሰበት ከ1980 ዓ.ም ጀምሮና፣ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮችም የዋሽንግተን ስምምነት የሚባለውን የመዋቅር ማስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Structural Adjustment Programms) ተገደው ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ጭምር ልዩ ዐይነት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የፖለቲካ ቀውስ ሊፈጠር ችሏል። በመጀመሪያ ደረጃ የዋሽንግተን ስምምነት በመባል የሚታወቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም የኢኮሚ ፖሊሲ አይደለም። አንድን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ፖሊሲ የሚያሰኘው ሳይንሳዊ ይዘት ሲኖረው፣ ሁለ-ገብ ሲሆንና የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ደረጃ በደረጃ እያሟላ ወደ ተሟላ የአገር ግንባታ ለማሸጋገር ሲችል ብቻ ነው። ልዩ ዐይነት ባህልና የኢኮኖሚ መሰረት በመጣል የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ኃይሎች የማሺን ኢንዱስትሪ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሲሆኑ ብቻ ነው። በአንፃሩ ግን የዋሽንግተኑ ስምምነት ወይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በቀላል የኢኮኖሚ መሳሪያዎች፣ የአገርን ከረንሲ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር መቀነስ(Devaluation)፣ ኢኮኖሚውን “በገበያ ህግ” መሰረት እንዲተዳደር ማድረግ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ሀብቶችን በመሸጥ ወደ ግል እንዲዘዋወሩ ማድረግ፣ በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ በየአገሮች ውስጥ ዘራፊ የሆኑ ኃይሎችን ሲፈጥር በዚያው መጠንም ያልተስተካከለ ዕድገትና ብልሹ የሆነ ባህል እንዲፈጠር ለማድረግ የበቃ ነው። ከዚህ አልፎ በመሄድ ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢ መቆሸሽም ሊከሰት ችሏል። በየከተማዎች ውስጥም ደግሞ ቁጥራቸው የማይታወቅ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች(Slums) እንደ አሸን ሊፈልቁ ችለዋል። በዚያው መጠንም አመጸኛ የሆነ የህብረተሰብ ክፍልና አገዛዝ በመፈጠር ምስኪኑን ህዝብ መግቢያና መውጫ ለማሳጣት የቻሉበት ሁኔታ ይታያል። በተለይም የአገራችን ሁኔታ የሚያረጋግጠው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የቱን ያህል አገርንና ባህልን አፍራሽ በመሆን ዘራፊ ኃይሎችን እንደሚፈጥር ነው። ይህ ዐይነቱ የተዘባበረቀ ሁኔታና ዘራፊ ኃይል መስፋፋት ደግሞ በቀላሉ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ያመቸዋል። ያሉትን የጎሳና የሃይማኖት ልዩነቶችን በመጠቀምና፣ እነዚህን ኃይሎች ተገን በማድረግ በየአገሮች ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋል። ዛሬ በተለያዩ አገሮች የሚታዩት ያለመረጋጋት ሁኔታዎችና በዩክሬይንም ያለው ሁኔታ በቀጥታ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ልቅ ያጣና ታሪከ-ቢስ  የውጭ ፖለቲካ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለጸረ ሙስና እና ቤቲን እንከሳለን በማለት ለዛቱ አቃቢያነ ህጎች የቀረበች ቆንጆ ፈተና => ሰምሃል መለስ ዜናዊ

አጠቃላዩን የአሜሪካ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢንተለጀንስ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ኤሊቱን አስተሳሰብ ስንመለከት አስተሳሰባቸው በጣም ወደ ኋላ የቀረ ነው። እያንዳንዱ አገር የራሱ ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድና ልዩ ልዩ እሴቶችና የአኗኗር ስልቶች እንዳለውና ይህም መከበር እንዳለበት በፍጹም አይረዱም። ቢረዱም እንኳ እነዚህ ልዩ ልዩ ባህሎችና የአኗኗር ስልቶች የአሜሪካንን የበላይነት የሚቀናቀኑ ስለሚመስላቸው እንዳለ ተወግደው በአሜሪካን አስተሳሰብና የአበላል ዘዴ መተካት አለባቸው።  በዚህም መልክ በቀላሉ የዓለምን ህዝብ መቆጣጠርና መሞከሪያ ማድረግ ይቻላል። ይህንን አስመልክቶ በአሜሪካን ኤሊት መሪነት በጠቅላላው የካፒታሊስቱ ዓለም፣ ዓለምን ለመቆጣጠር የነደፈውና በአብዛኛው ጎኑም ተግባራዊ ያደረገው የአሰራር ደንቦችና ህጎች አሉ። ይህም ስርዓት Rule Based System በመባል ይታወቃል። በዚህ ህግ መሰረት ማንኛውም አገር የአሜሪካንንና የተቀረውን የካፒታሊስት ዓለም የባላይነት መቀበል አለበት። አልቀበልም የሚል ወይም የራሱን ባህልና ወግ በማክበር አማራጭ የዕድገት ፈለግ ለመከተል የሚፈልገውን ደግሞ እንደ ዋና ጠላት በመቁጠር አንዳች ዐይነት ሰበብ በመፈለግ ከስልጣን እንዲወገድ ይደረጋል። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ባህልና ልምድ፣ እንዲሁም የአኗኗር ስልት በአጭር ጊዜ ውስጥ በመናጋት፣ በተለይም ተራው ህዝብ የሚመራበት ኖርሞችና አቅጣጫ እንዳይኖረው ይደረጋል። ከዘጠኝ ወራት ጀምሮ ዩክሬይንን አሳቦ በአሜሪካን መሪነት ሰላሳ የሚሆኑ አገሮች የሚሳተፉበት ጦርነት ዋናው ዓላማም ራሺያን እንዳለ አውድሞ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ቻይና ለመዞር ነው። በአሜሪካን ዶክትሪንም መሰረት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ኃያላን መንግስታት መኖር የለባቸውም። ስለሆነም ከሰባ ዓመታት በላይ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና የአሜሪካን የአኗኗር ስልት(The American Way of Life) በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮች ኤሊት ጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ ሽማግሌዎችና ደሃ ህዝቦች እየተሰቃዩ እንዲኒኖሩ ለመደረግ በቅተዋል።  በሌላ ወገን ግን ይህ ዐይነት የአኗኗር ስልት ዘመናዊ ቢመስልም ከጭንቅላት ተሃድሶ ጋር ያልተያያዘ በመሆኑ በየአገሮቹ ውስጥ የተዘበራረቁ ነገሮችና አመጽም ተስፋፍቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካንና ግብረአበሮቹ በተለይም ከ1989 ዓ.ም በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነታቸውን የተቀዳጁ ስለመሰላቸውና ይህም እንዳይነካ በማለት ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ በማድረግ ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችን በጦርነት እያመሱ ነው። የአሜሪካኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስተር ብሊንከንና በውጭ ጉዳይ ሚንስተር ውስጥ በአማካሪነት የምትሰራው ሱዛን ራይዝ የየራሳቸውን የጦር መሳሪያ አማካሪ ኩባንያ በመክፈትና የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪን በማማከር ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ በቅተዋል። በብዙ አገሮች ውስጥ ጦርነት ሲካሄድ የህዝብ ቁጥር መቀነሱ ብቻ ሳይሆን የትርፍ ትርፍም እናካብታለን ብለው ያስባሉ። አሜሪካ ጦርነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ በአጠቃላይ ሲታይ ወደ ዘጠኝመቶ የሚጠጉ የጦር ሰፈሮች ሲኖሩት፣ ለመከላከያ የሚመደበው የዓመት ባጀት ደግሞ  900 ቢሊዮን ዶላር ነው። ከሌሎች አገሮች በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ በኒጄርና በጂቡቲ እንደዚሁ ትላልቅ የጦር ሰፈሮች አሉት። ዋናው ዓላማውም የቻይናን ግፊት ለመቋቋምና፣ በተለይም በኒጄርና በማሊ ውስጥ ተትረፍርፎ የሚገኘውን የጥሬ-ሀብት ለመቀራመት ነው። ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ሰበብ እራሱ ሽብርተኞችን  እየፈለፈለ፣እያስታጠቀና እያሰማራ እንደናይጄሪያና ማሊ በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች፣ እንደፈረንሳይ ከመሳሰሉት ጋር በማበር ሽብርተኝነትን በአፍሪካ ምድር ውስጥ እያስፋፋ ነው። ለምሳሌ የፈረንሳይና የጀርመን ወታደሮች ማሊ ውስጥ ጦሮቻቸውን ካሰፈሩና፣ በተለይም የፈረንሳይ ጦር ውጊያ ከጀመረ ጀምሮ በማሊ ውስጥ የእስልምና አክራሪ ኃይሎች ቁጥር በብዙ እጅ እጥፍ ጨምሯል።   ባጭሩ የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ ኤሊቶች በከፍተኛ ደረጃ ለዓለም ህዝብ ስጋት እየሆኑና የሶስተኛው ዓለም ኤሊቶችን እያባለጉና ጦረኞች እያደረጓቸው ነው። አሜሪካንም ሆነ አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች የተለያየ መጠሪያ ስም ያላቸው ፓርቲዎች አለን ቢሉም ሁሉም ጦረኞችና ጠቅላላውን የዓለም ህዝብ ለብዙ ዓመታት ገዝተውና በዝብዘው ለመቆየት የሚፈልጉ ናቸው። ስለሆነም በአሜሪካን አገር በዲሞክራቶችና በሪፓብሊካን ፓርቲ መሀከል፣ በጀርመን በሶሻል ዲሞክራቲክና በአረንጓዴው ፓርቲ፣ እንዲሁም የሊበራል ፓርቲ ነን በሚሉት መሀከል የውጭ ፖሊሲን አስመልክቶ ስምምነት አለ። በተለያዩ ጊዜያት እየተፈራረቁ በምርጫ ስልጣንን የሚቀዳጁ ፓርቲዎች በሙሉ የሚሰሩት ለትላልቅ የካፒታሊስት ኩባንያዎችና ለሚሊታሪ-የኢንዱስትሪ ውስብስብ(Military-Industrial Complex) ነው። ሁሉም የወራሪነት መንፈስ አለባቸው ማለት ነው። በተለይም የአሜሪካኑ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ጦረኛ እንደሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነት የሚያስፋፋ መሆኑን ከፕሬዚደንት ክሊንተን አንስቶ እስከ ባራክ ኦባማና፣ አሁን  ደግሞ በጆን ባይደን የሚመራው አገዛዝ እያረጋገጡ ነው። ምንም ዐይነት ዲሞክራሲያዊ ባህርይ እንደሌላቸውና በአመጽ ብቻ እንደሚያምኑ ለዓለም ህዝብ እያስመሰከሩ ነው።  የየራሳቸውን ታሪክ እንኳ በደንብ ጠንቅቀው የማያውቁና የተለያዩ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም የስነ-ጽሁፍ ተመራማሪዎች ያበረከቱትን ለሰው ልጅ ሁሉ ጠቃሚ የሆኑ ምርምሮችን ቁም ነገር ውስጥ በመክተት መመሪያቸው የሚያደርጉ አይደሉም። ጠቅላላውን የምዕራቡን ኖርም ወደ ነፃ ገበያ፣ ወደ ሊበራሊዝምና ወደ ብዙሃዊነትን ብቻ በመቀነስ አገሮችን እያመሱ ነው። በተጨማሪም በግብረሰዶማዊነት ስም አሳበው በአንዳንድ መንግስታት ላይ ጫና በማድረግ ግብረሰዶማዊነት በዓለምአቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው በከፍተኛ ደረጃ ይሰራሉ። በሌላ ወገን ግን በእኔ ዕምነት እያንዳንዱ ግለሰብ ፍላጎቱ ካለውና ወደዚያ የሚያደላ ከሆነ መብቱ ነው። ችግሩ ግን ይህንን የመሳሰለው ነገር የአንድ ህብረተሰብ ኖርም መሆን የለበትም። ይህ ከሆነ ለአንድ አገር ጠቃሚ የሆነውና አንድ አገርም እያረጀ የሚሄደውን የህብረተሰብ ክፍል በተከታታይ ለመተካት ተፈጥሮአዊ የሆነው ቤተሰብን የመመስረት ጉዳይና ተተኪ ትውልድን የማፍራቱ ጉዳይ እየተዳከመ ይሄዳል ማለት ነው።  አዳዲስ ትውልድ ማፍራትም ከቤተሰብ አንፃር ብቻ መታየት ያለበት ጉዳይ ሳይሆን፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትም በጣም አስፈላጊ ነው። ተፈጥሮአዊ የሆነ የህብረተሰብ ኖርም ከመጣሱ የተነሳ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ከሌሎች ነገሮች ጋር በመደመር የማፍራትና (Fertility Rate) የመውለድ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ በመምጣት ላይ ይገኛል። ለማንኛውም የአንድ አገር ኖርሞች ወደ ሶስትና አራት ነገሮች መቀነስ የለባቸውም። ይህ ከሆነ ደግሞ ዕውነተኛ ነፃነት ምን እንደሆነና፣ መደረግና መደረግ በሌለባቸው ነገሮች ውስጥ መምታት ስለሚፈጠር በነፃነት ስም ሁሉም እየተነሳ የፈለገውን ሊያደርግ ይችላል። ስለሆነም የጀርመን ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች እንደሚያስተምሩን ግለሰብአዊ ነፃነት ከህብረተሰብአዊ ኃላፊነት ጋር አንድ ላይ መሄድ አለባቸው። ግለሰብአዊ  ነፃነት በአርቆ-አሳቢነት መነጽር በመታየት አንድ ማህበረሰብ በስምምነት ሊኖር የሚችልበት የአሰራር ስልት መነደፍ አለበት። ከዚህም ባሻገር የእየአንዳንዱ አገር  ባህልና የአኗኗር ስልት፣ እንዲሁም ሃይማኖትና ሌሎች ኖርሞች በመከበር ዘመናዊ ከሚባለው ስልጣኔ ጋር ጎን ለጎን ሊሄዱ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። አንዱ አገር በሌላው አገር ላይ ጣልቃ በመግባት የየአገሩን ባህልና የአኗኗር ስልት መጣስ የለበትም፤ በአገሮችም መሀከል የሚደረገው ግኑኝነት በማንአለኝበት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ በመከባበር ላይ መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው።

ወደ አገራችን ስንመጣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአብዮቱ ወቅት ከፀረ-ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የወጋን ወራሪ ኃይል ነው። ወያኔና ሻቢያም ስልጣንን ሊቀዳጁ የቻሉት በአሜሪካንና በተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች ዕርዳታ ነው። ወያኔም ስልጣንን ከተቀዳጀ በኋላ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲና የኤትኒክ ፌዴራሊዝም በአሜሪካና በእንግሊዝ የተቀነባበረ ነው። በዚህ ዐይነቱም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ወያኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ፡ራሱን ማደለብ ሲችል፣ በዚያውም መጠንም ከፍተኛ የሆነ የባህል ውድመት ሊያደርስ የቻለ ኃይል ነው። እንደ ግብረሰዶማዊነት የመሳሰሉት አፀያፊ ነገሮች የተስፋፉት በወያኔ ዘመን ነው። አሜሪካና ግብረ-አበሮችም እንደዚህ ዐይነቱን ሁኔታ በጥብቅ ይፈልጉታል። ራሱን የሸጠ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ኤሊት ካለ ብቻ ነው አንድን አገር እንደፈለጋቸው የሚበውዙትና ወደጦርነት እንዲያመራ የሚያደርጉት። ይህም የሚያሳየው ሊበራልና ዲሞክራት ነኝ የሚለው የነጩ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ ኤሊት በምንም ዐይነት ዲሞክራትና ሊበራል እንዳልሆነ ነው። የሚፈልገው አሸከሮችንና ህዝቦቻቸውን የሚያደኸዩ አገዛዞችን ነው።

ከዚህ ስንነሳ በወያኔና በአሜሪካን መሀከል ያለው ግኑኝነት የሎሌና የጌታ ግኑኘነት ነው። አሜሪካን ወያኔን የሚፈልገው ለዘለዓለማዊ ጦርነትና ለብዝበዛ ብቻ ነው። ለሌላ ጉዳይ አይፈልገውም። ስለሆነም ድርድር ከተካሄደና አንዳች ዐይነት ስምመነት ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ መቋጫ ሊያገኝ የማይችለው በአንድ በኩል በአሜሪካን ወራሪ ባህርይና አገሮችን ማከረባበት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በእኛ ኤሊቶች ድክመትና ለስልጣን መስገብገብ ነው። ምናልባት ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ህውሃትን የስልጣን ተካፋይ በማድረግ በኦሮሞ ኤሌቶች የሚመራው የብልጽግና “ፓርቲ” ከውሃት ጋር በመሆን ፋሺሽታዊ አገዛዝ በማቋቋም ብሄርተኛ በሚባሉት ወገኖች፣ በተለይም በአማራው ብሄረሰብ  ላይ አጠቃላይ ጦርነት ያውጃል። አሜሪካንም የሚፈልገው በተቻለ መጠን ብሄረተኛ ነን የሚሉ ኃይሎችን ማዳከምና ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው። ከዚህ ስንነሳ አገር ወዳድና ምሁራዊ ኃይሎች የስልጣን  ስግብግብነትን አሽቀንጥረው በመጣል ቆራጥና አርቆ-አሳቢነት የተሞላበት ፀረ-ኢምፔሪያሊዝም ትግል ማካሄድ አለባቸው። በተለይም የስልጣን ስግብግብነት በተስፋፋበትና ጥልቀት ያለውና የበሰለ ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር ውስጥ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በዚህም በዚያም በማለት በፍጹም እረፍት ስለማይሰጠን ይህንን በመረዳት ወደ ውስጥ ያተኮረ በምሁራዊ ጥልቀት የሚመራ ትግል ማካሄድ አለብን። እረፍት አለመስጠትና በጭንቅት ውስጥ መክተት የጠቅላላው የካፒታሊስት አገሮች ባህርይ ስለሆነ የውጭንና የውስጥን ጠላቶች መቋቋም የሚቻለው በተሰበጣጠረና ምሁራዊ መሰረት በሌለው ትግል አይደለም። የአሜሪካንና የተቀረው የካፒታሊስት ዓለም ፖለቲካ አንድን ህዝብና አገር ጭንቀት ውስጥ መክተት ስለሆነ፣ እፎይ ብሎ የሚኖር ህዝብ ለማሰብና ለመፍጠር ዕድል ስለሚያገኝ አገሮች በማያቋርጥ ጦርነት መያዝ አለባቸው። ይህንን ሚስጥር ስንረዳና ወደ ውስጥ ኃይላችንን ሰብሰብ አድርገን የአገር-ወዳድነት ስሜትን በማዳበር በምሁራዊ ኃይል ስንታገልና ተንኮልን ስናስወግድ ብቻ ነው ኢትዮጵያን እንደ አገር ማዳን የሚቻለው። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

Clint Smith; How the Word is passed: A Reckoning with the History of Slavery

across America, New York, 2021

Naomi Klein; The Shock Doctrine, New York, 2007

Stjepan G Meštroviċ; The Barbarian Temperament: Toward a postmodern

critical theory, London and New York, 1993

Tom Burgis;  The Looting Machine, London, 2015

https://www.youtube.com/watch?v=XtLRi9O1rg4

https://www.youtube.com/watch?v=BKIqjncl0nA

7 Comments

  1. እርስ በርሳችን ላለው ነገር፣ የፈለጉትን ቢሉ ችግር የለውም። ይቺ ወደ መዝጊያው ላይ “…..ጸረ ኢምፔሪያሊስት ትግል….” የሚልዋት አረፍተ ነገር ግን ትንሽ አልተመቸኝም። “በመከባበር እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖረን እንታገል” ማለቱ የሚበቃ ይመሰለኛል። ከአሜሪካ ጋር ግልጽ እና አላስፈላጊ ሳፋጣ መግባት የደርግ ጊዜ ኢትዮፒያን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ለመረዳት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፣ “የሻምላው ትውልድ” የሚለውን እና በ”ጓድ” ፋሲካ ሲደልል [የኢሠፓ ፖሊት ቢሮ አባል እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩ] የተጻፈውን መጽሃፍ ማንበብ ይበቃል።

    በነገራችን ላይ አንድ መፈክር ትዝ አለኝ። “[የአሜሪካን] ኢምፔሪያሊዝም የወረቅት ላይ ነብር ነው” የሚለው። ግራ እጄን እያወናጨፍኩ “ነው!” “ነው!” ያልኩትን አሁን ላይ ሳስበው ያስቀኛል። አይፈረድብኝም፣ እንደዛሬው ጊዜ ቢሆን ይህንን መፈክር በዚያ ለጋ እድሜያችን “በሉ” ያሉን ሰዎች ልክ “ቻይልድ ሶልጀር” እንደሚባለው በተከሰሱ ነበር። ብቻ አለፈ!

  2. ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንዲያቡትና እንዲማሩበት እመክራለሁ፤ የአሜሪካ መንግሥት ለጥቁር አፍሪካ ፋይዳ ያለው ስራ ይሰራል ብሎ ማመን እራስን ማታለል ነው። ጣጣው ግን፤ ምህራን ነን የሚሉ ተጠቃሚዎች አሜሪካን መተቸት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል ምክንያት ይመስላል ሲተቹ አይታዩም።

  3. ማለፊያ እይታ ነው። እውቁ ጸሃፊ፤ ገጣሚና ወታደር (በጦር ሜዳ ላይ የቆሰለ) ጆርጅ ኦርዌል በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር። The history of civilization is largely the history of weapons. መግደል፤ መገዳደል፤ በሃይማኖት፤ በነጻነትና በዘረፋ ስም ሃገሮችን ማበራየት የነበረ ያለም የሚኖርም ነው። እርግጥ ነው አሜሪካና አውሮፓን ወያኔ ላይ የሙጥኝ እንዲሉ ያደረጋቸውን ጉዳይ ሳናውቅ ሰላም ሰላም ቢባል ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው። ለዚህ ነው አሁን ወያኔ ስለ ሰላሙ መፈራረም ጉዳይ የተለያየና የተመሰቃቀለ መግለጫና ዜና የሚያናፍሰው። ሲጀመር መሳሪያ መታጠቅ የድንቁርና ምልክት ነው። የታጠከው መሳሪያ መከራ አዝናቢና ጨቋኝ ሲሆን ደግሞ የበለጠ መደንቆር ይሆናል። እኔ ያኔም ዛሬም ወያኔ አምኖ በሰላም ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። በዚህም በዚያም እንደ ተልባ ስፍር እየተንሸራተተ ውጊያ በከተማና በገጠርም ይሞክራል። ግን የትግራይ ህዝብ የሞተና የቆሰለ ወገኑን ቆጥሮና አስልቶ ሲያውቅ ወያኔ ላይ ይነሳል ብዬ አምናለሁ። ሰው እስከ መቼ ነው ውሸት እየተጋተና እየጋተ የሚኖረው?
    ባንጻሩ የብልጽግናው መንግስት ወያኔን ያለ ልክ ከመለማመጥ ይልቅ እውነተኛ አቋም ይዞ መፋለም ይኖርበታል። ደግሞስ ሰራዊቱ 70% ትግራይን ይቆጣጠራል ተብለን የለ እንዴ። ታዲያ ምን ቀረ? ጋዜጠኞችን ያለምንም መረጃ እስር ቤት ወርውሮ በወታደሩ ላይ መኪና የነድትን፤ በአፋርና በአማራ እንስሳት ሳይቀር በጥይት የገደሉትን እርቅ ገለ መሌ ማለቱ አሳዛኝ ነው። ግን ስለ ሰላም ሲባል ነው ተብለናል። ግን ሰላም ይኖራል ወይ? አይመስለኝም። ነገሩ ግን ውስብስብ ነው። በሰሜን ያለው የመከራ ዶፍ ማንጠባጠብ ጀመረ ሲባል ጊዜ የሰጣቸው በኦሮሚያ ክልል በሰው ላይ ያደረሱትና የሚያደርሱት ግፍ ይህ ነው አይባልም። ይህ ጨካኝና አረመኔ ኦነግ/ሸኔ ቡድን እንዲህ የሰው ደም እያፈሰሱ ቆመው መሄዳቸው በራሱ የምድሪቱን የክፋት ደረጃ ያሳያል። በአዲስ አበባ ከኤርፓርት እስከ ጉምሩክ ሥፍራው ሁሉ የተያዘው በኦሮሞዎች ነው። ታዲያ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ከሆነ ብልጽግና ከወያኔ የአገዛዝ ስልት የሚለየው የቱ ላይ ነው? ወያኔ በዚህም በዚያም ራሱ በድሎ ራሱ አለቀሰ እንዲሉ በሚያሰማቸው ኡኡታዎች ለትግራይ ህዝብ ይህን ሰርተን ይህን አቅደን በማለት ጠ/ሚሩ ሲናገሩ መስማት ያማል። በወሎ፤ በጎንደር፤ በአፋርና በሽዋ ወያኔ ያፈረሳቸውና የዘረፋቸው ንብረቶች ከታሸጉበት ተፈልገው ለተዘረፈው ህብረተሰብ መመለስ አስፈላጊ ነው። እርዳታውም እነዚህን ወገኖች ሁሉ ማካተት አለበት።
    በመዝጊያው የአውሮፓና የአሜሪካን የውጭ ፓሊሲ ለማወቅ የኢራንን ታሪክ ወደ ኋላ ተመልሶ መመልከት ያሻል። የእንግሊዙና የአሜሪካው የስለላ መረብ ለሃገር የሚያስቡ መሪዎችን አፈር አልብሰው ለእነርሱ አቤት የሚሉ ሰዎችን በስልጣን ላይ እያስቀመጡ ለዝንተ ዓለም ነዳጅ ሲያፍሱ እንደኖሩ በግልጽ ያሳያል። ነጩ ዓለም የሚያስቀድመው የሃገሩን ጥቅም ነው። ሌላው ሁሉ የማይታመን ለወፎች የሚሰጥ ነገር ነው። በመጨረሻም በጌታቸው አስፋ ዘፈን – ስህተቱን ማን ያምናል የሚለውን ዘፈን ፈልጋችሁ ስሙ። በቃኝ!

  4. ዶር ምን ይባላል እናመሰግናለን ከማለት በስተቀር ጽሁፉን ለኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ክልሎችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች ባድራሻቸው ቢደርሳቸው መልካም ነበር። እኛ ምሁር የምንለው ከምክንያቱ ጀምሮ እስከ መፍትሄው የሚወስደንን ነው ። በዚህ ጽሁፍ መረዳቱ ቢከብዳቸውም ባለስልጣኖች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ምሁር ሳይሆኑ ምሁር የሆኑትም ያነቡታል በየቦታውም የሀሳቡ አመንጭ በመምሰል ይጠቅሱታል። የሚገርም ነው አረጋዊ በርሄ፣ብርሀኑ ነጋ፣ዲማ ነገዎ፣መራራ ጉዲና እንዲህ ያለ ፍሬ ያለው ነገር ጽፈው የእውቀታቸውን ጥግ የሚያሳዩን መቼ ይሁን? ዘወትር የምናያቸው ፍሬ ያለው ሀሳብ ማፍለቅን ሳይሆን ንትርክ፣ተንኮል፣ጠለፋ፣ቅጥፈት ላይ ነው። እውነትም የካፒታሊዝም ተንኮል በሀገራችን መገለጫ እነዚህ ሰዎች ናቸው። እውቀት ያብዛልን

  5. ውድ ወንድሞቼ ለሰጣችሁኝ አስተያየት በጣም አመሰግናችኋለሁ። አቶ ዳሹሬ ቅሬታህንና ምክርህን እቀበላለሁ። በዚያን ጊዜ ፀረ-ኢምፔራያሊዝም ትግል አስፈላጊ ቢሆንም በዚያ መልክ መካሄዱ ትክክል አልነበረም። ለምን በዚያ መልክ እንደተካሄደና፣ በዛሬው የዓለምና የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በምንስ መልክ መካሄድ እንዳለበት ሰሞኑን ጊዜ ሲኖረኝ አጠር መጠን ባለመልክ ለማብራራት እሞክራለሁ።

    ፈቃዱ በቀለ

  6. ቀላዋጭ ፓለቲከኛ ምን ጊዜም ቢሆን የራስ አቋም የለውም። እንደ ጉንዳን የተሸከመውን ይዞ አብሮ መትመም እንጂ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ አሜሪካ በሙሉ ልቧ እንደምትሰራ በየጊዜው ባለስልጣኖች የሚናገሩትን ቃላት ልብ ማለት ይገባል። ዘር ማጥፋት፤ የጅምላ እስራት፤ የሰው መፈናቀል፤ የወልቃይት ጉዳይ ባጠቃላይ አሜሪካኖች የማይገቡበት ቀዳዳ የለም። 27 ዓመት ሙሉ ወያኔ የሰው ጥፍር ሲነቅል፤ ቆለጥ ላይ ውሃ ሲያንጠለጥል ሰው እንደፈለገ ሲገልና ራሱ አፈንድቶ ራሱ ከሳሽ ሆኖ ሲቀርብ እያወቁ (ዊኪሊክ ይመልከቱ) አሁን እንዲህ በወያኔ ላይ ያንገበገባቸው ጉዳይ ለማንም ግልጽ አይደለም። ግን ለትግራይ ህዝብ አስበው እንዳልሆነ አሁን ላልታያችሁ ጊዜ ይፋ ያደርገዋል። እኔ እንደሚረዳኝ ግን ወያኔን ወደ ስልጣን ለመመለስ የሰሜን እዝን እንዲመቱ ሁሉ ያደረጉት እነርሱ ናቸው ባይ ነኝ። ውጊያውም ከተጀመረ በህዋላ የሳተላይትና የቁስ እርዳታና ሌላም እሳቱ በሱዳን ሳይቀር እንዲቆሰቆስ ያደረጉ አሜሪካኖች ናቸው።
    ከቀን በፊት ኢትዮጵያ ላይ በተደረገ ስብሰባ Rep. Sherman ያቀርባቸው የነበሩ ጥያቄዎችና ያነሳቸው ጉዳዪች ሌላ መንግስት በአንዲት ሃገር ላይ ጣልቃ እንዲህ ሲገባ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ከትግራይ ችግር በስተቀር አሜሪካ ሌላው የሃገራችን ህዝብ ሰው አይደለም። ግልጽ የሆነውን ጭፍጨፋና ዝርፊያ እያወቁ የሚያወግዙት ሌላውን ነው። እነዚህ የፓለቲካ ሙታኖች እውነትን ለማየት አይናቸው ከታወረ ዘመናት ተቆጥሯል። እጅግ የሚያስገርመኝ ደግሞ ስለ ኤርትራ የሚሉት ጉዳይ ነው። ትላንት ለ 30 ዓመት ስንገዳደል በዚህም በዚያም እሳት እያቀበሉ ሲያጫርሱን ቆይተው አሁን ተንፈስ አለ ሲባል ማዕቀብ፤ እንዲያውም አልፎ ተርፎ ከእርዳታና ከመድሃኒት ሌላ ምንም እንዳይገባ ብሎክ ማድረግ እያለ ሲለፈልፍ መስማት ውስጥን ያበግናል። እነርሱ እንደ ፈለጉ የሚጭኑትና የሚያዙት ሰው ካልተገኘ ሃገር ማፍረስ ሙያ ብለው ይዘውታል። በዚህ ሁሉ ልፍለፋ የኮንግረሱ አባል ስለ ወያኔ ክፋት ሆነ በወያኔ ወረራ ስለተፈጠረው እልቂትና ውድመት በጭራሽ አላወሳም። በወያኔ ተክፍሎት የሚሰራ አንድ የግል ድርጅት ተወካይ እንጂ ህዝብን የወከለና የሰከነ የኮንግረስ አባል አይመስልም። ግን ያው ላቢይስቶች እኮ ጉቦ ከፋይ ናቸው። ሌላ ትርጉም የለውም። አቃምሰውት ይሆናል። ግን ከአሜሪካ ባለስልጣኖች እውነት ይገኛል? የፍሪቃ ሃብታም ሃገር የነበረችውን ሊቢያን ያፈራረሱት ለሊቢያዊን አስበው ነው እንዴ? አይደለም።
    አሁን እንሆ ኢትዮጵያና ኤርትራ ቢቧቀሱ ዋሽንግተን ላይ ሰርግና ምላሽ ነው የሚሆነው። አላማቸው የኤርትራውን መሪ መፈንገልና የራሳቸውን አሻንጉሊት ማስቀመጥ ነው። ለዚህም ነው ወያኔ ለዘመናት ኤርትራን በአሜሪካ እየታገዘ ማዕቀብ ውስጥ አስገብቶ ያቆያት። ተላላኪውን ወያኔን ደስ ለማሰኘት አንዲትን ሃገር በማዕቀብ ቀፍድዶ መያዝ። ይህ ነው የአሜሪካ ዲሞክራሲ! ደግሞ ደጋግሞ ሩሲያን ከደገፉ ሃገሮች አንዷ ኤርትራ ናት ይለናል። እና ምን ይጠበስ? የግድ እኛ ያልነውን ካልሰማችሁ ነው? ግን በምድር ላይ እንደ አሜሪካ የውጭ ፓሊሲ ያለ መሰሪ የፓለቲካ ጥልፍልፍ ነገር የለም። ስለሆነም ሃገራት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከአሜሪካ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ አለባቸው። ስንዴአቸው፤ የአለም ባንኩ ብድር ሌላውም ጥንቅር ይበል። ሃገሮችን እዳ ከማሸከም ሌላ የሚያመጣው ፍቱን የሆነ መድሃኒት ለሃገሮች የለምና። ኩባን ለ70 ዓመት ቆልፎ የያዘ ይህ ጭፍን እይታቸው ብዙም ለኩባዊያን የበደለው ነገር የለም። እዚያም ይኖራል አሜሪካም ውስጥ ይኖራል። የአሜሪካና የወያኔ ጋብቻ ገና ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። የዶ/ር ፍቃድን ቀጣይ ጽሁፍ እጠብቃለሁ። በቃኝ!

  7. ይህ ትችቴ ለአንባቢያን ለመድረሱ እርግጠኛ ባልሆንም ፣ምክንያቱም በተደጋጋሚ የምሰጣቸው ትችቶች በማላውቀውና ባልገባኝ ምክንያት ተለጥፈው ስላላዬሁ ስጋት ቢኖረኝም ከማስፈር አልተቆጠብኩም።
    በቅድሚያ ዶር ፈቃዱ በሚያቀርቡት ጽሁፎች የሚሰጡት ትንታኔ ዓይን ገላጭና አስተማሪነታቸውን የሚክድ ያለ አይመስለኝም።ትንታኔያቸው ከመርህና ከሳይንሳዊ ርእዩተዓለማዊ እይታም ስለሚነሳ ብዙም ግድፈት የለበትም።በድፍረት የዓለምን ፖለቲካና በፖለቲካ ዙሪያ በአውሮፓውያን በተለይም በአሜሪካኖች የሚፈጸሙትን ደባና ሴራዎች ፍንትው አድርገው እስከመፍትሔው በማሳዬት ይህ የመጀመሪያቸው ባይሆንም ግንባር ቀደም ምሁርነታቸውን ሳላደንቅ አላልፍም።
    ተወደደም ተጠላም በዓለም ላይ ለሰፈነው ማህበረሰብአዊ ቀውስ፣ማህበረሰብአዊ መፍትሔ ማምጣት ግድ ይላል።የዓለም ሕዝብን ወጥሮ የያዘው፣ለመከራና ለጦርነት የዳረገው የፖለቲካ አስተሳሰብና ከዚያም የሚጨለፈው የኤኮኖሚ፣የባሕል፣የአስተሳሰብ ስብራት ሊወገድና ዓለም ወደተሻለ ሰላማዊ ጎዳና የምታመራው፣የሰው ልጅ በሰላም ሰርቶ መብቱና እኩልነቱ ተከብሮለት ሊኖር የሚችለው ብዝበዛና ጭቆናን የጭኑበትን ሃይሎች ለማሶገድ ሲችል ብቻ ነው።ለዚያም የችግሩን ጠንሳሾችና ባለቤቶች ማወቅ ይገባል። የዶር ፈቃዱ መልእክትም ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ነው።ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ይባላል።ዶር ፈቃዱ በግልጽና በድፍረት አሳይተውናል።ቀጣዩ ሥራ ከዓለም አቀፉ የባርነት ሰንሰለት ለመውጣት በሚያስችለን ተግባር ላይ መሰለፍ ነው።በራስ ባህል፣በራስ እይታ፣በራስ ኤኮኖሚ፣ባለባበስ፣በቋንቋ፣ባመጋገብ ነጻነት ካወጅን የባርነት በሩን ዘጋን ማለት ነው።እዚህ ላይ ከሌላው ዓለም ሕዝብ ጋር ፍጹም ግንኙነት አይኑር ማለት ሳይሆን በመልካም መተሳሰብና እኩልነት ላይ የተመሠረተ ፣የባርያና የጌታ ግንኙነትን የሰበረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይኑረን ለማለት ነው። አንዱ አገር ወይም ሕዝብ በሌላው አገር ወይም ሕዝብ ኪሳራ አይኑር ለማለት ነው።የኢምፔሪያሊስት ሥርዓት ለጥቂቶች እንጂ ለብዙሃኑ አይተርፍም።ለብዙሃኑ የሚተርፈው ቢኖር ዶር ፈቃዱ እንዳብራሩት፣ግጭት፣እልቂት፣ስደት፣ድህነት፣በሽታ፣በዕዳ መተብተብ—ወዘተ ብቻ ነው። አንድ ሰው ብቻውን ለመኖር ከባድ እንደሚሆንና እንደማይችል ሁሉ አንድ አገርም ብቻውን ሊኖርና ሊንቀሳቀስ አይችልም፤የግድ ትስስርና አብሮ መሥራትን ይጠይቃል።የሳይንስ ግኝቶችን፣ዕውቀትን፣የተፈጥሮ ሃብትን፣ያለውን በሌለው እዬለወጠ፣ለለሌለው እያካፈለ በሚዛናዊ በሆነ መልክ ሊቀባበል ይችላል።መቻልም አለበት።ለዚህ ሁሉ መጀመሪያው በምዕራባውያን የሰፈነው ግለኝነትና እራስ ወዳድነት ያንንም ተከትሎ የመጣው ጭካኔና አረመኔነትን ለማሶገድ ቁርጠኛ ሆኖ መገኘት ነው።ችግሩን አውቀናል።ለችግሩ መውጫ መፍትሔውን መፈለግ አለብን። መፍትሔውም በምዕራባውያን የሚዘወረውን ቅኝ አገዛዝ፣የእጅአዙሩንም ጨምሮ ለማሶገድ ትግል ማካሄድና እራስን ነጻ ማድረግ ነው።የትግሉ መጀመሪያ መሠረታዊ አስፈላጊ ምርቶችን በማምረት፣ከውጭ የቅንጦት ቁሳቁሶችን ባለመጠቀም ዕዳ ውስጥ ላለመነከር፣ በራስ ምርት መጠቀምን፣በራስ ቋንቋ መጠቀምን፣የራስን መልካም ባሕልና እምነት ማክበርን ተግባራዊ በማድረግ ይጀመራል። የአገርን ክብርና ዋጋ በማያሳጣው የፖለቲካ አስተሳሰብ መታነጽ ለአንድነትና ለእድገት መሠረት እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል።ሕዝብ ለሕዝብ የሕዝብ የሆነ ሰብአዊና አገራዊ የፖለቲካ ባህል ልንከተል ይገባል።በአገራችን የሰፈነው የጎሰኞች አጥፍቶ የመጥፋትና የስግብግቦች ፖለቲካ የወራሪዎች ስልት ስለሆነ ማሶገድ የግድ ይላል።ጎራው መለዬት አለበት!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share