November 17, 2022
54 mins read

 የሁለት ክልሎች ወግ  – ኤፍሬም ማዴቦ

 

Ephrem Madeboኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])

ከአዲስ አበባ በሱሉልታ፣ በቱሉቦሎ፣በአቃቂና በሰንዳፋ በኩል እየወጡ የኢትዮጵያን ዋና ከተማ ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ጋር የሚያገናኙ አራት በሮች አሉ። እነዚህ አራት በሮች ደፍሮ ለጠየቃቸው ሰው ሁሉ የሚናገሩት የየራሳቸው ታሪክ አላቸው። የአደስ አበባ-ሰንዳፈ-ሸኖ በር ግን ሰው ጠየቀውም አልጠየቀው መንገዱ እራሱ አፍ አውጥቶ የሚናገረው የራሱ የሆነ ለየት ያለ ታሪክ አለው። ኦሮሚያ-አማራ፣አማራ-ኦሮሚያ እያለ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ሰንዳፋ፣ ደብረ ብርሃን፣ሸዋሮቢት፣አጣዬ፣ ከሚሴ ኮምቦልቻ እያለ ባቲ ድረስ የሚዘልቀው የአዲስ አበባ ደሴ መንገድ የኢትዮጵያን የ30 አመት የተበላሸ የብሔር ፖለቲካ አፍ አውጥቶ ይናገራል።

ከአዲስ አበባ ትንሽ ወጣ ሲል ለገጣፎ-ለገዳዲ፣ አሌልቱ-ቱለፋ፣ ቅምቢቢት-ሸኖ፣ሰምቦ-ጫጫ እያለ ደብረ ብርሃን ድረስ የሚዘልቀው የአዲስ አበባ ደሴ መንገድ፣ የኦሮሚያን ክልል ውልግድግዱ የወጣ የእንዱስትሪ ፖሊሲና ክልሉ ዉስጥ ስር የሰደደው ሙሰኝነት ኢንቨስተሮችን ምን ያክል እንዳንገፈገፈና ኦሮሚያን አታሳዩን አንዳሰኛቸው እማኝ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ደሴ መንገድ “ኦሮሚያ ክልል”፣ “ኦሮሚያ ልዩ ዞን”፣ “አማራ ክልል”  እያለ ከህዝብ ዉስጥ ህዝብ እየመረጠ አጥር የሚያጥረውን የኢትዮጵያን የብሔር ፖለቲካ ብልሹነት በግልጽ ያሳያል፣በተለይ ከአዲስ አበባ ደብረሲና ድረስ የመንገዱ ግራና ቀኝ የሚናገረው የፖለቲካውን እውነታ ብቻ ሳይሆን ይህንን ብልሹ ፖለቲካ ተከትሎ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተከተሉትን የተለያየ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በማያሻማ ቋንቋ ይናገራል።

ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚሄድ ሰው ከአዲስ አበባ ከተማ ወጥቶ ኦሮሚያ ክልል መግባቱን የሚያውቀው በቁቤ የተጻፉ የከተማ አስተዳደር ጽ/ቤቶችን፣ የጤና ጣቢያዎችንና የንግድ ቤቶችን ስም ሲመለከት ነው። ከኦሮሚያ ክልል ወጥቶ አማራ ክልል መግባቱን የሚያውቀው ደግሞ በየመንገዱ ግራና ቀኝ ተሰርተው በማምረት ላይ የሚገኙና ገና በመሰራት ላይ ያሉ የማምረቻ ተቋሞችን ብዛት ሲመለከት ነው። በአዲስ አበባ ደሴ መንገድ ላይ የሚገኙ የኦሮሚያም ሆነ የአማራ ክልል አካባቢዎች መልክዓ ምድር ተመሳሳይ ነው፣ የአካባቢው የአየር ንብረትና በአካባቢው የሚገኘው የተፈጥሮ ኃብት ብዛትና ስርጭትም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ለምንድነው ከሁለቱ የአገራችን ትልልቅ ክልሎች አንዱ ለማንነት ሌላው ለእንዱስትሪ ዕድገት ቅድሚያ የሰጡት?

ለምንድነው ከአዲስ አበባ ደብረ ብርሃን ድረስ ባሉት የአማራ ከተማዎች የሚታየው የእንዲስትሪ ብዛት በተመሳሳይ መንገድ ላይ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተማዎች ዉስጥ የማይታየው? ለምንድነው ባህር ዳርና ደብረ ብርሃን ውስጥ የሚታየው የእንዱስትሪ ዕድገት አዳማና ቢሾፍቱ ውስጥ የማይታየው? ለምድነው የአማራ ክልል ባለሥልጣኖች ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚጓዙትን ርቀት ሌላ ቢቀር ሲሶውን እንኳን የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣኖች የማይጓዙት? ለምንድነው ኢንቨስተሮችን የሚማርክ የተፈጥሮ ኃብት ያለው ኦሮሚያ ክልል፣ የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን መማረክ ሲገባው ጭራሽ የሚያሸሸው? ለምንድነው ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ኢንቨስተሮች ካፒታላቸውን እየያዙ ወደ አማራ ክልል የሚሄዱት? ለምንድነው ክልሎቻችን የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የማይወዳደሩት?

መቼም በዛሬዋ ኢትዮጵያ መሬት ቀምቶ ያጠረም፣የህዝብና የመንግስት ንብረት የዘረፈም፣ የገደለም፣አስገድዶ የደፈረም ሁሉም እየሄደ የሚደበቅበት ዋሻው ብሔሩ ነውና፣ ይህንን ጽሁፍ ገና የመጀመሪያውን ገጽ አንብበው ሳይጨርሱ የአቶ ኤፍሬም ኦሮሞ ጠልነት አያልቅም እንዴ የሚሉ ከራሳቸው ውጭ ሁሉንም የሚጠሉ የትየለሌ ነሆለሎች አሉ። እኔ ይህንን ጽሁፍ የጻፍኩት የምወደውና ከልጅነቴ ጀምሬ አብሬው የኖርኩት የኦሮሞ ህዝብ ከሙሰኝነት አደጋ ነጻ እንዲወጣ ነው። ደሞም ወገኖቼ የማወራው ስለ ኦሮሞ ህዝብ አይደለም፣ ይህ ህዝብ ስለሚኖርበት ክልል እንጂ! ስለጽድቅና ኩነኔም አይደለም፣ ክልል እንደ ሰው የሚጸድቅ ቢሆን ኖሮ አማራና ኦሮሚያ ክልል ሁለቱም የሚጠብቃቸው ኩነኔ ነው። ግን ሌላ ቢቀር አማራ ክልል ከአስርቱ ትዕዛዛት የመጀመሪያውን ያከብራል፣ ኦሮሚያ ክልል ግን አስሩንም አያከብርም።

የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ ከኢትዮጵያ ውጭ ለሁለት አስርተ አመታት የኖረው በዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ነው። ዋሺንግተን ዲሲ በቨርጂኒያና በሜሪላንድ ግዛቶች የተከበበች የአለማችን ሃብታሟ አገር ዋና ከተማ ናት። የዋሺንግተን ዲሲ ወሰን ተሰምሮ የተቀመጠ ስለሆነ ዲሲ አትሰፋም፣ አትጠብም። ነገርግን ዲሲን በከበቧት በቨርጂኒያና በሜሪላንድ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎችና ከተማዎች የዲሲ ዕድገት እያሳደጋቸው አሜሪካ ውስጥ ኃብታም ከሚባሉ ወረዳዎች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ መሆን ችለዋል። ከአምስት በጣም ሃብታም ከሆኑ የአሜሪካ ወረዳዎች ሦስቱ፣ ከአስራ አምስቱ ደግሞ ስምንቱ የሚገኙት በዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ በሚገኙ የቨርጂንያና የሜሪላንድ ግዛቶች ዉስጥ ነው።

ሃወርድ፣ፌርፋክስ፣ሞንቲጎመሪና ላውደንን የመሳሰሉ የሜሪላንድና የቨርጂኒያ ወረዳዎች በአሜሪካ ደረጃ ኃብታም ሊሆኑ የቻሉት፣ ቨርጂኒያና ሜሪላንድ እንደኛ አገሮቹ “ያዩትን ሁሉ የኛ ባዮች”  ከሁለቱ ግዛቶች ተቆርሳ የተመሰረተችውን ዋሺንግተን ዲሲን “የኔ ናት”፣“የኔ ናት” እየተባባሉና አገር እያመሱ አይደለም። ዋሺንግተን ዲስን የከበቧት በሁለቱ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙት ከተማዎች/ወረዳዎች በአሜሪካ ደረጃ ኃብታም መሆን የቻሉት ሁለቱ ግዛቶ አመቺ የዕድገት ፖሊሲ ስለሚከተሉና ዋሺንግተን ዲሲን በተመለከተ ያላቸው አቋም፣ ዲሲ የ”አገራችን ዋና ከተማ” ናት (Our nation’s capital) የሚል ስለሆነ ነው። ይህ “ሰዋዊ አቋም” እኛ ኢትዮጵያዊያንም ልንከተለው የሚገባ አቋም ነው።

ታዲያ ለምንድነው የታሪክ አጋጣሚ አድሏቸው በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ሱሉልታ፣ ሰንዳፋ፣ቱሉዲምቱ፣ለገጣፎ፣ቡራዩና ኮየፈጨን የመሳሰሉ የኦሮሚያ ከተማዎች የዋሺንግተን ዲሲ ዕድገት እንዳሳደጋቸው እንደ ፌርፋክስ፣አሌክሳንደሪያ፣ሲልቨርስፕሪንግ፣ ሮክቭልና ቤተስዳ ከተማዎች እራሳቸውን ሆነው እንዲያድጉ የማይፈቀድላቸው? ለምንድነው የኦሮሚያን ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ኤኮኖሚ በፍጥነት ማሳደግ የሚችሉ የኤኮኖሚ መንገዶች በማንነት ስም እንዲዘጉ የሚደረገው? ለመሆኑ ኦሮሚያ ክልል ቅድሚያ የሚሰጠው ለምንድነው? መታወቂያው ድህነት በሆነ ማንነት ላይ የሚኮራ ማህበረሰብ መፍጠር ነው ወይስ ድህነትን ያሸነፈ ማህበረሰብ መፍጠር ነው? ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ኦሮሚያ ክልልንም ባጠቃላይ አገራችን ኢትዮጵያንም በጣም ወደተለያየ ቦታ ነውና የሚወስደው እንዲህ አይነቱ ሸውራራ አመለካከት ካሁኑ መታረም አለበት።

ቨርጂኒያና ሜሪላንድ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ሲመጡ “እኔ እሻላለሁ”፣ “እኔ እሻላለሁ” እያሉ የሚያደርጉት ውድድርና ኢንቨስተሮች ወደግዛታቸው መጥተው መዋዕለንዋይ እንዲያፈሱ የሚሰጧቸው ማበረታቻ፣ እኛ አገር ዉስጥ ካለው የተበላሸ የማንነት ፖለቲካና አይን ያወጣ ሌብነት ጋር ሲወዳደር ምን ነካን የሚያሰኝና አንገት የሚያደፋ ነው። ሁሉም ነገር እኩል በሆነበት ሁኔታ አንድ ኢንቨስተር ከሜሪላንድ ቨርጂኒያን የሚመርጠው ቨርጂኒያ የተሻለ ማበረታቻ ከሰጠው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን፣ ለምሳሌ፣ ኦሮሚያ ክልል ለኢንቨስትመንት አመቺ ክልል ቢሆንም ብዙ ግዜ ኢንቨስተሮች ከኦሮሚያ ክልል አማራ ክልልን ይመርጣሉ። ይህ የሆነው ኦሮሚያ ውስጥ ከላይ እስከታች ያለውን በሙስና የተጨማለቀ አሰራር፣ከማንነት ጋር የተያያዘውን ማነቆ፣ እጅ እጅ የሚል ቢሮክራሲና ከሰው ሃይል ቅጥር ጋር የተያያዘውን ግዴታ የውጭ አገርም የአገር ውስጥም ኢንቨስተሮች ስለሚጸየፉ ነው።

ቨርጂኒያና ሜሪላንድ ኢንቨስትመንት ለግዛታቸው ይዞት የሚመጣውን ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ስለሚረዱ፣ የኢንቨስትመንት ካፒታል ወደ ግዛታቸው ይምጣ እንጂ ከሚመጣው ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው የስራ ዕድል የሚቀጠሩ ሰዎች ህጋዊ እስከሆኑ ድረስ፣ አሜሪካዊያን ይሁኑ፣ ከአፍሪካ ይምጡ ወይም ከቻይና ቨርጂኒያና ሜሪላንድ ጉዳያቸው አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ አንድ ኢንቨስተር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የኦሮሞ ተወላጆችን ካልቀጠረ በግልጽ ገንዘብህን ይዘህ ሂድ ተብሎ ነው የሚነገረው። በቅርቡ ሰፋሪኮም ከሚባል የውጭ ኩባንያ ጋር የተደረገው እሰጥ አገባም የሚያሳየን ይህንኑ ሃቅ ነው። አሁንማ ጭራሽ ኦሮሚያ ውስጥ የሚሰሩ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን የትኛው ባንክ ውስጥ ማስቀመጥ እንዳለባቸውም እየተነገራቸው ነው ይባላል። ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልልና ሲዳማ ክልል ውስጥ አንድ ኢንቨስተር የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት፣ መሬት ለመግዛትና የግንባታ ፈቃድ ለማውጣት በጉቦ ሰንሰለት የተያያዙ ባለስልጣኖችን ኪስ ካልሞላ አንድም ስራ መስራት አይችልም።

ኢንቨስትመንትን በተመለከት በየክልሉ የሚታየው ሌላው ችግር፣ የግል ባለኃብቶች ለበጎ አድራጎት ስራ የመጡ ይመስል የከተማ፣የዞንና የክልል አስተዳደር ጽ/ቤቶች በነጋ በጠባ ደብዳቤ እየጻፉ ገንዘብ አምጡ ማለት የተለመደ አስራር መሆኑ ነው። የፌዴራል፣ የክልል መንግስታትና፣ የከተማ አስተዳደር ጽ/ቤቶች የግል ባለኃብቶችን እርዱን ብለው ደብዳቤ ሲጽፉ፣ ደብዳቤው ትዕዛዝ እንጂ የትብብር ጥያቄ አለመሆኑን እንዴት ዘነጉት? በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የንግድ ድርጅቶች ማህበራዊ ኃላፊነት (Corporate Social Responsibility) እንዳለ ሆኖ፣ የግል ድርጅቶች ለትርፍ የሚሰሩ የንግድ ተቋሞች እንጂ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዳልሆኑ የክልል መንግስታትና የከተማ አስተዳደሮች ማወቅ አለባቸው። የግል ባለኃብቶች ህጋዊ ግዴታና የዜግነት ኃላፊነት ከመንግስት የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፍል ነው እንጂ፣ መንግስት፣ ፓርቲ፣ፌዴራልና ክልል አምጡ የሚሏቸውን ገንዘብ መስጠት አይደለም። እንዲህ አይነቱ “ህጋዊ” ዝርፊያ መቆም አለበት!

ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ የገፋፋኝ፣አማራና ኦሮሚያ ክልል ኢቨስትመንት ብለው የሄዱ የተለያዩ ሰዎችን አናግሬ ያገኘሁት መልስ ነው። ኢንቨስተሮችን ወደ ክልላቸው እንዲመጡ በመጋበዝ፣ በማበረታታትና በማስተናገድ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለው ልዩነት የቀንና የማታን ያክል ይለያያል። አንድ ኢንቨስተር አማራ ክልል ሲሄድ ከአማራ ክልል ባለሥልጣኖች አፍ የሚወጣው በየትኛው መስክ ላይ ነው ኢንቨስት ማድረግ ነው የምትፈልጉት፣ የት ቦታ ነው ኢንቨስት የምታደርጉት፣ምን እንርዳችሁ የሚል ጥያቄ ነው። ኢንቨስተሩ ከአዲስ አበባ በስልክ አናግሯቸው ከሆነ የሚሄደው፣ ባህር ዳር በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የሚገጥመው መስተንግዶ ማራኪ ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ነው። መስተንግዶው አውሮፕላን ማረፊያው ላይ አያበቃም፣ ኢንቨስተሩ ለኢንቨስትመንት የመረጠውን ቦታ ጎብኝቶ ወደመጣበት እስኪመለስ ድረስ ይቀጥላል።

የኢንቨስትመንት አመቺነትን በተመለከተ ኦሮሚያ ክልል ኢትዮጵያ ውስጥ ከየትኛውም ክልል ይበልጣል። ሆኖም አንድ የኢንቨስትመት ካፒታልና የስራ ዕቅድ ይዞ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ ከባለሥልጣኖች ጋር የተገናኘ ሰው የረሳው ዕቃ ቢኖር እንኳን ሁለተኛ ወደ ኦሮሚያ ክልል አይመለስም። ይህ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ሰው ሰራሽ የማንነትና ስነምግባራዊ ልዩነት የሚጎዳው ኦሮሚያ ክልልን ብቻ ሳይሆን አገራችን ኢትዮጵያን ጭምር ነውና፣ ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሙስና ስር የሰደደባቸው ክልሎች ከዚህ አይነት የቆሸሸ አሰራር የጸዱ እንዲሆኑ የፌዴራል መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰደ አለበት።

ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የግሉ ኤኮኖሚ ዘርፍ ባላደገባቸው፣ደሃና ኋላቀር በሆኑ አገሮች ውስጥ መንግስት በኤኮኖሚው ውስጥ መጫወት ያለበት ትልቅ ሚና አለ፣እንዲህ ሲባል ግን ማዕከላዊው መንግስት ከመንግስታዊ መዋቅር ውጭ ያሉ ሌሎች ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ተቋሞች የሚሰሩትን ስራ ተክቶ ይሰራል ወይም እነዚህን ተቋሞች እንዳሰኘው ይዘውራቸዋል ማለት አይደለም። የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ከብዙ አገሮች ውስጥ አንድን አገር የሚመርጡበት፣ በመረጡት አገር ውስጥ ደግሞ ለይተው አንድን አካባቢ የሚመርጡበት ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ኢንቨስተር ከሌሎች አገሮች ኢትዮጵያን የሚመርጠው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላም ሲኖር፣የፖለቲካና ማክሮ መረጋጋት ሲኖር፣ተከታታይ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ሲኖር፣አበራታች የግብር ፖሊሲ(Fiscal Incentive) ሲኖር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢንቨስትመንት ህግ ቀልጣፋና አመቺ ሲሆን፣ጥሬ ዕቃና ሌሎችም የተለያዩ ቁሳቁሶች በቀላሉ የሚገኙ ሲሆን፣ ችሎታ ያለው የሰራተኛ ኃይል ማግኘት ሲችል፣እያደገ የሚሄድ የአገር ውስጥ ገበያ አለ ብሎ ሲያምን፣አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት (Energy Supply) ሲኖር፣ ተደራሽ የሆነ የባንክ አገልግሎትና ቀልጣፋና የዳበረ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ሲኖር ነው።

ኢትዮጵያ በግብርና፣ በእንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች አመቺ አገር ብትሆንም፣ ከላይ ከተዘረዘሩት ለውጭ አገር ካፒታል አገር ውስጥ መምጣት አስፈላጊ ከሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ብዙዎቹ የሏትም፣ ወደ ክልል ወረድ ሲባል ደግሞ ከማንነት ጋር የተያያዙ ማነቆዎች አሉ፣ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እልህ አስጨራሽ ቢሮክራሲና ኪሱን በገንዘብ ካልሞሉለት እሺን የማያውቅ ባለስልጣን ቁጥር የትየለሌ መሆን ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ የውጭ ኢንቨስትመንት የማይመለከታት አገር እንድትሆን አድርጓል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛዎቹ የውጭ ኢንቨትመንትን የሚማርኩ ቅድመ ሁኔታዎች የሌሉት ከአሰራር ብልሹነታችንና ድክመታችን ጋር በተያያዘ ነው እንጂ ድሃ በመሆናችን አይደለም። የኢቨስትመንት፣የግብርና፣የእንዱስትሪ፣ የአገልግሎት፣ የአገር ውስጥ ንግድ፣ የውጭ ንግድና የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎቻችን የስራ ሂደትን ውስብስብ የሚያደርጉና እንደ ገመድ የሚያስረዝሙ እንጂ፣ ባለኃብቶችን የሚጋብዙ አይደሉም።

በቅርቡ ኢትዮጵያ የመጣው ሰፋሪኮም ኢትዮጵያን ከመረጠባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛ መሆኗ፣በቁጥር እያደገና በአይነት እየሰፋ የሚሄድ ትልቅ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግልት ገበያ መኖሩ፣ የኢትዮጵጵያ ቴሌኮም ዘርፍ በተለይ የብሮድባንድ አገልግሎት ዘርፍ በፍጥነት እያደገ የሚሄድ ትልቅ ዘርፍ በመሆኑ ነው። ሳፋሪኮም የመረጃ ቴኮኖሎጂ ኩባኒያ በመሆኑ ኢትዮጵያ ሲመጣ የመረጃ ቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸውንና ከመረጃ ቴክኖሎጂም ሳፋሪኮም ለተሰማራበት ዘርፍ የሚሆን ክህሎት ያላቸውን ሰራተኞች ይፈልጋል። ስለዚህ ሰፋሪኮም አዲስ አበባን ጨምሮ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ሄዶ ሰራተኛ ሲቀጥር፣ አመልካቾችን አወዳድሮ ይጠቅሙኛል የሚላቸውን ሰራተኞች ነው መቅጠር ያለበት እንጂ፣ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ እንደሚታየው የግድ ሁሉንም ወይም አብዛኛውን ሰራተኛውን የኦሮሞ ብሔር አባላት እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ ሊኖርበት አይገባም። አካባቢያዊ ኢ-ኢኩልነትን (Regional Inequality)  ለመዋጋት መንግስትና ሰፋሪኮም የብሔር ኮታ መጠንን በተመለከተ ሊስማሙ ይችላሉ፣ ነገርግን እሱም ቢሆን የአንድ ብሔር አባል ለኮታ ከመታጨቱ በፊት ችሎታው መታየትና በኮታው ውስጥ ለመካተት የሚያበቃውና ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር የሚስተካከል ወይም የሚበልጥ ችሎታ እንዳለው መረጋገጥ አለበት። በችሎታው ከሌሎች አንሶ ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ የሚቀጠር ሰው በመጀመሪያ የሚጎዳው ኦሮሚያ ክልልን ነው።

ሳፋሪኮም ለኢትዮጵያዊያን ቴሎኮም ተጠቃሚዎች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግልት በዝቅተኛ ዋጋ መስጠት የሚችለውና ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ቴሌኮም ዘርፍ ማሳደግ የሚችለው፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች አወዳድሮ መቅጠር ሲችል ነው እንጂ፣ የብሔር ተዋጽኦ እየተባለ በአስተዳደራዊ ውሳኔ የሚላኩለትን ማንበብና መጻፍ የማይችሉና የተግባቦት ችሎታ የሌላቸውን ገልቱዎች ሰብስቦ አይደለም። የኦሮሞ ልህቃን፣የኦሮሞ ማህበራዊ አንቂዎችና የኦሮሚያ ክልል መንግስት፣ሳፋሪኮም የንግድ ድርጅት እንጂ ፌዴሬሺን ምክር ቤት አለመሆኑን ሊያውቁ ይገባል። ሳፋሪኮም ሁሉም ሰራተኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች ባይሆኑም ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብቶ መስራቱ የኦሮሚያን ክልል ይጠቅማል እንጂ በፍጹም አይጎዳም። ስለዚህ ኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትን የሚገድብ የቅጥር ፖሊሲ ከሚያወጣ፣በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ሄደው መስራት የሚችሉ፣የተለለያየ ችሎታና ክህሎት ያላቸውና፣ በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳደረው ስራ ማግኘት የሚችሉ የኦሮሞ ወጣቶችን የሚያፈራ የትምህርት ፖሊሲ መቅረጽ አለበት። እንዲህ አይነት ትውልድ ሲፈጠር ነው በማንነቱ የሚኮራ ህዝብ አለኝ ማለት የሚቻለው። በድህነቱ አንገቱን የሚደፋ እንጂ የሚኮራ ህዝብ የለም፣አልነበረም፣ አይኖርምም!

የብሔር ማንነትም ድህነትም ሁለቱም ስማችን ላይ ተቀጥለው እኛነታችንን የሚገልጹ ማንነቶች ናቸው። እኔ በምኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ የብዙ ማንነቶች አባል ነኝ፣ከእነዚህ ማንነቶች ውስጥ አንዱ የብሔር ማንነቴ ነው። የብሔር ማንነቴን እወደዋለሁ፣ አከብረዋለሁ፣የብሔር ማንነቴን ሌሎች እንዲያውቁልኝም እንዲያክብሩልኝም እፈልጋለሁ። ሆኖም ግን የኔ ማንነት ተለይቶ የሚታወቀው በብሔር ማንነቴ ብቻ አይደለም። ድሃ ከሆንኩ፣ ድህነቴም ኤኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ማንነቴን የሚገልጽ “ማንነት” ነው፣ ነገርግን በፍጹም የማልወደው፣ የማልፈልገውና ልገላገለው የምፈልገው ግዜያዊ ማንነት ነው። የብሔር ማንነቴ ጎልቶ እንዲታይልኝ ይህንን ግዜያዊ ማንነት በፍጹም አሜን ብዬ አልቀበልም። የብሔር ማንነቴን ማንም አይወስድብኝም፣ የማልወደውን ድህነቴን ግን እኔ ካላጠፋሁት ማንም አያጠፋልኝም። በማንነት ስም ተግባራዊ የማደርጋቸው ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲዎች በአይን የሚታየውንና በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ የሚኖረኝን ክብርና ተቀባይነት አናሳ የሚያደርገውን ድህነቴን የማይቀንሱልኝ ከሆነ ምኑን በምን ይዤ ነው በብሔር ማንነቴ እኮራለሁ ወይም የሚያኮራ ማንነት አለኝ ማለት የምችለው?

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የፌዴራልም ሆነ የክልል መሪዎች፣የህዝብ ተወካዮችና የፓርቲ ባለሥልጣኖች ንግግር ሲያደርጉ፣ በምግብ እህል እራሳችንን እንችላለን፣ልማታችንን እናስቀጥላለን፣ ዕድገታችንን እናረጋግጣለን የሚሉ ሐረጎች ያሉባቸውን ንግግሮች ሲያደርጉ ማድመጥ የተለመደ ነው፣ ችግሩ እነዚህ ባለሥልጣኖች በአፋቸው የሚናገሩትን ቃል በተግባር አይኖሩትም። በነገራችን ላይ እነዚሁ ባለሥልጣኖችና የበታቾቻቸው ናቸው እንደ ህብረት ስራ ማህበር ከላይ እሰከታች ተደራጅተው የኢንቨስተሮችን ኪስ የሚያራቁቱትና ኢንቨስትመንትን የሚገድቡት!  ለመሆኑ መሬት ለመግዛት፣ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት፣ የህንጻ ግንባታ ስራ ለመጀመር፣ የባንክ ብድር ለማግኘት ባጠቃላይ አንድ ኢንቨስተር የልማት ስራ ለመስራት ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት ለማግኘት በየደረጃው ለሚገኙ ዘራፊ ባለሥልጣኖች ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈለ እንዴት ነው ኢትዮጵያ የምትለማው? ባለሥልጣኖቻችን ስለዕድገትና ልማት ሲናገሩ ስለ አገር ዕድገት ነው ወይስ ስለራሳቸው የባንክ ሂሳብ ዕድገት ነው የሚናገሩት?

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ከሚያስፈልጋቸው ታዳጊ አገሮች ውስጥ አንዷ ናት። ብዙ የአፍሪካ አገሮች የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመጋበዝ የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፣ ከሚወስዷቸው ብዙ እርምጃዎች ውስጥ አንዱ፣ አንድ ኢንቨስተር አገር ውስጥ መጥቶ የስራ ፈቃድ አውጥቶ ማምረት ወይም አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስ ያለውን ሂደት ቀልጣፋ፣ቀላልና አጭር ማድረግ ነው። ጎረቤታችን ኬንያን ጨምሮ ይህንን የሚያደርጉና ኢንቨስተሮችን የሚጋብዙ ብዙ የአፍሪካ አገሮች አሉ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ግን ከእነዚህ አገሮች ውስጥ አንዷ አይደለችም፣ እንዳዉም ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው ኢንቨስትሮችን ከቢሮ ወደ ቢሮ እያመላለሱ ማንገላታት ነው። ሁለት በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩ ጓደኞች በተመሳሳይ ግዜ አንደኛው ኢትዮጵያ ቢመጣና ሌላው ጎረቤት ኬንያ ቢሄድ፣ ኬንያ የሄደው ኢንቨስተር ምርት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ሲጀምር ኢትዮጵያ የመጣው ኢንቨስተር አኩርፎ ወደ መጠባት የመመለስ ወይም ጓደኛውን ፍለጋ ኬንያ የመሄድ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ለምድነው ሰው የማናሰራው፣ እኛም የማንሰራው?

ኢትዮጵያ ውስጥ በየክልሉ በተለይ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልልና ሲዳማ ክልል ኢንቨስትመንት ብሎ ከመሄድ አንዱኑ በልቶ የማይጠረቃ ባልሥልጣን ኪስ እንሙላ ብሎ መሄድ ሳይሻል አይቀርም። የክልል ባለሥልጣኖች ኢንቨስተር መጥቶ ሲያናግራቸው የሚያስቡት ለክልላችን ምን ይዞልን መጣ ብለው ሳይሆን ምን ያክል ይሰጠናል ብለው ነው፣ በተለይ አንድ ሰው ከዳያስፖራ መጣ ሲባልማ ዶላር አስጭኖ የመጣ ስለሚመስላቸው ንግግራቸው ሁሉ እንብላው፣ እንጋጠው ነው። በቅርቡ ቢሾፍቱ መሬት ለመግዛት የሄደ ሰው እንዳጫወተኝ፣ 1.8ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መሬት ለመግዛት ሁሉን ነገር ከጨረሰ በኋላ ተጨማሪ 400ሺ ብር ያለደረሰኝ መክፈል እንዳለበት ፊት ለፊት ተነግሮታል። ምነው አልበዛም እንዴ ብሎ ሲጠይቅ፣ ስንት ሰው እንደሚከፋፈለው ታውቃለህ? እንዳውም አንሷል ተብሎ ነበር የተነገረው።

ባለፉት ሠላሳ አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተለመደ የመጣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እነ እከሌ ቢኖሩባትም የክልሉ ባለቤቶች እነ እከሌ ናቸው፣ሌሎች መኖር ይችላሉ ነገርግን ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት፣ሃረሪ የሃሪዎች ናት የሚለው እንደ ሰው ሆነን ስናየው የሚያቅለሸልሽ አባባል አለ። ይህ አባባልና በዚህ አባባል ላይ ተመስርተው የሚቀረጹ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲዎች አገርን የሚጎዱ ቢሆንም መጀመሪያ የሚጎዱት ግን የዚህ ቆሻሻ አስተሳሰብ ባለቤት የሆኑትን ክልሎች ነው። ለምሳሌ፣ኦሮሚያ “ለኦሮሞ” ብቻ ነው የሚለው አጉል ፈሊጥ የሚጎዳው በፍጹም በዚህ ደረጃ የማያስበውን ገበሬውን፣ሰራተኛውን፣አንጠረኛውን፣አርብቶ አደሩንና ባጠቃላይ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚኖረውን ምስኪኑን ኦሮሞ ነው። ኦሮሚያ በቆዳ ስፋቷ፣ በተፈጥሮ ኃብቷና በህዝብ ብዛቷ ልክ እንድታድግ ከተፈለገ፣ በአንድ በኩል ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን ያለምንም መከልከል ኦሮሚያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ይዘው መግባትና ስራ መስራት መቻል አለባቸው፣ የኦሮሞ ተወላጆችም ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሲያድጉ ወደተለያየ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሄደው መስራት የሚያስችላቸውን ትምህርት እየተማሩ ማደግ አለባቸው።  በኔ እይታ ኦሮሚያ የምትለማው በኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ነው ብሎ የክልሉን በር ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን መዝጋት ኦሮሚያ እንዳትለማ በር ዘግቶ ሱባኤ ከመግባት ተለይቶ አይታይም። አንድ አዲግራት ውስጥ የተወለደ የትግራይ ተወላጅ ይርጋለም ከተማ ውስጥ ያለው መብትና ነጻነት፣ ይርጋለም ውስጥ ተወልዶ ካደገ የሲዳማ ተወላጅ ጋር እኩል እንደሆነ ሁሉ፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ተወልዶ የሚያድግ ኢትዮጵያዊም ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖረው መብትና ነጻነት ከኦሮሞ ተወላጅ ጋር እኩል መሆን አለበት። ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን ኦሮሚያ ክልል ሄደው መስራት መቻላቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው ያጎናፀፋቸው የማይገሰሰ መብት እንጂ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሚሰጠው ችሮታም መከልከል የሚችለው ልዩ መብትም (Privilege) አይደለም።

አያት የልጃቸውን የመጀመሪያ ልጅ ይጠሩና ማሙሽ ስታድግ ምን መሆን ነው የምትፈልገው ብለው ይጠይቁታል፣ የልጃቸው ልጅ ገና ንግግራቸውን ሳይጨርሱ ክልል ብሎ መለሰላቸው፣ አያት ይደነግጡና የትኛውን ክልል ነው መሆን የምትፈልገው ብለው ሁለተኛ ጥያቄ ይጠይቁታል፣ ልጁ የዋዛ አይደለም፣ የራሴ ክልል ብሏቸው ቤቱን በሳቅ ጨረሰው።

ለምንድነው ኢትዮጵያ ውስጥ ቀበሌዎች ወረዳ መሆን፣ ወረዳዎች ዞን መሆን፣ ዞኖች ደሞ ክልል መሆን የሚፈልጉት? ለምንድነው ትንሹም ትልቁም የሞራል ስብዕናውን እየሸጠ የመንግስት ባለሥልጣን መሆን የሚፈልገው? ለምንድነው ቄሱ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ረስቶ ከፍተኛ የስለት ገንዘብ የሚገባበት ደብር ለመቀየር ለበላዩ ጉቦ የሚሰጠው? መልሱ ቀላል ነው። ዞኑም፣ቄሱም ባለሥልጣን መሆን የሚፈልገውም ፍላጎታቸው አንድና አንድ ነው . . . . .  ህዝብንና አገርን እየዘረፉ ኪሳቸውን መሙላት! በዛሬዋ ኢትዮጵያ በፌዴራል መንግስት ደረጃ፣ በክልል፣ በዞንና በወረዳ አስተዳደር፣ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ ከላይ ከከተማው አስተዳደር እስከ ከክፍለ ከተማና ቀበሌ ድረስ ያለጉቦ የሚሰራ ምንም ስራ የለም። አንዳንዶቻችን አገራችን እንዲህ ናት እንዴ እያልን እንገረም ይሆናል፣ ምንም የሚገርም ነገር የለም። ኢትዮጵያ በሙስና ባገኘው ገንዘብ ትልቅ ቤት የገዛ፣ሪቮ የገዛ፣ ዱባይ የሚመላለስ፣ክብረ-ንጽህና ካለሽ ቪትስ እገዛልሻለሁ የሚልና ውስኪ ቤት ገብቶ መቶና መቶ ሃምሳ ሺ ብር ግማሽ ቀን በማይሞላ ግዜ የሚከፍል ሰው “እሱኮ አንበሳ ነው” ተብሎ የሚሞካሽባት አገር ሆናለች። የሞራል ስብዕናችን እንክትክት ብሎ መሬት የነካው የዘራፊዎቹ ብቻ አይደለም፣ የሚዘርፉንን ባለጌዎች የምናደንቀው የኛም ስብዕና መሬት ከነካ ቆይቷል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ዶማን “ዶማ” ማለት ካልጀመርንና ሙሰኝነትን ካልተጸየፍን እንኳን አድገን ኃብታም ህዝብ ልንሆን፣ ደርቅ ቂጣ የጧት ቁርስ የሚናፍቀን ግዜ ሩቅ አይደለም። የብሔር ፖለቲካ፣ መሰረታቸውን ብሔር አድርገው የተዋቀሩ ክልሎችና ይህንን አወቃቀር ተከትሎ አገራችን ውስጥ ስር የሰደደውን ብሔር ተኮር ዝርፊያን ከስሩ መንቅረን ካላጠፋን፣ሙስናና ሙሰኞችን አቅፈን ብዙ መጓዝ የምንችል አይመስለኝም።

የስነምግባር ብልሹነት፣ ለህዝብና ለአገር ያለን ግድየለሽነት፣ስግብግብነት፣አይን ያወጣ ሌብነትና ዝርፊያ አገራችንን አደጋ ላይ ጥለዋታል። እነዚህ ችግሮች እያሉ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዕድገትና ልማት ሊኖር ቀርቶ አሁን ያለንበትን ዝቅተኛ የድህነት ደረጃ ጠብቀን መሄድም አንችልምና፣እኛ ኢትዮጵያዊያን በበለጸገች ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም የመኖር ፍላጎታችን እንዲሰምር ከፈለግን በሙስና እና በሙሰኞች ላይ በሙሉ ኃይላችን መዝመት አለብን። ሙስና የአገርን ኃብት ከምርታማ ዘርፎች እያወጣ ምርታማ ወዳልሆኑና አገራዊ ልማትን ወደማያግዙ ዘርፎች እየወሰደ አገርን ወደ ኋላ የሚጎትት ማህበራዊ ቁስል ነው። ሙስና እምነትና መተማመንን የሚያጠፋ፣ዲሞክራሲን የሚያዳክም፣የኤኮኖሚ ዕድገትን የሚያደናቅፍ፣ ኢ-እኩልነትን፣ ድህነትን፣የተዛባ ማህበራዊ ክፍፍልን እና አካባቢያዊ ቀውስን የሚያባብስ ማህበራዊ በሽታ ነው። በዚህ ማህበራዊ በሽታ የተለከፈ ማህበረሰብ በግዜ ህክምና ካላገኘ፣ አገር አደጋ ውስጥ ይወድቃል።

ሙስና- የጤና፣ የትምህርት፣ የመጠለያና የፍትህ አገልግሎቶች ተደራሽነትን በመገደብ፣መግቢያና መውጪያ አሳጥቶ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚከተው ድሃውን ማህበረሰብ ነው፣ ኢትዮጵያ ደሞ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል መሰረታዊ አገልግሎት ማግኘት የማይችልባት የድሆች አገር ናት። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ዜጎች በነጻ ማግኘት መብታቸው የሆነውን የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት የገቢያቸውን ከፍተኛ መቶኛ በጉቦ መልክ ይከፍላሉ። በጉቦ መልክ ወደ ባለስልጣኖች ኪስ የሚገባው እያንዳንዱ ብር የድሃውን ማህበረሰብ አገልግሎት የማግኘት መብት ይቀማል። ሙስና ኢንቨስትመንት በርን ይዘጋል፣ የአገርን ዕድገት ወደኋላ ይጎትታል፣ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት ይሸረሽራል፣ ባጠቃላይ ሙስና ህዝብና መንግስት የገቡትን ማህበራዊ ዉል በማላላት ህዝብ ወደ ጽንፈኝነት፣ ወደ ግጭትና ወደ ህገወጥነት እንዲገባ በማድረግ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ተቆርጦ መጣል ያለበት ነቀርሳ ነው።

ሙስና በተለያየ መልኩ እየተከሰተ ማህበረሰብን የሚያሰቃይ በሽታ ነው – የመንግስት ሹመኞች  መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት ጉቦ ሲቀበሉ፣ ባለስልጣኖች ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸውና ለሌላም ጉቦ ለሰጣቸው ሰው ከቋሚ ንብረቶች ሽያጭ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የማግኘት ቅድሚያ ሲሰጡ፣የክልልና የፌዴራል መንግስት ባለሥልጣኖች የመንግስት ኮንትራት ለወዳጆቻቸው፣ ለዘመዶቻቸውና ጉቦ ለሰጣቸው ባለኃብት ሲሰጡና ባጠቃላይ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማትን የስራ ሂደት እራስን በሚጠቅም መልኩ ማዛባት (Distortion) እነዚህ ሁሉ በሙሉ ኃይላችን ልንዋጋቸው የሚገባ የሙስና አይነቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግስት ሙስናን ለማጥፋት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንደማይመለስ በተደጋጋሚ ተናግሯል፣ደሞም ከሰሞኑ የብሔራዊ ደህንነትና የፍትህ ሚኒስትሩን ያካተተ 7 አባላት ያሉት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ አቋቁሟል። ጅምሩ የሚያበረታታ ቢሆንም ሙስና በኮሚቴ፣ በመግለጫና በአዋጅ የሚጠፋ የዋዛ በሽታ አይደለም። መንግስት ሙስናን ለማጥፋት የሚዋጋው ከራሱ ጋር ነው፣ በራስ ላይ ጦርነት መክፈት ደግሞ ከጦርነቶች ሁሉ የከፋ ጦርነት ነውና፣ መንግስት ሙስናን መዋጋት ሲጀምር ጦርነቱ ከራሱ ጋር መሆኑን ማዋቁ የድሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው። ሙስናን ለመዋጋትና በሂደት ለማጥፋት ሁለተኛው ምዕራፍ በፌዴራልና በክልል መንግስታት አስራር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ከግብር ከፋዩ ህዝብ በተገኘ ገንዘብ የሚተዳደሩ የፌዴራልና የክልል መስሪያ ቤቶችና ተቋሞች በራቸውን ለሜዲያ ክፍት ማድረግ ግዴታቸው መሆኑን እንዲያውቁ መደረግ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ የቁጥጥር ተቋማት፣ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መገናኛ ብዙሃንና ህዝብ በተቀነባበረ መንገድ የሚሰሩበትን መዋቅር መፍጠርና፣ እነዚህ አካላት እንዳስፈላጊነቱ የመረጃ ቴክኖሎጂ የፈጠራቸውን የተለያዩ መሳሪያዎች በመጠቀም ተሰብስበው የተተነተኑ መረጃዎችን እንዲጋሩ ማድረግ ሙስናን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ያደርገዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ በኩል ምዕራባዊያን አገሮች፣ ሜዲያዎቻቸው፣ የአገር ውስጥና የአካባቢ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በጋራ ሆነው የከፈቱብንን ጦርነት መክቷል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራልና በክልል መንግስታት ዉስጥ ከላይ ከከፍተኛው ባለሥልጣን እስከ ቀበሌና ወረዳ ጉዳይ ፈጻሚ ድረስ ስር በሰደደው ሙሰኝነትና፣ ሙሰኝነት ያሳበጣቸውና ከመደበኛ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የፍርድ ቤቶችን ዉሳኔ በገንዘባቸው የሚያስለውጡ የዘመናችን ቱጃሮች በሚፈጽሙት ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ አሻጥር ቁም ስቅሉን እያየ መጀመሪያ አገሬን ላድን እያለ ዛሬ ድረስ ዘልቋል። ህወሓት ትጥቅ ፈትቶ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት ለማስወገድ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመስማማቱ፣በሰሜናዊው የአገራችን ክፍል የሚደረገው ጦርነት ዕልባት ያገኛል የሚል ትልቅ ተስፋ አለ (የህወሓት ወስላታነት እንዳለ ሆኖ)። ይህ ከህወሓት ጋር የተደረገው ስምምነት ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ ከዋለ፣ የሚቀጥለው ትልቁ ትግል ከሙስና እና ከሙሰኞች ጋር ነው።

እውነቱን ለመናገር ከሙስና ጋር የሚደረገው ትግል ከባለሥልጣኖች ጋር የሚደረግ ትግል ነው፣ ከሌቦች ጋር ሌብነትን መዋጋት ደግሞ እጅግ በጣም ከባድ ነው። ይህ ማለት ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ ከሙስና፣ አይን ካወጣ የመንግስት ባለስልጣኖች ዝርፊያና “ከወፈሩ ሰው አይፈሩ” ቱጃሮች ዕብሪት ጋር የምታደርገው ጦርነት በጣም ከባድ፣ውስብስብና ብዙ ግዜ የሚፈጅ ነው። የማይጠረቁ ሌቦችን ታዝለን ልማት ማለት ጥፋት ማለት ነውና፣ ፊታችንን ወደዚህ ከሙስና ጋር ወደሚደረገው ጦርነት ማዞር ግዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው።

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop