በኢትዮጵያ መንግስትና በአሸባሪው የትግራይ ቡድን (ከስምምነቱ በኋላ አሸባሪ የሚለው መጠሪያ መነሳት አለመነሳቱን ሳልረዳ በማንሳቴ ይቅርታ ይደረግልኝ) ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተጀመረው ጦርነት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በሰላም ንግግር እንዲፈታ በሁለቱም ወገኖች በተመረጡ ተወካዮች በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ባደረጉት የሰላም ንግግር ሕወሓት ትጥቅ እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሳቸውን አጣጥመን ሳንጨርስ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት ቡድን መካከል ያለውን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም ይረዳል ዘንድ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በምዕራብ ግንባር ማይፀብሪ ወረዳ 250 የሚሆኑ የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ለመፍታት መስማማታቸውንና ለወረዳው አስተዳደር ጥያቄ ከማቅረባቸው ባለፈ ወደ ጊዜያዊ ካምፕ እንደገቡ ሰምተናል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ወታደራዊ አመራሮች በአምስት ቀን ውስጥ እንዲገኙ ያዛል በተባለው መሠረትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የትግራይ ታጣቂ አዛዦች ባሳለፍነው ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በኬንያ ናይሮቢ እንደተገናኙና የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ውይይት እያደረጉ ባሉበት ወቅት ሰሞኑን በአማራ ክልል በመንግስት ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የአንደኛው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተከትሎ የመንግስት ሠራተኛው መንግስትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከስምምነቱ ያተረፉትን ትርፍ በሚመለከት የመወያያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡ በፀሐፊው የግል አስተያየት የሰላም ስምምነቱ እሰየው የሚያስብል ጅማሬ ቢሆንም ሕዝብ ስለ ሂደቱ በግልጽ ሳያውቅ ስምምነቱ ከፀደቀ በኋላ ለውይይት መቅረቡ ከደረት ድቂ ያለፈ ትውስታ እንደሌለውና ለስሟ መጠሪያ ቁና እንደሰፋችው እንደ አዲስ ጎጆ ወጪ ልጃገረድ የሚፈይደው እንደሌለ እየታወቀ በአጀንዳ መልክ ከመቅረቡ በላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት መርተውና ከ1.5 ትሪሊዮን በላይ የሚገመት መሰረተ ልማት አውድመው አሸነፍን ብለው የተመለሱት የኢትዮጵያ መንግስት ተደራዳሪዎች የአበባ ጉንጉን በአንገታቸው ሲጠልቅላቸው ማየት እንዴት ያማል! አሁንም የበልጽግና ፓርቲ አመራሮች ያልተሻገሩት ድልድይ እንዳለ ያመለክታል፡፡
ቦግ እልም፣ ፈካ ጭልም የሚለው የሰላም ስምምነቱ ከትግራዮች መንደር እየወጡ ያሉ መረጃዎች የኢትዮጵያ ሰላም የማግኘት ተስፋ ስጋት ያጠለለበት የመጣ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል እኛን የሚወክሉ አይደሉም ከስምምነቱ መንደር የተቀመጡት ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ ትጥቅ ለመፍታት በትግራይ ክልል የታጠቁ የውጭ ሠራዊት ክልሉን ለቀው ካልወጡ ትጥቅ አንፈታም የሚል የአሻፈረኝ ዕንደምታ ያለው አጉራ ዘለል ንግግር ማድረጋቸው እየታወቀ ለአማራ ክልል የመንግስት ሠራተኛ መወያያ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ምን ለማትረፍ ታስቦ ይሆን?
በድርድሩ ያልተወከሉና ተቋም በመምራት ብቻ የማወያየት ስልጣን የተሠጣቸው የአማራ ክልል አመራሮች ዓይናቸው በጨው ታጥበው ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል የስልጣን ጥማት ተጠናውቷቸው “ኢትዮጵያ አሸንፋለች” እያሉ ደጋግሞ በመናገር የወር ደመወዝተኛውን ሠራተኛውን ለማሳመን ከመጣር ይልቅ ለዘመናት የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የነበረውንና በጦርነት ቀጠና ያሉ የራያና የወልቃይት አካባቢ አካባቢዎች ከስምምነቱ በኋላ እንዴት እንደሚመለሱ ግልጽ ማብራሪያ አለመሰጠቱ ዛሬም ባሳለፍነው የኢህአዴግ ጎዳና እየተጓዝን እንደሆነ አካሄዳችን ያሳብቃል፡፡
ተወዳጁ የጥቁሮች መብት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ በአንድ ወቅት “እሚሞትለት ዓላማ የሌለው ሰው ለመኖር ብቁ አይደለም” ሲል የተናገረው ከዚህ ላይ ለማንሳት ተገድጃለሁ፡፡ የትህነግ ነገር ግራ አጋቢ ነው፡፡ ጉምቱ መሪዎቹ ጌታቸው ረዳና ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ በተገኙበት የተፈረመን የሰላም ስምምነት አናውቀውም ለማለት የከጀላቸወ ከምን መነሻ ነው? የፈረሙት ፊርማ ሳይደርቅ የክህደት ሊቁ ትህነግ ክህደቱን በገሃድ አሳውቋል። ትህነግን ማመን ቀብሮ ነው የምንለው በምክንያት ነው።
አሁንም ትህነግ የሰላም ስምምነት ያደረገው ጊዜ ለመግዛት በሰብአዊ ዕርዳታ ስም ቀለብ ለማግኘት እንጂ ሰላሙን ከአንጀቱ እንዳልተቀበለው በሥሩ በሚተዳደሩ ሚዲያዎች እያላዘኑ ነው። እኛ ታዲያ በምን ተዳችን ነው ለተለዩ ወጎኖቻችን፣ ለማይተገበር የስምምነት ሰነድ ሰርክ ደረት የምንደቃው፡፡ ደረት አልባ ከሆን ድፍን ሦስት ዓመታትን አስቆጥረናል፡፡ ደረታችን ከጀርባችን ጋር ተጣብቆ እያያችሁ ኑ ደረት ድቁ ማለት በከበሮው ቀን እንደማትፈልጉን ያመላክታል፡፡ ከበሮ ቀንማ ዘላዩ ብዙ ነው፡፡ ያም አለ ያም አለ አንዘናጋ ትህነግ ዕድሜ ልኩን ችግሮችን በሰላም የፈታበት ታሪክ የለም። በማታለልና በማዘናጋት ተቀናቃኞቹን በማጥፋት እንጂ። የትህነግ ነገር አሁንም ጥንቃቄ ያሻዋል። የአማራ ክልል አመራሮች የወልቃይት ጠገዴና ራያ ጉዳይ በሕገ መንግስቱ የሚፈታ ሳይሆን ከሕገ መንግስቱ በላይ በሆነ ፖለቲካዊ ውይይት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና ማስረጃዎች ብቻ እንደሚፈታ ለዘመናት ሲናገር ሕይወቱ ያለፈው ነፍሱን በአፀደ ገነት ያኑረውና የዶ/ር አምባቸው መኮንን ቃል ዘንግተው ለመንግስት ሠራተኛው አጀንዳ መዘርጋታቸው ዕርም እንደመብላት ይቆጠራል ባይ ነኝ፡፡