ሰላም ጦርነትን ሲያሸንፍ፣ የደቡብ አፍሪካው ስምምነት፣ ይዘቱ፣ ተፈጻሚነቱና ተግዳሮቶቹ – ባይሳ ዋቅ-ወያ

Kenyan President Uhuru Kenyatta (L), Redwan Hussein (2nd L), Representative of the Ethiopian government, African Union Horn of Africa envoy and former Nigerian president Olusegun Obasanjo (2nd R) and and Getachew Reda (R), Representative of the Tigray People’s Liberation Front (TPLF), look on after the signing of a peace agreement during a press conference regarding the African Union-led negotiations to resolve conflict in Ethiopia at the Department of International Relations and Cooperation (DIRCO) offices in Pretoria on November 2, 2022. (Photo by PHILL MAGAKOE / AFP)

ከሁለት ዓመት አውዳሚ ጦርነት በኋላ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በደቡብ አፍሪካ ተገናኝተው ለአሥር ቀናት ያህል ከተደራደሩ በኋላ አንዳች አመርቂ ስምምነት ላይ መድረሳቸው መላውን ሰላም ወዳድ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስደስቷል። ተፋላሚዎቹ ለድርድር እንዲቀመጡ ያስገደዳቸው ምክንያት ግልጽ ቢሆንም፣ መጨረሻ ላይ እንደዚህ በአንድ ሳምንት ውስጥ ልዩነታቸውን አቻችለው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ላይቀር፣ ገና ከመጀመርያው ይህ ሁሉ ጥፋት ሳይደርስ ለምን ሁለቱ ብቻ ያለ ውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት በሚግባቡበት ቋንቋ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ተነጋግረው ችግራቸውን በሰላም ለመፍታት አልቻሉም የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ወደ ጎን እንተውና፣ ስምምነት ላይ ለመድረስ የፈጀባቸው ጊዜ እጅግ በጣም ፈጣን መሆኑ በዘመናዊ የድርድር ታሪክ ውስጥ ክብረ ወሰንን ያስመዘገበ ይመስለኛል። ከዚያ ሁሉ ግድያ፣ መፈናቀልና መጠነ ሰፊ የሆነ የጦርነት ሕግና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አንጻር ሲታይ፣ ተደራድሮ ስምምነት ላይ ለመድረስ የወሰደባቸው ጊዜ ቅጽበታዊ ነበር ማለት ይቻላል። የራሱ የሆነ ምክንያት ግን ነበረው።

ያለመታደል ሆኖ አለመግባባትን “ጠላትን” በማሸነፍና በማስገበር ብቻ ማጠናቀቅ ባሕላችን አድርገን ለዘመናት ስለ ተላመድነው፣ ይህን ሁለቱም ተፋላሚ አካላት በእኩልነት ደረጃ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ተደራድረው የደረሱበት ስምምነት ለአንዳንዶቻን አልተመቸንም። አይፈረድብንም። የቆየ ልማድ በቀላሉ አይለቅም ይላል ፈረንጅ። በኔ ግምት የዚህ ድርድር ሂደትና ተከታይ ስምምነት ታላቅነት፣ በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ በሪኮርድ ጊዜ መጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን በታሪካችን ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ተፋላሚ አካላት በእኩልነት ደረጃ በአንድ ጣራ ሥር ቁጭ ብለው ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መቻላቸው ነው። የሚቀጥለው ትውልድ ካሁን በኋላ አለመግባባትን በሰላም ተወያይቶ የመፍታትን ዘዴ ፍለጋ ባሕር ማዶ መሄድ የለበትም ማለት ነው። መቼም ምኞት አይከለከልም!

በሰሜኑ የአገራችን ሰማይ ላይ አንድም ጥይት ሳይተኮስ መዋሉ፣ አዛውንትና ሕጻናት ከተደበቁበት ጉራንጉር ወጥተው በቂ ምግብ ባይኖርም የሰላም አየርን ብቻ ተንፍሰው የነገን ብሩህነት በተስፋ እያዩ መዋል፣ እንደኔ ጦርነትን በቅርብ ሲከታተል ለኖረ ግለ ሰብ ይቅርና ጦርነትን በወሬ ብቻ ለሚያውቅም ሰው ታላቅ የደስታ ቀን ነበር። ጦርነትን በቃላት ማስረዳት የማይቻል እጅግ በጣም አጥፊ የሆነና እግዚአብሔር የተቆጣን ቀን የጣለብን፣ ግን ደግሞ ልንገላገለው ያልቻልን ታላቅ የማኅበረሰብ ሸክም ነው። ጦርነት ማለት፣ አንድ ስሙን የማላስታውሰው ምሑር እንዳለው፣ በሚተዋወቁና በሚጠላሉ፣ ግን ደግሞ በማይገዳደሉና በጦርነቱ መጨረሻም ላይ እጅ ተጨባብጠው በሰላም በሚለያዩ ታላላቆች (አንጋፋዎች) ውሳኔ ምክንያት፣ የማይተዋወቁና የማይጠላሉ ወጣቶች የሚገዳደሉበት ክስተት ነው። አዎ! ወንድማማችና እህትማማች ቢሆኑም ተገናኝተው የማያውቁ የኢትዮጵያ ልጆች ጥቂት የፖሊቲካ ኤሊቶች በቀደዱላቸው የክፋት ቦይ ፈስሰው የተገዳደሉበት ጦርነት ነበርና፣ ጦርነቱን ያወጁት ራሳቸው በፈቀዱበት ሰዓት ለማቆም ተስማምተው እጅ ተጨባብጠው ሲለያዩ፣ የኢትዮጵያ ወጣት በጥይት ከመጋየት በሰላም ወደ ወታደራዊ ካምፕ ወይም ወደ ቤቱ መመለሱን በኅሊናም ቢሆን ከማሰብ የላቀ ደስታን የሚፈጥር ነገር ያለ አይመስለኝም።

የስምምነቱ ሰነድ ገና ለገበያ እንደ ቀረበ ብዙ ኢትዮጵያውያን የተደሰቱትን ያህል ያኮረፉም ነበሩ። የተደሰቱትም ያኮረፉትም የየራሳቸው ምክንያት ነበራቸው። ለተደሰቱት ወገኖች፣ (እኔንም ጨምሮ)፣ ዋናው ምክንያታቸው ሰላም መስፈኑ ሲሆን አኩራፊዎቹ ግን “ሕወሃት እጁን ሰጠ፣ የትግራይ ወጣቶች ያለቁት ለዚህ ነው ወይ?” “በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታል” ያሏቸው ጉዳዮች ሆን ተብሎ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው ወዘተ አሉ። የተደራዳሪ ወገኖች ባለሥልጣናትም በአሸናፊነት እንደወጡ በየፊናቸው ለደጋፊዎቻቸው በአደባባይ ዓውጀው አስደሰቷቸው። አዎ ሁለቱም ወገን “አሸንፈዋል”። ምክንያቱም ድርድር ማለት ሰጥቶ መቀበል ነውና! እንደኔ እንደኔ ግን ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ይበልጥ በርግጠኝነት መቶ በመቶ ያሸነፈው ሰላም ነው። ሰላም ጦርነትን አሸንፎ በአደባባይ የፎከረበት ቀን ነበርና! ሁለቱ አካላት እንዴት እኩል “አሸናፊ” ሆኑ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ፣ መጀመርያውኑ ወደዚህ አውዳሚ ጦርነት የገፋፋቸው ምክንያት ምን ነበር የሚለውን መሠረታዊ ጉዳይ ማወቅ ያፈልጋል። ይኸንን ዋነኛ ምክንያት ካወቅን በኋላ በድርድሩ ሂደት ውስጥ እያንዳንዳቸው “የተቀበሉትን” ከዋነኛው ጥያቄያቸው ጋር አመሳክረን እውነትም “አሸንፈዋል” ብለን መደምደም እንችላለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብን ብሎ የጠፋው የአብን አመራር ከወዴት ተገኘ?

 

ያኔ ልብ አላልንም ወይም የጦርነት ፕሮፓጋንዳ መስሎን አልፈነው ይሆናል እንጂ፣ ሁለታቸውም ከመጀመርያውኑ ወደ ጦርነቱ ለመግባት የገፋፋቸው ምክንያት፣ የሌላኛው ወገን ሕገ መንግሥቱን የመጣስ ጉዳይ እንደ ነበር መላልሰው ነግረውን ነበር። አቦይ ሥዩም በትግራይ ሚዲያ ላይ በአደባባይ ቀርበው፣ የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጪ የራሱን የሥልጣን ዕድሜ ስላራዘመ በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ዘንድ ቅቡልነት (legitimacy) የለውም ሲል፣ የፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሶ ያለ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ የራሱን ምርጫ አካሄደ፣ ከፌዴራል ፓርላማም ራሱን አገለለ፣ ይባስ ብሎም ሕገ መንግሥቱን ጥሶ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ወንጀል ፈጸመ ብለውን ነበር። የሁለቱም ክስና ወደ ጦርነቱ የገፋፋቸው ዋናው ምክንያት “የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ መጣስ” ከሆነ፣ ዛሬ አለመግባባቶቻቸውን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ለመፍታት መስማማታቸው፣ በርግጥም ሁለቱም ወገን ለዋነኛ ጥያቄያቸው ተገቢ መልስ አግኝተዋልና፣ በፖሊቲካ ቋንቋ አሸናፊ ነበሩ ብሎ መደምደም ትክክል ነው።

ስምምነቱን የሚቃወሙት ወገኖች ከሚያነሷቸው ክፍተቶች ዋነኛው ሁለት ዓመት በፈጀው ግጭት ወቅት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብትና የጦርነት ሕግን የጣሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ተጠያቂነት ጉዳይ በስምምነቱ ውስጥ በግልጽ አልተቀመጠም የሚለው ነው። ይህ በርግጥ አሳሳቢ ነው። ጉዳዩ፣ በስምምነቱ ውስጡ በአንዱ አንቀጽ ሥር የተወሸቀ ቢሆንም፣ ከጠፉት ነፍሳትና ከወደመው ንብረት አንጻር ሲታይ በዚህ ወንጀል የሚጠረጠሩትን ግለሰቦችና ቡድኖች ለፍርድ ለማቅረብ የተስማሙበትን ጭብጥ በግልጽና በዝርዝር  አለማስቀመጣቸው በርግጥም ያሳስባል። ሆኖም ግን፣ ሁለት ተጓዳኝ ነጥቦችን መጥቀሱ ቅሬታን ለሚያሰሙ ወገኖች ማረጋጊያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ሀ) እነዚህ ሁለት ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት “የይርጋ ዘመን”የላቸውም። ይህም ማለት፣ ወንጀል ፈጻሚዎቹ በዚች ምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ እንኳን ከኢትዮጵያ ውስጥ ይቅርና ከየትም የዓለም ዳርቻ ተይዘው በዚህ ወንጀል ተከስሰው ለፍርድ ሊቀርቡ ይችላሉ።

ለ) በዚህ ወንጀል የሚጠረጠሩትን ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ለፍርድ የማቅረብ መብቱ የማንም የሰው ልጅ ነው። ይህም ማለት ማንም የሰው ልጅ፣ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን የማንም አገር ዜጋ እንዲሁም በየትኛው አገር ያለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ በቂ መረጃና ማስረጃ እስካለው ድረስ በዚህ ወንጀል በተጠረጠሩት ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ ይችላል። ስለዚህ ምንም እንኳ በዚህ ስምምነት ውስጥ ጥልቅና ተገብ ትኩረት ባይሠጠውም፣ ከሳሽ አይጥፋ እንጂ፣ ወንጀለኞቹ ከምድራዊው ፍርድ የሚያመልጡበት አንዳችም አጋጣሚ አይኖርም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሒሣብ ማወራረድ የሚወራውን ያህል ቀላል አይደለም - ምሕረት ዘገዬ

ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ መሰናክሎች ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ። ሶስቱን ብቻ ለመጥቀስ ያህል።

1) የአንዳንዶቻችን ቅሬታ “በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታሉ” ተብለው በስምምነቱ ውስጥ ስለተካተቱ ጉዳዮች መሆኑ በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ከምንሰማውና ከምናየው የምንረዳው ነው። በኔ ግምት ተመሳሳይ ችግሮችን ለመፍታት ያለው ምርጫ ሁለት ብቻ ነው፣ ሰላማዊ ውይይት ወይም ጦርነት። ጦርነትን ሞክረን ስላላዋጣን የሚቀረን ብቸኛ ምርጫ ውይይት ነው ባይ ነኝ። ጠብመንጃን ከፖሊቲካ መድረክ ካወጣንና በቅንነት ከተወያየን የማንፈታው ችግር በጭራሽ አይኖርም። በአገሪቷ የሕግ የበላይነት ይስፈን ብለን ስንጮህ የነበረው እኮ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥቱ ይከበር ማለታችን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ደጋግሜ እንዳልኩትም ሕገ መንግሥቱ ፍጹማዊ ነው የሚል ዕብደት አይከጅለኝም። ሕገ መንግሥቱ እንደ ማንኛውም የአገሪቷ ሕጋዊ ሰነዶች በሕዝቦች ፈቃድ ሊሻሻል ወይም ሊሻር የሚችል ነገር ነው። በተረፈ ግን፣ ይኸኛው ብቻ ሳይሆን ከዚህም በፊት የነበሩት አምስት ተከታታይ ሕገ መንግሥቶቻችን በወቅቱ የነበሩ ገዢዎቻችን አርቅቀውና አጽድቀው “ለሕዝባችን የተሠጡ” እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያልተካፈለበት ስለሆነ ዛሬ ላይ የአንዳንዶች በማርቀቁም ሆነ በማጽደቁም ሂደት ላይ “የኛ ብሔር ስላልተሳተፈበት” ሕገ መንግሥቱ በኛ ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም ማለት ለሰላሙ ሂደት እንቅፋት እንጂ አንዳችም አዎንታዊ አስተዋጽዎ ያለው አይመስለኝም።

2) የትግራይ መከላከያ ሠራዊትን ትጥቅ ማስፈታት ጉዳይ ሌላው አስቸጋሪ ነገር ነው። ከልምድ እንዳየሁት፣ ከርስ በርስ ግጭት በኋላ ትልቁ ብሔራዊ ችግር ታጣቂ ኃይልን (በተለይም ወጣቱን) ከጠመንጃ ማላቀቅና ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ ነው። የቤተሰብ ኃላፊነት ያለበት ታጣቂ የጦርነቱን ማለቅ በደስታ ይቀበላል። የሚሄድበትና የሚጠብቀው  የቤተሰብ ኃላፊነት አለበትና! ወጣት ግን አንዴ ከጠመንጃ ጋር ከተላመደ ማላቀቁ እጅግ በጣም አታካች ነው። ለወጣት ልጅ ጠብመንጃ ማለት፣ የመኖር ዋስትና፣ የራሱን መብት የሚያስከብርበት፣ ሲያስፈልግ አድኖ አልያም ዘርፎ የሚበላበት፣ ቀንም ሌትም የማይለየው ታማኝ ወዳጅ ነው። በመሆኑም፣ ወጣትን ከጠብመንጃ ለማላቀቅ ከተፈለገ መንግሥት ይህን ሁሉ ማሟላት አለበት ማለት ነው። መንግሥት፣ ምግብና መኖርያ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ሕይወቱም ብሩኅ ተስፋን ጭምር ማቅረብ አለበት። ዛሬ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው የተማረ ወጣት ሥራ መፍጠር ያልቻለ መንግሥት እንዴት አድርጎ ለነዚህ ትጥቃቸውን ለሚፈቱ የትግራይ ተዋጊዎች መተዳደርያ የማዘጋጀቱ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው።

3) አወዛጋቢ ጉዳዮቹ በሙሉ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሰላም ቢያልቁ እንኳ፣ በሁለት ዓመት የጦርነት ሂደት ውስጥ የተደማማውንና የተቆሳሰለውን የትግራይና የሌላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለርስ በርስ ያላቸውን አመለካከትና ማኅበራዊ ትስስሩን ወደ ቅድመ ጦርነት ሁኔታ ለመመለስ እጅግ በጣም አታካች ሥራ ነው። ካለፈው ልምዴ እንደ ተገነዘብኩት፣ የርስ በርስ ጦርነትን የውጪ ወራሪን ለመመከት ከሚደረገው ጦርነት ልዩ የሚያደርገው፣

ሀ) የውጪ ወራሪን ለመከላከል የሚደረገው ጦርነት በአብዛኛው ጊዜ የሚካሄደው በድንበር አካባቢ ስለሆነ ሰላማዊ ዜጎችን ከቦታው ገለል ለማድረግ ስለሚቻል፣ በጦርነቱ ሂደት  ስጥ የሚጎዳው ሰላማዊ ሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ይሆናል።

ለ) በውጪ ወረራ ጊዜ፣ ጦርነቱ ከሞላ ጎደል የሚካሄደው በሁለቱ ወገን መከላከያ ሠራዊት ብቻ ስለሚሆን፣ የሁለቱ ወገን ሰላማዊ ሕዝቦች በጦርነቱ ሂደት ውስጥ የሚገናኙበትና  ሚቆሳሰሉበት ዕድል በጣም የጠበበ ነው። በየርስ በየርስ በርስ ጦርነት ወቅት ግን የሁለቱም ተዋጊ ኃይልና ሕዝቡም አንድ አካባቢ ስለሆኑ የግጭቱ ሰለባ የሚሆነው ሰላማዊ ሕዝብ ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የመቆሳሰሉ ደረጃም እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ እና ዶ/ር በያን ሱባ -በገበየሁ ባልቻ

ሐ) ስለሆነም፣ የውጪ ወራሪ አንዴ ተሸንፎ ከተባረረ በኋላ በሁለት አገር ሕዝቦች መካከል ሰላምን ለመፍጠር ብዙ ጊዜ አይፈጅም። ከሰላም ስምምነቱም በኋላ በሁለቱ ሕዝቦችም መካከል ዘላቂ ጥላቻ አይኖርም። ከየርስ በርስ ጦርነት በኋላ ግን ሁለቱም ወገኖች የአንድ አገር ሕዝብ ስለሆኑና በመሪዎች መካከል ስምምነት እንኳ ከተደረሰ በኋላ እዚያው በቅድመ ጦርነቱ ወቅት ይኖሩ እነበሩበት አካባቢ ስለሚቀሩና፣ በጦርነቱ ሂደት ውስጥ የቤተሰብ አባል፣ ዘመድ ወይም ጓደኛቸውን ከገደለባቸው የሌላ ወገን ታጣቂ ጋር አብረው በየ ድሩ፣ ሰንበቴውና ቅዳሴ ላይ ዘወትር ስለሚገናኙ፣ የጦርነቱን ጠባሳ በቀላሉ ረስተው “ከዘመዳቸው ገዳይ” ጋር በሰላም ለመኖር እጅግ በጣም ከባድ ነው። ሶስት ዓመት የፈጀው የዩጎዝላቪያ ጦርነት በስምምነት ካለቀ ከኸያ ሰባት ዓመት በኋላ፣ ዛሬ ሴርቦች፣ ክሮአቶችና ቦስኒያኮች እንደ ዘይትና ውሃ ጎን ለጎን ይኖራሉ እንጂ ለዘመናት የነበራቸውን ማኅበራዊ ትስስር መልሰው ሊጠግኑ አልቻሉም።

 

ምን ይጠበቅብናል?

ከላይ በአጭሩ እንዳስቀመጥኩት፣ ስምምነቱን በተግባር የመተርጎሙ የቤት ሥራ እጅግ አድካሚ እንደሚሆን ከወዲሁ ይታየኛል። የድርድሩን ሂደትና ከስምምነቱ በስተ ጀርባ የነበረውን እሰጥ አገባ ከቅርብ ሆነን ባንከታተለውም፣ ስምምነቱ በቅንነት ላይ የተመሠረተ ውይይት ውጤት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ሁለቱ አካላት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ቆመው በአደባባይ የገቡትን ቃል ያጥፋሉ የሚል ጥርጣሬም የለኝም። ከሱ በላይ እኔን እጅግ በጣም የሚያሳስበኝ ሌላ ጉዳይ አለ። እሱም የአገሪቷ ፖሊቲካ ድርጅቶች፣ የፖሊቲካ ኤሊቶችና የአክቲቪስቶቻችን እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት፣ በስምምነቱ ላይ ያላቸው አቋምና ስምምነቱ እንደ ታቀደለት እንዲተረጎም መጫወት ስላለባቸው ሚና ነው። በኔ ግምት፣ ሚናችን መሆን ያለበት፣ ተፋላሚ ወገኖቹ በታሪካችን ባልተለመደ መልኩ ግጭትን በሰላም ለመፍታት መስማማታቸውን በደስታ ተቀብለን ስምምነቱ በታለመለት መንገድ ተፈጻሚ እንዲሆን ሊኖረን በሚገባ አስተዋጽዖዎች ላይ መወያየት ዝግጁ መሆን ነው። መንግሥትና ሕወሃት በራሳቸው ተነሳሽነትም ሆነ በሌላ ምክንያት የሚጠበቅባቸውን ታሪካዊ ሚናቸውን ተጫውተዋል። እኛም በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር ያለን ኢትዮጵያውያን የዚህን ታሪካዊ ስምምነት ቃልና መንፈስ በተግባር ለመተርጎም እንዲረዳ በየሙያችን ተሠልፈን የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ። ሁለቱ አካላት ጦርነቱን ሲጀምሩ ባያማክሩንም፣ በጦርነቱ ሂደት እጅግ በጣም የተጎዳው ሰላማዊ ሕዝብ ነውና፣ የዚህን ሕዝብ የተጣሱትን የግልና የቡድን መብቶችን መልሶ ለማስከበርና በአገራችን ከዳር እስከ ዳር ሰላምና መረጋጋት እንዲሠፍን በጋራ እንትጋ!

ለሚዲያ ተቋማት ደግሞ የተለየ መልዕክት አለኝ፣ አብዛኞቻችሁ ሊገባን በማይችል ምክንያት ነጋም ጠባም በሕዝቦች መካከል የምትረጩትን የጥላቻ መልዕክት ተውና በስምምነቱ አወንታዊ ጎን ላይ ለማተኮር ሞክሩ። እያንዳንዷ የምትተፏት አሉታዊ ዓረፍተ ነገር ከአንድ የመድፍ ጥይት በላይ ውድመት ሊያደርስ ስለሚችል፣ በተቻላችሁ መጠን የስምምነቱን “ግማሽ ብርጭቆ ሙላት” አውሩ። ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ የሕዝቡን ፍላጎት አሟልቷል ማለቴ እንዳልሆነ ይገባችኋል። ግን ደግሞ፣ ከዚህ እጅግ በጣም አውዳሚ ከነበረው ጦርነት በኋላ ይህን መሰል ስምምነት ላይ መድረሳቸው በራሱ ትልቅ ድል ነውና፣ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ባለ ሙያዎች የሚወያዩበትን መድረክ ፍጠሩ። አምላክ ቅንነቱን ያብዛላችሁ።

******

ጄኔቫ፣ ኖቬምበር 8 ቀን 2022 /

wakwoya2016@gmail.com

 

1 Comment

  1. ባይሳ ሌሎች መልስ ሊሰጡህ ቢቸሉም አንድ የጠቀስከውን መዝዤ ጥያቄ ብጠይቅ ደስ ይለኛል፡፡ ብዙዎቻችሁ ትላንት የተደረገውን ጠቅላላ ረስታችሁ መንግስት አገኝሁት ባለው ድል ስትደልቁ አመለከታለሁ፡፡ ድርድር የማይፈታው የለም ብለሃል ድርድር የሚደረገው በሁለት ተደራዳሪ አካላት እውነትን ተንተርሰው ታሪክ አጣቅሰው፤አሃዝ መዝነው ነው፡፡ ይህ አካል ከስልጣን ከተባረረ በኋላ ያደቀቀው ክልል የአማራንና የ አፋርን ነው ለዚህም ምክንያቱ ሁለቱን ክልሎች ለማጠቃለል ከአረጋዊ በርሄ ዘመን ጀምሮ በፕሮግራም የያዘው በመሆኑና ስልጣንም በነበረበት ጊዜ በተገበረው ንድፉ ነው፡፡ ህወአትን ስታውቀው ምን ጊዜ ነው በምክንያታዊ ድርድር አምኖ ድርድሩን ተግባራዊ ያደረገው፡፡ ምርጫ 97 ህዝቡ አባረረው ሞኝህን ፈልግ ብሎ ስልጣን ላይ በድጋሚ ፊጥጥ አለ፡፡ ከኤርትራ ጋር እደራደራለሁ አለ ሞኝህን ፈልግ ብሎ ኢሳይያስ አፈወርቅን አየር ላይ አስቀረው፡፡ ወዳጄ በዚህ በህወአት ወርራ መከራውን ያየ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ የወደመበት የአማራ ክልል በጠላቶቹ ተወክሎ ያየኸውን ስምምነት ተፈርሟል ፎቶህን እንዳየሁት ትላንት የተወልድክ አይደለህም ነገሮችን ማገናዘብ የሚገባህ ጎልማሳ ነህ ግፍን ለማውገዝ እውነትን ለመቀበል ተዘጋጁ እንጅ፡፡ ለኢትዮጵያ የምታስቡ ከሆነ መከላከያውን አስቡት እንጅ ኢትዮጵያን የሚጠበቅ ሃይል መከላከያው ነው በተኛበት የታረደው በባዶ እግሩ የተሰደደው መኪና የተነዳበት በቅርቡ ደግሞ አንድ ሴት እህታችንን የመከላከያ ሰራዊት እንዴት እንዳወርዷት እንደደበድቧት ሳትመለክት አልቀረህም፡፡ እዚህ አንድ ጎረቤቴ ያለውን መንግስት ደጋፊ ታከለ ኡማ ለአዲስ አበባ ተማሪዎች ምሳ በነጻ አቀረበ ብሎ የሱን ገድል ሊነግረኝ ይፈልጋል ታከለ ኡማ ከደመወዙ ሳይሆን ከአባቶቻቸው ከተሰበሰበው ግብር ነው ያበላቸው ያንሳቸው እንደሆን እንጂ አይበዛባቸውም ታከለ ኡማ የሰራውን ጥፋት የኢትዮጵያ ጊዜ ሲመጣ የሚወጣ ነው፡፡ ሌላው የዚህ መንግስት አራጋቢና አናፋሽ ጋዜጠኞች የሚጽፉትን ዝባዝንኬ ነው “ለመጀመሪያ ጊዜ ፈተና ሳይሰረቅ ተፈተኑ” ይለኛል ጎበዝ ይህ ዜና ነውን? ፈተናስ መሰረቅ አለበት ወይ ሲጀመር፡፡ ስለዚህ ያለውን መንግስት ደገፍን ብለን ት ዝብት ውስጥ አንውደቅ ያለውን መንግስት ለማጠናከር ስህተቱን ነቅሶ እርምት እንዲያደርግ ነው የሚበጀው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው የኢትዮጵያ ኤታማዦር ሹም በአንድ ክልል ወምበዴ መሪ ፊትለፊት ተሸማቅቆ ሲቀርብ ያሳዝናል ሬድዋን ሁሴን እንኳን ውርደትን ለምዶታል፡፡ ስለዚህ እናውቃለን የምትሉ ለፓርቲያችሁ ለነገዳችሁ ባገኛችኋት ሽራፊ ጥቅም ሳይሆን ለሃገር ክብር ቁሙ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share