ህይወት፤ ሰላምና ዕድገት – በቀለ ገሠሠ

1ኛ/ መንደርደሪያ፤

በመጀመሪያ የሰዉ ህይወት ዉድና ቅዱስ መሆኑን አንርሳ። ህይወት በግፍ እየተቀጠፈ ሰላም አይኖርም። ሰላም ከሌለ ዕድገት አይታሰብም። መሞት፤ መፈናቀል፤ መሰደድ፤ ልመናና ሰቆቃ ብቻ ይሆናል ዕጣ ፈንታችን፤ ከሆነም እጅግ ሰንብቷል። አገራችን ሰፊ ሆና ሳለች አላስፈላጊ ችግሮችን ስንጋብዝ ምንኛ ግብዞች ነን? ትልቁ ኃጢያት ታሪክን ማዛባት ነዉ። የዉሸት ትርክቶች ለከባድ ጥቃቶች ጋርደዉናል። ሳናዉቅ ራሳችንን እያጠፋን እንገኛለን። እንንቃ፤  ሁላችንም እንደሰዉ እናስብበት፤ ህይወት አጭር ናት፤ ታሪክ ይታዘበናል፤ ንስሐ እንግባ፤ እንተቃቀፍ፤ እንተባበር፤ ሙሉ ትኩረት ለሰላም፤ ለልማትና ለዕድገት እንስጥ። በተለይ የኃይማኖት መሪዎች፤ የሀገር ሺማግሌዎች፤ ምሁራን፤ ወጣቶችና ሀገር መሪዎች በጥልቀት አስቡበትና የመፍትሔ አካል ሁኑ። እነዚህን ችግሮችና የሚታዩኝን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለዉ ሳቀርብ በጥሞና እንድትመለከቱልኝና ገንቢ ሚና እንድትጫወቱ በፈጣሪያችን ስም እለምናችኋለሁ።

 

2ኛ/ ለሰዉ ህይወት ክብር ይኑረን

ራሳችሁን፤ ወገኖቻችሁንና ጓደኞቻችሁን እንደምትወዱ ሌሎችም እንደዚሁ አፍቃሪዎች አሏቸዉ። የአንዱ ህይወት ከሌላዉ ፈጽሞ አይበልጥም፤ አያንስም። በእግዚአብሔር ለምናምን ሁሉ እርሱ በአምሳሉ የፈጠረን ህዝቦች ነን። የማሰብ አእምሮ ሰጥቶናል። ክፉና ደጉን እንድንለይ አብቅቶናል። ግን የዜጋ ደም በከንቱ እየፈሰሰ ይገኛል። ቅዱስ ሕይወት በገፍ እየጠፋ ይገኛል። ከዋናዎቹ ሕግጋት መካከል ‘አትግደል’ ይላል፤ ‘ባልንጄራህን ከራስህ አስበልጠህ ዉደድ ይላል’። ዛሬ ግን ሰዉ እንደቅጠል በግፍ እየረገፈ ይገኛል። እንደዚህ ዓይነቱ ዝርፊያ፤ ማፈናቀልና መግደል ከዬት የመጣ ነዉ? ሕግና ሥርዓት በሚከበሩባቸዉ ሀገራት ዉሾችና ድመቶች እንኳ መብት አላቸዉ። የአስተዳደሮች ብልሹነት እንደሆነ እንጂ በጭቁኑ ህዝባችን መካከል ጠላትነት አልነበረም። ይሄ አማራ፤ ይሄ ኦሮሞ፤ ይሄ ትግሬ፤ ወዘተ የሚለዉ ክፍፍል በቅርቡ የተፈጠረ የከፋፍሎ መግዣ ተንኮልና የዉሸት ትርክት ነዉ። ያለዉን ተካፍሎ ጥሮ ግሮ የሚያድር ብርቱ ህዝብ ነበር። አሁን ከመተላለቃችን በፊት ያንን መልካም ምግባር መልሰን መገንባት ይኖርብናል። መፍትሔ የሚመጣዉ ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል፤ በዜጎች መካከል ጥሩ ጉርብትናና ወዳጅነት ሲኖር፤ ዜጎች በነፃ ተዟዙረዉ የመስፈር፤ የመሥራት፤ የመነገድ፤ ወዘተ መብታቸዉ ሲጠበቅላቸዉ ነዉ። ለብዙ ሺ ዓመታት በሰላም የኖርነዉ በዚያ መልክ ነበርና።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያረጋገጥነው የምግብ ኢ_ዋስትናን (ዋስትና አላልኩም) ነው - ክፍል 5 [የመጨረሻው ክፍል]

 

3ኛ/ ሰላም ሳይኖር ዕድገት አይታሰብም

ሁል ጊዜ ስንደምናገረዉ፤ ቸሩ አምላካችን መርጦ የፈጠራት ሀገር ናት። ሁሉንም አሟልቶ ሰጥቷታል፤ የምድራችን ስፋት፤ የወንዞቻችን፤ የሃይቆቻችንና የጅረቶቻችን ብዛት፤ የህዝባችን ታታሪነት፤ ብርታትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት መሆኑን ስመለከትና ዛሬ የወደቅንበትን ደረጃ ስመለከት እጅግ በጣም አዝናለሁ። ዛሪ በዓለም ላይ ከሁሉም በታች ሆነን በአሳፋሪ ደረጃ ላይ እንገኛለን። በልጅነታችን ስንማርና ለዲሞክራሲ ስንታገል ዉዲቷ ሀገራችንን ከራስዋም አልፋ ለጎረቤት ሀገሮች ጭምር የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ ነበር። ይቻልም ነበር።

ገበሬዉ በሰላም ወጥቶ ካላረሰ መልካም ምርት ከዬት ይመጣል? ነጋዴዉ በነፃ ተንቀሳቅሶ ካልነገደ እንዴት ሊያተርፍ ይችላል? ተማሪ በነፃነት ወጥቶ ጥሩ ትምህርት ካላገኘ ህይወቱ እንዴት ሊሻሻል ይችላል? እስከመቼ ድረስ ይሰደዱ? ይሰቃዩ? ይዋረዱ? አሁን እኮ ያልተበተኑበት ምድር የለም። በመንገድ፤ በበረሃና በባህር ላይ የቀሩትም ብዙ ናቸዉ።

በመፍትሔ ምትክ ችግር መፍጠር ለምን አስፈለገ? በዕድገት ምትክ ዉድመት ለምን ተመረጠ? የዉሸት ትርክትና መርዝ ከመርጨት ሃቆች ለምን አይመሰከሩም? የሕገ መንግሥቱ ከፋፋይ መዘዞች ሀገር ለማፍረስ እንጂ ለመገንባት አይደለም። ጠንካራ አንድነትን ሳይሆን ከዞን ወደክልል፤ ከክልል ወደመገንጠል፤ ወዘተ የሚጋብዝ ሀገር አፍራሽ ነዉ። በዚህ መልክ ከቀጠልን ግድቡ እራሱ ብዙ ዋስትና አይኖረዉም።

 

4ኛ/ ህብረት ከሌለን በዉጪ ታሪካዊ ጠላቶች እንጠቃለን።

የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ፍላጎት በደንብ እናቃለን። በነፃነታችንና በብርታታችን ምክንያት ቂም ከያዙብን በጣም ቆይተዋለል። አፍሪቃን በባርነትና በቅኝ አገዛዝ የበዘበዙ ኃይሎች አይተኙልንም፤ ለምን? አፄ ቴዎድሮች በመቅደላ እጅ አልሰጡም። አፄ ዮሐናስ በመተማ ላይ ህይወታቸዉን ሰዉተዋል። በአፄ ምኒልክ መሪነትና በጠቅላላዉ ህዝባችን ትብብር በአድዋ ላይ አሳፍረናቸዋል። በማይጨዉ ወረራ ዘመን ጎበዝ አርበኞቻችን ለ5 ዓመታት ከባድ ትግል በማድረግና ከባድ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል የዉድ ሀገራችንን ነፃነት አስጠብቀዉልናል። ለአፍሪቃዉያን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መዉጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገናል። ካሪቢያኖች ቀና ብለዉ እንዲሄዱ ኩራት ሰጥተናቸዋል። ትብብር በነበረን ወቅት በእግዚአብሔር ኃይል እነዚያን ድሎች ሁሉ ተጎናጽፈናል። በውስጣችን ስንከፋፈልና ስንባላ ግን ለጥቃት እንዳረጋለን። በ1991 ዓ/ም በለንደን ላይ ስብሰባ ጠሩ፤ መሪዉ ሄርማን ኮህን ነበር። በስብሰባዉ ላይ ኅብረ-ብሄራዊ ፓርቲ እንዲሳተፍ አልተፈቀደም። ለሦስት ቀናት የታሰበዉ ኮንፈረንስ በግማሽ ቀን ተጠናቀቀ፤ ወያኔ ወደ አዲስ አበባ፤ ሸዓቢያ ወደ አስመራ። ይሄንን ያደረጉት ለትግራይና ለኤርትራ ህዝብ በመቆርቆር ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ገንዳው - በእውቀቱ ሥዩም (አሜሪካ እንደመጣ የፃፈው)

ግብፅ እንኳን የኛን ዉሀ እየጠጣችና በኛ አፈር እያመረተች ምስጋና የሚባል ነገር አታዉቅም። እኛ ዉሃና አፈር አልከለከልናት። እርሷ ግን ወንዛችንን ገድበን ከጭለማ እንዳንወጣ ታስፈራራናለች። ሱዳን ከርሷ ጋር በመተባበር ድንበራችንን እየደፈረች ትገኛለች። መፍትሔዉ ዉስጣዊ አንድነትና ሰላም ማስፈን ብቻ ነዉ። በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዉስጥ መሆናችንን ባንዘነጋ መልካም ነዉ። ካለዚያ ታሪክም እግረዚአብሔርም ይፈርዱባቸዋል፤ ልጆቻቸዉም ያፍሩባቸዋል።

ስለዚህ አሁን በሰላም፤ በልማትና በዕድገት ላይ እንድናተኩር አደራ እላችኋለሁ። እግዚአብሔር ይጨመርበት።

 

ዶ/ር በቀለ ገሠሠ (drbekeleg@gmail.com)

1 Comment

  1. ደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር” በተሰኘው የግጥም መጽሃፍ – በ1966 ዓ. ም “ዛሬን እንኳን” በሚለው ግጥሙ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር።
    አለመሳቅ እኮ ይቻላል አለማልቀስ ነው ጭንቁ
    የመንፈስን እንጉርጉሮ በመንፈስ እንባ ማመቁ
    ውስጥ ውስጡን እየደሙ በቀቢጸ ተስፋ መድቀቁ
    ለተስለመለመች እውነት የደም ደብዳቤ ማርቀቁ
    በቅሬት ሰደድ እሳት ህዋሳትን መጨፍለቁ
    አለመሳቅ እኮ ይቻላል አለማልቀስ ነው ጭንቁ።
    ይህ የግጥም ስንኝ ዛሬ ላይ ቆሞ ላየው የጊዜን መስታውትነትና የነገርን ድግግሞሽ የክፋቱ ክርፋትና የሰው ልጅን መከራ ቁልጭ አርጎ ያሳያል። የሃበሻው የመከራ ስንክ ሳር መለኮታዊ ሃይልን ተገን በማድረግ የሚገፈፍ አይደለም። ያ ቢሆን ኑሮ ለ 300 ሺ ዘመን ታፍራና ተከብራ የኖረችው የምትባለው ሃገራችን በየዘመናቱ ከድር አራዊት የከፉ፤ ጠበንጃ አንጋችና ከቀድሞዎቹ አለቆቻችን በእጥፍ ክፋትና ተንኮልን የተላበሱ በምድሪቱ ባልተራወጡባትም ነበር። የክፋቱ ጥግ ሰማይ ደርሶ አሁን እንሆ በክልል ፓለቲካ እየተቆራቆስን እንገኛለን። የዶ/ሩን በጎ ሃሳብ እጋራለሁ። ግን በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል ነው ነገሩ። በተደጋጋሚ እንዳልኩት የሚበልጠው የመከራ ዝናብ ምንጭ እኛው በእኛው ነን። የቀረው በነጩና በዓረቡ አለም የሚዘወር ተጨማሪ የመከራ ደመና ነው። የእነዚህ የሁለቱ የጥፋት ጥምር ህብረት ከድሮ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሃገራችን የመከራ ማጥ ውስጥ የከተታት። ያለፈውና የአሁኑ ይህን ከመሰለ የወደፊቱ ምን ሊሆን ይችላል? መልሱን ለማግኘት አሁን በምድሪቱ ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ መነሳት የግድ ይላል። ከሚታየውና ከሚዳሰሰው መረጃ ስንነሳ ችግራችን ውስብስብ እንደሆነና መላ ቅጡ እንደጠፋብን ያመላክታል። ግን አቤ ጉበኛ አልወለድም በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንደሚለን ” አንዴ ኢትዮጵያዊ ሆነን ተወልደናልና ተስፋ አንቆርጥም”። አልወለድም ስንል ተወልደንባታልና! እኔን የሚናፍቀኝ የዘር ፓለቲካው አገኘሁ በሚለው የቋንቋና የክልል ነጻነት የክልል ባንዲራ ማውለብለቡ ሳይሆን ሰውን በሰውነቱ የሚመዝን የሰው ልብ መገኘቱ ላይ ነው። ይህ ለእኔ ብቻ የሚለው አስተሳሰብ እስካልተቀየረ ድረስ ተሳዳጅና አሳዳጅ በምድሪቱ ሲሯሯጡ ለመኖራቸው ዛሬ የምናየው የወደፊቱንም አመላካች ነው እላለሁ። አለማችን የሚያፋጫት አብይ ጉዳይ የኢኮኖሚ የበላይነትን ፍለጋ ነው። ሌላው ሁሉ ሰበብ ነው። የሃይማኖት ግጭቱ፤ የዘሩ ፓለቲካ፤ የቋንቋው ጦርነትና ለድንበርህ ለሃገርህ መባሉ ሁሉ ሲፈተሽ የቅመራው ውጤት ለራስ ሲቆርሱ ላለማሳነስ የሚደረግ ፍትጊያ ነው። አበው ረጅም ድላ ባይመቱበት ያስፈራሩበት ማለታቸው ዛሬ ላይ እውን መሆኑን እያየን ነው። ችግሩ አሁን ላይ ሁሉም ረጅም ድላ ለመያዝ እየተሽቀዳደመ መሆኑ ነው። ያኔ በሁለት የፓለቲካ አስተሳሰብ ጎራ የተከፈለችው ዓለማችን አሁን ሁሉም ሚሳኤል አወናጫፊና በድሮን ሰው ገዳይ ሆኗል። ጉዳዪ እንዲህ ከሆነና ሁሉ ባለ ረጅም ከዘራ ሆኖ ና ግጠመኝ ካለ የዓለም መዳረሻዋ የት ይሆን? አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ላፈራረሷቸው እንደ ሊቢያ፤ ኢራቅ፤ ሶሪያና የመን ያሉ ሃገሮችሽ የወደፊት እድል ፈንታቸው ምን ይሆን? የእኛስ ሃገር በአሜሪካና በአውሮፓውያን ተንኮል በወያኔና በአባሪዎቻቸው ክፋት ከላይ ከተዘረዘሩት ሃገሮች ጎን ትሰለፍ ይሆን? ከሆነስ ማን አትርፎ ማን ይከስራል? የሰው ህይወት ሰክኖ ሰላምና እድገትስ በሃበሻው ምድር የምናየው መቼ ነው? ያ ቀን ይመጣ ይሆን? አላውቅም። እንደ ነገ ሊገደል እንደ ዛሬ ከዘመናት በፊት በእስር ቤት እያለ እንግሊዛዊው Conspirator and Poet Chidiock Tichborne ከጻፈው ግጥም ልጥቀስና ይብቃኝ።
    I sought my death and found it in my womb
    I looked for life and saw it was a shade
    I trod the earth and knew it was my tomb
    And now I die, and now I was but made;
    My glass is full, and now my glass is run,
    And now I live, and now my life is done.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share