በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ  ውሳኔ መወሰን ያለበት ማነው?  – ኤፍሬም ማዴቦ

  በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ  ውሳኔ መወሰን ያለበት ማነው?  

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)

በአንድ አገር ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ የሚወሰኑ አገራዊ ዉሳኔዎችን የሚወስነው ማነው የሚለው ጥያቄ መልስ በየአገሮቹ ውስጥ እንዳለው የፖለቲካ ሥርዓት አወቃቀርና እንደየአገሮቹ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታ ይለያያል። ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑት በህዝብ በተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ነው፣እንዲህ ማለት ግን ዲሞክራሲ ባለባቸው አገሮች ውስጥ ሁሉ አገራዊ ውሳኔዎች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ይወሰናሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ ጀርመንና አሜሪካ ዉስጥ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት መንገድ ይለያያል። አሜሪካ ውስጥ ህግ የማውጣት ሥልጣን ያለው ምክር ቤቱ ነው፣ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፕሬዚደንቱም ህግ የማውጣትና ምክር ቤቱ ያወጣውን ህግ ያለማጽደቅ ሥልጣን አለው። ጀርመን ውስጥ ግን ፕሬዚደንቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩም/ቻንስለር የአሜሪካ ፕሬዚደንት ያለው ሥልጣን የላቸውም። ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ ህገመንግስቱ እንደተጻፈበት መንገድ፣ የህግ አስፈጻሚው አካል፣ የህግ አውጪው አካል፣ፕሬዚደንቱ፣ ፕሬዚደንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የህግ አውጪውና የህግ አስፈጻሚው አካል በጋራ አገራዊ ውሳኔ መወሰን ይችላሉ። በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወስኑት በአምባገነን መሪዎች ናቸው።

ይህ በመግቢያው ላይ የተመለከትነው የውሳኔ አወሳሰን በሂደት ይለያያል እንጂ በየትኛውም ሉዓላዊ አገር ዉስጥ የሚኖር መደበኛ ሂደት ነው፣ ደሞም ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ መደበኛ ውሳኔዎች የሚወሰኑት በህዝብ በተመረጡ አካላት ነው። እንዲህ አይነቶቹ መደበኛ ውሳኔዎችና በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሳው “ውሳኔ” የሚለው ቃል በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ቢመሳሰሉም በቅርጽና በይዘት ግን ይለያያሉ። በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በአንድ አገር ውስጥ በህግ አውጪውና በህግ አስፈጻሚው አካል ከሚወሰኑ መደበኛ ውሳኔዎች ይለያሉ፣ እንዳውም አገራዊ ምክክር ያስፈለገው በመደበኛ ውሳኔ ሰጪ አካላት ደረጃ ሊወሰኑ የማይችሉ ውሳኔዎች በመኖራቸው ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ትላልቅ አገራዊ ውሳኔዎች የተወስኑት በጠመንጃ ኃይል ሥልጣን ላይ በወጡ ኃይሎች ነበር። በነገስታቱ ዘመን ንጉሱና በባለሟሎቻቸው፣ በደርግ ዘመን ኮሎኔል መንግስቱና ኢሠፓ፣ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ደግሞ መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ያሻቸውን ውሳኔ ወስነዋል። ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ከገዢው ፓርቲ ፍላጎት ውጭ የሆነ አገራዊ ውሳኔ አይወሰንም፣ ወይም ገዢው ፓርቲ የወሰነውን ውሳኔ ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ማስቀየር የሚችል አገራዊ ተቋም የለም። አገራችን ኢትዮጵያ ባለፈው ግማሽ ምዕተ አመት የተጓዘችበት ጨለማው የቁልቁለት መንገድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ መንግስታት የወሰኑት ውሳኔ ውጤት ነው። ይህ የጨለማ መንገድ ተቀይሮ የብርሃን መንገድ እንዲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት  መንገድም ውሳኔ የሚሰጡ አካላት ማንነትና ስብጥርም መቀየር አለባት።

የአለማችን የቀውስ፣ያለመረጋጋት፣ የግጭትና የርስበርስ ጦርነት ምልክት የሆነችዉ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምትገኝበት ውስብስብና አደገኛ ቦታ ላይ እንድትደርስ፣ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጨምሮ ሦስት ተከታታይ መንግስታትና በእነዚህ ሦስት መንግስታት ውስጥ የነበሩ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ልህቃን፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ የጾታ ማህበራት፣የእምነት ተቋማትና ማህበራዊ ስብስቦች በማድረግም ባለማድረግም የየራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ዛሬ የገባንበት አገራዊ ቀውስ ምንጩ ባለፉት ሃምሳ አመታት አንዱ ሌላውን፣ ለማጥፋት፣ለማሸነፍ፣ ለማሳነስ፣ ለማንቋሸሽ፣ ለማውገዝና ለማሳደድ የሄድንበት የግራ ኃይሎች፣ የቀኝ ኃይሎችና ግራ የገባቸው ኃይሎች አፍራሽ የፖለቲካ መንገድ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ እኔን ጨምሮ የኔ ትውልድ፣ ከኔ የቀደመው ትውልድና የዛሬው ትውልድ በግልም በቡድንም ያበላሸነውን የአገራችንን ፖለቲካ በጋራ መፍትሄ እንድንፈልግለት መንገድ ከፍቶልናል። ይህንን አገራዊ ምክክር ብለን የጀመርነውን አዲስ መንገድ ስንጀምር፣ ነገሮችን በተለየ መንገድ መመልከት መጀመር አለብን እንጂ፣ያለፈው ሃምሳ አመት ልምዳችንን ለመድገም መሞከር “ሁላችንም ተያይዘን ገደል እንግባ” ከማለት ያላነሰ ዕብደት መሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ አለብን።

በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ ልህቃን፣ምሁራን፣የማህበረሰብ ተወካዮች፣ሲቪክ ማህበራት፣የሰራተኛ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ወጣቶችና ሴቶች በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሂደት አሸናፊና ተሸናፊ፣ የሚከስርና የሚያተርፍ፣ የሚገንና ኮሳሳ ሆኖ የሚታይ፣ የሚኮራና የሚያፍር፣ የሚደሰትና የሚከፋ የማህበረሰብ ክፍል እንደማይፈጠር ተገንዝበውና፣ ከዚህ በፊት በተለያየ መልኩ ያደረጉት አፍራሽ እንቅስቃሴ በአገር ላይ ላደረሰው አደጋ ሃላፊነት ወስደው፣ ካሁን በኋላ ምንም አይነት አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ስራ እንደማይሰሩ ለራሳቸውና ለኢትዮጵያ ለህዝብ ቃል መግባት አለባቸው።

አገራዊ የምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን ህዝብ አሸናፊ የሚያደርግ እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ የሚፈጥር እንዳይሆን፣የአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሂደት መንግስትን ጨምሮ ማንም አካል የኔ ነው የማይለውና ማንም አካል እንዳሰኘው የማይዘውረው ነጻ፣ግልጽና ገለልተኛ ሂደት መሆኑ መረጋገጥ አለበት። የአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሥልጣንና ሃላፊነት ወሰን መወሰን ያለበት የጋራ በሆነ መድረክ ላይ እንጂ፣ በመንግስትም ሆነ በሌላ ሦስተኛ አካል መወሰን የለበትም። ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ከረጂም ግዜ ግጭትና የርስበርስ ጦርነት ተላቀው ከዲሞክራሲ ጋር በሚተዋወቁ አገሮች ውስጥ የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ሲዘጋጅ ሁለት ትልልቅ ችግሮች ይገጥሙታል – አንደኛው- በህዝብ ያልተመረጠና ህዝባዊ ቅቡልነት (Legitimacy) የሌለው መንግስት መኖር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ቢኖርም የተመረጠበት መንገድ አጠያያቂና ህዝባዊ አመኔታ የጎደለው ሲሆን ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ሁለተኛው አይነት ችግር ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረገው አገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ላይ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የምክክር ኮሚሺኑ ከሚጠይቀው አስተዳደራዊ፣ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስና የቴክኒክ ዕርዳታ ውጭ በጉባኤው ዝግጅት ሂደት ላይም ሆነ በጉባኤው ሂደት ላይ በምንም አይነት እጁን ማስገባት የለበትም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጥያቄዉ የሃይማኖት ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ነዉ ! አማኑኤል ዘሰላም

ብሔራዊ ውይይቶች ባለፉት ሃምሳ አመታት አውሮፓ፣ደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ በተለያዩ አገሮች ውስጥ ተካሂደዋል፣ እነዚህ ውይይቶች በየአገሮቹ የወደፊት ላይ የተለያዩ ዉሳኔዎችን ወስነዋል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ህገ መንግስት አሻሽለዋል ወይም አዲስ ህገ መንግስት አርቅቀዋል፣ አንዳንድ አገሮች ውስጥ ግዜያዊ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም አድርገዋል፣ በአንዳድን አገሮች ውስጥ ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሥልጣን ገድበዋል፣ የሽግግር ግዜ ፍትህ እንዲኖር ወስነዋል፣ ብሔራዊ የሰላምና ዕርቅ ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ የምክክር መድረክ ያስፈለገው በአንድ በኩል እኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ማህበራዊ ኮንትራት መፈራረም አለብን የሚል ዘመናት ያስቆጠረ ጥያቄ በመኖሩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የገባችበት እጅግ በጣም ውስብስብ የሆነ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግር በሥልጣን ላይ ባለው መንግስት የሚፈታ ችግር ባለመሆኑ ወይም መንግስት እራሱ የችግሩ አካል በመሆኑ ነው። እንዲህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ የምክክር መድረክ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ መክሮ የተለያዩ ውሳኔዎች ይወስናል ማለት ነው። ለመሆኑ በአገራዊ የምክክር መድረኮች ላይ ውሳኔ የሚወስነው ማነው? የሌሎች አገሮች ልምድ ምን ይነግረናል? እኛስ አገር በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ውሳኔ የሚወስነው ማነው?

የውሳኔ አወሳሰንን በተመለከተ በተለያዩ አገሮች ዉስጥ በተካሄዱ ብሔራዊ የውይይት መድረኮች መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትና ዘዴ ላይ ነው እንጂ፣ ጉባኤው ዉሳኔ የመወስን ሥልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለው ላይ አይደለም። አንዳንድ አገሮች ውስጥ ለምሳሌ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቤኒንና የመን ውስጥ የተለያዩ ውሳኔዎችን የወሰነው ጉባኤው ሲሆን፣ ሜክሲኮ ውስጥ በተካሄደው ብሔራዊ ጉባኤ ውሳኔ የወሰኑት ጉባኤው የሰየማቸው የስራ ቡድኖች (Working Groups) ናቸው፣ ሶማሊያና ቶጎ ውስጥ ደግሞ ለዚህ ጉዳይ የተቋቋሙ የውሳኔ አሰጣጥ ኮሚቴዎች ናቸው። በአገሮች መካከል እንዲህ አይነት የዉሳኔ አሰጣጥ ልዩነት የኖረው፣ በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ያለው ችግር፣ የውሳኔ አሰጣጥ ባህል፣ የልህቃኑ የርስ በርስ ግኑኝነትና የመተማመን ደረጃ ስለሚለያይ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ በእነዚህ ልዩነቶች ላይ ተመስርቶ ዲዛይን ስለሚደረግ ነው።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ውሳኔ የሚወስነው ማነው? ባለፈው ታህሳስ ወር የወጣው የአገራዊ ምክክር ኮሚሺን ማቋቋሚያ አዋጅ ውሳኔን በተመለከተ ምን ይላል? በአገራዊ ምክክሩ ላይ የውሳኔ አወሳሰንን በተመለከተ  የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 በክፍል ሁለትና በክፍል አራት ላይ የተቀመጡ ሁለት አንቀጾች አሉት – 

አዋጅ ክፍል 2 አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 10

የአገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልፅ ሰነድ በማዘጋጀት ለአስፈጻሚ አካሉ፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያቀርባል፣ ለህዝብም ይፋ ያደርጋል፣

አዋጅ ክፍል 4 አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 2

በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለአስፈጻሚ አካሉ፣ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው  የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ማፅደቅ፣ ይህ ሁለተኛው አንቀጽ (አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 2) ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ አስተያየት ቀርቦ ከተሻሻለ በኋላ የወጣው ነው፣ ከመሻሻሉ በፊት ይህን ይመስል ነበር “በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለመንግሥት እንዲቀርብ ማፅደቅ” የምክክር ኮሚሺኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ፓርላማ ቀርቦ ህዝብ አስተያየት ሲሰጥበት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ፓርላማ ተገኝቶ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራትና ሌሎችም የተለያዩ አካላት በተለያየ መልኩ ባቀረቡት ጥያቄ እንዲሻሻል ከጠየቁትና በዕለቱ ፓርላማው ውስጥ ከቀረቡት ህዝባዊ አስተያየቶች ውስጥ ብዙዎች እንዲሻሻል ከጠየቁት አንቀጽ ውስጥ ውሳኔን የሚመለከተው ይህ ካላይ የተቀመጠው  አንቀጽ አንዱ ነበር። ሆኖም ከላይ እንደምትመለከቱት በመጀመሪያውና በተሻሻለው አንቀጽ መካከል ያለው ልዩነት የቃላት እንጂ የይዘት አይደለም። ለኔ ይህ የሚያሳየኝ መንግስት በአገራዊ ጉባኤው ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከእጁ እንዳይወጣ መፈለጉን ነው። አሁንም ይህ አንቀጽ ተሻሽሎ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከመንግስት እጅ ወጥቶ ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው ካልተሰጠ፣ከዚህ ለአመታት ከተጮኸለትና ብዙ ከተደከመለት አገራዊ ምክክር እንደ አገርና እንደ ህዝብ የምናገኘው ብዙ ነገር አይኖርም! ለምንድነው መንግስት ባወጣው አዋጅ ላይ “አካታች” የሚል ቃል በተደጋጋሚ እየተጠቀመ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሲደርስ ግን አካታችነቱን ረስቶ የውሳኔ መወሰኑን ስራ ለራሱ የወሰደው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  አቶ አብርሃም ያዬህ የምላስዎትን አፈሙዝ በአቶ ገ/መድኅን አርአያ ላይ አያዙሩ!

በነገራችን ላይ የአገራዊ ምክክር ኮሚሺን ማቋቋሚያ አዋጅ ለኮሚሺኑ የሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት አዋጁ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፣ ኮሚሺኑ ብዙ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራ ቢሆንም የኮሚሺኑ ዋና ስራ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የምክክር ጉባኤዎችን ማደራጀት ነው። ኮሚሺኑ የሚያደራጀው ጉባኤ በተለይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚዋቀረው ጉባኤ የሚኖረው ሥልጣንና ኃላፊነት ግን በአዋጁ ላይ አልተቀመጠም። የአገራዊ ምክክር ጉባኤው የሚኖረውን ሥልጣንና ኃላፊነት የሚወስነው በኮሚሺኑ ነው እንዳይባልም ይህንን በተለመከተ አዋጁ ለምክክር ኮሚሺኑ የሰጠው ምንም ሥልጣን የለም። ለመሆኑ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቀውና ብዙ የተደከመለት አገራዊ የምክክር ጉባኤ ምን አይነት ሥልጣንና ኃላፊነት ነው ያለው? ጉባኤው የራሱ የሆነ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሌለው ለምን ተዋቀረ፣ ለምንስ አስፈለገ?

በአዋጁ ላይ “ምክረ ሃሳብ” የሚለው ቃልና “ዉሳኔ”/Decision የሚለው ቃል ተመሳሳይ ናቸው? ተመሳሳይ ከሆኑ ለምን አዋጁ ላይ ሁላችንም በቀላሉ የምንረዳው “ውሳኔ” የሚል ቃል አልተቀመጠም?  ሁለቱ ቃላት ተመሳሳይ ካልሆኑ፣ አንደኛ- ሁሉን አቀፍ ሆኖ የሚቋቋመው አገራዊ የምክክር ጉባኤ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ እንጂ ውሳኔ መወሰን አይችልም ማለት ነው፣ሁለተኛ- በአዋጁ መሰረት የጉባኤውን ምክረ ሃሳቦች ተመልክቶ ውሳኔ የሚወስነው መንግስት ነው ማለት ነው። ለምንድነው ምክረ ሃሳብ ለመንግስት ብቻ የሚቀርበው? ሌሎቹስ ባለድርሻዎች? ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ አላስማማ ብለው ባጋደሉን ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መንግስት የሚወስን ከሆነ አገራዊ ምክክር ለምን አስፈለገ? በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እምነት በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ውሳኔ መወሰን ያለበት በጉባኤው በራሱ ወይም ጉባኤው በሚሰይማቸው አካላት ነው እንጂ፣ መንግስት በምንም አይነት ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ሊሰጠው አይገባም!

በ2013ቱ ምርጫ በዕጩዎችና በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ፣ በምርጫ ዘመቻው ወቅትና በድምፅ አሰጣጡ ሂደት ላይ የታዩ መሰረታዊ ችግሮች አንዳሉ ሆኖ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ የተመረጠ ፓርላማ አለ። ፓርላማ ደግሞ የአንድ አገር ህግ የሚወጣበትና የተለያዩ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት ቦታ ነው። ሆኖም በኔ እምነት የኢትዮጵያን የሚቀጥሉት መቶና መቶ ሃምሳ አመታት ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ገጽታ የሚቀርጹ ትላልቅ አገራዊ ውሳኔዎች የአንድ ፓርቲ ቤት በሆነ ፓርላማ መወሰን የለባቸውም። በእርግጥ ፓርላማ የህዝብ ተመራጮች ያሉበት ቦታ ነው፣ ሆኖም ፓርላማ በተፈጥሮው በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ባለድርሻዎች በሙሉ የሚገኙበት ተቋም አይደለም፣ የኢትዮጵያ ፓርላማ ደግሞ ጭራሽ አንድ ፓርቲ ያለምንም ተቃውሞ ያሰኘውን ውሳኔ የሚወስንበት ፓርላማ ነው።

አገራዊ ምክክር ጉባኤ እንደ ፓርላማ በቀጥታ በህዝብ የተመረጡ አባላት ባይኖሩትም በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎችን ከፓርላማው በበለጠ መልኩ የሚያሰባስብ አካል ስለሆነ በአካታችነቱ፣በስብጥሩና በህዝባዊ ቅቡልነቱ ዛሬ በስራ ላይ ካለው ፓርላማ የበለጠና የተሻለ ነው የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ከዚህ በተጨማሪ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች መክረው የሚወሰኑት ውሳኔ፣ ሰፋ ያለ ግዜ ተወስዶባቸውና ጥልቅ ውይይት ተካሂዶባቸው የሚወሰኑ ህዝባዊ ውሳኔዎች ስለሚሆኑ፣ በውሳኔው ሂደት ውስጥ የተሸነፉ ወገኖች ውሳኔው ባይስማማቸውም  የውይይቱና የውሳኔ አሰጣጡ ሂደት አካል ስለሆኑ ውሳኔውን ያከብሩታል።

አገራዊ ምክክር በየትም አገር በተለይ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ካለው መንግስት በጎ ፈቃድ፣ትብብርና ድጋፍ ውጭ መካሄድ አይቻልም። አገራዊ ምክክር እንዲካሄድ የመንግስት በጎ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ፣የሎጂስቲክስና የጸጥታ ድጋፍም አስፈላጊ ነው። አገራዊ ምክክር ተካሂዶ፣ ዉሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ትብብር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን መንግስት ውሳኔዎቹ እንዲካሄዱ የተለያዩ ድጋፎችን ይሰጣል፣ ውሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ይተባበራል ማለት ነው እንጂ፣ መንግስት በምክክሩ ዝግጅት፣ በምክክሩ ሂደትና በምክክሩ ውሳኔዎች ትግበራ ላይ የሚፈልገውን ያደርጋል የማይፈልገውን አያደርግም ማለት አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለዛች አገር የሚገባት እውን ይሄ ነውን?

አገራዊ ምክክር በብዙ አገሮች ውስጥ በተለይ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ካለው መንግስት በጎ ፈቃድ፣ትብብርና ድጋፍ ውጭ መካሄድ አይቻልም፣ አገራዊ ምክክር ተካሂዶ፣ ዉሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ትብብር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን መንግስት ውሳኔዎቹ እንዲካሄዱ የተለያዩ ድጋፎችን ይሰጣል፣ ውሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ይተባበራል ማለት ነው እንጂ፣ መንግስት በምክክሩ ዝግጅት፣ በምክክሩ ሂደትና በምክክሩ ውሳኔዎች ትግበራ ላይ የሚፈልገውን ያደርጋል የማይፈልገውን አያደርግም ማለት አይደለም።

ከአገራዊ ምክክር ጉባኤው ስራዎች አንዱና ትልቁ የኢትዮጵያን የሚቀጥሉት ሃምሳና መቶ አመት ዕድል መወሰን ነው። ይህንን ግዙፍና በአሁኑ ትውልድ ላይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት በሚመጣው ተከታታይ  ትውልድ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችልንና ሁላችንንም የሚነካ (Consequential) ውሳኔ ለአንድ ፓርቲ፣ ለጥቂት ፓርቲዎች ወይም በሥልጣን ላይ ላለው መንግስት ብቻ በፍጹም መተው የለብንም! የአገራዊ ምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባለድርሻዎችና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያቅፍ ነጻና ገለልተኛ አካል እስከሆነ ድረስ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል። የውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ ግዜ ወስደን መወያየት ያለብን አገራዊ የምክክር ጉባኤዉ የወሰነው ውሳኔ እንዴት መጽደቅ አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ ነው እንጂ፣ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የመፍጠርን ውሳኔ በምንም አይነት ለመንግስት ብቻ መተው የለብንም።

ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል የሌለው ችኮ ልህቅ ያለባት አገር ናት። እንዲህ አይነት ልህቅና ችኮነት የተጠናወተው የፖለቲካ ባህል ባለበት አገር ውስጥ የወደፊቷን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽታ በሚወስኑ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ዉሳኔ ማሳለፍ ከባድና ብዙ ግዜ ሊወስድ የሚችል አድካሚ ስራ ነው። የአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሥልጣንና ሃላፊነት ምን ያክል ነው? ማነው ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሥልጣን የሚሰጠው? በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ውሳኔ ማን ይወስናል፣ እንዴትስ ይወስናል የሚሉ ጥያቄዎች አገራዊ ምክክር ጉባኤ በሚደረግባቸው አገሮች ውስጥ በጣም ቁልፍ የሆኑና በቀላሉ ስምምነት ላይ የማይደረስባቸው ጥያቄዎች ናቸው።

እንደ ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ በጦዘበት፣የፖለቲካ ልዩነቱን በውይይት የመፍታት ባህል የሌለውና ጎራ ለይቶ የተጋደለ የፖለቲካ ልህቅ ባለበት አገር ዉስጥ ዋናው ቁምነገር ህዝብ ለዘመናት የጠየቃቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘታቸው ብቻ አይደለም። ጥያቄዎቹ መልስ የሚያገኙበት ሂደትና እነማናቸው ጥያቄውን የሚመልሱት ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው መልስም አጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።  የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎችን ማን ይመርጣቸል፣ ተሳታፊዎች በምን መስፈርት ይመርጣሉ፣ ጉባኤው እነ ማንን ያካትታል፣ የጉባኤውን አጀንዳ ማን ይቀርጻል፣ የጉባኤውን ውሳኔዎች ማን ያጽድቃዋል ለሚሉ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ የጉባኤውን ዉጤታማነት፣ ቅቡልነት፣ህጋዊነትና ተግባራዊነት በቀጥታ ይወስናልና፣  የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ዲዛይን ሲደረግ ቁልፍ ባለድርሻዎች በተገኙበት በከፍተኛ ጥንቃቄ ዲዛይን መደረግ አለበት።

ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ የምክክር ጉባኤ ያስፈለገው ዘመን ያስቆጠሩ ችግሮቻችን አሁን በስልጣን ላይ ባለው መንግስትና መንግስታዊ መዋቅሮች የሚፈቱ ችግሮች ባለመሆናቸው ብቻ አይደለም፣ አብዛኛው  የኢትዮጵያ ልህቅና የፖለቲካ ባለድርሻ መንግስት የችግሩ አንዱ አካል ነው ብሎ ስለሚያምን ወይም መንግስት ብቻውን የችግሮቻችን መፍትሄ ይሆናል የሚል ዕምነት ስለሌለው ነው። ሰለዚህ ውሳኔን በተመለከተ አዋጁ ላይ የተቀመጡት ሁለቱ አንቀጾች ተሻሽለው፣ የተሻሻለው አዋጅ ውሳኔ የመወሰንን ሥልጣን በግልፅ ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው መስጠት አለበት። ይህ እንዲሆን፣ የምክክር ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቭክ ማህበራት፣የሰራተኛ ማህበራት፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች፣ የጥናትና ምርምር ተቋሞች፣መገናኛ ብዙሃን፣የሰብዓዊ መብት ተቋሞች፣ ሴቶችና ወጣቶች በገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከመንግስት እጅ ወጥቶ የጉባኤው ሥልጣን እንዲሆንና ባጠቃላይ አዋጅ ቁጥር 1265 ላይ ውሳኔን በተመለከተ የተቀመጡ ሁለቱ አንቀጾች እንዲሻሻሉ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደር አለባቸው።

 

6 Comments

  1. Real challenge to understand! Which one is intended to mean with these sentences?
    ” አሜሪካ ውስጥ ህግ የማውጣት ሥልጣን ያለው ምክር ቤቱ ነው፣ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፕሬዚደንቱም ህግ የማውጣትና ምክር ቤቱ ያወጣውን ህግ ያለማጽደቅ ሥልጣን አለው።”
    a. አሜሪካ ውስጥ ህግ የማውጣት ሥልጣን ያለው ምክር ቤቱ ነው፣ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፕሬዚደንቱም ህግ የማውጣትና ምክር ቤቱ presidentu ያወጣውን ህግ ያለማጽደቅ ሥልጣን አለው።
    b. አሜሪካ ውስጥ ህግ የማውጣት ሥልጣን ያለው ምክር ቤቱ ነው፣ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፕሬዚደንቱም ህግ የማውጣትና ምክር ቤቱ ያወጣውን ህግ presidentu ያለማጽደቅ ሥልጣን አለው።

  2. “….በአካታችነቱ፣በስብጥሩና በህዝባዊ ቅቡልነቱ …” Very far, far, from the truth. Actually, a sinister lie.

    Like an Amharic saying puts it, it is difficult to wake up someone who feigns sleep (awqo yetegna biTerut aysemam). It should be very apparent to a seasoned politician like Ato Efrem.
    1. The commission has been exposed as lacking any Amhara representation and the Amhara compose at least 35% of the Ethiopian population.
    2. The PM has illegally (against the founding rules) included 3 names in the final composition of the commission. That is way too much interference for the commission to be regarded as non-partisan.
    3. Above all, the Teregna PM has included seasoned political party members such as veteran and decorated OLF member Zegeye Asfaw. Why all this interference unless one wants to control the proceedings and outcome.

    Just another of Abiy Ahmed’s ploy to hang on to power using various gimmicks. What happened to all the other commissions that he commissioned with such pomp and fanfare?

  3. What a stupid comment is this! The article talks on who makes decisions on the upcoming national dialogue, and Ephrem clearly argues against the government making decisions. What are you opposing and what exactly are you saying? Are you sane?

  4. I totally agree with the second comment. You cannot be debating on how to finish the fifth floor of a five-story building and who to rent it to when you are being told the very foundation is faulty.

    “…የአገራዊ ምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባለድርሻዎችና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል .የሚያቅፍ ነጻና ገለልተኛ አካል እስከሆነ ድረስ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል። “
    ይቺ በሳል ፖለቲካዊ ማጭበርበር ትባላለች። ሁሉን አያቅፍም፣ አላቀፈም ነጻና ገለልተኛም አልሆነም ከአወቃቀሩ ጀምሮ የተዛባና ከመንግሥት የተጣባ ክፍል ያለበት ነው እየተባለ ከላይ ባለቸው አገላለጽ ዝኆን የሚያክለውን ግድፈት ክዶ ለማለፍ መሞከር ያስገምታል። “…ሁሉን የሚያቅፍ፣ ነጻና ገለልተኛ”? ወዴት ወዴት?

    “..ይህንን አገራዊ ምክክር ብለን የጀመርነውን አዲስ መንገድ ስንጀምር፣ ነገሮችን በተለየ መንገድ መመልከት መጀመር አለብን እንጂ፣ያለፈው ሃምሳ አመት ልምዳችንን ለመድገም መሞከር “ሁላችንም ተያይዘን ገደል እንግባ” ከማለት ያላነሰ ዕብደት መሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ አለብን።

    ትክክል ብለዋል አቶ ኤፍሬም። የተያዘው ግን ያለፈውን ሃምሳ ዘመን ልምድ እንዲያውም ይብስ በከፋ መልኩ መድገም ነው; ለዚህም ከስልሣዎቹ ትውልድ የበለጠ ሥልሳ የሆኑት ዶ/ር አቢይ (ኮሎኔል አስናቀ) ሁለት አንጋፋ የሱማሌና የኦሮሞ ስታሊኒስት ብሔርተኛ ፖለቲከኞችን አሥርገው ማስገባቱ አንሷቸው ከላይ እንደተጠቀሰው ደርዘን ከማይበልጡት ኮሚሽነሮች ውስጥ በሕገወጥ መንገድና ባለቀ ሰዐት 3 ሰዎቻቸውን በተጨማሪ ማካተታቸው ምን ያህል ኢህአዴግ ዛሬም በሴራ፣ በተንኮል፣ በቁማርና በአፈና አሠራር እንደቀጠለ የሚያሳይ ነው። ነገንም በዚሁ መንገድ ለመወሰን የሚደረግ ብርቱ መንደፋደፍ መኖሩን ከዚህ በላይ ማስረጃ ሊኖር አይችልም። የምክክር ሳይሆን የፉገራ ኮሚሽን ነው አሁን ያለን። የይስሙላ ኮሚሽን። የበሰበሰ እንቁላልና የተበላሸ ሽንኩርት መጥበሻ ላይ ጨምሮ ልዩ የሆነ ሸጋ የእንቁላል ጥብስ ቁርስ ለመሥራት ይቻላል? ሕንዶች ይሁኑ እንግሊዞች garbage in garbage out ይላሉ ይባላል።
    ምንም የአማራ ተወካይ የለም የሚለውን በኮሚሽኑ አወቃቀር ላይ የቀረበ ክስ መታወቂያቸውን ወይም የዘር ሐረጋቸውን ስላላየን መናገር ባንችልም አሳማኝ ማስተባበያ የሰጠ ባለመኖሩ ወያኔና ኦነግ ያለ አማራ ውክልና ያቋቋሙትን ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር ሥርዐት ያለ አማራ ውክልና ተመካክሮ ማስተካከሉ ይበጃል ከተባለ ማየት ነው እንግዲህ።
    መልካም ምክክር። ተማክራችሁ ስትጨርሱ “የምታፋፍሙትን አፋፍሙብን”።

  5. Sisay there is a grain of truth in Ahoon and Sergut’s comment. In my opinion the commission to function well their suggestion should be implemented. The way members chosen, their political personalities do not make them the right candidate and fit them to this high office post. Above all if 33% of the population is not represented well there is some hidden agenda at the mind of of the PM. The PM has problems choosing the right person for the right job, he thinks Ethiopia is his personal business, doesnt care choosing people for the right job. How do you give serious jobs for those people who have never worked in their entire life ( Berhanu Nega, Andargachewu Tsegie,Kejela Merdasa,Aregawi Berhea,Lencho Leta,Lencho Bati …) These people are moribund unable to produce new ideas not fit for young and vibrant society. Recently he filled his vacant with Alemnewu Mekonen and Shiferawu Shigutea I thing the man is in suicide mission.

  6. “…የአገራዊ ምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባለድርሻዎችና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል .የሚያቅፍ ነጻና ገለልተኛ አካል እስከሆነ ድረስ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል። “
    ይቺ በሳል ፖለቲካዊ ማጭበርበር ትባላለች። ሁሉን አያቅፍም፣ አላቀፈም ነጻና ገለልተኛም አልሆነም ከአወቃቀሩ ጀምሮ የተዛባና ከመንግሥት የተጣባ ክፍል ያለበት ነው እየተባለ ከላይ ባለቸው አገላለጽ ዝኆን የሚያክለውን ግድፈት ክዶ ለማለፍ መሞከር ያስገምታል። “…ሁሉን የሚያቅፍ፣ ነጻና ገለልተኛ”? ወዴት ወዴት?

    አቶ አለሙ የአቶ ኤፍሬም አባባል የገባዎት አይመስለኝም- እሳቸው የሚሉት አገራዊ የምክር ጉባኤው ኢትዮጵያን የፖለቲካ ባለድርሻዎችና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል .የሚያቅፍ ነጻና ገለልተኛ አካል እስከሆነ ድረስ ነው። እርሶ የሚሉት ሁሉን አያቅፍም፣ አላቀፈም ነጻና ገለልተኛም አልሆነም ከአወቃቀሩ ጀምሮ የተዛባና ከመንግሥት የተጣባ ክፍል ያለበት ነው። እስኪ መለስ ብለው ያሉትን ይመልከቱ፣ አገራዊ የምክክር ጉባኤውኮ ገና አልተዋቀረም። እንዴት ነው ሳይዋቀርና ሳናየው አካታች አይደለም፣ ነጻና ገለልተኛ አይደለም ማለት የሚቻለው? መጀመሪያ ሰው የሚለው ይግባዎት እንጂ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share