አእምሮ ኢትዮጵያ ገደል አፋፍ ላይ – በላይነህ አባተ

አጭበርባሪው ተማሪስ ካምፕ ውስጥ ተፈትኖ አረፈው! ማጭበርበሩን ያስተማሩት አገር ገዥዎች፤ ፒ ኤች ዲ፣ ክሀነትና ሽክና ሸማቾችስ የት ተፈትነው እውቀታቸውን ሊያሳዩ ነው?

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) 

እኔ እስከማውቀው ድረስ ተፈታኙ እጅግ አጪበርባሪ ፈታኙም እጅግ በዘርና በቋንቋ ደዌ የከረፋ ሆኖ የመልስ ወረቀት እየበተነ በማስቸገሩ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ካምፕ ውስጥ የተሰጠው በሃማኖትና በመንፈስ ልዕልና ትታወቅ በነበረችው ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ ተከንቱዎች እጅ በወደቀችው የዛሬዋ ኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ ይኸንን የከረፋ ደዌ ተማሪን ካምፕ ውስጥ እንደ እስረኛ በማጎር ለማዳን መዋተት ተቅማጥን እንትንን በመወተፍ ለማዳን እንደ መጣር ነው፡፡ ፈተና መስረቅ ወይም ማሰረቅ፣ ዲግሪ በተሰረቀ ገንዘብ መሸመት፣ በካድሬነት ለማገልገል ዲግሪ መጫን፣ መደቆን፣ መቅሰስ፣ መመንኮስ፣ መጰጰስ፣ መፐትረክም ሆነ ሼህ መሆን የሚቆመው አገር እንዲህ አይነት የውርደት መቀመቅ ውስጥ የወረደችበት ምንስዔ ሲፈተሽና መፍትሔ ሲፈለግለት ብቻ ነው፡፡

በረጅም የሃይማኖት አገርነትና በመንፈስ ልዕልና ትታወቅ በነበረቸው ኢትዮጵያ እንኳን የአእምሮን ፍሬ የባቄላ ፍሬም ሰርቆ መውሰድ እጅግ ጸያፍ ነበር፡፡ ሌባ ተሚኖርበት መንደር መኖርም እጅግ ያሳፍር ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ እንኳን ገንዘብና ወንበር ተራራ፣ ታሪክና የአእምሮ ሐብትም ተሞጭልፎ የሚሰረቅባት አገር ሆናለች፡፡ እንደ አለመታደል ብራና ፍቀው፣ ቀለም በጥብጠውና ቅጥቅጥ አብርተው በሁለት እጅ የማይነሱ የእውቀትና  የጥበብ መጻሕፍት ይፈልቁባት የነበረቸው ኢትዮጵያ አእምሮዋ ወድቆ ሊከሰከስ የተቃረበች አንጀቷ የተቃጠለ እናት ሆናለች፡፡

እንደሚታወቀው አንጎል ከጭንቅላት ውስጥ የሚገኘው የነርቭ ስጋ ሲሆን አእምሮ ደግሞ በዚህ ውስብስብ የነርቭ ስጋ ውስጥ ተነጥፎ እንደ ኮምፒዩተር ሶፍት ዌር የሚያስብ፣ የሚያስታውስ፣ የሚቀምር፣ የሚያሰላስል፣ የሚያመዛዝንና ውሳኔ የሚሰጥ በህሊና አፎት የተሸፈነ የሐሳብ ስለት ነው፡፡ ይህ የሐሳብ ስለትም የሥልጣኔ ምንጭ ነው፡፡ አእምሮ የስልጣኔ ምንጭ  የሚሆነው አፎቱን(ህሊናን) ቀዶ ካልወጣ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሥልጣኔ በህሊና መገዛት ነው፡፡

ለመሰልጠን የአእምሮን አፎት ወይም ህሊናን ማደርጀት ሊበቃ ይችላል፡፡ በስልጣኔ ለመበልጸግ ግን ህሊናን ካመደርጀትም  በተጨማሪ የሐሳብ ስለትንም እንደ ቢላዋ ማስላት ያስፈልጋል፡፡ የሐሳብ ስለትን ወይም አእምሮን እንደ ቢላዋ ለማስላትም የተፈጥሮ፣ የቤተሰብ፣ የጎረቢት፣ የመንደር፣ የአገር፣ የአለም፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የትምህርት ሞረዶችን መጠቀም ያሻል፡፡ አእምሮ ብሩክ ሆኖ ሲፈጠር፤ በመልካም ባህልና እምነት ሲግል፤ በትምህርትና በምርምር ሞረድ ሲላግ እንደ ሰማይ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ እንደ ሰማይ የሰፋ እአምሮ የተሸከመ ሕዝብ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን ትውልድ እያስተሳሰረ በሰላም ተከባብሮ ይኖራል፡፡ በህሊና በታሸገ ሰፊ አእምሮ የበለጸገ ሕዝብ የስርቆት፣ የቅጥፈት፣ የአጭበርባሪነት፣ የክፋትና የጭካኔ በሮችን ይከረችማል፡፡ በአእምሮ የበለጸገ ሕዝብ ከሰው ይልቅ ሰውነት ላይ፤ ከቋንቋ ይልቅ መግባቢያ ላይ፤ ከሃይማኖት ይልቅ እምነት ላይ ስለሚያተኩር ዘር ቆጠራን፣ ቋንቋ ምንዘራንና ሃይማኖት ጥንቆላን ይጸየፋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Video: “ልዩ ጥቅም” ከማን? ለማን? ለምን?

የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አእምሮ በተፈጥሮ፣ በባህልና በሃይማኖት ተሞርዶ በስልጣኔ የበለጸገ ስለሆነ ዘር ሳይቆጥር፣ ቋንቋ ሳይመነዝርና ሃይማኖት ሳይጠነቁል ካለፖሊስ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሲኖር ቆይቷል፡፡ አገዛዝ ባልነበረባቸው ጊዚያት እንኳን የህሊናን ግምጃ ለብሶ በስልጣኔ መበልጸጉን ለመለኮትም ሆነ ለአለም ሕዝብ አሳይቷል፡፡ ይህ በስልጣኔ የበለጸገ ሕዝብ አገዛዝ በተደጋጋሚ በርሐብ አለንጋ ሲገርፈውም ለመስረቅ እጆቹን ከሰው ንብረት ውስጥ ከመዶል፤ ለመዝረፍም ቆመጡን ወይም ቆንጨራውን ከማንሳት እየተቆጠበ በመኖር ላይ ይገኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ስልጡን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ውጪ  ከቶ የት ነበር? ዳሩ ግን ይህ የቦካ ሥልጣኔ እስከመቼ ይቀጥላል? ቤተክህነት በአጭበርባሪ ካህናት፤ ቤተመንግስት በነፍሰ-ገዳዮች፣ በሌቦችና፣ በቀጣፊዎች፤ የትምህርት ተቋማትም በካድሬዎችና በዲግሪ ሸማቾች ሲወረሩ ይህ በህሊና የመገዛት ቅዱስ ስልጣኔ እስከ መቼ ይዘልቃል?

አእምሯቸውን እንደ ሽቦ ያጨማደዱና ህሊናቸውን እንደሌጦ የገሸለጡ ቀጣፊ፣ ከሐዲና፣ አረመኔ ግዥዎችን እያዬ ያደገ አእምሮ ከየት የመሪነት እውቀት ሊገበይ ይችላል? ነፍስ በማጥፋት፣ በመዝረፍ፣ በመስረቅ፣ በመቀማትና በጉቦ የናጠጡ ጉምቱ ከበርቴዎችን የተመለከተ አእምሮ ሰርቶ ማግኘትን ከየት ሊማር ይችላል? እውነት የተናገረ በችጋር ሲሰቃይ፣ ንብረቱን ሲቀማ፣ ሲሰደድ፣ ከስራ ሲባረር፣ ሲታሰር፣ ሲገረፍና ሲሞት ያዬ አእምሮ እንዴት ወደ እውነት ሊጠጋ ይችላል? አንድነትን፣ አገርን፣ ባንዲራንና ክብርን የወደደ በጥይት ሲበረቀስ የተመለከተ አእምሮ እንዴት ለአንድነት፣ ለአገርና ለክብር ሊቆም ይችላል? የዘር፣ የቋንቋና የሃይማኖት ክልል የሚገነቡ ፖለቲከኞችን ስብከት ሲሰማ የኖረ አእምሮ እንዴት ከሰው ይልቅ ሰውነት ላይ፣ ከቋንቋ ይልቅ መግባባት ላይ፣ ከሃይማኖት ይልቅ እምነት ላይ ሊያተኩር ይችላል?

ካባቸውን እንደ ካፖርት ደርበው፣ ቆባቸን እንደ አክሊል ደፍተውና ጥምጣማቸውን እንደ አውሎ ንፋስ ቆልለው አስርቱ ቃላትን እንደ ዶሮ እየጫሩ ሲያፍርሱ የሚውሉ ካህናትን ሲያስተውል ያደገ አእምሮ በምን ተአምር በሃይማኖት ይታነጻል? ተበዳይ በዳይን ይቅርታ እሚያስጠይቅ “ሽማግሌ” እየተመለከተ የጎረመሰ አእምሮ በምን ቋንቋ የሽምግልናን ትርጉም ሊረዳ ይችላል? ጉቦኝነት፣ አቃጣሪነት፣ ሎሌነት፣ ስርቆትና አድርባይነት የኑሮ ፈሊጦች በሆኑበት ማህበረሰብ ውስጥ ያደገ አእምሮ በምን ተአምር በሥነ-ምግባር ሊታነጽ ይችላል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድሮስ ፤  ከእባብ እንቁላል እርግብ ይገኛልን ??? - ሲና ዘ ሙሴ

ጥላቻን በሚሰብክ ገለባ ሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ያለፈ አእምሮ እንዴት ፍቅር እሚያፈራ ዛፍ ሊሆን ይችላል? በእውቀትና በሥነ-ምግባር የተሳሉ ምሁራን ተነቅለው በድንቁርናና በምግባረ- ብልሹነት የዶለደሙ ካድሬዎች ከተተከሉበት የትምህርት ተቋም የዋለ አእምሮ በምን ሞረድ ሰልቶ ሊወጣ ይችላል? የአየነው እጅጉን ሳይሆን የቆስጠንጢኖስ በርሄን ክፍለ-ትምህርት እንዲከታተል የተፈረደበት ተማሪ በምን ሙያ ሊመረቅ ይችላል?

ቤተ-መጽሐፍት ከሚሰሩበት ሳይሆን መጻሕፍት ለስኳር መጠቀለያ በሚሸጡበት፣ የፍልስፍና ብራናዎች እየተሰረቁ በሚቸበቸቡበት አገር አእምሮ እንዴት በእውቀት ሊበለጽግ ይችላል? አለምን በጥበብ ያሸበረቀው ኢንተርኔት ተነፍጎት በጨለማ የሚደናበር አእምሮ እንዴት ብርሃን ሊያፈልቅ ይችላል? ዜናዎችንና ጦማሮችን የሚያቀርቡ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ራዲዎኖችና ቴሌቪዥኖች ከሚታፈኑበት አገር አእምሮ በምን መልክ በሐሳብ ሊሰላ ይችላል? በሆዳቸው  በሚያስቡ ካድሬዎች የውሸትና የቅጥፈት ምራቅ የረጠበ አእምሮ በምን ሐሳብ በስሎ ጠማ ሊል ይችላል?

አንገቱን በላባ የገዘገዘን የቆሎ ተማሪ አይታ አንገቷን በቢላዋ እንደ ቀነጠሰችው ጦጣ ምእራባውያን የሚያድርጉት ሁሉ ስልጣኔ እየመሰላቸው ትያትር፣ ዘፈን፣ ዜማ፣ ዳንኪራና ስም ሳይቀር እንደ ተስፋዬ አቢሶ አይናቸውን በጨው ታጥበው የሚገለብጡ ፊልም አዘጋጆችን፣ ተዋንያንን፣ ዘፋኞችንና ሌሎችንም በራሳቸው የሚያፍሩ ዜጎችን ሲመለከት የሚውል አእምሮ እንዴት በራሱ ሊተማመን ይችላል?

ለአእምሮ መስላትና ለስልጣኔ መበልጸግ የሚያስፈልጉት እምነት፣ ባህል፣ ትምህርትና ምርምር አንጎላቸውን በብር ብሎች ባስበሉ ገዥዎችና “የሃይማኖት መሪዎች” ስልተደቆሱ፤ ተበዳይ ከበዳይ እግር ተደፈቶ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚያድረጉ እነ ኤፍሬም ይስሃቅ የአገር ሽማግሌ ስልተባሉ፣ የትምህርት ተቋማት የዲግሪ ሸማቾችና የቅል ማምረቻ ጓሮዎች ስለሆኑ፤ የተማሩ ሰዎች አእምሮም ከአፎቱ ወጥቶ የቁርጥ መበያ ቢላዋ ስለሆነ፤ መጻሕፍት ለስኳር መጠቅለያና ለአየር ባየር ንግድ ስለዋሉ፤ በሃይማኖት ፍልስፍናና በቅኔ ፍክክር የገዳም ባህር ውስጥ መዋኘት የሚገባቸው ካክናትና መነኩሳት ከተማ ወስጥ የኮረዳ ጪን ሲመለከቱ ስለዋሉ፣ ቅጥፈት፣ ውሸት፣ አጭበርባሪነት፣ አድርባይነት፣ ባንዳነትና ሎሌነት በኑሮ ፈሊጥነት ስለተመረጡ አእምሮ ኢትዮጵያ ገደል አፋፍ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ አእምሮ ኢትዮጵያን ከመፈጥፈጥ የሚያድን ብልሐት እንድንፈጥር ይህ ዘመን ጠይቋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቀይ እምባባና ማንጁስ ወረራ፣ የትህነግ ጦር አበጋዞች ህዝባዊ ማዕበል ጥቃት፣ በአማራና አፋር ምድር!!!

በሽታን ለመፈወስ የበሽታውን መንስኤ ማስወገድ እንደሚበጅ ሁሉ አእምሮ ኢትዮጵያን ከአፋፍ ለመመለስም አፋፍ ያደረሱትን ያልተባረኩ “መንግስታዊ”ና “ሃይማኖታዊ” መዋቅሮች እንደዚሁም የእንጨት ሽበት ሽምግልናን ከሕብረተሰቡ እንደ ሙጀሌ ነቅሎ መጣል ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን መንስኤን በማስወገድ ብቻ የቆየ በሽታን ጠባሳ ለማዳን እንደማይቻል ሁሉ ከአፋፍ የሰነበተን አእምሮም ተማሪዎችን ከካምፕ አጎሮ በመፈተን ብቻ ማዳን አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሐሳብ ስለትን አፎት ወይም ህሊናን የሚተካ ሕግና ደንብ በዚች ምድር ላይ ባይኖርም አእምሮ ኢትዮጵያን ገደል የሚሰዱትን ህሊና ቢሶች ለመቆጣጠር የሚከተሉትን ዓይነት ተቋማት በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ማቋቋም የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡

፩. የዘመናዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ትምህርት መርሀ-ግብርን (curriculum) የሚያዘጋጅና የሚያሻሽል ተቋም

 

፪. የዘመናዊም ሆነ የእምነት ትምህርት ተቋማት በአካልና በአእምሮ የዳበረ ዜጋ ለማፍራት የተዘጋጁ መሆናቸውን የሚከታተል ተቋም (Institution Credentialing Agency)

 

፫.  ከዘመናዊም ሆነ ከእምነት የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት የሚፍትሽ በእየ አምስት ወይም በየ አስር ዓመቱ የሚፈትን ተቋም (Certification and Re-certification Committee)

 

፬. ጠቃሚ የሆኑ ባህሎችን እንዲስፋፉ ጎጅ ባህሎችን ደግሞ እንዲወገዱ ጥረት የሚያደርግ የባህል ምርምር ተቋም

 

፭. በሙያቸውም ሆነ በሌላ ዘርፍ ለእድገትና ብልጽግና ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዜጎችን የክብር ማእረግ የሚሰጥና  በአንጻሩም ሙያቸውን ለኢሰባዊ ድርጊት መፈጸሚያ ያዋሉትን ደግሞ በህይወት እያሉም ሆነ ካለፉ በኋላ ክብራቸውንም ሆነ ማእረጋቸውን የሚገፍ አካል

 

፮.  ወንጀለኞችን በአገር ውስጥም ሆነ በሌሎች አገሮች ፍርድ ቤቶች የሚያቅርብ አካል

 

፯. የንስሐ ተቀባይና የምግባር ማስተካከያ ተቋም (confession and redemption institution)

 

እነዚህን የመሳሰሉ መሰረታዊ ማስተካከያዎች ሥራ ላይ ካልዋሉ ለሰላሳ ዓመታት አገርን ውርደትና መቀመቅ ውስጥ የከተተው የነፈረቀ ደዌ ከአገር ገዥዎች፣ ከሆዳም ምሁራንና የሃይማኖት መሪዎች አጭበርብሮ መኖርን የተማረ ተማሪን ካምፕ ውስጥ አስገብቶ በመፈተን ብቻ ሊስተካከል ይችላል ማለት ዘበት ነው፡፡ አቀመ ቢሱ አጭበርባሪ ተማሪስ ካምፕ ውስጥ ታስሮ ተፈትኖ አረፈው፡፡ ማጭበርበሩን ያስተማሩት አገር ገዥዎች፤ ፒ ኤች ዲ፣ ክሀነትና ሽክና ሸማቾችስ የት ተፈትነው እውቀታቸውን ሊያሳዩ ነው?

 

ተመሳሳይ ጽሑፎች፡-

፩. ድንጋይን የሚያናግረው ውኃ ነው http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2012/12/dengay-21.pdf

፪. ሰው ምንድን ነው? www.addisvoice.com/article/sew2.pdf

፫. ደግነትና ክፋት ምንድን ናቸው? http://www.quatero.net/meta/GoodandEvil.pdfhttp://    

፬. ሙያን እንደ ሹካ  www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2010/08/muyya.pdf

፭. አባ ባህሩ ናፈቁኝ http://addisvoice.com/amh/AbaBahiru.pdf         

፮. ኮፍያ እንበልሽ ባርኔጣ http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2011/12/barnetta.pdf

፯. ምንድነው ምንኩስና?  http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2010/11/minkussina-1.pdf

፰.  ሰማይ አይታረስ ካህን አይከሰስ http://www.abugidainfo.com/wp-content/uploads/2014/08/kahin.pdf

፱.  ስም አውጡልኝ http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2010/05/sim_awutu.pdf

፲. ብጹዓንና ቅዱሳንን ያያችሁ! http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2013/04/qiddusan-1.pdf

፲፩. ድንጋይን ዳቦ ብሎ መጥራት ይብቃን http://addisvoice.com/wp-content/uploads/2014/10/dingayn-dabo-malet-yibkan.pdf

 

አመሰግናለሁ፡፡

 

መጀመርያ ጥር ሁለት ሺ ሰባት ዓ.ም. እንደገና ጥቅምት አስራ አምስት ዓ.ም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share