ሌሎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎቹ እንደተጠበቁ ሆነው አቤ ጉበኛ በአልወለድም አማካኝነት የሚነግረን ነፃነትን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ሰብአዊ መብትን፣ የዜግነት መብትን፣ የሰላም መስፈንን፣ የመተሳሰብና የጋራ እድገት ራዕይን እውን ለማድረግና ለማጎልበት የሚያስችል ሥርዓተ ፖለቲካን አምጦ መውለድ የማይችል ትውልድ እጣ ፈንታው ከአልወለድም ዘመን በእጅጉ የከፋ እንጅ የተሻለ ሊሆን እንደማይችል ነው። ይህ መንግሥትንና አሽቃባጮቹን በብርቱ የመሞገት ፖለቲካዊና ሞራላዊ ሰብዕናውና አቋሙ የዓመታት እሥረኝነት መስዋእትነትን አስከፍሎታል። እንደ አልወለድም አይነት ሥራዎችም የሳንሱር (censorsip) እና የመቃጠል ሰለባዎች ሆነውበታል ።
የረጅም ጊዜው የአገርነት አኩሪ ታሪካችን እንደተጠበቀ ሆኖ በገዥዎች የሚዘወረው የፖለቲካ ታሪካችን ግን ጀግናንና የእውነተኛ እውቀት ባለቤትን በማጎሳቆል እና አሾክሿኪንና አድርባይን በመሾምና በመሸለም አይታማምና አቤ ጉበኛም እ.ኢ.አ በ1980 ዓ.ም ከመሞቱ ቀደም ብሎ በደረሰበት ነገር ሁሉ ተረብሾ ለእራሱ ህይወት ፀር በሆነ ባህሪ ውስጥ ሲወድቅ ገዥዎችና ግብረ በላወቻቸው “ለይቶለት አበደ” በሚል ተሳልቀውበታል።
ይህንን እንደ መግቢያ ያነሳሁት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ሂደት ውስጥ ይህንን የመሰሉ ብቻ ሳይሆን ከዚህም የከፉ ሌሎች ስህተቶች አልነበሩም ወይም በተቃራኒው የሆነውና የተደረገው ሁሉ አሉታዊ ነበር ለማለት አይደለም። በብዙ የዘመን መፈራረቅ ሂደት ውስጥ በሥርዓት ብልሹነት ምክንያት ከሚመነጭ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፧ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ድህነት አዙሪት (vicious cycle) ሰብሮ ለመውጣት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ይባስ ብለን ለመገመት በሚያስቸግር ሁኔታ ማነፃፀሪያ በሌለው አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀናልና የጉልቻ ሳይሆን የሥርዓት ለውጥ ግድ ይለናል ለማለት እንጅ።
ይህ ቀጥተኛና ግልፅ አባባሌ የሚከብዳቸው ወይም ነውር ወይም ተራ ስድብ ወይም ጨለምተኝነት የሚመስላቸው በርካታ ወገኖች እንዳሉ በሚገባ እረዳለሁ። ምንም እንኳ የዚህ አይነቱ አስተሳሰብና ሥነ ልቦና ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ቢችልም ከዋናዎቹ አንዱ ከዘመን ሥልጣኔ ጋር ለመራመድ ያቃተው የፖለቲካ ባህላችን ያስከተለው መሆኑን ስለምረዳ ቢያሳዝነኝም አይገርመኝም።
ዛሬም የመከራና የውርደታችን ሁሉ ዋነኛ ምክንያት (root cause) የሆነውን የሦስት አሥርተ ዓመታት የኢህአዴግ/ብልፅግና የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ማስወገድን ዒላማው በሚያደርግና ወደ ትክክለኛው ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚወስድ የትግል መንገድ ላይ አይደለም። እንዲያው የሥርዓት ለውጥን እውን እናደርጋለን ብለን ከተነሳንበት ዓላማ፣ መርህና ግብ በመንሸራተት ሸፍጠኛ እና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የሚያደርሱብንን ሰቆቃ እየቆጠርንና በየእለቱ የሚወረውሩልንን ርካሽና አደገኛ አጀንዳ እንደ ጥንብ አንሳ ተሻምተን እያነሳን መልሰን የእነርሱው መሳቂያና መሳለቂያ ሆነናል። ዛሬም በፅኑ ዓላማና መርህ ላይ ቆሞ ይህንን እጅግ አስቀያሚ ደጋግሞ የመንሸራተት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣትና ወደ ትክለኛው የለውጥ መንገድ የሚመራንን የፖለቲካ ሃይልና ይህንኑ የሚያግዙ የሲቪክ አካላትን አምጦ ለመውለድ አልተሳካልንም። አሁንም የተጠመድነው ይህንን የዘመናት እንቆቅልሽ እንዴትና መቼ ፈትተን ወደ የሚበጀን ቀጣይ ሥራ እንግባ? የሚለውን ፈታኝ ጥያቄ ለመመለስ በሚያስችል ሥራ ላይ አይደለም ።
በደራሲ አቤ ጉበኛ ጊዜ የነበረውንና አሁን ከግማሽ ምእተ ዓመት በኋላ (በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) የምንገኝበትን ሁኔታ እውን ለማነፃፀር ይቻል ይሆን? ፈፅሞ የሚቻል አይመስለኝም። በእጅጉ የሚራራቁ ነገሮችን ለተነፃፃሪነት መጠቀም ይበልጥ ያሳስታል እንጅ ብዙም ትርጉም አይሰጥም።
እርግጥ ነው በአገር ምሥረታ ውጣ ውረድ ውስጥ እንደሚያልፍ ማነኛውም አገር በእኛ የታሪክ ሂደት ውስጥም በጥቂት ገዥዎች የሚዘወሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች የፈፀሟቸው ግፎችና በደሎች የመኖራቸውን ሃቅ መካድ አይቻልም።
የአሁኑ ሁኔታችን አስከፊነትና አሰፈሪነት ግን “ሊያጋጥም የሚችል ነው” እያልን እራሳችንን ልንሸነግል (ልናታልል) ከምንሞክርበት አጠቃላይ እውነታ (general truth) ፈፅሞ የተለየ ነው። ለዚህ አሁን ላለንበት ሁኔታ ለንፅፅር የሚሆን የፖለቲካ ታሪክ አጋጣሚ ፈልገን ለማግኘት እንቸገራለ።
በተለይም ከአራት ዓመታት ወዲህ የተፈፀመውንና አሁንም የቀጠለውን ወንድም ወንድሙን በግፍ ገድሎ በሬሳው ላይ የሚቀልድበትን፣ ከመቶዎች አልፎ ብዙ ሽዎች በማንነታቸው ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈው እንደ ማነኛውም የማይፈለግ ቆሻሻ አፈር የለበሱበትን፣ ሚስት ከባሏና ከልጆቿ ፊት የተደፈረችበትን፣ ህፃናት በአስከሬኖች መሃል እንቅልፍ ሲያንገላታቸው ያስተዋልንበትን፣ የዋህና ንፁህ እናት ገና ከማህፅኗ ካልወጣው/ችው ልጇ ጋር በስለት (በቆንጮራ) ስትዘነጠል ያየንበትን፣ ወንድም ወንድሙን በቁሙ በእሳት እያጋየ ሲፈነጭ የታዘብንበትን ፣ ወንድም ወንድሙን ገድሎ አንጨት ላይ በማንጠልጠል ትልቅ ትንሹ እንደ የመዝናኛ ትርኢት ዙሪያውን ቆሞ እንዲመለከተው ሲያደርግ በአይናችን በብረቱ ያየንበትን ፣ በርካታ አዛውንት መላ ቤተሰባቸው አይናቸው እያየ የግፍ ግድያ ሰለባ ስለሆነባቸው በቁም ሞት ላይ ሆነው የመቃብሩን ሞት እየተጠባበቁ መሆናቸውን የሰማንበትን፣ ሁለቱ የኢህአዴግ አንጃዎች ማለትም ህወሃትና ብልፅግና በሥልጣነ መንበር ሽኩቻ ምክንያት እያካሄዱ ያሉት የወንደማማቾች ጦርነት በዋጋ ሊተመን የማይችል አጠቃላይ ውድመት በማስከተል ላይ መሆኑን እየታዘብን ያለንበትን እና ይህ ሁሉ እየሆነ ቢያንስ በተለቪዥን መስኮት ወይም በሌላ መድረክ “ለሆነው ሁሉ አዝናለሁ” የሚል የአገር መሪ ያጣንበትን እጅግ ግዙፍና መሪር ሁኔታ የምናነፃፅርበት የፖለቲካ ታሪክ ፈልገን ለማግኘት የምንችል አይመስለኝም። እንደ አቤ ጉበኛ አይነት ኢትዮጵያዊያን ከመቃብር ተነስተው ለመታዘብ የሚቸሉ ቢሆን ኖሮ ግምገማቸውና ሃዘናቸው ከዚህ ቢብስ እንጅ የተሻለ እንደማይሆን ለመገመት ነቢይነትን አይጠይቅም።
በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ (እኢአ1980ዎቹ) በህገ መንግሥት ተደንግጎ እና በመንግሥት መዋቅራዊ አሠራር ተቀነባብሮ ሥራ ላይ የዋለው ህወሃት መራሹ የጎሳና የቋንቋ ማንነት አጥንት ስሌት የፖለቲካ ንግድ (ቁማር) ሥርዓት ያስከተለው የቀውስ አስከፊነት በአገራችን ታሪክ ውስጥ ፈፅሞ ማነፃፀሪያ የለውም።
ይህ እጅግ አስቀያሚና አደገኛ የፖለቲካ ሥርዓት ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት ያበቃለታል ብለን ስንጠብቅ የመጠሪያ ስያሜና የጉልቻ ለውጥ ባደረጉ ተረኛ የኦህዴድ ፖለቲከኞች የበላይነት እና ብኦዴንና ደህዴን በሚሰኙ ወራዶችና ጨካኞች አሽከርነት ቀጥሏል። ግልብ ስሜትን ከሚፈታተን የፖለቲካ አውድ እራሱን ተቆጣጥሮ ላስተዋለ ሰው ይህ እንደሚሆን ግልፅ የሆነው“ዒላማየና ዓላማየ መሠረታዊ ዴሞክራሲዊ የሥርዓት ለውጥ እንጅ የግለሰቦች (የጉልቻ) መቀያየር አይደለም” በሚል ይምልና ይገዘት የነበረው እጅግ አብዛኛው ፖለቲከኛና ምሁር ባይ አብይ አህመድ ሥልጣነ መንበሩን ሲረከብ ባደረገው የለየለት ሸፍጠኛና ሴረኛ ዲስኩር ተማርኮ የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ ደጅ መጥናትና መማፀን የጀመረ እለት ነበር። ይህ ደግሞ ለዘመናት የመጣንበትን አንድን አይነት አስተሳሰብና አካሄድ እየደጋገሙ የተለየ ውጤትን የመጠበቅ እጅግ የወረደ የፖለቲካ ምንነትና ማንነት አካል ነው።
የትግላችን መዳረሻ የመከራው ሁሉ ዋነኛ ምንጭ የሆነውን ሥርዓት ታግሎ ለማሸነፍና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ እንደሆነ አጥብቀን ስናስተጋባው የነበረውን ዓላማና ግብ የውሃ ሽታ ያደረገብን በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መርህና አሠራር መሠረት ላይ የቆመና ሁሉንም ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የሚያሳትፍ አገራዊ የፖለቲካ ሃይል አምጦ ከመውለድ ይልቅ በሚገርም ሁኔታ ኢትዮጵያ የሚለው ትልቅ ገላጭ ቃል ጨርሶ የተረሳ እስኪመስል ድረስ ወደ ታች እንዲደፈቅ በመፍቀዳችን ነው።
ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ የቀጠለው የአገራችን አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ቀውስ የሚከተሉትን ዘመን ጠገብና ፈታኝ ጥያቂዎች በትክክል ለመመለስ ከመቻል ወይም ካለመቻል ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፦
ከዚህ እጅግ የመከራና የውርደት ፖለቲካ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችለንን ብቸኛ መንገድ (እውነተኛ የሥርዓት ለውጥን) እውን ለማድረግ ለምንና እንዴት ተሳነን?
የጋራ በሽታችን ምንጭ የሆነውን ሥርዓት ፍቱን በሆነው የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ማስወገድና የጋራና የእኩልነት ሥርዓት እውን ማድረግ ሲገባን ዘመናትን ባስቆጠረና ማቆሚያ ባልተገኘለት ፖለቲካ ወለድ የግፍ አሟሟትና ልክ የሌለው የቁም ሰቆቃ ሰለባዎች ሆነን የቀጠልነው ለምንድን ነው?
መንጠባጠባችን ሳያንስ የመንጠባጠባችንን አሳፋሪነት ለማካካስ ከቤተ መንግሥት ፖለቲከኞች ጋር በፖለቲካ አመንዝራነት የምንዳራው (ጭራችን የምንቆላው) ለምድን ነው?
በእንዲህ አይነት እጅግ የተሳሳተና ለዘመናት ተሞክሮ ጥፋትን እንጅ ልማትን ባላስገኘ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ እየሄድን የተለየ ውጤት ከመጠበቅ ክፉ አዙሪት ለመውጣት እንዴት ይቻለናል?
የቤተ መንግሥት ፖለቲካቸው አማካሪ ያደረጓቸው የኦነግ ፖለቲከኞች ታጣቂ ክንፍ የሆነውን ሃይል ሸኔ የሚል የራሳቸውን የዳቦ ስም በመስጠት ከሚቀልዱትና ከቀድሞ ጠርናፊያቸው ህወሃት ጋር በተረኝነት ሽኩቻ ምክንያት በሚያካሂዱት የወገን ተወገን አሰቃቂ ጦርነት አገርን ምድረ ሲኦል በማድርግ ላይ ከሚገኙት እኩያን ፖለቲከኞች ጋር ከሚፈጠር ጭራቃዊ ጋብቻ (ሽርክና) እውነተኛ ዴሞክራሲ ይወለዳል ብከ መጠበቅ የከፋ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ይኖራል ወይ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው አራት ዓመታት ሙሉ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ንፁሃን ወገኖች የግፍ ጭፍጨፋና የቁም ሰቆቃ ሰለባዎች ሲሆኑ በየመናፈሻውና የእርሻ ቦታው እየዞረ በገፍ የሚያመርተውን ውሸትና ጭካኔ የተሞላበት ስላቁን በመከረኛው ህዝብ ላይ እንደ ጉድ ሲያወርደው ከምር የሚቆጣና አደገኛ ጉልቾች የሚቀያየሩበትን እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት በእውነተኛ የለውጥ ተጋድሎ ለመተካት የሚያስችል ፍላጎት፣ አቅምና ዝግጁነት ለምንና እንዴት አጣን?
“ይህን ማድረግማ ፖለቲካ ስለሆነ …” የሚል የሃይማኖት መሪ ፣ አስተማሪና አማኝ ካለ፦
ሀ) በጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የሚዘወረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ከተለመደ (ከሚጠበቅ) የፖለቲካ ችግርነት አልፎ ማንነትን እየለየ በህይወት የመኖርን እጅግ መሠረታዊ መብት ድምጥማጡን የማጠፋት እጅግ አስከፊና አስፈሪ ደረጃ መሸጋገሩን መቀበል ያልፈለገና ሃይማኖትን ከመሪሩ እውነታ መሸሸጊያነት የሚጠቀም መሆን አለበት ፤
ለ) ሃይማኖትን በሽፋንነት በመጠቀም እውነትና እውነት ብቻ ሊሆን የሚገባውን አምላካዊ ተልእኮ በአድርባይነትና በአስመስሎ የመኖር ካባ ለተሸነፈው እሱኑቱ አሳልፎ የሰጠ መሆን አለበት (ዲያቆን ዳንኤልን እና ክርስቶስ እነርሱ በሚያውቁት ተአምር ብቻ ወደ ምድር ወርዶ ከአብይ አህመድ ጋር በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እንደሚገኝ ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ጨርሶ ሃፍረት የማይሰማቸውን ነብይ ተብየዎችን ልብ ይሏል) ፤
ሐ) በእውቀት ጉድለት ምክንያት በተለምዶ ከሚያውቀው (ከለመደው) ቃለ ነቢብና ስብከት ዝንፍ ማለት ከሃይማኖታዊ እምነት በመውጣት ፈጣሪን ማስቀየም እንደሆነ አድርጎ የሚያስብ (የሚያምን) የዋህ አይነት ሰው መሆን አለበት።
በየሃይማኖታዊ እምነት በዓላትና ሌሎች ዝግጅቶች “ግልብጥ ብሎ ወጣ” በሚያሰኝና እሰየው በሚያስብል እይታና መንፈስ አደባባዩን የሚያጣብበው ምእመን ፣የሃይማኖት መሪና አስተማሪ ከልክ ያለፈውን የህዝብ መከራና ሰቆቃ ቢያንስ ሰላማዊ በሆነ ትእይንተ ህዝብ በአደባባይ ለማሰማት ወኔው የከዳው ለምንድን ነው?
እናም ላለንበት ዘመንና ለሁሉም አይነት መሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶች (ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ) መከበርን የሚያረጋግጥ የሥርዓት ለውጥ ታሪክ መሥራት ተስኖናልና በስሜት ከመሞቅና ከመቀዝቀዝ የፖለቲካና የሥነ ልቦና አባዜ ወይም ልማድ ወጥተን አቤ ጉበኛ ከኖረበት ዘመን ጋር ፈፅሞ ሊወዳደር በማይችል ደረጃ የምንገኝበትን የመከራና የውርደት ማንነት ፍፃሜ ልናበጅለት ይገባል።
የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዋነኛ የትግል ዒላማችን ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ኢህአዴጋዊ/ብልፅግናዊ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ማስወገድ መሆን ነበረበት። ከዚህ በተቃራኒ ግልብ ስሜትን በሚያማልሉ ዲስኩሮችና ክስተቶች ተጠልፈን በመውደቃችን የሥልጣን የበላይነት ሽኩቻውን አሸንፎ የአራት ኪሎውን የቤተ መንግሥት ፖለቲካ የተቆጣጠረውን ኦህዴድ መራሽ አንጃ እንደ የለውጥ ሐዋርያ በመቀበል ዳንኪራ የምርገጣችን እጅግ የወረደ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ያስከፈለንና እያስከፈለን ያለው ለመግለፅ የሚያስቸግር መሪር ተሞክሮ ከበቂ በላይ ትምህርት ሊሆነን ይገባል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን መያዣና መጭበጫ የሌለው እና እጅግ ደምሳሳ የመደመር ድርሰት እንደ የእውነተኛ ለውጥ ፍልስፍና ቆጥረን በግልብ ስሜት የከነፍን እለት ነበር ለዘመናት በዘለቀውና አፍተኛ ዋጋ በተከፈለበት የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እየቸለስን የተለየ ውጤት የምንጠብቅ ደካሞች መሆናቸን የታወቀው።
ነውርንና ውሸትን እንደ የፖለቲካ ስልት በመጠቀም በመከረኛው ህዝብ ላይ የሚሳለቀው ጉደኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዛኛው ህዝብ በተፈጥሮ ሳይሆን በእጅጉ በተበላሸ የፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት ፍፁም በሆነና ወደ ፍፁምነት በሚጠጋ ድህነት ውስጥ ሆኖ በሚያከብረው በዚህ የመስቀል በዓል ሰሞን ያፈጠጠና ያገጠጠ እውነታን ክዶ በጦርነት ውስጥም ቢሆን “የሚደነቅ የኢኮኖሚ ግሳጋሴ” ላይ መሆናችንን ከነገረ በኋላ ስለ ሰላም ሐዋርያነቱ ደግሞ “ለእኛ ስለ ሰላም ማስተማር ማለት ለዓሣ ዋናን ፣ ለወፍ መብረርን ማስተማር ነው” ሲል የሰላም እጦቱና መከራው የየእለት ህይወቱ አካል በሆነው መከረኛ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉን በሚያውቀው ፈጣሪ ላይ ጭምር ተሳልቋል።
በተረኝነት የተቆጣጠረውና ከየትኛውም ጊዜና ሁኔታ በከፋ ሁኔታ እያስኬደው ያለው የጎሳ/ የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር በተሳካ ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ ልክ በታከለ ኡማ አማካኝነት እንዳደረገው ሁሉ የአዲስ አበባ ህዝብ ከዚያው ከእራሱ ለከንቲባነት የሚሆን ሰው ጨርሶ ያጣ ይመስል በላዩ ላይ የሾማትና የተሰጣትን አስቀያሚና አደገኛ ፕሮጀክት ጨርሶ ይሉኝታ በሌለው ሁኔታ በማስፈፀም ላይ የምትገኘው አዳነች አበቤም “ከመስቀሉ ፍቅር መማር ያስፈልጋል” በሚል መልእክት በተቃኘ ዲስኩሯ በአዲስ አበባና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተሰቀለበት ጥልቅና ግልፅ ዓላማ ወይም ምክንያት ላይም ተሳልቃለች።
የሩብ ምዕተ ዓመቱ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ካስከተለው አስከፊ ውጤት በመማር የዚያው ሥርዓት ውላጆች ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ያስቀጠሉትን ያንኑ ሥርዓት ከማስወገድና ትክክለኛ የሥርዓት ለውጥ እውን ለማድረግ የጋራ ጥረት ከማድረግ ይልቅ በዚያው በተለመደው የውድቀት መንገድ እየተመላለስን የተለየ አወንታዊ ለውጥ የመጠበቃችንን ጉድ አቤ ጉበኛንና አልበርት አንስታይንን የመሰሉ ሰዎች በህይወት ተመልሰው ቢታዘቡን ምን ሊሉን እንደሚችሉ ለመገመት አያስቸግርም።
ወላጆቻችን ፣ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ሲሉ ወደ አዲሱ መስከረም ከመሸጋገራቸው በፊት ባለው በማነኛውም ወቅት ጨርሶ ያልተለመደ ወይም ጉድ የሚያሰኝ ክስተት መከሰቱን ለመግለፅ እንጅ እንደ እኛ እንደ ዛሬዎቹ የየእለት ህይወታቸው የጉድና የመከራ መናሃሪያ ስለነበረ አልነበረም።
የእኛ ጉድ ግን መስከረም ጠባ አልጠባ ሳይል በየደቂቃው፣ በየሰዓቱና በየለቱ ሳያቋርጥ ይግተለተላል። ከከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ፈፅሞ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ሁለመናችን የጉድ መናሃሪያ ሆኗል።
ከቁጥር ቀመርነቱ ያለፈ የእኛነት ትርጉም ያላገኘንበት የዘመን መለወጫም ትንሽ እንኳ ፋታ ሳይሰጠን ጉዳችንን ማግተልተሉን ቀጥሏል። ከተለምዶነት ያላለፈ የምኞት መግለጫ፣ የሰላምና የፍቅር መነባንብ፣ የርትዕ አንደበት ስብከት፣ ለስሜት የሚመች ዝማሬ፣ የከንቱ ውዳሴ ቅኔ፣ ለጆሮ የሚስማማ ሙዚቃ፣ ወዘተ የአስተሳሰባችንንና የአካሄዳችንን ቅኝትና ፍኖት እስካላስተካከልን ድረስ የትም አያደርሰንም።
በአንፃራዊነት የበኩላቸውን ድርሻ ለሚወጡ የፖለቲካ ንቅናቄ መሪዎች ወይም አስተባባሪዎች ፣ጋዜጠኞች እና የሰብአዊና የዜግነት መብት ተሟጋቾች የምንገኝበትን ዘመንና መሪር ሁኔታ በሚመጥን ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲታገዙ ለማድረግ ባለመቻላችን በሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እንደ ወንጀለኛ እየተዋከቡ በየሥር ቤቱና በየፖለስ ጣቢው ታጉረው እጅግ ውድ የሆነ የህይወታቸውን ክፍል በመስዋትነት በመክፈል ላይ ይገኛሉ።
ለዚህም ነው እንደ እስክንድር ነጋ አይነት ባለፅዕኑ ህሊና ወገኖች ድንገት አድራሻቸው ሲጠፋ ከማውራትና ከመብከንከን የዘለለ ሥራ መሥራት የተሳንን ። በመሪነት ያገለገለበት የፖለቲካ ድርጅትም እንኳን የእስክንድር ሁኔታን ለማወቅ ጥረት ሊያደርግ በእርስ በርስ የመካሰስና የመጠላለፍ ክፉ የፖለቲካ አረንቋ ውስጥ የመዘፈቁ መሪር እውነት በእጅጉ ህሊናን ያቆስላል።
የስንታየሁ ቸኮል አስከፊ እንግልትም በዚሁ አስቀያሚ የፖለቲካ አስተሳሰባብና አካሄድ እየተመላለስን የተለየ ውጤት የመጠበቃችን ክፉ አባዜ ውጤት ነው።
መዓዛ መሃመድን ፣ተመስገን ደሳለኝን ፧ ጎበዜ ሲሳይን ፣ ታዲዮስ ታንቱን እና መሰል የፅዕኑ እምነት ፣ዓላማና መርህ አርአያዎችን በየጊዜው አሳልፈን እየሰጠን እጅግ አሳፋሪና አስፈሪ በሆነ በፍቱልንና በማሩልን ጩኸት የተጠመድነው ያለምክንያት ሳይሆን ለዘመናት በመጣንበት ከክስተቶች ትኩሳት ጋር ከመቀዝቀስና ከመሞቅ ክፉ የፖለቲካ ባህል ወይም ልማድ ለመላቀቅ ባለመቻላችን ነው።
እንኳንስ እጅግ ለመግለፅ የሚያስቸግረውን አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ብልሹነት ማንኛውንም ዓላማ ተፈትኖ በወደቀ አንድ አይነት አስተሳሰብና አካሄድ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም።