September 3, 2022
17 mins read

የሰሚ ያለህ ምዕመናን! የመጻሕፍተ መነኮሳትን ትዕዛዛት የሚከተል አቡንና ጳጳስ በላንባ ዲና ተፈልጎም አልገኝ እያለ ነው! – በላይነህ አባተ

Al Mariamrrr

መፍትሔው በእጃችን ነው፡፡ እያጠፉት ያለውን መጻሕፍተ መነኮሳት አሳትመን፣ አንብበንና ጠንቅቀን አውቀን በእርሱ እንዲገዙ፣ ካልተገዙም ቆባቸውን ተአጥር ሰቅለው እንዲጠፉ ማድረግ ነው፡፡

 

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

በኢትዮጵያ ነገር ዓለሙ ሁሉ ባፈጢሙ ከተደፋና ግልብጥብጥ ታለ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አቀርቅሮ መኖር የሚገባው ከሃዲ ባንዳ ወንበር ይዞ አርበኛና ፋኖ ሲያሳድድ ይውላል፡፡ ዓለም በቃኝ ብሎ መመነን ያለበት የአቡንና የጳጳስ መነኩሴ በውጪ አገር ፓስፖርት  በአውሮጳና አሜሪክ ከተሞች ሲንፈልሳሰ ምእመናን ዓለም በቃችን እያሉ ሲመንኑና ገዳም ሲገቡ ይታያል፡፡

ለብዙ ዘመናት በተለይም ደሞ ባለፉት አራት ዓመታት በዘራቸው ምክንያት ምዕመናን እንደ ደን እንደተጨፈጨፉ፣ ተሞት የተረፉቱም የተራቡ ሕፃናትን ታቅፈው መንገድ ዳር እንደወደቁ፣ በርሃብና በበሽታም እያለቁ እንደሆነ ዓለም ያውቃል፡፡ የእነዚህን የግፍ ሰለባ ምዕመናን አስራት የሚሞጨልፉ አቡንና ጳጳሳት ግን ቁንጣን ሆዳቸውን በቆዘራቸውና በቆረጣቸው ቁጥር “ለመታከም እያሉ” ወደ አሜሪካና አውሮጳ መትመም የይህ አድግ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ዘመን አቡኖችና ጳጳሳት የተለመደ እኩይ ተግባር ሆኗል፡፡

Al Mariamrrrየይህ አድግ ባንዳ መሪዎች “አሳድገነዋል” እያሉ ውሸት እንደ አቡጀዲ የሚቀዱበትን የአገሪቱ የጤና አገልግሎት ለነሱ እንደማይመጥናቸውና አውሮጳ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኤሽና አረብ አገር እየሄዱ እንደሚታከሙት ሁሉ ለይህ አድግ ዘመን ጳጳሳትና አቡኖችም የአገሪቱ ጤና አገልግሎት ስለማይመጥናቸው የአገርና የቤተክርስትያን ንብረት እየዘረፉ ህክምናቸው በአሜሪካ፣ አውሮጳና ሌሎችም ከተሞች ሆኗል፡፡ በጸበልና ፀሎቱት መዳንም እንደ ጥገት ላም ለሚያልቡት ምእመናን እንጅ ለእነሱ እንደማይመጥን እያሳዩ ይመስላል፡፡

ከማንኛው የዓለም ክፍል በተለዬና በረቀቀቀ መንፈሳዊ ብቃት የተዋህዶ ቤተክርስትያን ምንኩስና ከሁለት ሺህ ዘመናት መተግበሯን እንኳን የኢትዮጵያ ገዳማትና ዋሻዎች የመላው ዓለም መንፈሳዊ ተቋማትም በሚገባ የሚያውቁት ነው፡፡ በዚህች ቅድስት ቤተክርስትያን ውስጥ እንደነዚህ ዓይነት ዓለምን ጉንጯ ትምክ እስቲል “እምጵዋ” አርገው ስመውና ከንፈራችው እስቲወድቅ ሙዝዝ ብለው ያፈቀሩ መነኩሴዎች መፈጠራቸው እጅግ የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ነው፡፡

እንደሚታወቀው መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ እሴት ኢትዮጵያን በአለት ላይ የገነባ ፀጋ ነው፡፡ ይኸንን ፀጋ እየተመገቡ ካህናትና መነኩሳት በሰላም ጊዜ በነፍስ አባትነት፣ በሽምግልና፣ በመምህርነትና በፈላስፋነት ያገለግሉ ነበር፡፡ ሰይጣንን መዋጋት የመነኩሴ ሥራም ስለሆነ ሰላምን የሚነሳ ሰይጣን የላከው ወራሪ ሲመጣም ጦር ሜዳ ሄደው እስከ መዋጋት የሚደርሱ የሃይማኖት አባቶች ቁጥር እልቆ መሳፍርት አልነበረውም፡፡ ለምሳሌ በአምስቱ ዘመን ፊልክስዩን(ከመጻሕፍተ መነኮሳት አንዱ) “የዋህ ሁን ለክፉ ግን የዋህ አትሁን” [1] የሚለውን መልዕክት ተከትለው መነኮሳት በእንቁላል ቀቃይ ባንዳዎች እየተመራ ሕዝብ የፈጀውን ፋሽሽት መሳሪያ ታጥቀው እንደተዋጉ የሚታወቅ ነው፡፡ የበቁ መነኮሳት  በደብረ ሊባኖስና በሌሎች ገዳማትም እንደተረሸኑ አፍ ቢኖራቸው ስጋቸውን የበሉት ሜዳዎችና ተራሮች እንደዚሁም ደማቸውን የጠጡት ወንዞች የሚመሰክሩት ነው፡፡

ዛሬ የዓባይን እናት ኢትዮጵያን ውሃ ጠምቷት እንኳን ሕዝብ እንደ ደን ሲጨፈጨፍ “መጀመሪያ እኔን ግደል” ብለው በመከታነት የሚቆሙ ገዳዩን የሚገዝቱና ለተጨፈጨፉትም ፀሎት የሚያደርሱ መነኩሳት እየጠፉ ነው፡፡ በዓለም ፍቅር ያበዱ መነኩሳት የመጻሕፍተ መነኮሳትን መመሪያዎችና ሕግጋት እንደ ቀበኛ ላም ቦጫጭቀው በልተው በዚች ከንቱ ዓለም እንዳልተገራች በቅሎ እየጋለቡ ነው፡፡ መፍትሔው የመጻሕፍተ መነኮሳትን ትዕዛዛትን ምዕመናን ተረድቶ በትዕዛዛቱ እንዲገዙ ወጥሮ መያዝ ነው፡፡ በሌለ ብፅጽእናና ቅድስና “ብፁዕ ቅዱስ” እያሉ ማንቆለጳጰስ አገሪቱንም ቤተክርስትያንንም እያጠፋ ነው፡፡

መጻሕፍተ መነኮሳት የመነኮሳትን ቃል ኪዳን፣ ግብር፣ ታሪክ፣ ተጋድሎና ተመከራም የሚያገኙትን ትሩፋት የሚያስተምር ተአዋልድ መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ የአዋልድ መጻሕፍት ትርጉም የመጻሕፍት ልጆች ማለት ሲሆን ወላጆችም ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው፡፡

ተብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን የተወለዱት መጻሕፍተ መነኮሳትም ሶስት ናቸው፡፡

ልጅ አንድ፡- ማር ይስሐቅ ስለመነኮሳት ቃል ኪዳን፣ ግብር፣ጾምና ተጋድሎ ያስትምራል፡፡

ልጅ ሁለት፡- ፊልክስዩስ ስለ መነኮሳት የገዳም ታሪክና ተጋድሎ ያስረዳል

ልጅ ሶስት፡- አረጋዊ መንፈሳዊ መነኮሳት መከራን ተቀብለው ስለሚያገኙት ፀጋ ወይ ትሩፋት ያስተምራል፡፡

አረጋዊ መንፈሳዊ ሥርዓተ ብሕትውናን ጳውሎስ፤ ሥርዓተ ምንኩስናን ደሞ እንጦስ እንደ ጀመረው ያስተምራል፡፡ [2] የናጠጠ ባለጠጋ ልጅ የነበረው እንጦስ ሥርዓተ መንኩስናን የጀመረው ቤሳ ሳያስቀር ሐብቱን ሁሉ ለዓለማውያን ትቶ ነው፡፡ የእርሱን ፈለግ በመከተል ቁጥር ስፍር የሌላቸው የኢትዮጵያ መነኮሳት ይህችን ዓለም ንቀው ገዳም ገብተው ቃል ኪዳንን እንደጠበቁ፣ በጾም አካላቸውን አድቀው በፀሎት ደግሞ መንፈሳቸውን አጠንክረው ሰይጣን የላከውን በፀሎት ብቻ ሳይሆን በመሳሪያም ታግለው እንዳለፉ ታሪክና ብቻ ሳይሆን ብዙ ቋሚም በዓይኗ በብረቷ ያየው ነው፡፡

ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ ግን ምንኩስና እንደ እንጦስና የቀድሞ ኢትዮጵያውያን አባቶች ከባለጠጋነት ወደ ድህነት የሚሸጋገሩበት መንፈሳዊ ድልድይ ሳይሆን ከድህነት ወደ ባለጠጋነት የሚሸጋገሩበት አካላዊ መሰላል እንደሆነ ሁሉም በየሰፈሩ የሚያየው ነው፡፡

በፓትርያሪክነት፣ በጵጵስናና በተለያዩ የክህነት መንበሮች የተቀመጡ መነኮሳት የመጻሕፍተ መነኮሳትን መለኮታዊ መመሪያ እረግጠው ለመመረጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፣ ለጥቅም በካድሬነት ነፈሰ ገዳይ ገዥዎችን ሲያገለግሉ፣ ገንዘብ ሲመዘብሩ፣ በደመወዝ ከምእመናን ጋርና እርስ በርሳቸው ሲጨቃጨቁ፣ የቤተክርስትያኗን ገንዘብ ለህክምና፣ ለውሎ አበል ወዘተርፈ እያሉ ሲመዘብሩ መታየታቸው እንኳን መለኮትን ሰይጣንንም የሚያስገርም ነው፡፡

ማር ይስሐቅ መነኮሳት እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሲያስተምር “ለሰውነትህ እረፍትን ኅድዓትን ታገኝ ዘንድ ዘወርትር መጽሐፍትን መመልከት ውደድ፤ ከንዑሳን ሕጣውእ ተከልከል” ይላል፡፡ ንዑሳን ሕጣውእንም “ማየት፣ መስማት፣ ያለመጠን መብላትና መጠጣት ናቸው” ይላል፡፡[3]  ማር ይስሐቅ ማስተማሩን ሲቀጥልም “የእንጨት ብዛት እሳቱን እንደሚያበዛው የምግብ ብዛትም ዝሙትን ያበዛል፡፡ በልቼ ጠጥቼ፤ አይቼ ሰምቼ፣ ንጽሕናየን ጠብቄ ከሴት ርቄ መኖር ይቻላል አትበል” ይላል፡፡ [4] ይኸንን ትዕዛዝ በመከተል ቅደምት መነኩሳት ራሳቸውን አግለውና እውቀት ላይ አተኩረው ብራና ፍቀው፣ ቀለም በጥብጠውና ቅጥቅጥ አብርተው ጥፈው ዛሬ የዓለምን ቤተ መጻሕፍት ያጥለቀለቁ መጻሕፍትን ጥፈው አልፈዋል፡፡ በዛሬው ቴክኖሎጅው ሁሉን ባቀለለበት ዘመን በዚህ ሥራ የተሰማራ አንድ ጳጳስ ወይ አቡን መጥራት ይቻላል ወይ? እነዲያውም አንዳንዶቹ ከንቱዎች እነዚህን ቅርሶች በማጥፋትና በመሸጥ ላይ የተሰማሩ ሳይሆን ይቀራል ወይ?

ማር ይስሐቅ መነኮሳትን ስለገንዘብ ማሳደድ ሲያስጠነቅቅም “ድሀ ትሆን ዘንድ ውደድ፣ ተርታ ልብስ መልበስን ውደድ” ይላል፡፡ [5] ይኸንንም በመከተል መነኩሴ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ስጋቸውን አድቅቀው፣ መቀባባትን፣ በልብስ ተከብሮ ለመኖር ተመጣር ፀያፍ ግብር እርቀው ኖረዋል፡፡ የዛሬዎቹ ግን ምግብ አግበስብሶ እንደ ሰንጋ መድለብን፣ በልብስ መዋብን፣ በእውቀታቸው ወይም በመንፈሳዊ ብቃታቸው ሳይኖን በካባቸው ለመከበር ሲወጣጠሩ ይታያል፡፡ በገንዘብና በስልጣን ሰክረው እርስ በርሳቸው ሲናከሱ ችግሩን ወደ መእመናን ያወርዱና ቤተክርስቲያኗን ከፋፍለው እንደ ፕሮቴስታንት ወይም ጴንጤ በየሰፈሩና ሽንቋቁሩ “ቤተክርስትያን” መክፈት ተጀመሩ ውሎ አድሯል፡፡

ድንበር ተሻግሮ የስንቱን ሕይወት እንደሚታደገው ዓባይ ስንቱን ውቂያኖስ ተሻግራ የዓለም ቤተመጻሕፍትን በመንፈሳዊ ሐብት የምትመግበው የእድሜ ባለጠጋዋ ኢትዮጵያ ዛሬ ቀን ጥሏት ውሀ እንደ ጠማት የዓባይ እናት በመነኩሴ ጥማት ስትሰቃይ ይታያል፡፡ ጥማቷን ለማርካት ከጸሎት በተጨማሪ “እርዱኝ እረዳለሁ” እንዳለው መጻሕፍተ መነኮሳትን አንብበንና ሕግጋቱን ጠንቅቀን አውቀን የይህ አድግ ጳጳሳት በመጻሕፍተ መነኩሳት ሕግጋት እንደ ቀደምት አባቶቻችን እንዲገዙ በመጠየቅ እግዚአብሔርን ልንረዳው ይገባል፡፡

የይህ አድግ ዘመንን አቡኖችና ጳጳሳትን ተቅድስት ቤተክርስትያን ክብርና ወደር የለሽ ታሪክ ጋር ማያያዝ  ሕፀጽ መሆኑን ልንገዘነብ ያስፈልጋል፡፡ ቅድስት ቤተክርስትያንን በይህ አድግ ዘመን አቡኖችና ጳጳሳት መመዘን በእውነተኛ የምንኩስና ህይወት ኖሮው ባለፉት ቅድመ አያቶቻችን ነፍስ እሾህ መከስከስ፣ በምድርና በስማይ ቤትም ለዘላለም የሚያስወቅስ ኃጥያት መሆኑን ልናጤን ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን የመጻሕፍተ መነኩሳት ትዕዛዛትን ሳያውቁ የመነኩሱ፤ አውቀው መንኩሰውም ትዕዛዛቱን ቦጫጭቀው የጣሉ ጳጳሶችና አቡኖችን ከቤተ ክርስቲያኗ ምንነትና ታሪክ ለይቶ መመልከት ቅድስና ነው፡፡ በሌለ ብፅጽእናና ቅድስና “ብፁዕ ቅዱስ” እያሉ የይህ አድግ አቡኖችንና ጳጳሳትን ማንቆለጳጰስ አገሪቱንም ቤተክርስትያንንም እያጠፋ ነው፡፡

የሰሚ ያለህ ምዕመናን! የመጻሕፍተ መነኮሳትን ትዕዛዛት የሚከተል አቡንና ጳጳስ በላንባ ዲና ተፈልጎም አልገኝ እያለ ነው! መፍትሔው በእጃችን ነው፡፡ እያጠፉት ያለውን መጻሕፍተ መነኮሳት አሳትመን፣ አንብበንና ጠንቅቀን አውቀን በእርሱ እንዲገዙ፣ ካልተገዙም ቆባቸውን ተአጥር ሰቅለው እንዲጠፉ ማድረግ ነው፡፡ አመስግናለሁ፡፡

ዋቢ፡-መጻሕፍተ መነኮሳት 1928 ዓ.ም ብርሃንና ሰላም እትም

  1. ፊልክስዩስ ገጽ 252-253
  2. አረጋዊ መንፈሳዊ፡ መቅድም ገጽ 3
  3. ማር ይስሐቅ ገጽ 10
  4. ማር ይስሐቅ ገጽ 57
  5. ማር ይስሐቅ ገጽ 14

ይቆይን!

ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ..

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Tedi Genocider
Previous Story

ዶክተር ቴድሮስ የአሸባሪው ሕወሃት ቡድንን እኩይ ተግባር በመደገፍ ኢትዮጵያ ላይ ሃሰተኛ መረጃ እያሰራጩ ነው

Amhara 7
Next Story

ጥቁር – ጠበንጃ  ወይስ ጥቁር -ሙጃ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop