አሻጋሪ ድልድይ ስትል የነበረው፣
መቀመቅ አስምጦ እየጨረሰህ ነው፡፡
ኩላሊትና ልብ ሳንባዬ ነው ያልከው፣
ምች ነቀርሳ ሆኖ ተምድር ሊያጠፋህ ነው፡፡
መብት ነፃነትህን ተእጅህ አዘርፈህ፣
ተእግር ብትደፋ እንዲመልስልህ፣
እንኳንስ ጭራቁ እግዜርም አይሰማህ፡፡
እርዳኝ እረዳለሁ ያለውን ዘንግተህ፣
አንጋጠህ ብትለምን እጅህን ዘርግተህ፣
እንደ አብያ በሬ አልምጠህ ተጋድመህ፣
አምላክ ጆሮው ጥጥ ነው ቅንጣትም አይሰማህ፡፡
ሙሴ ፈርኦንን በእምብርክክ ያስኬደው፣
ጀግንነቱን አይቶ መለኮት ሲረዳው፣
ባህሩን ሰንጥቆ መልሶ ሲሞላው፡፡
ዳዊት ጎልያድን ቀንድቦ የጣለው፣
ትጋት ልቡን አይቶ እግዜር ስላገዘው፡፡
ፋኖ መሶሎኒን ወገቡን የቀጨው፣
ማተብ ትግሉን አይቶ አምላክ ስለረዳው፡፡
ሁለት ልብ መሆን በአምላክ ቤት ፀያፍ ነው፣
መሐል እየሰፈርክ ጌታን አታስከፋው፣
ወይ ታራጅን አድን ወይ አራጁን እርዳው፡፡
ሕዝብ ሆይ ተመከር ልብህን ቁርጥ አርገው፣
መንታ መንገድ ሆነህ ታርደህ ልታልቅ ነው፡፡
ፈርኦን ጎልያድም ያልሰሩት ጉድ አየህ፣
ወህኒ ተኮላሸህ በመድሀኒት መከንክ፣
በቢላዋ ታረድክ ገደል ተወረወርክ፣
እርጉዝ አሰነጠክ ሕፃናት አሳረድክ፡፡
ኧረ ምን ነክቶህ ነው ያለ አባት አያትህ፣
እንደ ሙሴ ብትር ማንሳት የዘገየህ፣
እንደ ዳዊት ወንጪፍ ለመወርወር ዳ ያልክ፣
እንደ አምስቱ ዘመን ሞረሽ ጥራኝ ያላልክ?
እንደዚያ ጡርቂ ሰው ጅብ ቀኙን ሲውጠው፣
እራሱን እንዲያተርፍ ጓደኛው ሲነግረው፣
ግራዬን እንዳይደግም ዝም በል እንዳለው፣
ተጅብ ከፊ ጭራቅ ምህረት ጠብቀህ ነው?
የእናቶች መታረድ ተሩቅ የምታየው፣
እንደ ተርብ ተናድፈህ ዛሬ ታላቆምከው፣
ነገ ተአንተ ዘንድም ፈጥኖ ከች የሚል ነው፡፡
ልብ በል ሕዝብ ሆይ አይምሮን አሰራው፣
መብትን መለመን የሞኝ ጅል አመል ነው፡፡
የመኖር መብትህ ነፃነት በእጅህ ነው፣
ቀድሞ አለመዘረፍ ትልቁ ጥበብ ነው፣
ከተዘረፍክ ደሞ ቀምተህ ማምጣት ነው፣
እነ ኮስትር በላይ ያረጉት ያንን ነው!
እነ አበበ አረጋይ የሰሩት ይኸን ነው፡፡
በላይነህ አባተ ([email protected])
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.